ማስፈራራቱ አሁንም ቀጥሏል
ከይኄይስ እውነቱ
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የየጐሣችን ወኪሎች ነን የሚሉ ‹‹የፖለቲካ ማኅበራት›› ሊመክሩ ጉባኤ አድርገው ነበር ፡፡ በጐሠኞቹ ማኅበርተኝነት ተካፋይ ያልሆኑ ጥቂት ጉባኤተኞች/ድርጅቶች እንዳሉ አልዘነጋሁም፡፡ በጎላው ለመናገር ፈልጌ እንጂ፡፡ የሚመክሩት ለፖለቲካ ሥልጣን ተወዳድረው ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ ያለን ሕዝብ ለመምራት ይሁን የየጐሣቸው/የየነገዳቸው አለቆች ለመሆን አድማጩንና ተመልካቹን ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ የሺህ ዓመታት ሀገረ መንግሥትነትና ገናና ታሪክ ባለቤት ነኝ የሚል አገርና ሕዝብ ያፈራቸው የፖለቲካ ‹ዐዋቂዎች› በዚህ ጉባኤ የታደሙት መሆናቸው አሸማቆኛል፡፡ በኀፍረት የምገባበት ጠፍቶኛል፡፡ ለአገርም ለሕዝብም ማፈሪያና ውርደት መሆናቸውን ታዝቤአለሁ፡፡ ምነው በዚህ ትውልድ ባልተገኘሁም አስብሎኛል፡፡ ታዲያ የአገዛዞች መፈራረቅ ምን ያስደንቃል? ሕዝባችንም በአእምሮ ሕፃን ሆኖ ሁሌ በአምባገነኖች ሞግዚትነት ሥር ለመተዳደር የፈቀደው ለምን እንደሆነ በጭራሽ አይገባኝም፡፡ አሁንም ወጣት አዛውንቱ መሥዋዕትነት ከፍሎ ሲያበቃ የሥልጣን ባለቤትነቱን ሳያረጋግጥ ዕጣ ፈንታውን ዕድል ተርታውን ለጮሌ ፖለቲከኞች ትቶ ወይ ቤቱ ተቀምጧል አሊያም እርስ በርሱ ይናቆራል፡፡ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያን ወደ ጥንታዊ የጋርዮሽ ሥርዓት ለመመለስ የሚታገሉ ጉዶች እየተመለከትን ነው፡፡ እንዴት ነው ጎበዝ ራሳቸውን ‹ልሂቃን› ነን ብለው የኮፈሱ ሰዎች በተራ መንጋነት ተሰባስበው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሥልጣኔ ይልቅ ኋላ ቀርነትን የሚመኙት? ዕብደቱም ድንቁርናውም ‹ከፊደል መቊጠር› ጋር በእጥፍ ድርብ እየጨመረ የሚመጣባት አገር የኛው ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም፡፡
እንደተጠበቀው በጉባኤው ሁለት አመለካከቶች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ አንደኛው ወገን የፖለቲካ ማኅበር ጐሣን መሠረት አድርጎ መደራጀት አለበት የሚልና እንደ ወያኔ ትግሬ ፖለቲካን በጐሣ መሠረትነት ያደራጀ ሲሆን፣ ጥቂቶች ደግሞ የፖለቲካ ማኅበር መሠረቱ ዜግነት መሆን አለበት ብለው የሚያምኑ ቡድኖች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት የትኛው እንደሆነ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ድምፅ (public opinion polls) ተአማኒነት ባለው አካል ተሰብስቦ ወይም ጥናት ተደርጎ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ጐሣና ፖለቲካ በደምም በጉዲፈቻም ዝምድና እንደሌላቸው ብዙ ስለተነገረና ስለተጻፈ እዛ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ያም ሆኖ አንድ ግለሰብ ወይም የግለሰቦች ስብስብ የመረጠውን የፖለቲካ አመለካከት መያዝ/አቋም ማራመድ፤ ይህንን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በሰላም መታገል መብቱ እንደሆነም አምናለሁ፡፡ ለአገር ለወገን የሚበጀው የቱ ነው የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ‹‹የፖለቲካ ማኅበራቸውን›› በጐሣ ካደራጁትና ለጐሣ ፖለቲካ ጥብቅና ከቆሙ ወገኖች አንዱ የሆኑት የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የአገራችን የጐሣ ፖለቲካ አደረጃጀት የሚጎድለው ዴሞክራሲ በመሆኑ፣ ይህንን ማሟላት ከተቻለ የፖለቲካ ማኅበርን በጐሣ ማደራጀቱ ተመራጭ መሆኑን ሲከራከሩ ተደምጠዋል፡፡ ፕሮፌሰር! ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል ይላል የአገሬ ሰው፡፡ በኅብረተሰባችን ውስጥ ለሚታየው ጫፍ የረገጠ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ልዩነት ሥር መሠረቱ ጐሠኝነት/መንደርተኝነት መሆኑን የሚስቱት አይመስለኝም፡፡ በፖለቲካው ዐውድ ስናየው ጐሠኝነት በባህርይው አግላይና ጠባብ ነው፤ በአሳብ ልዕልና አያምንም፤ ለዴሞክራሲ ማዕከላዊ ዓምድ በሆነ የፖሊሲና የሃሳብ ክርክር አያምንም፤ የኛ ጐሣ አባል ከሆነክ እንደኛ አስብ፣ የኛን ‹ደም› ተጋራ፣ የኛን አምላክ አምልክ፣ ጥቅማችንን አስጠብቅ፣ ከኛ ውጭ ያለው ላይ የፈለግከውን ማድረግ ትችላለህ፣ በየትኛውም ሁኔታ ላንተ ጥብቅና እንቆማለን÷ የሚቃወሙህን ሁሉ እናጠፋለን፡፡ በሚል መሠረታዊ እምነትና አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ አመለካከት ነው፡፡ ባጭሩ መንጋነት ነው፡፡ ከሰው በታች የሚያደርግ ደዌ ነው፡፡ እነዚህ ባህርያት ደግሞ ዴሞክራሲ የሚባለው ፅንሰ ሃሳብ ተቃራኒ ናቸው፡፡ አንድም ዴሞክራሲ መንግሥተ ሕዝብ ማለት ነው፡፡ የጐሣ አገዛዝ እንዴት ሆኖ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የሕዝብ መንግሥት ሊሆን ይችላል? በሌለ አነጋገር ጐሠኝነትና ዴሞክራሲ አብረው አይሄዱም፡፡ (It is hard to think of tribalism co-existing with democracy) ምናልባት የወያኔ ጐሠኝነት ነገዱን በሙሉ አልጠቀመ ከሆነ ፕሮፌሰሩ የሚያስቡት ነገዳቸውን ‹በእኩልነት› የሚጠቅም ‹ዴሞክራሲያዊ ጐሠኝነት› (a term in contradiction) ይሆን? ድንቄም ‹ዴሞክራሲ›!!!
ሌላው ፕሮፌሰሩ ማንም ኢትዮጵያዊነትን ሰጪና ነሺ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡ እውነት ነው፡፡ ብሔራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት) በግለሰብ ወይም በቡድኖች ፈቃድ የሚታደልና የሚነፈግ አይደለም፡፡ ምናልባት በሕግ አግባብ ሊሰጥ ወይም ሊነሳ ካልቻለ በቀር፡፡
በሌላ በኩል ፕሮፌሰሩ በንግግራቸው የጐሠኝነት ፖለቲካ በዕውቀት፣ በአሳብ ልዕልና፣ በምክንያት (reasoning) እና አመክንዮ (logic) ላይ ሳይሆን በስሜታዊነት ላይ እንደተመሠረተ ፊታቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ ያናገራቸውን ታዝቤአለሁ፡፡ ይኸውም የፖለቲካ ማኅበርን በጐሣ ማደራጀት ካልተቻለ በዚህ መልክ የተደራጁትን ‹ወደማንፈልገው› መገንጠል እንዲያመሩ መንገድ መክፈት ነው በሚል እሳቸውም በተራቸው እንደ ወያኔ ትግሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስፈራርተዋል፡፡ ሕወሓት የሕዝብ ቁጣና ተቃውሞ ባየለበት ቊጥር ይቺን አገር እበትናታለሁ/አፈርሳታለሁ የሚለውን ማስፈራሪያ የአገዛዙ አንድ ስልት አድርጎ ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ ፕሮፌሰሩም ይህንኑ ደገሙት፡፡ ኢትዮጵያ በነገድ ፖለቲካ ትመራለች፡፡ እምቢ ካላችሁ ነገዳችንን ይዘን ለመገንጠል እንገደዳለን ዓይነት የፖለቲካ ቁማር ውስጥ የገቡ ይመስላል፡፡ እውነት ይሄ ካንድ ‹ምሁር› ነኝ ከሚል ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል? ወይስ ጽንፈኛ የፖለቲካ አጋሮቻቸውን ለማስደሰት? ፕ/ር በየነ ጴጥርስ እንደተደሰቱት፡፡
ቢሆን ቢደረግ ይሻላል ወደምለው የማጠቃለያ ነጥብ ከማመራቴ በፊት ጐሠኝነትና ፖለቲካን በሚመለከት በሀርቫርድ ኬኔዲ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ልማት አሠራር ፕሮፌሰር የነበሩት ኬንያዊው ካሌስቱወስ ጁማ “How tribalism stunts African democracy” ጐሠኝነት የአፍሪቃን ዴሞክራሲ እንዴት እንዳቀነጨረው የተናገሩት ሃሳብ ለዛሬው አስተያየቴ አግባብነት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
“Africa’s democratic transition is back in the spotlight. The concern is no longer the stranglehold of autocrats, but the hijacking of the democratic process by tribal politics.… The challenge to democracy in Africa is not the prevalence of ethnic diversity, but the use of identity politics to promote narrow tribal interests. It is tribalism. … The last 20 years of Somalia have shown the dangers of ethnic competition and underscore the importance of building nations around ideas rather than clan identities.
Much attention over the last two decades has been devoted to removing autocrats and promoting multiparty politics.
But in the absence of efforts to build genuine political parties that compete on the basis of ideas, many African countries have reverted to tribal identities as foundations for political competition.
Leaders often exploit tribal loyalty to advance personal gain, parochial interests, patronage, and cronyism.
But tribes are not built on democratic ideas but thrive on zero-sum competition.
As a result, they are inimical to democratic advancement.
In essence, tribal practices are occupying a vacuum created by lack of strong democratic institutions.
Tribal interests have played a major role in armed conflict and civil unrest across the continent.”
(https://www.belfercenter.org/publication/how-tribalism-stunts-african-democracy)
የፕሮፌሰር ጁማን ሃሳብ ጠቅለል ባለ መልኩ ለማስቀመጥ፤ በአሁኑ ጊዜ ለአፍሪቃ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደት ትልቁ እንቅፋት ፍጹማዊ ሥልጣን ያላቸው አምባገነኖች ሳይሆኑ የዴሞክራሲው ሂደት በጐሠኞች መጠለፍ ነው፡፡ ፤ ለአፍሪቃ ዴሞክራሲ ዋናው ተግዳሮት የጐሣ/ነገድ ብዝኀነት መኖር ሳይሆን የማንነት ፖለቲካን ጠባብ ለሆነ የቡድን ፍላጎት ማራመጃነት መጠቀም ነው፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ሶማሊያ ውስጥ የሆነው በጉልህ የሚያሳየን የጐሣዎች ውድድርን አደገኛነት እና አገርን ከጐሣ ማንነት ይልቅ በሃሳብ ዙሪያ መገንባት ያለውን ጠቀሜታ ነው፡፡ … አገዛዞች ብዙውን ጊዜ የነገድ/ጐሣ ታማኝነትን የግል ጥቅማቸውን ለማካበት፣ ጠባብ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም፣ ለታማኞቻቸው ሹመትና ልዩ ጥቅም ለመስጠት እና ለዘመድ አዝማድ ውለታ መፈጸሚያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን ነገዶች/ጐሣዎች በዴሞክራሲያዊ ሃሳቦች ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ ሌሎች ሙሉ በሙሉ ተሸናፊ በሚሆኑበት ወይም በሚያጡበት ሁናቴ ላይ ስኬታማ የሚሆኑ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ለዴሞክራሲ መሻሻል አመቺ አደረጃጀቶች አይደሉም፡፡
ማጠቃለያና ቀጣዩ ሁናቴ፤
ኢትዮጵያችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ በጥቅሉ ስገመግመው አገራዊ አለመረጋጋትና የፀጥታ በእጅጉ መደፍረስ፤ በመንግሥትነት የተሰየመው አካል ከዘለቄታው ይልቅ በጊዜያዊ ጉዳይ ላይ ማተኮር÷ አገራዊ ጉዳዮችን ዕቅድና ቅደም ተከተል አስይዞ ከመምራት ይልቅ በዘመቻና ውክቢያ መጠመድ፣ አገሩን በሚገባ አለመቆጣጠር፤ ባንድ ወገን፤ በሌላ በኩል ቊጥሩ ቀላል የማይባል የሕዝባችን ክፍል ወያኔ ትግሬና አሽከሮቹ በረጩት መርዝ አቅሉን ስቶ መቅበዝበዝ፣ ዓመታትን በዘለቀ ብሶትና ምሬት፣ በእልህ፣ በችጋርና በድንቁርና ወዘተ. የሚናጥበትና የሚንተከተክበት ሁኔታና ሥርዓተ አልበኝነት በስፋት ይስተዋላል፡፡ በዚህ ኹከት በነገሠበት ጊዜ የምርጫ ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑ ማንም በአእምሮው የሚገኝን ሰው የሚያስገርም ነው፡፡ ግርግሩ ለማን ነው የሚጠቅመው? ከዚህስ ሁናቴ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ ወይ ብሎ መጠየቁ አስተዋይነት ነው፡፡
እንዴኔ ትሁት እምነት የሽግግር ጊዜው ረዘም ብሎ የሚከተሉትን በቅደም ተከተል ብናከናውንስ?
- የአገራችንን ሰላምና ፀጥታ ቅድሚያ ሰጥቶ ዘለቄታነት ባለው ሁኔታ ማረጋጋት፤
- ኹላችንም ወደ ቀልባቸን/ልቦናችን የምንመለስበት የጥሞና ጊዜ መስጠት፤
- ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን የሚያደራጁበትና ዓላማና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋወቁበት፤ ዐበይት በሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ለሕዝብ ግንዛቤ የሚያስጨብጡበት በቂ ጊዜ መስጠት፤
- በዐቢይ የሚመራው ‹ግንባር› ራሱን በወንጀል ተጠርጣሪ ከሆኑ አባላቱ አፅድቶ በስም ለውጥ ብቻ ሳይሆን ከጐሣ ውጭ በመደራጀት (መሠረቴን አጣለሁ በሚል አስተሳሰብ ሳይያዝ) ለሌሎች አብነት ቢሆን፤
- ከ80 በላይ እንዳሉ የሚነገሩት ስብስቦች ውስጥ አብዛኛዎቹ በየትኛውም መመዘኛ እውነተኛ የፖለቲካ ማኅበራት ባለመሆናቸው፣ ገሚሱም በወያኔ ሕወሓትና አሽከሮቹ ተቃዋሚዎችን ለማሰናከል ድርጎ እየተሠፈረላቸው የተቋቋሙ የውሸት ‹የቤተዘመድ ስብስቦች› በመሆናቸው በጠ/ሚ ዐቢይ የሚመራው ‹ግንባር› በተለየ መድረክ ሰብስቧቸው እንደ ሁኔታው እንዲበተኑ ወይም በይዘትም በቅርፅም ተለውጠው አንድ ወይም ሁለት ሆነው እንዲደራጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
- የሕዝብና የቤት ቆጠራ ከአገር መረጋጋት በኋላ ቢካሄድ፤
- ሽግግሩን የሚመራው አካል ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተወካዮች ጋር አገራዊ ጉባኤ በማካሄድ፣ በማኅበረሰብም ደረጃ እስከታችኛው የአስተዳደር ዕርከን ወርዶ ውይይቶችን በማድረግ፣
1ኛ/ በፖለቲካ ፓርቲዎች መወሰን የሌለባቸውን ቊልፍ አገራዊ ጉዳዮችን በመለየት ከምርጫ በፊት ለሕዝብ ውሳኔ እንዲቀርቡ ማድረግ፡፡ ወይም በጉባኤው ብሔራዊ መግባባት የተደረሰባቸውን አንኳር ጉዳዮች የሕግ ቅርፅ ማስያዝ፡፡ ለአብነት ያህል ፖለቲካችን በዜግነት ወይስ በጐሣ ላይ ይመሥረት፤ ሥርዓተ መንግሥታችን ሲቪክ ፌዴራላዊ ወይስ የአስተዳደር ነፃነት የሚሰጥ አሐዳዊ፤ ወይስ የባህላዊውና ሲቪክ ፌዴራላዚም ቅልቅል፤ ቅርፀ መንግሥታችን ፕሬዚዳንታዊ ወይስ ፓርላሜንታዊ ወይስ በተሞክሮ ካለ የሁለቱ ዲቃላ ወዘተ. የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
2ኛ/ ‹‹የምነቅፍብህ ነገር አለኝ›› በሚለው አስተያየቴ (
ከፍ ብዬ የተጠቀስኳቸው አሳቦች ቅንነት፣ ፍላጎትና ዝግጁነቱ ካለ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከአንዳንድ ወዳጆቼ ጋር በአገር ጉዳይ ላይ ስንወያይ ይህ አመለካከት ተምኔታዊና አሁን ምድር ላይ ባለው ጽድቅ መሠረት ሊፈጸም የማይችል ምኞት (ideal) አድርገው ይወስዱታል፡፡ የበኩሌንና የተሰማኝን አካፍዬአለሁ፡፡ እስቲ ደግሞ እናንተ እንደ ብጤታችሁ ተወያዩበት፡፡