>

ኦሮሙማ እና የሶማሊ ተፈናቃዮች ነገር.. ለምን ሐውዜንን ያስታውሰናል??? (አሰፋ ሀይሉ)

ኦሮሙማ እና የሶማሊ ተፈናቃዮች ነገር.. ለምን ሐውዜንን ያስታውሰናል???
አሰፋ ሀይሉ
    «An unexamined life is not worth living.” 
  «ያልተመረመረ ሕይወት ፤ መኖር የሚገባው ሕይወት አይደለም፡፡»
– Socrates (ሶቅራጠስ)
የዛሬ 30 ዓመት – በሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ.ም. – በሐውዜን የገበያ ሥፍራ ላይ – የወታደራዊው መንግሥት የጦር አውሮፕላኖች ባካሄዱት ምህረት የለሽ የቦምብ ድብደባ – 3,000 ያህል የከተማዋ ገበያተኞች ነፍስ ባንድ ጀምበር ሲቀጠፍ – እና በሺኅዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአካል ጉዳት በደረሰባቸው ማግስት – ህወኀቶች ያን የሐውዜንን አሰቃቂ የወገን ጭፍጨፋ – በወታደራዊው መንግሥቱ ላይ ለጀመሩት የትጥቅ ትግል – እንደ ዓይነተኛ የትግራይ ተወላጆችን ማሰባሰቢያነት እንደተጠቀሙበት – ወይም ያ በትግራይ የሐውዜን ነዋሪዎች ላይ የደረሰው አጋጣሚያዊ ግፍ – ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እና ሰብዓዊ ፍጡር አሳዛኝ ክስተት ሆኖ ማለፉ ምንም አጠያያቂነት የሌለው እውነታ ነው፡፡
ቢሆንም ግን – ያ ክፉ አጋጣሚ ግን – በተለይ – ለያኔዎቹ ህወኀቶች – የትግራይ ብሔርተኝነትን እንደጋራ ማዕከላዊ አጀንዳው አድርጎ – በጋራ የተጠቂነትና የተሳዳጅነት መንፈስ – ታይቶ የማይታወቅ ሕዝባዊ (ማዕበላዊ) ድጋፍና አጋርነት – ለህወኀቶች እንዳስገኘላቸው – ሳይደግስ አይጣላም በሚል ከሐውዜን ማግስት የሆነውን – እውነቱን ፍርጥ አድርገው የሚያነሱት ብዙዎች ናቸው፡፡
ያ ሐውዜንን ከነገበያተኞቿ የጠራረገው ጭፍጨፋ ሁልጊዜም ቢሆን በወገን ላይ ያንን ዓይነት ግፍን ላለመድገም በብዙዎች አዕምሮ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ያ ክፉ አጋጣሚ ለያኔዎቹ ህወኀቶች – በምንም ዓላማና ፖለቲካ ልትገዛው የማትችለው –  ኃይለኛ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆኖ እንዳገለገላቸው ደግሞ – ሁልጊዜም አብሮ ተያይዞ መነሳት ያለበት እውነታ ነው፡፡
ዛሬ ላይ ሆኜ – ያን የዛሬ 30 ዓመት በትግራይ ምድር ያለፈ – አሳዛኝ የሐውዜን ክስተት – ከነፖለቲካዊ ቱሩፋቶቹ – አሁን ላይ የሚያስነሳን ነገር ምን ተገኝቶ ነው?
ጥሩ፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ወደኋላ 30 ዓመታትን የኋሊት ተንደርድረን – የሐውዜንን ትዝታ ሳንወድ በግድ ለማስታወስ የምንገደደው – ዛሬ ላይ ያንኑ ሐውዜንን ተከትሎ ግልጋሎት ላይ የዋለውን ፖለቲካዊ ቅስቀሳና ትልቅ የመሰባሰቢያ ምክንያት የማግኘት ዓይነት – በዓይነቱ ያንኑ የሚመስል ተመሣሣይ አካሄድ – በሶማሊ ክልል ልዩ ኃይሎች ተፈናቀሉ ተብለው – ዕድሜልካቸውን ሲኖሩበት ከነበሩበት ምድር – አንዲወጡ ስለተደረጉት – እና ወደ ተነሱበት እና መኖሪያቸው ወደሆነው ወደትክክለኛ ሥፍራቸው ከመመለስ ይልቅ – የኦሮሚያ የፖለቲካ አቀንቃኞችና አስተዳዳሪዎች – እነዚያን የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የሶማሊ ተፈናቃዮች – በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማስፈርን – የእርዳታ ማሰባሰብን – ወገናዊ ቅስቀሳን – እና በኦሮሞዎች ላይ ደረሱ የሚባሉ ሰብዓዊ ኪሣራዎችን ብቻ በማጉላት መጮኽን ስለምን መረጡ???
እነዚያን ከመኖሪያቸው በኃይል የኦሮሞ ተወላጅ ነዋሪዎች – በህገወጥ መንገድ ያፈናቀሏቸውን ኃይሎችና አካሎች በአስቸኳይ ለህግ አቅርቦ – ነዋሪዎቹን ግን – ወደኖሩበት – መንደራቸውን ወደቀለሱበት – ወደዚያው ወደሚገባቸው የተፈናቀሉበት ትክክለኛ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ለምን አልተደረገም? ወደነበሩበት መኖሪያቸው እንዲመለሱ ቢደረግና – ተመሣሣይ ኢሰብዓዊ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ተገቢው መንግሥታዊ ክትትልና ጥበቃ ቢደረግ ኖሮ – በሚሊዮኖች ደረጃ የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ እዚያው ባጭሩ መግታት – እዚያው ላይ መልሶ ማቋቋም – እዚያው ላይ መፈናቀሉን ማብቃት አይቻልም ነበር ማለት ነው?
እነዚያ በሚሊየን የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጅ ነዋሪዎችን – ወደትክክለኛ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ – በኦሮሚያ ሕዝብ ዘንድ ትኩስ እይታና አትኩሮት (‹‹አቴንሽን››) እንዲያገኙ በሚያደርግ ሁኔታ – ሰዎቹን በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እንዲጠለሉ – በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አዲስ መኖሪያ ሥፍራና ኩርማን መሬት እንዲሰጣቸው – ዳግም በማያውቁት አካባቢ እንደ አዲስ ኑሮን እንዲጀምሩ ማድረግ – በምን ዓይነት መሥፈርት ነው ቅድሚያ የተሰጠውና ዓይነተኛ አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው??
ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ – በዚህ አሳዛኝ ሰብዓዊ ቀውስ የተፈናቀሉ ዜጎችን – ወደ ኖሩበት ህጋዊ መኖሪያቸውና አካባቢያቸው ስለመመለስ ከማሰብና – ያንኑ የሚያረጋግጥ ተግባር እንዲወሰድ ከመጣጣር ይልቅ – ስለምን የኦሮሚያ ፖለቲከኞችና አስተዳዳሪዎች – ልክ እንደፍልስጥዔም ቀብርተኞች – የተፈናቀለውን ሕዝብ ከየኖረበት ክልል በወሳንሳ ይዘው – በኦሮሚያ ሕዝብ መሐል ማጓጓዙንና መበተኑን – ስለምን እንደ ዓይነተኛና ዘላቂ አማራጭ ቆጠሩት??
ወይስ – ድሮ የሐውዜን ጭፍጨፋን ተከትሎ ህወኀቶች ክስተቱን ወደዓይነተኛ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት በማዋል ሕዝባዊ ብሐየርተኛ የድጋፍ ማዕበል ለመፍጠር ተጠቅመውበታል እንደተባለው – ልክ እንደዚያው ሁሉ – የአሁን የኦሮሚያ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ እና የኦህዴድና ኦነግ የመሣሠሉት – ህዝባዊ ድርጅቶችና የፖለቲካ አቀንቃኞቻቸው – ይህን ያህሉን ግዝፈት ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ወደነበረበት እንዲመለስ የማድረግን ጉዳይ ሁለተኛ ጆሮአቸውን ብቻ መስጠቱን ለምን መረጡ??
ይህን ያህሉን ግዝፈት ያለው ሰብዓዊ ቀውስስ ሁለተኛ ጆሮአቸውን በመስጠት – እና ይህን ያህል ስፋት ያለውን ሀገራዊ ሰብዓዊ ቀውስ – ለታላቅ የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ዓይነተኛ መሣሪያ አድርገው በመጠቀም – ሕግ የሌለበት፣ የኑሮ/የህይወት ዋስትና ባልተከበረበት ሀገር ነው እየኖርን ያለነው፣ እኛ ኦሮሞዎች ተለይተን እየተጨፈጨፍን ነው፣ ተለይተን እየተፈናቀልን ነው፣ የኦሮሞ ተወላጆች ተለይተው ተጠቂዎችና ተሳዳጆች ሆነዋል የሚሉ – እና ልክ ሐውዜንን ተከትሎ በመላ ትግራይ ተወላጆች ዘንድ እንዲሰራጩ እንደተደረጉት – የጋራ ሰብዓዊ ብሔርተኛ አጋርነትን – ታላቅ የጋራ ኦሮሞአዊ ግንባርን፣ በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍል ባሉ የኦሮሞ ተወላጆች መካከል ነበሩ የሚባሉትን ልዩነቶች ሁሉ አስወግዶ – ታላቅ የጋራ ኦሮሞነትን – ታላቅ ኦሮሞነትን ማዕከል ያደረገ ትኩስ (‹‹ሴንሴሽናል››) ብሔርተኛ መሰባሰቢያ አጀንዳን ፈጥሮላቸው ይሆን???
እና ነጥቤ – ልክ የያኔውን የዕለተ ዕሮቡን የሰኔ 15/1980 የሐውዜንን ታላቅ ሰብዓዊ ቀውስ – ህወኀት ታይቶ ወደማይታወቅ ሕዝባዊ ብሔርተኛ ማዕበል ማሰባሰቢያ መሣሪያ አድርጎ እንደተጠቀመበት ሁሉ – ልክ እንደዚያው – አሁንም – በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ – ይህን ከሱማሊ-ክልል ኦሮሞዎች እንዲፈናቀሉ የመደረጉን ይህን ታላቅ ሀገራዊ ሰብዓዊ ቀውስ – እንደ ዓይነተኛ በኦሮሞነት ዙሪያ ሁሉንም ፖለቲከኞች የሚያሰባስብ ትኩስ ጉልበት ያለው ታላቅ ብሔርተኛ ማዕበልን መቀስቀሻ እና መሰባሰቢያ – ኃይለኛ የፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ሰጥቷቸው ይሆን ወይ? ያ የሶማሊ-ተፈናቃይ – ወደ ኦሮሚያ መልሶ-ሰፋሪ – ጉዳይ – ለኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች – እግረመንገዱን – ወይም በቀውሱ ማግስት – «ሣይደግስ አይጣላም!» ሆኖላቸው ይሆን ወይ?? – ጥያቄዬ ያ ነው፡፡ ጨርሼያለሁ፡፡
«An unexamined life is not worth living.” «ያልተመረመረ ሕይወት ፤ መኖር የሚገባው ሕይወት አይደለም፡፡» እንዳለው ሃቀኛው ፈላስፋ Socrates (ሶቅራጠስ) – ለማንኛውም – የሄድንበትን አኳኋን በእርጋታ እናጢነው፣ እንፈትሸው፣ እንመርምረው – እና ሕግ ባለበት ሀገር ላይ ሌሎችን አባርሮ መቀመጥ አይቻልምና – አሁንም ሆነ፣ መቼውኑም ቢሆን – ከመኖሪያቸው «የተፈናቀሉ» ኢትዮጵያውያን ዜጎችን – ወደዚያው ወደቀደመው መኖሪያቸው በአስቸኳይ ተመልሰው በሠላም መብታቸው ተጠብቆ የሚኖሩበትን አማራጭ – መቼውኑም አንዘንጋው፡፡ እንዲያውም ቅድሚያ እንስጠው፡፡ አበቃሁ፡፡
አምላክ ሕዝቦቻችንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ የጃጋማ ኬሎ ሀገር፣ የብዙሃን እናት፣ እምዬ ኢትዮጵያ ሀገራችን፣ ለዘለዓለም ትኑር፡
Filed in: Amharic