>

አንድ ጉልበተኛን በዘጠኝ ጉልበተኛ ተክተን የት ልንደርስ ይሆን? (ያሬድ ሀይለማርያም)

አንድ ጉልበተኛን በዘጠኝ ጉልበተኛ ተክተን የት ልንደርስ ይሆን?
ያሬድ ሀይለማርያም
በለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ጉልበተኛው እና ፈላጭ ቆራጩ አንድ ግለሰብ ወይም አንድ ቡድን ነው። ያሻውን ያስራል፣ ይገድላል፣ ይዘርፋል፣ ያፈናቅላል፣ ከአገር ያሳድዳል። ሚሊዮኖችን ጸጥ ለጥ አድርጎ እና አሽቆጥቁጦ ይገዛል። በታሪክ እንደታየውም አንድ ጉልበተኛ አንባገነናዊ ሥርዓት ፍርሃትን እና ነፍጥን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ትንሽም ይሁን እንደ ኢትዮጵያ ያለ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያለበትን አገር እሱ በፈቀደው መንገድ ይመራል፤ ቀጥ ቅድርጎ ያስተዳድራል። ሌሎች ጉልበተኞች እስኪፈጠሩ እና አቅሙን እስኪያመነምኑት ድረስ ብቸኛው ጉልበተኛ እሱ ነው።
አንድ ጠንካራ አንባገነን ባለበት አገር አንጻራዊ ሰላም እና የሕግ የበላይነት ይኖራል። እሱ ብቻ ስለሆነ ከሕግ በላይ የሚሆነው ሌሎችን ሎሌ የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ ነው። በአንባገነን ሥርዓት ውስጥ የሕግ የበላይነት ሲባል ግን ፍትሕ እና ዕርትእን አይጨምርም። ሕግም ከማፈኛ መሳሪያዎቹ አንዱ ነው። በአፓርታይድ ሥርዓትም ውስጥ ሕግ ይከበር ነበር። ሆኖም ግን የሚከበረው ሕግ አፋኝ እና ኢ ፍትሐዊ ስለሆነ በጊዜ ሂደት ሰላሙም በግፏን አመጽ ይደፈርሳል። ሕግ የማስከበር አቅሙም ይዳከማል።
አንባገነናዊ ሥርዓት ሲዳከም አንድ ወይም ብዙ አዳዲስ ጉልበተኞች ይፈጠራሉ። የነበረውን አንባገነናዊ ሥርዓት እንዲዳከም ያደረገው ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ እና ለፍትሕ የተደረገ የሕዝብ ንቅናቄ ከሆነ እና ሕዝብም ትግሉን እስከ ጫፍ ድረስ ይዞ የለውጡ ባለቤት ሲሆን ላቆጠቆጡት አዳዲስ ጉልበተኞች እድል ስለማይፈጥር ወደ ተሻለ ሥርዓት የመሸጋገር ተስፋው ሰፊ ይሆናል። ሕዝብ ንቅናቄውን አድፍጠው ይጠብቁ ለነበሩ ተረኛ ጉልበተኞች አስረክቦ የለውጡን መጨረሻ እና ፍጻሜውን ሳያስተካክል በነበረው የአንባገነናዊ ሥርዓት መንኮታኮት ብቻ እረክቶ ለውጡን ለተረኞች ትቶ ወደ ቤቱ ሲገባ ግን የመከራ ዘመኑን በከፈለው የደም መስዋትነት እንዳደሰው ይቆጠራል። አዳዲሶቹ ጉልበተኞች ባሮጌው ተተክተው ሲያሰቃዩት ይኖራል።
ድህነትን፣ መከራን እና ስቃይን ለልጅ ልጆቹም ያወርሳል። ይህ አይነቱ ጉልበተኛን በጉልበተኛ የመተካት አባዜ ደጋግሞ ደጋግሞ አጥቅቶናል። የዛሬ ስልሳ አመትም፣ የዛሬ ሃያ ሰባት አመትም የሆነው ይሄው ነው። ዛሬ የሚሞቱ ሕጻናት እና ታዳጊ ወጣቶች የወረሱት የትውልድ እዳ ነው። አንዳንዱ ወላጅ ሃብትና ጸጋ ለልጅ ልጆቹ ጭምር አውርሶ ያልፋል። ሃብት ለማፍራት ያልተሳካለት ደሃም ድህነቱን እና የኑሮ ብልሃቱትን ለልጆቹ ትቶ ያልፋል። የከሸፈው ደግሞ ኪሳራን እና በልጅ ልጅ ተከፍሎ የማያልቅ እዳን አውርሶ ያልፋል። አዲሱ ትውልድ የዘመናት እዳን ከከሸፈ ትውልድ ተሸካሚ የሆነ ይመስላል።
አሁን ባለንበት የለውጥ ሂደትም ውስጥ አስፈሪ የሆኑ ነገሮች ከወዲሁ እየታዩ ነው። የአሁኑን ግን ለየት የሚያደርገው የጉልበተኛው ብዛት ነው። ሕውኃትን ተገላገልኩ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ (ከትግራይ ክልል በቀር) በሌሎች ጉልበተኞች እጅ ሊወድቅ የሚችልበት አስፈሪ ሁኔታ ጎልቶ እየታየ ነው። ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት የማይችሉበት፣ ተማሪዎች በሚማሩበት የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንኳ ለጥቃት የተጋለጡበት፣ በሚሊዮኖች ከመኖሪያ ቤታቸው እና ቀያቸው ተፈናቅለው እና ተሳደው በየጥሻው የወደቁበት፣ ሰዎች ወደፈለጉት የአገሪቱ ክፍል በነጻነት መንቀሳቀስ እና የፈለጉበት ሥፍራ ሔደው ሰርቶ መኖር የማይችሉበት፣ ባለሃብቶች ለንብረታቸው ዋስትና ያጡበት፣ በጠራራ ጸሃይ ባንኮች የሚዘረፉበት፣ አፍንጫቸው ድረስ የታጠቁ ግለሰቦች እና ቡድኖች መሳሪያ ይዘው በአደባባይ የሚንፏለሉበት፣ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት እና ጭነት መኪኖች በየመንገዱ የሚዘረፉበት እና አሽከርካሪዎች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑበት፣ የደቦ አጃቢ ያላቸው ግለሰቦች ያሻቸውን የሚናገሩበትና የመንግስትን አካላትን የሚያሽቆጠቁጡበት፣ አሁንም አይደፈሬ የሆኑ ቡድኖች አና ግለሰቦች እዚም እዛም የሚታዩበት አስፈሪ ሁኔታ ተፈጥሯል።
እነዚህ አብዛኛዎቹ ችግሮች እና ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያሉት በየአካባቢው ባሉ የለውጥ ጎርፍ ባመጣቸው አዳዲስ ጉልበተኞች ነው። እነዚህን ጉልበተኞች እንደ ተራ የመንደር ወንበዴ እንዳንቆጥራቸው ብዙዎቹ አደረጃጀታቸው እና እንቅስቃሴዎቻቸው የፖለቲካ እንድምታ ጭምር የያዘ ነው። ወንበዴ ፖለቲከኞች ወይም ትናንሽ አንባገነኖች ናቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ በብዙ ትናንሽ አንባገነኖች ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላው ተወራለች። በየመንደሩ ፈላጭ ቆራጮ ብዙ ነው። ሕዝብ ከአንድ አንባገነን እጅ አመለጥኩ ብሎ ሌሎች ዘጠኝ ትናንሽ አንባገነኞች እጅ ላይ የወደቀ ይመስላል።
ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት ሁለት ነገሮች ማስቀመጥ ይቻላል። የመጀመሪያው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የሕግ የበላይነትን በአገሪቱ በአፋጣኝ ለማስፈን አለመቻል ወይም እያቃተው መምጣቱ ነው። በዚህ ጉዳይ በቅርቡ ዝርዝር ነገር ስለጻፍኩ አልመለስበትም። ሁለተኛው እና ዋናው ምክንያት ግን የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች ከእነዚህ አዳዲስ የመንደር አንባገነኞች ጋር ያላቸው ጥብቅ ቁርኝት ነው። እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች በአንድ እግራቸው በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ ቆመው ለውጡ የሚያመጣውን ፍሬ ለመቋደስ አሰፍስፈው ይታያሉ። በሌላኛው እግራቸው ደግሞ ከዚህ ለውጥ የምንፈልገውን ባናገኝ ከሚል እሳቤ ይመስላል ከነውጥ ኃይሎች ጋር ቆመው በሃሳብ እና በምግባር ሲደጋገፉ ይታያል። የነውጥ ኃይሉ መጥፎ ሲሰራ እኛ የለንበትም ወይም ዝም ይላሉ። ይሄው ቡድን አንዳንድ ጥሩ የሚመስሉ ነገሮችን ሲፈጽም ደግሞ አብረው ይፈነጥዛሉ።
የአብይ አስተዳደር በሕግ ማስከበሩ ሥራ ላይ ቆፍጠን ካላለ እና እነዚህም የነውጥ ቡድን ደጋፊ የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ከእኩይ አድራጎታቸው ታቅበው አገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድታመራ በጎ አስተዋጾ ማበርከት ካልጀመሩ ገና ብዙ መርዶ የምንሰማባቸው ቀኖች ከፊታችን ሊጠብቁን ይችላሉ። ከዘጠኝ አንባገነን አንድ አንባገነን ይሻላል። ከአንድ አንባገነን ደግሞ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አገሪቱን የሚያስተዳድር፤ ፍትሕ እና ሰላምን የሚያስከብር ሕዝባዊ መንግስት ይሻለናል። ይህን ሕዝባዊ መንግስት በቀጣይ በሚካሔደው ምርጫ ለማምጣት ግን ከወዲሁ መንግስት፣ ሕዝብ እና የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ሆነው እነኚህን የመንደር አንባገነኖች ከሕግ በታች ማዋል ይገባል።
የሃያ ሰባት አመቱን ትተን ባለፈው አንድ አመት ብቻ የደረሰብን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በዚህ ከቀጠለ አዲዎስ ሰላም፣ አዲዎስ ዲሞክራሲ፣ አዲዎስ የሕግ የበላይነት፣ አዲዎስ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ።
የአብይ አስተዳደር የትኩረት አቅጣጫ ቅደም ተከተል መዛባት የገጠመው ይመስላል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ እጅግ አንገብጋቢ እና በይደር ሊቆዩ ከማይችሉ ነገሮች ይልቅ እጅግ በተጋነኑ እና አገር ሲረጋጋ ሊከወኑ በሚችሉ ሰፋፊ እና ከፍተኛ የገንዘብ አቅም በሚጠይቁ ብዙ የሥራ እቅዶች ውስጥ የተዘፈቀ ይመስላል። ከሸገር ገበታ አንስቶ ሌሎች ወደ አሥር የሚጠጉ እና እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቁ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ትኩረቱን እነሱ ላይ አድርጓል። ሸገርን የማዘመኑን እቅድ እጅግ ብደግፈውም ከሱ የሚቀድሙ ብዙ ሥራዎች አሉ ብዮ አስባለሁ። የሸገር ልማት እንዳለ ሆኑ አዲሱ እቅድ ምርጫው ተካሂዶ እና አገር ከተረጋጋ በኋላ ቢሆን ምን ይገዳል። አዲስ አበባ የት ትሄድብናለች? ከዛ ይልቅ ጊዜ የማይሰጡትን ሌሎች ገበታዎች ማስቀደም አይሻልም ነበር ወይ? የተፈናቃዮች ገበታ፣ የሰላም ገበታ፣ የሕግ የበላይነት ገበታ፣ ያበጡና ከአገር በላይ የሆኑ ክልሎችን የማስተንፈስ ገበታ፣ የተጠያቂነት፣ የፍትህ እና የሰብአዊ መብት ገበታ፣ የሕዝብ ቆጠራ እና የምርጫ ገበታ፣ የገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ገበታ እያልን ልንዘረዝር እንችላለን። ለእኔ በዚህ የሽግግር ወቅት የአብይ መንግስት እነዚህን ነገሮች በአግባቡ ቢከውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ውለታ እንደዋለ ይቆጠራል። በታሪክም ሲወሳ ይኖራል። በእነዚህ መደላድሎች ላይ ሆነን የሸገር፣ የአዳማ፣ የባህርዳር፣ የደሴ፣ የመቀሌ፣ የሀረር እና ሌሎች ገበቶችን ማሰብ እና መከውን እንችል ነበር።
ለውይይት እንዲያመቸን ይህን ጥያቄ ላንሳና ሃሳቤን ልቋጭ። ዛሬ ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ለእርሶ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አገራዊ ጉዳይ ምንድን ነው? በመንግስት፣ በተቃዋሚ ኃይሎች፣ በሲቪክ ማህበራት እና በሌሎች ባለ ድርሻ አካላትስ ዘንድ አንድ አይነት አገራዊ መግባባት እና የቅድመ ትግበራ ሂደት ላይ በይዘትም ይሁን በአፈጻጸም እረገድ መግባባት አለ ወይ? ሕዝብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እና የመንግስት ቅድሚያ ትኩረት አንድ አይነት ነው ወይ? ተቃዋሚዎች ትኩረት ያደረጉበት ጉዳይ የሕዝብ አጀንዳ ነው ወይ? ሚዲያዎች ትኩረት ሰጥተው የሚያራግቡትስ አጀንዳ የሕዝብን ወይስ የመንግስትን ወይስ የተቃዋሚዎችን ወይስ ሌላ?
+++++++
ለውይይት መነሻ የተሰነዘረ ጽሑፍ ስለሆነ እንደ ሌላው ጊዜ ተሳዳቢዎችን አላስተናግድም። ማንኛውንም ሃሳብ በድጋፍም ይሁን በተቃውሞ ለመስማት ግን ዝግጁ ነኝ።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic