>

የአዲስ አበባ አ.ዴ.ፓ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ!!!

የአዲስ አበባ አ.ዴ.ፓ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ!!!
በአዲስአበባ_ከተማ መገናኛ ብዙሀን የግለሰብ ተክለስብዕና እየገነቡ ስለመሆኑ፣
* የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሕዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ አለመሆኑን፣
* ተቋማዊ አስራር ሳይፈርስ በግለሰብ ፍላጎት ይሁንታና አድራጊ ፈጣሪነት የአመራር ምደባና ሽግሽግ እየተከናወነ ስለመሆኑ፣
*  የመሬት ህገወጥ ወረራ እየተፈፀመ ስለመሆኑ…
***
    እኛ በየደረጃው የምንገኝ የአዲስ አበባ አዴፓ አመራሮች ከነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በ2011ዓ.ም መደበኛ የድርጅትና የፖለቲካ ስራዎች አፈፃፀም እንዲሁም በከተማዋ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንቅስቅሴ ዙሪያ የከተማችንን ህዝብና ወጣት መሰረታዊ ፍላጎቶች ለመመለስ፣ ባከናወናቸው ተግባራት የነበሩንን ጠንካሬና ጉድለቶች በዝርዝር ገምግመናል፡፡ በከተማችን አዲስ አበባ የተቀጀመረውውን ለውጥ ጉዞ በትክከለኛ መንገድ እንዲቀጥልና የከተማዋን ህዝብ ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይር ተጠቃሚነት ከማሰፈን አንፃር በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ ያሳመዘግበናቸው  በርካታ ስኬቶች ነበሩ፡፡ በሌላ መልኩ በየደረጃው ያለ አመራር በቁርጠኝነትና በተነሻስነት ያከናወንበት አመት ቢሆንም እንኳን በውስጥም በውጪም ተግዳሮቶችን ያስተናገድንበት ክስተትም ተፈጥሯል፣ የድርጅታችንን ታላላቅ መሪዎች ያጣንበት በክልሉ ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ የአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው መፈናቀል ሌላኛው ችግር ነበር፡፡ ይሁንና ያጋጠሙን ፈተናዎች ለቀጣይ ለትግል የሚያነሳሱን እንጂ ከትግል እንድናፈገፍግ የሚያደርጉን አይደሉም፡፡ በዚህ መሰረት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በመግባባት ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው አውጥተናል፡፡
1. በሳለፍነው አንድ ዓመት በከተማችን ውስጥ ባከናወናቸው የፖለቲካና የድርጅት ስራዎች ያስመዘገብናቸው ስኬቶች የጀመርነውን ሀገራዊና ከተማዊ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የራሱን መሰረት ያስቀመጠ መሆኑን ገምግመናል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡ ቀጣይና ተቋማዊ ሆኖ እንዳይቀጥል በተለያዩ ሀይሎች እየገጠመው ያለውን ተግዳሮትና የማጠልሸት ተግባር የከተማችንን ህዝቦች ሁለንተናዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚጎዳ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምርረን የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
2. በከተማችን ሲከናወኑ የቆዩ የልማትና መልካም አስተዳር ተግባራት ዙሪያ አመራራችንና መዋቅሩ የራሱን የማይተካ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በቀጣይነት መላው የከተማችን ህዝብ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ህገ ወጥ ተግባራት እንዲወገዱ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ የከተማችን ሰላምና የነዋሪዎቿ አንድነት እንዲጠበቅ ከመቼውም በላይ ተግተን የምንሰራ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
3. የመገናኛ ብዙሀን የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱን ለከተማዋ ዕድገት ብልፅግናና ለብዝሃነት ያለውን ፋይዳ የከተማዋን ህዝብ ድምፅና ስሜት ከማስተጋባት ይልቅ የግለሰብን ተክለ ስብዕና በመገንባት ላይ ያተኮረ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ እንዲሆን እየተደረገ ያለው አሰራር ለማንም የማይበጅ እንዲሁም ህዝበኝነትን የሚያነግስ የከተማዋን የዘላቂ ልማትና የሰላም አጀንዳ ሁሉንም አካታች እንዳይሆን የሚያደርግ አካሔድ በመሆኑ እንዲታረም እንታገላለን፡፡
4. በከተማችን አዲስ አበባ የኑሮ ውድነት የህዝቡን ህልውና እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል ሁሉን አቀፍ እንቅስቀሴ መደረግ እንዳለበት እናምናለን፡፡ ከዚህ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ችግር አንዱ ሲሆን ይህንን ለምፍታት የተዘረጋው የቤቶች ልማት ፕሮግራም በሚፈለገው ፍጥነት የህዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ባለመሆኑ የነባር ግንባታዎችም ሆነ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲጠናቀቁና የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እንታገላለን፡፡
5. በከተማችን አዲስ አበባ የህዝባችንን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በድርጅት አስራርና አደረጃጀት መመሪያ መሰረት ተቋማዊ አስራን በተከተለ ሁኔታ የአመራር ምደባና ስምት እንዲሁም ሽግሽግ የሚተገበር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ተቋማዊ አስራር ሳይፈርስ በግለሰብ ፍላጎት ይሁንታና አድራጊ ፈጣሪነት የአመራር ምደባና ሽግሽግ እየተከናወነ በተለይም አምባገነናዊ ስርዓት እንዲሰፍን እየተሰራ ያለበት ሂደት በመኖሩ ይህ ድርጊት ታርሞ በቀጣይ የሰው ሀይል ምደባና ስምሪት የፈረሰው ተቋማዊ አሰራር ተስተካከሎ በየደረጃው ተግባራዊ እንደደረግ እንታገላለን፡፡
6. የአማራ ህዝብ ካሁን ቀደም በበሬ ወለደ የሀሰት ትርክት ግፍና በደል ሲደርስበት ቆይቷል፡፡ ይህንን ከታሪክና ከዕውነት የተቃረነ የሀሰት ትርክት ከህዝባችን ጋር ታግለን የጣልነው ቢሆንም የለበሰውን አቧራ እያራገፈ የተለያዩ ተቀፅላዎችን በመለጠፍ ህዝባችንን ለማሸማቀቅ፣ አንገት ለማስደፋትና ማንነቱን እንዲጠላ ለማድረግ የሚጥሩ ሀይሎች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡና በዚህ ሰበብም ያለአግባብ የታሰሩ አካላትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንታገላለን፡፡
7. በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ባሉ አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች ለአገልግሎት የሚመጡ ነዋሪዎቻችን የድርጅቱ አባል ፓርቲዎች የሚወክሏቸው ህዝቦች ብቻ ባለመሆኑ ለህብረ ብሔራቷ ከተማ ያለማንም ያልተገባ ድጋፍ እና እርዳታ በዕውቀቱ በአቅሙ ተወዳድሮ ቦታውን የሚዝ የሰው ሀይል እንዲኖርና፣ የሲቪል ሰርቪስ ምደባ መመሪያው ከሚፈቅደው ውጪ የተለየ ምደባ እንዳይሰራና  በቀጣይም በተቀመጠው ህጋዊ አሰራር መሰረት ብቻና ብቻ ተፈፃሚ እየሆነ እንዲሔድ እንታገላለን፡፡
8.  በከተማችን አዲስ አበባ ውስን የሆነው የመሬት ሀብታችን ህጋዊ ባለሆነ አግባብ እየተወረረና ህገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ይህ ተግባር የህዝብንም ሆነ የመንግስት ጥቅም የሚያሳጣና ኢ-ፍትሐዊነትን የሚያነግስ አካሔድ በመሆኑ እንዲታረም በፅኑ የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
9. በከተማችን አዲስ አበባ የሚኖረው የአመራርና የሰው ሀይል ምደባና ስምሪት የህዝብን ቀመር ማዕከል ያደረገ እንዲሁም የከተማዋን ህዝቦች የሚመስል ስርዓት በመዘርጋት አዲስ አበባችን የነዋሪዎቿና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኗን በተግባር እንዲረጋገጥ ተቋማዊ ትግል እናደርጋለን፡፡
10. ትላንት የገጠሙንን ውስብስብና ፈታኝ ሴራዎችና አደጋዎች በጋራ ትግላችን በፅናት እያለፍን እንደመጣነው ሁሉ ወደፊትም የሚገጥሙንን ማናቸውንም ፈተናዎች መላ ህዝባችንን ከጎናችን አሰልፈን በፅናት የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
11. እኛ በአዲስ አበባ ከተማ የምንገኝ የአዴፓ አመራሮች በከተማዋ የሚኖሩ አማራዎችን በማሰባሰብ፣ በማደራጀት ለመላው ህዝብ ተጠቃሚነት ከምንግዜውም በላይ የምንተጋ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ታሪክ፣ ወግ፣ ልማድና ትውፊት ለትውልድ ለማስተላፍ የአባቶቻችን ገድል በመዘከር ትክክለኛ ታሪክንና ትውፊትን በማስረፅ ተሸጋሪ የታሪክ ክታብ በመተየብ በየ ተግባራቱ ሁሉ እያካተቱ በማስተዋወቅ የአማራ ባህል ከሌሎች ህዝቦች ጋር እንደ ትላንቱ የሚያስተሳስረንና የሚያጋምደን ኢትዮጵያዊ ኩራት ሆኖ እንዲቀጥል እናደርጋለን፡፡
የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ አዴፓ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም በፅናት ይታገላል!!!!
ነሐሴ 26/ 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic