>

"የኦሮምያ የለቅሶ ፓለቲካ!!!" (በለጠ ሞላ - አብን ም/ሊቀመንበር)

“የኦሮምያ የለቅሶ ፓለቲካ!!!”
በለጠ ሞላ – አብን ም/ሊቀመንበር
የኦሮሞ ልሂቃን ፖለቲካ “ሁሉንም ባንዴ አሁኑኑ ለኔ” ከሚል አክሳሪ ሩጫ ወጥቶ፤ ይልቅ የኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅሙ በተገቢው ይረጋገጥለት ዘንድ የሚያስችለውን አዋጭ አካሄድ መከተል እንዳለበት ደጋግመን ለማስገንዘብ ሞክረን ነበር….ግን ይህን አልሰማ ብሎ “መምራት አትችልም አሉኝ” በሚል አሳፋሪ የቡድን ልቅሶ ተቀምጦ ሲነፋረቅ እያየን እኛንም አሳፍሮናል።
ኦዴፓ በእጁ የገባለትን ስልጣን በአግባቡ፣ በርጋታና በአስተውሎት ዘመንተሻገሪ ትሩፋት አንዲኖረው አድርጎ ካልያዘው በቀር የበዛ ብልጣብልጥነትን (ፖለቲካዊ ሞኝነትም ሊሆን ይችላል) ከወደደ ስልጣን ከእጁ በማንኛውም ግዜ እንደሚሾልክና ይህም ሲሆን ቀድሞ የሚጎዳው በዋናነት ራሱ እንደሆነ ማሰቡ ልባምነት ነው።
የኦሮሞ ልሂቃን ፖለቲካ የኦሮሞን ህዝብ በዘላቂነት ተጠቃሚ ማድረግ ካሻው “እገሌ የተባልኩት በምንሊክ ምክንያት ነው” ከሚል የዝቅተኛነት ስነልቦና ቅኝት ነፃ ሊወጣ ካልቻለና “ሁሉም ነገር ባንዴ አሁኑኑ ለኔ ብቻ” ከሚል አውዳሚ አስተሳሰብ የተፋታ መሆኑን ማረጋገጥ ካልቻለ የታወቀ አቅጣጫ ሊኖረው አይችልም።
የኦሮሞን ህዝብ በዋናነት የሚጎዱት እነዚህ ሁለት የተሳሳቱ የልሂቃኑ እሳቤወች ናቸው ….ሁለቱም ጤነኛ ስላልሆኑ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያጠፉ ስለሚሆኑ!
————-
ተወደደም ተጠላም የኦሮሞ ልሂቃን ፖለቲካ ለወደፊት በራሱ ዘንድም ይሁን በሌሎች ዘንድ የሚያስመዘግበው ቅቡልነት በዋናነት በኦሮሞ ድርጅቶች የፖለቲካ ስራ ላይ የሚመሰረት እንደሆነው ሁሉ፤ ኦሮሞ ባልሆኑ ህዝቦችና ድርጅቶች መካከል ቅቡልነትን ማግኘት መቻል ላይም የሚወሰን ይሆናል። የሚገጥመው ውድቀትም እንዲሁ ከራስ ስህተት እንደሚመነጨው ሁሉ ከሌላው አቅጣጫ በሚመጣ ቅዋሜም ጭምር ይሆናል!
————————
ሜንጫውን ግን አትፍረዱበት….”short-term memory” ያለው በመሆኑ (ሌላው እንደዛ ብሏልና)፤ ራቅ ያለ ታሪካዊ እውነታን ሊያስታውስ ይቅርና የቅርቡን የትላንቱን ዘመን ተጋድሎ እንኳ በውል ለማስታወስ እንደተቸገረ እየታዘብን ነው። እንዲህም በመሆኑ እዘኑለት እንጅ አትዘኑበት! በርግጥም በረራን ይቅርና አዲስ አበባን እንኳ በውል ማወቅ ተቸግሯል….አያውቃትማ!
————————
ትግላችንን በተመለከተ እኛና ህወሓት እውነታውን እናውቀዋለን። ህወሓት ተኝታ ሌሊት ስትቃዥ ደጋግማ የምትጠራው “አማራ ነፍጠኛ፣ ፋኖ ትምክህተኛ፣
ምንሊካውያን፣ ደመቀ፣ መሳፍንት፣ እስክንድር፣ ተመስገን፣ ማሙሸት፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ወልድያ፣ ቆቦ፣ መርሳ….” የሚሉ ቃላቶችን ነው።
ሌላውን በቅዠቷ እምብዛም አትጠራውም።
ይህን ለማረጋገጥ የፈለገ ሰው መቀሌ ሄዶ ሆቴል ውስጥ አልጋ ይዞ አንድ ሌሊት ማሳለፍ በቂው ነው! ደማቁ እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ተከታይ እውነታወችም አሉና በተከታይነት እንዲሁ ይታወሳሉ ዋጋቸውንም ታሪክ በልካቸው ይዘክረዋል።
እደግመዋለሁ….የቄሮ ትግልና መስዋእትነት ኦሮሞ ወደ ፍትህና እኩልነት መንበር ይመጣ ዘንድ ካልሆነ በቀር ህዝብን ከርስቱ እንዲወጣ ታስቦ ከነበር መጨረሻው በከንቱ ህልሙ የታሪክ ቀጭን ገመድ ታንቆ መጥፋት ብቻ ይሆናል!
———————–
ለማንኛውም የእውነትን ስር መሰረት የማዳፈን አባዜ፣ የትላንትን ሀቅ የመርሳት አባዜ፣ ዛሬን ያለማጤንና ነገን በስክነት አሻግሮ ያለማየት አባዜና ይህንን መሰሉን ጠቅላይ ችግር ጀርመናዊው ፈላስፋ Martin Heidegger ስም ሰጥቶታል ….Oblivion ይለዋል…..ዝንጋኤ! ይህ አይነቱ የታሪክ፣ የስነ ኑባሬና፣ የነገሮች ስረመሰረት ጠቅላይ ዝንጋኤ ብዙ ግዜ የሚፈጠረው በደንብ ያልተፈተሸ ችግር ላይ በመነሳትና ባልጠለቀ ግንዛቤ በመመራት የቸኮለ ድምዳሜና ማጠቃለያ ላይ ለመድረስ ከሚደረግ ጥድፊየና የበዛ ጉጉት የሚመነጭ ነው። እናም በዚህ ዝንጋኤ በሽታ ክፉኛ የተመታ መንጋ ቢኖር እሱን እዘኑለት እንጅ አትዘኑበት!
————————–
ከሁሉ ከሁሉ….የአፄ ዳዊት መዲና በረራ እንዴት ትረሳለች? የትላንቷ አዲስ አበባስ እንዴት ትረሳለች? የዛሬዋ አዲስ አበባስ እንዴት ከእውቀታችን ታመልጣለች??  የአለም ታሪክ ግን በረራን ያስታውሳል! የመጀመሪያው የአለም ካርታም ቢሆን እንዲሁ በረራን ያውቃል እንጅ አልካደም አልደመሰሰም! ይህቺ ታላቅ ስልጣኔ ትላንትም ባለቤት ነበራት፤ ትውልዷም ሁሉ እነሆ ዛሬ በከተማዋና በዙሪያዋ ከተሜ ሆኖ ይኖራል።
“አዲስ አበባ” ስንል በቀዳሚነት ህዝቧንና ታሪኳን ማለታችን እንጅ ህንፃወቿን ብቻ ማለታችን አይደለም! እንዋጠው የሚሉት የከተማዋ ህዝብ ግትር–ህንፃ ሳይሆን ዛሬም ድረስ የደመቀ ኑባሬ ያለው የፒያሳ፣ የአራት ኪሎ፣ የሽሮ ሜዳ፣ የኮተቤ፣ የቦሌ፣ የመርካቶ፣ የሳሪስ፣ የመገናኛ፣ የላፍቶ፣ የመነን፣ የፈረንሳይ፣ የካዛንችስ፣ የጎፋ፣ የአያት፣ ሰሚት፣ ሲአምሲ፣ አራብሳ፣ ኮየፈቸ፣ አቃቂ፣ ቃሊቲ፤ አስኮ ….አጠቃላይ የአዲስ አበባ ህዝብ ማለት ነው! ይህንን የማያውቅ ከተማዋን የማያውቅ ነው፤ የማያውቃት ደግሞ አያውቃትም!
——————————
How come that I, the Amhara nationalist, concur with those indigenous to Addis Ababa (perhaps with every Ethiopian except those in Mencha’s feather) on the question regarding the status of the city and on the direction about how it should go!? Isn’t it because we are sane enough to appreciate what is true to the city? Isn’t it because we have a proper/common understanding of the facts about the city now and in its long past? Isn’t it because we have a shared vision for tomorrow? Isn’t it also because the other voice is totally ungrounded. It definitely is!
———————
Yes, Berara/Addis Ababa is my City, our City!!
Filed in: Amharic