>

እኔ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነኝ፤  የላቲን ፊደል የኛ እንዳልሆነና  የመጣበትንም ዓላማ ጠንቅቄ አውቃለሁ!!! (ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ)

እኔ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነኝ፤  የላቲን ፊደል የኛ እንዳልሆነና  የመጣበትንም ዓላማ ጠንቅቄ አውቃለሁ!!!

 

ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ

አዲስ ዘመን/ ዳንኤል ወልደኪዳን

 

የትውልድ አካባቢያቸው ጅማ ዞን ጋሌ ቡሳሴ ትባላለች፤ አንደኛ ደረጃን እዛው ተምረዋል። ወደ ጅማ ከተማ አቅንተው ሁለተኛ ደረጃን ከተማሩ በኋላ፤ ከጅማ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም በመምህርነት ሙያ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል በምህንድስና ሙያ፣ ከኒውጀኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ግሎባላይዜሽን እንዲሁም ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በMBA ተመርቀዋል። በአጫጭር ሥልጠናዎች በሰብዓዊ መብትና የጋዜጠኝነት ሥልጠና ወስደዋል። በሊሙ ገነት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በኦሮምኛ ቋንቋ አስተማሪነት፣ በጅማ ካቶሊክ ትምህርት ቤት በመምህርነት፤ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች(ኢሰመጉ) የምዕራብ ኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። በጅማ ማዘጋጃ ቤት በምህንድስና ሙያ፣ በሼር ኢትዮጵያ የሳይት መሀንዲስ እና የቴክኒካል ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።

በፖለቲካው መስክም ተሳትፏቸው ከፍተኛ ነው። የመኢአድና የቅንጅት የወቅቱ የጅማ ተወካይ፣ የብርሃን ለአንድነት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የአንድነት (የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት) አሁን የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በተጓዳኝም የኮንስትራክሽን ድርጅት አቋቁመው በመሥራት ላይ ናቸው። ከሰፊው የህይወት ልማዳቸው እንዲያካፍሉን የዘመን እንግዳ አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ!

አዲስ ዘመን፦ የልጅነት ህልምና አስተዳደግዎን እንዴት ያስታውሱታል?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ እኔ ከእናቴ ነው ብዙ ነገርን እየወረስኩ ያደኩት። እናቴ በአስተሳሰብ ከዘመኑ የቀደመች ነበረች። ምንም አልተማረችም ስሟን እንኳ መጻፍ አትችልም። ግን አስተሳሰቧ የተለየ ነበር። ሀገርህን የሚጠቅም ሥራ መሥራት አለብህ ትለኝ ነበር። እኔም መሀንዲስ መሆን መመኘት ጀመርኩ። እናቴ በችግር ነው ያሳደገችኝ። የትውልድ አካባቢዬ ጅማ ዞን ጋሌ ቡሳሴ ትባላለች፤ እልም ያለች ገጠር ናት። እስካሁን ድረስ ትራንስፖርት እንኳን የላትም። እኔና ጓደኛዬ ነን ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ይዘን የገባነው። እናታችን አረቄ ታወጣለች፣ ጠላ ትሸጣለች፣ እኔ በኩራዝ ነው የማጠናው። በሌሊት ተነስቼ አልባለሁ፣ ከብቶች አሰማራለሁ፣ ከዛ ተመልሼ ነው ወደ ትምህርት ቤት የምሄደው። ከትምህርት ቤት ስመለስ ከብቶች አስገባለሁ፣ የማታውን አልባለሁ። ሁልጊዜም ህይወት እንደቀለበት እየተሽከረከረች ትቀጥላለች። ሰባትና ስምንተኛን ክፍል ሊሙ ሻይ ተማርኩ። 9ኛ እና 10ኛ ክፍልን አጋሮ ተማርኩ። በትምህርቴም አንደኛ ነበር የምወጣው። ሚኒስትሪ ስፈተን በሀገር አቀፍ ሦስተኛ ደረጃ ነበር የወጣሁት።11እና 12ኛ ክፍልን ደግሞ ጅማ ተማርኩ።

አዲስ ዘመን፦ ልጅ እያሉ በትምህርት ቤት የተነገረችዎት ኢትዮጵያን ሲያድጉና ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀሉ እንደጠበኳት አገኟት?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ከ27 ዓመት ወዲህ ተበላሸችብኝ እንጂ እኔ እንደ ያኔው ነበር የማስባት። ቀድሞ የነበረው የትምህርት ሥርዓት በጣም ደስ ይል ነበር። እኛ ስንማር መጀመሪያ ቄስ ትምህርት ቤት እንማራለን፤ ጎን ለጎን ቁርዓን እንቀራለን፤ የሃይማኖት ልዩነት የሚባለውን ካደግን በኋላ ነው ያወቅነው። እኔ ቁርዓን ቀርቻለሁ ሙስሊም ጓደኞቼም ዳዊት ደግመዋል። 4ኛ ክፍል ስንደርስ ስለ ክፍለሀገራት ነበር የምንማረው ክፍለ ሀገራቱን ስናውቅ ስለመገለጫዎቹም ጭምር ነበር የምንረዳው። ኢትዮጵያን በሚገባ ተረድተን ነው ያደግነው። እናቴም ኢትዮጵያን እንድረከብ አድርጋ ነው ያሳደገችኝ። ‹‹የትምህርት አድማስ ግንባርህን ሳይመታው እንዳትመለስ›› ትለኝ ነበር። ትምህርት ምን ያህል ማለቂያ የሌለውንና የማይደረስበት እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። እነ አጼ ቴዎድሮስ እንዴት ለሀገራቸው ሲሉ ራሳቸውን እንደሰዉ፤ የአጼ ዮሐንስን፣ የአጼ ምኒልክን ታሪክ ማን እንደነገራት ባላውቅም በሚገባ ትተርክልኝ ነበር። ያኔ የሳልኳት ኢትዮጵያ መንግሥት ሲቀየር፤ በብሔር ብቻ ማሰብ ሲጀመር፤ ክልል በቋንቋ ሲከፋፈል የተምታታ ነገር ሆነብኝ። እኔ ኦሮምኛ ቋንቋን ጠንቅቄ አውቃለሁ። አማርኛም በሚገባ እችላለሁ። ሌሎች የምሰማቸው የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች አሉ። ቋንቋ ምንም ነገር ነው ብትለኝ አይገባኝም። ምክንያቱም የቋንቋ ሚና ማግባባት ብቻ ነውና።

አዲስ ዘመን፦ 2009ዓ.ም ላይ የታተመው ‹‹የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሣፍንት እና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ፈተና›› የተሰኘው መጽሃፍ መነሻው ምን ነበር?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሣፍንት እና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ፈተና መሳፍንታዊ አስተሳሰብ የመንደርተኝነት አስተሳሰብ ነው። ሁሉም በቀበሌው መሪ መሆን ይፈልጋል። ስለአንድነት አይታሰብም። አንድነት የሚመጣ ከሆነ ከሁለታችን አንዳችን ሊቀመንበርነቱን ቦታ ልናጣው ነው። የድሮዎቹ መሳፍንቶች እኔ የሠፈሬ አለቃ መሆን አለብኝ ብለው የሚዋጉ ነበሩ። ይህ ደግሞ እንደሀገር ለመቀጠል ከባድ ነው የሚሆነው። የኢትዮጵያ የመፈራረስ ስጋት በውስጤ ከተፈጠረ ቆይቷል። ኦሮሞን ገንጥለህ ሀገር አድርግህ ልታስቀምጠው የማትችልበት ዘመን ነው። ምክንያቱም ባሌ፣ ወለጋ፣ ሽዋ… እየተባባልን ተከፋፍለናል። ወለጋ እራሱ ምእራብ ወለጋ፣ ደቡብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ እየተባባልን ተከፋፍለናል። ወደ አማራ ብንመጣም ያው ነው። የጎንደር አማራ፣ የጎጃም አማራ፣ የሸዋ አማራ እየተባባልን ነው። ኢትዮጵያ የማን ናት? ከየት ነው የመጣችው? ብየ ቀደምቷን ኢትዮጵያን አስቀመጥኩ። ዘመናዊ መሳፍንቶች እነማን ናቸው? ቢባል ተቃዋሚዎች፣ አንዳንድ ዲያስፖራዎች፣ መንግስትና ምሁራን ናቸው። አንዳንድ ምሁራን መግለጫ ሲሰጡ ያሳፍሩኛል።እናንተ ጋዜጠኞችም እንደዛው ናችሁ። ጋዜጠኛ የተደረገውን ነገር በአግባቡ የሚያስቀምጥ እንጅ ነገሮችን የሚያራግብ መሆን የለበትም።

አዲስ ዘመን ፦ የአንባቢው ምላሽ እንዴት ነበር?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ምላሹ ጥሩ ነበር። በስልክ በፌስቡክ የሚያስፈራሩኝም ብዙ ነበሩ። አንተ ኢትዮጵያን የምትቆራርጠው ማን ሆነህ ነው? የሚሉት ሀሳቡን ከተረዱት በኋላ ይቅርታ የጠየቁም ነበሩ። ሽፋኑ ላይ ባዩት ነገር ብቻ የፈረጁት ብዙ ናቸው። ካነበቡት በኋላ ውስጡና ውጪ እንደሚለያይ የነገሩኝም ነበሩ። ብዙ ሰዎች የሽፋን ሥዕሉ ይቀየር የሚል አስተያየት ሰጥተውኛል። እኔም ተስፋ ያለው እንዲሆን አስቤያለሁ። ለምሳሌ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መሣፍንቶች ኢትዮጵያ ትቆራረጣለች የሚለው ስጋት ይህ ትውልድ ዶዘር ሆኖ ከመቆራረጥ ይታደጋታል የሚል ተስፋ እንዲኖረው አስቤያለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ሀሳቡን ግልጽ እናድርገው?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ዶዘር በሠራው መንገድ ላይ አይሄድም። ዛፉን የሚገነድሰው፣ መንገዱን የሚደለድለው የሚያስተካክለው ዶዘር ነው። መንገዱ ተስተካክሎ ከተሠራ በኋላ ግን ዶዘሩ ተጭኖ ነው የሚያልፈው። እኛም የምንሠራው ሀገር ልጆቻችን ተዝናንተው እንዲኖሩበት ነው ማሰብ ያለብን። የልጅ ልጆቻችን ደግሞ ይበልጥ ዘና ብለው የሚኖሩባት ሀገር ናት የምታስፈልገን። አሜሪካኖች አባቶቻቸው በሠሩላቸው ሀገር ነው ተዝናንተው የሚኖሩት። እንደዛ ያለ ሀገር ለመፍጠር ነው መሥራት ያለብን። በመሆኑም ሽፋኑን በስቲከር አስተካክዬ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ አደርጋለሁ።

አዲስ ዘመን፦ በመጽሐፉ ከተጠቀሱ ሃሳቦች መካከል የተወሰኑትን ማንሳት እንችላለን?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ መጽሐፌ ላይ የጻፍኩት ይች ሀገር የምትፈልገውንና መደረግ ያለበትን ነበር። ይህ ካልተደረገ ኢህአዴግ ሥልጣን ከእጁ እንደሚወጣና «እናንተ አጥፍታችሁ እኛንም እንዳትቀጡን» ነበር ያልኩት። ስንጠፋ አብረን ነው የምንጠፋው። ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ጭምር ነበር ያመላከትኩት። ከማን ምን ይጠበቃል? የሚለውንም ጠቃቅሻለሁ። ለምሳሌ ላቲን ፊደል ለምን እንድንጠቀምበት እንደተደረገ በድፍረት ነው የጻፍኩት። በወቅቱ አይነኬ የሆነ ሀሳብ ነበር። እኔ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነኝ። ነገር ግን ላቲን ፊደል የኛ እንዳልሆነ አምናለሁ። የመጣበትን ዓላማ ስለማውቀው በመጽሐፌ ላይ በዝርዝር ጽፌዋለሁ። በተጨማሪም ሰፊ ጥናት እንዲሠራም እፈልጋለሁ። ያለንን ነገር እንዳናውቅ እንጅ የኛ ቋንቋ ከነሱ የመግለጽ አቅም አንሶ አይደለም። ሳባ ፊደል የአማርኛ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፊደል ነው። የሳባ ፊደልን ብሄር ብሄረሰቦች አንድ ላይ ሆነው እንደመሰረቱት ነው የማምነው። በዓለም ላይ የራሳቸው ፊደል ያላቸው 6 ሀገራት ናቸው። አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ይሄ ደግሞ ኩራት አንጅ ውርደት ሊሆን አይገባም። በራሳችን የተጻፉትን ታሪኮቻችንን አንብበን እንዳንረዳ ነው ያደረጉን። ኦሮምኛም ቢሆን በሳባ ፊደል ቢጠቀም የበለጠ ለመረዳት ይጠቅማል እንጅ የሚጎዳው ነገር የለም። ይህን በመጻሀፌ ላይ በሰፊው አስፍሬዋለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ወደ ፖለቲካው የገቡበት አጋጣሚ ምን ነበር?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ እውነት ለመናገር እኔ እማወራው በእናቴ ሀሳብ ውስጥ ነው። እኔ በሷ የተሠራሁ እንስራ ነኝ። እሥራኤልን ከግብፅ ባርነት ነጻ ያወጣችው ሙሴ ሳይሆን የሙሴ እናት ናት። ልጇን በሥነ ሥርዓት ቀርጻ አሳድጋዋለች።‹‹ከፈርኦን ቤት የተንደላቀቀ ኑሮ ይልቅ ከእናቱ ቤት ችጋርን መረጠ ይላል›› እናቱ አርቆ የሚያስብ አድርጋዋለች። እሱ ሲደክም የተሻለ ሰው መርጦ ለእያሱ አስረከበው። እሥራኤላውያንን እርሱ እንደማያደርሳቸው ያውቅ ነበር። እንዲህ ያለ መሪ ነው እናቱ የፈጠረችው። እኔም እንዲህ አይነት መሪ እንደሚያስፈልገን ቀድሜ ነበር የጻፍኩት። ዶክተር ዐብይም እናቴ ናት የቀረጸችኝ ብሏል። በዓለም ላይ አባቶቻቸው የቀረጿቸው ሰዎች ታውቃለህ? ወንዶች የቀረጿቸው ሴቶች የሉም። እናቶች የሠሯቸው ግን በጣም ብዙ ናቸው።

አዲስ ዘመን፦ የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ኢንጅነር ዘለቀ ፦ ከ1995ዓ.ም ጀምሮ ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት። ጅማ ላይ የመኢአድ አባል ነበርኩ። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባል ስሆን ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ ጨፍልቆ እንዲገዛ አልፈልግም። ከነልዩነታችን አንድ መሆን እንችላለን ብዬ አምናለሁ። በ1997ዓ.ም ጅማ ላይ በነበረው ምርጫ የአንበሳውን ድርሻ ወስጃለሁ። በወቅቱ እኔ የመወዳደር ፍላጎት አልነበረኝምና የኛ ተወካይ እንዲያልፍ ጥረት አድርጌያለሁ። ከኋላ ሁኜ መሪ ማፍራት ነበር የምፈልገው። የህብረተሰቡ ፖለቲካ ብስለት ማነስና የኛም ችኩልነት ታክሎበት የ1997 ምርጫ የብዙ ሰው ልፋት ከንቱ ሆነ። ለ2002ዓ.ም ምርጫም ብርሃን ለኢትዮጵያ የሚባል ፓርቲ ተመሰረተ። የተበታተነ ትግል የትም አያደርሰንም የሚል እምነት ስለነበረኝ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጋር ተዋሃድን። በወቅቱ ፓርቲው ውስጥ ለሥልጣን ሳይሆን ለሀገር የሚያስቡ ሰዎች ነበሩበት። ወደ አንድነት ፓርቲ ስንገባ የተሻለ ሰው ይምራ ብለን ነበር። አሁንም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ።

አዲስ ዘመን ፦ በፓርቲዎቹ ቆይታዎ ስለሀገራችን ፖለቲካ ምን ታዘቡ? ምንስ ተማሩ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ብዙ ሰው ወደ ፓርቲ ትግል የሚገባው ሥራ ፍለጋ ነው። በአጠቃላይ ስናየው ድህነታችን ነው ነጻ ያላወጣን። ከዳያስፖራው ጋር ትተሳሰርና ጥቅም መፈለግ አለ። ዳያስፖራው ውጭ ሀገር 100 ሺ ዶላር ከሰበሰበ ሰማኒያውን ያስቀርና ሃያውን ይልካል። እዚህ ያለውም የተወሰነውን ያስቀርና በቅርንጫፍ ላሉት ያከፋፍላል። አሁን ግን የፓርቲዎችን ነገር ህዝቡ ስለነቃባቸው አካሄዳቸው የትም አያደርሳቸውም። ከዚህ በኋላ የተሻሉ ሰዎች ወደፊት እንደሚመጡ አምናለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በኋላ በዶክተር ዐብይ ልክ እንኳ ሰው አይፈልግም። ከእርሱ የተሻለ ነው የሚፈልገው። አሁን ገበሬው ሳይቀር የሚናገረው ፖለቲካ የሚገርም ነው። መብትና ግዴታውን ብቻ ማወቅ ሳይሆን የወደፊቱም እያሳሰበው ነው የሚናገረው። ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻግር የሚችል ሀሳብ ያለው መሪ ነው የሚፈልገው።

አዲስ ዘመን፦ሰሞኑን 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል ምን ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ አንድ ፓርቲ አለ የሚባለው ምን ሲያድርግ ነው? ጠቅላላ ጉባኤ አለው ወይ? ማዕከላዊ ኮሚቴ አለው ወይ? የአባላት ብዛቱ ምን ያህል ነው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። ባለ አንድ አባል ፓርቲዎች አሉ። ሊቀመንበር፣ ሥራ አስፈ ፃሚ የሆኑ አሉ። ይህን ማስተካከልና ትክክለኛ ፓርቲዎች መኖራቸውን መቆጣጠር ያለበት ምርጫ ቦርድ ነው። 107 የተባሉት ፓርቲዎች ቢጣሩ107 ሳይሆን በትክክል መቆም የሚችሉት 15 ላይሆኑ ይችላሉ። መስፈርቱን የማያሟሉትን እንዲያሟሉ ማድረግ ካላሟሉ ፈቃድ እስከመሰረዝ መሄድ አለበት። ፓርቲዎቹ በዛችሁ ተዋሃዱ ማለት ብቻ ሳይሆን መደገፍና የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸትም ይገባል። አንዳንዶቹ ፓርቲዎች አመሰራረታቸው ለመተዳደሪያ ነው። እንደ ገቢ ምንጭ ነው የሚቆጥሩት። ወደ ትክክለኛው የትግል ፓርቲ እንዲመጡ መንግሥት ሊያግዛቸው ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ እንደፖለቲከኛ አሁን ባለው የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ምን አስተዋሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ አሁን የማየው ነገር ጨለማ እየሆነብኝ ነው። መንግሥት የገባውን ቃል እየተወጣ አይደለም። መንግሥት የሚባለው አካል የተፈጠረው ህዝብ ከራሱ መብት ቀንሶ የአስተዳደሩን ሥራ እንዲሠራለት የሚሰጠው አካል ነው። ይሁን እንጅ አሁን በተለያዩ ቦታዎች በምናየው ሁኔታ መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም። ለምሳሌ እርስ በራሳቸው እየፈጠሩ ባሉት ግጭት በህብረተሰቡ መካከል ፍቅር እንዲጠፋና አንዱ አንዱን እንዲያጠቃ እያደረጉ ነው።

ብታወጡትም ባታወጡትም እውነቱን መናገር አለብኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጌዴኦ ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸው ከመንግሥት ፈፅሞ የሚጠበቅ አልነበረም። ምክንያቱም አንተ የምታስተዳድረው ከተበላሸ ማን ሊያስተካክለው ይችላል። በመንግሥት አስተዳደር ስር ሆነው ያፈናቀሉትን ህዝብ ሄዶ መጎብኘት ተገቢ አልነበረም። የመንግሥት ሥራ እንዳይፈናቀሉ ማድረግ ብቻ ነው። ህግ ማስከበር ነው ያለበት። ይህ አካሄድ ህዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ የሚያደርግ ነው። ማንም ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባቱ ዋስትና እያጣ ነው።

መንግሥት ለሚያስተዳድረው ህዝብ እርዳታ ይለምናል። ይሄ በጣም ነው የሚያሳፍረው። ህዝባችን መረዳት ስላለበት እንሳተፋለን እንጅ ለኛ ውርደት ነው። አማራው ተወልዶ ባደገበት ቦታ ይፈናቀላል፤ የጌዴኦ ህዝብም እንዲሁ ተወልዶ ባደገበት ቦታ ነው የተፈናቀለው። ሌላውም በራሱ ህዝብ ነው እየተፈናቀለ ያለው። የሌላ ሀገር ወራሪ ያፈናቀለው ሲሆን ተሸንፈን ነው ብለን እናምን ነበር። ህወሓት በራሱ መንገድ እየሄደ ነው፣ አዴፓ በራሱ መንገድ ይጓዛል፤ ኦዲፒ በራሱ መንገድ እየተጓዘ ነው፤ ደኢህዴንም እንደዛው። እርስ በርስ ተጣምረው አንድ ፓርቲ መሆን ሲገባቸው አንዱ አንዱን ጥሎ የበላይ ለመሆን ነው ሲጥሩ የሚታየው። ይህ ደግሞ ለሀገር አይበጅም። ለእነርሱም አይጠቅመም። ኢህአዴግ በውስጡ ካሉት ፓርቲዎች ጋር ቁጭ ብሎ ባልተነጋገረበት ሁኔታ ለመፎካከር የመጡትን ፓርቲዎች ተዋሃዱ ለማለት ያስቸግራል። መንግሥት እራሱ ነው አርአያ መሆን ያለበት።

አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ኢንጅነር ፡ ኢትዮጵያ አሁን ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋታል። ማስቀደም ያለብን ሰላሟን መመለሱ ላይ ነው። ኢትዮጵያውያን ራሳቸው የሠሩትን ቤት «ቤት የእግዚአብሔር ነው» ብለው ነው የሚያምኑት። ይሄ ነው ከሌላው የሚለየን።

የሁላችን የሆነችውን ከተማ የማን ነች? ብሎ ጥያቄ የሚያነሳው እራሱ የመንግሥት ድክመት አንዱ ማሳያ ነው። እስከዛሬ ድረስ የምናውቀው እኔ ከጅማ ነው የመጣሁት፤ ሌላው ከማርቆስ፣ ሌላው ከጎንደር፣ሌላው ከወለጋ፣ ሌላው ከባሌ፣ ከሀዋሳ… ነው የመጣው። አዲስ አበባ ውስጥ ከየት ነው የመጣኸው? ተብሎ ተጠይቆ አያውቅም። አቅም ያለው ቦታ ገዝቶ ቤት ሠርቶ፤ የሌለው ተከራይቶ የሚኖርበትን ከተማ እንዴት የእኔ ነው ይባላል?

አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማነት አልፋ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ከተማ በሆነችበት ጊዜ የማናት? ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም የማንም መሆን አትችልምና! ኢትዮጵያ ውስጥ ያለነገር በሙሉ የሁላችንም እንደሆነ ስናስብ ነው ኢትዮጵያዊነት የሚሰማን። አዲስ አበባም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ላቡን አንጠፍጥፎ የሠራት ከተማ ናት። ለዚህ ችግር ተጠያቂው መንግሥት ነው። እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ሲነሱ በህግ አግባብ መልስ ሰጥቶ የህግ ተጠያቂነት ማምጣት ይገባው ነበር። በዓለማችን ላይ የፈረሱ ከተሞችን ማሰብ ተገቢ ነው። ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ የሚባሉ ከተሞች ፈራርሰዋል። ከእነርሱ ትምህርት ልንወስድ ይገባል። በሚያስማሙን ነገሮች ላይ መሥራት ሲገባን የሚያለያየንን እየመረጥን የምንሠራው ነገር ተገቢ አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች። አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታም በተስፋና በፈተና መካከል ላይ እንደሆነች ያሳየናል። ፈተናውን ለማለፍ ምን ማድረግ ይገባል ይላሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ በመጽሐፌ ላይ ጠቅሼዋለሁ። ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ወርቃማ እድሎች አጋጥመዋታል። በዛው ልክ ወርቃማ የሆኑትን እድሎች ሳትጠቀምባቸው አምልጠዋታል። ሀገሪቱ የእግዚአብሔር አገር በመሆኗ ያመለጣትን እድሎች ለከፍተኛ ውድቀት አልዳረጋትም። አሁንም ጥሩ እድል ነበር የገጠመን ይሁን እንጅ አሁንም በአግባቡ እየተጠቀምንበት አይመስለኝም።

አዲስ ዘመን- ለምሳሌ ምኑን ነው ያልተጠቀምንበት?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ አሁን በዶክተር ዐብይ ዙሪያ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጅ በዙሪያው ያሉት ሰዎች አጭር እይታ እንዲኖረው እያደረጉት ይመስለኛል። እነሱን ብቻ እንዲያይ ጋርደውታል። ቁመታቸውን ዘለግ ዘለግ አድርገው ሌሎች ብዙ ሰዎችን ጋርደዋል። ሀገራችን ላይ ብዙ የተደበቁ ቅን ሰዎች አሉ። በእምነት ተቋማት፣ በማህበራት፣ በእድሮች ሳይቀር ብዙ ለሀገር አሳቢ የሆኑ በእውቀትና በቅንነት የታነጹ ሰዎች አሉ። ከመጥፎ ጥገኝነት እራሳቸውን ባላቀቁ ሰዎች ዶክተር ዐብይ የሚታገዝ ከሆነ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይችላል። ማገዝ ሲባል ድንጋይ ማቀበል ሳይሆን ሁሉም በተሰማራበት ሙያ በቅንነትና በታማኝነት ከሠራ አገዘው ማለት ነው። አሁን አንተ በተሰማራህበት በታማኝነት ከሠራህ በተለይም የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ተሻለ ቦታ እንዲመጡ፤ እንዲሁም ችግር ያለባቸው ከሥራ ይልቅ በቲፎዞ ወደፊት የመጡትን በማጋለጥ ልታግዘው ትችላለህ። ችሎታ የሌላቸው ሰዎች በዙሪያቸው ከእነርሱ ያነሱትን ብዙ ሰዎችን ይሰበስባሉ። በርግጥ ፈተናው ከባድ እንደሚሆን ቢታመንም ይህን ማጋለጥ የሚዲያው ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፦ ዶክተር ዐብይ ወደሥልጣን ከመጡ አንድ ዓመት ሊሞላቸው ነው በእነዚህ ጊዜያት ምንያህል የሀገሪቱን ችግር ፈተዋል ብለው ያምናሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ በዶክተር ዐብይ ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሃይማኖትም ይሁን በፖለቲካ የመጀመሪያ ሥራቸው መሆን ያለበት ራሳቸውን በማንቃት ህዝብን ማንቃት ነው። ከእነርሱ የተሻሉ ሰዎችን ወደፊት እንዲመጡ በማድረግ ሊሆን ይገባል። ዋናው ነገር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር በመሆኑ መተባበር ነው የሚገባው። ዶክተር ዐብይ የተሸከመው ኃላፊነት እጅግ በጣም ብዙ በመሆኑ ከብዶታል። ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ነው እንደሚባለው ሁሉ የዐብይን ሀሳብ በሚገባ የተረዱ ሰዎች እስከ ቀበሌ ድረስ ካሉ ሥራው ሁሉ ቀበሌ ላይ ያልቃል ማለት ነው። ወረዳ፣ ዞንና ክልል ላይም ሥራዎችን እዛው የሚጨርሱ ሰዎች ካልተፈጠሩ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። አሁን ግን ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው ዙሪያውን ከበው አስፍቶ እንዳያይ ያደረጉት። ሁሉን ችግር ዶክተር ዐብይ እንዲፈታው እየተጠበቀ ነው። ይህ መቀጠል የለበትም። አብዛኛው ሰው ወዳለፈው ሥርዓትና አስተሳሰብ መመለስ አይፈለግም። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደወላድ አይደለም። እናት ስትወልድ የደረሰባትን ስቃይ ካለፈችው በኋላ ምጡንና ስቃዩን ረስታ ድጋሚ ለመውለድ ትፈልጋለች።

የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ወዳለፈው ነገር መመለስ አይፈልግም። እኛ ባለፈው ሥርዓት ምንም ደስታ አልነበረንም። ጥቂት ሰዎች ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸውን ጠቅመው ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እንደምናውቀው ከድህነት አልወጣም። ራሳቸው ሰርቀው ልጆቻቸውን ስርቆት ያስተማሩ የዘቀጠ ሰብዕና ያላቸው ሰዎችን አይተናል። ያ ጊዜ እንዲመለስ የሚፈልግ አይኖርም። ስለዚህ ዶክተር ዐብይ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች መፈተሽ አለበት። ከተሠራው ይልቅ የፈረሰው እየበዛ ይመስለኛል።

አዲስ ዘመን- መፍትሄው ምን መሆን አለበት?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ዋናው ነገር መፍትሄው ላይ መሥራቱ ነው። መፍትሄው ምንድን ነው ከተባለ፤ አንደኛ በዐብይ ዙሪያ ጋርደው የቆሙትን ሰዎች ማንነት ማጋለጥ። ይህን ለማድረግ የሚዲያ ሰዎች መፍትሄ አፈላላጊ መሆን ይኖርባችኋል። በተለያዩ ሙያዎች ላይ ፎረሞችን በማዘጋጀት ብቃት ያላቸው ሰዎች እንዲታዩና ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ አለባችሁ። ዶክተር ዐብይ በሁሉም ሙያ ላይ ዕውቀት ሊኖረው አይችልም። እውቀትና ብቃት ያላቸውንም ሰዎች ማወቅ አይችልም። ስለዚህ ሚዲያው ብቃት ያላቸውን ሰዎች ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ አለበት። ወደ ግብርና ሚኒስቴር የሚመደቡ ሰዎች በፖለቲካ እውቀታቸው ሳይሆን በሙያው ያለፉ፣ ችግሩን የሚያውቁ፣ እንዲሁም አርሶ አደሩን በማገልገላቸው የሚረኩ ሰዎች መሆን አለባቸው። ትምህርት ሚኒስቴርም እንዲሁ ለሙያው ቅርብ የሆኑትን መምረጥ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከሚዲያው የተሻለ አማራጭ ሊኖር አይችልም።

አዲስ ዘመን፦ ከእርስዎን ዘመን ጋር ሲያነጻጽሩት አሁን ያለው ወጣት ለሀገር ያለው ፍቅር እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ አሁን አሳፋሪ ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማኛል። ወንድም ወንድሙን የሚገድለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ተማሪዎች እውቀት ላይ ከሚያደርጉት ፉክክር ይልቅ በብሔራቸው፣ በአካባቢዎቻቸው ተቧድነው የበላይነታቸውን ለማሳየት እየተጋደሉ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ብዙ ሊሠራ ይገባል። በተለይም ወላጆች ላይ መሥራት ይገባል። የእናቶችን ተደማጭነት በመጠቀም የልጆቻቸውን ባህሪ እንዲገሩ ማድረግ ይቻላል። የእናቱን ትዕዛዝ የሚቃወም አይኖርም። ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ የላኩትን እናቶች በመሰብሰብ ችግሩን በማስረዳት የመፍትሄው አካል ማድረግ ይገባል። እናቶች በየጊዜው እየሄዱ ልጆቻቸውን ሊመክሩ ይገባል።

በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ሰዎችም ከግል አመለካከታቸውና ጥቅማቸው ወጥተው ለትውልድና ለሀገር ማሰብ አለባቸው። ሁሉም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ማሰብ አለበት። አገሪቱ በጋራ የምትለማ፤ የጋራ ሀገር መሆኗን ማስተማር ይገባል። አንዱ ግብር ከፋይ ሌላው ግብር ተቀባይ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ሁሉም ለሀገሩ እኩል ግብር ከፋይ እኩል ተጠቃሚ መሆኑን ማሰብ ካልቻለ መጨረሻው አያምርም። አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ መሆን የለበትም። ይህን አስተሳሰብ ለማምጣት ትንሽ ሥራ ነው የሚፈልገው። ግን ዝም ብሎ ኢትዮጵያ፣ ኢትየጵያ ማለት ለውጥ አያመጣም። ኢትዮጵያ ቅብ ነው የሚሆነው። አሁን እንደምናየው ብዙ ሰው ኢትዮጵያ ቅብ ነው። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ያወራና ብዙም ሳይቆይ ወደ ብሔሩ፣ ወደ ጎሳው ይደበቃል።

አዲስ ዘመን፦ ይህ ችግር ከምን የመጣ ይመስልዎታል?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ችግሩ የተፈጠረው ካሳለፍነው የትምህርት ሥርዓት ነው። የዚህች ሀገር ችግሮች በአንድ ጊዜ የተፈጠሩ አይደሉም። አሁን እኮ ሲቪል ኢንጅነሪንግ ተምረው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ አሉ። ሥርዓተ ትምህርቱም ሆነ የማስተማር ዘዴው በራሱ መፈተሸ አለበት። መምህርነት ሥራ ለማግኘት የሚሠራ መሆን የለበትም። ሁሉም ሙያውን አምኖበት መሥራት አለበት። ኢንጅነሪንግ ያጠና ኬጂን ሲያስተምር ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም። በሀገሩ ላይ እየተማረረ የሚያስተምር መምህር ምን ሊፈጥር እንደሚችልም ይታመናል። ወጣቱ በዘረኝነት አስተሳሰብ ብቻ አይደለም የተመረዘው። በአቋራጭ የመክበር አባዜ ተጠናውቶታል። አሁን ብዙ ቦታ ስትሄድ ፋይልህን ሳይሆን እጅህን ነው የሚያዩት።

አብዛኛው ቢሮ ስትሄድ ታፍራለህ። ብዙ የሥራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ተስፋ ቆርጠው ተቀምጠዋል። ጋዜጠኞችም እንደነዚህ ያሉትን ችግሮች ለማጋለጥ አትደፍሩም። አሁን የትኛውም ማዘጋጃ ቤት ብትሄድ የምታገኛቸው ወጣቶች ለመሥራት ዝግጁ አይደሉም። ሥራ በመጎተት ሰውን ሲያማርሩ ነው የምታየው። አለቆቻቸው ጋር ብትሄድም ሥራ በዝቶበት ነው በማለት እነሱን ለመሸፈን ነው የሚጥሩት። ምክንያቱም ሠራተኛውና አለቃው የጥቅም ግንኙነት አላቸው።

አዲስ ዘመን፦ የጎበጠውን አስተሳሰብ ለማስተካከል ምን ይደረግ ይላሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ የጎበጠውን ለማቃናት ተደጋጋሚ ሥልጠናና ውይይት ያስፈልጋል።ደረቅ ውይይት መሆን የለበትም። ከእወነተኛ የሕይወት ልምድ የሚቀዳ እውነተኛ ልምድ ነው ሰውን የሚያስተምረው። እንዲሁም የሌሎች ሀገራትን ልምድ በማካፈል ማስተማር ይገባል። የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ልምድ ከፒኤችዲ ይበልጣልና እሱን በመጠቀም ማስተማር ይቻላል። ከባድ የሚሆነው ከጎበጠው ይልቅ የደረቀውን ማቃናት ነው። ምክንያቱም ላቃናው ስትል ልትሰብረው ትችላለህ። ብዙ መልፋት ያስፈልጋል። ከታች ያለውን ግን አስተካክሎ ማሳደግ ቀላል ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፦ ዛሬ ላይ ዘግናኝ የሆኑ ሙስናዎች እየሰማን ነው። ይህ የሞራል ዝቅጠት ምክንያቱ ምንድነው ብለው ያስባሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦አንዳንድ ጊዜ ሳስበው የምናየውና የምንሰማው የሙስና ታሪክ ያስደነግጣል። በዛው ልክ የሙስናውን አፈጻጸም ሥልጠና እየተሰጠ የሚሠራ ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ ለሙስና አጣሪዎቹ ገንዘብ ማገኛም ዘዴ እየሆነ ነው። እኛኮ ብዙ ነገር አሳልፈናል። ምንም ህጋዊነት ሳይኖራቸው ህጋዊ መስለው ብዙ አጭበርብረውናል። ደረሰኝ ያቀርባሉ ከቀናት በኋላ የገዛንበት ሱቅ ተመልሰን ስንሄድ ተዘግቶ ይጠብቅናል። ስንገዛ የነበረው በሐሰተኛ ደረሰኝ ነበር። እነርሱው በሐሰተኛ ደረሰኝ ገዝቷል ብለው መልሰው ይከሱናል። እዛው ውስጥ ያሉት ሰዎች አዳራዳሪ ሆነው ይመጡብሃል። መታሰር ስለማንፈልግና ልጆቻችንን ማሳደግ ስላለብን ሳንወድ በግድ ለድርድር እንቀርባለን። የሙስና ጉዳይ አስቸጋሪ ሆኗል። ግን ደግሞ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። መጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት ምንጩን ማድረቅ ነው። ነጋዴ ግብር ሲጠራቀምበት ነው ግብር ለመክፈል የሚቸገረው።

በየጊዜው ከሚያገኛት ትርፍ መክፈል የሚችልበት አሰራር ቢዘረጋለት ምንም ሳይመስለው ይከፍል ነበር። አንድ ነጋዴ በዓመት አምስት መቶ ሺ ብር ከሚከፍል በየወሩ 5ሺ ብር ቢከፍል ይመርጣል። በሌሎች ሀገራት ግብር መክፈል በሁለት እግር ቁሞ እንደመሄድ ነው የሚቆጠርው። ይህ ድንገት የተፈጠረ አይደለም። ሲስተም ስለሆነለት ነው። በማስፈራራት ምንም ማድረግ አትችልም። እኔ ኮንትራክተር ነኝ አንድ ሚሊዮን ብር ኮንትራት ስፈራረም ስንት መክፈል እንዳለብኝ ቀድሜ ማወቅ አለብኝ። ሙስና ሊጠፋ የሚችለው ሥርዓት በመዘርጋት እንጅ በሥልጠና አይደለም። ቀን አሠልጥነው ማታ ሙስና የሚሰሩት እራሳቸው ናቸው። ማህበራዊ ሚዲያው ለሙሰኛው እየጠቀመው ነው። አንዱን በሙስና ሲጠየቅ ሃሳቡን ይገለብጥና ከብሔር ጋር አያይዘው የሚዘምቱት በማህበራዊ ሚዲያ ነው። አሁን ክልሎች ላይ መሥራት ከባድ እየሆነ ነው። አንድ ሰው ተነስቶ መኪናህን አቁምና ውጣ ሊልህ ይችላል።

አዲስ ዘመን፦ ማህበራዊ ድረገጽን እንዴት ለመልካም ነገር እንዲያገለግል እናስተካክለው?

ኢንጅነር ዘለቀ ፦ ልጄ ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ነው የሚማረው። በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ይህችን ሀገር ያግዛል ብዬ ተስፋ እጥልበታለሁ። እናቴ እኔን ተስፋ አድርጋለች፤ እኔም ልጄን ተስፋ አደርጋለሁ። ሀገርን የሚጎዳ ሀሳብ ሲተላለፍ የሚያግድ ሶፍትዌር እንዲፈጥር እፈልጋለሁ። እስካሁን በማህበራዊ ሚዲያ ከተጠቀምነው ይልቅ የተጎዳነው ይበልጣል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ነገር ብቻ እንድንጠቀምበት እፈልጋለሁ። ይህ የሚሆነው ደግሞ በመከልከል ሳይሆን በራሱ በቴክኖሎጂው ይሆናል ብዬ አስባለሁ። አሁን ፌስቡክ ላይ ንግድ ተጀምሯል። ብዙ ሰው በጎበኘው ቁጥር የሚከፈሉት ነገር ያለ ይመስለኛል። ምንም ነገር አድርገው ብር ለማግኘት ብቻ የሚተጉ ሰዎች ተበራክተዋል።

የዛሬ 20 ዓመት የሆነ ሀገር ላይ የተፈጠረ ምስል አውጥተው አሁን እንደተደረገ አድርገው የሚያቀርቡ ህሊና ቢሶችም ተበራክተዋል። ሞራል የሌለው ትውልድ ስለገነባን የሚጠበቀው ይህው ነው የሚሆነው። የሚያሳፍረው መንግሥት ራሱ ሥልጣኑን ለማቆየት ደመወዝ እየከፈላቸው ኢንተርኔት ላይ ተቀምጠው የሚሳደቡ፤ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱ፤ የጥላቻ መልዕክት የሚያስተላልፉት ብዙ ነበሩ። ብዙዎቹን በስም መጥቀስ ይቻላል። ኢትዮ ቴሌኮም እየከፈላቸው የጥላቻ መልእክቶችን ሲፈበርኩ የነበሩትን ግለሰቦች አይተናል። አገርን እንዲያጠፉ መክፈል የመዝቀጣችን ማሳያ ሊሆን ይችላል። ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ መንግሥት መውሰድ ያለበት እርምጃ ወሳኝ እንደሆነ ማሰብ አለበት። ካልሆነም በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚገኘው መረጃ ጥንቅር ብሎ ይቅርና መዘጋትም ካለበትም መዘጋት አለበት። የዶክተር ዐብይ መንግሥት እጁ ላይ የገባው እድል ሳያመልጠው ፈጥኖ መሥራት አለበት። ሌሎች ሀገራት እንዴት እንደተቆጣጠሩት ማየት ይገባል። አሁን በዶክተር ዐብይ ዙሪያ በኦሮሚያና በአማራ አካባቢ ሆነው ሀገርን እያበጣበጡ ያሉ ሰዎች አሉ። እርሱ ከሚያውቀው በላይ ህዝብ ነው የሚያውቃቸው። ከህዝብ የሚመጡ ጥቆማዎችን መሰረት አድርጋችሁ ማጋለጥ ያለባችሁ ደግሞ እናንተ ሚዲያዎች ናችሁ።

አዲስ ዘመን፦ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ደርሳ ማየት ይመኛሉ?

ኢንጅነር ዘለቀ፦ ከሦስት ዓመት በፊት የጻፍኩትን ብታይ ትገረማለህ። ኢትዮጵያ ሆና ማየት የምፈልገውን ሆና እንደማያት እርግጠኛ ነኝ። በቅርብ ጊዜ ትልቅ ሆና አያታለሁ። ልጆቿ ከመሰደድ ስደተኞችን ወደ መቀበል ይሸጋገራሉ። በትንሽ ማሳ ላይ ብዙ የሚያመርት ገበሬ፤ እርዳታ የማይቀበል ዜጋ፤ ልጆቿ ምላሳቸው ሳይሆን ደማቸው ኢትዮጵያዊ የሆነ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲባል የአንድ አካባቢን ባህልና ቋንቋ የበላይ አድርጎ ማሰብ ሳይሆን ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ እንድትሆን እፈልጋለሁ። ሁሉም እኩል የሚያስባት፤ ኢትዮጵያን በቅርቡ እናያታለን። ሥራዎች ሁሉ የመንግሥት ነው ብለን ካልተቀመጥን፤ ተባብሮ መሥራት ከቻልን ኢትዮጵያችንን ማሳደግ እንችላለን። የምንአገባኝ መንፈስ መወገድ አለበት። ሁላችንም ለኢትዮጵያችን ያገባናል። አሁን የፓርቲ ፉክክርም አያስፈልገንም። መጀመሪያ ኢትዮጵያችንን ከፊት እናስቀድማት። የምንፎካከርበትን ቦታ እንፍጠር። ዝንጀሮ እሾህ ተወግታ የትኛውን ልንቀልልሽ ስትባል መጀመሪያ የመቀመጫዬን ነው ያለችው። እኛም መጀመሪያ ኢትዮጵያችንን እናስቀድም። ከዛ በኋላ ዶክተር ዐብይን ካልፈለግነው ውረድ እንለዋለን። ዘላለም ግዛቱ አይደለም። የሚተካውም ይመጣል፤ እርሱም ካልቻለ ይወርዳል። ዋናው ነገር ሥርዓት ማበጀት ነው። ሥርዓት ከተዘረጋ በመቀባበል ሀገራችንን ማሳደግ እንችላለን።

አዲስ ዘመን፦ ሀሳብዎን ስላካፈሉን በዝግጅት ክፍላችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ!

ኢንጅነር ዘለቀ፦ እኔም አመሰግናለሁ!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011

ዳንኤል ወልደኪዳን

Filed in: Amharic