>

“...የኢትዮጵያ ህልውና ኣደጋ ላይ ነው፤ ሃገራችን ከብርሃን ወደ ጨለማ ገብታለች!!!” (የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)

“…የኢትዮጵያ ህልውና ኣደጋ ላይ ነው፤ ሃገራችን ከብርሃን ወደ ጨለማ ገብታለች!!!”
የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
* የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ 28ተኛውን የግንቦት 20 በአልን አስመልክቶ ያወጣው  መግለጫ 
* የኢፌዲሪ ሕገ መንግስትና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን ከባድ ኣደጋ ተደቅኖበታል።..” 
*   “ ሃገራችን ኢትዮጵያን ከብተና ለማዳን፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክንዳቸው ኣጣምረው የሚታገሉበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን…
—-
ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች አስቀምጠነዋል
ግንቦት 20፣ የፅናት፣ የአይበገሬነትና የአቸናፊነት አርማ!! በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ላለው 28ኛው ዓመት፣ የግንቦት 20 የድል በዓል፣ እንዃን በሰላም ኣደረሳችሁ!! ኣደረሰን!!
ግንቦት 20 በህወሓት /ኢህአዴግ/ መራሹ ህዝባዊ መስመር ጥላ ስር የተደራጁት፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያውያን ሃይሎች፣ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን ከጎናቸው ኣሰልፈው ለ17 ዓመታት ያህል የዘለቀውን ረዥምና እልህ ኣስጨራሹ መራራው የትግል ጉዞ፣ ክቡር የህይወት መስዋእትነት ከፍለው፣ የድህነት ዘበኛ የነበረውን አፋኙ ፋሽሽት ወታደራዊ የደርግ ስርዓት፣ ከእነ ግሳንግሱ ግብኣተ መሬቱ እንዲፈፀም ያደረጉበት ዕለት ነው፡፡ በመሆኑም ግንቦት 20፣ በኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ዘንድ ለዘላለም ሲዘከርና ሲከበር የሚኖር ታላቅና የተቀደሰ የድል ቀን ነው፡፡
በመሆኑም ዘንድሮ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የግንቦት 20 የድል በዓል ለ28ኛ ጊዜ የሚያከብሩበት ምክንያት፣ የደርግ ስርዓት የተገረሰሰበት ዕለት በመሆኑ እና ታጋይ ሰማእታት ለማሰብ ብቻ ኣይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅምና ልእላዊነት መከበር ሲሉ የተሰውት ታጋዮች ማሰብ ኣንዱ ዓብይ ምክንያት ነው፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን፣ ግንቦት 20 የኢትዮጵያ የህዳሴ ትንሳኤ ጉዞ የተበሰረበት እና በአጠቃላይ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የተገኙ ዙርያ መለስ ድሎች፣ በዋነኛነት ደግሞ በ1993 ዓ.ም ከተካሔደው ስር ነቀል ተሃድሶ ማግስት ጀምሮ፣ የዓለም ማህበረሰብ ጭምር ደጋግሞ ምስክርነቱ የተሰጠበትን እና ባለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት የተመዘገቡ ባለሁለት አሃዝ፣ ፈጣን፣ ዘላቂነት የነበረው እና ሁሉም በየደረጃው ፍትሓዊ ተጠቃሚ የሆነበትን ማህበረ-ኢኮነሚ ዕድገት አሁን ያለበት ደረጃ ገምግመው፣ ለቀጣይ የትግል ጉዞ እና ተደማሪ ድሎች ለማስመዝገብ ቃላቸው የሚያዱስበት ነው፡፡
ነገር ግን ከሩብ ክ/ዘመን የትንሳኤ ብሩህ ጊዜው ጉዞ በኋላ፣ የግንቦት 20 ትሩፋት የሆኑት የሰላም፣ የዲሞክራሲ እና የማህበረ ኢኮኖሚ ግስጋሴው፣ ካለፉት ኣራት ዓመታት ጀምሮ እንደተገታ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያውያን ሐይሎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ 28ኛው የድል ቀናቸው ሲያከብሩ፣ ፈጣኑ፣ ባቡር ተንገራግጮ፣ ለምንና በማን ችግር ውስጥ እንደወደቀ በጥልቀት ፈትሸው የመፍትሔ አቅጣጫ ቀይሰው ትግላቸው በፅናት እንደሚቀጥሉ ጥርጥር የለውም፡፡
በአጭሩ አገራችን ኢትዮጵያ፣ በአጠቃላይ ካለፉት ጥቂት ኣመታት ጀምሮ፣ በተለይም ካለፈው መጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከድጡ ወደ ማጡ በሆነ የማሽቆልቆል ጉዞ ውስጥ ሰጥማ እየዳከረች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ ከትንሳኤ የለውጥና የህዳሴ ጉዞ ያጣጣማቸውን ድል ተነጥቃ መመለሻ ወደሌለው የውድቀት ጉዞ ገብታለች፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች፣ ደም የተፃፈው፣ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስትና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታትን ብግላጭ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ የህግ የበላይነት ጠፍቶ የጎበዝ አለቃ በየስርቻው እንደ አሸን ተፈልፍሎ የህዝባችን ሰላም አሳጥታል በመሆኑም፣ የህዝቦችን መገለጫ የሆነው የሃገራችን ሉኡላዊነት ኣደጋ ላይ ወድቋል፡፡ የፖሊሲ ነፃነት ቀርፃ ልኣላውነቷ በማስከበር ለዓለም ተምሳሌት ሆና የቆየች አገራችን፣ በአሁኑ ወቅት፣ ገፅታዋ ተበላሽቷል፣ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ስደት፣ ሞት፣ የዕለት ተዕለት ትእይንት ከሆነ ውሎ አድራል፡፡ በህዳሴ ማግስት የተቀረፀት ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ኣልያም እንዲቆሙ ተደጓል፡፡ ምርትና ምርታማነት ቀንሷል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኣጋጥሟል፡፡ የዋጋ ንረት ጣሪያ ነክቷል፡፡
በሃገራችን የተደቀነው ይህንን ሁሉ ችግር እና የመበተን ኣደጋ፣ ዋነኛ ተጠያቂ ከውስጥና ከውጭ የተሰባሰቡት ፀረ -ህዝብ፣ ፀረ-ሰላምና ፀረ- ዲሞክራሲ የጥፋት ሃይሎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የኢፌዲሪ መንግስት እየመራ ያለው ኣካል የጥፋት ሃይሎቹ ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ካላደረገ፣ መዘዙ በኣራቱም የሃገሪቱ ኣቅጣጫ ያለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጋተው መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ይህ ከመሆኑ ግን፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እና የፌዴራል ስርዓቱ የሚደግፍ ሓይሎች፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵ ብሄር፣ ብሄረ ሰቦች እና ህዝቦች፣ 28ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል በድምቀት ሲያከብሩ፣ ኣደጋ የተጋረጠበት ሉኣላዊነታቸው እና ዋነኛ መገለጫቸው የሆነውን ሕገ መንግስታቸው እና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታቸውን ለማዳን፣ ሰላማዊ እና ሕጋዊ ትግላቸው የሚያጧጡፉበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የትግራይ ህዝብና በህወሓት የሚመራው የትግራይ መንግስት፣ ባለፉት 44 ዓመታት ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኣንድነትና ሰላም መከበር፣ ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረ-ሰቦች እና ህዝቦች እኩልነት፣ እንዲሁም ለማህበረ-ኢኮኖሚ ዕድገት እና ፍትሓዊ ተጠቃሚነት በፅናት የታገሉ እና በገንዘብም ሆነ በየትኛውም ሚዛን ሊለካ የማይችል ወደር የሌለው ክቡር የህይወትና የንብረት መስዋእትነት የከፈሉና ኣሁንም በመክፈል ላይ ናቸው፡፡ ይህንን ዘመን ተሻጋሪ ታሪካቸው ደግሞ የሚኮሩበት እንጂ የሚያፍሩበት አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብና በህወሓት የሚመራው የትግራይ መንግስት ከማይናወጥ ህዝባዊ መስመር ፈቅ ሳይሉ ሁሉንም ህዝቦች በእኩል ዓይን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ነገር ግን “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንዲሉ ግንቦት 20 እውን እንዲሆን፣ ከ60 ሺ በላይ የህወሓት ታጋዮች የህይወት መስዋእትነት እንዲከፍሉ ከ100ሺ በላይ ታጋይ አርበኞች ደግሞ አካለ ጎደሎ እንደሆኑ እየታወቀ፣ በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብናልጆች በኢትዮጵያ አብዮት የራሳቸውን የማይደበዝዝ ህያው አሻራ በማሳረፋቸው ብቻ፣ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የትግራይ ህዝብ ሰልዩ ተጠቃሚ እንደሆነ፣ ህወሐት ደግሞ ባለፉት ዓመታት ለተፈጠሩ ችግርች መንስኤና ብቸኛው ተጠያቂ ተደርጎ፣ በሁሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ፣ በተለይም በወጣቱ ትውልድ እንዲታይ፣ ፀረ-ህዝብና ፀረ-ዲሞክራሲ ሐይልች ዘረኛና መርዘኛ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከማሰራጨት ባሻገር፣ በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የትግራይ ህዝብን ጉሮሮ ለማነቅ የሚያስችል እኩይ ተግባራት ፈፅሟል፡፡
አሁን ሰይጣናዊ ተግባራቸው አጠናክረው ቀጥለውበታል። ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተለይም ኢትዮጵውያን ወጣትች፣ ይህንን የመሰለ እኩይና ጭካኔ የተሞላበት የጥፋት ሃይሎች ሴራ ጊዜው ይረዝም እንደሆነ እንጅ እውነታው ሲገነዘቡ ክንዳቸው በእነዚህ ሐይልች ላይ እንደሚያሳርፉት ጥርጥር የለወም፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ከኣደጋ ለማዳን ክንዳቸውን ኣፈርጥመው ሊነሱ ይገባል፡፡ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እና ትግል የኢፌዲሪ ሕገ- መንግስት እንዲከበር፣ የሕግ የበላይነት እንዲነግስ እና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከኣደጋ ለማዳን ነው፡፡ ስለዚህ የጋራ በዓላችን የሆነውን ግንቦት 20 ለ28ኛ ጊዜ ስናከብር የሚከተሉት መልእክቶች ጨብጠን እንደሚሆን አንጠራጠርም።
•የኢትዮጵያ ህልውና ኣደጋ ላይ ነው። ሃገራችን ከብርሃን ወደ ጨለማ ገብታለች። የኢፌዲሪ ሕገ መንግስትና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን ከባድ ኣደጋ ተደቅኖበታል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሕገ መንግስታዊ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን ለመጠበቅ እንነሳ!
•ሃገራችን ኢትዮጵያ ከብተና ለማዳን፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክንዳቸው ኣጣምሮው የሚታገሉበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን!
•ብዝሃነት ላይ የተመሰረተው፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኣንድነት፣ በትግል በተገረሰሰው ኣሮጌው የግዛት ኣንድነት ለመተካት መንቀሳቀስ ኢትዮጵያን የሚበትን ነው!!
•ዲሞክራሲያዊ ኣንድነትን፣ በግዛት ኣንድነት ለመተካት መፍጨርጨር፣ ጊዜ ያለፈበት ኋላቀር አካሄድ ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ ኣይቻልም።
•የኢፌዲሪ ሕገ- መንግስትና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው!!
•ኢትዮጵያ ብዙሃነት በተቀበለ ህዝባዊ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ መስመር እንጂ፣ ውሉ በጠፋበት የተዳቀለ ኣስተሳሰብ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን አትችልም፣ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገትም ማስመዝገብ አትችልም።
•የአሁኑ ትውልድ፣ ለመጭው ትውልድ፣ ነፃ ኢትዮጵያዊ ፖሊሲ፣ የህዝብ ወሳኝነትና የሉኣላዊነት ክብር፣ የስራ ፈጠራ፣ እና በራስ መተማመን እንጂ የውጭ ሐይሎች ጥገኛ መሆንና ልመና ፈፅሞ አያወርስም።
•የኢፌዲሪ ሕገ- መንግስትና ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን፣ በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክቡር መስዋእትነት እና ደም የተፃፈ ወርቃማ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው!!
•በኣሁኑ ወቅት በኣገራችን የተደቀነው ኣደጋ ተጠያዊዎቹ ከውስጥ እና ከውጭ የተሰባሰቡት የጥፋት ሃይሎች ናቸው።
• ላለፉት 25 ዓመታት ሉኣላዊነትዋና ፖለቲካዊ ነፃነትዋ ኣስከብራ፣ ዘላቂነት ያለው ተከታታይ እና ፈጣን ዙሪያ መለስ እድገት በማስመዝገብ ተምሳሌት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ህልውናዋ ኣደጋ ላይ ወድቋል!!
•አሁንም ለኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ልማት መፋጠን ዋስትና ህዝባዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ብቻ ነው።
• ምርጫ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝብች ዋነኛው የሉኣላዊነታቸው መገለጫ ነው። በመሆኑም በ2012 ዓ.ም የሚካሄደው 6ኛው ዙር ሃገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ቀነ ገደቡ ጠብቆ የሚከናወን ጉዳይ ህገመንግስታዊ መብት በመሆኑ ፈፅሞ ለድርድር ሊቀርብ አይገባም።
•ዘለኣለማዊ ክብር ለታጋይ ሰማእታት!!
ግንቦት 20 ለዘለኣለም ስትከበር ትኖራለች!!
ትግላችን መራራ ነው!! ድላችን አይቀሬ ነው!!
የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ
ግንቦት 14/2011 ዓ/ም
Filed in: Amharic