>

የጎሳ ፖለቲካ በሕግ እንዴት ይታገድ? (ሀይለገብርኤል አያሌው)

የጎሳ ፖለቲካ በሕግ እንዴት ይታገድ?
ሀይለገብርኤል አያሌው
ወድሞቻችን የጎሳ ፖለቲካ በሕግ ይታገድ ሲሉ ዛሬ ሰልፍ ወጥተው ውለዋል:: ”አይጥ በድመት አፍንጫ በኩል ሄዶ ገበያው ቀና ነው ቢሏት ሸመታው መልካም ነበር መንገዱ ባልከፋ” አለች ይባላል::
ሃሳቡ መልካም ነው:: ቢሆንልንና ዘመኑን የሚዋጅ የፖለቲካ ርዕዮት ብንታደል ባልከፉ:: ከጎሳ አስተሳሰብ  ተላቀን የዜግነትን አመለካከት ለማንገስ በመጀመሪያ ሁሉም በሗላ ኪሱ የያዛትን ጎጠኝነትና የቡድን ፍላጎት አራግፎ በንጹህ ሕሊና መሰለፍ አለበት:: በመርህ ላይ ተመስርቶ እንጅ በፖለቲካ ብልጠት ላይ መሆን የለበትም::መሬት ላይ ያለው እውነት ተቀብሎ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሃሳቡን ማራመድ ይጠበቅበታል::
ሕዝባችን የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን ያሉትን በገንዘቡ በችሎታውና በሕይወቱ ጭምር አግዟል:: አብሯቸው ተሰልፎ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል:: የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞችና የትግሉ መሪዎች የተነሱለትን አላማ ከግቡ እንዲደርስ በወኔና በጽናት መምራት አቅቷቸው ትጥቃቸውን ፈተው የጎሳ መሪዎች ካዳሚና ሎሌ መሆናቸውን አይተናል:: ተስፋ አድጏቸው የኖረውን ሕዝብ ሜዳ ላይ ጥለው አፈግፍገዋል:: መናኛ ጎጠኞች አደባባዪን ያለከልካይ እንዲዙት ለቀው የጏዳ ጠባቂ ሆነዋል::
ምሳሌ የሚሆን ለመርህ የሚቆም የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ድርጅት በሌለበት የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሕዝቡ ምን ማድረግ ነበረበት:: ወይ በማንነቱ ተደራጅቶ የመጣበትን አደጋ መታገል አለያም ቁጭ ብሎ የሚደርስበትን መቀበል::
ለጥቂቶች እንደ ኦነግና ሕወሃት ላሉት በዘር መደራጀት ቀደም ያለ የጥላቻ የበቀልና የዘረፋ ፍላጎት ማራመጃ የፖለቲካ አቅጣጫ ሆኖ ቆይቷል:: ለተቀረው እንደ አማራው ጋንቤላ አፋርና የደቡብ ብሄሮች በማንነት መደራጀት እራስን ከጥፋት ለመከላክ ያለው ብቸኛ ምርጫ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል::
በተለይ የአማራው ሕዝብ በዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነን ባሉ የፖለቲካ ነጋዴዎች አዘናጊ ቅስቀሳ ተወናብዶ እራሱንም ሃገሩንም ማዳን በሚያስችለው መንገድ ተደራጅቶ እንዳይገኝ ተደርጎ ቆይቷል:: ዛሬ ላይ ጊዜና ሁኔታው አንቅቶት በሚያስደምም ሁኔታ አማራው በማንነቱ ተደራጅቶ ሊቃጣበት የሚችለውን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ተዘጋጅቷል:: ይህ የአማራው ጠንካራ ዘውጌ አደረጃጀት ያስደነበረው ጥላቻ ያሰከራቸው  ጽንፈኞችን ብቻ ሳይሆን በዜግነት ፖለቲካ ሲነግድ የኖረውን ተንበርካኪ የፖለቲካ ነጋዴ ጭምር ነው::
ከእንግዲህ የብሄር አደረጃጀትን ካለበቂ ዋስትናና ሃገራዊ የፖለቲካ ማሻሻያ ውጪ በተለይ የአማራው አደረጃጀት በምንም መልኩ መለወጥ የለበትም:: አማራው መነሻውም መድረሻውም ኢትዮጵያዊነት ነው:: ከኢትዮጵያም ያነሰ ሃገር የለውም:: አማራው በጸረ ኢትዮጵያ የበታችነት ስነልቦና ያዳሸቀውን ግመሬና ጥላቻ ያሳበደውን መንጋ አደብ ሳያስገዛ ማህበራዊ ሰላምና ሃገራዊ እርጋታ የማያገኝ በመሆኑ የጀመረውን የዘውግ አደረጃጀት በመፈክር ጋጋታም ሆነ በባዶ አዋጅ ሊተው አይችልም::
ወደ ዜግነት ፖለቲካ ለማምራት የሃገራችን የፖለቲካ ምህዳር በመጀመሪያ መስተካከል ይኖርበታል:: ለዚህም በመጀመሪያ
#ያለ ሕዝብ ፈቃድ በሃገሪቷ ላይ የተጫነውና የዘር ፖለቲካው መመሪያ አመንጪው ሕገ መንግስት ለማሻሻል ሲቻል
#ብሄራዊ መግባባት ላይ ሲደረስ
# በጥላቻ ትርክት ላይ የቆሙ ሃይሎች በይፉ አቋማቸውን ማስተካከል ሲችሉ::
#አማራውን ጠላት ተደርጎ የተነዛው ፕሮፓጋንዳ ስህተት እንደነበር በብሄራዊ ደረጃ  ታምኖበት መገለጽ ሲችል::
#የሃገሪቱ መሪዎች የአፍ ሳይሆን የተግባር የአሻጥር ሳይሆን የሃቅ አድሏዊነትን ትተው በእኩልነት ለመፍትሄው መቆም ሲችሉ::
#መንግስት ሕግና ስርአትን ማስከበር ሲችል መፈናቀልና ዜጎችን በማንነታቸው ማሳደድ እንዳይኖር ሲከላከል ሃገር የመምራት ቁመና ሲኖረው
 ያኔ ቢያንስ መነጋገር ከብሄር ፖለቲካ ወደ ዜግነት ርዕዮት የመሸጋገሪይ አቅጣጫን መያዝ ይቻላል::
ሰልፈኞች የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ አክቲቪስቶች እነዚህን ሁኔታዎች እንዲሟሉ መጠየቅ ተገቢ ሆኖ እያለ ሁሉንም በብሄር ተደራጀ በሚል በአንድ ቅርጫት ከቶ ማውገዝ ተገቢም ሚዛናዊም አይደለም መፍትሄም አያመጣም:: የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ሳይከተሉ በውግዘትና በመፈክር ጋጋታ የበለጠ የጎሳ ፖለቲካውን እንዳያጠብቁት መጠንቀቅም አስተዋይነት ነው::
በመጨረሻም በቅንነት የጎሳ ፖለቲካ ይታገድ ስትሉ ለተነሳችሁት ወንድሞቼ ያለኝን አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ:: እንደ ሃገር የመዳኛችን መንገድም እንደሆነ እረዳለሁ:: ነገር ግን በአካሄድና መሬት ላይ ካለው እውነታ አንጻር መንገዳችን ቢለያይም  መዳረሻችን ግን ተመሳሳይ እንደሆነ እምነቴ ነው::
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅልን!
Filed in: Amharic