>

የምኒልክን እምዬነት ፤ የአድዋን ድል ነጻነት የሚሞግት ክፉ ትውልድ!!! (ማእረጉ ስነወርቅ)

የምኒልክን እምዬነት ፤ የአድዋን ድል ነጻነት የሚሞግት ክፉ ትውልድ!!!
ማእረጉ ስነወርቅ
ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ “…ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ ሰው ናቸው፡፡…” ሲል የመሰከረላቸው ሰው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ባቡር፣ መኪና፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ሲኒማ… ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁት፡፡ የምንወዳትን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያውለበለቡትም እርሳቸው ናቸው፣ ከልማዳዊ አስተዳደር ተላቅቀው ሚኒስትሮችን መሾም የጀመሩትም እሳቸው ናቸው፣ የመጀመሪያውን ዘመናዊ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል የከፈቱትም እሳቸው ናቸው፡፡
አውሮጳውያን አፍሪቃን ሲቆራመቱ ኢትዮጵያን ግን የነርሱ ቅርጫ ከመሆን ያተረፏት እርሳቸው፣ ራሳቸውና ብልሕ አመራራቸው ነው፡፡ በርግጥ ምኒልክ ዘመን አውሮጳውያን በስልጣኔ ጎዳና ላይ ብዙ እጥፍ ተጉዘው ነበር፡፡ ምኒልክ ግን የተረከቧትን ኢትዮጵያ ከነድንቁርናዋ ለተከተዮቹ አላስረከቡም፡፡ አቅማቸው የሚፈቅደውን ያህል ለኢትዮጵያ ብርሃን አሳይተው፣ ከዚያ በፊትና በኋላ ለኢትዮጵያውያን መሪዎች ያልተፈቀደ የሚመስለውን ታምሞ የመሞት ዕድል አግኝተዋል፡፡
የአፄ ምኒልክ ደግነት፣ ዘመናዊነትና መልካም አስተዳደር ዘመን የሚዘክረው ቢሆንም÷ አፄው ለኢትዮጵያ ካበረከቱት ትሩፋት ይልቅ ጨቋኝነታቸው ይገንናል የሚሉ ወገኖችም አልጠፉም፡፡ በዘመናቸው የነበረው ሕዝብ ግን ‹እምዬ ምኒልክ› እያለ ነበር የሚጠራቸው፡፡
እውን ምኒልክ ‘እምዬ’ ነበሩ?
“ምኒልክ መጓዙን የምትጠይቁኝ፤
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ፡፡” ~
 የሚኒልክን መሞት አስመልክቶ እረኞች የተቀኙት፡፡
የዚህን ጦማር ርዕስ ያወጣሁት ከዚህ ሕዝባዊ ግጥምና ከሌላ “የምኒልክን እምዬነት እና የአድዋ ድል ነፃነትን የሚሞግት” ጦማር ላይ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹ ነገሥታትን የሚያወድሱ ግጥሞች በሃገራችን የተለመዱ ቢሆንም ይህንኛውንና ሌሎቹንም ለዳግማዊ ምኒልክ የተገጠሙትን ሕዝባዊ ሙገሳዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ሚኒልክ ከሞቱ በኋላ ሳይቀር ውዳሴው በመቀጠሉ ነው፡፡ ሕዝባዊ ግጥሞቹ የወቅቱን ሕዝባዊ ስሜት እንደሚያንፀባርቁ አይካድም፡፡ ለማወዳደሪያነት አፄ ቴዎድሮስና ምኒልክ በንግሥና ላይ እያሉ እና ከዚያ በኋላ ከተገጠሙላቸው ሕዝባዊ ግጥሞች ጥቂት ተጨማሪ ምሳሌ እንውሰድ፡፡
ለዳግማዊ ምኒልክ (በንግሥናቸው ዘመን፤ ካለፉም በኋላ ህዝቡ የተቀኘላቸው!
* ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ!
* እንዲህ ያለ ንጉሥ የንጉሥ ቂናጣ
ውሃ በመዘውር ሰገነት አወጣ
አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ፡?!?
ሞታቸው ሲሰማ፤
አጤ ምኒልክ ሲሞቱ
ምነው አትሔዱ ከፍታቱ?
እናንት ሰዎች ክፋታችሁ
አለማስቀበራችሁ?!?
እንዴት ውላችኋል÷ ንጉሥ ወዴት ዋሉ፤
እስከጊዜው ድረስ ገበያ ነበሩ፡፡
ያ ዳኘው ምኒልክ ሁዳዱን አስፍቶ፤
በየቦታው ተልሞ፣ በየቦታው ተግቶ፤
ሳይጨርስ አረፈ አዝመራውን ትቶ!!
 (ጳውሎስ ኞኞ፤ አጤ ምኒልክ)
ለአፄ ቴዎድሮስ (በንግሥናቸው ዘመን፤ ህዝቡ የተቀኘላቸው!)
* አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፣
እንደዚህ አንድዶ÷ ለብልቦ ይፍጃችሁ፡፡
* ሞጣ ቀራኒዮ ምነው አይታረስ፣
በሬሳ ላይ መጣሁ ከዚያ እስከዚህ ድረስ፡፡
* ልብሴንም ገፈፈው ለበሰው እርዘኛ
በሬዬንም ነዳው አረደው ነፍጠኛ
እህሌንም ዘረፈው በላው ቀለብተኛ
ንጉሥ የቀረዎት ጥቂት አማርኛ
ምነው ሆድ አይዘርፉ ዐርፌ እንድተኛ!?!
ሞታቸው ሲሰማ፤ በተቃዋሚዎቻቸው የተነገረ
* ቀስ ብለው ግቡ፣ ዝግ ብለው ግቡ፣
ደሞ እዚያ ላይ ወጥተሁ÷ እንዳታስቸግሩ፤
እኔው ብቻ ልግዛ ነውና ነገሩ!!!
* እሳት መጥቶ ተቋራ
ድፍን አበሻን ሊበላ፤
እንግሊዝ መጥቶ አጠፋው÷
ለእግዜርም እግዜር አለው!!!
 (ተክለፃዴቅ መኩሪያ፤ አፄ ቴዎድሮስ)
የዳግማዊ ምኒልክን እምዬነት የምናረጋግጠው÷ በሕዝባዊ ግጥሞች ብቻ አይደለም፤ በሌሎችም የግል ባሕሪያቸው ነው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ግብር በሚያበሉበት በማንኛውም ጊዜ አገልጋዮቻቸው ሳይበሉ ፈጽሞ አይበሉም ነበር፡፡ እንኳን በራሳቸው ድግስ ቀርቶ በመኳንቶቻቸው ድግስ ሲገኙም፣ የራሳቸውንም የመኳንንቶቻቸውንም አገልጋዮች ቀድመው እንዲበሉ ያደርጉ ነበር፡፡
ምኒልክ ለዘመናት ሲገፋ፣ ባለቤቱን በሹመኙች ሲቀማ እና አላግባብ ሲዘረፍ የኖረውን ገበሬ ችግር በመቅረፍ ለወታደሩ ደመወዝ በመቁረጥ ‘ባላገሩ ከሚገብው ግብር በስተቀር እንዳይነካ’ ብለው አወጁ፡፡ ይህንን አዋጅ ያላከበረ ወታደርም ከነአለቃው ከፍተኛ ቅጣት ስለሚቀጣ ገበሬውን ማስተንፈስ ችለዋል፡፡
ባንድ ወቅት ምኒልክ ሐረር ሳሉ ወደታች ገድላቸውን የምንተርክላቸው ራስ ጎበና መፈንቅለ መንግስት ሞክረዋል ተብለው÷ መኳንንቱ ይገደሉ ወይስ ይታሰሩ እያለ ሲከራከር፤ ፍርዱን የሚያፀድቁት ምኒልክ ግን “…ጎበናን እዚህ ለማድረስ 30 ዓመት ፈጅቶብኛል፤ አሁን አንድ ስህተት ሰራ ብዬ አልፈርድበትም፡፡” ብለው በነፃ ለቀዋቸዋል፡፡ ሌላ ጊዜ አንድ መሪጌታ የሚንልክን ልጅ ልዕልት ዘውዲቱን መሬት በግፍ ቀምታኛለች ብለው ከስሰዋቸው÷ መሬቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ በመፍረድ በፍትሕ ጉዳይ ከልጃቸውጋም ቢሆን እንደማይደራደሩ አስመስክረዋል – እምዬ ምኒልክ፡፡
ዘመናዊነት
“…በምኒል ዘመን የአገሪቱ ክብር አደገ፡፡ የዘመናዊ አስተዳደር መሰረትም ተጣለ፡፡ ንጉሡም በዘመናዊና በዘዴ አስተዳደር ይሰራሉ…” ኡላንዶርፍ፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ፤ አጤ ምኒልክ፤ ገጽ 378)
“ከዘመናዊነትጋ ስማቸው አብሮ ይነሳል፤… የምዕራባውያንን ቴክኖሎጂ እና አስተዳደራዊ ስልጣኔ ወደኢትዮጵያ ለማምጣት ጥልቅ ጉጉት ነበራቸው፡፡” ~ wikipedia.org
ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለው ሥፍራ የሁለቱን (ቴዎድሮስ እና ዮሐንስ) ሕልምና ትልም ገሐድ ማድረግ ነው፡፡” (2003፤ ባሕሩ ዘውዴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገጽ 66)
የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ የፈጠሯት ምኒልክ ናቸው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ በመልክም በግብርም ከዚህችኛዋ ጋር አትመሳሰልም፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ለዕውቀት ጉጉ የነበሩ ከመሆናቸው የተነሳ ከአውሮጳውያን ጋ በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ፍላጎትና ብቃት ነበራቸው፡፡ በወቅቱም አገራቸውን ከየትኛው የአፍሪቃ አገር የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ችለውም ነበር፡፡
ፍትሐዊ አስተዳደር
“…ምኒልክ በጥበብ ሕዝቡን ሲያስተዳድር፤ ሕዝቡ በፍቅር እንዲከተለው እንጂ በፍርሐት እንዲገዛለት አይፈልግም… በዚህም ምክንያት በአስተዳደሩ በኩል የወጣለት ጥሩ መሪ ነው፡፡…” ግሊከን፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ፤ አጤ ምኒልክ፤ ገጽ 378)
“…በምኒልክና በሕዝቡ መካከል ርቀት የለም፡፡…” ሮድ፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ፤ አጤ ምኒልክ፤ ገጽ 387)
አጤ ምኒልክ የአፄ ቴዎድሮስን ምናባዊት ኢትዮጵያ አንድነት ለማረጋገጥ፣ በየአቅጣቸው ራሳቸውን በማንገስ ዘመነ መሳፍነትን ለማስቀጠል ይፍጨረጨሩ የነበሩ የጎሳ እና የአካባቢ ገዢዎችን ለማስገበር ዘምተዋል፡፡ ማስገበር ማለት በዘመናዊ አነጋገር ‘ታክስ መሰብሰብ’ ማለት ነው፡፡ ገዢዎቹ ከምኒልክጋ መስማማት እስከፈለጉ ድረስ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአካባቢውን ግብር እየሰበሰቡ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይችሉ ነበር፡፡
ለማዕከላዊው የምኒልክ መንግስትም ዓመታዊ ግብር ያስገቡ ነበር፡፡ ይሄ ዓይነቱ አስተዳደር በባሕሪው ‘ፌዴራሊዝምን’ ይመስላል፡፡ ምኒልክ አቅም ኖሯቸው ያንን ግዛት ባያስፋፉ እና እንዲት ኢትዮጵያን ባይፈጥሩ ኖሮ ወይ የሌላ አካባቢ ገዢዎች የርሳቸውን ሥራ ይሰሩላቸው ነበር፤ አሊያም ዛሬ አንዲት ኢትዮጵያ የምንላት ፈፅሞ አትኖርም ነበር፡፡
በዚህ ሰለጠንን፣ ረቀቅን፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብት አረጋገጥን በምንልባት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የጎሣ ፌዴራሊዝም እንኳን ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ ጥገኝነት አልተላቀቁም፣ ወይም ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን አልቻሉም በሚባልበት ጊዜ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ግን “ማዕከላዊው መንግስት ተጽዕኖና ቁጥጥር ከማድረግ ይቆጠብ ነበር፡፡ ለምሳሌ ምኒልክ የእስልምና ተከታይ በሆነው አባ ጅፋር ግዛት ቤተክርስቲያን ላለመትከል ቃል እስከመግባት ደርሶ ነበር፡፡” (2003፤ ባሕሩ ዘውዴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገጽ 94)
አፄ ምኒልክ ከአፄ ቴዎድሮስ በተለየ በጎሳ እና አካባቢ ንጉሦች ላይ፣ ከአፄ ዮሐንስ 4ተኛ በተለየ ደግሞ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠባቸው የአስተዳደራቸውን ሚዛናዊነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ማስረጃ ነው፡፡ ምኒልክ ከሁለቱ ቀደምቶቻቸው የተማሩት ለሃገሪቱ የሚበጀውን ብቻ ነበር፡፡
ዳግማዊ ምኒልክና የኦሮሚያ ተወላጆች
ጎንደር የተወለዱት፣ ኦሮሞዋ ጀግና ጣይቱ ብጡል ባለቤት እና የኦሮሞ ተወላጇ እጅጋየሁ ለማ አዲያም ልጅ የሆኑት ዳግማዊ ምኒልክ በእናትነትና በሚስትነት ለሚተሳሰሯቸው የኦሮሚያ ተወላጆች ጠላት እንደሆኑ አድርገው የሚጽፏቸው ሰዎች አሉ፡፡ እውን ምኒልክ እንደዚያ ዓይነት ሰው ነበሩ?
የኦሮሚያ ተወላጅ የሆኑትና የሚኒልክ የቅርብ ወዳጅ የነበሩት ራስ ጎበና፤ ምኒልክ ከመቅደላ እስር አምልጠው ሲመጡ ጀምሮ በሸዋ ያላቸውን ግዛት እንዲያጠናክሩ የረዷቸው ሰው ናቸው፡፡ ራስ ጎበና በዚህ አልተወሰኑም፡፡ ምኒልክ ጎጃምን ለማስገበር በንጉሥ ተክለሃይማኖት ላይ ሲዘምቱ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ግዛታቸውን ወደደቡብ ማስፋፋት በቀጠሉ ጊዜም ራስ ጎበናም (በደጃዝማችነታቸው ዘመን) የሚኒልክን የደቡብ እና የምስራቅ ሰራዊት መርተዋል፡፡
“ዳግማዊ ምኒልክና ራስ ጎበና፣ የብሔራዊ ድንበር እና ሉዐላዊነትን ፅንሰ ሐሳብ በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ስር ያስተዋወቁ ሁለት ታሪክ የሚጠቅሳቸው ሰዎች ናቸው” በማለት አፄ ምኒልክ በማሕበራዊውም ሆነ በፖለቲካ ሕይወታቸው ውስጥ ከኦሮሞዎች ተነጥለው የማያውቁ መሆኑን ቢያረጋግጡም፤ ነገር ግን ጥቂቶች የንጉሡን ከኦሮሞዎችጋ በእናትና ሚስት መተሳሰር የሚተቹበት ቢያጡ፣ ራስ ጎበናን የኦሮሞን ሕዝብ የከዱ ሲሉ ያወግዟቸዋል፡፡
ዘረኝነት በያይነቱ
ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን ለጋብቻ ከመረጡበት መስፈርት በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በእናታቸው ኦሮሞ በመሆናቸው አለመሆኑን ነው፡፡ ያኔ (የዘመን ጉዳይ ነውና) የንግሥና ዘር ግንድ እንጂ፣ የብሔር ዘር ግንድ እምብዛም ወሳኝ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ያ ሁሉ ተቀይሮ በኢትዮጵያችን ሰው ማንነቱ የሚዳኘው በብሔሩ ሆኗል፡፡ ምኒልክን የማጥላላቱ መያዣ መጨበጫ የሌለው ፈሊጥም የተወለደው ከዚህ ብሔር ተኮር ዘመነኝነትጋ ተያይዞ ነው፡፡
ልክ አሁን ኢሕአዴግን የሚደግፍ ሰው ሲመጣ÷ በአባቱ ወይ በእናቱ ትግራዋይ እንደሆነ መጠየቅ የሚቀናንን ያህል ምኒልክን የሚያጥላላ ሰው ሲገጥመንም በአባቱ ወይ በእናቱ ኦሮሞ ይሆን ወደማለቱ እየተዳረስን ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ኢሕአዴግን በተመለከተ እንደዚያ መጠርጠሩ ከሞላ ጎደል ምክንያታዊ እና አሳማኝ ቢሆንም፤ ምኒልክን ግን ከኦሮሚያ ጠላቶች ውስጥ መመደብ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነው፡፡ የእኛን ዘመን ድክመት ባለፈው ላይ ማላከክ – ዳግማዊ ምኒልክ ዘረኝነትን አያውቁትምና!
ነገሥታቶቻችን በሙሉ የቻሉትን ያህል ግዛት ሲያስፋፉ ኖረው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ አኑረዋል፡፡ ነገሥታቶቻችን ግዛት የማስፋፋት ሕልም ባይኖራቸው ኖሮ፣ ምናልባትም ዛሬ የምናገኘው አንዲት ኢትዮጵያን ሳይሆን ብዙ ብጥስጣሽ አገራትን ነበር፡፡ ዳግማዊ ሚኒልክም እንደሌሎቹ÷ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅም ሆነ በደቡብ ያደረጉት የማስፋፋት ዘመቻ (ጦርነት፤ ወይም የማስገበር ሙከራ እንጂ) የዘር/ጎሣ ማጥፋት አልነበረም፤ ታላቋን ኢትዮጵያ የመፍጠር ሕልም ነው፡፡
ከመደምደሜ በፊት ግን ጥያቄ አለኝ፤ ምኒልክ በፈጠሯት ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ÷ ‘አንተን ጠቅመውሃል፤ አንተን ደግሞ በድለውሃል’ እያሉ÷ ከመቶ ዓመት በኋላ ሕዝቡን በሁለት ጎራ ለመክፈል የሚፍጨረጨሩት ወገኖች የሚጠቀሙት ምንድን ነው? እውን ሚኒልክ አድርገውት የነበረ ቢሆንስ እርሳቸውን የሚዳኙት ሰዎች የሚሻሉት በምንድን ነው?
Filed in: Amharic