>

የመንደር ብሔርተኞች ድንቁርና. . . (አቻምየለህ ታምሩ)

የመንደር ብሔርተኞች ድንቁርና. . . 
አቻምየለህ ታምሩ
የወረዱ ዘረኛ አስተሳሰቦች ተቋማዊ እየሆኑ ይገኛሉ። «ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም የሚሉን አሉ» ሲሉ ፈጥረው ሲናገሩ የሰማኋቸው ለማ መገርሳና ዐቢይ አሕመድ ናቸው። ይህ ፋሽስት ወያኔ በምርጫ 97 ማግስት «ሰው ወደ መቀሌ፣ ሀብቱ ወደ ቀበሌ» ተባልን ብሎ እንደፈጠረው ያለው ነውረኛነት ነው”
 እነ ዐቢይና ለማ የፈጠሩትን ነውረኛነት የተከተሉ አፍ ነጠቆች ጉብዝናን ወይንም ውድቀትን  ከደምና አጥንት ጋር እያገናኙ ሲጽፉና ሲናገሩ  እያየን ነው። በርግጥ እንደዚህ አይነት የወረደ የዘረኛነት አስተያየት በሁሉም ብሔርተኞች በኩል በየቀኑ  ሲቀነቀን  የምናየው የእውቀት ጾመኛነት ነው።
በትግራይ ብሔርተኞች ዘንድ አንድ የትግራይ ሰው  ውጤታማ ቢሆን ውጤታማ የሆነው  ማንም ብርታትና ጥንካሬ ያለው  ሰው  እንደሚያደርገው ሁሉ  ብርታትና ጥንካሬውን አሟጦ ስለተጠቀመ ሳይሆን  የውጤታማነቱ ምንጭ ትግሬ መሆኑ  ነው ብለው ያስባሉ። አንዱ የወያኔ ደንቆሮ  ምሁር  ነኝ ባይ “ደርግን እኛ ትግሬዎችን ባንሆን  ኖሮ የሚያሸንፈው ኃይል አልነበረም” ሲል ጽፎ ማንበቤን አስታውሳለሁ።
በኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድም ተመሳሳይ ነው። በኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ አንድ ኦሮሞ  የተዋጣለት ጎበዝ  ቢሆን  ማንም ብርታትና ጥንካሬ ያለው  ሰው እንደሚያደርገው ብርታትና ጥንካሬ ስላለው ሳይሆን ኦሮሞ  ስለሆነ ነው ጎበዝ የሆነው ብለው ያስባሉ። የኢትዮጵያን ስመ ጥር የኦሮሞ አትሌቶች ጀግንነት ኦሮሞ ከመሆናቸው ጋር የሚያያይዙ  ብዙ የኦነግ “ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች” አሉ።
ዐቢይ አሕመድና ለማ መገርሳ  ከአስር ወራት በፊት የነበራቸው፣ ግን ለጊዜው  የደበቁት  ባሕሪያቸው አገርሽቶ ወያኔን ያስናቁ  ዘረኞች  ቢሆኑ «ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም» ወደሚያስብል የወረደ ዘረኛነት ሊያስደርስ አይችሉም! ዐቢይ አሕመድና ለማ መገርሳ ወያኔን ያስናቁ ነውረኞችም ቢሆኑ ኢትዮጵያን የሚያኮሩ መሪዎቹም ቢሆኑ  ጉዳዩ ያለው ከግለሰቦቹ ባህሪ ጋር እንጂ ኦሮሞ ከመሆን ካለመሆናቸው ጋር የሚያገናኘው አንዳች  ነገር የለም።
እነ ዐቢይና ለማ የቀደሙትን ስመጥር ታላላቅ የኦሮሞ ትውልድ ያላቸው  የኢትዮጵያ መሪዎች ክደው ራሳቸውን የመጀመሪያዎቹ  ስልጣን ያላቸው  የኦሮሞ መሪዎች  አድርገው  ቢፈጥሩና ስኬታቸውንና ውድቀታቸውን ከኦሮሞነት ጋር ቢያስተሳስሩትም የአገራችንን ታሪክ ላነበብን  ግን ኦሮሞ ኢትዮጵያን ያኮሩ ስመ ጥር መሪዎች እንዳፈራ እናውቃለን።
አገር የመምራት ችሎታ  በትህምርት፣ በልምድ፣ በብርታትና ጥንካሬ  የሚገኝ፤ ከጠንካራ የስነ መንግሥት እሳቤ የሚቀዳ እንጂ በመወለድ  የሚሰጥ ችሮታ አይደለም። የዐቢይ አሕመድና  የለማ መገርሳም እንደዚያው ነው። ዐቢይና ለማ የሥነ መንግሥት  እሳቤ የላቸውም። የኢትዮጵያ መሪ ሆነው ሳለ «ኦሮምያዊ» ካልሆንን ሞተን እንገኛለን ብለዋል።
ካገር ጫፍ እስከጫፍ በጥላቸው  ከልለው ተራራው የኔ ነው ብለው መግለጫ የሚያወጡ ናቸው። እንዲህም የሆኑት ኦሮሞ ስለሆኑ ሳይሆን ብሔርተኞች ስለሆኑ ነው! ማንኛምው ብሔርተኛ በነሱ ቦታ ቢሆን የሚያደርገው ያንን ነው።  የብሔርተኛነት መመሪያ እንደነ ዐቢይና ለማ መሆንን ይፈቅዳል። ብሔርተኛነት የመንደር ሀሳብ ነው።  የመንደር መሪ ሀሳቡም የመንደር ነው። ነገሩ የጠፋው የመንደር ሀሳብ የያዙት ብሔርተኞች የአገር መሪ ሲሆኑ ነው።
Filed in: Amharic