>

“ሀገሬን በፌስታል ጠቅልዬ ለአንድ ግለሰብ አምኜ አልሰጥም” (አቶ ሙሼ ሰሙ -ሸገር ታይምስ)

  • ሀገሬን በፌስታል ጠቅልዬ ለአንድ ግለሰብ አምኜ አልሰጥም
    አቶ ሙሼ ሰሙ ፖለቲከኛና የኢኮኖሚክስ ባለሙያ 
  • ማፈናቀል ለእነሱ ብቻ የተሰጠ አማራጭ አይደለም፡፡
  • አዲስ አበባ እንጂ “ፊንፊኔ”ም ሆነ “ሸገር” የሚባል ከተማ የለንም

በ1992 ዓ.ም መጀመሪያ ኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢ.ዴ.ፓ) ተመስርቶ በዚህ ድርጅት ውስጥ ገብተው የፖለቲካ ትግል ከመጀመራቸው በፊት በአገራቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ የግላቸው ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ፤ በወቅታዊ ጉዳዮችም ላይ በመፅሔቶች በሬዲዮ እና በመሰል ሚዲያዎች ሐሳባቸውን በመፃፍና በመግለጽ በፖለቲካው ላይ የራሳቸውን ጠጠር ሲያስቀምጡ ቆይተው በ1992 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ኢዴፓ ሊመሰረት በውይይት ላይ እያለ ጀምሮ ፓርቲውን በመቀላቀል፤ በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡ የዛሬው እንግዳችን አቶ ሙሼ ሰሙ፡፡

ፓርቲው ውስጥ ከተቀላቀሉ በኋላ ፓርቲው በ1992ቱ ምርጫ ተሳትፎ 14 ያህል የምክር ቤት መቀመጫ እንዳገኘ የሚናገሩት አቶ ሙሼ በመጨረሻም የኢዴፓ ሊቀመንበር ሆነው 4 ዓመት መርተው ከጨረሱ በኋላ ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን አርቀው አሁንም በግላቸው የአገሪቷን አጠቃላይ ሁኔታ በተለያዩ ጋዜጦች ፣ መፅሔቶች እና የሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ በመፃፍና ሐሳባቸውን ፣ ትዝብታቸውንም ሆነ ትችታቸውን ከማንፀባረቅ ወደ ኋላ አላሉም ለዛሬ ከሸገር ታይምስ ባልደረባ መክሊት ኃብታሙ በወቅታዊ የሀገሪቷ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ላይ ላቀረበቻቸው ጥያቄዎች  ያላቸውን ተስፋ ፣ ስጋት ፣ ቁጭትና ይበጃል ያሉትን ሐሳብ እንዲህ  አካፍለዋል፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  ከሀገሪቱ አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ እንጀምር አስኪ ለውጡ መጣ ከተባለ በኋላ ያለውን እና እየሆነ ያለውን ነገር እንዴት ይገመግሙታል? አስኪ በአጭሩ ይግለጹልን?

አቶሙሼ ፡-  በአጭሩ ግለጽ ብትይኝም የአነሳሽው ጥያቄ  ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሀገር ከአንድ የሥልጣን ዘመን ወደ ሌላ የስልጣን ሽግግር ያለውን ሂደት በአጭር ቃላት እና ንግግር ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ ነገሩ ቀላል በሆነልን እና ለውጥ አለ ወይም የለም ብለን ወስነን ወደ አንድ የፖለቲካ ትግል በገባን ነበር፡፡ ለእኔ ግን ኢትዮጵያ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ፈተናዎች የተደቀኑባት እና የተጋረጡባት ብትሆንም በዚያኑ ያህል ደግሞ ብዙ ነገሮች የታዩበት ነው ባይ ነኝ፡፡ እነዚህ በጎ ነገሮች የምናውቃቸው እና ያየናቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ የነበሩ ዜጎቻችን ያለ አግባብ በየእስር ቤቱ ሲማቅቁ ነበር ዛሬ ተፈትተው በነፃነት መንቀሳቀስ ጀምረዋል ይህ ደግሞ አዲስ መንፈስ ይሰጣል፡፡ የነበረውን የቂመኝነት ፣ የቁርሾና የግጭት መንፈስ አርቆ በአዲስ እና በመግባባት መንፈስ ለመስራት መንፈስን ያነቃቃል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን የኢኮኖሚ ተቋማት በአንድ ቡድን ወይም በአንድ ሰርክል የተያዘ ነበር፡፡ ያንን ፈልቅቆ ከዛ ቡድን ለመውጣት በዙ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ የሀገራችን ድህነት ልክ የለውም፡፡ በዚህ ድህነት ላይ ያለችው ጥቂት ሀብት በአንድ ቡድን ተይዞ ድህነቱ ብሶ ነበር ያንን በአንድ ቡድን የተያዘውን ጥቂቱን ያለንን አቅም ፈልቅቀሽ አውጥተሸ ሕዝቡ ተካፋይ እንዲሆን ካላደረግሽ ምንም ያህል ጥረት ቢደረግና ዲሞክራሲ ቢሰፍን ለውጥ አያመጣም፡፡

ሸገር ታይምስ፡-   እስኪ ከአንድ ቡድን ተፈልቅቀው ወጥተዋል ያሉኝን ሴክተሮች ምን ምን እንደሆኑ ግልጽ ያድርጉልኝ?

አቶሙሼ ፡-  እዚህ ነገር ላይ ጉዳዩን በጥንቃቄ ተመልከቺው የሆነ ቡድን በሞኖፖል ተቆጣጥሮ ይሰራበት የነበረን የሆነ ሴክተር ቀምቶ ለሌላ ቡድን መስጠት ማለት አይደለም፡፡ ምን ለማለት ነው የመንግስትን ስልጣን ተጠቅሞ በተለያየ መንገድ የመንግስትን እና የህዝብን ሀብት የግል ማድረግ ስራ እጅግ የቆየ ሒደት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ ከሜቴክ ጀምረሽ ቴሌኮሚዩኒኬሽንን ብታይ፣ መብራት ኃይልን ብትወስጂ ትልልቅ የመንግስት መሰረተ ልማት ያለባቸው ሴክተሮች ከአንድ ቡድን ጋር የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ ያ የፈጠረው እድል ምንድን ነው በጨረታ ወቅት ቀድመሽ መረጃ እንዳታገኚ የመንገድ ጨረታ እንዳታሸንፊ እየተደረገ የተወሰነ ቡድን ሲጠቀም ኖሯል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጨረታ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በኢንዱስትሪው ወይም በግብርናው አይደለም ያደገው በግንባታው ዘርፍ ነው ብዙ ሥራ ሲሰራ የነበረው፡፡ መንግስት በግንባታው ብዙ ጨረታዎችን ያወጣል ሁሉም የዘርፉ ሰዎች ጨረታውን ይሳተፋሉ ቀድሞ መረጃው የደረሳቸው የቡድኑ የቅርብ ሰዎች ያሸንፋሉ መጠቀም የቻሉት ዛሬ የሀብት ማማ ላይ ወጥተዋል፡፡

አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ስታይው በአንድ የግንባታ ዘርፍ ላይ ነው ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው ይህንን አሰራር ነው አሁን ከአንድ ቡድን አውጥቶ ሁሉም በዘርፉ አቅም ያለው እንዲሳተፍ ለማድረግ እየተሞከረ ያለው፡፡ ይህ ማለት ዜጎች እንደኢትዮጵያዊነታቸው እኩል የሚሆኑበትን አሰራር ለማምጣት ተሞክሯል ተደርጓል አይደለም ተሞክሯል! ፖለቲካው እና ኢኮኖሚው በጣም ተቆላልፈው ስለተቀመጡ ከዚህ ቁልፍልፍ ነፃ ለመውጣት እየተሞከረ ነው፡፡ እንደምትመለከችው በአንድ አካባቢ ላይ ያሉ ማኅበረሰቦች ተሰግስገውበት ሌላው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ ሌላው ፖለቲካው ላይ ያለው ተፅዕኖ ነው በዚህ በኩል ብንመለከት መሠረታዊ የሚባሉ ተቋማት ከዲሞክራሲ ግንባታ. ከመልካም አስተዳደር፣ከደህንነት ከፖሊስና ከመከላከያም አኳያ ብናየው የአንድ ብሔር ወይም ቡድን ተፅዕኖ የነበረባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡

እነዛንም ከዚህ አውጥቶ ተመጣጣኝ የሆነ ተሳትፎ የሚኖርባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ሥራ ተሰርቷል ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር መሆኗን ያሳየ አካሄድ ነው፡፡ እነዚህ ገንቢ ጎኖች ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አብዛኞቻችን ከዛ ወጥተን እየሄድንበት ያለው መንገድ ምን ያህል አስተማማኝ እና ከዚህ በፊት ያሳለፍነው ነገር ላለመደገሙ ዋስትና የሚሰጥ ነው? የሚለው ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ ኔትወርኩን ከአንድ ብሔር ወደ ሌላ የማሸጋገር ጉዳይ ነው ወይስ ያንን የተማረርንበትን አባሮ ሁሉንም በእኩልነት በሁሉም ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ጉዳይ ነው? የሚለው ስጋቴ ነው፡፡

የሕግ የበላይነትን በተመለከተ  ሕግን በአግባቡ የማስከበር አቅም በእጅጉ የተዳከመበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ በየአካባቢው የምናየው ግጭት እና መፈናቀል እንዲሁም ግድያ ከመስመር የወጣ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ የምናየው ሽኩቻና ንትርክ ሕግን እና ሕገ መንግስትን ማዕከል ያደረገ አይደለም፡፡ ይህንን የምልበት ምክንያት አዲስ አበባ ላይ እስከ ዛሬ ሕገ መንግስቱ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ያጎናፀፋቸው መብት አለ በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ አበባ እንጂ ፊንፊኔም ሆነ ሸገር የሚባል ከተማ የለንም አሁን ባላንስ ለማድረግ ከመፈለግ የተነሳ እየተለመደ የመጣው አዲስ አበባን ግማሹ ፊንፊኔ ይላል ግማሹ ሸገር ይላል ይህ ከሕገ መንግስቱ አንፃር ለእኔ አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡

ሸገር ታይምስ እንዴት እስኪ ያብራሩልኝ?

አቶ ሙሼ፡-  በጣም ጥሩ አሁን ያለው መንግስት ሲመጣ በሕገ መንግስቱ መሰረት ሀገርን እና ሕዝብን ለማገልገል እስከመጣ ድረስ ሰዎች ከሕገ መንግስቱ ውጪ ፍላጎታቸውን ለማንፀባረቅ የሚሉትን ነገር መከተል እና መቀበል የለበትም፡፡ ለሁሉም ነገር መመሪያው እና ገዢው ሕገ መንግስት ነውና፡፡ ሰሞኑን የሚታየው የ5 ሚሊዮን ብር ባነር ሸገር ይላል ለመሆኑ ሸገር የሚባል ከተማ አለ ወይ? እኔ ሸገርም ፊንፊኔም የሚባል ከተማ  አላውቅም፡፡ እኔ የማውቀው አዲስ አበባን ነው ለምሳሌ እኔ ብድግ ብዬ አዳማን ናዝሬት ማለት እችላለሁ? አልችልም፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነት ተነፍጎታል ትኩረት ግን ሊያገኝ ይገባል፡፡

ስለ ሕግ የበላይነት ይህን  እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ እየተጣሰ ያለው በብዙ መንገድ ነው ሰዎች በግል ፍላጎታቸው እየተነሱ የፈለጉበትን የሚያደርጉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ አንዳንዴ ሕግን የሚቆጣጠረው ማን ነው? እንዴት ነው? እንዴት ነው እየተቆጣጠርን ያለነው? ሥርዓት ሰፍኗል ወይ? አሁን እኮ አንድ ክልል አንዱን ብሔር ውጣ ይላል ፣አንዱ ብሔር ሌላው እኔ የበላይ ነኝ ይላል፣ አንዱ ጉልበተኛ የሌላውን ሀብትና ንብረት በጉልበቱ ይነጥቃል፣ አሁን አዲስ አበባ ላይ አረንጓዴ ቦታ በማይኖርበት ሁኔታ በሰዎች እየተወረረ ነው፡፡ ይህ ሕጋዊ ነው ወይ? ለምንድነው ሕጋዊ መሰረት የማይዘረጋለት? ፍርሐት ነው ወይስ ጫናውን አለመቋቋም? ያ ከሆነ ያለፈው ሥርዓት ከዚህ የተለየ ምን አደረገ? ገንዘቡ ጠመንጃው ሁሉ ነገር በእጁ ስለነበር የፈለገው ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁን ይሄ እየተደረገ ላለመሆኑ ዋስትናችን ምንድን ነው? እዚህ ላይ አስምሬ የምነግርሽ የሕግ የበላይነት ለማስከበር መንግስት ማን እንደሆነ መለየት አለብን፡፡

ሸገር ታይምስ፡- እንግዲህ መንግስት ነኝ ብሎ እየመራ ያለው ኢሕአዲግ  መሰለኝ፡፡ መንግስት ማን እንደሆነ መለየት አለብን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ሙሼ፡- እኔ በአሁኑ ሰዓት መንግስት ማን እንደሆነ ግራ ገብቶኛል፡፡ ኢህአዲግ ነው?  ኦዴፓ ነው?  ኦነግ ነው ? አብን ነው ወይስ አዴፓ?  ግራ የሚያጋባና ውጥንቅጡ የወጣ ነገር ነው የሚታየውና የሚደረገው ሠላሳ ጥቃቅን መንግስት ይዘሽ ሀገርን በሠላም ልትመሪ አትችይም፡፡ አሁን ሰላሳ እና አርባ መንግስት ነው ያለው፡፡ ፓርቲው መንግስት ነው፣ ግለሰቦች መንግስት ናቸው ሕዝብ ያስፈራራሉ ፣ ትዕዛዝ ይሰጣሉ ፣ ያስጠነቅቃሉ ይህ ሁሉ ነገር ካለው ተስፋ በላይ ሥጋቱን ያጎላዋል፡፡

ሸገር ታይምስ፡- እነዚህ ስጋቶች የሀገሪቱ እዚህም እዚያም ግጭትና መፈናቀል፣ የመንግስት ሕገ መንግስቱን እና የሕግ የበላይነቱን ጠንከር ያለ ሥርዓት አለማስከበር እና መሠል ስጋቶች ያየነውን ተስፋ ሊያጨልሙ እና ለውጡን ሊቀለብሱ ይችላሉ ብለው ያምናሉ?

አቶ ሙሼ፡- በደንብ አምናለሁ፡፡ ለምን ሁሉም ጫፍ ለጫፍ ሆኖ ገመድ ጉተታውን ተያይዞታል፡፡ ኦዴፓ የራሱን ገመድ ይጎትታል ፣ አብን ይጎትታል ፣ ቄሮ በዚህ በኩል ዘራፍ ይላል፣ ግለሰብ እንደመንግስት ይህ ካልሆነ ሀገር አትቀጥልም ይላል፣ አዴፓም በአንድ አቅጣጫ የሚፈልገውን ይላል፣ ሕውሃት በአንድ ከተማ ከትሞ ሀገር ነኝ ይላል ይህ ሁሉ መሳሳብና ውጥረት ባለበት ተስፋ ለውጡ ይቀጥላል ብዬ አላምንም፡፡ ገመድ ጉተታው የግል ፍላጎትን ከማሟላት የመጣ ነው ሀገራዊ አጀንዳ ቢኖረው በጋራ መነጋገር ና መወያየት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም በየፊናው ትንኮሳ ነው የያዘው፡፡ ደብረፂዮን በዛ በኩል ይተነኩሳል ፣ ለማ በዚህ በኩል ይተነኩሳል ፣ ዶ/ር ዐብይ በዚህ በኩል ይተነኩሳል ፣ ገዱ እዛ ማዶ ሆኖ ይተነኩሳል፤ በአጠቃላይ ግለሰቦች የሚናገሯቸው ንግግሮች በጠቅላላ ተንኳሾች ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች የግጭቱን ደረጃ ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በአማራና በትግራይ መካከል ያለው ነገር ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችል አዝማሚያ ነው፡፡ በሁለቱም ክልሎች መካከል ወደ ጦርነት የተቃረበ ሰዎችን መስዋዕት እስከማስከፈል የደረሰ ትንኮሳ አለ፡፡ በሱማሌና በኦሮሚያ መካከል ያለው ነገርም ገና አልበረደም፡፡ በዚህ በግጭት እና በትንኮሳ 3.5 ሚሊዮን ሕዝቦች ከቀያቸው ከኑሮአቸው ተሰደው ነው ያሉት ጌዲኦ ፣ ኦሮሚያ ፣ ትግራይ ፣ አማራ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ የተከሰተው መፈናቀል ያለመረጋጋት ምልክት ነው፤፡፡ እነዚህ ነገሮች የነበረውን ብሶት እጥፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው ብሶት የድህነት እና የሥራ አጥነት ብቻ ነበር፡፡ የነበረውን ኢኮኖሚ አንድ ቡድን፣አንድ ብሔር እና አንድ ቤተሰብ ሲጠቀም ስለከረመ እኩል ያመጠቀም እና የሥራ አጥነት ብሶት ነበር፡፡ አሁን የተከሰተው እኮ ግጭት ነው፡፡ ለምሳሌ በየቀኑ ወደ ከተማ የሚገባው የጦር መሳሪያ ቁጥር ስትመለከቺ በጣም ነው የሚያስደነግጠው አገሪቷን ወደ ጦርሜዳነት ለመለወጥ የታቀደ ነው የሚመስለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስጋቶች አደገኞች ስለሆኑ ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቷቸው መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል በለገጣፎ ፣ በወላይታና በደራሼ ወረዳ የሚገኙ የኩሱሜ ማኅበረሰብ ሰዎች ቤታቸው በላያቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ ወድቀዋል ይህ ድርጊት ማኅበረሰባዊና ሥነ-ልቦናዊ ጫናው እንዳለ ሆኖ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጫና ምን ያህል ነው ይላሉ? ሕገ -ወጥ ግንባታ አለ ቢባል እንኳን መንግስት ምን አይነት እርምጃ ነበር መውሰድ የነበረበት?

አቶ ሙሼ፡-  ትልቁና መሰረታዊ ነገር ሊሆን የሚችለው “ሕገ ወጥ” የሚለው ነገር ነው፡፡ ምንድን ነው ሕገ-ወጥ ማለት እርግጥ እኔም ሕገ-ወጥነትን የማበረታታ አይደለሁም፡፡ ግን ሕገ-ወጥ ማለት ምን ማለት ነው? ለመሆኑ እዚህ አገር ላይ ሕገ ወጥ ያልሆነስ ምን አለ? መንግስት ማለትም አሁን ያለው ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣበት መንገድ ሕገ ወጥ ምርጫ ነው፡፡ በተጭበረበረ ምርጫ ስለመጣ እና ሕገወጥ ስለሆነ አልቀበለውም ምክንያቱም መቶ ፐርሰንት አሸንፎ ወደ ሥልጣን የሚመጣም የመጣም መንግስት በዓለም ላይ የለም፡፡ አንዳንዴ ስለ ሕገወጥነት ስናወራ መለስ ብለን ራሳችንን ማየት እና እኛስ ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን መመልከት አለብን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ግንባታዎች ሕገወጥ አይደሉም ወይ? አሁን እዚህ አካባቢ ከእንጨት እና ከላስቲክ የሚሰሩ ሕገ ወጥ ግንባታዎች አሉ መሐል ከተማ ላይ ነው የምልሽ፡፡ እነዚህ ከለገጣፎ እና ከሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ላለፉት 10 እና 15 ዓመታት በዚያ ቦታ ላይ ኖረዋል ያንን መሬት ለማግኘት በተዋረድ ካለ የመንግስት አካል ጋር ተደራድረዋል፣ ገንዘብ ከፍለዋል፣ የውሃና የመብራት እንዲሁም መሰረተ ልማት ተዘርግቶላቸው አሟልተዋል፡፡ ግንባታውም በእንጨትና በላስቲክ አይደለም፡፡ ሲሚንቶ ፣ አሸዋ ፣ ቆርቆሮ ፣ ብረት ፣ ቀለም ፣ መስታውት ፣ሚስማር ፣ የሰው ጉልበት አጠቃላይ ለግንባታ የሚውል ማንኛውም ነገር ወጥቶበታል፡፡ ይህ ሁሉ ሂደት አልፎ ቤቱ ሲገነባ እንዴት ነው መንግስት ሕገ ወጥነቱ ያልታየው? ሕገ ወጥ ቢሆን እንኳን እርምጃውን መንግስት በምን መልኩ ማድረግ ነበረበት የሚል ጥሩ ጥያቄ አንስተሻል፡፡ ከላይ የጠቀስነው የግንባታ ቁሳቁስ ለአንድ ቤት እንኳን ምን ያህል እንደሚፈጅ ይታወቃል እንኳን 3 እና 4 ሺ ቤት ቀርቶ፡፡ ይህ የሀገር ሀብት ነው የፈሰሰበት በሚሊዮን የሚያወጣ ገንዘብ የፈሰሰበትን ቤት በግሬደር መናድ በሀገር ሀብት መቀለድ ነው፡፡ ወደ አነሳሽው ጥያቄ ስመለስ ሕገ ወጥ ከተባሉ እንኳን ወደ ሕጋዊነት ለመመለስ መንግስት ሕዝቡን ሰብስቦ በመፍትሔው ላይ መወያየት እና ስምምት ላይ መድረስ አማራጮች መቀመጥ ሲገባቸው ጠዋት ቁርሱን በልቶ ወደ ት/ቤት የሄደ ሕፃን ተማሪ ወደ ቤት ሲመለስ ቤቱን ሲያጣው እንደማየት የሚያም እና የሚያሳቀቅ ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች የሀገራቸው መንግስት የመኖሪያ ቤትም ሆነ ቦታ ስላላመቻቸላቸው መውደቂያ በማጣትነው እኮ እዛ ሄደው ቤት የሰሩት፡፡ ካላቸውም ከሌላቸውም ላይ ቆጥበው አንጀታቸውን አስረው አይደል እንዴ ልጆቻቸውን በዛ ጎጆውስጥ የሚያስተምሩት? አሁን ላይ ዜጎች እንደ ሰው ሳይቆጠሩ ፣ ሰውነታቸው ሳይከበር ፣አማራጭና ተገቢው ካሳ ሳይከፈላቸው የተሰራው ሥራ በሕዝቡ ስነ ልቦና ላይ እንዲሁም ሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ከቤት መፍረስ ከሀብት ውድመትም በላይ በእነዚህ ዜጎች ላይ የሚሰነዘሩት ቃላት ያቆስላሉ፤ እንደ ወንበዴና እንደወንጀለኛ እየታዩ ነው ያሉት፡፡ ቅድም እንዳልኩት እነዚህ ሰዎች እዛ የሄዱት ወንጀል ለመስራት አይደለም አማራጭ በማጣት ነው፡፡ ሕግ ለማስከበር ነው ከተባለ እነዚህ ሰዎች ቤቱን ሲሰሩ ያስተባበሩ ፣ ያማከሩ ፣ ያመቻቹ የመንግስት አካላት ለፍርድ ሲቀርቡ አናይም፡፡ አንዱ መከራከሪያ ደግሞ እኛ ስንፈናቀል የት ነበራችሁ? የሚል ነው፡፡ የለገጣፎ መፈናቀል እና ባለመረጋጋት እንዲሁም በግጭት የተከሰቱ መፈናቅሎችን ልናወዳድር አንችልም፡፡   ያኛው ማለትም የጌዲኦ ተወላጆች ከጉጂ ፣ የአማራ ተወላጆች ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉበት የግጭት ውጤት ነው፤ የለገጣፎውን መፈናቀል ያስፈፀመው ራሱ መንግስት ነው እንዴት ነው ሊወዳደሩ የሚችሉት? እርግጥ ነው በሁለቱም መንገድ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ያሳዝኑናል፤ መፈናቀላቸውም ያመናል ነገር ግን መንግስት ሆን ብሎ ያፈናቀላቸውን እና በግጭት የተፈናቀሉትን አናወዳድርም፡፡

ሌላ ታፔላ መለጠፍ እና አጉል ንግግርን ምን አመጣው? እነዚህን ሰዎች የምንክስበት መንገድ አለ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ላለፉት 27 ዓመታት ሕገ ወጥ ግንባታዎች ሲካሄዱ ምን አድርገናል? ሕገ ወጥ ግንባታ ተብሎ የፈረሰው የድሆች ቤት ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የሀገር ሀብት እንደመሆኑ መፍትሔው ማፍረስ ሳይሆን 10 እና 15 ዓመት የኖሩትን ሕጋዊ አድርጎ ከዚህ በኋላ በዚያ መንገድ የሚገነቡትን ማስቆም ነበር የሚሻለው፡፡ ሀገር ወይም ከተማ ማለት መሬት ብቻ አይደለም እኮ!! አዲስ አበባን አዲስ አበባ የሚያስብላት ሰው ፣ ግንባታና ኢኮኖሚው ነው፡፡ መሬቱ ብቻውን አዲስ አበባ አያስብላትም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወገኖች መካስ አለባቸው፡፡ የሚካሱበት መንገድ ሁለት ነው፡፡ 1ኛ ንብረታቸው ወድሟል ተገምቶ አግባብ ያለው ካሳ ያስፈልጋቸዋል፡፡ 2ኛው የሞራል ካሳ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ዜጋ እንደዜጋ ጠዋት ልጁ ት/ቤት ሄዶ ለምሳ ሲመጣ ቤቱ ፈርሶ እና እንዳልነበረ ሆኖ ሲያገኘው ምን ማለት እንደሆነ ከላይ ደጋግሜ ነግሬሻለሁ፡፡

ለሕፃኑ፣ለወላጁም ከዚህ በላይ የሞራል ኪሳራ ሊደርስባቸው አይችልም፡፡ ስለዚህ የንብረታቸውም ፣ የሞራልም ሆነ የለመዱት አካባቢ ተመልሰው መኖር የሚያስችላቸው ካሳ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሄ ማፈናቀል የሚቀጥል ከሆነ ማፈናቀል ለእነሱ ብቻ የተሰጠ አማራጭ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ሁሉም በየክልሉ ያፈናቅላል፡፡ ይሄ ደግሞ ሀገር ያፈርሳል እንጂ ማንንም አይጠቅምም፡፡

ሸገር ታይምስ፡- አዲስ አበባ የማን ናት? እና በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የሚባለው ጉዳይ እስከ አሁን ለንትርክ እና ለሙግት መነሻ ሆኖ ውስጥ ውስጡን ሽኩቻ እየፈጠረ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የማን ናት እና በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የሚባለው ንትርክ መቆሚያ መፍትሔው ምንድን ነው? እውነታውስ ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ ሙሼ፡-  መጀመሪያ ካልሽው ይልቅ መጨረሻ ላይ ያነሳሽው እውነታው ምንድ ነው የሚለው የበለጠ ጥሩ ነው፡፡ የሰዎች ምኞትና ፍላጎት ጣሪያ ሊነካ ሰማይ ሊደርስ ይችላል፡፡ በተግባር የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ምንድንነው የሚለውን ካየን እውነታው ላይ ያደርሰናል፡፡ ሰዎች ፍላጎታቸው እና ምኞታቸውን መግለጽ ይችላሉ፡፡ እርግጥ በዚህ መንገድ የሚነሳና የሚከሰት አለመረጋጋት ሀገሪቱን ያልተፈለገ አደጋ ላይ ይጥላታል፡፡ አሁን ከሕገ መንግስት ሁለት መሰረታዊ አንቀፆችን እንመልከት የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት ዋና ከተማ አዲስ አበባ ይሆናል ይላል አለቀ፡፡ ፊንፊኔ አይደለም፣ ሸገርም አይደለም፣ በረራም አይደለም በቃ አዲስ አበባ ነው፡፡ ይህን ሕገ መንግስት ለውጠን በሌላ እስካልቀየርነው ድረስ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ሕገ-መንግስቱ ተሳስቷል ፣ ልክ አይደለም ፣ መለወጥ አለበት ሌላ ነገር ነው፡፡ ውሳኔ ግን ይዘሽ ልትመጪ አትችይም፡፡ ለመወሰን በጋራ ቁጭ ብለን ተወያይተን ሕገ መንግስቱን እስከመለወጥ ልንደርስ እንችላለን፡፡ እኔ ተነስቼ አዳማን ናዝሬት ወይም ቢሾፍቱን ደብረዘይት ማለት እንደማልችለው ሁሉ ለደብረዘይት ወይም ለናዝሬት ከተማ አስተዳደር ብዬ መፃፍ እንደማልችል ሁሉ ሌላውም ኃይል ለፊንፊኔ ወይም ለሸገር ወይም ለበረራ ብሎ መፃፍ አይችልም፡፡

ህገ መንግስቱ  የምትፈልጊውን እየተጠቀምሽ የማትፈልጊውን እየተውሽ የምትሰሪበት ሕግ አይደለማ! ስናከብረው ደግሞ ሙሉውን ማክበር አለብን፤ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችም ሕገ-መንግስቱን በአግባቡ ማክበር መለማመድ አለባቸው፡፡ የማን ናት? የሚለው ራሱ ሕገ መንግስትን አለማወቅ ወይም ሆን ብሎ ንትርክ መፈለግ ካልሆነ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ስለመሆኗ በማያሻማ ሁኔታ በሕገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ማንም በታሪክ ፊንፊኔ የሚባል ከተማ አለ አላለም፤ አለም ከተባለ አንድ መንደር የሚወክል ስም አይደለም፡፡ አሁን በረራ የሚባል ነገርም ተጀምሯል፡፡ የት ጋር ነው በረራ ? ዛሬ አዲስ አበባ በዚህ መጠን ሰፍቶ ኢኮኖሚው አድጎ በርካታ ብሔር ብሔረሰብ ተሰባጥሮ አብሮ እየኖረ የጋራ የባለቤትነት ስሜት መምጣት ሲገባው የእኔነት ጥያቄ መነሳቱ የበለጠ አፍራሽ ነው ለእኔ፡፡ ይህ ጥያቄ ችግር ስላለበት ነው በደንብ ማውራት ያለብን፡፡ አንድ ከተማ ተነስተሸ የእኔ ነው ስትይ ምን ማለትሽ ነው?እሺ ያንቺ ነው ተባልሽ በቃ የእኔ ነው ብለሽ ረክተሸ ዝም ትያለሽ ወይስ ምንድ ነው?  የእኔ ነው ብቻ ሳይሆን ልዩ ጥቅም ይገባኛል የሚለውም አለ፡፡ ይሄ ተከታዩ ነገር ነው እኮ ችግሩ፡፡ ይሄ የእኔ ነው የእኔ ነው የሚለውን ከፈቀድሽ በኋላ የሚከተሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እነዛ ነገሮች ናቸው ስጋቶቹ፡፡ ልዩ ጥቅምን በሚመለከት ሕገ መንግስቱ የሚለውን አሁንም እንመልከት፡፡ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦቱ ወይም ያሉትን የሀብት አጠቃቀሞች በተመለከተ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ያለው ጥቅም ይጠበቅለታል ይልና 3 ነገሮችን ነው የሚያነሳው የመጀመሪያው አገልግሎት እና አቅርቦት (Service) አገልግሎት ማለት እንግዲህ ቆሻሻን ወደ  ዛ ትደፊያለሽ፣ ውሃ ከዛ ትጠቀሚያለሽ በዚያ ላይ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም አለ፡፡ ስለዚህ ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ የተፈጥሮ ሀብት ሲሰጥ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የሚጠብቀው ነገር አለ፡፡  ለምን አገልግሎት ሰጪ ስለሆነ፡፡ ሌላው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ያው አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል ስለሚገኝ ከአዲስ አበባ ስትወጪም ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ ስትገቢም ኦሮሚያን ስለምታቋርጪ ኦሮሚያም አዲስ አበባን ያቋርጣል፡፡ ለምሳሌ መብራት ሲዘረጋ ኦሮሚያን አቋርጦ ይሆናል፤ መንገድ ሲዘረጋ እንዲሁም ድንበር ላይ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት የሚነሱ ነገሮች ካሉ ጥቅሙ ይጠበቅለታል በሱ መሬት ላይ ስለምትመጪ ማለት ነው፡፡ ይህም ጥቅም ይጠበቅለታል የሚለው ለኦሮሚያ እንጂ ለግለሰብ አይደለም፡፡

ክልሉ እንደ ክልል እንጂ ጥቅም የሚጠበቅለት የዚህ ተወላጅ የዛ ተወላጅ የሚባል ግለሰብ ጥቅም አይደለም ጥቅሙ የሚጠበቅለት፡፡ እርግጥ ነው የክልሉ ጥቅም ሲጠበቅ በተዘዋዋሪ ባለበት ሆኖ ግለሰቡም ጥቅሙ ተጠበቀለት ማለት ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው ከኦሮሚያ በመወለዴ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይገባኛል ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግስቱ ላይ የለም፡፡

ለምሳሌ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ለሚያገኘው አገልግሎት የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ ክፍያ መክፈል ቢኖርበት ለኦሮሚያ ክልል እንጂ ለግለሰብ አይደለም፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ያንን ከአዲስ አበባ የተቀበለውን ልዩ ክፍያ መንገድም ሰራበት ጤና ጣቢያም ገነባበት ትምህርት ቤትም ከፈተበት የኦሮሚያ ተወላጅ ከነዚህ መሰረተ ልማቶች ይጠቀማል፡፡ ይሄ በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ገብተው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ መብራት እነሱ ድንበር ድረስ ከተዘረጋ የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ ለልጆቻቸው ት/ቤት ማመቻቸት ያስፈልጋል ለምን ይሄ ከአዲስ አበባ የተለየ ጥቅም ያስፈልጋል በሚል የሚመጣውን ጭቅጭቅ ለማስወገድ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ኦሮሚያ ክልሉ እንጂ ጥቅም የሚያገኘው ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ከላይ በተነጋገርነው መሰረት ነው ህገ-መንግስቱ ያስቀመጠው ተመልክቺ ዛሬ አዲስ አበባ የኔ ናት የሚል ነገር ተነሳ፡፡ ነገ ደግሞ ሀዋሳን ውሰጂ ሀዋሳን ለመገንባት ሲዳሞ ወይም የደቡብ ክልል  ብቻ አይደለም የደከመው፡፡ የማዕከላዊ መንግስትም ጭምር ነው መንግስት ያንን የክልል ከተማ ለማድረግ ከበጀቱ እየቀነሰ ሰጥቶ ነው የገነባው፡፡ ከተለያየ አከባቢ የመጡትም ገንብተዋል፡፡ ከዛ ሀዋሳ ሲለማና ሲያድግ አንዱ ተነስቶ የኔ ነው አለ እሺ ዋና ከተማ የት ይገንባ? ባህርዳርም ብትሄጂ ሌላ ቦታ ይሄ ጥያቄ አይቆምም፡፡ ውጡ ይመጣል፡፡ እንዴት እንዴት ያለ ነገር ነው እያየንና እየሰማን ያለነው? አንድ ነገር አለ ይሄ ከተማ የፍቅር ከተማ ሆኖ ሁላችንም በፍቅርና በሰላም እየኖርን የምንበለፅግበት ይሆናል ያለበለዚያ የግጭት መንስኤ ሆኖ ሁላችንንም ሊያፈርሰን ይችላል፡፡ በተለይ የኔ የተለየ ጥቅም ይከበር በሚለው ንትርክ በሚነሳ ችግር የግጭትና የመፍረስ መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ አዲስ አበባን ዛሬ አጓጊና ተፈላጊ ያደረጋት እሷ ላይ የተፈጠረው ሀብት ነው እንጂ መሬት ጠፍቶ ወይም ጠቦ አይደለም ስለዚህ ይህንን ሀብት በመፈለግና በመቀራመት የሚነሳው ግጭት ወደፍርስራሽነት እንዳትቀየር ከወዲሁ እሳቱን ማጥፋትና ህገ-መንግስቱን መሰረት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የትኛውም ብሄር እኮ ባለው የህዝብ ቁጥር ልክ በጀት ተመድቦለት ነው የሚኖረው በጀት የሚሰራው በህዝብ ቁጥር ነው፡፡ ይሄ እኩልነትን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ከዚያ ያለፈ በጀትና ልዩ ጥቅም ግን ለምን ይንፀባረቃል?

ሸገር ታይምስ፡- እስከአሁን በተነጋገርናቸው አገሪቱ ላይ ባሉት ችግሮች ምክንያት ዶ/ር አብይ መጀመሪያ ሲመጡ የነበራቸው ተቀባይነት እየቀነሰና በጥርጣሬ እየታዩ ነው የሚሉ አሉ፡፡ መቼም የዲሞክራሲና ህግ ተቋማትን በአግባቡ ስላልገነባን የእኛ አገር ፖለቲካ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነውና ህዝቡም እንደተለመደው ዶ/ር አብይ ላይ ተስፋ ነበረው አሁን ወደ ጥርጣሬ ተቀይሯል የሚሉ አሉ እርሶስ በዶ/ር አብይ ላይ እምነትዎ እንዴት ነው?

አቶ ሙሼ፡- እኔ ግለሰብን አይደለም የምጠረጥረው መንግስትን እንጂ፡፡ በበኩሌ አንድን አገር እንደ አንድ ቁስ በፌስታል ጠቅልሎ ለአንድ መንግስት መስጠት አግባብ አይደለም፡፡ እኔም በግሌ አገሬን በፌስታል ጠቅልዬ ለአንድ መንግስት አምኜ የምሰጥ ሰው አይደለሁም፡፡ ሁልጊዜ መመለስ የሚገባው ጥያቄ አለኝ እኔ በአገሬ ጉዳይ ላይ ማንንም አላምንም፡፡ ከመጠን በላይ ማንንም አላምንም፡፡ ይህንንም ሀላፊነት አምኜ በተለየ ሁኔታ የምሰጠውም ሰው የለም፡፡ በተለይ መርጬ የምሰጠው ሰው የለኝም፡፡ ለተወሰነ የስልጣን ዘመን ለተወሰነ ሥራ ሀላፊነት እንዲወሰድ የማደርገው ሰው ድርጅት ወይም መንግስት ይኖራል ከዚያ በተረፈ ግን ሀገሬን በፌስታል ጠቅልዬ ለአንድ ግለሰብ አምኜ አልሰጥም፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም መንግስት መጠርጠር እና በስጋት መታየት አለበት፡፡ መንግስት በሁሉም ነገር ሊታመን አይችልም፡፡ መንግስት አምላክ አይደለም ሁሉንም ሊያደላድል አይችልም፡፡ የብሄር የአከባቢ ጥቅምና ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ይህ ባይሆንማ የተቃውሞ ፓርቲ ለምን እናቋቁማለን? መንግስትን ስለምንጠራጠርና ታማኝ አይደለም ብለን ስለምናምንኮ ነው፡፡ በምርጫ አሼንፎ ስለመጣ እንቀበልዋለን የምርጫ ጉዳይ ነውና፡፡ ግን እታገላለው፣ ሁሌም አማራጭ እፈልጋለሁ በተሻለ ብቃትና ሀሳብ አገሪቱን እመራለሁ የሚል እስካለ ድረስ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ ሀገር ለግለሰብ፣ ለቡድን፣ ለድርጅት ወይም ለቡድን ታምኖ በፌስታል ተጠቅልሎ አይሰጥም፡፡

 ሸገር ታይምስ፡-  ሰሞኑን የፀረ ሽብር አዋጁን ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ ሰነድ ለውይይት ቀርቧል-፡፡ ግማሾቹ ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት ሲሉ ገሚሶቹ ግዴለም የነበሩት ጥሩዎች ቀጥለው ጥሩ ያልሆኑት ቢሻሻሉ ይሻላ ይላሉ እርስዎ ከየትኛው ወገን ነዎት?

አቶ ሙሼ፡- ለእኔ ሁለቱም አካሄዶች ፅንፈኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ከነ ብዙ ችግሩ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ውስጥ ያለ ነው፡፡ አገሮች እንዳላባቸው የሽብርተኝነት መጠን ልክ ጥብቅ ያደርጉታል፡፡ አንዳንድ አገሮች ደግሞ አላልተውታል፡፡ ኢትዮጵያን በሽብርተኝነት ጉዳይ ስትመለከቻት የ2016ቱን የአለም አቀፉን ፀረሽብር ኢንዴክስ አይቸዋለሁና የሽብር ስጋቷ በጣም ዝቅተኛ ከሚባሉት ውስጥ ናት፡፡ የደረሰባት የሽብር አደጋ ውስን ነው፡፡ ለምሳሌ አፍጋኒስታን፣ኢንግሊዝ፣አሜሪካ፣ሶማሊያ፣ሶሪያጎረቤታችን ኬንያንም ጭምር ስታያቸው የሽብር አደጋ በጣም በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው አገራት ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ስጋቷ ዝቅተኛ  ነው፡፡ የሚያስፈልጋትም ህግ በጣም የጠበቀ መሆን የለበትም፡፡ ያለፈው የፀረ ሽብር አዋጁ ያለበትም ችግር ይሄው ነው፡፡ መንግስት የፀረ ሽብር አዋጁን እንደ ፖለቲካ ግብ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት ነበር፡፡

ያንን ለማስፈፀም አብዛኛዎቹ ህጎች ደግሞ ሰፊ ናቸው፡፡ እንጂ ተመጣጣኝ አይደሉም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ስትወጪ የመንግስት ንብረት ማውደም ይልሻል፡፡ ከአንድ ዜጋ ላይ ናሙና መውሰድ ያስፈልጋልኮ፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ሽብር ሲፈፀም የተጠቀመበት ኬሚካል ምንድን ነው ብልሽ ልትመረምሪ ትችያለሽ፡፡ እኛ አገር የነበረው ይህ አዋጅ መንግስት የሚገዳደሩትን ሀይሎች እንደመቅጫ መሳሪያ ነው ሲጠቀምበት የነበረው፡፡ ነገር ግን የሰብአዊ ከመጠበቅና በመጠበቅና ከለላ በመስጠት በኩል ደግሞ ደካማ ነው፡፡ ሰብአዊ መብትን ለመግፈፍ መደበኛው ህግ እድል ስለማይሰጥ መንግስት በአጠቃላይ ሰብአዊ መብትን ለመግፈፍ ነው ሲጠቀምበት የነበረው፡፡ አሁን የተወያዩበት ርቀት ከአንድ ሲቪል ሂውማንቴሪያን አስተሳሰብ በመነጨ በጣም በሳል አካሄድ ሄደውበታል፡፡ በጣም መብትን እስከማስጠበቅ ሁሉ ይሄዳል፡፡ ጥሩ አድርገው ተወያይተውበታል፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የፀረ ሽር አዋጅ በባህሪው ይለያል የእኛ የፀረ ሽብር አዋጅ ከመደበኛው የወንጀል ህግ በምን ይለያል?

አቶ ሙሼ ፡- ቀጥዬ የምመጣበትና የማገኝበትም ችግር ይሄው ነው፡፡ አሁን ባለው መልኩ የሚፀድቅ ከሆነ ወደ መደበኛ ህጉ የማይካተትበት መንገድ አይታየኝም፡፡ ሌላም ህግ መፃፍ አያስፈልግም፡፡ ሽብር ግን እንዳልሽው ልዩ የሆነ ባህሪ አለው፡፡ በግለሰብ ተፀንሶ በግለሰብ ታቅዶ በግለሰብ ይፈፀማል፡፡ አለም አቀፍ ደረጃ ውስብስብ የሆነ  ባህሪም አለው፡፡ ሽብርን መቋቋም አትችይም ቴክኖሎጂን ይጠቀማል፡፡ በግለሰብ ብቻ ብዙ ጥፋት የሚያደርስ ድርጊት ነው ሽብር፡፡ ታዲያ ይሄንን አስቸጋሪ ነገር ለመከላከል ህጉም የራሱ የሆኑ ልዩ ባህሪዎች ያስፈልጉታል፡፡ ይህንን ደረጃ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን በግልፅ ያስቀምጠዋል እነዛን እነዛን ስታንዳርዶች(ደረጃዎች) ማሟላት አለበት ያለበለዚያማ መደበኛው ህግ ምን አለን፡፡

መደበኛው ህግ ውስጥ የሌሉትን ወደመደበኛው አካትተን ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ መንግስት እንዳልኩሽ መሳሪያ ይዞ ወታደር አሰልፎ ኢኮኖሚውን ይዞ እንደገና ዜጎቹን የሚያጠቃበት ሌላ መሳሪያ ልንሰጠው አይገባም፡፡ ነገር ግን መንግስት ደግሞ ሌላ ሀላፊነት አለበት ዜጎችን ከሽብር የመከላከል፡፡ ስለዚህ አሸባሪን የመግደል ብቸኛ ባለመብት መንግስት ነው፡፡ ይህንን ነገር ከመንግሰት ብቸኛ ከነጠቅነውና ‘ሞኖፖሊ ኦፍ ቫዮለንስ’ ወይም አሸባሪን የመግደል መብት የሁሉም ከሆነ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል፡፡ ስለዚህ ከመደበኛው ህግ የተለየ ለፀረ- ሽብር የሚሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፀረ ሽር ህግ ማውጣትና ከመደበኛው ህግ የተለየ ዜጎችን ለማጥቂያነት የማይጠቀም መሆን ማድረግ አለበት እላለሁ አመሰግናለሁ፡፡

ሸገር ታይምስ፡- በተጣበበ ግዜዎ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ስለሰጡን እናመሰግናለን፡፡

Filed in: Amharic