>

"የተሰራ አእምሮ የፈረሰ አገር ይገነባል፤ በአንጻሩ ያልተሰራ አእምሮ የተገነባ አገር ያፈርሳል!!!" (ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ) 

“የተሰራ አእምሮ የፈረሰ አገር ይገነባል፤ በአንጻሩ ያልተሰራ አእምሮ የተገነባ አገር ያፈርሳል!!!”
ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ 

ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ይባላል። የተወለደው ቄሌም ወለጋ ነው። የአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም የተከታተለው በእዛው በትውልድ ስፍራው ነው። የመጀመሪያ ዲግሪውን በታሪክ ትምህርት ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። ሁለተኛ ዲግሪውን በመንግሥት እና ልማት ጥናት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል።

በሥራ አመራርና በሰው ኃይል አስተዳደር ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎችን ተቀብሏል። በተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች አስተምሯል። ሊድ ስታር የተባለ ኮሌጅን በጀኔራል ማናጀርነት ለሦስት ዓመት መርቷል። አምስት መፅሐፎችን የፃፈ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በቅርቡ የታተመው «ከጥቂቶቹ አንዱ መሆን» የሚለውና ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ ያለ መፅሐፍ ነው።በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የማነቃቂያ ንግግሮችን ያደርጋል።

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማማከር እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ከረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ!

አዲስ ዘመን፡- በርካታ ትምህርቶችን ተምረህ እስከ ረዳት ፕሮፌሰርነት ደርሰሃል፤ በርካታ መፅሐ ፍትንም ፅፈሃል እዚህ ለመድረስ ያስቻለህ ብርታት ምን ነበር?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- በእኔ እምነት ለእድገት ሁለት ነገሮች ወሳኝ ናቸው። አንደኛው ፈጣሪ ማንኛውም ሰው አድጋለሁ ካለ ያሳድገዋል። ሁለተኛው ደግሞ እኔ ራሴን ካልጣልኩ ማንም አይጥለኝም የሚል ነው። አንዱ በር ሲዘጋብኝ ሌላ በር እንዳለ ማሰብ እችላለሁ። እኔ ለዚህች አገር ሸክም ለማንሳት እንጂ ሸክም ለመሆን እንዳልተፈጠርኩ አምናለሁ።

በህይወቴ በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሙኝም ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር ስለማላውቅ የምፈልገውን ለማሳካት ችያለሁ። የመጀመሪያ ዲግሪዬንና ማስተርሴን የተማርኩት ልጆችን እያስጠናሁ ነው። የምኖረውም ከማስጠናት በማገኛት አነስተኛ ገንዘብ ስለነበር አንድ ብር እንኳን ያጣሁባቸው በርካታ ጊዜያት ነበሩ። ያ ግን ለችግር እጄን እንድሰጥ አላደረገኝም። ምክንያቱም የተሻለ ህይወት መኖር አለብኝ የሚል ፅኑ እምነት ስለነበረኝ።

ደግሞም ማንነቴን በሚገባ አውቃለሁ። የቱ ጋር መቀመጥ እንዳለብኝ ጭምር። በጣም የሚገርመኝ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለምን እንዳልተማሩ ሲጠየቁ የሚያነሱት ምክንያት «ድሃ ስለሆንኩ፣ የሚያስተምረኝ ዘመድ ስለሌለኝ፣ ገጠር ስለተወለድኩ» የሚል ነው። በእኔ እምነት እነዚህ ምክንያቶች ተቀባይነት የላቸውም።

ከዚያ አልፈን መሄድ እንችላለን። ብዙዎቻችን ችግርን ብቻ ነው የምንገልፀው። ግን ችግርን አሳምረን ስለገለፅነው መፍትሄ ልናገኝ አንችልም። ችግርን በቅላፄም፣ በዝማሬም፣ በግጥምም ስለገለፅነው መፍትሄ አናገኝም። ችግር ያው ችግር ነው። እኔ ለሰፈር ብቻ የምበቃ ሰው መሆን እንደሌለብኝ ስለማምን ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት የሚል እምነት አለኝ። ደግሞም ገና ብዙ ነገር እንደሚጠብቀኝ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡– አሁን በመንግሥት ተቋም በከፍተኛ አመራርነት ላይ ነው ያለኸው። አመ ራርነት እንዴት አገኘኸው? እዚህ ስትመጣ ምን ለመለወጥ አቅደህ ተነሳህ? ምን ያህልስ እየተሳካልህ ነው?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- እዚህ ስመጣ በዋናነት አስቤ የመጣሁት በቀናነት መምራትን ነው። ቅንነት የጎደለው መሪ ደግሞ መሪ ሳይሆን መረን ነው የሚሆነው። በቅንነት አገርን የምናገለግል ከሆነ የእዚ ህችን አገር ችግር ይፈታል ብዬ አስባለሁ። ሁለተኛ ደግሞ እኔ የተቀመጥኩበት ወንበር ላይ ጉድለት እንዲኖር አልፈልግም። ስለዚህ ወደእዚህ ተቋም ስመጣ መጀመሪያ ያደረግሁት ሠራተኞችን ሰብስቤ ያልኳቸው «እኔ ስለመጣሁ ለውጥ ላይመጣ ይችላል።

እናንተ ስላላችሁ ግን ለውጥ ይመጣል» ነው። መሪ በተለወጠ፤ በተቀያየረ ቁጥር መፍትሄ አይመጣም። በተለይ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ተቋማት ያሉ መሪዎች አንድ ቦታ ላይ የሚቀመጡት ቢበዛ ለስድስት ወራት ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ላይ ለውጥ ላይመጣ ይችላል። እዛ ያለው ሠራተኛ ኃላፊነቱን አውቆ እንዲሠራ ማድረግ ግን ወሳኝ ነው። ማነሳሳትም ይጠይቃል። አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ጡረተኛ የሆነ አስተሳሰብ ነው ያለው። ጡረታ ሳይወጣ ጡረታውን የሚጠብቅ ማለት ነው። እነ ትራንፕ በ70 ዓመታቸው ዓላማቸውን ያሳካሉ። እያንዳንዱ ሰው ለእዚች አገር ማበርከት የሚገባውን ሁሉ ስለማበርከቱ ራሱን መጠየቅ አለበት የሚል እምነት አለኝ።

ከዚህ አኳያ እንግዲህ እኔ ወደምመራው የትራንስፖርት ዘርፍ ስንመጣ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቷል፤ አልሰጠምም የሚል አቋም ነው ያለኝ። ይህንን ያልኩበት ምክንያት ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት የትራንስፖርት ዘርፉን ነው። የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ መንገድን ታይቷል፣

ይህንን ችግር ሳንፈታ ህዝቡ አሁንም በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ምሬት አለው። መንግሥት ይህንን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ቢያደርግም የሚገባውን ያህል ነው ማለት አልችልም። በዋናነት ለትራፊክ አደጋ መባባስ መንገዱ አንዱ ምክንያት ቢሆንም የሰዎች አዕምሮ ላይ አልተሠራም። ሰው ሁሉ ቶሎ መኪና መያዝን እንጂ በሰው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት አስተውሎት አይደለም።

የትራንስፖርት ዘርፉ ለአንድ አገር እድገት በጣም ወሳኝ ነው። ግን ምን ተሠራ? ብለን ብንጠይቅ ብዙ

የጎላ ሥራ እንዳልተሠራ መረዳት አያዳግትም። ግን ደግሞ መንግሥት ትኩረት አልሰጠም ብለን መቀመጥ እንደሌለብን አምናለሁ። ለእዚህም ነው ወደእዚህ ስመጣ በዋናነት «በትራፊክ አደጋ አንድ ሰው መሞት የለበትም» የሚለውን መርህ ከመፈክርነት አውርደን መሬት ላይ መተግበር እንድንችል አልሜ እየሠራሁ ያለሁት።

የሚገርመው አሁንም ድረስ አንድም ሰው አይሙት እያልን በዓመት ከ3ሺ እስከ 4ሺ ሰዎች ይሞታል። ስለዚህ እንደ ኦሮሚያ ክልል መንግሥት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በየቀኑም ለውጥ እየመጣ ነው። ለውጡ ግን በአንድ ጊዜ የህዝቡን ችግር ይፈታል ብለን አንጠብቅም። ይህንንም አጠናክረን የምንቀጥል ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡- ለወጡ የሚፈለገውን ያህል እንዳይሆን በዘርፉ ስር የሰደደ የሌብነት አስተሳሰብ መኖሩን ነው የሚጠቀሰው። በዚህ ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

ረ/ፕሮፌሰር፡- እውነት ነው! እንደአገር የሌብነት አስተሳሰብ ስር የሰደደ ችግር ነው። ሌብነት ከዋናው ቢሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የተሳሰረ ነው። አሁን ኤስ. ኤም. ኤስ የሚባል ሲስተም ዘርግተናል። ይህ ሲስተም ሥራ ላይ እንዳይውል የኛ ሠራተኞች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ኔት ወርኩ እየሠራ አይደለም ብለው ይቀመጣሉ። ምክንያቱም ሲስተሙ ለሌብነት ስለማይመች። ይህንን ለማጥራት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሠርተናል። በእኔ እምነት ለውጥ ከውጭ አገር ታሽጎ አይመጣም።

ለውጥ ከእኔ ነው ሊጀምር የሚገባው። ለውጥ ከእኔ የማይጀምር ከሆነ ሪፎርም ሳይሆን ዩኒፎርም ነው የሚሆነው። እያንዳንዱ ሰው ተለውጫለሁ ወይ ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። በትራንስፖርት ዘርፉ ያሉ ሁሉም ተዋናዮች በዚህ አስተሳሰብ የታሰሩ ናቸው። ህብረተሰቡም ቢሆን መብቱን ለማስከበር አይጋፈጥም። ምንአልባት ስለተናገርን ብቻ መፍትሄ ላይመጣ ይችላል። ሁሉም የመፍትሄው አካል መሆን አለበት። ሌብነትን መቀነስ የምንችለው ሁሉ አገሩን መውደድ ሲችል ብቻ ነው። የመንግሥት ለውጥ… ለውጥ ስላለ ብቻ ለውጥ አይመጣም። በኛ ስህተት አንድም ሰው መሞት እንደሌለበት አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ባለፈው አንድ ዓመት የነበረ ውን የለውጥ ጉዞ እንዴት አየኸው?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- በቀጥታ ወደእዚህ ጉዳይ ሳልገባ አንድ ነገር ልንገርሽ። በማኔጅመንት ውስጥ ሦስት አይነት ለውጦች አሉ። አንደኛው ተሃድሶ የሚባል ሲሆን ቀጣይነት የሌለውና ወቅታዊ ለውጥ ነው። ለጭብጨባ፣ ለሽብሸባ፣ ለስብሰባ ብቻ ታስቦ የሚደረግ ማለት ነው። ሁለተኛው ነገሮች ቦታ እንዲለውጡ የማድረግ ሲሆን በዚህ በኩል የነበረውን ለውጥ በዚያ በኩል ማውጣት ማለት ነው።

የበሩ መውጫ ተለወጠ እንጂ የቤቱ ይዘት ያው ነው። ሦስተኛውና ትክክለኛው የሚባለው ለውጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው። አንድ የተለወጠ አዕምሮ ለእዚህች አገር ያስፈልጋታል። የተለወጠ አዕምሮ የፈረሰን አዕምሮ ይገነባል። የፈረሰ አዕምሮ ግን የተገነባውን ያፈርሳል። ብዙውን ጊዜ በሚዲያ ላይ እንደምናገረው በመጀመሪያ አገርን መገንባት ሳይሆን ያለብን አዕምሮን መገንባት ነው። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እያደረገ ያለው የአዕምሮ ለውጥ ለማምጣት ነው። ግን ሙሉ አይደለም።

ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የተከፈለ ዋጋ አለ። ሁሉም ሰው ለውጥ ሲባል አሁን እንዲሆንለት ነው የሚፈልገው። ለውጥ ግን ሂደት ነው። አንዱ የለውጥ ባህሪ ሂደት መሆኑ ነው። ሂደቱን የማይጠብቅ እድገት ይፈርሳል። ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችም በአንድ ሌሊት ብትገነባ ኖሮ በአንድ ሌሊት ትተፍርስ ነበር።

ስለዚህ በሂደት ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው። አንዳንዶች በአደባባይ በድፍረት ለውጥ የለም ይላሉ። ለእኔ ዛሬ ላይ ቆመው ለውጥ የለም ማለታቸው በራሱ ለውጥ ነው። ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በፊት ማንም በአደባባይ ለውጥ የለም ማለት አይችልም ነበር።

በደቦ የሚሠራ ሥራ ተሳክቶ አያውቅም። አገር በሲስተም እንጂ በደቦ አይገነባም፤ አገር ማለት ሲስተም ነው። ከስሜት ወጥተን ወደ ሲስተም መምጣት አለብን። በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለውጥ ታይቷል። ለውጥ ነገም ይቀጥላል። በአሁኑ ወቅት ሁለት ነገሮች ከለውጡ ጋር ተደበላልቀው መጥተዋል።

ይኸውም ስሜትና ዓላማ መር ህይወትን መለየት አለመቻላችን ነው። ይህም ማለት በዓላማ ነገሮችን ማድረግና በስሜት ነገሮችን ማድረግ ተቀላቅሎብናል። እነዚህን ነገሮች መለየት መቻል አለባቸው። በስሜት ተነስተን አገርን መምራት፤ በስሜት ተነስተን መደገፍና ከመቃወም መወጣት አለብን። ብዙውን ጊዜ ከለውጥ ጋር ችግሮች ይመጣሉ። ግን የእኛ ችግር በስሜት መመራታችን ነው። መንግሥትን ስንደግፍ በዓላማ፤ ስንቃወምም በዓላማ መሆን አለበት።

በእኔ እምነት ለውጡ ተጨባጭ ነው ይታያል። የሚዳሰስም ነው። በነገራችን ላይ ለውጡን ስናስብ ተቆጥሮ ኪስ የሚገባ ላይሆን ይችላል። አሁን አሁን «ለውጡ ምንም አላደረገልንም» ይባላል። ግን አይባልም። ጎረቤቴ ሰላም ሲሆን ነው እኔ ሰላም የምሆነው ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ለውጥ መጣ የሚባለው ለእኔ ሥልጣን ሲሰጠኝ ወይም የኔ ወገን ሲሾም አይደለም።

ለውጥ ከእኔ መሾምና መሻር ጋር የተያያዘ መሆን የለበትም። እኔ ስመራ አገር አለ ብዬ እኔ ስሻር አገር የለችም ብዬ መሆን የለበትም። ስለዚህ እኔ እዚህች ምድር ላይ የመጣሁት ለዓላማ ነው። መንግሥት ይመጣል፤ ይሄዳል፤ ጊዜያዊ ነው። ህዝብ ግን ይዘልቃል። እኛ ጊዜያዊና የሚዘልቀውን ነገር መለየት አቅቶናል።

በአጠቃላይ አገርን በሃሳብና በዓላማ መገንባት አለብን ብዬ አምናለሁ። አሁን የተጀመረው ነገር ጥሩ ነው። ግን ከስሜት መውጣትና ሁሉም ሰው ግብ ሊኖረው ይገባል። ከዓመታዊ ገቢ ይልቅ ዓመታዊ ግብ ያስፈልገናል። እንደ ህዝብም እንደአገርም እንደግለሰብም።

አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ሊያደናቅፈው ይችላል ብለህ እንደስጋት የምታየው ነገር አለህ?

ረ/ፕሮፌሰር፡- እኔ እንደስጋት የማየው ሳይጣላ የታጣላ ህዝብ ማስታረቅ ከባድ መሆኑን ነው። ህዝቡ ለምን ተጣላ ብለን ብንፈትሽ ሊያጣለው የሚችል እዚህ ግባ የሚባል ነገር ማግኘት አንችልም። ግን ተጣልቷል። ለእዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ነው ብዬ የማስበው ከዚህ በፊት የነበረን ጥላቻ እየተነገረው ስለሄደ ብቻ የተጣላ ህዝብ ነው አብዛኛው። ምክንያቱ ግን ሲፈተሽ ምንም መሰረት አይኖረውም።

ስለዚህ እናስታርቅ ብለን ስንመጣ የተጣለበት ምክንያት አይኖርም። ይህም ደግሞ ለማስታረቅ ከባድ ይሆናል። ስለዚህ መንግሥት ሊያደርገው ይገባል ብዬ የማስበው ጋምቤላ ጫፍ ያለውን፣ ትግራይ ጫፍ ያለውን፣ አፋር ጫፍ ያለውን፣ ቤኒሻንጉል ገሙዝ ጫፍ ያለውን፣ ደቡብ ጫፍ ያለውን ሰው እና ቤተመንግሥት ያለውን ሰው እኩል ማየት መቻል ነው። ከዚያ ነው ሊጀምር የሚገባው። ከዚያ ነገሮችን መሰረቱን አስተካክለን ከተነሳን ህዝብ ከእኛ ጋር ይነሳል።

ብዙውን ጊዜ ለውጡን ያመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያሉ ሰዎች ናቸው እያልን እንናገራለን። ይህንን ማለታችን እውነትም መልካምም ነው። ግን ደግሞ ህዝብ ባይደግፍ ኖሮ ይህንን ለውጥ ማምጣት እንደማንችል ማሰብ ይገባናል። ለህዝብም እውቅና መስጠት አለብን። ብዙውን ጊዜ «ህዝቡ እኮ አይገባውም፤ ለውጡን አይቀበለውም» እያልን ህዝቡ ላይ ትችት እንሰነዝራለን። ግን ህዝብ ባይደግፈው ኖሮ ይሄ ለውጥ አይንቀሳቀስም ነበር። ልክ ቤተክርስቲያን ወይም መስጂድ ሄደን የሃይማኖት አባቱ ምዕመኑ ካልተቀበለው ሊቀጥል እንደማይችል ሁሉ መንግሥትም ለህዝቡ ተገቢውን እውቅና ካልሰጠ ተቀባይነቱን ማጣቱ አይቀሬ ነው።

ስለዚህ የእኔ ስጋት የህዝቡ ስጋት ነው። ይህም ማለት ህዝቡ መንግሥትን ማመን አለበት፤ መንግሥትም ህዝቡን ማመን አለበት። በሥራ አመራር አስተሳሰብ በመንግሥትና በህዝብ መካከል መገንባት ያለበት ትልቁ ድልድይ መተማመን ነው። መተማመን መፈጠር አለበት የሚል እምነት አለኝ። መንግሥት የቱንም ያህል ሥራ ቢሠራ ህዝቡ ጋር ካልደረሰ ህዝቡ መቼም አያምነውም።

ህዝብ ጋር ያለው ነገር መንግሥት ጋር ካልደረሰ መቼም መንግሥት ህዝቡን አያምንም። በህዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን ካልተፈጠረ ለአገር ስጋት ነው የሚሆነው። መንግሥት መተማመን ላይ መሥራት መቻል አለበት።

የህዝብ የመጀመሪያው ጥያቄ በሰላም መኖር ነው። ሰላምን በቃላት ደረጃ መናገር ሳይሆን ሰላምን የሚያመጡ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል። በተጨማሪም መንግሥት የሚናገረውን ነገር በተጨባጭ መተግበር ይገባዋል። የሚናገረውን ነገር መተግበር ካልቻለ ህዝብ ሊያምነው አይችልም።

ደግሞም አርቴፊሻል ፍቅር አያስፈልግም። ሰላም ነው እያለ ዞር ብሎ ወንድሙን የሚገድል መሆን አይገባንም። እኔ እንደ ኢትዮጵያዊ ያለ ሌላ ሰው መኖር አልችልም። ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአማራ ተማሪዎች ኦሮሚያ ውስጥ በስጋት የሚኖሩ ከሆነ፤ በአማራ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የኦሮሞና የትግራይ ተማሪዎች በስጋት የሚማሩ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት የቱ ጋ ነው? አማራ ሲጎዳ ኦሮሞው የማይሰማው ከሆነ፤ ትግሬው የማይሰማው ከሆነ ምኑን አንድ ሆንን? ኢትዮጵያዊነትን መፍጠር የምንችለው ከእነርሱ ጋር ነው።ልዩነት ሊኖረን ይችላል።

ነገር ግን ልዩነቶቻችን ተቀብለን ተቻችለን የምንኖርበት ጥበብ ሊኖረን ይገባል። ኦሮሚያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሄጄ ተማሪዎች በስጋት ሲኖሩ አይቻለሁ። ከኮሪያና ከቻይና የመጡት መምህራን ደግሞ ደረታቸውን ነፍተው ይሄዳሉ።

እንዴት ነው ዜጋ የሆነ ሰው በአገሩ በስጋት የሚኖረው? እኛ የት ነው በመተማመንና በኩራት የምንኖረው? ስለዚህ አርቴፊሻል የሆነ ፍቅር አያስፈልገንም። «እኔ ያለ ወንድሜ ብቁ አይደለሁም» ብሎ ማመንና መኖር መቻል አለብን። አንድ ኦሮሞ ከአማራው ወይም ከትግሬው ጋር መኖር ሳይችል ከቻይና ጋር መኖር ይችላል ካልን ፍቅራችንና ህብረታችን የውሸት ነው ማለት ነው።

በመሆኑም በመጀመሪያ ቤታችን ውስጥ ያለውን ነገር እናስታርቅ፤ ወደ ጓዳችን እንመለስና የጠፋውን እናስተካክል። ስጋት ይቁም! አርቴፊሻል ፍቅር ይቅር! ፍቅር ስላወራን ፍቅር ላይኖረን ይችላል። በሥራ ማሳየት መቻል አለብን።

ተምሬያለሁ የሚለው መምህር ለተማሪው ጥላቻን የሚያስተምር ከሆነ፤ ተማሪም ጥላቻን ተምሮ ከወጣ በሠራተኛነት ህይወቱ ደግሞ የጥላቻ አስተማሪ ይሆናል። አይተሽ ከሆነ ጥላቻን የሚያስተምር የሃይማኖትም ሆነ የትምህርት ተቋም የለም። በአሁኑ ወቅት ግን ጥላቻ እያንዳንዳችን ቤት እያንኳኳ ነው።

ማስተናገድ የለብንም። ውስጣችን ያለው ጥላቻ እንዲሞት ከፈለግን መድኃኒት መቃወም ብቻውን መፍትሄ አይሆንም። ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አገር የለኝም። ሌላ አገር ለእኔ የስደት አገሬ ነው። ትራምፕ ጠርቶ ኋይት ሃውስ ቢያስቀምጠኝም ሀገሬ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ፈጣሪ የሰጠኝ ኢትዮጵያን ነው። ኢትዮጵያን ሲሰጠኝ ግን ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጋር በጋራ እንድኖር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ለአንተ ምንድን ነው? ከዚህ ጋር ተያይዞ አንተ በተለይ የምትታወቅበት አንድ አባባል አለች «እኛ የምንጣለው ኢትዮጵያ ስለማትበቃን ሳይሆን እኛ ለኢትዮጵያ የሚበቃ አስተሳሰብ ስለሌለን ነው የምትል» ለዚህ አባባልህ መነሻው ምንድን ነው?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ፈጣሪ የሰጠኝ ብራንድ ነው። ማንም በግድ የጫነብኝ አይደለም። ወይም በትምህርቴ ያገኘሁትም አይደለም። ፈጣሪ እዚህ እንደኖር ፈቅዶ የተሰጠኝ ስጦታ ነው። ስለዚህ ነገ ለሚያልፍ ፖለቲካ ብዬ ለኢትዮጵያዊነቴ የማይሆን ትርጓሜ አልሰጥም። ኢትዮጵያዊነት ትክክለኛ ማንነቴ ነው። ይህንን ማንነቴን አውቄ መጠቀም ግን የእኔ ድርሻ ነው። በሌላ አነጋገር ለምሳሌ ቦሌ ላይ የገዛሁትን ብራንድ እቃ መገናኛ መንገድ ዳር ከሚሸጡ ሰልባጅ እቃዎች ጋር ቆሜ ብራንድ እቃ ነው ግዙኝ ብል

ማንም ሰው አያምነኝም። ምክንያቱም ብራንድ እቃ ቢሆንም እንኳ ለመሸጥ የሞከርኩት ያለቦታው ነው። እኛም እንደዚሁ ነን። ብራንድ ሰዎች ነን ግን ራሳችንን አውርደናል። እንዲሁም ብራንድ የሆነችንን አገር ርካሽ አድርገን የምናወራ ሰዎች አለን። ኢትዮጵያዊነት ከአንድ መንግሥት ጋር የሚሄድም የሚመጣ ነገር አይደለም።

ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት እዚህ እንድኖር ፈጣሪ የሰጠኝ ልዩ ስጦታ ነው። ብዙውን ጊዜ እንደምናገረውና አንቺም እንዳልሽው የምንጣላው ኢትዮጵያ ስለማትበቃን ሳይሆን እኛ ለኢትዮጵያ የሚበቃ አስተሳሰብ ስለሌለን ነው ብዬ አምናለሁ። እኛ የተሰጠን በቂ አገር ነው። ለመኖር የሚበቃ ነገር ተሰጥቶን እኛ ስንጣላ እንኖራለን። በሚበቃ አገር ውስጥ በማይበቃ አስተሳሰብ ውስጥ እየኖርን ነው።

ሃሳባችን በድንበር ገድበናል። ከጅቡቲ ወይም ከኬንያ የዘለለ ድንበር ሊኖረን ይገባል። አብዛኛውን ጊዜ በትንንሽ ነገር ነው የምንጣላው። ለምንድን ነው ከኢትዮጵያ ወጥነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ድርሻ እንዳለን የማናስበው። ስለዚህ ከፍ ብለን ማሰብ መጀመር አለብን። ሰው ከፍ ብሎ ማሰብ ሲጀምር ታች ያለውን መናቅ ይጀምራል። አሁን ጥቃቅኑን መናቅ ያቃተን ከፍ ማለት ስላልቻልን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያሉት ምሁራን ለአገር ግንባታ ከመሥራት ይልቅ ለማፈራረስ ምክ ንያት እንደሆኑ ይነገራል። አንተ በዚህ ሃሳብ ትስማ ማለህ?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡– ለእኔ ምሁር የሚለው ትርጓሜ በራሱ ግልፅ አይደለም። ስለተማሩና ማዕረግ ስለጫኑ ብቻ ምሁር ያሰኛቸዋል? እኔ ስለተማረ ብቻ ምሁር አልለውም። ለአገሩ ለህዝቡ በጤናማ አስተሳሰብ ውስጥ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የሚፍጨረጨርና የሚሠራ ሰው ነው ምሁር የምለው።

ከራሱ ጥቅም ይልቅ አገሩን የሚያስቀድም፤ የጠፋውን ፈልጎ የሚያመጣ፤ የተጣላውን የሚያስታርቅ፤ የተራራቀውን የሚያቀራርብን ሰው ነው ምሁር ብዬ የምጠራው። ከሱ ውጪ የሱ ዶክትሬትና የሱ አክቲቪስትነት በእኔ ዘንድ ምሁር አያሰኘውም። ስለዚህ አንድ ሰው ተምሮ ተሳካለት የሚባለው ፎቅ ስለሠራ ወይም ዲግሪ ስለጫነና በዓለም ላይ ታዋቂ ስለሆነም አይደለም። ይልቁንም በሰው ህይወት ላይ መልካም ነገር መጫን ሲችል ነው።

በሰው ህይወት ከላይ መልካም ነገር መጨመር ስንችል፤ ተስፋ የቆረጠውን ሰው ተስፋ ስናለመልም ነው። ከዚህ ቀደም ለውጥ እንዲመጣ ድንጋይ አስቀምጠን መንገድ ስናዘጋ ነበር። ነገር ግን ነገም ዛሬም ድንጋይ ልናስቀምጥ አይገባም። ዛሬ ላይ ድንጋይ ማስቀመጥ ያለብን መንገድ ለመዝጋት ሳይሆን መንገድ ለመገንባት ነው።

ከአገሪቱ ህዝብ 75 በመቶው ወጣት ነው ከተባለ ይህንን ትውልድ የምናንፅበትን መንገድ በአግባቡ ልንፈትሸው ይገባል ባይ ነኝ። ወጣት ማለት በራሱ ለክፉም፤ ለመልካሙም ነገር ጫፍ የወጣ ማለት ነው። ወጣቱን ግደል ከምንለው ዓላማ ይኑርህ ሥራህን ሥራ ማለት ነው ከተማረው ሰው የሚጠበቀው። እኛ አገር የ30ዓመቱንም ወጣት ተሸክመን ነው የምንኖረው ምክንያቱም ራሱን እንዲችል ስላላስተማርነው።

ከሥራ ይልቅ የመጣበትን ብሄር ነው ስናስጠናው ያኖርነው። መርዝ እያጠጣነው ኖረን ዛሬ ከየት አምጥቶ ነው ስለአንድነት የሚያወራው? ሰው ውስጡ የሞላውን እኮ ነው የሚያወራው። በዩኒቨርሲቲ ያለ ምሁር አንድነትን ሳያስተምር ንድፈ ሃሳብን ብቻ አስተምሮ ቢወጣ ምን ጥቅም አለው? 45 ደቂቃ ንድፈ ሃሳብ ከሚያወራ 15 ደቂቃ ስለአገር ፍቅርና አንድነት ብናወራ ይህንን ትውልድ እንታደገዋለን።

የሠለጠኑት አገራት በአገራቸው ጉዳይ ላይ አይደራደሩም። እኛ አገርን የምናየው በፖለቲካ ዓይን ነው። ግን ማየት የሚገባን በአገር ዓይን ፖለቲካን ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች አፍርሰን አገርን እንገነባለን እንጂ፤ አገርን አፍርሰን ፖለቲካ ፓርቲዎችን አንገነባም።

አዲስ ዘመን፡- አንድነት ከዚህ በኋላ አይፈ ጠርም ብለሃል፤ ሌሎች ደግሞ ለዚህ ምክንያት የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እንደሆነ ያነሳሉ። አንተ ይህ በብሄር ላይ የተመሰረተ የፌዴሬሊዝም ሥርዓት ለአገሪቱ ይበጃል ብለህ ታምናለህ?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጀው ፌዴራሊዝም ነው። አጠቀቃሙ ከዚህ በፊት መጥፎ ነበር፤ የትናንትናውን ውድቀት እን ደጠላት ማየት የለብንም። የትናንትና ውድቀት አስተማሪያችን ነው ሊሆን የሚገባው። ላለፉት 27 ዓመታት የፌዴራሊዝም አተገባበር መጥፎ ስለሆነ ብቻ ከኢትዮጵያ ታሪክ ቆርጠን መጣል አንችልም። ከእርሱ መማር ነው የሚገባን። አሁንም ማስተካከል የምንችልበት እድል አለ።

አዲስ ዘመን፡– የምንከተለው ያው መጥፎ ያልነው የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ከሆነ በምን መልኩ ነው ጥሩ ሥርዓት ማምጣት የምንችለው?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- ሳይንሱን ያበላሸው ያጠ ቃቀም ችግር ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ህዝቡን ግደል አይልም። ግን በአጠቃቀሙ ላይ ስለተሳሳቱ ህዝቡን ገደሉት። አሁን ማድረግ አለብን ብዬ የማስበው የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የተፃፈውን ብቻ በተግባር መተግበር ነው። ጎን ለጎንም ፌዴራሊዝምን በአግባቡ የሚጠቀም አስተሳሰብ ማሳደግ ይገባናል። ይህንን ስናደርግ ሥርዓቱ ብቻውን አይጎዳንም። ለዚህ ደግሞ እንደናይጄሪያ ያሉ አገራት ማሳያ ናቸው። ግን ደግሞ የትኛውም ሥርዓት ቢሆን የራሱ አሉታዊ ጎን ይኖረዋል።

የእኛ አገር ፓርቲና ፖለቲካ የተመሰረተው ሌላውን ጥላሸት በመቀባት ነው። የራሱን ትክክለኛ አስተምህሮ ለማስረፅ ጥረት አያደርግም። የእርሱን መሻልና መልካምነት በተግባር አሳይቶ ሳይሆን ሌላውን በማንኳሰስ ለመጠቀም ብቻ ነው ጥረት የሚያደርገው። ሌላ የተሻለ አማራጭ አለ የሚባል ከሆነ በተጨባጭ ማቅረብና ማሳየት ያስፈልጋል። ግን አይበጀንም ብቻ ሳይሆን መፍትሄም አይሆንም።

እኔ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ለኢትዮጵያ ይበጃል እላለሁ። ምክንያቱ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ማንነቱ እንዲከበርለት ስለሚያደርግ ነው። ሁሉም ባህሉና ቋንቋው ተከብሮለት በእኩልነት መኖር መቻል አለበት። ሁሉንም ማስተናገድ የሚችለው ደግሞ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው።

ገና አዲስ ሥርዓት እናምጣ ካልን አገሪቱን ወደ ኋላ እንደመመለስ ነው የማየው። በአጠቃላይ የትናንትናውን ፌዴራሊዝም የተገበሩ ሰዎች አሰራሩን አበላሽተዋል። እኛ ከእነርሱ ተምረን መልካም ፌዴራሊዝም እንገንባ የሚል መልዕክት ነው ያለኝ። ስለሀገራችን መልካም ሥርዓት ለመገንባት ደግሞ መልካም አስተሳሰብ ይኑረን።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን መንግሥት አሰራር የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙም አሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወገንተኛ ነው የሚል ትችት እየተሰነዘረበት ይገኛል። አንተ በግልህ መንግሥት ወገንተኛ ነው ብለህ ታምናለህ? የህዝብ አመኔታንስ እያጣ ያለው? በምን ምክንያት ነው?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡– እንደእኔ ህዝብና መንግ ሥት የተለያዩ አካላት አይደሉም። አሁን አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ የምረዳው መንግሥት ወዲያ ማዶ፤ ህዝብን ወዲህ ማዶ አድርገው እየገለፁ ነው። እኔ አለ ብዬ የማስበው ችግር የሀሳብ ልዩነት ነው። ይህም ደግሞ የመነጨው በተግባቦት ችግር ነው። መንግሥት በቀጥታ የህዝቡን ትርታ ስለማያዳምጥ፤ ህዝብም መንግሥትን በቀጥታ የሚያገኝበት መንገድ ስለሌለ መረጃው ተባዝቶ ነው የሚደርሰው። በአመራሩና በመንግሥት መካከል ክፍተት ተፈጥሯል።

ብዙውን ጊዜ የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት አለብን እየተባለ ይነገራል። እኔ ግን መሰብሰብ የማንችለውን ነገር ማስፋት የለብንም የሚል እምነት የለኝም። መቆጣጠር እስከማንችል ድረስ ማስፋት የለብንም። በየደረጃው ማስፋት የሚገባው እንጂ በአንድ ጊዜ አሰፋለሁ ካልን ወደማንወጣው ነገር ውስጥ ነው የምንገባው። በመጠኑ ቢሆን ጥሩ ነበር።

አሁን መቅደም ያለበት የአገራዊ አጀንዳ የቱ ነው? የሚለው ነገርም በውል አይታወቅም። ለምሳሌ ዶክተር ዐብይ የሚመሩት መንግሥት ለእዚህች አገር መልካም ነገር ይዞ እንደመጣ አምናለሁ። ነገር ግን በየደረጃው ያለው አመራር ልክ እንደ ዶክተር ዐብይ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው።

ብዙውን ጊዜ እንደምለው አብዛኛው አመራር ዳይፐር ተጠቃሚ ነው። ይህም ማለት ዶክተር ዐብይ የሚናገረውን ኮርጆ ይናገራል እንጂ ታች ወርዶ ችግር ለመፍታት አይሠራም። ቀበሌ ላይ ያለው እባብ የምታክል ችግር እዛው መግደል ሲቻል ወደ ወረዳና ወደ አገር ደረጃ ሲሸጋገር ዘንዶ ሆኖ ብዙ ሰዎችን ይውጣል። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ላይም ሆነ በየክልሉ የሚፈጠሩ ችግሮች በየደረጃው ያለው አመራር ችግር ፈቺ ባለመሆኑ ነው። ጥቂት የማይባሉት አመራሮች ቦታው ባዶ እንዳይሆን ብቻ የሚቀመጡ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- የጥያቄያችን መነሻ ይሄ አልነበረም፤ በግልፅ ለመነጋገር ያህል መንግሥት ለአንድ ብሄር ያደላ ነው እየተባለ ይተቻል የሚል ነው?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡- የሚገርምሽ በኦሮሚያ ክልል የሚባለው ደግሞ ሌላ ነው። ዶክተር ዐብይ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት ያበዛል፤ ኦሮሚያ እያለ ብዙ ነገር ቃል ገብቶ ነበር አልፈፀመም የሚል ነው። ጥያቄያችንን አልመለሰም የሚል ቅሬታ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ለኦሮሚያ ወገንተኛ ነህ ይሉታል። እኔ አንድ ስጋት አለኝ። እነዚህ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን እንዳያገሉና ጥለው እንዳይወጡ ነው።

ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እኮ እንደሁላችንም ሰዎች ናቸውና በሰላም መኖር ይፈልጋሉ። ይሄ ልዩነት የመጣው አንድም በተግባቦት እጦት ነው። ሁለትም በመካከል ገብተው ህዝብና መንግሥት በሚያቃርኑ ሰዎች አማካኝነት ነው። እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቴ አምናለሁ። ግን ደግሞ ኦሮሞ መሆኔን አውቃለው። ኦሮሞ ስለሆንኩ ግን ከሌላው ህዝብ የተለየ አዲስ ነገር እንዲደረግልኝ አልፈልግም።

ዶክተር ዐብይ እዛ ጋር ሲቀመጥ ለኦሮሞ ህዝብ የሚወግን ከሆነ ትናንትና ህወሃት ለትግራይ ህዝብ በማዳላት በሌላውን ህዝብ ላይ በደል ፈፅሟል እንደተባለው ሁሉ፤ ከዓመታት በኋላ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እንዲደረግ አልፈልግም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአንድ ዓይን በእውነት መምራት መቻል አለበት።

ከላይ ኢትዮጵያዊ ከስር ደግሞ ለኦሮሞ ህዝብ የሚወግኑ ከሆነ የሚደበቅ ነገር አይኖርም ነገ ግሃድ ይወጣል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ተደብቆ አይቀርም። ስለዚህ ዛሬ ላይ ለምንሠራው ሥራ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደውም ማድረግ የሚገባን የራቁትን ማቅረብ ነው። ካልሆነ ግን የትናንትናውን ነው የምንደግመው።

በአሁኑ ወቅት ግን ወገንተኝነት አለ ለማለት አልችልም። ምክንያቱም እኔ ኦሮሞ ስለሆንኩ ሳይሆን እንደማንኛውም ህዝብ ጫማ ስር ሆኜ ነገሮች ስለማይ ነው። ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተበደለና ዋጋ የከፈለ ህዝብ ነው። ለኦሮሞ የተለየ ነገር ይደረግ ማለትና ሌላው እንዲጎዳ መፍቀድ ማለት በመሆኑ ለልጅ ልጆቻችን ላይ እሳትን መጫር ነው።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት እየተተቸ ያለበት ነገር ቃል የገባውን ያለመተግበሩና ቁርጠኝነት ችግር ነው። ለእዚህ ደግሞ ብዙ በደል የፈፀሙ የህወሃት አመራሮችን በክልላቸው ታጥረው ሲቀ መጡ በህግ ተጠያቂ ያለማድረግ ጉዳይ ሲሆን፣ ሌላው በህዝብ ላይ በደል ያደረሱ እንደ ኦነግ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ተገቢውን የህግ እርምጃ ያለመውሰዱ ነው። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ፡– እንደተባለው ልጅን ወተት ብቻ እየጋቱ ብቻ ማሳደግ አያስፈልግም። አንዳንዴም ቁንጥጫ ያስፈልጋል። በእኔ እምነት መንግሥት ማለት አባት ነው። ጊዜው ሲደርስ የሚገባውን ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ። ህዝብ ግደል፣ እሰር ሲል ከገደለና ካሰረ የራሱ የሆነ መርህ የለውም ማለት ነው። እንደእኔ እምነት የራሱ የሆነ መርህና የጊዜ ሰሌዳ ሊኖረው ይገባል።

አሁን ዘመናዊ እስር ቤት ሳይሆን ዘመናዊ አስተሳሰብ ነው የሚያስፈልገን። መንግሥት የሚያደርገውን ሁሉ ከህዝብ ጋር እየተማከረ ማድረግ አለበት ብዬ አላምንም። የዝምታው ውጤት ታይቶ አገርን የሚጠቅም ከሆነ ቶሎ እርምጃ መውሰድ ነው የሚገባው። መንግሥት ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብቷል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመንግሥት እተዋለሁ። እንደአባትነቱ ግን ቁጣም ያስፈልገዋል። ልናደርግ ነው ሳይሆን መባል ያለበት አድርጎ ማሳየት ነው።

ስለህወሃት አመራሮች ላነሳሽው ጉዳይ ዶክተር ዐብይ ዝም ቢልም ያጠፋ አካል ጊዜው ሲደርስ መጠየቁ አይቀርም። ምክንያቱም ሰው የዘራውን ስለሚያጭድ። በአንድ አገር ውስጥ ሆነን ያጠፉ አካላት በክልላቸው ተሸሸጉ ሲባል ለመንግሥት አሳፋሪ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሊደረግላቸው የታሰበው ይቅርታ ለይስሙላ ነው? ወይስ ፍቅር የሚያሳያቸው እነርሱን እስከሚያስር ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ደግሞም ይህችን አገር የበዘበዟት እነርሱ ብቻ አይደሉም፤ መሬት የሸጡት ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ አመራሮችም ናቸው። ስለዚህ እዚህ ያለው አካል ምንም ሳይደረግ እነርሱ ላይ ብቻ እርምጃ ይወሰድ የሚለውን ሃሳብ አልቀበለውም። አንዳንዱ እኮ አምባሳደር ሆኖ እየተሾመ አይደለም እንዴ? የትናንትናውን ሌባ ጠጋግነን ወደ ቦታው የምናስቀምጥ ከሆነ አዲሱ አመራር እንዴት ነው የሚቀጥለው? ፃድቅ የሆነ ሰው ባይኖርም አገርን የሸጠና ህዝብን የገደለ ሥልጣን ላይ መቀመጥ የለበትም። አሁንም የእኔ አቋም ይህ ነው። እነሱን ጉያችን ውስጥ አስቀምጠን ስለኢትዮጵያ ማውራት አንችልም።

በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ ፓርቲዎች ምህረት ተደርጎላቸው ቢገቡም የምህረቱና የይቅርታውም ጊዜና ገደብ ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። መንግሥት የምናውቀው በኢትዮጵያ መንግሥትነቱ ነው። ከዚያ ውጪ ሌላ መንግሥት የለም። ራሳቸውን መንግሥት አድርገው ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ አካላት መንግሥት ፈቅዶላቸው ከሆነ ሊነገረን ይገባል።

Filed in: Amharic