>

አንድ ክልል ሌላ ላይ ጦርነት ካወጀ፣ ታጣቂዎችን የሚደግፍ ከሆነ የፌደራል መንግሥቱ ሥልጣንና ግዴታ…..


አንድ ክልል ሌላ ላይ ጦርነት ካወጀ፣ ታጣቂዎችን የሚደግፍ ከሆነ የፌደራል መንግሥቱ ሥልጣንና ግዴታ…
..
ውብሸት ሙላት
በኢትዮጵያ፣የፌደራሉ መንግሥት ወደ ክልል በመግባት የክልል መንግሥትን ሥራ ሊሠራ የሚችልባቸውን ምክንያቶች እና አገባቡንም በሚመለከት በሕገ መንግሥቱ ላይ ሠፍሮ እናገኘዋለን፡፡ በአራት አኳኋን ወደ ክልል ሊገባ እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ከክልል መንግሥታት የመቆጣጠር አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መድፍረስ ሲያጋጥም በክልል መስተዳድር  ጠያቂነት በጠቅላይ ሚኒስትር ትእዛዝ፤
በክልል ውስጥ በሚፈጸም የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሲያጋጥም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አነሳሽነት በፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመሆን ለፌደራል መንግሥቱ እና ለክልሉ ምክር ቤት በሚሰጥ መመሪያ፤
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በክልል ውስጥ ሲከሠት በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ፤
ክልሎች በሚያስተዳድሯቸው ወሰን ውስጥ በፌደራል መንግሥት ማለትም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ሊገባ ይችላል፡፡
ከላይ የአንድ እስከ አራት በተቀመጠው መሠረት የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ከሚገባባቸው ሁኔታዎች መካከል አንዱ ክልል ሌላ ክልል ላይ ጦርነት ካወጀ፣ወይም ድጋፍ የሚያደርግላቸዉ ቡድኖች በሚነሩበት ጊዜ ወደ ክልል የሚገባዉ በሦስተኛዉ አማራጭ ስለሆነ እሱን እንመልከት፡፡
በዚህ መንገድ ለመግባት በክልሉ የተፈጸመው ወይም በመፈጸም ላይ ያለው ድርጊት ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጭ የሚፈጸሙ ተግባራት በመኖራቸው ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ሥርዓት አደጋ ላይ የጣሉ ሲሆኑ ነው፡፡
ክልላዊ መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ከጣሉ፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመፍረስ ለመታደግ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልሉ በመግባት ሁኔታዎችን እንዲያስተካክል ሊወሰን ይችላል፡፡ ይሄ ዓይነቱን አሠራር ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 62 (9) ላይ በመፍትሔነት አስቀምጦታል፡፡
ከሕገ መንግሥቱ ባለፈም የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው፣ከላይ በገለጽነው፣በአዋጅ ቁጥር 359/1995 ከአንቀጽ አስራ ሁለት ጀምሮ እስከ አስራ ሰባት ድረስ የሚዘልቁ ዝርዝር ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በእነዚህ አንቀጾች የተካተቱት ነጥቦች በርከት ያሉ ስለሆኑ አንኳር አንኳር የሆኑትን ብቻ እንመለከት፡፡
የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ክልሉ በራሱ ተሳትፎ ወይም በሚያውቀው ድርጊት ሕገ መንግሥቱን ባለማክበር በትጥቅ የተደገፈ አመጽ እየተደረገ ከሆነ፣ክልሉ ከሌሎች ብሔሮች ወይም ክልሎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ሰላማዊ መፍትሔ ካላገኘ፣የፌደራሉን መንግሥት ሰላምና ፀጥታ የሚያናጋ ድርጊት ውስጥ ከተሰማራ ወይም ደግሞ የሰብኣዊ መብት ጥሰት በመፈጸሙ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት የሰጡትን መመሪየ እያከበረ ካልሆነ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለ ይቆጠራል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የጣሉትን ሁኔታዎች መከሠታቸውን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች (ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ከሚኒስትሮች ምከር ቤት ወዘተ..) ሊሰበስብ  እንደሚችል  በሕጉ ተገልጿል፡፡
በተለይ ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ፋንታ ችግር የተፈጠረበትን ክልል ሁኔታ ለፌደሬሽን ምክር ቤት በማቅረብ አስወስኖ ጣልቃ በመግባት የአገሪቱ ኅልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመታደግ ሊገባ ይችላል፡፡ ማለትም፣የፌደሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን መርመሮ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል እንዲገባ ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡
የፌደራል መንግሥቱ ችግሩ ወደ ተፈጠረበት ክልል በመግባት የተፈጠረውን አደጋ የማስወገድ ተግባር ያከናውናል፡፡ ይህንን ለማድረግም የፌደሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ሊሰጥ፣ክልሉንም ሊነፍግ ይችላል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት የመከላከያ ሠራዊት እና/ወይም የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ በመግባት የተፈጠረውን ችግር እንዲያስቆሙ ሊያዝ ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈም፣የክልሉን ሕግ አውጪም ይሁን ሕግ አስፈጻሚ እንዲበተን ወይም እንዲታገድ  የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ችግር ፈጣሪዎችን ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ማቅረብ፣ሕጋዊ አሠራር ድጋሚ እንዲሰፍን ማድረግ ተግባርም ይወጣ ዘንድ ግዴታ ሊጣልበት ይችላል፡፡ የፌደራል መንግሥቱም የክልሉን አስተዳደር አፍርሶት ከሆነ ከእንደገና ምርጫ እስኪከናወን ድረስ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ያደርጋል፡፡ የክልሉ ከፍተኛው የሕግ አስፈጻሚ ተቋም ሊያደርግ የሚችለውን ሁሉ የማከናወን ሥልጣን አለው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ይህንን ለማከናወን ሁለት ዓመት ጊዜ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማከናወን ይችል ዘንድ ጣልቃ ለገባው ለፌደራል  መንግሥቱ፣ ለስድስት ወራት ያህል ለማራዘም ፌደሬሽን ምክር ቤት ይችላል፡፡
ስለክልሉ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየሦስት ወሩ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል፡፡ የክልሉን ሕዝብ ጨምሮ ለሌላው መረጃ በየጊዜው የመሥጠት ኃላፊነት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ተጥሎበታል፡፡
በዚህ መልኩ ወደ ክልል በመግባት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመታደግ የሚፈጀውም ጊዜ እንዲሁ ሊረዝም ይችላል።
ካሁን በፊት የፌደራል መንግሥቱ በዚህ መንገድ ጋምቤላ ክልል ገብቶ ነበር፤ (በ1995 ዓ.ም.?)
የፌደሬሽን ምክር ቤት በዚህ አኳኋን ካልወሰነ የፌደራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለዉ ክልላዊ መንግሥት ላይ አስቸኳይ ጌዜ አዋጅ ማወጅ ይችላል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ እና ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሠት በአንቀጽ 77(10) እና 93 መሠረት የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲፈጸምና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት የሚስተካከል በማይሆንበት ጊዜ የፌደራል መንግሥት  ቦታውንና ጊዜውን ወስኖ ወደ ክልል ሊገባ ይችላል፡፡ እንዲገባ መጀመሪያ ላይ የሚወስነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን ውሳኔውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡
አንድ ክልል ሌላ ክልልን ለመዉረር፣ ወይም ግጭት ለመፍጠር እንቅሳቃሴ እያደረገ ከሆነ (ማለትም ዝግጅት፣ሙከራም ወይም ትንኮሳም፣ ግልጽና ቅርብ ድርጊት /clear and present dangerous activities/ እየፈጸመ ከሆነ የፌደራል መንግሥት በፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ጦር መስበቅ የጀመሩ ክልሎች ዉስጥ ጣልቃ በመግባት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ መታደግ ግዴታ አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እየተከሠቱ መሆናቸዉን እያወቀ የፌደራል መንግሥቱ ዝምታን ከመረጠ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እየጠበቀ አይደለም ብቻ ሳይሆን ነገር አለ ማለት ነዉ፡፡ ነገሩ ምን ማለት እንደሁ እንደሁኔታዉና እንደፖለቲካዊ ንፋሱ መተንተን እና የተለያዩ አማራጮችን ማዘጋጀት ነዉ፡፡
Filed in: Amharic