>

“....(እነሆ) የአንድአርጋቸውን “ትውልድ (አ) ይደናገር፣ እኛም እንናገር” መፅሐፍ....“ (መሰለ ተሬቻ)

ትውልድ (አ) ይደናገር፣ እኛም እንናገር ●●

የድርሳኑን ወራዳ ይዘት፥
የትውልዱን የፖለቲካ ጠባይ ክፋት፥
የኢትዮጵያን ታሪክ ለመከለስ የትጋቱን ነገር፥ ለመረዳት፤
(እነሆ) የአንድአርጋቸውን “ትውልድ (አ) ይደናገር፣ እኛም እንናገር”፥

… ጅመርኩ ላቃቅር !!

መሰለ ተሬቻ

●●●

ይህ አባባል ደግሞ የእኔ መስሎህ ተሳዳቢ ለስድብህ እንዳትሽቀዳደም። አባባሉ የAndey-አባቡ “ትውልድ” ደብተራ እያለ ሲያጠለሻቸው የኖሩት፣ የ16ኛው መ.ክ.ዘ ኢትዮጵያዊ ምሁር፣ የአባ ባሕሬይ ነው። ወረት የማያውቁት አባ ባሕሬይ፣ የሙታኑ ዓለም ሲያሰለቻቸው፣ አንዳንድ መፅሐፍት (እንደ ክብረ-ነገስት፣ ፍትሐ-ነገስት፣ አውደ-ነገስት፣ ስንክሳር፣ ሐይማኖተ-አበው፣ ዜና መዋዕላት … ወ.ዘ.ተ) ሊያገላብጡ ከእኔ ዘንድ ይመጣሉ። ታዲያ ባለፈው ሰሞን የአፅጌ ሰርፀ ድንግልን ዜና-መዋዕል ሊያገላብጡ መጥተው፣ እንደ አጋጣሚ የአንዳርጋቸው መፅሐፍ ጠረጴዛ ላይ ተሰጥቶ ተመልክተውት፣ እንደው እንደዘበት ገልበጥ ገልበጥ አደራርገው ከተመለከቱት በኋላ፣ የተናገሩት ቃል ነው። “ይህ ታሪክ በፍፁም ሊሆን የማይችል የልጆች እንቅልፍ ማስተኛ ተረት ተረት ነው” ብሎ የሚከራከር ሰው ቢነሳብኝ “ከስራው-ከንቱ አንዳርጋቸው ‘ትውልድ (አ)ይደናገር፥ እኛም እንናገር’ መፅሐፍ የቀሰምኩት የክፋት ትምህርት እንዲህ ያለ ሲሆንብኝ ምን ብዬ ይህን አቃቂር እንድከፍትልህ ትጠብቅ ኖሯል” በሚል ጥያቄውን በጥያቄ እመልሰለታለሁ። በነገራችን ላይ Andey-አባቡ የአንዳርጋቸው ፅጌ የእንግሊዝና የሐገር ቤት ጣምራ ቅጥል ስም ነው።

●●●

በፈረንጅና በሐገር ቤት ጣምራ ቅጥል ስሙ Andey-አባቡ፣ በድፎ ዳቦ ስሙ አንዳርጋቸው ፅጌ “ያቀናበረው” ይህ ታሪክ አፍራሽ እና ከላሽ፣ በዓላማው ከተሰጠው ርዕስ በተቃራኒ “አደናጋሪ”፣ በአብላጫ ይዘቱም ከሃምሳኛው ገፅ ተላልፈው ሊያነቡት ኮሶ የመጠጣት ያህል የሚያንገሸግሽ፣ የአሉባልታና የእንቶ-ፈነቶ “ድግር” ድርሳን ነው። ከዚህም የተነሳ የዚህን ወራዳ መፅሐፍ ርዕስ “ትውልድ ይደናገር፣ እኛም እንቀባጥር” በሚል እንዲታረም ምክረ-ሐሳብ መሰለ ተሬቻ በታላቅ አክብሮት ለደራሲው ያቀርባል። አንባቢ ሆይ ላንተም ምክር አለኝ። Andey-አባቡ ይህን ከንቱ ከላሽ መፅሐፉን ታቅፎ በየቴሌቪዥን ጣቢያው ሲቅለሰለስ አይተህ፣ ይኸውም መፅሐፉ ቁም ነገር ያለበት መስሎህ ተታለህ፣ 379 ብር አውጥተህ ገዝተህ፣ በኋላ ማንበብ ስትጀምር ሰውዬው ስለምን እንደ ፃፈ ግራ ገብቶህ እንዳታቃትት፣ ከወዲሁ መፅሐፉን ከመግዛትህ በፊት እንድታስብበት ምክር አወርድልሃለው። እኔስ አንዴ ተታለልሁ … የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም!! “ከእስር እንደ ተፈታሁና ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዳገኘሁት … ምን እናድርግለህ ሲለኝ የፃፍኩት መፅሐፍ አለ። እርሱን እንድታሰጠኝ ነው ያለ …” ምናምን እያለ ሲያወራ ሰምቼው፤ “መቼም ጠቅላይ ሚንስትሩን ከምንም በፊት የፃፈው መጽሐፍ እንዲያሰጡት መጠየቁ ቁም ነገር ቢኖርበት ነው” ብዬ ገዝቼ ተሸወድኩ። … በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር Andey-አባቡ ስለፃፈው መፅሐፍ ወራዳነት ምንም ግንዛቤ የሌለው መሆኑ ነው። መፅሐፉን በማንበብ አንድ ግልፅ የሚሆንልህ ነገር በእስር ሆኖ አንደ ወረደለት ከፃፈው በኋላ ተመልሶ የፃፈወን ፅሑፍ ምን አልገመገመውም ወይንም ሌላ ሰው እንዲገመግምለት አላደረገም። … አንድም መቼም ይህ ሰው ታሪክ ከላሽነትና አፍራሽነት የተጣባው ከተፈጠረበት ትውልድ ነውና ይህን በማብራራት፤ ሁለትም አውቆ በሴረኝነት ሳያውቅ በድንቁርና፤ ብዙ አጥፊ የንድፈ-ሐሳብ፣ የሥነ-ዘዴ፣ የትንታኔ እና የደረቅ ዕውነታ ግድፈቶችን በመፅሐፉ የእውነት አስመስሎ አቅርቧልና እነኚህን ጉድፎች ነቅሶ ለማረቅ እነሆ አቃቂሬን ብዬሃለው። …

●● ሥለ መጽሐፉ ጥቅል ማብራሪያ ●●

አሁን ለአቃቂር የምንበቃው የአንዳርጋቸው ሥራ የተሟላ መረጃው ይህ ነው፤ “አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ትውልድ አይደናገር፥ እኛም እንናገር። አዲስ አበባ፥ አንድ ቤተሰብ፥ አብዮቱና ኢሕአፓ 1877-1970 ዓ.ም (የታተመመበት ከተማ ያልተገለጠ፣ ነፃነት ማተሚያ ቤት፣ 2011 ዓ.ም)፣ xii + 664 ገፆች፤ ዋጋው 379 የኢት. ብር። ይህ መፅሐፍ በቅረፅና የይዘት አቀራረቡ በከፊል ከኔበንተኔ (Autobiography) የትውስታ ድርሳን ፣ በከፊል ደግሞ ከታሪክ ሥራ ዓይነት የሚመደብ ነው። እንደ ኔበንተኔ ድርሳን የመጀመሪያ መረጃ ምንጩን በፀሐፊው የምልሰት ትውስታ ላይ፤ እንደ ታሪክ ስራ በሌሎች የፅሑፍና የቃል የታሪክ ሁለተኛ ደረጃ መረጃ ምንጮች ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ታሪክ አፃፃፍ እና ታሪክ ፀሐፊዎች ላይ ከላሽ ትችት ያቀርባል። ከዚህ ከፀሐፊው ከላሽ ትችት ጀርባ ግን የተገተረው የፖለቲካ ፍላጎት እንጂ ለኢትዮጵያ ታሪክ አጠናን አጋዥ አበርክቶ አይደለም። ይህ ስራ ለኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት አጋዥ አበርክቶ ሊሆን ይችል የነበረው፤ ወይ ፀሐፊው ያየውንና የሰማውን ከራሱ ምልከታ አንፃር በግለ-ታሪክ መልክ አቅርቦት ቢሆን፣ አልያም እንደ አንድ የታሪካዊ ጥናት ድርሳን ያሉትን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ መረጃዎችን አሟጦ መርምሮና መዝኖ አቅርቦ ቢሆን ነበር። በአጠቃላይ የአንዳርጋቸው መፅሐፍ ዋንኛ የክለሳ አንብሮ (deconstructionist thesis) በዘመናዊት ኢትዮጵያ በቋንቋም ይሁን በጎጥ ተነሳሽነት “የበተለይ ለኔ ይገባኛል” ጥያቄ የሚቀርብባቸውን አንኳር አንኳር ወታደራዊ/ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ምጣኔያዊ የታሪክ ክስተቶች (ለምሳሌ የአደዋን ድል፣ የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ … ወዘተ) ባለቤትነትን፤ እግራቸውን ለጋሬጣ፥ ደረታቸውን ለጥይትና ጦር ሰጥተው፥ ብሽሽታቸው እስኪላጥ ፈረስ ጋልበው አገር ካቀኑት ዳር ድንበር ካስከበሩት፥ ችካል መተው ከተሞችን ከቆረቆሩት፣ ከነገስታቱ፥ ከመኳንንቱ፥ ከመሳፍንቱ እና ከመልከኛ እስከ ጭሰኛ ምንዝሮቻቸው እጅ አውጥቶ፤ ለማኅበረሰቡ ሕዳጣን ናቸው ላላቸወ ለ“ባርያዎች”፣ ለ“ሴተኛ-አዳሪዎች”… ወዘተ በማጎናፅፍ፣ በዚህ አዲስ ትርክት ውስጥ የራስን የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎት መደላድል አርቆ መፍጠር ነው። ይግረምህና በትግረኛ ቋንቋ አፉን እንደ ፈታ ሰው ሲኮለታተፍ የምታውቀው Andey-አባቡ፤ በዚህ መፅሐፉ ኦሮሞነቱን አውጆ ብቅ ከማለቱም፣ “ፊንፊኔ የአያቶቼ ጥጃ ማሰሪያ ነበር ያለ፣ የከተማው ባለቤትነትም የአያቶቼ ነው ያለ፣ ካስፈለገ የባለቤትነት ጥያቄ ማቅረብ የሚቻል ነው ያለው” በማለት መልሶ መላልሶ ሲያለቃቅስ ታነባለህ (ገጾች 64-71፣ 79፣ መደምደሚያውን ተመልከት)። አንተዬ/አንቺዬ የ “ያ ትውልድ” ዘመን የማያበርደው የስልጣን ጥማት ይገርማል። ለሌለ “ባርያ”ና “ሸርሙጣ” የከተማን ባለቤትነት ሰጥቶ፤ መልሶ ደግሞ እኒህ ህዳጣን ዛሬ በኅብረተሰብ መደብነት ኖረው የባለቤትነት ጥያቄ ማቅረብ ስለማይችሉ፤ በአጋጣሚም አያቶቼ የአደአ ኦሮሞ ሆነው በአንድ ወቅት “ፊንፊኔን” ለጥጃ ማሰሪያነት ይጠቀሙበት እንደነበር ስለታወቀ፤ እውነተኛው የከተማው ባለቤትነት የሚገባው ለእኔ ነው … ብሎ ነገረ-ትርክት ማንበብ የሚቻለው መቼም በኢትዮጵያ ብቻ ይመስለኛል። Andey-አባቡ ቅማል የወረረውን ቡታንታውን የካርቱም አየር ጣቢያ ወርውሮ እንግሊዝ መኖር የጀመረው እ.አ.አ ከ1983 ዓ.ም። በዚያም ሲኖር ባስጠጉት እንግሊዞች ላይ “እናንተ ከምትኖሩት ተመሳሳይና አሰለልቺ ህይወት ጋር ሲተያይ እኔ የኖርኩት 30 ዓመት የማይሞላ ዕድሜ የ250 ዓመታት ያህል ነው” በማለት ይታበይባቸው እንጂ፤ በመሰረቱ Andey-አባቡ እንግሊዝ ሲኖር የሐሳብ ድንግልናውን ከምንም በላይ ጠብቆ እንደ ኖረ ከዚህ በላይ አስረጂ አይገኝለትም። እስኪ መጀመሪያ ታሪክን አጠልሽቶ መክለን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ የሚጠቀመው የAndey-አባቡ “ያ ትውልድ” ሁሉ ነውና ጥቂት ስለዚህ የተውልድ ዕዳ ጠባይ ተናግረን የAndey-አባቡ ሥራ ወደ ማቃቀሩ እንመለስ።

●● ነገረ “ያ ትውልድ” ●●

መቼም በ20ኛው መ.ክ.ዘ እንደ አባ ባሕሬይ በዛ ድንቁርና በሰለጠነችበት “ያ ትውልድ” በደብተራ ታሪክ ፀሐፊነት ኩነኔና ስድብ ያስተናገደ ሰው ያለ አይመስለኝም፤ ምንም እንኳ የሰውዬው ስራዎች ከስነ-መለኮት እና ሥነ-ሰብ የትምህርት ዘርፎች ተርታ የሚመደቡ ቢሆንም። በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ በመዋዕለ ዜና ፀሐፊዎቹ በነ አባ ባሕሬይ፣ ደብተራ ዘነብ፣ አለቃ ገብረማርያም፣ የተጀመረው “የደብተራ ታሪክ ውግዘት” (ደብተራነት የኢትዮጵያ ታሪክ እጣ ፋንታ እንዳልሆነ ሁሉ) አንድ ጋት ወደፊት ተራምዶ የልምድ ታሪክ ፀሐፊዎቹን እነ አለቃ ታየ ገ/ማርያምን፣ አለቃ አጥሜ ጊዮረጊሰ ገ/መሲህን፣ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይገዳኝን፣ አለቃ ተክለ እየሱስን፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስን፣ አምባሳደር ተክለፃድቅ መኩሪን … ወዘተ ሲያጠቃልል የአ.አ.ዩ የታሪክ ት/ም ክፍል “ተራማጅ ምሁራን” የውግዘቱ ተባባሪ ነበሩ። “ግዜ በጄ ብልህ እንዳመጣልህ በጅራፍ አትዠልጥ፣ አንድ ቀን የጅራፉ ጫፍ ታጥፎ እራስህን ያገኝሃልና” የሚባለው ብሂል እውነት ሆኖ፤ በ20ኛው መ.ክ.ዘ ማገባደጃ ላይ ይኸው ኩነኔ ጎልብቶ “በዘመናዊ ታሪክ ሙያተኞች የተፃፈውም የኢትዮጵያ ታሪክ የደብተራ ታሪክ ነው፣ ሙያተኞቹም የገዢ መንግስታቱ ፍርፋሪ ሻች ደብተራዎች ናቸው” ወደ ሚል ደረጃ ተሸጋግሮ ለመታየት በቃ። የዚህ “የኢትዮጵያን ታሪክ እና ታሪክ ጸሐፊዎችን የማጠልሸት” ዘመቻ መሰረታዊ ምክንያት ግን ፖለቲካዊ እንጂ እምብዛም እውነትነት የሌለበት ነው። የመዋዕለ ዜና እና ገድል አፃፃፍ መንገዶችና የሚፃፉበት ዓላማ ከሌላው ዓለም የኢትዮጵያ የተለየ ሆኖ አይታይም። የልምድ ታሪክ ፀሐፊዎቹም አኳኳንና የፅሑፋቸው ይዘትና አቀራረብ ከሌላው ዓለም የተለየ ሆኖ አይገኝም። ሁሉን የሚያግባባ ታሪክ በአውሮጳም በሰሜን አሜሪካም በዓለም ሁሉ ታይቶ አይታወቅም። “ታዲያ የዚህ የሌለ ኩነኔ ባለቤትና የኩነኔው ፖለቲካዊ ግብ ማንና ምን ይሆኑ?” ለዚህም መልሱ ይህ ነው፤ … ባለቤቱ የአንዳርጋቸው “ያ ትውልድ”፣ ዓላማውም ታሪክን በከለስ የኢትዮጵያውያንን ነባር መኅበረ-ፖለቲካ አደረጃጀት አፈራርሶ “ትውልዱ” በሚያቀነቅነው የግራ ዘመም ማኅበረ-ፖለቲካ በቀላሉ ለማደራጀት የኃልዮተ-ዕሴት መሰረት በማግኘት ለስልጣን መብቃት ነው። የዚህም ትውልድ አስኳል በ1927 ዓ.ም (የጣልያን ወረራ) እና በ1953 ዓ.ም (የታህሳሱ የመንግስቱ ነዋይ ግርግር) መሃል ተወላጅ ሆኖ ታሪክ ከላሽነትን የፖለቲካ ስራቴጂ ያደረገ፣ ከሚወክለው የፖለቲካ ቡድን የስልጣን ግብ ውጪ ኅብረተሰባዊም ሆነ ሐገረሰባዊ ተልዕኮ የሌለው ነው። ከኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ሕወኣት፣ አብዮታዊ ሰደድ፣ ማሌሪድ፣ ወዝሊግ … ወዘተ ታሪክ እንደሚንረዳው፤ ይህ ትውልድ ወከልኩት ለሚለው የፖለቲካ ቡድን የኢትዮጵያን ሕዝብ፥ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አባላትን በጠላትነት ደምስስ፥ እራስህን ሰዋ፥ ቢባል ወደ ኋላ የማይል፤ የፖለቲካ ስብዕናውን ከማክሲዝም፥ ሌኒኒዝም፥ ስታሊኒዝም ቀነጫጭቦ ተጎናፅፎ ሳያውቅ ያወቀ መስሎ ለመታየት የሚተጋ፤ በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ እንጂ በሥራና ጥረት የማያምን፣ ይህም ሆኖ ግን ከኔ ትውልድ ባላይ አዋቂ ላሳር በማለት የሚታበይ፤ ላለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያን ቆራርጦ ያጠፋ፣ ከጥፋቱ ግን መማር ያልቻለ፤ ለራሱም አሳዶ ተሳዳጅ፣ የብብት ውስጥ ቡግንጅ፤ ክፉ ትውልድ ነው። ይኸውም ትውልድ በጓድ ፕሬዘደንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ በጠቅላይ ሚኒሰቴር መለስ ዜናዊ፣ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወረቂ፣ በጃል ዳውድ ኢብሳ፣ በዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ፣ በአቶ ስብሃት ነጋ፣ በአቶ ሐይሌ ፊዳ፣ በዶ/ር ሰናይ ልኬ፣ … ወዘተ የተወከለው ነው። ታዲያ ይህ ትውልድ ይህን የፖለቲካ ስብዕናውን ከምን አመጣው ብለህ ለምትጠይቀኝ ሦስት ዋና ዋና ሐገረሰባዊና ዓለም-ዓቀፋዊ አውዶችን አመለክትሃለው። እነኝህም ከአምስቱ ዓመት የጣልያን የቋንቋ፣ የኃይማኖት… ከፋፋይ የፖለቲካ ሴራዊ አስተዳደር፣ ከዓምስት ዓመታት ስደት በኋላ አፄ ኃይለ ሥላሴ መልሰው ከተከሉትና መሬትን መሰረት ካደረገው ጉልታዊ ስርዓት (በዚህ አውድ ሥር ኤርትራን ከኢትዮጵያ የማቀላቀል የምዕተረ-ዓመቱን ተስተካካይ የማይገኝለት ሥህተት ልብ ማለት አትርሳ) እና ከሩሲያ-ቻይና-ኩባ ድረስ ተሰራፍቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ከነበረው ዓለም ዓቀፋዊ የኮሙኒሰት/ሶሻሊት ዐውዶች ነው። ይህን ግን በቅጡ ለማስረዳት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይፈልጋልና በሌላ ግዜ ብንመለስብት ሳይሻል አይቀርም። ብቻ ለግዜው የካቲት 1፣ 1946 ዓ.ም የተወለደው አንዳርጋቸው ፅጌ ታሪክ ከላሽነት ቢጣባው ከተፈጠረበት ትውልድ ውርዴ ሆኖበት እንጂ ግለኛ ጠባይ ሆኖበት እንዳልሆነ አገንዝቦ ከወሰድክ ይበቃል። ከዚህ ቀጥለን አንዳርጋቸው ከመረጃ ምንጮች ልየታ፣ ምዘናና አቀራረብ እስከ የኢትዮጵያ ታሪክ አጠናን ንድፈ-ሃሳብ ክለሳ ትችት የፈፀማቸውን የንድፈ-ሐሳብ፣ የሥነ-ዘዴ እና የደረቅ ዕውነታ ሕፀፆች እንንቅሳለን።

●● ሕጸጸ ንድፈ ሐሳብ ●●

አንዳርጋቸው፣ እንደ አበዛኛዎቹ ማርክሲስት-ሌኒኒሰት-ሰታሊኒሰት ፅንፈኛ የትውልድ ተራማጅ ጓዶቹ፣ ታሪክ ሰሪውና የታሪኩም ዋንኛ ባለቤት ከላዕላዩ የኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ ምንዝሩ/ሕዳጡ ነው የሚል ጽኑ አመለካከት አለው። እርግጥ ነው ኢትዮጵያን ጨምሮ ለምዕተ ዓመታት ታሪክ ፀሐፊዎች ከመደዴው የኅብረተሰብ ይልቅ ለነገስቱና መሳፍነቱ፣ ከተራው ወታደር ይልቅ ለጀነራሉ፣ ከሴተኛ-አዳሪዎች ይልቅ ለልዕልታቱ/ወይዛዝርቱ፤ ከማኅበራዊውና ባሕል ታሪክ ይልቅ ለፖለቲካው … ወዘተ ታሪክ ትኩረት ይሰጡ ነበር። ይኸውም ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ታሪክ አጠናን በአንድ ታሪካዊ ክስተት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑትን አካላት በሙሉ የሚገባቸውን የውክልና ሥፍራ አይሰጥም በሚል የሰላ ትችት ሲያስተናግድ ከምዕተ ዓመት በላይ እድሜን አስቆጥሯል። ችግሩም ዛሬ ድረስ ሙሉ ለሙሉ ሳይቀረፍ መዝለቁ እውነት ነው። ለዚህ ችግር ዘልቆ ዛሬ ድረስ መምጣት ዋንኛ ምክንያቱ፣ የገንዘብና ሙያተኛ እክሎች እንዳሉ ሆነው፤ ካልተደራጀው የኅብረተሰብ ክፍል የተደራጀው፣ ከተራ ወታደሩ ይልቅ ጀነራሩ፣ ከርዝራዥ ቢሮክዮክራቱ ይልቅ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፣ ካልተደራጀው ቀጥቃጭና ሸክላ ሰሪ ይልቅ የተደራጀው የፋብሪካ ወዛደር፥ አስተማሪው፥ ወታደሩ … ለመረጃ ቅርብ መሆናቸው ነው። አንዳርጋቸው ወደደም ጠላም ከአንድ የምንጃር ጭሰኛ ይልቅ በድምፅ፣ በፅሁፍና በምስል፣ በሰዎች ትውስታ ውስጥ መረጃ ጥሎ አልፏል። እንዲያም ሆኖ እንኳን የዕውቀቱን ክፍተት ለመሙላት ኢትዮጵያን ጨምሮ የታሪክ አጠናን ዘዴዎች በየግዜው መሻሻል እያደረጉ የዕውቀት ክፍተቱ እየተሞላ ነው። “የሞኝ ለቅሶ፣ መልሶ መልሶ” እንደ ሚባለው Andey-አባቡነና ትውልዱ ይህንን ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ የታሪክ አጠናን ትችት ዛሬም ድረስ ለታሪክ ክለሳ ብልሃታቸው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። አንዳርጋቸውም በዚህ መፅሐፉ “ሁሉም በሚወከለበት አንድ የታሪክ ክስተት ተገቢውን ውክልና ያግኝ የሚለውን የታሪክ አጠናን ትችት” ትችት፤ ለተነሳበት የታሪክ ክለሳ ሴራው በሚያመቸው መንገድ አጣሞ፤ የነገስታቱ፣ የመሳፍንቱ፣ የጀነራሎቹ የታሪክ ውክልና ተሰረዞ በመደዴው የኅብረተሰብ ይተካ በሚል ያቀርበዋል። ከዚህ የተዛባ ግንዘቤው ተነስቶ የታሪክ መረጃዎችን አዛብቶ በመተርጎም፣ አፄ ምንልክና መኳንንቶቻቸው አዲስ አበባ ተጋድመው ብርዶዋቸውን በጠጅ እያወራረዱ “ባርያዎቻቸውን” አደዋ ድረስ ልከው አዋግተው ድል የተቀዳጁ ይመስል፣ የአደዋን ድል ባለቤትነት ለ“ባሪዎች”፣ “ሕዳጣን ሙስሊሞች” ለሚላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ያጎናፅፋል። ይህን የግንዛቤ ስንኩልነቱንም ሲያልቀው በመፅሐፉ የኢሕአፓን የላዕላይ አመራር ታሪክ እንኳ ትኩረት አልሰጠውም በማለት በየምዕራፉ ሲምልና ሲገዘት ይስተዋላል (ለዓብነትም “መግባቢያ” ባለው ክፍል ላይ ያቀረበውን ሐተታ ፥ ገፅ 497 ተመልከት)። የአንድ ተራ የፓርቲውን አባል ያክል ታሪኩ ተጠንቶ የማይታወቀውን የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን ታሪክ በአመራር ስለሆነ ብቻ አግልሎ ሽፋን አለመስጠት እንደምን የኢሕአፓን ታሪክ ምሉዕ ሊያደርገው እንደሚችል የሚያውቀው አንዳርጋቸው ብቻ ነው። ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ለኢሕአፓ አወቃቀር የላዕላይ መደብ አካል ቢሆን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከሕዳጣን ተርታ ስለመሆኑ ታሪክ ከላሹ Andey-አባቡ መቼም ቢሆን የሚገባው አይመስለኝም። የሚገርመው አባቡ ይህንን የታሪክ አጠናን አገንዝቦውን እንግሊዝ ከ30 ዓመት በላይ ሲኖር ወቅታዊ የታሪክ አጠናን ዘዴ መፅሐፍትን በማንበብ አለማዳበሩና በሕይወት ተመክሮው (የኢሕአፓ የትግል ጓዶቹ “ታሪክ ሰሪው ሰፊ ሕዝብ ነው!” በሚል ሲያወርዷቸው ከነበሩት መፈክሮች፣ እንግሊዝ በስደት ሲኖር ከተከታተላቸው የቴሌቪዥን ትዕይቶች … ወዘተ) ብቻ መመስረቱ ነው (በተለይ ክፍል አንድ ምዕራፍ ሁለትን ተመልከት)።

●● ሕጸጸ መረጃ ልየታ ፡ ወ ፡ ትርጓሜ አንድምታ ●●

ይህንንም ቁንፅል የመፈክር ዕውቀቱን በተግባር መንዝሮ ነበሩን የኢትዮጵያ ታሪክ ከመሰረቱ ከልሶ ለሚፈልገው የፖለቲካ ርዕዮት መደላድል አመቻችቶ ሲያቀርብ Andey-አባቡ የመረጃ ልየታው ላይ ሁለት የመረጃ ልየታ አሻጥሮች ይሰራል። የመጀመሪያው የአሻጥር ብልሃቱም ለክለሳው የማያመቹትን የታሪክ ምሁራንና ስራዎቻቸውን በጅምላው በማጠልሽት በሥራው አለማካተት ነው። የኢትዮጵያ ታሪክንና ታሪክ ፀሐፊዎችም ላይ ትችቱን ሲያወርድም፤ የኢትዮጵያ ታሪክ የባሪያዎችንና የሴተኛ አዳሪዎችን እውነተኛ የታሪክ ባለቤትነት በአስጠያፊነት ፈርጆ የማይቀበል የልጆች እንቅልፍ ማስተኛ ተረት ተረት ነው፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች የጦርነት ሥፍራዎችን፣ ቀናትን፣ የላዕላይ መሪዎችን ሥምና በጦርነቶች የተሳተፉ አጋሰሶች ቁጥር ሲዘረዝሩ ግዜ የሚያባክኑ፣ የታሪክ ክስተቶችን ድምር የውጤት ገፅታ በሚያሳይ ትንታኔ መስጠት የማይችሉ የቤተ-መንግስት ፍርፋሪ ናፋቂ አድረባዮች ናቸው ይላል (ገፆች 36-41)። በተለይ በኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ላይ የሰነዘረውን “የማይመች ታሪክ ደባቂነት ጠባይ” በአብነት ሲያስረዳም፤ በአደዋ ጦርነት ላይ የተሳተፉና ሕይወታቸውን ለአገራቸው የሰዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሐይማኖታቸው ምክንያት ቀብር መከልከላቸውን በታሪክነቱ እንዳይነገር ሆነ ብለው መደበቃቸውን ይጠቅሳል፤ ስለታሪክ ትንታኔ ክህሎታቸው ውስንነትም የአደዋ ድል በአለም ዙሪያ የገታውን የአውሮጳውያንን የሰፈራ ፕሮግራም ተመልክተው ትንታኔ ለማቅረብ አልቻሉም በማለት ሲወቅስ፤ ለታሪክ ባለሙያዎቹም አድረባይነት ማስረጃ ሲጠቅስም ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ እ.አ.አ በ2009 “The Ethiopian Revolution” በሚለው መፅሐፉ ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከንግስት ጣይቱ ብጡል ጋር አመሳስሎ ያቀረበውን ውዳሴ ከንቱ ገለጻ ይጠቅሳል። እዚህ ላይ ለዚህ የአንዳርጋቸው አደገኛ በሴራ የተተበተበ የድንግር ትችት ማረሚያ መስጠት ተገቢ ነው።

የድንግር ማረሚያ፤ የRaymond Jonas, The Battle of Adawa ገጽ 291ን ጠቅሶ፣ የአደዋ ዘማች የእስልምና እምነት ተከታዮች የቀብር ክልከላ በሚመለከት ያቀረበው ትችት፣ ከምንጭ ምንጭ ተዛንፎ ተጠቅሶ የቀረበ ነው። አንዳርጋቸው አገኘሁ ብሎ የተባለውን ትርክት ተቀብሎ ወሬ ለማራባት ከመጣደፉ በፊት ቆም ብሎ የጆናስን ምንጭ መመርመር ነበረበት። ጆናስ የዚህን መረጃ አገኘሁ ብሎ የጠቀሰው ከ Augustus Wyled, Modern Abyssinia, pp. 147-48, 172, 173, 213, ነው። አብዛኛዎቹ ገፆች (pp. 147-48, 173፣ 213) የተባለውን መረጃ የሚያመለክቱ አይደሉም። በዋይሌድ መጽሐፍ ገፅ 172 ላይ የተመለከተውም ቢሆን ጆናስ “Ethiopians did not bother to bury their Muslim dead” በሚል አጠቃሎ እንዳቀረበው የሚያመለክት አይደለም። ዋይሌድ ያለውን ቃል በቃል ለማስቀመጥ “Not a single body of the Mohammedan Gallas had been touched, and carcasses of the horses and mules were strewn” የሚል ነው። ይባሱን ደግሞ ዋይሌድ ይህን ያልተቀበረ እሬሳ አየሁ የሚለው ጦርነቱ ተደርጎ ከአራት ወራት በኋላ ነው። እሬሳው የሙስሊም ይሁን የክርስቲያን ለ4 ወራት ሳይበሰብስ ለመለየት ቢችል እንኳን ይህ አልተቀበረም የተባለ የሙስሊም ኦሮሞ ፈረሰኞች ጦር የወሎው ንጉስ ሚካኤል ጦር እንደ ነበር ከሁኔታዎች ለመገመት ይቻላል። ንጉሱ ለምን ለቀብር እንዳላደረሳቸው ዛሬ ላይ ሆነን ግምታችንን ከመስጠት በተስቀር እውነተኛውን ምክንያት ለማወቅ አይቻለንም። በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ እንደ ምንረዳው ትልቅ ጦርነት ተደርጎ ከሶስት ቀናት በላይ ጦርነቱ በተደረገበት አከባቢ አለመቆየቱን ነው። ተነስቶ ከሚናኝ የተስቦና ኮሌራ ወረርሽኝ ፍራቻ ጦርነት ከተካሄደበት ስፍራ እግሬ አውጪኝ ብሎ መሸሽ የተለመደ ነው። ከሰገሌ እስከ ባድሜ ታሪካችን ከጦርነት ማግስት ሟች ከመቅበር የሚቀናን ሽሽት መሆኑን እናውቀለ። ግን አደዋን በሚመለከት በጦርነቱ ወቅት የሰው እና የእንስሳት እሬሳ በ40 ማይል ንፍቀ-ክበብ መበተኑን ጆናስም አመልክቷል። የተቀበሩትም ቢሆኑ በአግባብ እንዳልተቀበሩና ግማሽ አካላቸው ውጭ መሆኑን አመልክቷል። ነገር ግን ስለ ሐይማኖታቸው የሙስሊም የአደዋ ተዋጊዎች በሙሉ ቅብር የተከለከሉ አስመስሎ ማቅረብ በእውነት መጀመሪያ ከጆናስ ቀጥሎ ከአንዳርጋቸው የሚጠበቅ ስራ አይደለም። አንባቢዎች ሆይ አስኪ Andey-አባቡን ሰበሉ እንደላኩት ራቱ ሐገርህን አፈራርሰህ ወደ ትቢያ ለመቀየር አትትጋ በሉልኝ። አደዋ የአውሮፓውያንን የዓለም ዙሪያ ሰፈራ ገቷል የሚለው ትርክትም ትክክል አይደለም። በጆናስ መፅሐፍም ውስጥ ፈልጌ ማየት አልቻልኩም። አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ከአደዋ አራት መቶና ሶስት መቶ አመታት በፊት ጀምሮ ለጤና ተስማሚነት ባላቸው ቦታዎች ሁሉ (ደቡብ አፍሪካ፣ ሲውታ፣ አልጄሪያ … ወዘተ) ሰፍረዋል። ያልሰፈሩት አፍሪካውያን በብዛት በሰፈሩባቸው (የምዕራብ አፍሪካ አከበባቢዎች) እና ለጤና ተስማሚ ባልሆኑ ቦታዎቸ ነው። አፍሪካ ለሰፈራ ከመምጣታቸው በፊት (ከአደዋ ጦርነት በፊት) በአለም ዙሪያ ሰፍረው በቅቷቸዋል። እ.ኤ.አ በ1896 የተካሄደው የአደዋ ጦርነት … የትኛው የአለም ክፍል ላይ ሰፈራን እነዳስቆመ ግልጥ አይደለም። በእንዲህ ያለ ቅጥፈት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ቢቀር ይሻላል።

ፕሮፌሰር ገብሩን ታረቀን ጠቅሶ የታሪክ ምሁራን ላበላቸው የሚጮሁ አድርባዮች ናቸው በሚል ላቀረበውም የጥቅል ትችት፤ ይህ የፕሮፌሰር ገብሩ ፕሮፈሰር ትንታኔ እንኳን ፕሮፌሰር ባህሩን፣ መርድን፣ ታደሰን፣ … ወዘተ ስራዎች ሊወክል ይቅርና የራሱንም ስራዎች አይወክልም። የእነኝህንም ምሁራን ስራዎች የጦርሜዳ፣ የዓመተ ምህረትና የአጋሰስ መዘርዘሪያ መዝገብ ነው ብሎ መተቸት ተገቢ አይደለም። አበበ በቂላ ማራቶን ሮጦ ኢትዮጵያን ከአውሮጳ፣ ሩቅ ምስራቅ (ቶኪዮ) እና ላቲን አሜሪካ (ሜክሲኮ) ካስተዋወቀው ባልተናነሰ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ A History of Modern Ethiopia 1855-1991 በሚለው መፅሐፉ ኢትዮጵያን በአለም ዙሪያ የቀለሙ አለም አስተዋውቋል። Andey-አባቡ እስካሁን ይህን መፅሐፍ ያላነበበው እንደሆን Pioneer of Change in Ethiopia (2002) እና The Quest for Socialist Ethiopia (2014) ጨምሮ “ከቀረ የዘገየ ይሻላል” በሚለው ፈሊጣዊ አባባል አሳሳቢነት አፈላልጎ እንዲያነብ መክረ-ሐሰብ ወርውረንለታል። … ለታሪክ ክለሳ ብልሃቱ ባያመቹት አስወግዷቸው እንደሆነም … ባልተገባ ጥላሸት መቀባቱ አግባብ እንዳልሆነ የቅርብ ዘመድ አዝማድ ሊመክረው ይገባል። የAndey-አባቡ ሁለተኛው የታሪክ ክለሳ ብልሃቱ ዋንኛ የመረጃ ምንጩን የኔበንተኔ Autobiography (የተክለ ኃዋርያት ተክለማርያም፣ “ኦቶባዮግራፊ/የሕይወት ታሪክ”፤ የራስ የዕምሩ ኃይለ ሥላሴ፣ “ካየሁትና ከሰማሁት”፤ የጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ፣ “እኛ እና አብዮቱ”፤ የክፍሉ ታደሰ፣ “ያ ትውልድ”፤ የጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ “ትግላችን” … ወዘተ)፤ የልምድ ታሪክ ፀሐፊ ሥራዎችን (የተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከአፄ ቴውድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ”፤ አጼ ዮኋንስና “የኢትዮጵያ አንድነት”፤ ዘውዴ ረታ፣ “የኤርትራ ጉዳይ”፤ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት”፤ “ተፈሪ መኮንን ረዥም የሥልጣን ጉዞ” … ወዘተ)፤ የኅብረተሰብና ሥነ-ሰብዕ ሥራዎች (የ Donald Levine, Wax and Gold) እና የሁለተኛ ደረጃ አፋዊ መረጃዎች (አባቱና ሌሎች ዘመድ አዝማድ ነገሩኝ የሚላቸው መረጃዎች) ማድረጉ ነው። አንድ የታሪክ ፀሐፊ በተለይ የኔበንተኔ እና የሁለተኛ ደረጃ አፋዊ መረጃዎችን በምንጭነት ሲጠቀም እጅግ መጠንቀቅ፤ መረጃዎቹንም ከሌሎች የኔበንተኔ ተጓዳኝ ፥ የበተርሱ (biography)፥ የሰነድ፥ የዕለት ውሎ ድርሳናት፥ የሁለተኛ ደረጃ … ወዘተ መረጃዎች ጋር መላልሶ ማመሳከር፣ ማገናዘብና መመዘን ይኖርበታል። የሁለተኛ ደረጃ አፋዊ መረጃ ከአፍ አፍ ሲተላለፍ የመዛባቱን ያህል የኔበንተኔ ድርሳናትም የሚፃፉት ከባለ ግለታሪኩ ሰው የአተያይ አቅጣጫ ብቻ ነው። ከዚህም የተነሳ ለታሪክ ክለሳ ውንብድና የተጋለጡ ናቸው። Andey-አባቡ የእነኝህ መረጃዎችን ክፍተት ጠንቅቆ አውቆ አንባቢን ለማወናበድ ተጠቅሞበታል። እነሆ አብነት ካሻህ ተከተለኝ።

●● ሕጸጸ አተረጓጎም፡ ወ፡ ግድፈተ እውነታ ●●

የአደዋ ድል ታሪክ ያለተዘመረላቸው (የሴት) የባሪያዎች ታሪክ ነው የሚለው Andey-አባቡ የመፅሐፉንም መታሰቢያነት ወለተ አማኑልን ለመሳሰሉ የአደዋ ጀግና የሴት ባሪያዎች ሰጥቻለሁ ይላል (የመታሰቢያ አበርክቶ ገፅ፣ ገፅ 38፣ 153 ተመልከት)። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ወለተ አማኑል “አገልጋይ” እንጂ ባሪያ አይደሉም። ባርነትን ሆነ ብሎ መረጃ አዛብቶ በሴትዮዋ ላይ የለጠፈባቸው ታሪክ ከላሹ Andey-አባቡ ነው። ይህንንም ከዋናው የመረጃ ምንጭ የተክለ ሐዋርያት የሕይወት ታሪክ ቅጂ ለማጣራት ይቻላል። ለራሱ ተደናግሮ አደናጋሪው Andey-አባቡ በአጠቃላይ በዚህ መፅሐፉ ውሰጥ አስሬ ተቆርቋሪ መስሎ “ባሪያ” “ባሪያ” በማለት የሚያቀርባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በ “አሽከርነት”፣ “አገልጋይነት”፣ “ሎሌነት”፣ አንዳንዴም “ጭሰኞነት”፣ ወዛደርነት/ሰራተኛ … ወዘተ የሚታወቁትን ሁሉ ነው (ገፆችን 38፣ 76-78፣ 113፣ 144፣ 347 ተመልከት)። ዶ/ር መላኩ በያን በብርሐንና ሰላም ጋዜጣ መጣጥፎቹ “እኔ የአልጋ ወራሽ አሽከር ነኝ” ማለት የቀናዋልና እንደ አንዳርጋቸው ዶ/ር መለኩ በያንም “ባርያ” ነበር ማለት ነው። Andey ታሪክ ፀሐፊዎች ደብቀውለት ነው እንጂ አፄ ምንሊክም የባሪያ ልጅ ነው (ገፅ 77 ተመልከት) በሚል ሐሜት የረጨውም የእናትየውን (እጅጋየሁ ለማ አድያሞ) አገልጋይነት ከባርነት ጋር አደናግሮ ነው። ሴትዮዋ እንደተባለው ባሪያ እንኳ ቢሆኑ በኅብረተሰባችን ችግር እንዳልሆነ ከላይ አመልክቻለሁ፤ ባሪያ የላዕላይ መደብ አባል ነው ብዬ። በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዘሩን በእናቱ ወገን አለመቁጠሩ እንዳለም መዘንጋት የለበትም። ድንግሩን ሲያከፋው ደግሞ እነኝህን “ባሪያ” የሚላቸውን የኅብረተሰቡ ክፍሎች ከአሜሪካኖቹ “ባሮች” ጋር አንድ አድርጎ ያቀርባቸዋል (ገፅ 82 ተመልከት)። እኛ ግን ስናውቅ የኢትዮጵያ “ባሪያ” መደቡ ከሕዳጣን ተርታ ሳይሆን “ከላዕላዩ” የኅብረተሰብ ተርታ ነው። የኢትዮጵያ ባርያ እንደ ሰሜን አሜሪካ ባርያ መሬት አርሶ የገንዘብ ትርፍ የማያመጣ፤ ተቀዳሚ ስራውም በቅሎ ጭኖ አንግቶ ጌታውን በማጀብ ከወዲያ ወዲህ ሲንገላጀጅ የሚውል፤ የተስካርና የክበረ-በዓላትን ጌሾ መውቀጥ፤ ከዕልፍኝ አዳራሽ እያለ ጌታው በማይኖር ግዜ ወይዛዝርቱን ሲያማግጥ የሚውል፤ የቤተ-መንግስት ሥርዓት እያጠና፥ ፈረስ ማጋለብ፥ ጦር መወርወር እየቻለ፥ በየ አውደ ጦርነቱ ጀብድ እየሰራ፤ እስከ ብትወደድነት ማዕረግ የሚጎናፀፍ ነው። ይህን እህል ፈጅ የ “ባሪያ” ወገን መቀለቡ እየተሳነው መኳንንቱና መሳፍንቱ እንኳን ከሁለትና ሶስት በላይ መያዝ አይፈልግም። ይህንን ምቾት ለምዶ በኋላ አርነት ወጥተሃል ሂድ ወዳሻህ ቢባል “አሻፈረኝ ብሞት ከጌታዬ ቤት አልወጣም” ያለውም በዚሁ ምክንያት ነው። በዚህ መፅሐፉ Andey-አባቡ የአዲስ አበባንም የባለቤትነት ታሪክ በቸርነት የመጀመሪያ ሰፋሪዎች ናቸው ለሚላቸው “ባሪያዎች” እና “ሴተኛ-አዳሪዎች” ሲሰጥ በየቦታው ይነበባል (ገጾች 72-73፣ 76፣ 81፣ 113፣ 347 ተመልከት)። ይህ ትርክት ግን ምንም መስረጃ የማይቀርብበት “የልጆች እንቅልፍ ማስተኛ ተረት ተረት ነው!!)።

የAndey-አባቡ ችግር መረጃ አዛብቶ እንደፈለገው ተንትኖ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ እንደ ልብ ወለድ ትርክት ፈጥሮ እመነኝ ብሎ መጠየቁም ነው። ለዚህ አብነት ከሻህ እነሆ። በ1877 ዓ.ም አጤ ዮኋንስ ለንጉስ ምንልክ ግብፆች ከሐረር እንደ ወጡ ይህንን መልዕክት ላኩበት ይልሃል፤ “ምን ይዞህ ነው ያልተቀሳቀስከው? እንዲህ አይነቱን ነገር ግዜ ሳያጠፉ መፈጸም ይጠይቃል። የግብጦች እግር ሲወጣ አገሩን በእጃችሁ ያላገባችሁት ለምንድን ነው? የማትዘምት ከሆነ እኔው እራሴ እመጣለሁ።” (ገፅ 56) … አንባቢ ሆይ ይህ ምን ማለት እነደሆነ ታውቃለህ? በ19ኛው መ.ክ.ዘ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ሸዋና አጤ ምንሊክ ወደ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ ኢትዮጵያ የደረጉትን መጠነ ሰፊ መስፋፋት አጤ ዮኋንስ በደጀንነት ይደግፉት ነበር ማለት ነው። ይህም አባባል እስከ ዛሬ የምናውቀውን ታሪክ ባፍ ጢሙ የሚያቆም ነው። … ታዲያ የኔ ብጤ ጨዋ የመረጃ ምንጩን መሰስ ብሎ ይፈትሻል። Andey-አባቡ የመረጃ ምንጩን ሲጠቅስ ግን እንዲህ ይላል “እንዲህ ማለታቸውን መፅሐፉን ማስታወስ ባልችልም ግን ማንበቤን እርግጠኛ ነኝ” ብሎህ ያርፈዋል። ስለዚህም አባባሉ እንዲሀ ብለኝ እንመልሳለን “Andey-አባቡ ሆይ አንተን የመሰሉ ታሪክ ከላሾች በበዙበት በዚህ ዘመን በአንብቤለሁ መሃላ አናምንምና … ቧልትህን ትተህ የመረጃህን ምንጭ በበትክክል ጠቅሰህ አሳየን !!” በሌላ ቦታ ደግሞ ደጃች ነሲቡ ዘአማኑኤል (በ1927ቱ ጣልያን ወረራ ግዜ የደቡቡ ግንባር ዋና አዝማች) እንዲህ ይላል። በሐምሌ 1928 ዓ.ም እነ ባልቻ አባ ነብሶ አዲስ አበባን ከግራዝያኒ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ሙከራ አድርገው የከሸፈው “ደጃች ነሲቡ መረጃ አውጥተው ለጣልያኖች ስለሰጡ ይመስለኛል። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ለእነ ራስ ድስታ ሆስፒታል፣ ለደጃች ገብረማሪያም ጋሪ የሊሴ ገብረማርም ት/ቤት በመታሰቢያነት ሲሰየምላቸው ለደጃች ነሲቡ ያልተሰየመላቸው። ተሳስቼ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ይላል (ገፅ 144-145)። መፅሐፍ ፅፎ የሰው ስም ካጠፉ በኋላ እንደ ዘበት በይቅርታ አድረጉልኝ ቀላል መስሎ ሚታየው በታሪክ ከላሹ Andey-አባቡ አተያይ ብቻ ነው። … ወደጄ ደጃች ነሲቡ የደቡቡ ግንባር በታላቅ ጅግነነት ተዋግቶ በሽንፈት ጦሩ እንደ ተፈታ በጅቡቲ በኩል አውሮጳ ሄደው … እነ ባልቻ ሳፎ አዲስ አበባን መልሰው ለመያዝ ሙከራ ከማድረጋቸው ከአንድ አመት በፊት በሳንባ ነቀርሳ ስዊዘርላንድ ውስጥ ሞተው ተቀብረዋል። ከዚህ ታሪክ ጋር አያይዞ Andey-አባቡ ያቀረበው የራስ ደስታ ዳምጠው እና የደጃች ገብረማርያም በጦር ግንባር መሰዋት፣ የሱማሌና የኦሮሞ ሕብረተሰብ የጋራ ግንባር ፈጥረው ከጣልያን በመወገን “የነፍጠኛውን” ልጆች ሳይቀር አንገት ቀልተው ከሐረር አስወጥተዋል (ገፆች 144-148)…. ወዘተ የሚለው የበሬ ወለደ ትርክት በሙሉ የታሪክ ክለሳ የፈጠራ ድርሰት ነው።

በአጠቃላይ ይህን መፅሐፍ አንብበህ አዳርጋቸው በአንድ ወገን ለኢሕአፓና ለኤርትራ ጥያቄ የሚያሳየውን ፍፁም ኢፍትሃዊ ተቆርቋሪነት (ገፆች 369-371፣ 399-400፣ 416-423፣ 488-489፣ 505-507፣ 588-589 ተመልከት) ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ለንጉሳዊውና ለደርግ ስርዓቶች የሚያሳየውን ስር የሰደደ ጥላቻ ሲረዳህ (ገፆች 100-103፣ 131-132፣ 342፣ 382-387 ተመልከት) … በኢትዮጵያውያን ያለፈ ግማሽ ምዕተ ዓመት እንጭጭ/ዘገምተኛ የፖለቲካ እሳቤ ባህል ላይ የምር ተስፋ ትቆረጣለህ። ይህን ሁሉ ልብ ብለህ ካስተዋልክ በኋላ እውነትም የዚህ ሰው መፅሐፍ ርዕስስ “ትውልድ ይደናገር፣ እኛም እንቀባጥር” መባል ሲያንሰው ነው ብለህ ፍርድ እንደምትሰጠኝ ተስፋዬ የፀና ነው። በል ወዳጄ ለዛሬው አቃቂሬን በዚሁ ላክትም። ለቀጣዩ ቸር ይግጠመን!!! by Mesele Terecha

Filed in: Amharic