>

እነሆ መሃከለኛው መንገድ ! አማራጭ የሽግግር ኣሳብ (ገለታው ዘለቀ ከተባበረችው አሜሪካ)

እነሆ መሃከለኛው መንገድ !

አማራጭ የሽግግር ኣሳብ

ገለታው ዘለቀ ከተባበረችው አሜሪካ

 

መግቢያ

ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ በመሆኗ ዜጎቿ ተስፋን ሰንቀዋል:: ምንም እንኳን ስጋቶች በግራም በቀኝም የተደቀኑ ቢሆንም ነገር ግን የህዝቡ ተስፋ ሃያል ነው። በተጨባጭ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ ርምጃዎች ብዙዎችን አነቃቅተዋል። ታዲያ የከረምንበት ፖለቲካ ውጤትና ራቅ ካለ ዘመን ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ችግር አለና ይህን የማሰናከያ ድንጋይ ገለል ኣድርጎ ዴሞክራቲክ ኔሽን ለመሆን ስርዓታዊ ለውጦችን ይጠይቃል። ወደ ዴሞክራሲ ለምናደርገው ሽግግር በርግጥ የስርዓቶች ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ኣለብን። ትርክቶቻችንን ከውጭ ወደ ውስጥ፣ ከውስጥ ወደ ውጪ እያገላበጥን አይተን የሚጠቅመንን ይዘን የማይጠቅመንን እያራገፍን በፍጥነት ወደ ዴሞክራሲ ማምለጥ ኣለብን።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ታሪካችን አልተራመድንም። ከብዙ ኣፍሪካውያን ወደ ኋላ ቀርተናል። ይህ ሊቆጨን ይገባል። በመሆኑም በሽግግሩ ወቅት የተሻለ ስርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት የተሻለና የላቀ ኣሳብ ያስፈልገናል። ዶክተር ኣብይ እንዳሉት የምናመጣው የመፍትሄ ኣሳብ ደግሞ ሃገር በቀል የሆነ መሆን ያስፈልገዋል። ሀገሮች በኩረጃ ችግሮቻቸውን ኣልፈቱም። ከሌላው ዓለም የሚማሩት ነገር ቢኖርም ነገር ግን ሃገሮች ሁሉ የየራሳቸውን መፍትሄ እያመጡ ነው ችግራቸውን የፈቱት። ስለዚህም ችግሮቻችንን በማጥናት ሃገር በቀል መፍትሄ ለማምጣት መጣር አለብን። ከዚህ በፊት ስንከተላቸው የነበሩ ትርክቶች አንዳንዶቹ ከኛ ጋር የማይሄዱ ነበሩ። የኛን ማህበረሰብ በምልዓት የማይገልጹ ነበሩ። ታዲያ እነዚህ ትርክቶች ከኛ ጋር የማይሄዱ ሆነው በግድ

እንዲሄዱ ስናደርግ የሚፈጠር ማህበራዊ ምስቅልቅል ይኖራል። ችግሮቻችንን መለየትና መፍትሄ ማምጣት የኛ ድርሻ ነው።

ሃገርን ሃገር የሚያሰኘው በጠገጉ ስር ያለው ማህበራዊ ት ስ ስር ነው። ይህ ትስስር ደግሞ የተለያዩ መርሆዎች ይኖሩታል። እኛ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩን የትስስር መርሆዎች (organizaing principles) ለሃገራችን ሰላምና ልማት እጅግ ወሳኝ ናቸው። ብሄሮችን እንዴት ቀጥታና ተዋረድ ማስተሳሰር ፈለግን? የብሄሮችና የዜጎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች በምን ህግ ሊገዙ ይገባል? የሚለው ነገር በሚገባ መጠናት አለበት።
በዚህች ጽሁፍ ስር የማቀርበው ነገር ለሃገራችን መሰረታዊ ችግሮች አማራጭ መፍትሄ ለመስጠት ነው። በተቻለ መጠንም በአዲስ ሃገራዊ ማህበራዊ ኪዳን ላይ በሚደረግ የከፍተኛ ቃል ኪዳን ትስስር የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ለማስተካከል ነው።

ወደ መፍትሄ ከመሄዴ በፊት ድህነቱ፣ የመልካም ኣስተዳድሩ ችግር እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ከነዚህ ችግሮች እንዳንወጣ የሚያናቁሩ፣ሰላም የሚነሱ፣ ዴሞክራሲን እንደ ልብ እንዳንለማመድ የሚያደርጉ መሰረታዊ ችግሮች በፖለቲካ ትርክቶቻችንና በመንግስት ስርዓታችን ውስጥ አሉ። በስርዓታችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኣንዳንድ ኤለመንቶች ሰላማችንን የሚያናጉ ግጭትንና መፈናቀልን የሚያመርቱ ናቸው። የማንነት ጉዳይ፣ የአስተዳደር ጉዳይ፣ የወሰን ጉዳይ ከግጭት መንደር ለምን አይርቁም? መፈናቀልና ግጭት ለምን ይከተሏቸዋል? ከፍቅርና ከመደመር ሰፈር ርቀው ለምን ለግጭት ቀረቡት? ከስርዓቶቻችንና ከትርክቶቻችን ምን ዓይነት ሶሻል ካፒታል አመረትን? ስርዓታችን ለኢኮኖሚ እድገትና ለፍትህ ያላቸው አስተዋጾ ምን ይመስላል? ብለን የምንመረምርበት ዘመን ላይ ነን። በቅርቡ የኢትዮጵያ ፓርላማ እነዚህን ጉዳዮች ያጠና ዘንድ ኮሚሽን ማቋቋሙ የሚያሳየው ቁምነገር በነዚህ ጉዳዮች ኣካባቢ ብዙ አሳሳቢ ችግሮች መኖራቸውን ነው:: ሃገራችን ኢትዮጵያ በረጅም

ዘመን ታሪኳ ብዙህ ሆና የኖረች ሃገር ብትሆንም ነገር ግን ብዝሃነትን በሚገባ አላስተናገደችም። በተለይም ከብሄር ማንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብዙ ችግሮች አሉባት። በመሆኑም ሃገራችን ለውጥ በፈለገችበት በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ የማንነት ጉዳይና የብሄር ጥያቄ መነሳቱ ትክክል ነበር። ችግሩ ይህንን ጥያቄ ጠቅላይ ጥያቄ በማድረግ የችግሮቻችን ሁሉ ማጠንጠኛና ሁለንተናዊ ማሳያ ሆኖ መቅረቡ ነበር ስህተቱ ። የብሄር ጥያቄ ጥያቄዎችን ሁሉ ጠቅልሎ መዋጡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን ነገር ፖለቲካዊ ወደአደረገ የፖለቲካ ትርክትና ስርዓት ውስጥ ኣስገብቶናል። የሰውን ልጅ ሁለንተና ፖለቲካዊ ማድረግ ደግሞ ከዴሞራሲ መርሆዎች ጋር ስለማይሄድ ይህ ትርክት ወደምንፈልገው ዴሞክራሲ እንዳንዘረጋ እየጠለፈ ይጥለን ጀመር። ፖለቲካዊ ያደረግነው ማንነት ሁሉ የስልጣን ቅርምት ውስጥ ከቶናል። ዋናውን የጋራ ችግር መዋጋት ትተን ወደ ጎን በማንነት፣ በአስተዳደር፣ በወሰን ጉዳይ ተያያዝን። ስለዚህም የሚፈለገውን ያህል ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት አልቻልንም። በርግጥ ለዚህ ተጠያቂው ሁላችንም ነን።

እንግዲህ ሃገራችን ሽግግር ላይ ስትሆን ወደፊት የተሻለ ስርዓት ገንብታ ለመኖር እንድትችል ከዚህ ለውጥ ባሻገር የምትገባበትን ቤት በዚህ በሽግግሩ ወቅት ኣሳምረን መስራት ኣለብን። ይህ የሽግግር ወቅት የጽሞና ጊዜ ነው። ከፍ ሲል እንዳልኩት በተለይ የማህበረሰባችንን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህንበራዊ ትስስሮች የፍልስፍና መሰረት፣ ከዴሞክራሲ መርሆዎች ጋር ያላቸውን ዝምድና፣ የሚያመርቱትን ማህበራዊ ካፒታል፣ ወዘተ የምንገመግምበት ሰዓት ነው።

መፍትሄ ወዳልኩት ኣሳብ ከመምጣቴ በፊት ያሉትን መሰረታዊ ስርዓታዊ ችግሮች እንደሚከተለው አንድ ሁለት እያልኩ ላቅርብና ወደ መፍትሄው እመጣለሁ

ጎልተው የሚታዩ ችግሮቻችንና በሽግግሩ ወቅት መፍትሄ የሚሹ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው:-

1. የማንነት ኣያያዝ
በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ገንነው የወጡ ማንነቶች ያሉ ሲሆን እነዚህ ማንነቶች የብሄር ማንነትና ብሄራዊ ማንነት ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች ሳይፈራረሱ፣ ሳይደባደቡ አብረው የሚኖሩበት ስርዓት አልገነባንም። አንዱ ዋና ችግር ይሄ ነው። ህገ-መንግስታችን ራሱ ኣንቀጽ ሰላሳ ዘጣኝ ላይ ኣንዱን ፈራሽ አንዱን ኣፍራሽ ያደርገዋል። ብሄራዊ ማንነት በብሄር ማንነት ሊመታ ወይም ሊፈርስ የሚችልበት ስርዓት ነው ያለን። በየትኛውም ጊዜ ሊፈርስ በሚችል የጋራ ቤት ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ልማት ኣይታሰብም። ኣንዱ ችግራችን ይሄ ነው። እንደ ስርዓት ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ማንነት ዙሪያ ግልጽነት የለም። የብሄር ማንነት ስንል የሚገነባው ከባህል ከቋንቋ በተያያዘ ሲሆን ብሄራዊ ማንነትን የሚሰራው ኤለመንት ምንድን ነው? ብለን ኣጥብቀን ኣልጠየቅንም። የብሄራዊ ማንነት መገንቢያ ኤለመንቶችን አንጥረን አላወጣንም። በመሆኑም ብሄራዊ ማንነታችን ወይም ኢትዮጵያዊነታችን በአደባባይ ኣቅም ኣንሶት ሰነበተ። ዛሬ ዶክተር ኣብይ ከወደቀበት ኣንስተው ከፍ ሲያደርጉት ሲታይ የኢትዮጵያ ህዝብ ደስ ብሎት እናያለን። ፖለቲካችን ቤቱን የሰራው በዋናነት በየብሄሩ ሲሆን ብሄራዊ ማንነትን እንደ መገናኛ መድረክ ብጤ ያየነው ይመስላል። ይህ ደግሞ ኣካባቢያዊ ጡንቻዎችን ያፈረጥምና የርስ በርስ ግጭትን ያመጣል።

2. የ “ራስ” (Self) ትርክት
በስርዓታችን ውስጥ መስመር ያለፈ የ “ራስ” (Self) ትርክት መኖሩ ኣንዱ ሌላ ችግር ነው።

ራስ (self) ማለት ምን ማለት ነው? ከሚለው ብያኔ ጀምሮ ወደታች በተግባር ሲወርድ ብዙ እምቅ ግጭቶችን ይዟል። ይህ ትርክት ምን እንደሆነ ኣልተመረመረም። ይህ ትምህርት ከሚከተሉት ማእዘኖች አንጻር በጥብቅ ሊታይ ይገባዋል:-

1. ከኢትዮጵያውያን ማህበረ ፖለቲካ (sociopolitics) ታሪክና ጉዞ ኣንጻር
2. ከኢትዮጵያውያን ብሄሮች ስነ-ኑባሬ (ontology) አንጻር
3. ከኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ዋና እሴቶች (core values) አንጻር
4. ከኢትዮጵያውያን የወደፊት እድል (future of the nation) ኣንጻር
5. ይህ ትርክት በጋራው ቤታችን ውስጥ ምን ዓይነት የስልጣናት ቀመር (power sharing formula) ይጠይቃል ከሚለው ጥያቄ አንጻር
6. በጋራው ቤታችን ውስጥ ምን ዓይነት ማህበራዊ ሃብት (social capital) ያመነጫል ከሚለው አንጻር
7. ይህ ትርክት ከዘመናዊነቱና ዴሞክራሲን ለማንሸራሸር ከመርዳቱ ኣንጻር በጥብቅ መመርመር ይገባናል።
በስርዓቶቻችን ውስጥ የምናመጣቸው ትርክቶች ሁሉ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ትስስሮቻችንን የሚገዙ ገዢ ሃሳቦች ስለሆነ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ እውቀትና ኣቅምን ማፍሰስ ኣለብን። እኔና እኛ ሳይጠፋፉ ወይም ኣንዱ ባንዱ ላይ ሳይነሱ የሚያኖር ስርዓት ያስፈልጋል።

1. የበጀት ፌደራሊዝም (fiscal federalism)
የበጀት ፌደራሊዝማችን በራሱ በተለይ ራስ ከሚለው ትርክት ጋር ተያይዞ የተፈጥሮ ሃብት ኣጠቃቀምና የባለቤትነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ብዙ እምቅ ችግሮችን ኣምጥቷል። የተፈጥሮ ሃብትን የመቀራመት ችግር ውስጥ ገብተናል።

1. የማንነት ድምጽ (identity vote)
የገባንበት የፖለቲካ ትርክት በጅጉ ለማንነት ድምጽ (identity vote) ኣጋልጦናል። ይህ ችግር በዴሞክራሲ መርሆዎች ላይ እንድንረማመድ የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሯል። ብሄሮች የብሄራቸውን ሰው በስልጣን

ከፍታዎች ላይ የማየት አይን በሃይል ተከፍቷል። ደምና ኣጥንት ቆጣራ ውስጥ ገብተናል።

5. ብዝሃነት
ሃገራችን ኢትዮጵያ ብዙህ እንደመሆኗ ይህንን ብዝሃነት ለማስተናገድ የሄደችባቸው ሁለት መንገዶች አደገኞች ናቸው። ቀደም ባለው ጊዜ ወደ ምስለት (assimilation) ያዘነበለ አካሄድ የተከተለች ሲሆን ይህም የብሄሮችን ማንነት አደጋ ላይ የጣለ ነበር። ባለፉት ሃያ ሰባት ኣመታት አካባቢ የተከተልነው የሶሺዮ ፖለቲካል ቲየሪ ደግሞ ከምስለት ወደ ልዩነት ያደላ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ነበር። ሁለቱም ከብዝሃነት ጋር የተጻረሩ ኣካሄዶች ናቸው። ብዝሃነት ማለት በአንድ የፖለቲካና ኢክኖሚ ማህበረሰብነት ጥላ ስር ብዙ ብሄር ወይም ሃይማኖት ሆኖ መኖር ማለት ነው። ብዝሃነት ማለት አንድነት ከብዙህነት ጋር ተደምሮ የሚኖርበት ረቂቅ ህግ ነው። ብዙነት ለአንድነት ተግዳሮት የማይሆንበት፣ ኣንድነት ለብዙነት ተግዳሮት የማይሆኑበት ስርዓት ማለት ነው። እኛ የተከተልናቸውን ስርዓቶች ስናይ ቀደም ሲል የነበረው ስርዓት አንድነት ለልዩነቶች ተግዳሮት እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ኣሁን ያለነብት ስርዓት ደግሞ ልዩነት ለአንድነት ተግዳሮት እንዲሆን ኣድርጓል። በተለይ አሁን ያለንበት ስርዓት ልዩነትን እያፈካ አንድነትን ያኮሰሰ ነው። ይህ ትርክት ኣደገኛ ነው። ባለፈው ጊዜ በኢትዮጵያ ትቅደም! ስም የብሄሮች ማንነት

ተደፈጠጠ። በአሁኑ ጊዜ በብሄር ይቅደም! ስም ኢትዮጵያዊነት በብሄር ክንድ ተደፈጠጠ፣ ፈራሽ ሆኖ ተዋቀረ። በደርግ ጊዜ ብሄር ፈራሽ ሊሆን ይችላል እንጂ ኢትዮጵያ ኣትነካም የሚል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግም ተቃራኒው መጣ። እነዚህ ሁለቱም ትምህርቶች ከብዙህነት (pluralism) ጋር የተጋጩ ናቸው። ብዙህነት ልዩነትንና ኣንድነትን በአንድ ጊዜና ቦታ ማኖር የሚያስችል ሳይንስ ነው። ብዙህነት

ማንነቶችን ውድድር ውስጥ ሳያስገባ ማስተናገድ የሚችል ነው። አንድ ዜጋ ከሃይማኖትህ ማንነት እና ከሃገርህ የቱ ይበልጥብሃል? ተብሎ መፈተን ወይም መጠየቅ የለበትም። ሁለቱንም ወዶ መኖር ይችላል። ዋናው ጉዳይ ግን ለሃይማኖቱና ለፖለቲካው የተለያዩ መስመሮችን ማበጀት ነው የብዝሃነት ትምሀርት የሚመክረን። የብሄር ማንነትና የብሄራዊ ማንነት ጉዳይም እንደዚሁ ነው። ማበላለጥ ሳይሆን ሁለቱንም ሳይፈራረሱ መጠበቅ ነው ብዝሃነት ትምህርት የሚያስተምረን። የሃገራችን ፖለቲካ መሰረታዊ ችግር እዚህ ጋር ነው።

1. ሳቢ ህግ (pulling force)

በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ ያለው ሳቢ ህግ (pulling force) ማንነት በመሆኑ ሌሎች ማንነቶችን የሚገፋ ሃይል አምርቶብናል። ይሄ መሰረታዊ ችግር ነው። ስርዓቱ ሲዋቀር እንዲሳሳቡ የተፈለገው ተመሳሳይ ማንነቶች በመሆናቸው ልዩነትንና ኣንድነትን በኣንድ ጊዜና ቦታ ማኖር የሚያስችል ስርዓት እንዳንገነባ ተግዳሮት ሆኖብናል። ተመሳሳይ ማንነቶች ሲሳሳቡ ልዩ የሆነውን ማንነት የሚገፋ ሃይል ሳናውቀው ኣምርተን ቁጭ ኣልን። በአንድ የፖለቲካ ዩኒት ውስጥ ልዩነቶች በሰላም መኖር አልቻሉም። ዛሬ በሚሊዩን የሚቆጠር ዜጋ የሚፈናቀለው የዚህ የመሳሳብ ህግ የፈጠረው ኣላስፈላጊ ሌላ ገፊ ሃይል ስላመጣብን ነው ::

1. የኔሽን ግንባታ

የኔሽን ግንባታ ስራችን ተጓቷል። የተበታተነ ኔሽን ሆነን ኣንድ ሃገር ለመመስረት ኣንችልም። የምንከተለው የፖለቲካ ትርክትና ስርዓት ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ የማይመች ነው። አንድ ሆነን ብዙ ደግሞ ብዙ ሆነን አንድ መሆን የምንችለው ቡድኖች ለሃገር የሚሆኑ መስዋእቶችን ኣጭደን ሳንበላ ስንቀርና ለብሄራዊ ማንነት መስሪያ የሚሆነውን ዋልታና

ማገር ምሰሶ አዋጥተን ስንሰራ ነው። አንድ ነን የሚያሰኘን የሆነ አንድ የሚያደርገን ዋና ጉዳይ ሲኖር ነውና ለዚህ ለብሄራዊ ማንነት ሁላችን መዋጮውን ማዋጣት አለብን።

1. ምርጫ

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚኖረው የሃሳብ ትግል ባለበት ሃገር ነው። መድብለ ፓርቲ ስርዓት ማለት ሜዳው ተስተካክሎ፣ ዳኛና ታዛቢ ባለበት ህዝብ ፈራጅ ሆኖ ፓርቲዎች በሃሳብ የሚታገሉበት ጨዋታ ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ መሰረታዊ ጉዳዮች በብሄራዊ መግባባት የሚፈቱ ናቸው። መጀመሪያ ብሄራዊ መግባባት (national concensus) ያስፈልጋል። በሆነ የጋራ ማንነት ስር ነው ምርጫ የሚኖረው። ግማሹ በብሄር ግማሹ በበብሄራዊ ኣንድነት ግማሹ በመልክዓምድር ተሰልፎ የምርጫ ድግስ የለም። ዴሞክራሲ መደላድል ይጠይቃል። የሆነ የጋራ ማንነት ሳይኖር ዴሞክራሲ የለም። ዴሞክራሲ በአንድ የሆነ ማንነት ስር ያደሩ ዜጎችን የሚያስተዳድር ስርዓት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሆኑ ስር ነቀል ልዩነቶችን ይዘን ምርጫ መግባት ወደ ዴሞክራሲ ኣያሻግረንም። ለዚህ ነው በሽግግሩ ሰዓት ኪዳን ያስፈልጋል የምላችሁ። የጋራ የሆነ መነሻ ይዘን ከዚያ በሁዋላ በፖሊሲ ተያይዘን መከራከር እንችላለን። በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምርጫ ሮጠው አንዱ አንዱን እያሸነፈ ስልጣን ቢቀያየሩም የመጠፋፋት እድል ግን የለም። እርስ በርስ አይጠፋፉም። የሃገራችን ፖለቲካ ከምርጫው በሁዋላ መጠፋፋት አለበት። ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ ኣሸንፎ ስልጣን ቢይዝ የፖለቲካ መስመሩና የፌደራል ስርዓቱ የተለየ ስለሆነ በዘውግ ላይ የቆሙትን ፓርቲዎች ያጠፋል። በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካውን ተግባራዊ ሲያደርግ እነዚህን የብሄር ድርጅቶች ያጠፋል።

የብሄር ድርጅቶች ደግሞ ይህን ያንድነቱን ፓርቲ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍል ሳይቆጣ እንዲኖር ለማድረግ መደራጀታቸውን ኣይከልክሉ እንጂ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ኣይሹም። እንዲህ ዓይነት ስርነቀል ለውጥ የያዙ ሃይላት ወደ ምርጫ ሳይሆን መጀመሪያ መሄድ ያለባቸው ወደ ብሄራዊ መግባባት ነው። የሆኑ ዋና ዋና ጉዳይ ላይ ቃል ኪዳን ገብቶ ነው ምርጫ መግባት የሚቻለው።
ኣሰላለፍን ማሳመር ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ማድረግ የአንዱን በሬ ፊት ወዲህ የሌላውን በሬ ፊት ወዲያ ኣድርጎ እርሻ እንደመጀመር ይቆጠራል።

9. የሃብት ዝውውር

በኢትዮጵያ ውስጥ በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ የተነሳው የመሬት ላራሹ ጥያቄ ታሪካዊና ፍትሃዊ ነበር። ይሁን እንጂ ሃገራችን ይህንን ጥያቄ እስካሁን በተገቢው መንገድ ባለመመለሷ ለተለያዩ ችግሮች ኣንድም በቀጥታ ኣለያም ለችግሮቹ ገባር በመሆን እየጎዳን ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ ስለሃብት ዝውውር ስናነሳ መሬት ነው ትልቁ ሃብትና ይህንን ሃብት የያዝነብት ፖሊሲ መጠናት ኣለበት። የሃብት ዝውውራችን ጉዞ የሚያሳየው መሬት ኣንዴ በፊውዳል፣ ቀጥሎ በመንግስት ፣ ቀጥሎ በብሄሮች አካባቢ ነው
የተዘዋወረው። በተለይ በአሁኑ ሰዓት ስቴቶች የመሬት ባለቤት በመሆናቸው የመጣ የወሰንና የድንበር ጥያቄ ኣለ። ከዚህ በላይ የዜጎች መሰረታዊ መብት ኣልተከበረም። ዋና ዋና የምንላቸው ችግሮች ከፍ ሲል ያነሳናቸው ሲሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚከተለው መፍትሄ ይጠቅማል።

የመፍትሄ ኣሳብ

1. አዲስ ሃገራዊ ኪዳን መግባት
ሃገራዊ ኪዳን ማለት ህገ-መንግስት ማለቴ ኣይደለም። ሽግግራችን እጅግ ያማረ እንዲሆን ህዝቡን መሰረት ያደረገ ቃል ኪዳን ውስጥ መግባት የሽግ ግራችን የመጀመሪያ ደረጃ ቢሆን መልካም ነው። ይህ ቃል ኪዳን የምለው ጉዳይ በይዘቱና በአገላለጹ የኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳን (covenant) ነው። በውስጡ ሊይዛቸው ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል:-
1. ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሄር በታች የማትከፋፈል ኣንድ ህዝብ ነን የሚል
2. ተደምረን ለመኖር፣ ብዝሃነትን ለማክበር እርስ በርስ ለመረዳዳትና ለሰላም መቆማችንን የሚገልጽ
3. ኢትዮጵያውያን ለተገፉ ሁሉ የምንቆም መሆናችንን የሚገልጽ
4. ያለንን ሃብት የኔ የኔ ሳንል የእኛ ብለን ለመኖር ቃል መግባታችንን የሚገልጽ
5. ኢንተርጀነሬሽናል የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ኣጠቃቀምን በሚመለከት
6. ለዓለም ሰላምና ልማት መቆማችንን የሚገልጽ
7. የሪፐብሊክ ሃገር መመስረታችንን የሚገልጽ
8. እሴቶቻችንን ኣክብረን የምንኖር ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የምናከብር መሆናችንን የሚገልጽ ቃል ኪዳን ያስፈልገናል።

ይህ ቃል ኪዳን በህዝቡ ከተፈረመ በሁዋላ ለትውልድ የምናሻግረው ዶግማዊ ኪዳን ይሆናል። ሃገር የሚባለው ጠገግ የሚቆመው በዶግማና ቀኖና ነው። ሃገር ራሱ ዶግማ ሲሆን በየግዜው የምናሻሽለው ህግና ኣሰራር ደግሞ ይኖረናል። የሚነካና የማይነካ ቃል ነው ሃገርን የሚመሰርተው። ስለዚህ ዶግማዎቹን ኣውጥተን ከላይ ማስቀመጥ ሽግግራችንን በጣም ያሳምረዋል። ለወደፊት የረጋ ሃገር ይኖረናል። ይህ ኪዳን ፖለቲካዊ ሳይሆን ማህበራዊ ይሆንና የሃገራችን ዶግማዊ ዶክመንት ይሆናል።
ዶግማዊ ቃል ኪዳን ያስፈልገናል የሚያሰኘን በሚከተሉት ጉዳዮች ነው
1. ለኔሽን ቢዩልዲንግ መሰረት ስለሚሆን ነው። ኔሽን ሊገነባ የሚችለው በዚህ ቃል ላይ ነው።
2. ለሲነርጂ ወይም መደመር። ተደምረን ለመኖር መደመር የሚያመጣውን የላቀ እሴት (greater value) ለመጠቀም ይህ ቃል ኪዳን ኣሳሪ ይሆናል
3. በህገ-መንግስት የማይገለጹ የሞራል፣ የህብረተሰብ መተሳሰሪያ ገመዶችን ኣንጥሮ ኣውጥቶ በቃለ መሃላ ለማጽናት። እንዋደድ፣ እንረዳዳ እንተማመን የሚሉትን ዋና ዋና የህብረተሰብ መተሳሰሪያ መረቦች በህገ መንግስት ኣንገልጻቸውም። እነዚህ ማህበራዊ ሃብቶች ከምንም በላይ ለህዝብ ትስስር መሰረት ናቸውና ይህንን ለመግለጽ ይጠቅመናል። ማበራዊ ሃብት(social capital) ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ
በህገ መንግስት ኣይገለጽም። በዚህ ኪዳን ላይ ግን በመሃላ መልክ መግለጽ ይቻላል።
4. የማይነበብ የህዝብን ዶግማዊ ኪዳንን (hiden covenant) ለመግለጽ። ዶግማዊ ኪዳናችንን ኣውጥተን መግለጻችን ኣንድነትን ያጠነክራል።

5. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የመቀራመት ኣዝማሚያ ስለነበረ ይህንን ለመለወጥ ይህ ኪዳን ያስፈልጋል።
6. አርበኛ ዜጎችን ለማፍራት። ሃገር ወዳድ ዜጎችን ለማፍራት።
(covenant patriotism) 7. ለብሄራዊ መግባባት
8. መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ይህ ኪዳን ለራእያቸው መነሻ የተጻፈ ሰነድ ይሆንላቸዋል።
9. ሃውልት ኣድርገን እናስቀምጣለን። ተተኪው ትውልድ ይጠብቃል።
10. የሃገርና የህዝብ ልእልናን ከፍ ኣድርጎ ለማሳየት
በነዚህ በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ይህ ኪዳን ይረዳናልና በሽግግር ወቅት ይህ ነገር ቢታሰብ መልካም ነው።

2. ሄራን ማሻሻል

(ሄራ የምለው ህገ-መንግስት የሚለው ቃል በሚገባ ገላጭ ስላልሆነ ነው በዚህ አገባብ ሄራ ማለት ህገ-መንግስት ወይም(constitution) ማለት ነው።)
ሄራችን እንደ ሰነድ የሚሻሻል ዶክመንት ይሆናል። ትልቁ ቀኖናችን ይሆናል። ይህ ሄራ ሲዘጋጅ የሪፐብሊክን ጽንሰ ሃሳብ የሚገልጽ፣ ለቡድንና ለግል መብት
የሚጨነቅ፣ ማንነትን የማያፈራክስ፣ የኢትዮጵያን ዳርድንበር የሚገልጽ፣ ለገጸ በረከቶቿ እውቅና የሚሰጥ፣ ዘመናዊ የሆነ ሄራ ያስፈልገናል። በተጨማሪ ሄራችን ለህዝቡ ሃገራዊ ቃል ኪዳን ክብርና ልእልና የሚሰጥ ይሆናል። ሄራችን መሰረታዊ ህግ ይሆነናል።

1. የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት

የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት (Two wing Federalism) ማለት ምን ማለት ነው?
ሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ማለት የብሄር የባህል ፌደራል ስቴትና የዜጎች ፌደራል ስቴት በአንድ ጊዜ መመስረት ማለት ነው። ይህ ሲስተም ቡድኖችን ከአሲምሌሽንም ያወጣቸዋል። ሁለቱ ስቴቶች የሚመሰረቱት በህገ መንግስት ሲሆን የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስቴት የሚመሰረተው ከሁሉም ባህላዊ ማንነቶች በባህላቸው መሰረት ተውጣጥተው የሚመሰርቱት የአርበኞች ቤት ነው። ይህ ቤት በስሩ የባህልን ጉዳይ፣ የሰላምና እርቅ ጉዳይ፣ የሙዚየም ጉዳይ፣ የኬር ቴከር ጉዳይን ይመራል። ቡድኖች ሁሉ ባህላቸውን እንዲጠብቁ ስቴቶችን ይፈጥራል። እነዚህ ስቴቶች ከቦታ ውጭ ይሆናሉ። ምን ማለት ነው? በመሬት ላይ የሚሰመር ግዛት ሳይሆን የሚኖራቸው የዚያ ብሄር ቡድን ባሉበት ቦታ ሁሉ ባህላዊ መንግስቱ ገዢ ይሆናል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዜጎች የፌደራል ስርዓት ግንባታ ነው። ይህ የፌደራል ስቴት በመሬት ላይ የሚነበብ ካርታ ይኖረዋል። ለአስተዳደር ኣመቺነት፣ ቋንቋ ወዘተ ታሳቢ ኣድርጎ የሚመሰረት ዘመናዊ የፌደራል ስቴት ይሆናል። እነዚህን ስቴቶች ካንቶን ብለን ልንሰይማቸው ይቻላል። ልክ እንደ ስዊዘር ላንድ የተለያዩ ካንቶኖችን መፍጠርና የፌደራል ስርዓቱን ማቋቋም ይቻላል። ይህ የፌደራል ስቴት የፖለቲካ፣ የልማት የኢኮኖሚ የትምህርት ጉዳዮቻችንን የምናካሂድበት ሲሆን የብሄር ፌደራል ስቴቶቹ ደግሞ ከፍ ሲል ያነሳናቸውን ስራዎች ይሰራሉ። ይህን በማድረግ በአንድ በኩል የባህል ኢእኩልነትን እያጠፋን እኩልነትን እያመጣን በሌላ በኩል ደግሞ ለጋራው ቤታችን በጋራ በመስራት ኣገራችንን ኢትዮጵያን ከድህነት በማላቀቅ የዜጎችን ህይወት እናሻሽላለን።

ለምን ሁትዮሽ የፌደራል ስርዓት ኣስፈለገን?
1. ብዙህ ስለሆንን ብዙህነትን ለማስተናገድ በጣም የተሻለ ሲስተም ስለሆነ
2. ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ማንነትን ለይቶ ምርታማነትን ለማምጣት
3. በብሄራዊ ማንነትና በብሄር ማንነቶች መካከል ያለውን ግጭት ለመቅረፍ
4. ሃገርን በሁለት ጠንካራ ምሶሶ ለማቆም
5. የጠፉ ባህሎቻችንን ለማስመለስ፣ የተበጠሱ አኩሪ ታሪኮችን ለመቀጠል
6. የፍትህን ገበታ ለማስፋት
7. የተለያዩ እድሎችን ለማስፋት፣ብዙ በሮችን ለመክፈት፣ ለፈጠራ ስራ፣ ያለንን ማህበራዊ ሃብት ወደ ኢኮኖሚ ሃብት ለመቀየር
8. የዜግነት ፖለቲካንና የብሄር ፖለቲካን ለማስታረቅ
9. የብሄሮችን ጥያቄ ለመመለስ
10. እሴቶቻችንን ለመጠበቅ ይረዳናል።
በነዚህና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች የሁለትዮሽ የፌደራል ስቴት ግንባታው ኣስታራቂ ሃሳብ ነው። በተለይም ደግሞ በቡድን መብትና በግለሰብ መብት ለተራራቀው ፖለቲካችን ይህ ሲስተም መካከለኛና ሁሉን ኣስታራቂ ሲስተም ነው። ሃገራችንን ሳናጣ በሌላ በኩል ብሄራዊ ማንነታችንን ሳናጣ ኣብረን መኖር እንድንችል የሚያደርግ ስርዓት ነው። በአጠቃላይ የሁለትዮሽ ወይም ባለሁለት ክንፍ የፌደራል ስርዓት ማለት የፌደራል ስርዓትን በኢትዮጵያ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚያስችል የፌደራል ስርዓት ማለት ነው። ኢትዮጵያዊ ፌደራሊዝም ማለት ነው። የፈደራል ስርዓት ለባህል ማንነት ብዙ የሚጨነቅ ባለመሆኑ በኛ ሁኔታ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል የፌደራል ስርዓት ለማምጣት ታስቦ ነው። ሃገር በቀል ፌደራሊዝም ነው። ብዝሃ ፌደራሊዝም ማለት ነው።

4. ቋንቋ
ስርዓታዊ ለውጥ ስንል ቋንቋንም ይመለከታል። ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን የማንነት መግለጫ ነውና እጥፍ ድርብ ክብርና ጥንቃቄ ይሻል። የሰው ልጅ በቋንቋው የመናገር በቋንቋው የማሰብ ሙሉ ነጻነት ኣለው። የራሱ ቋንቋ ያለው ኣንድ ማህበረሰብ ሃገር ሲመሰርት ከነቋንቋው ተከብሮ ሊኖርበት ይገባል። በቁጥሩ በማነሱ ቋንቋው ኣይነካበትም። ስለዚህ የቋንቋ ኣጠቃቀማችንን ማስተካከል ኣንዱ የሽግግር ዋና ሃሳብ ነው። በዚህ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በሚከተለው መንገድ የቋንቋ ህጓን ልታሻሽል ይገባል
1. ብሄራዊ ቋንቋ።
የብሄራዊ ቋንቋነት ታይትል ሁሉም ብሄሮች ሊጎናጸፉ ይገባል። የሁሉም ቋንቋዎች ዝርዝር በህገ-መንግስት መቀመጥ ኣለበት። እነዚህ ቋንቋዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሃብት ናቸው ስንል የብሄራዊነት ደረጃን እናጎናጽፍ።
2. ኦፊሺያል ቋንቋ
የኢትዮጵያን ቋንቋዎች በሙሉ በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ኦፊሺያል እናድርግ። ዜጎች በማዘግጃ ቤት ኣካባቢ በቋንቋቸው ይገልገሉ።
3. የህብረት ቋንቋ ይኑረን
ይህ ቋንቋ የፌደራል ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ታች ድረስ በአራቱም ኣቅጣጫ አገልግሎት ላይ ይዋል። ይህ ቋንቋ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ወደ ጎን የሚያገናኝ ቋንቋም ይሆናል። የፌደራሉን የህብረት ቋንቋ ከአንድ በላይ ማድረግ ይቻላል።

4. እንግሊዘኛ
ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ትገናኝ ዘንድ የተሻለ ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት እንግሊዘኛን ጠንክረን እናስተምር በቋንቋ ዙሪያ እነዚህን ማሻሻያዎች ካደረግን በአግልግሎቱም በማንነት መገለጫውም ቦታውን ያገኛል። የዜጎች በቋንቋ የመጠቀም መብት ይከበራል። ቋንቋዎች ያድጋሉ።

5. የሃብት አያያዝ መሬት ለአራሹ

ኢትዮጵያ ሃገራችን ብዝሃነትን በማስተናገድ በኩል ችግሮች እንዳሉባት ሁሉ በሃብት ዝውውር ጉዳይም ከፍተኛ ችግር ኣለብን። በሃገራችን ሁኔታ ሃብት ስንል ዋናው ሃብት መሬት ነው። ኣብዛኛው ህዝብ ገበሬ ነው፣ ኢኮኖሚያችንም በዚህ ላይ የተመሰረተ ነውና። በኣስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ የመሬት ላራሹ ጥያቄ መነሳቱ ልክ ነበር። ያ ጥያቄ የተመለሰበት ኣግባብ ግን
ችግር ነበረው። ደርግ የሃገሪቱን ሃብት ከፊውዳሎች ቀማና ለአብየታዊ መንግስት ኣደረገው። ገበሬው በገመድ ኣንዳንድ ጥማድ ስለደረሰው የተሻለ ለውጥ መሰለንና ተደስተን ይሆናል እንጂ ለውጡ ግማሽ መንገድ ሄዶ ነው የቀረው። ሁለተኛውን የሃብት ዝውውር ስናይ (ከመሬት ሃብት ኣንጻር) የአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ ሃብት ወደ ቡድኖች ዞሯል። ተመልከቱ፣ መጀመሪያ መሬት በፊውዳሉ እጅ ነበር ሲቀጥል ወደ መንግስት ተዛወረ ቀጥሎ ደግሞ የህዝብና የመንግስት በሚል ሽፋን የቡድኖች ሆነ። እነዚህ የሃብት ዝውውሮች የየራሳቸው ማነቆ ኣላቸው። በተለይ መሬት የቡድን ሲሆን የመጣው ጉልህ ችግር በቡድኖች መካከል የይገባኛል ጥያቄን
የወሰን ጥያቄን ነው። ይህ ችግር የሚፈታው የሃብት ዝውውርን በማሻሽል ነው። ይህ ዝውውር ደግሞ ከፍ ሲል ባነሳነው የኢትዮጵያውያን ኪዳን መሰረት መሬት በሚከተሉት ይዞታዎች ስር እንዲሆን ስንስማማ ነው።

1. በግል
የመሬት ባለቤትነትን ዜጎች ሊጎናጸፉ ይገባል።
2. በኮሙኒቲ ።
የእምነት ተቋማት፣ ወይም የግጦሽ መሬት፣ ወይም የባህል መከወኛ ቦታዎች በቡድን ሊያዙ ይገባል
3. መንግስት ።
መንግስት በግለሰብና በኮሚኒቲ ያልተያዙትን መሬቶች፣ ደኖች፣ ታራራዎች ሰማይና ወንዞች ሊይዝ ይችላል።
ይህ ለውጥ የቡድኖችን የወሰን ጥያቄ ይፈታል። ቡድኖች በቀበሌና በኩሬ ውሃ የሚጋደሉት መሬት የቡድን የወል ሃብት ስለሆነ ነው። የመሬት ፖሊሲ ሲለወጥና መሬት የግል ሲሆን በወልቃይት ጉዳይ ኣማራና ትግራይ ኣይዋጉም። ጉጂና ቡርጂ አይጋጩም። ኦሮምያና ሶማሌዎች ኣይጋጩም ወዘተ። መሬት ለአራሹ ማለትም ይሄው ነው። መሬት ላራሹ ማለት ለብሄሩ ወይ ለመንግስት ሳይሆን ለሚሰራበትና መስራት ለፈለገ ዜጋ ሁሉ ነው። በሌላ በኩል ኣስተዳደራዊ ጉዳዮችንም ቢሆን ይህ ኪዳን ይፈታል።
ኢትዮጵያውያን ሃገር ሲመሰርቱ ከራስ ትርክት ወጥተው በእኛ ኪዳን ኣብረው ሲኖሩ ከስርዓታችን ውስጥ ራስ ወዳድ ኣስተዳደርን እናጠፋለን። ገፊ ሃይሎችን እናባርራለን።

ማጠቃለያ

ከፍ ሲል እንዳነሳነው በሃገራችን የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ማንነት ግጭትን ኣምራች የሆነ ሃይል ኣምጥቷል። ማንነት በራሱ የሚያጋጭ ስለሆነ ሳይሆን ማንነት ወደማይፈልገው ጨዋታ ውስጥ በመግባቱ ነው። ልኩ ያልሆነ ማልያ ስለለበሰ ነው። ስለዚህ ነው ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ማንነትን ነጥለን ለማካሄድ ሰርጀሪ ያስፈልጋል የምንለው። ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው እንዳልነው ሁሉ ባህልንም ከዚህ ነጥለን ኣውጥተን ነገር ግን የቡድን መብት ይጠበቅ ዘንድ ለቡድን መብት ጠገግ መስራት ይገባናል።

የዜግነት ፖለቲካ ኣራማጆች የቡድንን መብት እውቅና እንዲሰጡ በአንጻሩ ደግሞ የቡድን መብት ኣማኞች ለዜግነት መብት ክብር እንዲሰጡ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ይህ ሲስተም ያግዘናል። ብሄራዊ ማንነትና የብሄራዊ ማንነት ተጠባብቀው እንዲኖሩ ያደርጋል። ይህ ስርዓት ከሁሉ በላይ በጎ የሆነ ማህበራዊ ሃብት እንድናመርት ያደርገናል። በተለይ ባለፉት ሁለት ኣስርት ዓመታት በጣም በሚያሳስብ ሁኔታ የወረደው ማህበራዊ ሃብታችን ነው። ማህበራዊ ሃብታችን ጠፍቶ ሃብታም ብንሆንም ያንን ያለማነውን እናጠፋዋለን። ማህበራዊ ሃብት (social capital) ሃብት ነው የሚባለው ማህበረሰብ የሚያመርተውና ኢንቨስት የሚያደርገው ነገር ስለሆነ ነው። ማህበራዊ ሃብትን ለማምረት ደግሞ ዴሞክራሲ፣ ሳይንሳዊ ፖለቲካ ማራመድ ኣለብን። ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በአሁኑ ሰዓት መንግስትን ኣሳስቦት ኮሚሽን እስከማቋቋም የደረሰበትን የማንነት፣ የኣስተዳደርና ወሰን ጉዳይ ለመፍታት እንዲህ ዓይነት ሲስተም በጣም ኣዋጭ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የወሰንን ጥያቄ ለመፍታት በስቴቶች መካከል የሚደረግ የመሬት ላይ መስመር ኣይፈታውም።

በጉጂና ቡርጂ መሃል በአማራና ትግራይ መሃል በኦሮምያና ሶማሊያ መሃል በሁሉም ኣካባቢዎች የወሰን ጥያቄ የሚነሳው መሬት በብሄሮች ስለተያዘ ነው።
ስለዚህ ይህ ሞዴል ሳይሸራረፍ በስራ ላይ ከዋለ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ለውጥ ኣድርጋ ዓለምን ልታስደምም ትችላለች። ከሁሉ በላይ ደግሞ የጠፉ ባህሎቻችንን በማስመለስ ኢትዮጵያውያን ግርማና ሞገሳችንን እናስመልሳለን። የባህል ፌደራል ስቴቱ ሲቋቋም በራያና በትግራይ መካከል ግጭት ኣይኖርም። በቅማንትና ኣማራ መካከል ግጭት ኣይኖርም። በደቡብ የሚነሱ የክልል ጥያቄዎች ምላሽ ኣገኙማለት ነው። ወደፊት በነዚህ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን። ለዛሬው ግን ከፍ ሲል ያነሳሁትን ኣሳብ ጠቅልሎ የያዘውን ስእላዊ ማሳያ ቀጥሎ ይመልከቱ። ይህ ቤት የኢትዮጵያ ቤት ይሆን ዘንድ ምኞቴ ነው።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

geletawzeleke@gmail.com

የኢትዮጵያ ሮድ ማፕ

የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣሰራር

Filed in: Amharic