>
6:31 am - Wednesday December 7, 2022

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስላባዎቹ (በአሸናፊ በሪሁን ከseefar )

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስላባዎቹ

በአሸናፊ በሪሁን ከseefar 

በዓለም ላይ አትራፊ ከሆኑ ወንጀሎች መካከል ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አንዱ እና ቀዳሚው ነው፡፡ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለብዝበዛ ዓላማ ሰዎችን በተለይም ሴቶችና ሕፃናትን በኃይል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ ወይም በተበዳይ ላይ ኃላፊነት ላለው ሰው ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በመስጠት መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል ማለት ነው፡ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በተደራጀ የማፍያ ሰንሰለት የሚመራ ነው:: ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውሩን የሚመራው ራሱም በህገ ወጥነትና በምስጢራዊነት የተደራጀው ኃይል መረቡ ከአውሮፓ ጀምሮ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካና በዓረቡም ዓለም በስፋት የተዘረጋ የራሱ የግንኙነት ድርና መዋቅር ያለው ነው፡፡ህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ደላሎች በየሀገራቱም በስውርና በድብቅ የሚሰሩ ወኪሎች አሏቸው፡፡ ከከተሞችና ከገጠር መንደሮች ወጣት ወንዶችንና ሴቶችን ከእርሻና ከትዳራቸው እያፈናቀሉ የተሻለ ስራና ከፍተኛ ክፍያ ታገኛላችሁ በሚል ማማለያ ከፍ ያለ ገንዘብም በመቀበል አንዳንዴም ቤተሰብ ሳያውቅና ሳይሰማ በስውር ደብቀውና ሸሽገው እንዲኮበልሉ ያደርጓቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ከሀገር የሚወጡት ይህንን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚመሩትና የሚያደራጁት ደላላዎች በሚያወጡት ፕሮግራም መሰረት ነው፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት በአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 77 በመቶ የሚሆኑት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ናቸው፡፡ በተለይም ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች ከሆኑት እና ወደተለያዩ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ስራ ፍለጋና ሌሎች ምክንያቶች ከተጓዙት ኢትዮጵያውያን መካከል 7.5 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 17 ዓመት ሲሆን እና ከእነዚህም ውስጥ 87 በመቶ የሚሆኑት የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች እንደነበሩ ሌሎች ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገሪቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን እስከ 95 በመቶ የሚሆኑት ደቡብ አፍሪካ የደረሱት በሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች በኩል ነው፡፡
ሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች የሀገሪቷን ጠረፍ ከተሞችና መውጪያ ኬላዎች ይጠቀማሉ፡፡ከኢትዮጵያ በጅቡቲና በየመን አድርገው ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገቡበት አንደኛው የስደት መስመር ነው፡፡ ከኮምቦልቻ ተነስተው በ ሸዋሮቢት —- አዳማ—- አፋር—- ጂቡቲ —- የመን በማድረግ ወደ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎችም የአረብ ሀገራት ይገባሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ሶማሌ ላንድ፣ ቦሳሶ፣ የመን በኩል እንዲሁም በሶማሌ ላንድ በርበራ፣ የመን አቆራርጠው ሳዑዲ ፣ኩዌት፣ ኳታር እና ዱባይ የሚገቡም አሉ፡፡ ይህ የጉዞ መስመር የምሥራቅ መውጫ በሮችን የሚከተል ሲሆን፣ የሰሜን ምዕራብ መውጫ በሮችን የሚከተሉ ደግሞ ወደ እስራኤልና ጣልያን ይገባሉ፡፡ ይህም መነሻውን ከመተማ——ሱዳን——ሊቢያ——-አዉሮፓ (ጣሊያን ፣ ስፔን ፣ ግሪክ ፣ ማልታ እና ሌሎች የአዉሮፓ ሃገራት) የሚገባበት መስመር ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ የመግባት ፍላጎት ያላቸውም የደቡብ መውጫዎችን ያማትሉራ፡፡ ከሀድያ (ከምባታ) በመነሳት —- ሻሸመኔ —- ሀዋሳ——–ሞያሌ——ኬንያ —–ደቡብ አፍሪካ ይደርሳሉ ፡፡
በአፋር ክልል የጋላፊን መስመር በመከተል፣ ወደ ጅቡቲ የሚመላለሱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በትራንስፖርትነት በመጠቀም፣ ድንበር አካባቢ ሌላ ተቀባይ ደላላ በማዘጋጀት ጨለማን ተገን አድርገው በባጃጅ ይተማሉ ፡፡ መተማ ድንበር ላይ የሚገኙ ደላሎችም ጨለማን ተገን አድርገው ስደተኞቹን የሱዳንን ድንበር ያሻግራሉ፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ መግባት የሚፈልጉም የሞያሌን ድንበር አልፈው ኬንያ እንደሚገቡ፣ ሶማሌ ክልል የሚገኙ መውጫዎችን ተጠቅመው ወደ ጅቡቲና ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገቡም ብዙ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት የሚጀምረው ከምልመላ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ተጠቂዎች የሚጠመዱት የተሻለ ነገር እንደሚያገኙ ተደልለው እና የተሳሳተ መረጃ ተሰጥቷቸው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተጠቂዎቹ ለምን ጉዳይ ወይም ስራ እንደሚሄዱ ቢያውቁም ስለስራ ሁኔታው ትክክለኛ መረጃ አይኖራቸውም፡፡ ምልመላውም የሚካሄደው በቤተሰብ አባላት፣ በዘመዶች፣ በጓደኞች፣ በጎረቤቶች፣ በደላሎች፣ በኤጀንሲዎች ወይም በሌላ አካል ሊሆን ይችላል፡፡የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች ከተመለመሉ በኋላ ከተመለመሉበት ቦታ ወደ ሌላ ከተማ ወይም አካባቢ አንዳንዴም ወደ ሌላ አገር ይጓጓዛሉ፡፡ በዚህም ሂደት ዝውውሩን በማቀላጠፍ፣ አስፈላጊ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ በመንገድ ላይ ማረፊያ በማመቻቸቱ ረገድ የተለያዩ ሰዎች ይሳተፉበታል፡፡ አልፎ አልፎም ድንበር ጠባቂዎች፣ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ወይም የሕግ አስከባሪ አባላት በሂደቱ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ተጠቂዎችን የማዘዋወር ዋነኛው ዓላማ በተለያዩ መደበኛ ባልሆነ ስራ፣ የቤት ውስጥ ስራ እና የግዴታ ስራዎች ላይ በማሰማራት ተጠቃሚ መሆን ነው፡፡ ዋነኛ ዓላማቸውም ተጠቂዎችን በመበዝበዝ ትርፍ ማጋበስ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በመዳረሻ ቦታዎች ተጠቂዎችን በመቀበል እና የመታወቂያ ሰነዶችን በመቀማት በሚኖሩበት ቦታ በሕገወጥነት እንዲታዩ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ከደረሱ በኋላም ተጠቂዎች እንዳያመልጡ፣ ወደመጡበት ሀገር እንዳይመለሱ ወይም ሌላ ቦታ እንዳይኮበልሉ ያግቶቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አንፃር አዘዋዋሪዎች በአምስት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት ተጠቂዎቹ በሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ የአካባቢ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች በመጠቀም ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እና ተጋላጭ ግለሰቦችን በመለየት የዝውውር ሂደቱን የመጀመረ ሚና አላቸው፡፡ በሁለተኛው ምድብ ያሉት ደግሞ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ድንበር የሚያሻግሩ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች በማስተላለፍ በቅብብሎሽ ያደርሳሉ፡፡በሶስተኛ ደረጃ የሚገኙት ደግሞ በትላልቅ ከተሞች የሚንቀሳቀሱና ወደ መዳረሻ ቦታዎች በመደበኛ የጉዞ መስመሮች የሚደረገውን ጉዞ የማቀላጠፍ እና ቅጥር የማመቻቸት ሃላፊነት የሚወስዱ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች ከአካባቢ ደላሎች ሰዎችን ተቀብለው በመዳረሻ አገራት ለሚገኙ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህም ከሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር ተመሳሳይ ነገር ግን ህገወጥ የሆነ ስራ ይሰራሉ፡፡ በአራተኛው ምድብ የሚገኙት ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ ሌሎች ሰዎች እነሱ ወደነበሩበት አገር በመሄድ እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በግል ትውውቅ ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ የሚሹ ዘመድና ጎረቤቶችን ከማገዝ ባለፈ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመደበኛነት በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በመጨረሻ የምናገኛቸው በመዳረሻ አገራት የሚገኙ እና መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች በመዳረሻ ቦታዎች የሰዎች ዝውውር ላይ የተጠመዱ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እነዚህ አዘዋዋሪዎች በመዳረሻ አገራት የሚገኙ ደላሎች፣ የስራና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ወይም ቀደም ብለው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ተጠቂዎችን በማታለል፣ በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ለብዝበዛ በቀጥታ የሚያጋልጡ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜም በብዝበዛው ሂደት ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች ለተለያዩ ጉዳቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተው መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች በሚያደርጉት አደገኛ ጉዞ፣ በዝውውሩ ሂደት በአዘዋዋሪዎች እጅ የሚደርስባቸው ጥቃትና ብዝበዛ፣ በመዳረሻ አገራት የሚያጋጥማቸው አስከፊ የሥራ ሁኔታ ተደማምረው ተጠቂዎች የአካል እና የማህበረሰባዊ ጉዳት ሰላባዎች ይሆናሉ፡፡ ሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ወጣትነት ጊዜያቸውን ከቤተሰቦቻቸውና ከማህበረሰባቸው ርቀው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያሳልፋሉ፡፡ በመሆኑም የተሟላ ስብእና ለመገንባት የሚችሉበት ጊዜ ይባክናል፡፡ይህም ከሚደርስባቸው ብዝበዛና ጥቃት ጋር ተደማምሮ ለተለያዩ የስነልቦና ችግሮች ያጋልጣቸዋል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች ገቢያቸው ላይ የሚያሳድረው ጫናም ከፍተኛ ነው፡፡ ከመነሻው ሕገወጥ ደላሎች የሚጠይቁትና በማታለልም ሆነ በግድ የሚወስዱት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ተጠቂዎች ለከፍተኛ ዕዳ ይዳረጋሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ብዙውን ጊዜ ደመወዛቸውን በጊዜውና ሳይቀናነስ የማግኘት ዕድል ስለማይኖራቸው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም በቂ ገንዘብ አይኖራቸውም፡፡ አፍላ የወጣትነት ጊዜያቸውን ለአዘዋዋሪዎች ጥቅም ማሳለፋቸውም በዘላቂ ህይወታቸው ሰርተው የማግኘት ዕድላቸውን ያጠበዋል፡፡ ከሁሉም በላይ አስከፊ የሆነው እና በተጠቂዎች ላይ የሚደረሰው ችግር ግን በጤናቸው ላይ የሚደርሰው ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት የአእምሮ መታወክ፣ አካላዊ ጉዳት እና ሞት በተጠቂዎች ላይ በተደጋጋሚ ይደርሳሉ፡፡
ሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ህይዎት ለመታደግም ለተጠቂዎች ተገቢውን መረጃ በመስጠት እና የደርጊቱን ዋነኛ ተዋንያንን በማጋለጥ እና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ ድንበር ሲያቆርጡ ፣ በአውቶቡስ ተርሚናሎች፣ በኤርፖርቶችና በሌሎች መሰል የትራንስፖርት ማዕከላት አዘዋዋሪዎችና ተጠቂዎች ሊለዩ ይችላሉ፡፡ እንደሁኔታው በብዝበዛ ወቅትም ሰዎች የህገወጥ ዝውውር ሰለባ መሆናቸው ሊታወቅ ይችላል፡፡ ህብረተሰቡም ስለ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳት ከማስተማር እና ከማሳወቅ ባለፈ የህገወጥ ሰዎች ዝውውር ድርጊቶችን በምናይበት ጊዜም ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ህይወት ለመታደግ የድርሻችን መወጣት ይኖርብናል እላለው፡፡

Filed in: Amharic