>

ታሪክን ማዕከላዊ እና ዳርቻ የማድረግ መዘዞች!!! (ሞሀመድ እድሪስ)

ታሪክን ማዕከላዊ እና ዳርቻ የማድረግ መዘዞች!!!
ሞሀመድ እድሪስ
“Public Diplomacy የሚባል ኮርስ ስወስድ ፕሮፌሰሩ አንድ ከ5 እስከ 10 ገፅ የምትሆን አጭር ፔፐር እንድንሰራ ያዘናል፡፡ የፔፐሩ ርዕስ “The future of ……” የሚል ነበር፡፡ ሁሉም ተማሪ በአገሩ ጉዳይ በውስጡ ጥያቄ የፈጠረበትን እና የወደፊት መፃዒ ዕድሉ በሚያሳስበው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ፅሁፏን እንዲያዘጋጅ ነበር የታዘዘው፡፡
ከ3 ሳምንት በኋላ ፅሁፋችንን ስናስገባ መምህሩ ላይ ግርምት ቢጤ የጫሩበት ሁለት ርዕሶች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው “The Future of Liberal Values in Liberal Democracy” የሚለው የአንዲት ቱኒዚያዊ ተማሪ ርእስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እኔ ይዤ የቀረብኩት “The Future of History” የሚለው ርዕስ ነበር፡፡ ‹‹የሊበራል ዴሞክራሲ እሴቶች›› ዛሬ በምዕራቡ ዓለም በተለይም ከስደተኞች ጉዳይ ጋር በተያያዘ የገቡበትን ቅርቃር ባየሁ ቁጥር ሁሌም በዚያች ወዳጄ ርዕስ እደመማለሁ፡፡ የአገሬ መፃዒ ዕድል ከነገው የፖለቲካ ግብ ይልቅ በታሪክ ላይ የተንጠለጠለ እየሆነ መሄዱ፣ ታሪኩ ደግሞ በተራው እጣ ፈንታው ያልለየለት መሆኑን በተረዳሁ ጊዜ ደግሞ በራሴ ርዕስ እገረማለሁ፡፡
“The Future of History” ለሚለው ሥራ ማጣቀሻ በዋናነት የ“John Lukacs”ን ጨምሮ የተለያዩ መፅሀፍትን ለማገላበጥ ሞክሬያለሁ፡፡ ብዙዎቹ በታሪክ አስተምህሮ፣ በታሪክ አጠናን፣ በታሪክ ሚና፣ በፖለቲካ-ታሪክ መስተጋብር እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያተኩሩ ነበሩ፡፡ የእኔ መሰረታዊ ጥያቄ የህዝቦቿ ታሪክ ገና ባልተጠናላት አገራችን ኢትዮጵያ ከታሪኮቿ አንዱ ተጠንቶ ወደ መድረክ ሲመጣ የሚያጋጥመው መፃዒ ዕድል ምን ሊሆን እንደሚችል መልስ መሻት ነበር፡፡
ለዚህ ጥያቄ መነሻው በጣም ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላት አገር ነች፡፡ ህዝቦቿም በተናጠል ሰፊ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ የጋራ ታሪካቸውም ገና በወጉ አልተዳሰሰም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት በሆኑ አገራት ውስጥ የታሪክ ስራዎች ብቻ በርካታ ቤተ መፅሀፍትን ሊሞሉ በተገባ  ነበር፡፡ በአገራችን ግን ማጣቀሻ የሚሆኑ ስራዎች እንደልብ በማይገኙበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ከስራዎቹ ማነስ በላይ ግን ወደፊት የሚጠኑ ሰፊ የህዝብ ታሪኮችን እጣ ፈንታ አስቀድመው ከተዘጋጁ ጥቂት ስራዎች አንጸር ብቻ የማየቱ አባዜ እና አዳዲስ ስራዎች እንደአገር ዋነኛ ታሪክ ተገቢ ስፍራቸውን ሊያገኙ የሚችሉበት አካሄድ ግልፅ አለመሆኑ ትልቅ ትኩረትን የሚሻ ሆኖ ይታየኛል፡፡
በባለፈው ፅሁፌ ታሪክ የተፃፈውም ያልተፃፈውም፣ ወደፊት የሚፃፈውም፣ ምናልባትም በጭራሽ የመፃፍ እና የመነገር እድል ላያገኝ የሚችለውንም በሙሉ የሚያጠቃልል ያለፉ ክስተቶች ጥቅል ስያሜ መሆኑን አስምሬ ማለፌ ይታወሳል፡፡ ታሪክ ገናናነትን፣ ጭቆናን፣ ትብብርን፣ ጦርነትን፣ ስልጣኔን፣ ኋላ ቀርነትን… ሁሉንም ያካተተ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ታሪካቸው ያልተነገረ የህብረተሰብ ክፍሎች ታሪካቸውን መጻፍ ሲጀምሩ የትኛውን ክፍል ሊተርኩ ይገባል?›› የሚል ጥያቄ መነሳቱ ሙያዊ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም ታሪክ እንደሙያ የባለሙያዎቹ አቅም እስከፈቀደ ድረስ ሁሉንም የመዘገብ ድርሻ ነው ያለው፡፡
ይህን መሰል ጥያቄ መነሳቱ ሙያዊ ካልሆነ ደግሞ ፖለቲካዊ ዓላማን ያዘለ ነው ማለት ነው፡፡ በፖለቲካ ዓላማ ስር ደግሞ አሸናፊ መሆን እና የበላይነትን መጨበጥ የታሪክ አቀራረብን ለመጠምዘዝ የመዋሉ ምስጢር ‹‹ታሪክን አሸናፊዎች ይፅፉታል›› የሚለው ብሂል መስካሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ማህበረ ፖለቲካ ውስጥ አልፎ አልፎ ከይቅር ባይነት ባህሪ፣ ብዙውን ጊዜ ግን ከራስ የምቾት ቀጠና (comfort zone) ላለመውጣት ከመፈለግ የተነሳ የህዝቦችን የጭቆና ታሪክ ለመስማት ያለመፈለግ ተዋስኦ ይታያል፡፡ ታሪካችን ተጽእኖውን የጨረሰ፣ የዛሬው ህይወታችንም ሁላችንንም በሚያስደስት መልኩ ከኢፍትሃዊነቶች የጸዳ ቢሆን ኖሮ በእርግጥም የበደል ታሪክ አይወራ መባሉ ምክንያታዊ  በሆነ ነበር፡፡ ተጨባጫችን ግን እንዲያ አይደለም፡፡ ታሪካችን ተጽእኖውን አልጨረሰም፡፡ ሁላችንም በተስተካከለ መደብ ላይ እንደምንገኝ ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችል አካልም የለም፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ‹‹ሁሉም ህዝብ በጎ ታሪክ አለውና የታሪኩ ገናና እና በጎ ክፍሎች ተመርጠው ይተረኩ›› የሚል ሌላ አማራጭ ይቀርባል፡፡ ለዚህ አማራጭ ማንሳት የምፈልገው መሰረታዊ ጥያቄ ‹‹የሁሉም ህዝቦች ገናና ታሪክ በኢትዮጵያ “mainstream” ታሪክ ውስጥ ቦታው የት ነው?›› የሚል ይሆናል፡፡ በሌላ አገላለፅ ‹‹የህዝቦች ታሪክ አስቀድሞ ‹የኢትዮጵያ› ተብሎ አካዳሚክ እና ፖለቲካዊ የበላይነትን ተቆጣጥሮ ከያዘው ትርክት አንፃር መፃዒ እድሉ ምንድን ነው?››
በበኩሌ  የታሪካችንን መፃዒ ዕድል ከሚወስኑት መሰረታዊ ጉዳዮች ዋነኛው የህዝቦች በአገራቸው ያላቸው የባለቤትነት ድርሻ እና ሚና ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ Trimingham “Islam in Ethiopia” በሚለው መፅሀፉ ‹‹የእስልምና ታሪክ በኢትዮጵያ ያለ ክርስቲያን አቢሲኒያ ታሪክ ባዶ ነው – ቦታ የለውም›› ሲል በታሪክ ውስጥ ማዕከላዊ እና ዳርቻ የሚባሉ ስፍራዎች እንዳሉ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ እንግዲህ አቢሲኒያ/ኢትዮጵያ እንደ አገር መነሻ ከተደረገች የኢትዮጵያ ክርስትናም ያለ ኢትዮጵያ ታሪክ ቦታ አይኖረውም ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እስልምናም እንዲሁ ያለ ኢትዮጵያ ታሪክ ቦታ አይኖረውም፡፡ የዋቄፈታ እምነትም ያለኢትዮጵያ ቦታ አይኖረውም፡፡ እምነቶቹ እንደእምነት የራሳቸው ታሪክ እና ድርሻ ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው ታሪክ ግን ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
አቢሲኒያ የአንድ አካባቢ እና እምነት መጠሪያ ተደርጋ ከተሳለች ግን ዛሬ ላይ አቢሲኒያ ከመንደር የዘለለ ታሪክ አይኖራትም፡፡ ምክንያቱም የአቢሲኒያ ንጉሶች ከሚያስተዳድሩት ግዛት እና ህዝብ በላይ ያስተዳድሩ የነበሩ የሌሎች ህዝቦች መሪዎች በዚህችው በኢትዮጵያ ምድር ነበሩና፡፡ አቢሲኒያ አይታ የማታውቃቸው ስልጣኔዎች በሌላው የኢትዮጵያ ምድር አብበው አልፈዋልና፡፡ ግና የዛሬዋን ኢትዮጵያ የፈጠሯት በተናጠል ራሳቸውን ያስተዳድሩ የነበሩ ግዛቶች እና ህዝቦች እንደመሆናቸው የአንዱ ታሪክ ያለሌላው ባዶ ነው፡፡ የአቢሲኒያ ታሪክ ያለእስላማዊ ሱልጣኔቶቹ ታሪክ ባዶ ነው፡፡ የአቢሲኒያ ታሪክ ያለ ገዳ ስርዓት ባዶ ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ለማውራት አቢሲኒያን መሀል ላይ አስቀምጦ ሌሎችን የማሰስ ዘይቤን የተከተለ የታሪክ አፃፃፍ ስልትም ሚዛን የሳተ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው ነጥብ ‹‹ኢትዮጵያን እናስቀድም፤ ሁሉም ያለኢትዮጵያ ጎዶሎ ነው›› ብለው በሚያምኑ ወገኖች ዘንድ ጥቅል ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል፡፡ ፈታኙ ነጥብ ግን በታሪክ ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ ለመጨበጥ በሚደረገው ጥረት ‹‹ኢትዮጵያ›› የምትባለዋን እመቤት እስትንፋስ እና ደም ግባት በነገስታቱ ታሪክ አምሳል የተቀረጸ ብቻ አድርጎ የማቅረቡ ሂደት ነው፡፡ በተጨማሪም የአቢሲኒያ ነገስታት ታሪክ በመፅሀፍ መልክ ተሰድሮ ሲዘጋጅ ለነገስታቱ የተወሰነ ባህል እና እምነት በማውረስ ‹‹አንድ ራዕይ የነበራቸው፣ ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠርም የትግሉን ባንዲራ እየተቀባበሉ ያለፉ›› እንደሆኑ አድርጎ ለመሳል ጥረት ሲደረግ ይታያል፡፡ በእነዚህ ነገስታት መካከል የጊዜ ክፍተት የሌለው እና መተካካት የነበረበት ፍፁም ወጥ የሆነ የታሪክ ሰንሰለት የነበረ አስመስሎ ለማቅረብ ሲጣር ይስተዋላል፡፡ ከሰንሰለቱ ያፈነገጡ የሚመስሉ እንደ ዘመነ የጁ ያሉ ታሪኮች ሲያጋጥሙ ኢትዮጵያ የተበታተነችበት ኢትዮጵያዊነት አደጋ ውስጥ የገባበት የሚል ታፔላ ከፍ ይላል፡፡
ይህን መሰሉ የታሪክ አቀራረብ የጊዜ ቅደም ተከተልን ብቻ የሚያመላክት፣ በነበረው ወርድ እና ስፋት በማይለካ መልኩ የቀረበ ቢሆን ኖሮ አቀራረቡ ላይ መስማማት ባልከበደ ነበር፡፡ ከዚህ የነገስታት ታሪክ ሰንሰለት በስተጀርባ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ግን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ታሪክ ይህንን ሰንሰለት የተከተለው ክፍል ብቻ መሆኑን እና የሌሎች ህዝቦች ታሪክ ደግሞ ከዚህ ሰንሰለት አንፃር ብቻ እየተቃኘ የሚለጠፍ፣ ተቆርጦ የሚገባ እና ተንጠልጥሎ የሚሄድ የታሪክ ዳርቻ እንደሆነ አድርጎ የማቅረብ ተልዕኮን ያነገበ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሲሆን የታሪክን ማዕከላዊነት እና ዳርቻ ለማሳየት የሚደረገው ጥረት የታሪኩ ባለቤት ነን የሚሉትንም በዚያው መጠን በአገሪቱ ላይ ያላቸውን አሻራ እና ስፍራ ወደመወሰን ይሸጋገራል፡፡ ህዝቦች ያልተፃፉ ገናናም ይሁን የጭቆና ታሪክ ቢኖራቸው የታሪክ ዳርቻ ተደርጎ ከተሳለ ሚዛኑን እንዳጋደለ ይቀጥላል፡፡
በዚህ የተሳሳተ ትርክት መሰረት የአፄዎቹ ዜና መዋዕል እና የንግስናቸው ሰንሰለት የኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹እምብርት›› (መሐል) ተደርጎ ስለሚወሰድ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ ከዚህ ጋር በማስታከክ የመተረኩ ሂደት እንደ ህግ እንዲቆጠር ይጠበቃል፡፡ ሌሎች ታሪኮች የሚተነተኑበት እንድምታም ከማዕከላዊው ታሪክ ጋር በነበራቸው ግንኙነት፣ ባሳደሩበት እና ባሳደረባቸው ተጽእኖ ብቻ እንዲወሰን ለማድረግ ይሞከራል፡፡ ይህንን የአተራረክ ስልት ብዙዎቹ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ምሁራን መከተላቸው ለታሪክ ሙያ ትልቅ በደል ሆኖ ይታየኛል፡፡
እንዲህ ባለው የገነገነ ስህተት ውስጥ በገባ የታሪክ አተራረክ ውስጥ ያልተጠኑ የህዝብ ታሪኮች ወደገበያ ሲመጡ እጣ ፈንታቸው አይታወቅም፡፡ የታሪክ መጻዒ ዕድልም አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ህዝብ ግን ታሪኩን ሲፅፍ መፃዒ እድሉንም አያይዞ መወሰን ይፈልጋል፡፡ የታሪኩን እና የታሪኩን ባለቤት እጣ ፈንታ የጋረደ የታሪክ ግድግዳ ሲያጋጥምም ያለው አማራጭ አንድም ሁሉም የራሱን ታሪክ የታሪክ እምብርት አድርጎ ሌሎች ታሪኮችን ከራሱ ታሪክ ዳርቻ አስጠግቶ ይተርካል አልያም እንደ ‹‹እምብርት›› የተቆጠረውን ታሪክ ዳር አድርጎ የማቅረብን ዘይቤ የሚከተል ‹‹የፉክክር›› ታሪክ አፃፃፍ ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ ‹‹መሐሉን ስትነካው ዳሩ መሀል ይሆናል›› እንዲሉ፡፡ አገራችን በፉክክር ደጃፍ ክፍት እነዳታድር ስለታሪካችን መፃዒ ማን ይጨነቅለት?
የ‹‹ኢትዮጵያዊነት አደጋ ውስጥ ወድቋል›› ስሞታም መሰረታዊ መልዕክቱ ‹‹የነገስታቱ ታሪክ ማዕከላዊ ታሪክ ተደርጎ መወሰዱ እያበቃ ነውና ተሀድሶ ይፈልጋል›› የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡
እንደእኔ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ውስጥ የሚወድቀው ስለኢትዮጵያ መኖር ቀርቶ በኢትዮጵያ ስም መቆመር ሲጀመር ነው፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት የጎበጠን ለማቅናት ጎንበስ በማለት ፈንታ ኢትዮጵያዊነትን ረግጦ በልጦ ለመታየት የሚደረገው አጉል መንጠራራት ብዙም አያራምድም፡፡ የዒትዮጵያ ታሪክ ያለበት ችግር መረጣ እና ማዛባት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ አተራረኩ ሊፈተሸ ይገባል እላለሁ፡፡
(ከአንድ እና ሁለት አመት በፊት የማህበራዊ እና ሌሎች ሚዲያዎች የመከራከሪያ አጀንዳ «ታሪክ» ላይ ያተኮረ ነበር። እኔም በገፄ ላይ ተከታታይ ፅሁፎችን አስነብብ ነበር። ይህ ፅሁፍ ከሁለት አመት በፊት በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተከተበ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ሊባል የሚችል ነው። ከሁለት አመት ወዲህ የተወዳጃችሁኝ ታነቡት ዘንድ እጋብዛለሁ። በዚሁ አጋጣሚም ማህበራዊ ሚድያው አሁን ያለንበትን ወቅታዊ ትኩሳቶች ላይ ካተኮረ ውይይት ተሻግሮ ቀጣይ እጣፈንታችንን በሰከነ መንፈስ መወያያ እንዲሆን እመኛለሁ_ተስፋም አደርጋለሁ።)
Filed in: Amharic