>

በእነ አቶ በረከት ስምኦን አንድኛው ክስ ላይ  የተሰጠ ምስክርነት!!! (ውብሸት ሙላት)

በእነ አቶ በረከት ስምኦን አንድኛው ክስ ላይ  የተሰጠ ምስክርነት!!!
ውብሸት ሙላት
ዐቃቤ ህግ 9 ምስክሮችን ቢያቀርብም 5ቱ የመሰከሩት በቂየ ነው  አለ። ዓቃቤ ህግ በነ አቶ በረከት ላይ ከመሰረታቸው 4 ክሶች ውስጥ በ1ኛ ክስ ብቻ ሊያሰማ ካቀረባቸው 9 ምስክሮች ውስጥ የ5ቱን ብቻ ካሰማ በኋላ አምስቱ ከመሰከሩት ውጭ ስለማይናገሩ የተሰሙት ይበቁኛል በማለቱ ፍ/ቤቱ ቀሪዎቹን ምስክሮች ዐቃቤ ህግ አልፈልጋቸውም ስለአለ መሄድ ትችላላችሁ ሲል  የምስክርነት ቃላቸውን ሳይቀበል ምስክሮቹን አሰናብቷል፡፡
ዐቃቤ ህግ ቃላቸውን ያሰማቸው ምስክሮች ቃል የሚከተለው ነው፤
ዐቃቤ ህግ የምስክሮቹን ቃል ማሰማት ቀጥሎ 2ኛ ምስክር ዳሽንን በጥራትና ብዛት ለማስፋፋት በማሰብ ካርስበርግ የሚባል ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራ ተነጋግረን ነበር፡፡ይህ ድርጅት በቢራ ጠመቃ ከፍተኛ ልምድ ያለውና እስከ 4ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም የነበረው ድርጅት ቢሆንም በነ አቶ ታደሠ ትዕዛዝ ከዱየት ባሳሪ ጋር እንድንሰራ ተወሰነ፡፡ዱየት ገንዘብ አለው እጂ የቢራ ጠመቃ ልምድ አልነበረውም፡፡ ዱየት ባሳሪ ወደ ድርሻ ግዥ ከመግባቱ በፊት ብዛት ያላቸውን ባለሙያዎች በማሰማራት የአዋጭነት ጥናት አስጠንቷል፡፡ ዳሽን በወቅቱ 385 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ የሚያገኝ ፋብሪካ ነበር፡፡በማለት መስክረው ሲቀጠሉ ዳሽን ሜታ ቢራ ፋብሪካን ለመግዛት 175 ሚሊዮን ዶላር ቢያቀርብም አሸናፊው ድርጅት በ225 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶታል ብለዋል፡፡
በወቅቱ የዳሽንና የሜታ የማምረት አቅም ምን ያክል ነበር ተብለው የተጠየቁት ምስክሩ ሲመልሱ ዳሽን 790 ሽህ ሜታ ደግሞ 600 ሽህ ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ነበራቸው ብለዋል፡፡
ከዱየት ጋር የነበረውን ድርድር ሲያስረዱም የዱየት ሰዎች እኔ ጋ መጥተው ስለዋጋው ስንነጋገር 80 ሚሊዮን ዶላር አቀረቡልኝ እኔ ከ150 ሚሊዮን አይቀንስም ስላቸው የመጨረሻ የምንሰጠው 85 ሚሊዮን ዶላር ነው ብለውኝ ወጡ፡፡ ከአቶ ታደሠ ቢሮ ገቡና ከሳቸው ጋር በ90 ሚሊዮን ዶላር  ተስማምተው ሽያጩ ተፈፅሟል ብለዋል፡፡
ፈረንጆች እኛ ጋ ሲፈራረሙ ብዙ አይነት ባለሙያ  ሲያሣትፉ እኛ ግን ሶስታችን ብቻ ነበርን ይህ በመሆኑም ዳሸንን ከፍተኛ ጥቅም አሳጥተነዋል፡፡
የኔ ስልጣን አሁን ሳየው ምስክር ሆኖ መፈረም እንጅ  ስልጣን አልተሰጠኝም፡፡ ድርጊታቸው  አቶ ታደሰ የሰጣችሁን ብቻ ተቀበሉ አይነት ነው የነበረው ፡፡
63ዐ ሺህ ይሮ  በስምምነቱ ያልነበረ ቢሆንም ከስምምነቱ በኋላ ግን ለዱየት ባሣሪ የአዋጭነት ጥናት ላስጠናበት ተከፍሎ የስምምነቱ አካል ተደርጓል፡፡
125 ሚሊዩን ዶላር ለሜታ የከፈልነው ያላግባብ ነው ሲል ገዢው ቢያጆ ከሽያጩ በኋላ ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ይህን ያውቃው ተብለው የተጠየቁት ምስክርሩ አላውቅም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የጥናት ሠነዱን ዳሸን እየተጠቀመበት ከሆነ ክፍያው መፈፀሙ ምንድነው ችግሩ ተብለው የተጠየቁት ምስክሩ ዱየቶች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ላስጠኑት ጥናት ከግዥ በኋላ ጥረት እንዲከፍል መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ መስክረዋል፡፡ አቶ ታደሰ በመስቀለኛ ጥያቄያቸው ጥናቱን ዳሸን አሁን እየተጠቀመበት አይደለም ወይ በማለት ጠይቀው አዎ እየተጠቀመበት ነው ነገር ግን ሸር ሆልደር ከሆነ ተቧዳኝ ለመጣ ዶክመንት ሊከፍል አይገባም ሲሉ ምስክሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ የፈረምኩት በማኝነት ደረጃ ነው ብለዋል ምን ማለት ነው? ስራ አስኪያጅ አይደሉም ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ሀሣቤን የመግለጽ ስልጣን አልነበረኝም፡፡ ሁሉንም የሚወስኑት አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ነበሩ፡፡ ዱየትባሳሪ ገንዘብ ስላለው ብቻ የተመረጠው ፍላጐት የነበረው ሰው ነበረ ወይ? የገንዘብ እጥረት ባለበት ገንዘብ ያለው መምጣቱና መቀበሉ ችግሩ ምንድን ነው ተብሎ ከዳኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ አማራጮችን የማየት እድል በፍፁም አልተሰጠም፡፡ ቢኖር ኖሮ በልምድም፣ በገንዘብም የተሻለ ይገኝ ነበር፡፡ አብረን መስራት ከጀመርን በኋላ ችግር መፍጠር ጀመሩ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ገንዘብ እንጅ ልምድ ስላልነበራቸው ነው፡፡ ጥናቱ እራሱም ዳሸን አውቆት የተጠና ጥናት አልነበረም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአቶ በረከት ሚና ምን ነበር ተብሎ ከዳኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዳሸንን የሚያክል ለጥረት ድርጅቶች የገንዘብ ምንጭ የሆነ ኩባንያ ላይ የሚወስነው ውሣኔ ያለበረከት እውቅና አይፈፀምም በማለት የምስክርነት ቃላቸውን አጠናቀዋል፡፡
ችሎቱ የምስክሮችን ቃል መቀበል ቀጥሎ የዐቃቤ ህግ 3ኛ ምስክር የሙያ ምስክርነታቸውን በፕሮጀክተር አስደግፈው ለማቅረብ ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤቱን ፈቃድ ቢጠይቅም የተከሳሽ ጠበቃ ቀድመን ስላላወቅነውና ምላሽ ለመስጠት ስላልተዘጋጀን ምስክሩ በቃል ብቻ እንዲያስረዱ እንዲደረግልን እንጠይቃለን በማለት ያቀረቡትን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ በመቀበል ምስክሩ የሚችሉትን ያህል በቃል እንዲያስረዱ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡
ምስክሩም  አንድ ኩባንያ ከመሸጡ በፊት መደረግ ስለአለበትና ማን መሸጥ እንዳለበት እንዲገልጹ በዐቃቤ ህግ ተጠይቀው ሲያብራሩ ፤« ዳሸን ቢራ ሲመሠረት ቦርዱ ሊሸጥ፣ስጦታ ሊሰጥ እንዲሁም አክሲዮን ሊያስገባ የሚችለው ስልጣን ተሰጥቶት ከነበረ ብቻ ነው፡፡ የውሣኔ ጉዳይ ማን ያስፈጽመው የሚለው በቃለ ጉባኤ ላይ ተገልጾ መፃፍ አለበት፡፡ ዋጋው በሁለት መንገድ መሠራት አለበት፡፡ ምክንያቱም አክሲዮን ገዢው የሚገዛው ትርፍ እንጅ ብረት ስላልሆነ ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት ልምድ ያለውን ካምፖኒ አማክሮ ብቻ ነው መሆን ያለበት ፡፡ ገማቹ አማካሪ መነሻ ዋጋ ይሰጣል ይህ ውሣኔ ለባለቤቶቹ ይቀርብና በቃለ ጉባኤ ‹አዎ ይሸጥ › ተብሎ እንዲወሰን ይደረጋል፡፡ የቀረበው ዋጋ በቅደም ተከተል ለባለአክቢዮኖቹ ይቀርብና ባለቤቶቹ ጥሩ ነው ይስማማናል ያሉትን ይመርጣሉ ቦርዱ ይህን ያስፈጽማል» በማለት ሙያዊ ምስክርነታቸውን መስጠት የቀጠሉት የሙያ ምስክሩ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበሩ ፋብሪካዎችንና ዳሸንን የመሰለ ዘመናዊ ፋብሪካ እኩል አይወዳደሩም ፡፡ እንደ ዳሸን ጨረታውን አሸንፈን ሜታን ብንገዛው ኑሮ ያሉትን ማሽኖች አስወግደን በአዲስና ዘመናዊ ማሽኖች ነበር የምንተካቸው ምክንያቱም ዳሽን የ21ኛው ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጅ የታጠቀ ፋብሪካ ነው ብለዋል የሙያ ምስክሩ፡፡ዳሽን አክሲዮን በሚሸጥበት ወቅት ቢራ ፋብሪካዎች የነበራቸውን የማምረት አቅም ያውቁ እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ አዎ አውቃለሁ፡፡ በወቅቱ ፤
ሐረር ቢራ 2ዐ ሚሊየን ሊትር
ሜታ ቢራ 4ዐ ሚሊየን ሊትር
ዳሽን ቢራ ደግሞ 75 ሚሊየን ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ነበራቸው፡፡
ሜታ ቢራ በ225 ሚሊየን ዶላር ሙሉ በሙሉ ሲሸጥ የዳሽን ቢራ 5ዐ.14 ሼር በ9ዐ ሚሊየን ዶላር ተሽጧል፡፡ ሜታ 225 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ ማለት በማምረት አቅሙ ስናካፍለው 1 ሊትር ቢራ 5.39 ዶላር አውጥቷል ማለት ነው፡፡ በዚህ ስሌት የዳሽንን ብንሰራው 425 ሚሊየን ዶላር ያወጣ ነበር በማለት የሙያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
 በተከሳሾች መስቀለኛ ጥያቄ 
በ2ዐዐ3 ዳሽንን ለምን ለቀቁ ?
ምስክሩ ሲመልሱ በወቅቱ ማብራሪያ ለብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዳቀርብ ባህር ዳር ተጠራሁ፡፡ እኔም በአማረኛ እና በእንግሊዝኛ አዘጋጅቼ ለማቅረብ አዳራሽ ስገባ ያሉት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡…እነሱ ያሉት ማንን ነው ተብለው የተጠየቁት ምስክሩ ፤እኔ እነ አቶ አዲሱንና ሌሎች የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጠብቄ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በፊት ደጋግሜ ጉዳዩን ያስረዳኋቸው
1ኛ በረከት 2ኛ ታደሰ 3ኛ ምትኩ 4ኛ ዮሴፍና 5ኛ ወንድወሰን ነበሩ የተገኙት ማብራሪያውን አቅርቤ ከአዳራሽ እንደወጣሁ እራሴን እስር ቤት አገኘሁት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ያሳሰሩዎት ስለሆኑ ምስክርነት እየሰጡ ያሉት ቂምይዘው አይደለም ተብለው በተከሳሽ ጠበቃዋ የተጠየቁት የሙያ ምስክሩ፤እኔ እየመሰከርኩ ያለሁት የሙያየን እንጅ በቂም በቀል አይደለም፡፡ እንደተፈታሁ ለአቶ በረከት ደውየለት ብዙ ተነጋግረናል፡፡ እኔ አቶ በረከትን እንደ ታላቅ ወንድሜ ነው የማየው እሱም እንደ ታናሽ ወንድሙ ነው የሚያየኝ በበዓላት ቀናት ሁሉ ቢያንስ ቢያንስ በቴክስት እንኳን አደረሰህ እለዋለሁ፡፡ አቶ ታደሰ ጋር ብዙም አንተዋወቅም ፡፡ስለዚህ በቂም ሳይሆን ሙያዊ ምስክርነት ነው እየሰጠሁ ያለሁት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምስክሩ ሲቀጥሉ ዳሽን ደብረ ብርሃን የጣዕም ችግር የገጠመው ጊዜ ለአቶ በረከት ደውየ አናግሬዋለሁ እንዲያውም ቃል በቃል
You are spoiling My baby! ነበር ያልኩት፡፡ስሉ የምስክርነት ቃላቸውን አጠቃለዋል፡፡
4ኛ ምስክር የኦዲቲንግ ባለሙያና አማካሪ ናቸው፡፡ ዐቃቤህግ ኦዲተር ነኝ ብለዋል፡፡ የት የት ሰርተዋል፡
መልስ ዳሸን፣ አምባሰል እና ጥቁር አባይ ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡
ዱየት ከገባ በኋላ ኦዲት እንድናደግ ተቀጥረናል ብለዋል፡፡ እንዴት እንደገባ ያውቃሉ?
የውሉን ስራ ሰራን እንጂ ዱየት እንዴት እንደገባ አናውቅም፡፡
ዐቃቤ ህግ፡- የቢዝነስ ኢቫሎየሽን ዳሽን እንድትሰሩለት ጠይቋችሁ ነበር?
መልስ ፡- አልነበረም፡፡
ዐቃቤ ህግ ፡- አንድ ድርጅት ሊሸጥ ሲታሰብ ምን መደረግ አለበት?
 መልስ፡-  የመነሻ ግምት ዋጋ በባለሙያ ማስገመት አለበት፣ የአስር አስራአምስት አመት ሊውል የሚችል ጥናት ይጠናል፡፡
ዐቃቤ ህግ ፡- ኦዲት ስታደርጉ የአገኛችሁት ነገር ነበር?
በዳሸን ቢራ ስም ሲውዘርላንድ ገንዘብ ተቀምጧል ተባልነ ማረጋገጫ ጠየቅን አዎ አሉን ወደ ኢትዮጵያ ይመለስ አልነ ፕሮሰስ ተጀመረ
ዐቃቤ ህግ፡-ገንዘቡ መቼ ገባ መቼ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ?
4ኛ ምስክር፡-  ኦክቶበር አካባቢ ገብቶ ሜይ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ
ዐቃቤ ህግ፡- ከ6-7 ወር ቆይቶ ተመልሷል ማለት ነው?
4ኛ ምስክር፡- አዎ በኢትዮጵያ ቅድሚያ መሠራት የተለመደው አሰራር ቢዝነስ ኢቫሎየሽን ነው ፡፡ ዲውዴሊጀንስ በዋናነት የሚሰራው ገዥው በሻጩ በኩል የግብርና የመሳሰሉት እዳዎች ኖረውበት ገዥው ድርጅቱን ከገዛው በኋላ ጥያቄ እንዳይቀርብበት ነው፡፡
ዐቃቤ ህግ፡- ኦዲት ለማድረግ ምን መከተል አለብን?
4ኛ ምስክር፡- የInternational Audit Standards መሠረት ተደርጎ ኦዲት ይሰራል::
የፍርድ ቤት የማጣሪያ ጥያቄ
ኦዲት ስታደርጉ ያገኛችሁት ችግር ነበር?
መልስ፡- ስራ አልሰራንም ምክንያቱም ስለማይመለከተን ሲሉ የሙያ ምስክርነታቸውን አጠናቀዋል፡፡
5ኛ ምስክር እራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ ምስክርነታቸውን የቀጠሉት ለጥረት ቦርድ መንግስት ቢራ ፋብሪካዎችን እየሸጠ ስለሆነ ዳሸንም መሸጥ አለበት በሚል እነ አቶ በረከት ለጥረት ቦርድ ሀሣብ አቀረቡ፡፡ የዳሸን ቢራ ባለድርሻዎች እነማን ናቸው ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ ጥረት፣ ጥቁር አባይ እና አንባሰል የዳሸን ባለሸሮች ናቸው በማለት መልስ ሰጥተው ከባለአክሲዮኖቹ ጋር እነማን ናቸው የተደራደሩት በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ወንዶሰን፣አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ነበሩ ጉዳዩን ከባለአክሲዮኑ ጋር የሚደራደሩት በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
 
የፍርድ ቤት የማጣሪያ ጥያቄዎች
ሁለት ሁለት እጣዎች ለበረከት፣ ታደሰና ወንዶሰን እንዲሰጡ ተወስኗል ብለዋል፡፡ ይህ ውሣኔ ተፈጽሟል? በሚል ከዳኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ አዎ! ባይፈፀም ኖሮ እንደገና ሀሣብ እንድንሰጥ ይሰበስቡን ነበር ብዬ ነው የማምነው
ባለአክሲዮኖቹ ስንት ነበሩ ?
መልስ፡-  ሶስት፡፡ እነሱም ጥረት፣ጥቁር አባይና አምባሰል ነበሩ በማለት የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
የፍርድቤት ትዕዛዝ
የተሰሙት የምስክሮች ቃል ወደ ፁሁፍ ተገልብጦ የመዝገቡ አካል ይሁን ብለናል፡፡
የ3ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ባለመቅረባቸው ምክንያት በቀሪዎቹ ሶስት ክሶች ላይ የምስክሮችን ቃል መስማት ስላልተቻለ ለግንቦት 28 ቀን 2ዐ11 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተናል በማለት ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ በረከት ላይ በ1ኛ ክስ ብቻ የቃል ምስክሮችን ያሰማበትን ችሎት አጠናቋል፡፡
Filed in: Amharic