>

ያልጠገገው የሀዋሳ ቁስል!!! (ቢቢሲ)

ያልጠገገው የሀዋሳ ቁስል!!!
ቢቢሲ
ሐሙስ ሰኔ ሰባት ቀን 2010 ዓ.ም የሀዋሳ ከተማ ከዚያ ቀደም ብዙም የማታውቀው ዓይነት የብሄር መልክ ያለው ግጭት ካስተናገደች ስምንት ወራት አለፉ፤ ሆኖም ከተማዋ ጠበሳዋ የደረቀላት፣ የወትሮ ድምቀቷን መልሳ የተላበሰች አትመስልም።
በግጭቱ ሰዎች ተደብድበዋል፤ ተገደለዋል፤ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ተዘረፈዋል፤ ለህልውናቸው ዋስትና እንዳጡ የተሰማቸው ዜጎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ሸሽተዋል።
በወቅቱ መንግሥት አስራ አምስት ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ገልፆ የነበረ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ቁጥሩ ከዚህም ይልቃል ይላሉ።
የግጭቱን መርገብ ተከትሎ እርቅ ተካሂዷል፤ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተከናውነዋል፤ ባለስልጣናት ከመንበራቸው ገሸሽ ተደርገዋል፤ ለፍርድ የቀረቡና የሚፈለጉም አሉ።
እነዚህ ሁሉ እርምጃዎች የራቃቸውን የደህንነት ስሜት መልሰው እንዳላስገኙላቸው በከተማዋ ለተገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ያጫወቱት ወደ ስድሳ ዓመታቸው እየተጠጉ ያሉት ጴጥሮስ አብርሃም (የተቀየረ ስም) ናቸው።
ከሦስት አስርት ዓመት በላይ በከተማዋ የኖሩት ጴጥሮስ በቆይታቸው ሁሉ ባለፈው ክረምት መባቻ ያጋጠመውንና እርሳቸው “ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት” የሚሉትን መሰል ክስተት አይተው እንደማያውቅ ያስረዳሉ።
በከተማዋ ዳርቻ የገነቡት መኖሪያ ቤታቸው በድንጋይ ውርጅብኝ መሰባበሩን በሳግ በታፈነ ድምፅ የሚገልፁት ጴጥሮስ ቤታቸውን ተመልሰው ሊኖሩበት ቀርቶ ሄደው ለማሳደስ እንኳ እንዳልቻሉና ‘ዳግመኛ ጥቃት ይደርስብኝ ይሆን’ የሚል ስጋት እንደጥላ እንደሚከተላቸው ይናገራሉ።
ለአዛውንቱ ጴጥሮስ ባለፉት ወራት በከተማዋ የሰፈነው ሰላም ከስክነት የተፋታ፥ ውስጥ ውስጡን ውጥረት የሚርመሰመስበት ነው፤ ጥቃት አድራሾች ነበሩ የሚሏቸው ግለሰቦች ለፍርድ ሲቀርቡ አላየሁምም ይላሉ።
“ምንም ደህንነት አይሰማኝም። ምክንያቱም እስካሁንም ድረስ የህግ የበላይነት አልተጠበቀም። አሁንም እየተፈራራን ነው ያለነው። እንጅ እንደበፊቱ እንኖራለን የሚል ተስፋ የለኝም” ብለዋል።
ወደ ትውልድ ቀያቸው ወላይታ እንዳይመለሱ ህይወታቸውን የገነቡት በሀዋሳ የመሆኑ እውነታ አግዷቸዋል።
ጴጥሮስ ከወርሃ ሰኔ አንስቶ ቤተሰባቸውን ይዘው በከተማዋ እምብርት በኪራይ ይኖራሉ፤ የሦስት ወራት የቤት ኪራይ እና የአንድ ወር ቀለብ መሸፈኛ ነው የተባለ ክፍያ ከመንግሥት ቢወስዱም የተደረገላቸው ድጋፍ በቂ ነው ብለው አያምኑም።
ተሰማ ኤልያስ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። የካቲት 13 ቀን የሲዳማ ብሔር ክልላዊ አስተዳደር የመሆን ጥያቄ በአፋጣኝ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድበት የሚጠይቅ ሰልፍ ሲካሄድ ከአስተባባሪዎቹ መካከልም አንዱ ነበሩ።
በሰልፉ ዋዜማ በከተማዋ ውጥረት የነበረ ፣ በዕለቱም በርካታ የንግድ ተቋማት በሮቻቸውን በፍራቻ ጠረቃቅመው የነበረ ቢሆንም ሒደቱ ያለአንዳች ኮሽታ መጠናቀቁን የሚገልፁት በኩራት ነው።
የወርሃ ሰኔውን ግጭት ተከተሎ ከተማዋን የሰነጉትን ፖለቲካዊ ሕመሞች “አርቴፊሻል” እና “በተለይ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት ግጭት ገጥሟቸው የማያውቁ የወላይታ እና የሲዳማ ብሄርን በማላተም” ፖለቲካዊ ጥቅም ለማካበት የሚጥሩ ወገኖች ስሪት ናቸው ይላሉ አቶ ተሰማ።
የወቀሳ ጣታቸውም “ለሃያ ሰባት ዓመት ያህል ሕዝቦችን በመጋጨት ስልጣኑን ሲያደላድል ነበር” የሚሉት ገዥው ፓርቲ እና “በብሄር ፖለቲካ የማያምኑ፥ የከተማ ፖለቲካ የሚያራምዱ የአንድነት ኃይሎች” የሚሏቸው አካላት ላይ ያነጣጥራሉ።
ቢቢሲ በከተማዋ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የሰኔ ሰባቱ ግጭት ከመፈንዳቱ አስቀድሞ እውነታ ላይ ያልተመሠረቱ ነገር ግን ስሜትን የሚኮረኩሩ፣ የተጠቂነት መንፈስ የሚኮተኩቱ ወሬዎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እና በአካልም ሲነዙ እንደነበር ይመሰክራሉ።
መሰል ወሬዎች አሁንም አልፎ አልፎ በማኅበራዊ ሚዲያም በአካልም ሲሰራጩ የሚስተዋል መሆኑ ተመሳሳይ ግጭት ዳግመኛ ላለመከሰቱ መተማመኛ እንዳይኖራቸው እንዳደረገ የተናገሩም አሉ።
የታሪክ ዕዳ
የሲዳማ ክልል መመሥረትን የሚመለከት ሕዝበ ውሳኔ እንዲከናወን የሚጠይቀው ሰልፍ ጅማሮውን ያደረገው ከሀዋሳ ወጣ ብላ ከምትገኘው ሎቄ ነው።
ከአስራ ሰባት ዓመት በፊት በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡባት ቦታ ናት ሎቄ። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች በወቅቱ እንዳጠናቀረው ዘገባ የመንግስት ኃይሎች ቅዋሜ ለማሰማት በተሰባሰቡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ በከባድ መሳርያዎች በከፈቱት ተኩስ ሃያ አምስት ሰዎች ተገድለው፣ ሃያ ስድስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
መንግስት በበኩሉ የሟቾቹን ቁጥር ወደ አስራ አምስት ዝቅ አድርጎ ያሰማራቸው የፀጥታ አስከባሪ አባላትም መገደላቸውን ገልጿል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የራስ አስተዳደርን ጥያቄ በሚያነሱ የሲዳማ ተወላጆች ሎቄ የመሰባሰቢያ ነጥብ ሆናለች ሲሉ የአካባቢውን ፖለቲካ የሚከታተሉ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁር ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በተለይ በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ እስከጠቅላይ ሚኒስትርነት ለደረሰ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ስልጣን መመረጣቸው ፣ ድርጊቱን የፈፀሙ ታጣቂዎች እና ያዘዙ ባለስልጣናት ተገቢ ፍርድ አላገኙም ሲሉ ለሚብሰከሰኩ ተወላጆች የእግር እሳት ሆኖ መቆየቱን ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉት ምሁር ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስልጣን ለቅቀው አብይ አህመድ ከተተኩ በኋላ ታዲያ ታፍኖ የቆዩ ጥያቄዎች እና ስሜቶች ገንፍለው ወጥተዋል እንደእርሳቸው አገላለፅ።
በደምሳሳው ኤጄቶ እየተባሉ የሚታወቁ ወጣቶች እና የፖለቲካ ተሟጋቾች በቅርብ ጊዜ የአደባባይ እንቅስቃሴዎች የሎቄን ግድያ በአልባሳት ህትመቶች ማሰባቸው፣ ክስተቱ በሕዝባዊ የትውስታ ማህደር ያለመደብዘዙን የሚያመላክት ይመስላል።
ኤጄቶ ማን ነው?
ከሲዳማ ብሔር ፖለቲካ ጋር በተያያዘ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰርክ ስሙ የሚነሳ ቡድን ነው ኤጄቶ። በከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ሳይቀር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለውን ለውጥ በማምጣት ረገድ ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል እየተባሉ የሚሞካሹትን ኢመደበኛ ቡድኖች ፈለግ ተከትሎ በአካባቢው ለፖለቲካዊ ለውጥ የሚሠራ ይመስላል።
ኤጄቶ ለሲዳማ መብት መከበር በእውነት ላይ የተመሠረት ትግል ለሚያደርጉ የብሔሩ ጎበዛዝት የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው ሲሉ የብሔሩ ተወላጆች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የሲዳማ ብሔር በተለያዩ መንግስታት ውስጥም ራሱን የማስተዳደር መብቱን ለማስከበር ሲታገል፣ ብዙዎች የሞቱለትን ዓላማ ግብ ለማድረስ ስያሜውን ተላብሰው የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን የያዘ ቡድን ነው ይላሉ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲው ተሰማ ኤልያስ።
“ኤጄቶ በአንዳንድ ሰዎች እና ሚዲያዎች እንደሚባለው የመንጋ ፖለቲካ አራማጅ አይደለም። በእውነት ላይ ተመሥርቶ ለሕዝብ ድምፅ የሆነ ቡድን ነው።”
ተሰማ፣ ኤጄቶ ወጣቶችን በብዛት ይሰብሰብ እንጅ፣ በዕድሜያቸው ገፋ ያሉም፣ በመደበኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚሳተፉም ሆኑ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ለሲዳማ መብት መከበር በሃቀኝነት እስከታገሉ ድረስ ስያሜው ይገልፃቸዋል ሲሉም ያክላሉ።
ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት
ይሁንና ቡድኑን በበጎ የማያነሱት አልጠፉም። የሀዋሳ ከተማ ከልዩ ልዩ ብሔሮች የተውጣጡ ብዙሃንን አቅፋ እንደመያዟ፣ በዋናነት ለሲዳማ የራስ ማስተዳደር መብት ይታገላል የሚባለውን ቡድን በጥርጣሬ የሚገረምሙት አሉ።
በሰኔ ሰባቱ ግጭት ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦችን የማማከር ሥራ ስሠራ ቆይቻለሁ የሚሉ የሲዳማ ብሔር ተወላጅ ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ኢጄቶ የመንግስት መዋቅሮችን ተጠቅሞ የዳበረ ቡድን ነው ይላሉ።
“ፖለቲከኞች ፖለቲከኛ በመሆናቸው ብቻ በግልፅ ማድረግ የማይችሏቸውን ድርጊቶች በጀርባ የሚያስፈፅሙበት ቡድን ነው። ፖለቲከኞቹ የሚፈልጓቸውን ግቦች ለማሳካት እንደመደራደሪያም እንደማስፈራሪያም ይጠቀሙበታል።
“ስማቸውን ብንገልፅ ለደህንነታቸው ስጋት እንደሚገባቸው የነገሩን እኚሁ የከተማዋ ነዋሪ በርካታ ሥራ የሌላቸው ወጣቶች በኤጄቶ ጥላ ሥር መሰባሰባቸውን እና ቡድኑ መደበኛ ባለመሆኑ በስሙ ለሚፈፀሙ ጥፋቶች ተጠያቂ እንዳይሆን ነፃነት ሰጥቶታል ይላሉ።
የከተማዋን ሁኔታ “አሳዛኝ” ሲሉ የገለፁልን እኚሁ ነዋሪ የውስጥ ለውስጥ ውጥረቱ መርገብ ያለመቻሉ ማሳያ ዜጎች የሚኖሩባቸውን ሠፈሮች ከመምረጥ አንስቶ ያለመተማመን መኖሩ ፣ የእምነት ቦታዎቻቸውን እስከመለየት መድረሳቸው ነው።
ቢቢሲ ባለፉት አስር ወራት በሌሎች የኢትዮጵያ መሰል ከተሞች የማይስተዋል ዓይነት በተለይ ስሱ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ኃሳብን በነፃነት የመግለፅ ፍርሃት፣ በሃዋሳ እንዳለ አስተውሏል።
በቅርብ ዓመታት ትልልቅ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ስቴድየም፥ ከአገሪቱ መዲና ጋር በአፋጣኝ የሚያገናኝ የአውሮፕላን መስመር እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት መኩራሪያ የሆነ የኢንዱስትሪ ፓርክ ያገኘችው ሀዋሳ ክፉኛ ካናወጣት ህመም ሙሉ በሙሉ ያገገመች አትመስልም።
Filed in: Amharic