>

"አገር እንደ አገር እንዲቀጥል - የሰላም ዘንባባ ብቻ ሳይሆ የፍትህ ሰይፍም ያስፈልጋታል!!!" (መጋቢ ዘሪሁን ደጉ)

“አገር እንደ አገር እንዲቀጥል – የሰላም ዘንባባ ብቻ ሳይሆ የፍትህ ሰይፍም ያስፈልጋታል!!!”

መጋቢ ዘሪሁን ደጉ

(ኢፕድ)

ሕግ ከሌለ ሰው መረን ይወጣል። ሰው ሕግ እንዲያከበር የተፈጠረ ፍጡር ነው፤ ስለዚህ ሕግን የማስከበር ኃላፊነት የተጣለበትና በአደራ የተሰጠው መንግሥት ነው።

በመሆኑም ህዝቡ አስተዳድረኝ የሚል አደራ የተሰጠው መንግሥት ህዝቡ በአግባቡ የሕግ የበላይነት እንዲከበር መሥራት አለበት። ክፍተቶችን መንግሥት መድፈን አለበት። ካልሆነ ብጥብጡ እየጨመረ ይሄዳል። ከ70 ሚሊዮን የማያንስ ወጣት ያለበት አገር ውስጥ ነን። ወጣት ደግሞ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርገው ሥርዓትና ሕግም ጭምር ነው። ስለዚህ ይሄንን ሁሉ ሥርዓት ለማስያዝ አንዱ መንገድ የህግ የበላይነት እንዲያከበር መደረግ አለበት። 

ኮሽ ባለ ቁጥር መንገድ ተዘጋ ሲባል ነው የሚሰማው። ድንጋዩ ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ መንገድ መዝጋት ነው። ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም። ጥያቄ በአግባቡና በሥርዓት ማቅረብ አስፈላጊ ነው። ህጋዊነት የሌላቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መውደቃቸው አይቀርም። ስለዚህ ህግን ተከትሎ መሄድ በራስ የመተማመንም ምንጭ ነው። በመሆኑም ጥያቄ ያለው አካል ህግን ተከትሎ መሄድ ሲችል ነው ውጤታማ የሚሆነው።

በአሁኑ ወቅት ወጣቶቻችን ብዙ ጥያቄዎች እንዳላቸው ይታወቃል። ሠላም ማጣቱ የበለጠ ሥራ አጥነቱን እያባባሰው ይሄዳል እንጂ አይቀንስም። ሠላም በሌለ አገር ውስጥ ኢኮኖሚ ሊያድግ አይችልም። ሠላም በማጣታችን በእያንዳንዱ ቀን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አገሪቱ እንደምትከሰር ይታሰባል። ስለዚህ መልሶ ለማገገም ሌላ ጊዜ፣ ሌላ ዘመን ይፈልጋል። ወጣቶቻችን የሚፈልጉትን ዕድገትና ልማት ሳያዩ በችግርና በድህነት ይገፋሉ።

ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንበረ ሥልጣኑ ከመጡ በኋላ ከውስጥም ከውጭም ብዙ ለውጦች አሉ። በጎረቤት አጋራት ጋር ያለው ግኝኙነት በጣም ጥሩ ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ቀጣናውን በኢኮኖሚና በሠላም ለማስተሳሰር የተደረገው ጥረትም በጣም የሚደነቅ ነው። በአገር ውስጥ ብዙ ሪፎርሞች ተደርገዋል። ይህ በጣም የሚደነቅና ለቀጣይም ብዙ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ እራሳችን በፈጠርነው ችግር በርካታ ዜጎቻችን የተፈናቀሉበትና የራሳችን ወገኖች ችግር ውስጥ የገቡበት ወቅት ነው። ምናልባትም የዛሬ ዓመት በዓል በቤታቸው ያከብሩ የነበሩ ሰዎች በእኛ አለመከባበር፣ አለመተማመን፣ ችግሮችን በውይይት ባለመፍታታችን ብዙ ወገኖች አደጋ ውስጥ ወድቀዋል፤ ኑሯቸው ተቃውሷል።

አዲስ ዘመን፡- እንኳን ለፋሲካ በዓል በሠላም አደረሰዎ እያልኩ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገነዘቡታል። ለችግሮቹስ መፍትሄ እንዴት ይመጣል ብለው ያስባሉ?

መጋቤ ዘሪሁን፡- በቅድሚያ የፋሲካ በዓል ስለሆነ እንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በዓሉ የደስታ የሠላም፣ ኢትዮጵያ ደግሞ አሁን ከገጠማት የሠላም እጦት ወጥታ ወደነበረን አንድነትና ሠላማችን የምንመለስበት ትልቅ ዓመትና በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ። በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በማሰብና እነሱን በማቋቋም ሂደት ተጠናክረን ሁላችን መደገፍ አለብን። ሌሎች እንዳይፈናቀሉም መፀለይና መሥራት ያስፈልጋል።

ለመፈናቀሉም መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ማድረጉ እንዲሁም ሌላውን አካል ብቻ ተጠያቄ ማድረጉ አስፈላጊ አይደለም። ለመፈናቀሉ ሁላችንም ኃላፊነት ወስደን ሌላ እንዳይፈናቀል በአንድነትና በአብሮነት መሥራት ይገባል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የገጠማትን ችግር ለማቃለል በመንግሥት በኩል መደረግ ያለበት ነገር አለ። የሕግ የበላይነት ማስከበር አለበት። ይሄንን በሁለት ከፍለን እንየው። በመጀመሪያ ሕግ ከሌለ ሰው መረን ይወጣል።

ሰው ሕግ እንዲያከበር የተፈጠረ ፍጡር ነው፤ ስለዚህ ሕግን የማስከበር ኃላፊነት የተጣለበትና በአደራ የተሰጠው መንግሥት ነው። በመሆኑም ህዝቡ አስተዳድረኝ የሚል አደራ የተሰጠው መንግሥት ህዝቡ በአግባቡ የሕግ የበላይነት እንዲከበር መሥራት አለበት። ክፍተቶችን መንግሥት መድፈን አለበት። ካልሆነ ብጥብጡ እየጨመረ ይሄዳል። ከ70 ሚሊዮን የማያንስ ወጣት ያለበት አገር ውስጥ ነን። ወጣት ደግሞ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርገው ሥርዓትና ሕግም ጭምር ነው።

ስለዚህ ይሄንን ሁሉ ሥርዓት ለማስያዝ አንዱ መንገድ የህግ የበላይነት እንዲያከበር መደረግ አለበት። ሁለተኛው ደግሞ የመብት ጥያቄን የሚጠየቅበት መንገድ እንዴት ነው? ጥያቄው ራሱ መሄድ ያለበት በህግ ነው። ኮሽ ባለ ቁጥር መንገድ ተዘጋ ሲባል ነው የሚሰማው። ድንጋዩ ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ መንገድ መዝጋት ነው።

ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም። ጥያቄ በአግባቡና በሥርዓት ማቅረብ አስፈላጊ ነው። ህጋዊነት የሌላቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መውደቃቸው አይቀርም። ስለዚህ ህግን ተከትሎ መሄድ በራስ የመተማመንም ምንጭ ነው። በመሆኑም ጥያቄ ያለው አካል ህግን ተከትሎ መሄድ ሲችል ነው ውጤታማ የሚሆነው። በአሁኑ ወቅት ወጣቶቻችን ብዙ ጥያቄዎች እንዳላቸው ይታወቃል።

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ አሉ። ሥራ የማግኘት ጉጉት አላቸው። ፍላጎቶች እየጨመሩ ነው። ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት የሚችሉት መንግሥት የህግ የበላይነትን አስከብሮ መሄድ ሲችል ነው። አገር ሠላም ስትሆን ነው ልማት የሚኖረው፣ ኢንቨስተሩ መጥቶ ፋብሪካ የሚያቋቁመው። ባለሀብቱም ገንዘቡን የሚያፈሰው። ነጋዴውም ንግዱን የሚነግደው። ሠራተኛውም ወደ ሥራ የሚሄደው።

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ የኢኮኖሚው መሰረት ናቸው። ሠላም ከሌለ በእያንዳንዱ ቀን የራሳችንን ዕድል ነው እያበላሸን የምንሄደው። ሠላም ማጣቱ የበለጠ ሥራ አጥነቱን እያባባሰው ይሄዳል እንጂ አይቀንስም። ሠላም በሌለ አገር ውስጥ ኢኮኖሚ ሊያድግ አይችልም። ሠላም በማጣታችን በእያንዳንዱ ቀን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አገሪቱ እንደምትከሰር ይታሰባል። ስለዚህ መልሶ ለማገገም ሌላ ጊዜ፣ ሌላ ዘመን ይፈልጋል። ወጣቶቻችን የሚፈልጉትን ዕድገትና ልማት ሳያዩ በችግርና በድህነት ይገፋሉ።

አዲስ ዘመን፡- ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል። በነዚህ ዓመታት የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታዎች በሚገባ አስተውለዋል። አሁንስ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ያለውን የአገራችንን ሁኔታ እንዴት አስተዋሉት?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንበረ ሥልጣኑ ከመጡ በኋላ ከውስጥም ከውጭም ብዙ ለውጦች አሉ። በጎረቤት አጋራት ጋር ያለው ግኝኙነት በጣም ጥሩ ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ቀጣናውን በኢኮኖሚና በሠላም ለማስተሳሰር የተደረገው ጥረትም በጣም የሚደነቅ ነው። በአገር ውስጥ ብዙ ሪፎርሞች ተደርገዋል። ይህ በጣም የሚደነቅና ለቀጣይም ብዙ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ እራሳችን በፈጠርነው ችግር በርካታ ዜጎቻችን የተፈናቀሉበትና የራሳችን ወገኖች ችግር ውስጥ የገቡበት ወቅት ነው። ምናልባትም የዛሬ ዓመት በዓል በቤታቸው ያከብሩ የነበሩ ሰዎች በእኛ አለመከባበር፣ አለመተማመን፣ ችግሮችን በውይይት ባለመፍታታችን ብዙ ወገኖች አደጋ ውስጥ ወድቀዋል፤ ኑሯቸው ተቃውሷል። ይህን በዓል ስናከብር በሁለት ስሜት ውስጥ ሆነን ነው። ይህ በለውጥ ውስጥ ያለ አገር የሚገጥመው ነው ብንልም እኛ አገር ግን ትንሽ በዝቷል።

በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያን ለኃይማኖታችን በጣም የቀረብን ነን እንላለን፤ የኃይማኖት ሰው ሲኮን በዓል ማክበርም ደስ ይላል፤ ትልቅ ነገርም ነው። ይሁንና በእኔ አስተሳሰብ የእኔ ኃይማኖት ለሌላ መፈናቀል ምክንያት ከሆነ፣ ለአገር አለመረጋጋት ምክንያት ከሆነ፣ ለአንድነትና ለአብሮነት የማንሠራ ከሆነ ኃይማኖታችን በአግባቡ ተከትለናል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ስለዚህ የኃይማኖት ሰዎች መገለጫው ለአገር ሠላም፣ ለአብሮነትና ለአገር አንድነት መቆምና መሥራት ነው።

የእኔን ሃይማኖት አንተ የምታውቀውና የምትገነዘበው በስሜ አይደለም፤ በምግባሬ ነው። ምግባሬና ሃይማኖቴ አብሮ እንዲሄድ ማድረግ ደግሞ ኃላፊነት አለብኝ። ይህ ሁሉ ሃይማኖት ባለበት አገር ውስጥ ከችግር ቶሎ መውጣት አለብን። ከዚህ በሁለት መንገድ መውጣት ይቻላል። አንደኛው ወደ ፈጣሪ በፀሎት እየቀረብን ነው። ለነገሥታትና ለአብሮነታችን እንድንፀለይና በጋራ እንድንኖር የሚመከር እሴት በሃይማኖታችን ውስጥ አለ። ሁለተኛው የሃይማኖት ሰው ስትሆን ቅድሚያ የምትሰጠው ለሠላም ነው።

ይሁንና የሚገርመው ነገር እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በሃይማኖት ውስጥ የሌሉና የተከለከሉ ነገሮች የተፈቀደ ይመስል አሁን ስንተገብረው በጣም ያሳዝናል። ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት። በቅርቡ የሙስሊም ወንድሞቻችን የረመዳን ወር ይገባል። ስለዚህ ቢያንስ ወንድሞቻችን ፆምና ፀሎት ከቤታቸው ሆነው እንዲያሳልፉ ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው። ከነገ ጀምሮ ፋሲካ በዓል ነው። ክርስቲያኖችም እንዲሁ በሠላማዊ መንገድ ማክበር አለባቸው።

ከሁሉም የሚበልጠው ግን ከሌሎች ጋር ለመኖር የኢትዮጵያን አንድነትና ሠላም ማጠናከር ይገባል። ኢትዮጵያ ሠላም ካልሆነች ሃይማኖትን በነፃነት ማራመድ አይቻልም። ሀገር ከፈረሰና ከወደቀ በኋላ የዚህኛው ሃይማኖት ተከታይ ነኝ ብለህ የምትቆምበት መሰረት የለም። ስለዚህ ህግና ሥርዓትን ተከትለን ለህዝባችን አብሮነት ለአገራችን አንድነት እንድንሠራ አደራ እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ለእምነታቸው ትልቅ ዋጋ ከሚሰጡት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ይታወቃል። ወዲህ ደግሞ ከኃይማኖት፣ ከባህልና ከሞራል ማፈንገጥ ይታያል። ለዚህም የእምነት ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የሚል ወቀሳ ይሰነዘራል። እርሰዎስ ምን ይላሉ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- በተደጋጋሚ ይህን ጥያቄ እንመልሳለን። መጀመሪያ የሃይማኖት ተቋማት በደንብ አልሠሩበት ይሆናል የሚል ሃሳብ አለ። በተወሰነ ደረጃ እውነትነት አለው። ግን የሃይማኖት ተቋማት የሚያስተምሩት ቀርቶ ሰው በተፈጥሮ እግዚአብሔር የሚለውን ያለመቀበል ባህሪ አለው። በአንድ በኩል የሃይማኖት አባቶች እያስተማሩ ነው። ይህን በድፍረት የምናገረው ምክያት ስላለኝ ነው። ቤተክርስቲያንና መስጂድ የሚሄድ ሰው ቀርቷል ወይ ብለን ስንጠይቅ እንደውም ቁጥሩ ጨምሯል።

አዲስ ዘመን፡- ወደ ቤተ እምነት የሚሄደው ምዕመን የበረከተው የህዝብ ቁጥር ስለጨመረ ወይስ ሰው አማኝ ስለሆነ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- አይደለም! ወደ ቤተ ዕምነቶቹ የሚሄዱት እየተበራከቱ ፍላጎቱም እየጨመረ ነው። ቤተ እምነቶች ሁሌ ሙሉ ናቸው። በኦርቶዶክስም ሆነ የሌላ እምነት ተከታዮች የበዓላት ቀን በነቂስ ወጥተው ነው የሚያከብሩት። ወደዚያ የሚሄዱትም ከሃይማኖት አባቶች እውቀት ለማግኘት ነው። ስለዚህ የሃይማኖት አባቶች ያስተምራሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ አይደለም። መጠይቅ ያለበት የተማረውን መተግበርና መታዘዙ ላይ ነው። ሃይማኖት ከሌሎች ነገሮች የሚለየው ያገኘኸውን እውቀትና ሃይማኖቱ የሚያስገድደውን መተግበር ስትችል ነው ሃይማኖተኛ የምትሆነው። ሃይማኖቱ የሚለውን ለመተግበር የሚገዳደር ኃይል ሲመጣ እርሱን ተቋቁሞ ማለፍም ትልቁ ነገር ነው። ወደ መስጅድና ቤተክርስቲያን መሄዱ ጥሩ ሆኖ ዋናው ነገር ሃይማኖቱ የሚለውን መተግበር ነው። ለምሣሌ ‹‹መጥላት›› በሁሉም ሃይማኖት የተከለከለ ነው። ባልንጀራን እንደ ጠላት መቁጠር፣ መግደል፣ ማሳደድ በሃይማኖቶች የተከለከሉ ናቸው። ይህን ማድረግ ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝም ብሎ መቆም በግለሰቡ ሞራል ላይ ይመሰረታል። ሁለተኛው የአገርን ሕግ ማክበር ሃይማኖታዊ ነው። የአገሬን ሕግ ሳከብር ኃይማኖቴንም እንዳከበርኩ ይቆጠራል። ሃይማኖትም የአገርን ህግ ማክበር እንደሚገባ ያዛል። ይህ ከሆነ ሰዎች ፀብ ጫሪዎች አይሆኑም። በአሁኑ ወቅት የሃይማኖት መሪዎች በብዛት ያስተምራሉ። ግን ውጤት ለምን አልመጣም የሚለው ያጠያይቃል። ያገኙትን እውቀት ይተገብሩታል ወይስ አይተገብረቱም የሚለው ነው አጠያያቂ የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ይመልሱት። ይተገብራል ወይስ አይተገብርም?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ቢተገበር ይህ ሁሉ ችግር አይመነጭም። ይህ የሚመጣው አንዳንድ ቦታዎች ላይ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ራሳቸውም የመፍትሄ አካል ሳይሆኑ የችግሩ አካል ይሆናሉ። ሃይማኖት መሪ ስትሆን ያመንከውንና ያሰብከውን ሁሉ በአደባባይ አትናገርም ምክንያቱም ተከታይ ስላለህ። መስመር የሳቱ የሃይማኖት መሪዎች በሚገኙበት ጊዜ ሰው እነርሱን መስማትና መታዘዝ ይከብደዋል።

ከእነርሱ ያገኘውን እውቀት ለመተግበርም ይከብደዋል። ይህ ግን አጠቃላይ ስዕሉን አያሳይም። በአገራችን ውስጥ ያለው እኛ እነርሱ የሚል መከፋፋል ስላለ በ‹‹እኛ›› እና በ‹‹እነርሱ›› ላይ የተፈፀመ በደል ነው ብለህ ስታወራ በቀላሉ ሰው የእኔ ጎሳ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት ተነካ በሚል ወዲያውኑ ሃይማኖት የሚለውን ለማሰብ ጊዜ አይወሰድም። ቶሎ ብሎ ወደ ዚህ ይሳባል። ስለዚህ አቅም አግኝቷል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ፓስተሮች፣ ዲያቆናት እና ኡስታዞች በአስተምህሮ ወቅት የሚከተሉት መንገድና የሚጠቀሟቸው ምሣሌዎች ችግሮች የሚያቃልሉና የሚጠግኑ ናቸው ብለን መግለፅ እንችላለን?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ሠርቻለሁ፤ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ኃላፊነቴን እጨርሳለሁ። የሃይማኖት መሪ ስትሆን ከብዙ ነገር ገለልተኝነትህ መረጋገጥ አለበት። ለአብነት በሁለት የእምነት ተከታዮች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር የሃይማኖት መሪዎች በዚህ ጊዜ ችግሩ ላይ ብቻ ማተኮር እንጂ እከሌ ከማን ወገን ነው? ብሎ ዳኝነት የሚሰጥና አንዱን ለማገዝ ሌላውን ለማጥላላት የሚሄድ ከሆነ መለያያቱን በጣም ያሰፋዋል። ስለዚህ አልፎ አልፎ የሚታዩ የወገንተኝነት ችግሮች አሉ። የእምነት መሪዎች ይህን በተከታዮቻቸው ላይ የመስበክና የመዝራት ዕድል ካገኙና ከተጠቀሙ አገርን ያፈርሳሉ። ሕገ መንግሥቱም ኃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው የሚለው ወዶ አይደለም። ይህ በጣም ጠቃሚ ሕግ ነው። ከሁሉ በላይ የማንኛውም እምነት ተከታይ ሆነ እኔም የሚታየኝ ሰውን ማወቅ ያለብኝ በብሔሩ፣ በሃይማኖቱ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ ነው። የሚያግባባንና ወደ ጋራ መሠረት የሚያመጣን ይህ ነው። የተለያዩ እምነት ተከታዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ሰው መሆናችን እኔ እና አንተ ሳንባባል ዋጋ ሊኖረን ይገባል። ሁሌ እርግጠኛ መሆን የሚገባን የእኛን ሃይማኖት ስናስተምርና ስናስፋፋ አገር እና በህዝብ ላይ የሚመጣ ጥላቻና መለያየት በውስጡ አለመኖሩን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። በማናቸውም እምነት ውስጥ ስትሄድ ጥላቻ፣ ማሳደድ፣ ቂም በቀልና መለያየት የተከለከሉ ናቸው። ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ሃይማኖት ነው ያለው። ስለዚህ በአንተ ላይ ሊደረግ የማይገባውን በሌሎች ላይ አታድርግ የሚል እምነት ነው። የሃይማኖት መሪዎችም ይህን በማስተማር ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት አለባቸው። ይሁንና አልፎ አልፎ እጃቸውን በተለየ ሁኔታ በማስገባት ወጣቶቻችን ለማሳሳት የሚያደርጉት ጥረት የለም ማለት አይቻለም።

አዲስ ዘመን፡- ዘጠኝ ዓመታት በኃላፊነት ከቆዩበት ተቋም ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚለቁ ገልፀዋል። በጠንካራ እና በደካማ ጎን ምን ታዝበዋል? ወደ ፊት የሚያራምዱ ምን ነገሮችን ተሠርተዋል? 

መጋቢ ዘሪሁን፡- አንዱ በኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ህዝቡ ዘንድ አብሮ አገራቸውን ለመጥቀም ይጥራሉ። በተናጠልም ቢሆን በጎ አስተሳብና ትልልቅ መልካም ሥራዎች በአገሪቱ እንዲከናወኑ የሚጨነቁ አባቶች አሉ። ሁለተኛ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሼ ጥናታዊ ጽሑፎች አቅርቤያለሁ፣ ስብሰባዎች ተሳትፌያለሁ፣ ውይይት መርቻለሁ፣ አብሬም ሠርቻለሁ፡፡ በፖለቲከኞቹ ዘንድ በስልጣን ላይ ለመቆየት አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ የሚዘሩት መራራና የክፋት ዘር፤ የሚሠራ ሸፍጥ እና ወንጀል ስለሚበዛ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም የምትኮራበትና ከፍተኛ ሰብዕና ያለው ሕዝብ ነው። በቆይታዬ የታዘብኩት በየቦታው አንዳንድ መሰሪ ሰዎች አሉ። በፖለቲካ አቅጣጫ የሚወስዱ፤ ከብሔር ጋር አያይዘው ማጥቃት የሚፈልጉና የእኔ ብሔር ነው ለሚሉት ብቻ ለመደገፍ የሚጥሩ አይቻለሁ። ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሞና ችሎ አብሮ መኖር ግዴታ ነው። በፖለቲካው ዓለም የሚታየው ነገር በኃይማኖት ውስጥም አልፎ አልፎ ነፀብራቆቹ ይታያሉ። ይህ በጣም አደገኛ እንደሆነ ይታየኛል።

አዲስ ዘመን፡- ከኃይማኖት ያፈነገጡ የሽብር ድርጊቶች በቅርቡ በግብጽና እና ሲሪላንካ መከሰቱ ይታወሳሉ። ይህ በኢትዮጵያ የመከሰት ዕድልና የሥጋት ደረጃቸውን እንዴት ይገልፁታል? በተለይ ፅንፈኝነቱ ወደዚያ አያመራንም?

መጋቢ ዘሪሁን፡- እዚህ ላይ የተለየ አቋም አለኝ። ሲሪላንካን ብንወስድ በአንድ ቀን 300 የሚጠጉ ሰዎች ናቸው የፋሲካ በዓላቸውን ሲያከብሩ በደረሰ ጥቃት የሞቱት። ከ500 ሰዎች በላይ ተጎድተዋል። ይህ በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው። ይህ ያመጣው ከፅንፈኝነትና የእኔ እምነት ብቻ ትክክል ነው ከሚል ጥላቻ የመነጨ ነው። በሌሎች አገራትም መሰል ድርጊቶች ተከስተዋል። ለእኔ በኢትዮጵያ የዚህ ሥጋት አይታየኝም። ፖለቲከኞቹ አደብ ቢገዙ፣ በህግና ሥርዓት ብቻ መኖር ቢችሉና ሌቦችን መቆጣጠር ቢቻል መልካም ነው። መንግሥት እነዚህን የፅንፈኝነት አስተሳሰቦች ማስቆምና ፈር ማስያዝ አለበት። ሃይማኖት መሸሸጊያ ከሆነ አደጋ ያመጣል። መንግሥት በአጉሊ መነፅር መከታተል ይጠበቅበታል። እኛ አገር የሚያፈናቅሉት፣ የሚያጋጩት፣ ጉልበት የሚሰጡትና ጊዜ የሚወስዱት ጥቃቅን ነገሮች ናቸው። ሁል ጊዜ ትንንሽ ነገሮች ላይ ማተኮርም ተገቢ አይደለም። በዱሮ ባህላችን ቡና እየተጠጣ የሚፈታ ችግር ነው በትልቁ የሚራገበውና አገር እያፈረሰ ያለው። ስለዚህ መንግሥት በዚህ ላይ መሥራት አለበት። ወደ ዋናው ነጥባችን ስንመለስ ኢትዮጵያ ከሃይማኖት አንፃር ሥጋት አለባት የሚል እምነት የለኝም። ምክያቱም ክርስቲያንና ሙስሊም ወይንም ሌሎች እምነት ተከታዮች ፈፅሞ ርዕስ በርዕሳቸው የመጠፋፋት ፍላጎት የላቸውም። ለዚህ የሚሆን መሰረትም የለም። ምናልባት መንግሥት በቀጣናው ያለውን ጂኦ ፖለቲክስ ላይ ትኩረት ቢያደርግ መልካም ነው። በርካታ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ውስጣዊ ችግሮችን ትቶ ወደ ውጭ አተኩሯል ይላሉ። በእኔ እምነት ግን የጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኬኒያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ጉዳይ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በተለይም እንደ ሶማሊያ ያሉ ፀረ ኢትዮጵያ መፈልፈያ ቦታዎችን በሚገባ መከታታል ይገባል። በእርግጥ እነዚህ ቀደሞም ጅምሮች ነበሩ። መሪዎችም የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ችላ ብለው አያውቁም። የተለየ የሚያደርገው ዶክተር አብይ ጠንከር አድርገው ትስስሩን ማጠናከራቸው ነው። ይህም ትክክለኛ አካሄድ ነው። አሁንም ቢሆን በእምነት ውስጣዊ ችግር የመፍጠር ፍላጎት የለም ብሎ መደምደም አይቻልም። ለአብነት ላለፉት ሦስት ዓመታት የኃይማኖት ግጪት ለመቀስቀስ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። ብዙ መራራ ዘር ተዘርቷል፤ ይህንን በቅርበት ስለማውቀው ነው የማወራው። ግን የእምነት ተከታዮችም ሆኑ ትውልዱ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚያነሳሳ ሳይሆን አንዱ ለሌላው ከለላ ሆኗል። አሁንም ቢሆን ፍላጎት የለም ማለት አይቻልም። ግን ወደ ተግባር ለመቀየር ኢትዮጵያ ምቹ አገር አይደለችም። ከሰባት ዓመት በፊት ዩኒቨርሲ ቲዎችን ውስጥ የጦር አውድማ ለማድረግ ከፍተኛ ስትራቴጂ ተቀይሶ ይሠራ ነበር። ሌላው ቀርቶ ሙስሊምና ክርስቲያን ተማሪዎች አብረው እንዳይቀመጡና ሻይ እንዳይጠጡ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ነበር። ግን የሃይማኖት አባቶች፣ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና ወጣቶች በመተባበር አክሽፈውታል። ይሁንና ትናንት የተሞከረው ስለከሸፈ ነገ አይሞከረም ማለት አይደለም። በዚህ ላይ በጥንቃቄ መሥራት ይገባል። አሁን ያለው ችግር ፖለቲካ ሽኩቻ ሲሆን፤ በውይይት የሚፈታ ነው። የሃይማኖት ግጭት ከተነሳ ግን እንዲህ ቀላል አይሆንም። ይልቅስ የሚያስፈራው አንዱ ሃይማኖት በሌላው ላይ የሚያስነሳውን ሳይሆን ሃይማኖቶች ውስጣቸው ያለው አስተዳደር ችግር ሃይማኖቶቹን አደጋ ውስጥ እንዳያስገባቸው መሥራት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በተለይ ጂኦ ፖለቲክሱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የመንግሥታቸው አካሄድ በጥሩ ጎኑ የሚታይ ነው ብለዋል። የኤርትራን ጉዳይ ጨምሮ የቀጣናው ጉዳይ ከውስጥ ጉዳይ የተለየ ተደርጎ አይታይም ያሉበት ምክንያት ምንድን ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ዶክተር አብይ ከመምጣታቸው በፊትም ኢትዮጵያና ኤርትራ መሀል እርቅ መኖር እንዳለበት አምናለሁ። ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም መኖር አለብን። ከዚህ በፊትም ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገናል። በተለያዩ ጊዚያት ይህን ሀሳብ አቅርበናል። ለምሳሌ ከዶክተር አብይ በፊትም ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፓርላማ ንግግር ሲያደርጉ «ኤርትራ ድረስ ሄጄ እታረቃለሁ» ብለዋል። ትክክል ነው። ጎረቤትህን ሠላም ካላደረግህ የአንተ ሠላም ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። አሁን ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ዓለም አንድ ሰፈር ሆናለች። ዕከሌ ሩቅ ስለሆነ እኔን ምንም አያደርገኝም የሚባልበት ዘመን አይደለም። ወይም እኔ ምንም ልጎዳው ልጠቅመው አልችልም የሚባልበት ዘመን አይደለም። ዓለም ተሳስሯል። ወደ ጎረቤት ሀገር ደግሞ ስትመጣ የበለጠ የተሳሰረ ነው። ስለዚህ ከሩቆቹ ጋር መገናኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ወደ ጎረቤትህ ስትመጣ ደግሞ እጅግ እጅግ አስፈላጊ ነው። እነሱ እንደ አጥር ናቸው፤ እኛ በእነሱ መሃል ነው ያለነው። እኛ እንደ አጥር ነን የወደብ ጉዳይ፤ የህዳሴ ግድብ፣ የጽንፈኞችና ኃይማኖት አክራሪዎች ጉዳይ፣ በቀይ ባህር ደግሞ ድንበር ተሻግሮ የሚመጣ ወንጀል አለ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይና በሌሎችም የኢኮኖሚ ትስስሩ አለ፤ ትልቅ አገር ነን። ከእነሱ ጋር ግንኙነት መፍጠሩ ለኢኮኖሚያችን ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። ከዚህ አንፃር ከጎረቤት አገራት ጋር የሚደረገው ግንኙነት ከበፊቱ በተጠናከረ መልኩ መሄዱ በእጅጉ ጥሩ ነው። ከኤርትራ ጋር ደግሞ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን እግዜር ሳይሆን ሰው ነው የለያቸው። አንድ የነበሩና ሊለያዩ የማይችሉ ህዝቦች ሆነው ሳለ ፖለቲካ ነው የለያቸው። ሁለት አገር ሆነን እንኳን ድንበር ሳያስፈልግ መኖር ሲቻል የፖለቲካው ሁኔታ ይሄን ችግር ፈጥሯል። ኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን አግብተዋል ወልደዋል። ኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ የሄዱት እንኳን እግራቸውና አካላቸው ነው እንጂ ልባቸው እዚህ ወይም እዚያ ነው ያለው። እነዚህን ህዝቦች አንድ ማድረግ በብዙ መልኩ ይጠቅማል።የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሥራቱ ያንን ችግር ለማርገብ ተችሏል።

አዲስ ዘመን፡- ጉባኤው በበጀት ራሱን ችሎ ሳይሆን መንግሥት ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የመንግሥት አጀንዳ ፈፃሚ ናቸው የሚል መከራከሪያም ይቀርባል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- በጀት ከመንግሥት ነው መባሉ ትክክል አይደለም። ትልልቅ ተቋማት አብረውን ይሠራሉ። ከተባበሩት መንግሥታት በጀት የሚያገኙ እኛን ጨምሮ ጥቂቶች ናቸው። እኛ ተወዳድረን፤ ፕሮፖዛል ሠርተን በሥራ አሳምነን ነው የምንቀበለው። የመንግሥትን አጀንዳ የምንሠራ ቢሆን እነዚህ ተቋማት ከእኛ ጋር አይሠሩም። እ.ኤ.አ በ2018 በአፍሪካ ለሠላም ትልቅ አበርክቶ በማሳደሩ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ተሸልሟል። ከቀድሞ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም እውቅና የተሰጠው ተቋም ነው። በበጀት ረገድ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ድርጅቶች ናቸው የሚያግዙን። ሌላው እዚህ ውስጥ ያሉ ተቋማት እነማናቸው ብለን እንጠይቅ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ይዘን በጀት ችግር ውስጥ የምንወድቅበት ምክንያት የለም። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች አለ። የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርሲቲያን ራሳቸው ይደግፉናል፤ ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ስለሆነችም ከሚደግፉን አካላት ጋር ያገናኙናል። ሰባት ተቋማት ድጋፍ ያደርጋሉ። ስለዚህ ከመንግሥት አንለምንም። ወደፊት ግን መንግሥት መደገፍ አለበት ብዬ አምናለሁ። መንግሥት ገንዘብ የሚሰበስበው ከታክስ ከፋዩ ነው። ስለዚህ ለታክስ ከፋዩ ፍላጎት መቆም እንጂ ለመንግሥት አይደለም የምንቆመው። መንግሥት ቢሰጠንማ እልል ብለን ነው የምንቀበለው። ግን ብሩን ወስደን ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም መሥራት አለብን። በተረፈ መንግሥት ይህን ብር እንስጣችሁና ይህንን አድርጉ ብሎ ማዘዝ አይችልም። መንግሥት ራሱ በጀት ለማስተዳደር ባለአደራ ነው። ኃላፊነቱ ኢትዮጵያ ህዝብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንዲያውም የኃይማኖት ሰው ንግግር የተገደበ ነው ይባላል፤ እርስዎ ምን ይላሉ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- አይ! እኔ በእሱ አላምንም፤ የምትገደበው ለራስህ ጥቅምና ክብር እንዲያውም «እናንተ እንዲህ ተሰሚነቱ እያላችሁ ለምን አትናገሩም? ይሉናል። እኔ ወጣቶቹን አነሳስቼ ወደ እሳቱ ልከታቸው አልፈልግም። ራሴን በዲሲፒሊን መምራት አለብኝ። ያመንከውን በሙሉ በአደባባይ አትናገርም። የግልህሲሆን ነው እንጂ። በዚያ ደረጃ በአደባባይ ተናግረህ ሰዎች ወደ ግጭት እንዲሄዱ ማድረግ የለብህም። አንዳንዴ እያመመህም ዝም እያልክ የምትሸከመው ነገር አለ። ምክንያቱም እኔና አንተ የምንነጋገረው ንግግር አንድ አይደለም። እኔ ስሳሳት እንኳን «መጋቤ ዘሪሁን የተናገረው እውነት ቢሆን ነው» ብሎ ህዝብ ይወስዳል። እኔ ተሳስቼ ህዝቡ መሳሳቴ እስኪገባው ድረስ ይከተላል። ስለዚህ አደገኛ ነው። ለዚህ ነው በጥንቃቄ ስንናገርም ስንሄድም የቆየነው። አሁን የምናገረው ነገር የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ተብሎ ነው የሚሄደው። ከሁለት ሳምንት በኋላ ስናገር ደግሞ መጋቤ ዘሪሁን የቀድሞ ጠቅላይ ፀሐፊ ተብሎ ነው። በጣም ልዩነት አለው። አሁን የምናገረው በዛ ትርጉም ስለሚሄድ ነው። ከዛ በኋላ የሚሄደው ግን የማምንባቸው ለአገር የሚጠቅመውን ይህ ነው ብዬ የማምንበትን ሃሳብ በራሴ የማራምደውን አራምዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ከእውነት ይሸሻሉ ማለት ነው?

መጋቢ ዘረሁን፡- አልሸሽም። እውነቱንማ ነግሬሃለሁ። እውነት በሁለት ይከፈላል። አንዳንዱ አንፃራዊ ነው። ሙሉ ለሙሉ እውነት በሆነው ላይ ወደ ኋላ አልልም። ሃይማኖቴም ስለማይፈቅድለኝ እውነት የሆነውን እውነት እላለሁ። አንፃራዊ የሆነ እውነት ግን ለእኔ እውነት የሆነ ነገር፤ ለሌላው እውነት ላይሆን ይችላል። ስለዚህ እኔ የምናገረው ስለ ክርስቲያን እውነት የሆነ ነው ብዬ የምናገረው በሌላው ሃይማኖት ደግሞ እውነቱ ሌላ ሊሆን ይችላል። በዚህ ማዕዘን ማየት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከሁለት ሳምንት በኋላ አሁን ካለሁበት ኃላፊነት እለቃለሁ ብለዋል። ምናልባት በኃላፊነቱ ይቀጥሉ የሚል ጥያቄ ቢቀርብስ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- እኔ መልቀቂያ አስገብቼ የነበረው ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ እንድቀጥል ተጠይቄ መቀጠል እንደማልፈልግ አሳውቄያለሁ። ለስምንትና ዘጠኝ ወራት ገደማ በዚህ አጀንዳ ላይ ነበር ስንወያይ የቆየነው። አሁን ግን መተማመን ላይ ደርሰናል። ምክንያቱም አንድ ቦታ ላይ ስምንት ዓመት ከሠራህ በቂ ነው። ሰባቱም ሃይማኖት በተደጋጋሚ እንድቀጥል ጠይቀውኛል። ነገር ግን የጋራ ተቋም ሲሆን ደግሞ የዋናው ፀሐፊውም ስልጣን ከተለያየ የእምነት ተቋማት መሆን አለበት። እኔ እዛ ሙጭጭ ብዬ ስምንት ዓመት መቆየቴ አብሮነትንም አያሳይም። የእኔ አቅም እዚህ ድረስ ማምጣት ነበር። ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ ከእኔ የተሻለው መጥቶ ከፍ ወዳለ ደረጃ ይወስደዋል ብዬ አምናለሁ። ዕድሉ ደግሞ ለሌሎች መሰጠት አለበት። መሪነቱም ከተለያየ የሃይማኖት ተቋማት ሲሆን አብሮነቱም እየጎለበተ ይሄዳል ብዬ ስለማስብ ጭምር ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሚጨምሩት ሀሳብ ካለ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ብዙውን አንስተናል፤ አንዲት ነገር ግን መጨመር እፈልጋለሁ። የክልልም ሆኑ የፌደራል መንግሥታት አገር የመምራት ነገር ቀላል ባለመሆኑ ነገሮችን በሰከነ መንገድ የማየት፣ ተረጋግቶ አብሮነት ላይ መሥራት እንዲችሉ የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋል። መንግሥት ውጤታማ እንዳይሆንና ነገሮችን እያወሳሰብክ እንዲያቅተው ታደርገዋለህ። በተቃራኒው እንዲሳካለት የምትሻ ከሆነ ነገሮችን እያቀለልክ እንዲሳካለት ታደርጋለህ። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ እንዲሁም አገር እንደ አገር እንዲቀጥል ህዝባችን ሠላሙ እንዲጠበቅ፣ የሚሞትና የሚጣላ ህዝብ እንዳይኖር ለማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት።

አንዳችን ለሌላችን በጎና ቅን እያሰብን አብረን የምንኖርባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት ትብብር ያስፈልጋል። መንግሥትን መደገፍ ማለት ግለሰብ ከመደገፍ የሚያልፍ ነገር ነው። ሌላው የትንሣኤ በዓል ስለሆነ ምናልባት በጥላቻ በቂም በመለያየት ውስጥ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት አንዳቸው ለሌላቸው ስልክ ደውለው «በዚህ ምክንያት እኔ ያንተ አካሄድና አሠራር አልተመቸኝም ነበር።

ነገር ግን ለአገራችን ሠላምና አንድነት አብሬ መቆምና መሥራት እፈልጋለሁ። ስለዚህ በአንድነት እንደገና ተነስተን አብረን እንቁም» ብለው ተነሳሽነትን መውሰድ ይገባቸዋል። አንዱ የክልል ፕሬዚዳንት እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ይዞ ቢሄድ፤ ጠቅላይ ሚንስትራችን ራሳቸው እንደዚህ ዓይነት የአብሮነት ጥሪዎችን እያስተላለፉ በጋራ እንድንቆም ማድረግ ቢቻል መልካም ነው።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችንም ወጣቶችን በማነሳሳት ህዝቡና የኃይማኖት ተቋማት በተመሳሳይ ለሠላምና ለአንድነት መተባበር አለባቸው። ኢትዮጵያ አማራጭ የሌለን ብቸኛ አገራችን ናት። ወጣቶቻችን የተሻለ ነገር ስለሚፈልጉ እኛም ስናልፍ ቢያንስ ከጥሩ ክብር ጋር ለማለፍ በቀሪ ዕድሜያችን ጠንክረን መሥራት ይጠበቅብናል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

መጋቢ ዘሪሁን፡- እኔም ስለሰጣችሁኝ ዕድል አመሰግናለሁ

Filed in: Amharic