>

ኢኮኖሚያዊ አሻጥር...  (ውብሸት ሙላት)

ኢኮኖሚያዊ አሻጥር – አንድ!!!
ውብሸት ሙላት
ወቅቱ የብዥታ፣ የግርታ፣ የድንግርግርታ ነዉ፡፡ የጠራ፣የታወቀ፣ግልጽ የሆነ አገራዊ ግብም ፖሊሲም የለም፡፡ መዳረሻዉም ይሁን መጓዣ መንገዱ በዉል ተለይቶ አይታወቅም፡፡ በየዕለቱ የሚከሠቱ ችግሮች ከመብዛታቸዉ የተነሳ የችግሮቹን ምንጮች አቅዶ የሚፈጠሩ መዋቅራዊ ኃይሎች (የዉስጥ ወይም የዉጭ አሊያም ሁለቱም-በተናጠል ወይም በቅንጅት) አማካይነት የሚፈጠሩ መሆን አለመሆናቸዉን በአንክሮና በትኩረት ማስተዋል ግድ ነዉ፡፡
ኢትዮጵያ፣ ፈተናም መስቀለኛ መንገድም ላይ ናት፡፡ ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትሁን እንጂ፣ ፈተናና ስጋቱ ደግሞ የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ከፍ ያለ ነዉ፡፡ አማራ ላይ የተደቀነዉ ከሁሉም ከፍ ያለ ነዉ፡፡ የስጋቶቹንና የተጋረጡበትን ፈተናዎች መዘርዘር ባልፈልግም፣ በእንደዚህ ዓይነት የብዥታ ወቅት ብልጣብልጥነት የተሞላባቸዉ ሕግ፣ፖሊሲ እና አሠራር ሥራ ላይ የሚዉሉባቸዉ ስለሆነ ነቅቶ፣ዙሪያ ገባዉን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ “ጅብ ከሔደ ዉሻ ጮኸ” መሆንን ከዘመነ ሕወሃት/ኢሕአዴግም ሆነ ደርግ  መማር ግድ ነዉ፡፡
ለአሁኑ የደርግን አላነሳም፡፡ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ሥራ ላይ አዉሏቸዉ የነበሩ የተወሰኑ ፖሊሲ፣ሕግና አሠራር ዉስጥ አስር አስረጂዎችን አቀርባለሁ፤ ኢኮኖሚያዊ ሻጥርን በማንሠራፋት የተወሰነ ቡድን አለቅጥ የጠቀሙ (ለመጥቀም የታቀዱና የተተገበሩ)፣ የተወሰነ ቡድንን፣በተለይም የአማራ ሕዝብን፣አለቅጥ ለጉዳት የዳረጉ፡፡ እነዚህ አሻጥራዊ ሕግ፣ፖሊሲና አሠራር የተዘረጉት ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን የተወሰኑት በዘመነ ዉዥንብሩ (በሽግግር ጊዜ) ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ቀጥለዉ ነበር፡፡
በቅርቡ ከተፈጸሙት አሻጥሮች አንዱን ላንሳ!
ሕወሃት፣የትግራይ ተወላጆችን በገፍ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በኢንቨስትመንት ሰበብ ጋምቤላ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችም ዉስጥ እንዲታደሉ አደረገች፡፡ ብዙዎቹ ባዶ እጃቸዉን የሄዱ ናቸዉ፡፡ ባዶ እጃቸዉን ወደ እነዚህ ክልሎች ሔደዉ በመቶ እና በሺ የሚቆጠር ሔክታር መሬትን ተረከቡ፡፡
ባዶ እጃቸዉን ተመልሰዉ ልማት ባንክ ይሄዳሉ-እነዚሁ መሬት የወሰዱ ሰዎች፡፡ ልማት ባንክ ቅድሚያ ለአግሮፕሮሰሲንግ እና ግብርና የሚል ፖሊሲ አዉጥቶ ስለነበር የማስያዣዉም ጉዳይ ከወትሮዉ ተለየ፡፡ በባዶ ኪስና በባዶ እግር ሔዶ መሬት ተረክቦ፣በመቶ ሚሊዮኖችና አንዳንዱም ከቢሊዮን የሚያልፍ ገንዝብ ከልማት ባንክ ወሰዱ፡፡ ከዚያ መሬቱን ለአካባቢዉ ኗሪ እያከራዩ፣ገንዘቡን ለሌላ ቢዝነስ አዋሉት፡፡
ልማት ባንክ በዚህ መንገድ ገንዝብ ማፍሰሱን ሲቀጥል ገንዝብ አነሰዉ፤መሬት የሚታደሉት ደግሞ በዙ፡፡ እንዲጨመርም ተወሰነ፡፡ ገንዘብ ሲያጥር ሌሎቹ የንግድ ባንኮች የእያንዳንዱን ብድር ላይ 27 ከመቶ ወደ ልማት ባንክ እንዲያስገቡ የሚያሰገድድ ሕግ ወጣ፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ልማት ባንክ ገባ፡፡ ለእነ አጅሬም ልማት ባንክ ከምኞታቸዉ በላይ የሆነ ገንዘብ ጎረፈላቸዉ፡፡
የግል ባንኮችም ሌሎች ሰዎች የሚያርቡትን ብድር ቀነሰባቸዉ፡፡ ብድር ፈላጊም ገንዘብ አጣ፡፡ በዚያ ላይ ከባንክ ለመበደር የሚጠየቀው ማስያዣ እና ለምን ለምን ፕሮጀክት ብድር ማቅረብ እንዳለባቸዉ በሕግ ጥፍንግ ተደርገዉ ተያዙ፡፡
 ሕግና ፖሊሲዎች ሲወጡ ፣ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ኢኮኖሚያዊ አንድምታቸዉ ምን እንደሆነ አስቀድሞ ማስላት ይገባል፡፡ አለቆች አሁን ትኩረታችን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ነዉ፤ አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዉ ነዉ በማለት ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ጥቂት ሰዎች እጅ እንደገባ አመቻቹ፡፡ ፋብሪካዉም የለም፡፡ አግሮፕረሰሲንግ ኢንዱስትሪዉማ አይነሳ፡፡ የብድር ገንዘቡም የተበላሸ ብድር ሆነ፡፡
ብድሩ እንጂ የተበለሻዉ ገንዘቡ አልተበላሸም! ገንዘቡስ የተበዳሪዎቹ እንደሆነ ነዉ!
ይቺ አንዲት ማሳያ ናት፡፡
ኢኮኖሚያዊ አሻጥር –  ሁለት
ደርግ መሬትን በሕዝብ አደረገ፡፡ በኢሕአዴግ መሬት የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሐየረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ሆነ፡፡ ከዚያም አስተዳዳሪዉ መንግሥት ሆነ፡፡ ማለትም ስለ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሆኖ መንግሥት ያስተዳድራል በማለት በሕገ መንግሥቱ ተካተተ፡፡
ደርግ፣መሬትን የግል ቢያደርግም መሬትን ለግለሰብ መሸጥና መለወጥ ዉስጥ አልገባም፡፡ ይኼንን ሥልጣንም ለራሱ አልሰጠም፡፡ ኢሕአዴግ ግን ከደርግ በተለየ ሁኔታ መሬትን  ለተለያዩ ሰዎች፣ ከአንዱ እየነጠቀ ለሌላዉ ሰጠ፡፡
በከተሞች ዉስጥ አብዝኃኛዉ ነዋሪ ብሔሩ ምን እንደሆነ ጠንቅቆ አዉቋል፡፡ ኢኮኖሚዉን መቆጣጠር ፖለቲካዉንም መቆጣጠር ነዉ ብሎ አዉጇል፡፡ ይሄንን የተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ በግልጽ አስፍሮታል፡፡
የከተማ ቦታ የገበያ ዋጋ  በመረዳት የከተማ ቤትን በጣራና ግድግዳ ዋጋ ስሌት ሰዎች ቤታቸዉን አጡ፡፡ መርካቶ ላይ ያለን አንድ ቤት ከ40 እና 50 ዓመታት የተገነባበትን የግድግዳና ቆርቆሮ ዋጋ በመስጠት አንድ ካሬ ሜትር መሬትን ከ300000 ሺ ብር በላይ ተሸጠ፡፡ መርካቶ፣ አንድ ቤት ያለዉ ሰዉ በልማት ሰበብ ሲነሳ፣ የአንድ ካሬ ሜትር መሬት ዋጋ ያህል እንኳን ካሳ አይከፈለዉም፡፡
ባጭሩ፣ በየከተማዉ የሚኖረዉን የሕዝብ ስብጥር በማሰብ፣ መሬትን የሕዝብ ነዉ በማለት፣መንግሥት ደግሞ አስተዳዳሪ ነኝ በማለት ራሱን ሹሞ ቀድሞ ሀብትና ንብረት በተለይም ቤት የነበራቸዉ ሰዎች ያለ ቤት ቀሩ፡፡ አዳድስ ሰዎች የቤት ባለቤት ሆኑ፡፡ ብሔራዊ ስብጥሩም ተቀያየረ፡፡ አማራዎችምም (እንዲሁም ጉራጌና ስልጤ) በሰፊዉ የነበራቸዉን ቤት በጣራና ግድግዳ ዋጋ (የገበያ ሳይሆን) አጡ፡፡
እንዲሁም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በገፍ አጋበሱ፡፡ እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ፣ለዚያዉም ለ99 ዓመት በሆነ የሊዝ ሥርዓት በእጃቸዉ አስገቡ፡፡ መሬት የሌላቸዉ ባለመሬት ሆኑ፡፡
የኢትዮጵያ የመሬት ሥርዓት ፣ መሬት የሌላቸዉ ሰዎች መሬት ያላቸዉን ለመቀማት የተደረገ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ መሬት የግል የሚሆነዉ በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ነዉ መባሉም መሬት የግል ከሆነ ህወሃት እንደምትሞት ስለገባቸዉ ነዉ፡፡ የኢኮኖሚ ምንጯ መሬትን በማጋበስ፣ በነጻ በሚባል ዘዴ በመዉሰድ ነዉ፡፡
በየከተማው ማን በጣራ እና ግድግዳ ዋጋ ተነጥቆ ማን እንደተተካ፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችም ማን እንዳግበሰበሰ ማንም የሚያውቀው ሐቅ ነው። እናም የመሬት ሕጉም ሆነ ፖሊሱ ሻጥርን ያዘለ ነው። አንዱን በድሎ ሌላውን ያለመጠን ለመጥቀም። እዚህ ላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ላይ የሚኖሩ ኦሮሞዎች ላይ የደረሰውን በደልም ማንም የሚያውቀው ነው።
ኢኮኖሚያዊ አሻጥር – ሦስት!!!
ለረጅም ዘመናት ጥረዉ ግረዉ፣ላባቸዉን ጠፍ አድርገዉ ጥሪት የቋጠሩ ነጋዴዎችንና ባለሃብቶችን “ጥገኛ ባለሃብት” የሚል አሸማቃቂና አዋራጅ ስድብ ተጨምሮላቸዉ ከንግድ ሥርዓቱ እንዲወጡ ፖሊሲ ተቀርጾ ተሠርቶበታል፡፡ እነዚህ ባለሃብቶች ብሔራቸዉ ቀድሞ ስለታወቀ፣ እና ሕወሃትም የሚጠላቸዉ ስለነበር ኢሕአዴጋዊዉን አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዲሁም ወደ ኋላ ላይ ልማታዊ ዴሞክራሲ የሚባሉ ርእዮተ ዓለሞችን እንደማሳመኛ ምንክያት (justification) በመዉሰድ ቀድሞ ሃብትና ጥሪት የቋጠሩ ባለሃብቶችን ጠላት ተደርገዉ ተሳሉ፡፡
ጥገኛ ተብለዉ የተፈረጁ ባለሃብቶችንም አይደለም ድጋፍ ሊደረግላቸዉ ይቀርና ከገበያና ከንግዱ ዓለም እንዲወጡ፣እንዲከስሩ ተደረገ፡፡ በምትካቸዉ ልማታዊ የተባሉ ባለሃብቶችን ኢሕአዴግ ፈጠረ፡፡ ኢሕአዴግን የሚደገፉና ራሳቸዉ ኢሕአዴግ የሆኑ በአብዝኃኛዉ አማራ ያልሆኑ ባለሃብቶች ተፈለፈሉ፡፡
ጥገኛ ተብለዉ የተፈረጁና የኢንቨስትመንትና ንግድ አከርካሪያቸዉ የተሠበሩ ባለሃብቶች እና ልማታዊ ተብለዉ ኢሕአዴጋዊ እንክብካቤ የተደረገላቸዉን ብሎም ከአቅምና ችሎታቸዉ በላይ ሃብት ያጋበሱ ባለሃብቶችን የብሔር ዳራ ተመልከቱት! ስትፈልጉ ቁጠሯቸዉ፡፡ ይህን ለማድረግ፣ አብዮታዊም ሆነ ልማታዊ ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለምም በሉት ፖሊሲን ሰበብ ሆነዋል፡፡
 ባለሃብትን በዚህ መንገድ እንዲከፋፈል ሲደረግ የአማራም ይሁን የጉራጌና ስልጤ ተወላጅ የሆነ አመራሮችም አብረዉ ነበሩ፡፡ በሹምባሽነት/ባንዳነት አሊያም ባለማወቅ የራሳቸዉን ብሔር ተወላጆች እየተጠረጉ እንዲከስሩና ከንግድና ኢንቨስትመንት እንዲወጡ ተባብረዋል፡፡
ፖሊሲዎች ሲወጡ ማንን እንደሚጎዱ፣ማንን እንደሚጠቅሙ ትርፍና ኪሳራቸዉን እንዲሁም ማንን ሰለባ ማንን ነጻ ጋላቢ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማስላት ይገባል ለማለት ነዉ፡፡
በዚህ መንገድ የባለሃብት ንቅለተከላ  የተደረገዉ በዋናነት ኢኮኖሚዉን የተቆጣጠረ ፖለቲካዉን ይቆጣጠራል በሚል ነዉ፡፡ “Seek economic kingdom first” እንዲሉ የኩዋሜ ንኩርማህን “seek political kingdom first” የሚለዉን ገልብጠዉ መርሃቸዉ ያደረጉ ጎበዞች፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብና ከኦሮሚያ ደግሞ ሸዋ፣ አብዝኃኛው ምርቱ ጤፍ ነው። ጤፍ ያመርታል። ጤፍን ሽጦ የተለያዩ ቁሳቁሶችንና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ይሸምታል። ለመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብም ጤፍ በማቅረብ እንጀራ ያበላል።
ጤፍን ወደ ውጭ በመላክ፣ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እንዳያገኝ ቢያንስ  እ.አ.ኤ. እስከ 2016 ድረስ ለአስር ዓመታት ገደማ ፍጹም ክልከላ ተደርጎበታል።
እጅግ አድካሚ የሆነ የማምረት ሂደትን አሳልፎ የሚያኘውን ምርቱን ለልፋቱ በማይመጥን ዋጋ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ እንዲታጠር ሲወሰን ሌላ ምንም አይነት ማበረታቻና ድጋፍ እንኳን አይደረግለትም።
ሌላው እንጀራ እንዲበላ የአማራ እና የሸዋ ገበሬ በዚህ ልክ መጎዳት የለበትም። ይሄም ሌላው ሻጥር ነው።
ጤፍን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገበሬው የተሻለ ገቢ የማግኘት ዕድሉ መስፋት አለ
አሁንም ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ሲወጡና ሲተገበሩ በቅጡ አጢኗቸው!
Filed in: Amharic