>
5:13 pm - Wednesday April 20, 4861

የቋንቋ ፌደራሊዝምና የአብሮነት ፈተናዎች!! (ከድልበቶ ደጎዬ ዋቆ፣)

የቋንቋ ፌደራሊዝምና የአብሮነት ፈተናዎች!!
 
ከድልበቶ ደጎዬ ዋቆ፣ 
ኢትዮጵያን ወደ 80 ትናንሽ የሚበጣጥሰው የቋንቋ ፌደራሊዝም (ብሄርተኝነት) ለዓለማችን 2ኛ የዓለም ጦርነት ከወለደላት ለኢትዮጵያችን ምን ሊወልድላት ይችላል?!?
ብሄርተኝነት በ19ኛው ምእተአመት የአሜሪካና የአውሮጳ የፍልስፍና አዋቂዎች ነን በሚሉ ጥቂት ሰዎች ( አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ውድሮ ዊልሰን፣ ኢጣልያዊው ጁሴፔ ማዚኒ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ) የተቀነቀነ አይዲዎሎጂ ነበር። “የብሄርተኝነት አይዲዎሎጂ” እንደሚሰብከው እያንዳንዱ የራሴ ቋንቋና የዘውግ ማንነት አለኝ ብሎ የሚያምንና የሚኮራ ማህበረሰብ የሚኖርበት ጂዎግራፊያዊ የመሬት ይዞታ በትክክል ተከልሎ፣ ወሰኑ ተረጋግጦና የአስተዳደር ወሰኑ የድንጋይ ችካል ተደርጎበት ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲችል እድል ከተሰጠው በዚህች አለም ላይ የማይናጋ የዘለቄታ ሰላም ይሰፍናል ተብሎ የተውረገረገ አይዲዎሎጂ ነበር። ለዚህም አይዲዎሎጂ መተግበሪያ ያግዛል ተብሎ በአንደኛው የአለም ጦርነት ማክተሚያ ወቅት በአለም ሉአላዊ አገሮች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲገዛ በተደነገገው የኢንተርናሽናል ህግ አካል ሆኖ የታወጀው “የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት” የሚል መርህ ነበር። የአንደኛውን የአለም ጦርነት በድል አድራጊነት ያጠናቀቁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውድሮ ዊልሰንና የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሎይድ ጂዎርጅ የብሄርተኝነትና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ርእዮተአለም በመተግበር አውሮጳን በአያሌ ትናንሽ አገሮች በታተኗት፣ የቀድሞ ሰፋፊ የአውስትሮ—ሃንጋሪ የመሳሰሉትን ኢምፓየር ግዛቶችን ብትንትናቸውን አወጡ፣ የዘለቄታ ሰላማዊ አብሮነት በሁሉም አገሮች መካከል እንዲደሰፍን እናደርጋለን በሚል ህልም አይሉት ቅዠት! (Elie Kedourie, Nationalism, fourth edition, pp xv—xviii)። ይህም በትናንሽ የቋንቋ አሃዶች የመከፋፈል ሂደት ቀጥሎ በነበሩት ዘመናት መላዋን አውሮጳ የሰላም ቀጠና አላደረጋትም፣ ወደእርስ በእርስ ግጭትና የሽብር አዘቅት ውስጥ ከተታት እንጂ። ቀጥሎም ያንኑ አይዲዎሎጂ ተከትለው በርካታ የቋንቋ/የዘውግ ማህበረሰቦችን በሶሻሊዝም ግንባታ ሽፋን በአንድ ግዛት ስር በመጠቅለል ለመግዛት የሞከሩት የሶቪየት ሶሻሊስት ህብረት፣ የዩጎዝላቪያና የቼኮዝሎቫኪያ ሬፑብሊኮችም የቡድን መብቶችን እንጂ የግለሰብ መብቶችን በመጨፍለቃቸው፣ የመንግስትና የፓርቲ ሚናን በግልፅ ባለመለየታቸው፣ የህዝብን ሳይሆን የፓርቲን የበላይነትና ጠቅላይነት በማስፈናቸው፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ እሴቶችን ሳይሆን ኮሙኒስታዊ የአፈና መሳሪያዎችን በመዘርጋታቸውና የኢኮኖሚ እድገትን በከፍተኛ ደረጃ እውን ለማድረግ ባለመቻላቸው ከላይ የተጠቀሱት ሬፑብሊኮች የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ማክተሙን ተከትለው እኤአ በ1989 አም ብትንትናቸው ወጥቷል፣ በቃላት ሊገለጽ የማይቻል የህዝቦች እልቂትና የአገር ውድመት ለመታዘብ ተገድደዋል።
ከላይ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተገለፀው የእነውድሮ ዊልሰንና የእነጁሴፔ ማዚኒ የ”ብሄርተኝነት” እና “የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት/ መርህ” አይዲዎሎጂ  የአውሮጳ አገሮችን ከማፈራረሱም በላይ ሳይውል ሳያድር በቃላት ተገልጾ የማያልቅ እልቂትና ውድመት ያስከተለው የሁለተኛው የአለም ጦርነት (1939—45 እኤአ) መላውን አለም (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በደም ጎርፍ አጥለቀለቃት፣ በብዙ ሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት የንብረት ውድመትና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት፣ ለመፈናቀል፣ ለስደትና ለመከራ ዳረጋቸው። አውሮጳውያን ከዚያ የመከራ መቀመቅ ሊላቀቁ የቻሉት በ1960ዎቹ አመታት በፈረንሳይና በጀርመን አርቆ—አሳቢ መሪዎች ብልህነት የአውሮጳ ህብረትን በመመስረትና በአንድነት በመሰለፍ ለአገሮቻቸው የጋራ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሳያሰልሱ በመጋደልና በእነውድሮ ዊልሰን የተከለሉትን የቋንቋ ክልሎች፣ የተቸከሉትን የድንበር ወሰኖችንና የድንጋይ ችካሎችን በማስወገድ ነበር። ከዚህ አስደንጋጭ የአለም ልምድና አውዳሚ የታሪክ አስተምህሮ መልካም ትምህርት ቀስመን ያንን አጥፊ አይዲዎሎጂ ላለመከተልና የሌሎችን ስህተት ላለመድገም ከመወሰን ይልቅ የቋንቋ ፌደራሊዝምን ለመተግበር ከሚታትሩ አገሮች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ለመጨበጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ላለፉት አምሳና ከዚያ በላይ ለሆኑ አመታት (ከ1960ዎቹ ጀምሮ) በከንቱ እየተፍጨረጨርን እንገኛለን፣ ባለፉት 27 አመታት ውስጥ የቋንቋ ፌደራሊዝምን ለመተግበር ያላደረግነው ጥረት፣ ያልሞከርነው ሙከራና ያልፈነቀልነው ድንጋይ የለም። ጥቂት እንደልጓም የሀገሪቷን መበታተን እስካሁን ገትቶ ያቆየው የ56 በላይ የቋንቋ ማህበረሰቦችና የዘውግ ቡድኖች በአንድ “የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል” በአንድነት እንዲተዳደሩና ለኢትዮጵያ አንድነት ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እድል በመቀዳጃታቸው ነው ብዬ እገምታለሁ። ይህ የታሪክ እድል ተፍቆ አሁን የሲዳማ ዘውግ/ብሄር የራስን የተናጠል ክልል የመፍጠር ጥያቄ ህገመንግስታችን የሚፈቅድላቸው መብት እንደመሆኑ መጠን ይህ ተግባራዊ ውጤት ካስገኘ የተቀሩት  የክልሉ የቋንቋ ማህበረሰቦች አብዛኛዎቹ (ምናልባት ሁሉም ባይሆኑ) የሲዳማን ብሄር ፈለግ መከተላቸው እንደማይቀር የወላይታ፣ የሀዲያ፣ የከምባታ፣ የካፋ፣ የጋሞ፣ ወዘተ ብሄረሰቦች የቅርብ ጊዜ “የክልልነት ጥያቄዎች” አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። በዚህም የተነሳ አገራችንን የመበታተኑን አስቂኝ ድራማ ስለገፋንበት ዛሬ በመላው አገራችን የእርስ በእርስ ግጭትና የቋንቋ/የብሄር ተኮር መፈናቀል እየተባባሰ በመቀጠል ላይ ይገኛል። አሳዛኝ ትርክት ነው።
ዛሬ የቋንቋ ፌደራሊዝምን በመንግስታዊ ውሳኔ ለመግታት ይቻለናል ወይ ብለን ለመጠየቅ ብንገደድ ምላሹ በቀላሉ ሊሳካልን አይችልም ነው። “ላም እሳት ወለደች፣ እንዳትልሰው ፈጃት፣ እንዳትተወው ልጇ ሆነባት”፣ እንዲሉ እኛው አሚጠን የወለድነውን ልጃችንን መጥፎም ቢሆን አሽቀንጥረን ልንጥል ጭካኔ አይኖረንምና። የሆነ ሆኖ የወለድነው ልጃችን (ብሄርተኝነት) ሁላችንንም እንደሚያቃጥለን ስንገነዘብ ያንጊዜ too late ይሆንና የሚከተለው የዩጎዝላቪያ፣ የሶቪየት ህብረት፣ የቼኮዝሎቫኪያ፣ ወዘተ እጣፈንታ እንዳያጋጥመን፣ ወደፍጅትና ወደመበታተን እንዳያመራን ብዬ በብርቱ እሰጋለሁ። ዴሞክራሲ ገና ስር ባልሰደደበትና ኢኮኖሚያችን እጅግ ባላደገበት ሁኔታ የቋንቋ ፌደራሊዝም ከእሳት ጋር እንደመጫወት ይቆጠራል። ለሁሉም የቋንቋ ክልሎች የወሰን ችካል ከተተከለና ይህ የኔ ክልል ነው፣ ሌላው ወደዚህ ድርሽ እንዳትል የሚል አደገኛ ብሄርተኝነት ይጦዝና ሁላችንንም ወደግጭትና ወደደም መፋሰስ ምእራፍ ይዘፍቀናል ብዬ እፈራለሁ። የህዝብ ብዛት እየጨመረ፣ የስራአጡ ቁጥር የትየሌለ እየሆነ ሲሄድ የመሬትና የሌላው ሀብት ተጠቃሚነት ጥያቄ የሞትና የህይወት ጥያቄ እየሆነ ስለሚሄድ ለዘመናት አብሮ የኖረ የሌላ ብሄር/ክልል ተወላጅ በግድ ተገፍቶ እንዲወጣ መደረጉ አይቀሬ ይሆናልና የቋንቋ ፌደራሊዝም ወደጥፋት እንጂ ወደልማት ጎዳና ያስገባናል ብዬ አላምንም። ዛሬ ከተለያዩ ክልሎች በግድ የሚፈናቀለውና የሚገደለው ዜጋ በዚሁ የresource ውሱንነትና ግፊት እንደሆነ አለመገንዘብ አጉል ጅልነት ነው፣ ይህ እንዳያጋጥመን አስቀድሞ በመንግስት የተደገፈ አገራዊ የውይይትና የምክክር  ጉባኤ ተጠርቶ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የተለያዩ ልሂቃን፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ግልፅና ሃላፊነት የሚሰማው ሰፊ ውይይት፣ ብሄራዊ መግባባትና ስምምነት ከተደረገ በሁዋላ ሌላ ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታና ለሰላማዊ አብሮነታችን (peaceful co—existence) ዋስትና የሚሆነን አማራጭ ደረጃ በደረጃ መተግበሩ ይመረጣል፣ ለጊዜው ግን የቋንቋ ፌደራሊዝም ይቅር ለማለት እጅግ አዳጋች እንደሚሆንብን ይታየኛል፣  የዋለ ያደረበት የውርዴ በሽታ በቀላሉ ሊፈወስ አስቸጋሪ ነውና። እግዚአብሄር ቀና ልቦና ይስጠን። የወደፊቷ ኢትዮጵያ እጣፈንታ ያስፈራኛል።
Filed in: Amharic