>
5:14 pm - Wednesday April 20, 8208

'የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ' ዘመቻ የትዝብት ዳሠሳ! (መላኩ ከበደ)

‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ ዘመቻ የትዝብት ዳሠሳ!
መላኩ ከበደ
‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ የሚለው የማህበራዊ ገፅ ዘመቻ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊ ማንነት መቀጠልና አለመቀጠል ላይ ተመርኩዞ መጭውን የፓለቲካ እውነታ ለመዳሰስና ለመቃኘት (bode of confidence) የተደረገ የዳሰሳ ዘመቻ ነው:: ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ የሚለው ዘመቻ ለኢትዮጲያዊ ጎሣዎች ደህንነትና ህልውና የሚበጅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዐት እንዲመሠረት ጥርጊያ መንገድ ማዘጋጀት እንጂ እነዚህን ጎሣዎች ለማጥፋት የተወጠነ ፓለቲካዊ ሤራም አይደልም::
በዚህ ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ በሚለው ዘመቻ ሁለት ዓይነት የሐይል አሰላለፍን እስተውለናል:: ከድጋፍና ተቃውሟቸው ጀርባ ያለውን ምክንያትንም መርምረናል::
1. ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ እንዲታገድ’ የተስማሙና የጠየቁ የዘመቻው ደጋፊዎች
አንደኛው ሃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝቧን አንድነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን ለማነፅ ግብዐት መሆኑን የሚቀበሉና በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው የማይጠራጠሩ ግለሰቦች: ቡድኖችና ድርጅቶችን ያቅፋል:: ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ የሚሉትም ይህ ፓለቲካ ያስከተለውንና እያስከተለ ያለውን የሕዝብ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት መሰናዶን አስተውለው ይህን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አደረጃጀትና ፓለቲካ በማስወገድ በኢትዮጵያ ላይ ያንጃበበውን የ1991ኑን የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ዳመና ለመግፈፍ አይነተኛ መፍትሄ ለማምጣትና የሕግ የበላይነት በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ማህፀን እንዲቋጠር ከመፈለግ ነው::
 ይህ የዘመቻ መርሃ ግብር ድርጅታዊ ሣይሆን ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው::
2. ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ እንዲታገድ’ ምክንያት አለን ብለው ያልተስማሙ፣ ያልተሳተፉና ውድቅ ያደረጉ
በዚህ ጎራ ሁለት ዓይነት የሐይል አሰላለፍና የአስተሳሰብ ክንፎችን እስተውለናል::
ሀ). ክንፍ አንድ
‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ እንዲታገድ’ የሚፈልጉትን ሐይሎች ከፓለቲካ ድርጅት ጋር በማጣመር “የኛን አደረጃጀት ለመደምሰስ የታቀደ ነው:: መጀመሪያ መክሰም ያለበት ኦዴፓ ነው” የሚሉን ጉዶች ናቸው (Laim Excuse)::
 የሚገርመው የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ከታገደ እነርሱ ከስመው ኦዴፓ የጎሣ ድርጅት ሆኖ የሚቀጥልበት እነርሱ የገባቸው እኛ የጠፋን እውነታ ነው:: “የጎሣ ፌደራሊዝም” እና የጎሣ ፓለቲካን ታቅፈው ከተቻለ ኢትዮጵያን በትነው “የጎጥና የመንደር መንግስት” ለመመሥረት የወሰኑ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን ክደው ኢትዮጵያን ከነርሱ በፊት ክደው ለመፈረካከሷ ከሚሰሩትና ‘በክንፍ ሁለት’ ስር ከተጠቀሱት ወያኔዎችና ኦነጋውያን ጋር የአላማ አንድነት የፈጠሩ ከሃዲዎች ናቸው::
የአባቶቻቸውንና የእናቶቻቸውን ገድል አራክሰው በደምና እጥንታቸው የገነቧትን ሐገር ለመናድ ከጠላቶቿ ጋር እጅና ጏንት የሆኑ ናቸው::
 በሚሊዮን በሚቆጠሩና ከክልላቸው ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከድተው ለእልቂታቸው መከውን ከጠላቶችቸው ጋር የወገኑ ሸርታታ ከሃዲዎችም ናቸው:: ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ ዘመቻን ተሳልቀውበት የመንግስት ሹመኞችን ሲያብጠለጥሉና በነርሱ ላይ ዘመቻ ሲያደርጉ ተሰተውሏል:: የአንዱን ፓስት ሌላው እየገለበጠ ኢትዮጵያን ረስተው ያፈቀሩትን “የጎሣ ፌደራሊዝም” እና የጎሣ ፓለቲካ ኮረፌ በሽክና ሲቀባበሉና አሉባልታ ሲያራግቡ ውለዋል::
ለ). ክንፍ ሁለት:-
በዚህ ክንፍ የአፓርታይድ ሥርዐትን ተግብሮ የከሸፈው ነገር ግን በደመ ነፍስ የሚፈራገጠው ወያኔ እና የወያኔን ፈለግ ተከትሎ “የቁጥር አብላጫ አምባገነንነትን” ለመጫን ካልቻሉ ኢትዮጵያን ለመበተን ሁለት አባት ይዘው የቀረቡ ኦነጋውያን ናቸው:: በነዚህ ሐይሎች ‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ የሚለው ጥያቄ ለውይይት ሳይቀርብ ከመጀመሪያው ውድቅ አድርገውታል (Dead-on-arrival)::
3. ፍትጊያውና ትዝብቱ
ይህ የዳሠሳ ዘመቻ ግጥሚያው “የጎሣ ፌደራሊዝም” እና የጎሣ ፓለቲካን በማስቀጠል ሐገረ ኢትዮጵያን ለመበተን በቁጥር 2 የተጠቀሱት በክንፍ አንድና ሁለት’ የተሰለፉና የዓላማ አንድነት የፈጠሩ በአንድ ወገን፣ የኢትዮጵያን የሕዝቧን አንድነትና ሉዓላዊነት ተጠብቆ ዴሞክራስያዊ ሥርዐት እንዲታነፅና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን መካከል ነበር:: በኢትዮጵያ ሥም እየማሉ ኢትዮጵያዊነታቸውን በሸጡ፣ ኢትዮጵያን በካዱ ሹምባሾችን በኢትዮጵያዊነታቸው የፀኑ ኢትዮጵያውያን መሃል ነው::
2. የዳሠሳው ውጤት
ሁሉም የጎጥና የመንደር ድርጅቶች አንድ መሆናቸውን ነው:: ሁሉም እንሠሦች አንድ ናቸውና:: ሁሉም ድርጅቶች ፀረ-ኢትዮጵያ እንደሆኑ ነው:: ለዚህም ማረጋገጫው አንድም የጎጥ ድርጅት ወይም በጭፍን የሚነዱት መንጋ በዚህ ሁሉንም ብጋራ ሊያሣትፍ በሚችል ዘመቻ ላይ የሉም:: ይህ ኢትዮጵያ ሐገራቸውን ክደው ከወራሪ ጠላት ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያ ሐገራቸውን ከወጉ ባንዳና ሹምባሾች ከሠሩት ክህደት ጋር አንድ ነው:: የጎጥና የመንደር ህልማቸውን ለማሳካት ሲሉ በሚሊዮን ዜጎች ላይ የሞት ፍርድ መፍረዳቸውን ነው::
መንደርታኞችና ጎጠኞች ያማራቸው የኢትዮጵያ መንሰራራት ሣይሆን የእነርሱ የጎጥ ባላባት መሆን ነው!
የጎጠኞቹ አፍራሽ የራስ ቅል እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም!
የጎሣ ፓለቲካ መታደግን የሚደግፉ ኢትዮጵያን ለማዳን የቆረጡ አርበኞች ናቸው!
Filed in: Amharic