በፍቃዱ ኃይሉ
በኦሕዴድ/ኦዴፓ የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ሲቆጣጠር አስቀድሞ ይወስዳቸዋል ብዬ ጠብቄያቸው ከነበሩት እርምጃዎች መካከል ኦሮምኛን የፌዴራሉ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ማድረግ አንደኛው ነበር። የኦሮምኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ መሆን ላይ የጎላ ተቃውሞ የለም። በማኒፌስቶው ላይ ይህንን የሚቃወም የተደራጀ ኃይልም የለም። ይሁንና ባልታወቀ ምክንያት መንግሥት ይህንን እምብዛም ተቃውሞ የሌለበትን ጥያቄ መመለስ አልፈለገም ወይም አልቻለም።
ይህ በእንዲህ እያለ የትምህርት ሚኒስቴር አዲስ የትምህርት ፖሊሲ በማውጣት፣ በነባሩ የትምህርት ፖሊሲ በክልሎች ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጥ የነበረውን የአማርኛ ትምህርት ከአንደኛ ክፍል አስጀምራለሁ ማለቱ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶበት ነበር። የኋላ ኋላ የኦሮሚያ መንግሥት “በዚህ ውሳኔ አልተማከርኩም፤ በክልሌ አይፈፀምም” በማለቱ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “ያወጣሁት ፖሊሲ ሳይሆን ምክረ ሐሳብ ነው” የሚል ማስተባበያ ሰጥቷል፤ መሳቂያ መሳለቂያ አድርጎት ከርሟል። የቋንቋ ፖለቲካ ኢትዮጵያውያንን ለምን ያወዛግባል?
የቋንቋ ፖለቲካ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቋንቋ ፖለቲካ ነው። ፌዴራሊዝሙ በቋንቋ ላይ በተመሠረተ የብሔር አረዳድ የተዋቀረ ነው። በ1987 የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተቀረፀበት ወቅት ትልቁ የቋንቋ የነበረው አጀንዳ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ማግኘት፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የቀበሌ አገልግሎት ማግኘት እና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ዳኝነት ማግኘት ነበሩ። የፌዴራሉ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ላይ የጎላ ተቃውሞ ያልተነሳ ከመሆኑም ባሻገር፣ ተጨማሪ ቋንቋ ያስፈልጋል የሚለው አጀንዳ ሆኖ አላከራከረም።
ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ግን የኦሮምኛ ተናጋሪዎች ቋንቋችን የፌዴራሉ ሁለተኛ ቋንቋ መሆን አለበት የሚለውን ፖለቲካዊ ጥያቄ ግንባር ቀደም ጥያቄያቸው አድርገውታል። ይህ በእንዲህ እያለ በኦሮሚያ እና ሌሎችም ክልሎች ያሉ የአማርኛ ተናጋሪዎችም ቋንቋችን ሁለተኛ የክልሎቹ የሥራ ቋንቋ ይሁንልን የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው። ነገር ግን ምንም እንኳን ዜጎች ቋንቋን እንደመግባቢያ መሣሪያ ቢመለከቱትም ፖለቲከኞቹ እና መሪዎቹ ግን የተፅዕኖ ማሳያ አድርገው ይወስዱታል። ስለዚህ የኦሮሚያ ክልልም ይሁን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ጥያቄውን ከቁብ የቆጠሩት አይመስልም።
የፖለቲከኞች ቋንቋ
የኢፌዴሪ የምኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ውስጥ አብዛኛዎቹ ከአማርኛ ውጪ የሚናገሩት የአገር ውስጥ ቋንቋ አለ።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚዘውሩት ቢያንስ ሁለት የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሆነዋል። የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ እና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማርም መሥራትም ዕድል የተሰጣቸው መሆኑ ሁለቱንም ቋንቋዎች ለማቀላጠፍ ረድቷቸዋል። በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ግን ከአማርኛ ውጪ በሌላ የአገር ውስጥ ቋንቋ ትምህርት አለመሰጠቱ ከዚህ ዕድል አርቆናል ብለው የሚከራከሩ አሉ። ስለሆነም የኦሮምኛ ቋንቋ የፌዴራሉ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ መሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ሁለት የአገር ውስጥ ቋንቋ የመናገር ዕድል ይፈጥርላቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም።
የፊደል ፖለቲካ
የኦሮሞ ብሔርተኝነት የተቃኘው በቅኝ አገዛዝ ትርክት ነው። ምንም እንኳን ኦነሲሞስ ነሲብ መጽሐፍ ቅዱስን በግዕዝ ፊደላት “መጫፈ ቁልቁሉ” በሚል ከ100 ዓመታት አስቀድመው የተረጎሙት እና ከዚያ በኋላም በግዕዝ ፊደላት፣ በኦሮምኛ ቋንቋ የተለያዩ መጽሐፍት የተጻፉ ቢሆንም፥ ፖለቲከኞቹ የላቲን ፊደልን መጠቀም መርጠዋል። ለዚህ የተለያዩ ቴክኒካዊ ማስረጃዎችን የሚጠቅሱ ቢሆንም ይህንን ምርጫቸውን የኦሮሞን ታሪክ ከኢትዮጵያ ታሪክ ለመነጠል የተደረገ ጥረት አድርገው የሚቆጥሩባቸው በርካቶች ናቸው። እናም ይህንን ጥርጣሬ መሠረት አድርገው ኦሮምኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ መሆን ካለበት የግዕዝ ፊደልን መጠቀም አለበት የሚል መደራደሪያ የሚያነሱ አሉ። እነዚህ ነገሮች በቋንቋ መጠቀምን ከፍትሕ አንፃር ሳይሆን፥ ከፖለቲካዊ ግብ አንፃር ስለሚመለከቷቸው እስጣገባዎቹ በቀላሉ መልስ የሚያገኙ አይመስሉም።
ወላጆች እና ልጆች
ኦሮምኛ ቋንቋን በቁቤ (በላቲን ፊደሎች) ማስተማር የተጀመረው በኢሕአዴግ ዘመን ነው። በዚህም ምክንያት ምንም እንኳን አነባበቡን መማር ቀላል ቢሆንም፣ ኦሮምኛ መናገር ግን በቁቤ ማንበብ የማይችሉ (ግን የተማሩ ሰዎች) አሉ። ይህ የተወሰነ የትውልድ ክፍተት እንደፈጠረ የሚናገሩ አሉ። የአዲሱን ትውልድ አባላት “የቁቤ ትውልድ” እያሉ የሚጠሯቸው ለዚህ ነው። የቁቤ ትውልድ አባላት አባቶቻቸው ያልጠየቁትን ኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን የሚል ጥያቄ አንስተዋል። የቁቤ ትውልድ አባላት የአማርኛ ቋንቋ እውቀታቸው አጠያያቂ እንደሆነ ይነገራል። ለዚህ አንዳንዶች የአማርኛ ትምህርት በአግባቡ እንዳይሰጥ መደረጉን ይወቅሳሉ። ሆኖም ተማሪዎቹ በተመሳሳይ እንደ አንድ ትምህርት የሚሰጠው እንግሊዝኛ ቋንቋም ላይ እምብዛም ናቸው። ስለዚህ ችግሩ የትምህርት ጥራቱ ሊሆን ይችላል የሚል መከራከሪያም አለ።
ወላጆች የልጆቻቸውን ቋንቋ የመወሰን ሙሉ ሥልጣን አላቸው። ወደ ትምህርት ቤት ሲልኳቸውም እንዲሁ መርጠው ነው። አሁን አሁን ግን ክልሎች ትምህርት ቤቶች ትምህርት የሚሰጡበትን ቋንቋ በግድ እየወሰኑላቸው ነው። ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ኑሮ የተመቻቸላቸው ስለሆኑ ልጆቻቸውን በዓለም ዐቀፍ ቋንቋዎች ትምህርት የሚሰጥበት ቦታ ይልካሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ማድረግ የማይችሉትን ቤተሰቦች ልጆች አማራጮች ለመገደብ ሲታገሉም ይታያሉ። በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የቋንቋ ፖሊሲ ማውጣት አዳጋች እንዲሆን የሚያደርጉት እንደዚህ ዓይነቶቹ ንቅናቄዎች ናቸው።
“አይደፈሬው” ሕገ መንግሥት
በኢሕአዴግ ስንጥቃት ሳቢያ ሕገ መንግሥቱ አደጋ ላይ ወድቋል በሚል ሕወሓት የተለያዩ አጋሮችን እያሰባሰበ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሚደፍሩ አይመስሉም። ነገር ግን ኦሮምኛን የፌዴራሉ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው ሕገ መንግሥቱ ከተከለሰ በኋላ ነው። ይህንን ብዙኀንን የሚያስማማ የቋንቋ ጉዳይ ለማሻሻል ሕገ መንግሥቱን መድፈር ቢቻል፥ ሕገ መንግሥት ለሕዝቦች ጥቅም ሲባል በፈቃዳቸው ሊሻሻል የሚችል ነገር እንደሆነ ለማስተማሪያም ጥሩ አጋጣሚ ይሆን ነበር። በተጨማሪም፣ ከፖለቲካ ጥያቄዎች ባለፈ ማኅበራዊ ችግሮችንም መፍታት በተቻለ ነበር።