* ግዛታዊ ኣንድነት ለትግራይ ህዝብ ህልውና የማስቀጠል ጉዳይ ነው!!
ኣንድ ብሄር በቋንቋው ለመማር፣ ለመዳኘትና ለመተዳደር እንዲሁም ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ታሪኩ፣ ፍልስፍናው፣ ስነ ጥበቡ ወዘተ ለመጠቀም፣ ለማበልፀግና ለመጠበቅ የራሱ ግዛት ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ ማህበራዊ መሰረቱ በማጥበብና ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን በማሳጣት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነቱን ለማዳከም በግዛትና በኣገር የከፋፈሉት መንግስታትና ስርኣቶች ብረት ኣንስቶ ታግሎ ሊጥላቸው የወሰነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በተሟላ መልኩ ባይሆንም በእልህ ኣስጨራሽ ትግልና መስዋእት መነሻ ሊሆን የሚችል ውስጣዊ ሉኣላዊነቱ እና ግዛታዊ ኣንድነቱ ሊጎናፀፍ ችሏል፡፡
ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦችም ተመሳሳይ የመብት ጥያቄ ኣንግበው ይታገሉ ስለ ነበር የትግራይ ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማረጋገጥ ኣልሞ ያካሄደው ትግልና የተጎናፀፈው ድል ተጋርተውታል፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት የሚያጎናፅፋቸውን ውስጣዊ ነፃነት ያላቸው ክልላዊ መንግስታትና በጋራ ኣስተዳደር የሚመራ ፌዴራላዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል ህገ መንግስት ኣፅድቋል፡፡ ውስጣዊ ሉኣላዊነትና ግዛታዊ ኣንድነት በዘላቂነት ለመጠቀም፣ ለማጎልበትና ለመጠበቅ ዋስትና የሚሰጥ ህገ መንግስታዊ ስርኣት እና ህገ መንግስታዊ ኣሰራር ኣስቀምጠውለታል፡፡
ይሁን እንጂ የህዝቦች ኣንድነት፣ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማይዋጥላቸው የፖለቲካ ሃይሎች በመራራ ትግልና መስዋእትነት የተረጋገጠውን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ላይ የቆመው ውስጣዊ ሉኣላዊነት እና ግዛታዊ ኣንድነት ለማረጋገጥና ለማስቀጠል የተዘረጋውን ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርኣቱን ለማፍረስ ከመንቀሳቀስ ኣልቦዘኑም፡፡ በዚህ መሰረት የተስፋፊነትና የጠቅላይነት ምኞታቸውን የገደበ መስሎ ስለ ተሰማቸው በግዛታዊ ሉኣላዊነትና ኣንድነት ፣ በህዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የቆመው ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርኣቱ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ተፈጥረዋል፡፡
መንግስታዊ ስልጣን የተቆጣጠረው ኢህኣዴግ ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ኣሰራሩን በማርቀቅና በማፅደቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ቢሆንም ባለፉት የትግበራ ዓመታት ፌደራላዊ መንግስታዊ ቅርፅ ያለው በተግባር ግን የክልሎች ውስጣዊ ሉኣላዊነት በሚፃረር መልኩና ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ማሕበራዊና ሌሎች ፖሊሲዎች ከአንድ ማዕከል በመዘርጋት ኣሃዳዊ ስርዓት ሲገነባ እንደነበር ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ያምናል፡፡ይባስ ብሎ ደግሞ በኣሁኑ ወቅት ህገ መንግስቱ እና ፌዴራላዊ ስርኣቱ ለሚፃረሩ የፖለቲካ ሃይሎች ድጋፍ እየቸራቸው ብቻ ሳይሆን ራሱ ኢህኣዴግ ፀረ ህገ መንግስት ኣቋም እያራመደ እንደሆነና ህዝቦችን ያስተሳሰረው ቀጭኑና የመጨረሻው የፌደሬሽን ገመድ ለመበጠስ እየሰራ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል።
በዚህ መሰረት ኢህኣዴግ በብቸኝነት የተቆጣጠረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህገ መንግስቱ እና ህገ መንገስታዊ ስርኣቱ (ኣሰራር) የጣሰ የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኣጣሪ ኮሚሽን የሚባል ሊያቋቁም ችሏል፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መረጋገጥ እንዳለበት እውቅና በመስጠቱ በህዝቦች ትግል ለስልጣን የበቃው ኢህኣዴግ ህገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርኣቱን በመናድ፣ውስጣዊ ሉኣላዊነት በመጋፋትና በውጤቱም አገር ለመበተን መንቀሳቀሱ ታሪካዊ ምፀት ያደርገዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኣጣሪ ኮሚሽን በፌዴራል እና በትግራይ ክልል በየደረጃ ባሉ ምክር ቤቶች በተወካዮቹ በኩል እንዲሁም በሰልፍ ተቃውሞውን ኣሰምቷል፣ የኮሚሽን ማቋቋሚያ ኣዋጁንም ኣውግዞ ውድቅ ኣድርጎታል፡፡ ሆኖም የትግራይ ህዝብና በየደረጃው ያሉ ተወካዮቹ ተቃውሞ ችላ በማለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ በኣብላጫ ድምፅ ሾሟል ።
ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በፌዴራል እና በክልል ምክር ቤቶች ለተወከሉና የህዝባቸውን አቋም ላሰሙት ኣባላት ያለውን ኣክብሮት ከፍተኛ ነው፡፡ ለወደፊቱም የራስን እድል በራስ የመወሰን ኣርነት በመጣስ የተስፋፊነት ምኞት ከግብ ለማድረስ የተቋቋመው ህገ መንግስታዊ መሰረትና ኣሰራር የሌለውን የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኣጣሪ ኮሚሽን በትግራይ ላይ ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ኣብሮ በፅናት እንደሚታገል በዚህ ኣጋጣሚ ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡
የትግራይ ህዝብ በመራራ ትግሉ እና መስዋእትነቱ ያረጋገጣቸው እንደ ህዝብ ማንነቱ ጠብቆ የመቀጠልና ያለ መቀጠል ወሳኝ የሆኑ ውስጣዊ ሉኣላዊነት፣ ግዛታዊ ኣንድነት እንዲሁም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብቶች ለድርድር የሚቀርቡ ኣይደሉም፡፡ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የትግራይ ህዝብ በትግሉ ያረጋገጣቸው ኣላማዎች ለመጠበቅና እንዲሁም ቀሪዎቹን ከግብ ለማድረስ በፅናትና በቁርጠኝነት ይታገላል፤ ህገ መንግስቱ እና ህገ መንገስታዊ ስርኣቱ በማፍረስ ፌደሬሽኑን ለመበተን የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳስባል፡፡
ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የህገ መንግስት ጥሰት የኢትዮጵያ ህዝቦች በኣንድ ፌዴራላዊ ስርኣት ለመኖር የገቡት ቃል ኪዳን ማፍረስና ፌደሬሽኑን መበተን እንደሆነ ነው የሚረዳው ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ፌዴራሊስት ሃይሎች ጉዳዩ የሀገሪቱና የፌደሬሽኑ ቀጣይ ዕጣፈንታ የሚወስን እንደመሆኑ ኢህኣዴግ ከህገ መንግስታዊ ጥሰት እንዲቆጠብና በተወካዮች ምክር ቤት በኣብላጫ ድምፅ የተቋቋመው የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኣጣሪ ኮሚሽን እንዲሻር በፅናት እንዲታገሉ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ጥሪ ያስተላልፋል ።
ዘለኣለማዊ ክብር ለትግራይ ሰማእታት!!
ሳልሳይ ወያነ ትግራይ
ግንቦት 9 /2011 ዓ/ም
መቐለ