>

ውሱን የአገር ሀብትን የማባከን አንዱ መገለጫ (ከይኄይስ እውነቱ)

ውሱን የአገር ሀብትን የማባከን አንዱ መገለጫ

ከይኄይስ እውነቱ

 

ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ የሚያሳስቡን አገራዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በዐበይትነት የምናያቸው የሰላምና ፀጥታ እጦት÷ በዚህም የአገር ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ፤ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍላተ ሀገራት የዜጎች ከአካባቢያቸው መፈናቀል መቀጠልና በዚህም ለዘመናት የለፉበት ቤት ንብረት ‹በወር ተረኞች› (ተረፈ ወያኔዎች) መውደምና የኑሮ ዋስትና ማጣት፤ አዲስ አበባን እና ድሬደዋን የግጭት ቀጣና ለማድረግ በገዢው ኦሕዴድና በአክራሪ ጎሠኞች ጥምረት የታቀደና የተቀናጀ የሚመስል እንቅስቃሴ ሥር እየሰደደ መምጣት፤በወያኔ ሕወሓት ምትክ በአዲስ ገዥኘነት የተሰየመው ወያኔ ኦሕዴድ ወያኔ ትግሬ በተጓዘበት ተመሳሳይ መንገድ የመሄድ አደገኛ አዝማሚያ፤ አሁንም መንግሥት እና ገዢ የፖለቲካ ‹ፓርቲ› መካከል ያለው ልዩነት አደናጋሪ መሆን፤ ሕዝብን በቃላት እየሸነገሉ ከጀርባ የለየለት ጎሠኝነትን/መንደርተኝነትን ማራመድ፤ ጅምር ‹ለውጡ› ወደ ቢሮክራሲውና ወደ ታችኛው የአስተዳደር ዕርከን ሳይወርድ በጅምር የመቅረት አዝማሚያ ማሳየት፤ በሰውነት÷ አለፍ ሲልም በኢትዮጵያዊነት ተጀምሮ ወደ መንደርተኝነት መውረድና መዋረድ በዚህም በዚህም ብዙዎች ተስፋ ያደረጉት ጅምር ወደ ቀቢፀ-ተስፋነት እየተለመወጠ መምጣት ወዘተ. ናቸው፡፡
በዛሬው አጠር ያለ አስተያየቴ ማንሳት የምፈልገው ርእሰ ጉዳይ ባንፃራዊነት አንገብጋቢ ባይመስልም ከአንኳር ጉዳዮቹ ጋር ተያያዥነት ያለውና ትኩረት የሚሻ መሆኑ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይኸውም ባንድ የ‹ፌዴራሉ› መንግሥት ተቋም ያስተዋልኩትን ተሐዝቦት ለሕዝብ በማጋራት ሌሎችም የራሳቸውን ፍተሻ እንዲያደርጉ መልእከት ለማስተላፍ የታሰበ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በበጀት የሚተዳደሩ የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች (ሚኒስቴር መ/ቤቶችን ጨምሮ) መዋቅራቸው፣ አቋማቸው፣ ቊጥራቸው፣ ተጠሪነታቸው፣ ስያሜአቸው፣ ወዘተ እንዳስፈላጊነቱ ጥናትን መሠረት አድርጎ ከጊዜ ወደጊዜ ሊሻሻል ይችላል፡፡ በተቃራኒው ያለ ጥናት፣ ያለ በቂ አመክንዮ፣ በፖለቲካ ውሳኔ ወይም የአንድ ፖለቲካ ቡድንን ዓላማ ለማስፈጸም ተብሎ፣ አንዳንዴም ተሰሚነት ባለው ግለሰብ ባለሥልጣን ተጽእኖ በግብታዊነት የመንግሥት መ/ቤቶችን ማፍረስና አዳዲሶችን ማወቀር እንደ ኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በሌለበት እና የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት በሌለበት አገር ገዢዎች በቃዡ ቊጥር የሚስተዋል ክስተት ነው፡፡ በተለይም በደርግና በወያኔ አገዛዞች በሚገርም ድግግሞሽ እንዲህ ዓይነቱን አገራዊ ሀብት ማባካንን በእጅጉ ታዝበናል፡፡ አንዳንዴም ለገዢዎች ታማኝ የሆኑ ሎሌዎች/ባለሟሎችን ለማስደሰት ኮሚቴዎች መ/ቤት ሆነው እንዲቋቋሙ የተደረገበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡

ዛሬ እንደ አብነት ላነሳ የፈለግኹት ስለ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መ/ቤት ነው፡፡ ይህ መ/ቤት ባለፉት 27 ዓመታት የስም ተፋልሶዎች ገጥመውታል፡፡ ጽ/ቤት፣ ባለሥልጣን፣ ኮሚሽን፣ ኤጀንሲ፣ እንደገና በቅርቡ ኮሚሽን ተብሏል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ማንሳት ያሰብኹት መሠረታው ችግር የስያሜው ጉዳይ አይደለም፡፡ ለኮሚሽኑ መ/ቤት ሦስት ምክትል ኮሚሽነሮች እና ከግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ የተሰበሰበውን ገንዘብ በሌለ አቅም ከብር 60 ሺህ እስከ 80 ሺህ ተከፋይ የሆኑ ግለሰቦች ‹በአማካሪነት› ስም ተመድበው ያለ በቂ ሥራና ኀላፊነት የመቀመጣቸው ጉዳይ በእውነት መዋቅሩ አስፈላጊ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር አንዳንዶቹ የኃላፊነት ቦታዎች በመዋቅር የተመለከቱም አይደሉም፡፡ ለምክትል ኮሚሽነሮቹ የተሰጠው ኀላፊነት በአብዛኛው በዳይሬክተሮች የሚሸፈን ሥራ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ምናልባት ኮሚሽነሩ በማይኖርበት ጊዜ በሱ ምትክ ሆኖ የሚሠራ አንድ ም/ኮሚሽነር መኖሩ አግባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ውጭ የሚታየው የም/ኮሚሽነሮችና የ‹አማካሪዎች› ጋጋታ ከፍተኛ የአገር ሀብት ብክነት ሆኖ ይሰማኛል፡፡
ሌላው ኮሚሽኑ ከተመሠረተበት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በበላይነት የሚያስተዳድረው የሥራ አመራር ቦርድ (የኢንቨስትመንት ቦርድ) አለ፡፡ የዚህ ቦርድ አባላት በተደጋጋሚ እንደሚታየው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት (የገዢው ፓርቲ ባለሟሎች) ሲሆኑ፣ ባመዛኙ በስብሰባ ወቅት የማይገኙ ወይም ዕውቀቱ ያላቸውን ባለሙያዎች በምትካቸው የማይልኩ፣ በአጀንዳነት የሚነሱ ጉዳዮችን በቅጡ የማያውቁ ብቻ ሳይሆኑ አስበውበት÷ አማክረውና ተዘጋጅተው የማይመጡ፣ አንዳንዶቹ በቦርድ አባልነታቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት ካለመወጣታቸውም በተጨማሪ ከሕግ ይልቅ በባለሥልጣን ቀረቤታ የሚተማመኑ ‹ባለሀብቶች› ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት ያላቸው፣ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ‹ባለሀብቶች› ከሕግ ውጭ ጥቅም እንዲያገኙ በኮሚሽኑ መ/ቤት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ጫና የሚፈጥሩ፣ በፖሊሲ ደረጃ የሚታዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የኮሚሽኑ የዕለት ተዕለት ተግባር በሆኑ ባንድ ግለሰብ ባለሀብት ጥያቄ ላይ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ መሆናቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ በተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶችና ድርጅቶች መዋቅር ውስጥ የተደራጀ የሥራ አመራር ቦርድ ካስፈላጊነቱ ጀምሮ እስከ አባላት አመዳደብ (በተለይም ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ያሉ ተወካዮሥርበሰበውንችን በበቂ ቊጥር በማሳተፉ ረገድ) ጥናትንና ምርጥ ተሞክሮን መሠረት አድርጎ እንደገና ሊታይ ይገባዋል ባይ ነኘ፡፡ በተለመደው እገሌ ይጠቀም በሚል የትውውቅና የፓርቲ ሎሌዎች ስብስብና የተወሰነ ቡድንን ፍላጎት (interest group) ተልእኮ ማስፈጸሚያነት ከቀጠለ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ጠ የሚያመዝን ይሆናል፡፡

ሌላው የታዘብኹት ጉዳይ ኮሚሽነሩን ለማነጋገር ቀጠሮ መያዝ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከጸሐፊ አልፎ ‹ቺፍ ኦፍ ስታፍ› የሚል ተጨማሪና አላስፈላጊ ያልተጻፈ መዋቅር በመሰንቀር ከልክ ያለፈ ቢሮክራሲ (red tape) መፍጠር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኮሚሽነሩን ለማነጋገር የሚፈልግ አንድ ባለ ጉዳይ ሊጠይቅ ያሰበውን ወይም ምክር የሚሻበትን ጉዳይ በዝርዝር ለጸሐፊ የማሳወቁ አሠራርስ ተገቢ ነው ወይ? ትርፍን አልሞ እግረ መንገዱን ለዜጎቻችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የሥራ አመራርና የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለማሸጋገር፣ ጥሪትን በተለይም የውጭ ካፒታልን ለማስገኘት ወዘተ የሚመጣ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ እውነተኛ ባለሀብት በዚህ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለበት ወይ? የኢንቨስትመንት ተቋም የፕሮሞሽን ኤጀንሲ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ለባለሀብቱ ጋባዥ (investor-friendly) ይሆናል ወይ? ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ለማጠቃለል የየመንግሥት መ/ቤቶች መዋቅሮች በቅጡ ቢፈተሹ ባንድ በኩል የአገርን ውሱን ሀብትን የሚያባክኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎቶች በብቃት የማይሰጡ ወይም ጭራሹኑ የማያስፈልጉ በርካታ የሥራ ክፍሎችና አላስፈላጊ ሹመቶች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ መዋቅር በሕግ የተሰጠን ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም የተቋምን ዓላማ ማስፈጸሚያ እንጂ ግለሰቦችን መጥቀሚያ አለመሆኑ ታውቆ በዚሁ መንፈስ ነባሮቹንም ሆነ አዲስ የሚቋቋሙ ተቋማትን ከአስፈላጊነት ጀምሮ እስከ መዋቅር፣ ተጠሪነት እና ስያሜ በጥናትና ምርምር ታግዘው ቢደራጁ ለሕዝብም ለአገርም ጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡

Filed in: Amharic