>

"የኦሮምያ ቤተ ክህነት"፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ!!! (ዳንኤል ክብረት)

“የኦሮምያ ቤተ ክህነት”፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ!!!
ዳንኤል ክብረት
ከሰሞኑ የኦሮምያን ቤተ ክህነት የመቋቋም ነገር ገፋ ብሎ እየመጣ ነው፡፡ ነገሩን ያነሡት አባቶችና ምእመናን መነሻቸው ቅንዐተ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በኦሮምያ አካባቢ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተዳከመ መምጣቱ አሳስቧቸው፣ ‹እኛ ልጆቿ እያለንማ እንዲህ አይደረግም› ብለው የተነሡ ቆራጥ ምእመናንና አባቶች ናቸው፡፡ ያነሷቸው ችግሮችም በአካባቢው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ መፍትሔም የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአንድ በኩል የምእመናኑ ተገቢ ጥያቄ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተገቢውን ጥያቄ ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልግ ኃይል አለ፡፡ለዚህ ማሳያዎቹ የሚሰጡ መግለጫዎች ናቸው፡፡
ከሰሞኑ የሚሰጡት መግለጫዎች ሦስት መሠረታዊ ስሕተቶች ይታዩባቸዋል፡፡
1. የመጀመሪያው በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጡትን ፈተናዎች ሁሉ ሰብስበው ለአንድ አካባቢ መስጠታቸው፤
2. ከዚህ በፊት ለነበሩ ጥረቶች ምንም ዕውቅና ባለመስጠት ችግሩን ይሁነኝ ተብሎ የተተወ ማስመሰላቸው፤
3. ሦስተኛም ለችግሩ የሰጡት መፍትሔ ችግሩን የማይፈታ መሆኑ ነው፡፡
በኦሮምያ አካባቢ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተዳክሟል፣ የካህናት እጥረት አለ፤ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚቀድስና የሚያስተምር አገልጋይ በበቂ ሁኔታ አይገኝም፤ የአስተዳደር ችግር አለ በሚል የሚነሣው ቅሬታ ትክክለኛ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር በኦሮምያ አካባቢ ብቻ የሚስተዋል አይደለም፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሠተ ችግር ነው፡፡ የሚለያየው የችግሩ መጠን ብቻ ነው፡፡ በአማራውና በትግራይ ክልልም በገጠሩ የአገልጋዮች እጥረት አለ፡፡ በተለይም ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ የሚያገለግል ካህን እጥረት አለ፡፡ ያ ባሆን ኖሮ የተሻለ አገልጋይ አለ ከሚባልበት አካባቢ ወደነዚህ ቦታዎች ሰባክያን እየተጋበዙ መሄድ ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ እንዲያውም በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን ስለሚስቡ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በድንኳን ሰፊ አገልጋዮች ነው የሚገለገሉት (የራሳቸውን መሬት እያረሱ በሚያገለግሉ)፡፡ በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋ የሚቀደስባቸው የትግራይና የአማራ ክልል አጥቢያዎች ከ25 በመቶ አይበልጡም፡፡ ቅዳሴያቸው ቋንቋ ግእዝ ነው፡፡ የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ችግርም በእነዚህ አካባቢዎች ቢብስ እንጂ የሚሻል አይደለም፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የሚያታብቡትን የቅሬታ ፋይሎች መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡
በኦሮምያና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ አንዳንድ ወገኖች በሰሜን ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በቋንቋቸው የሚገለገሉ ይመስላቸዋል፡፡ ምእመኑ በእምነት ተቀብሎት ስለሚኖር እንጂ አብዛኛው አገልግሎት የሚሰጠው በግእዝ ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ በኦሮምያም፣ በደቡብም፣ በአፋርም፣ በጋምቤላም፣ በሶማሌም እንደሚደረገው ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጉዳይ ነው ይብዛም ይነስም በሁሉም አካባቢ ያለውን ችግር ለአንድ አካባቢ ብቻ አንስጠው የምንለው፡፡ ችግሩ የጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን ፈተና በመሆኑ በጋራ ሆነን የጋራ ፈተናችንን እንለፈው፡፡
አብዛኞቹ ለአገልግሎት የሚውሉት ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ አማርኛ ከተተረጎሙ ከ50 ዓመታት በላይ አይሆናቸውም፡፡ ብዙዎቹም ታትመው የተሠራጩት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ነው፡፡ በዚሁ በኛው ትውልድ ዘመን፡፡ ራቅ ያለውን የአማርኛ የትርጉም ሥራ ብንቆጥር እንኳን ከመቶ ዓመት አይዘልም፡፡ በራስ ተፈሪ ዘመን የተጀመረውን ከያዝን፡፡ እነዚያ መጻሕፍት በስፋት ታትመው፣ ለሕዝቡ ተዳርሰው፣ ካህኑና ሕዝቡ ለምዷቸው ለአገልግሎት እስኪውሉ ዘመናትን ፈጅተዋል፡፡ አማርኛም የተመረጠው በወቅቱ በነበረው ሀገራዊ መግባቢያነቱ እንጂ እንደዛሬው የአንድ ወገን ቋንቋ ተደርጎ አልነበረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን የጸሎት ቋንቋዋ ዛሬ የማንም ብሔር ያልሆነው ግእዝ ነው፡፡ ሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ ለእርሷ እኩል ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያን በአማርኛ ማስተማርና ማገልገል የጀመረችው በቅርቡ ነው፡፡ በሌሎች ቋንቋዎች በሚገባ ያልሄደችው ስለማትፈልግ አልነበረም፡፡ ፈተናው አላሠራ ብሏት እንጂ፡፡ ለዚህ ደግም ትልቁ ፈተና ቤተ ክርስቲያኒቱ ፋታ አለማግኘቷ ነው፡፡ ከግራኝ ጦርነት በኋላ ዘመነ መሳፍንት መጣ፣ ከዚያም የደርቡሽና የእንግሊዝ ጦርነት ተከሠተ፣ ከዐፄ ምኒልክ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በተገኘው አንጻራዊ ሰላም ነው ከግእዝ ወደ አማርኛ ለመሻገር የተሞከረው፡፡ ያ ዘመን ቢቀጥል ኖሮ ወደ ሌሎች ቋንቋዎችም ቀድሞ ለመሻገር ይቻል ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ መጀመሪያ የጣልያን ወረራ ተከሠተ፣ ቀጥሎም አብዮት ፈነዳ፡፡ ይሄው እስከዛሬ ቤተ ክህነቱ እንዳነከሰ ነው፡፡
ይሄንን የማነሣው ራሱ አማርኛም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሲውል ልጅ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ያንን ያህል ቀድሞ የሄደ፣ተጉዞ የነጎደ አይደለም፡፡ እንዲያውም ከግእዝ ወደ አማርኛ ከተደረገው ሽግግር ይልቅ ወደ ኦሮምኛ የተደረገው ሽግግር አጭር ጊዜ ብቻ ፈጅቷል፡፡ በአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ለማግኘት አንድ ምእተ ዓመት ሲፈጅ፣ በኦሮምኛ ከ50 በላይ መጻሕፍትን ለማግኘት ከ25 ዓመት በላይ አልፈጀም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ዋናዎቹ የጸሎት መጻሕፍት አንዱ ግብረ ሕማማት ወደ አማርኛ የተተረጎመው በ199ዎቹ መጨረሻ ነው፤ ስንክሳር ወደ አማርኛ የተተረጎመው በ1990ዎቹ መጀመሪያ ነው፡፡ እውነታው እንደሚባለው አይደለም፡፡
እንዴት እንደሆነ ቀጥሎ እናያለን፡፡
ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች አገልግሎቷን መስጠት እንዳለባት የሚነግሯት ቅዱሳት መጻሕፍቷ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ሃምሳ ስትመሠረት የተሰጣት አንዱ ጸጋ የቋንቋዎች ጸጋ ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ፍሬምናጦስን ለኢትዮጵያ ጳጳስ ሲያደርገው ምክንያቱ ‹የሕዝቡን ቋንቋ፣ ባሕልና ታሪክ ታውቃለህ› የሚል ነው፡፡ ከእርሱ በኋላ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳንም መጀመሪያ በአኩስም በቤተ ቀጢን ተቀምጠው የሕዝቡን ባሕልና ቋንቋ ነው ያጠኑት፡፡ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመላ ኢትዮጵያ ሲያስተምሩ የጎበኟቸው ሕዝቦች አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ እንዳልነበሩ ገድሎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ሁሉንም በየቋንቋቸው ነው ያስተማሯቸው፡፡
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማስተማራቸውን ገድሎቻቸው ምስክሮች ናቸው፡፡ በአምሐራ፣ በትግራይ፣ በዳሞት፣ በጋፋት፣ በአርጎባ፣ በጉራጌ፣በሲዳማ፣ በጋሞ፣ በሐድያ፣በኦሮሞ፣ በሶማሌ፣ በጉምዝ፣ በወላይታ፣ ወዘተ. አካባቢዎች አስተምረዋል፡፡ አማርኛ ወይም ግእዝ በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉ የሚነገር አልነበረም፡፡ ታድያ በየሀገሩ ቋንቋ ካልሆነ በምን ያስተምራሉ?
እኔ ባለኝ መረጃ በኦሮምኛ ቋንቋ በማስተማር ቀደምቶቹ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግልና አቡነ አኖሬዎስ ናቸው፡፡ በአቡነ ቀውስጦስ ገድል ውስጥ አቡነ ቀውስጦስ ያስተማሯቸው የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች ተጠቅሰዋል፤ ያስተማሩባቸው ቦታዎች ሲጠቀስ አንዳንዶቹ የኦሮምኛ ስም ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ሕዝቦች ያስተማሯቸው በቋንቋቸው ነው፡፡
ገድለ አቡነ ቀውስጦስ በአንድ ቦታ ላይ ‹ዘሀለወት ደብር ወበል ስማ ሰገሌ – ሰገሌ የምትባል ደብር ነበረች› ይላል፡፡ በሌላም ቦታ ‹ደብረ ሰገሌ› ይላታል (Gli Atta di Qawsetos, 240) ሰገሌ ኦሮምኛ ነው፡፡ ‹ድምጽ› ማለት ነው፡፡ ‹ግበር ሎቱ(ለገላውዴዎስ) መልዕልተ የይ፤ ወለቴዎድሮስ ላዕለ ደብረ መንዲዳ – ለገላውዴዎስ በየይ ተራራ ላይ (ቤተ መቅደስ) ሥራ፤ ለቴዎድሮስ ደግሞ በመንዲዳ ተራራ ላይ› ይላል(ገጽ 119፤139)፤ መንዲዳ ኦሮምኛ ነው፡፡ ‹የዱር ቤት› እንደማለት ነው፡፡ ዛሬ ከደብረ ብርሃን ከተማ ወደ ጅሩ በሚወስደው መንገድ መንዲዳ የምትባል ከተማ አለች፡፡ ‹ወለፊቅጦርኒ በሀገረ ለሚ ዘትሰመይ ደብረ ዲባናው – ፊቅጦርንም ደብረ ዲባናው በምትባል በለሚ ሀገር› ‹ለሚ›፣ በኦሮምኛ ‹ዜጋ› ማለት ነው፡፡ ‹ወይብሉ ርእዩ ሰብአ ገላን ወየይ – የገላንና የየይ ሰዎችን ተመልከቱ አሉ›(ገጽ 121)፤ ገላን የኦሮሞ ጎሳ ስም ነው፡፡ ‹ወአጥመቆሙ በህየ ሰብአ የይ፣ ወመሐግል ወገላን፣ ወሰብአ ጋሞ ወወላሶ ወቀጨማ – የየይን፣ የመሐግልንና የገላንን፣ የጋሞን፣ የወላሶ(ወሊሶ)ና የቀጨማን ሰዎች አጠመቃቸው›(ገጽ 137)፡፡ ወላሶ(ወሊሶ) ዛሬ በስሙ ከተማ የተሠራለት የኦሮሞ ማኅበረሰብ ስም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሸዋ ከወግዳ አጠገብ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ አቡነ ቀውስጦስ አስተምረዋል፡፡ በግራኝ ጊዜ ነው ብዙ ነገር የጠፋው፡፡ አቡነ አኖሬዎስም በባሌ አካባቢ ሲያስተምሩ ኦሮምኛን ይጠቀሙ እንደነበር መዛግብቱ ይነግሩናል፡፡ የተዳከመው ደግሞ በሁሉም አካባቢ ነው፡፡
በኋላ ዘመን ይህንን የቤተ ክርስቲያን ቀደምት አገልግሎት እንደገና ለመመለስ ቢያንስ ስድስት ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
1. ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በገዛ ገንዘባቸው አገልጋይ መድበው ወንጌል በቋንቋቸው እንዲሰጥ ካደረጉባቸው አካባቢዎች መካከል የዛሬው የኦሮምያ ክልል አንዱ ነው፡፡
2. ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ገዳምና ማሠልጠኛን ተክለው ከሠሩት ሥራ አንዱ በኦሮምኛ የሚያስተምሩና የሚቀድሱ ካህናትና ሰባክያንን ማፍራት ነው፡፡ እንዲያውም ከሰሜን ኢትዮጵያ ከሚመጡት ይልቅ ከደቡቡ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡት የበለጠ ቦታ ይሰጡ ነበር፡፡ ከወላጆቻቸው የድኾችን ልጆች ተቀብለው በማሳደግም ‹ሕጽው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ› ያለውን የሚተካ ሥራ ለመሥራት ተግተዋል፡፡ በዚህም ሁለት ዓይነት ሐዋርያትን አፍርተዋል፡፡ ከልዩ ልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መጥተው ኦሮምኛን በሚገባ የሚናገሩ እና ከኦሮምያ አካባቢዎች መጥተው ቋንቋውንና ግእዝን በሚገባ የሚያውቁ ፡፡ (እነ ኤፍሬም እሸቴ፣ ግርማ ወልደ ሩፋኤል፣ እሸቱ ታደሰ፣ ሙሉጌታ ስዩም፣ በላቸው ወርቁ፣ ንዋይ ገሠሠ፣ ታደሰ ዱገ፣ አሸናፊ ዱጋ፣ ቀነኒ፣ ወዘተ) የዚያን ዘመን ሐዋርያት ነበሩ፡፡
3. የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ጅምር ለፍሬ ያበቃው ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከምሥረታው ጀምሮ ነው ለልዩ ልዩ ቋንቋዎች አገልግሎት ትኩረት የሰጠው፡፡ ከሀገር ውሰጥ ለኦሮምኛና ትግርኛ፣ ከውጭ ለእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ትኩረት በመስጠት ላለፉት ሃያ ዓመታት ሠርቷል፡፡ በዚህም፡-
ሀ. በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን በመርዳት
ለ. አገልጋይ ለሌለባቸው በገንዘብ በመመደብ
ሐ. በኦሮምኛ ቋንቋ ለሚያገለግሉ ካህናትና ሰባክያን ሥልጠና በማዘጋጀት
መ. በኦሮምኛ ቋንቋ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ (ከአምቦ እስከ አሶሳ በተደረገው እኔም ተካፍዬ ነበር)
ሠ. በኦሮምኛ ቋንቋ መጻሕፍትን በማዘጋጀት
ሸ. በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ አገልጋዮችን በዋናው ማዕከል ደረጃ መድቦ እጥረት ያለባቸውን አካባቢዎች እንዲረዱ በማድረግ
ቀ. በኦሮምኛ ቋንቋ የሚዲያ አገልግሎት በመስጠት
በ. በኦሮምኛ ቋንቋ መዝሙሮችን በማዘጋጀት፤- የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡
ተ. በምዕራብ ወለጋ ቂልጡ ካራ ያለውን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምና ማሠልጠኛ እንዲመሠረት በማድረግ ከምዕራብ ኦሮምያ የሚመጡ አገልጋዮቸ ተገቢውን ሥልጠና እንዲገኑ ለማድረግ ጥሯል፤
ቸ. በግቢ ጉባኤያት በኦሮምኛ ቋንቋ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በማስተማር፣
4. የጽርሐ ጽዮን መንፈሳዊ ማኅበር፤ ከመነሻው በደቡብ ኢትዮጵያ የሚከናወነውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማበርታት የተቋቋመው የጽርሐ ጽዮን መንፈሳዊ ማኅበር የአገልጋዮች ማሠልጠኛ በኦሮምያ ክልል የክህነት አገልግሎትና ስብከተ ወንጌል በኦሮምኛ ቋንቋ የተጫወተው ሚና ምትክ የለሽ ነው፡፡ ወደ ማሠልጠኛው ለመግባት አንዱ መመዘኛም ከአማርኛ ቋንቋ ውጭ ሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋ ለመናገር መቻል ነው፡፡ ከኦሮምያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተመርጠው የሠለጠኑና ዛሬም እያገለገሉ ያሉትን አገልጋዮች ብዛትና ማንነት ከማሠልጠኛው ፋይል መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንን ማሠልጠና በብረቱ ሲደግፉ ከነበሩት መካከል አንዱ ቀሲስ በላይ መኮነን ነበሩ፡፡
5. ደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ ማኅበር፡፡ በ1998 ዓም በጅማ አንዳንድ ቦታዎች የተከሠተውን ችግር መነሻ በማድረግና በአካባቢው ያለውን የአገልግሎት መዳከም ለማበርታት የተቋቋመው የደጆችሽ አይዘጉ ማኅበር በዋናነት የሚሠራው በኦሮምያ ክልል ጅማ አካባቢ ነው፡፡ በአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን በገንዘብና በቁሳቁስ በመደገፍ፣ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ካህናትንና ሰባክያንን ማሠልጠኛ ገንብቶ በማሠልጠን፤ ለአገልጋዮቹ ደመወዝ በመክፈል፣ በየጊዜው ወደ አካባቢው መንፈሳዊ ጉዞ በማዘጋጀት፣ በአካባቢው አገልግሎቱ እንዲበረታ ከ12 ዓመታት በላይ ደክሟል፡፡
6. ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ያደረጉት ጥረት እዚህ ላይ መነሳት አለበት፡፡ በኦሮምያ አካባቢዎች ሊያስተምሩ የሚችሉ ኦሮምኛ ተናጋሪ ካህናትን በመመደብ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ ጳጳሳትን በብዛት በመሾም፣ መጻሕፍት ወደ ኦሮምኛ እንዲተረጎሙ በማበረታታት ታላቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያዎቹ አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ሲሾሙ ከአምስቱ ቢያንስ አንዱ(አቡነ ጴጥሮስ) ኦሮሞ ነበሩ፡፡ ዛሬም ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ 1/3ኛው ጳጳሳት ኦሮምኛ የሚናገሩ ናቸው፡፡ በኦሮምያ ክልል ከተመደቡ ሊቃነ ጳጳሳት ከ5ቱ በቀር ሁሉም ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ከሀገረ ስብከቶቹ ሥራ አስኪያጆች 90% ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡
በአቡነ ጳውሎስ ዘመን የተጀመረው የትርጉም ሥራ ተበረታትቶ መጽሐፈ ቅዳሴና ተአምረ ማርያም በኦሮምኛ ተተርጉሟል፤ ቃለ ዐዋዲውም በኦሮምኛ ቋንቋ ሊታተም ተዘጋጅቷል፡፡ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ነው ቀሲስ በላይ መኮነን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት፡፡ በኋላም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ነበር፡፡ በዚህ ታላቅ ሹመት ሲቀመጡ ምን ሠሩበት? ብሎ ነው መጠየቅ፡፡
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የተደረጉት በአካባቢ ተወላጆች ብቻ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተለየ አካባቢ የለውምና፡፡ በአንድ አካባቢ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠናከር ማገዝ ርዳታ መስጠት አይደለም፡፡ግዴታን መወጣት ነው፡፡ በአንድ አካባቢ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መዳከም በሁሉም አካባቢ እንዳጋጠመ መዳከም ይቆጠራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት አካል ናትና፡፡ በአካል ውስጥ የአንድ ብልት መታመም የአካል ሁሉ መታመም ነው፡፡ ወደ ሕክምና የሚሄደውም መላው አካል ነው፡፡ ለድኅነቱም የሚረባረበው መላው አካል ነው፡፡
በኦሮምያ አካባቢ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠናከሩ፣ የክህነት አገልግሎት እንዲበረታ የታገሉት የኦሮምያ ክልል ተወላጆች ብቻ አይደሉም፡፡ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፤ ከኩርሙክ እስከ ቶጎ ጫሌ ያሉ ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ናቸው፡፡ ዛሬ የሚሰጡ መግለጫዎች እነዚህን ሁሉ ጥረቶች የሚያመለክቱ አይደሉም፡፡ ይሁነኝ ተብሎ በችግሩ ላይ ብቻ እንዲያጠነጥኑ የተደረጉ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ችግሮቹ ያሉ ቢሆኑም ተወዝፈው የተቀመጡ ግን አይደሉም፡፡ እነርሱን ለማስተካከልም አያሌ አባቶችና ምእመናን ተጋድለውባቸዋል፡፡ የችግሩን ያህል መፍትሔ አልተሰጠው ይሆናል፤ ችግሩን ተረድቶ መፍትሔ ለመስጠት ግን የሕይወት መሥዋዕትነት ሳይቀር ተከፍሎበታል፡፡ በኦሮምያ ክልል ሲያስተምሩ ኦነግ ናችሁ ተብለው የታሠሩ፣ በተቃራኒውም ሌላ ስም ተሰጥቷቸው መከራ የተቀበሉ ብዙ ናቸው፡፡
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ችግሩን ለምን በሚፈለገው መጠን ሳይቀርፉት ቀሩ? የሚለው ግን መነሣት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
1. እንዲህ ያለን ችግር ከሥሩ ነቅሎ ለመፍታት ዋናው ቤተ ክህነት ስትራቴጂ ነድፎ፣ ተቋም አደራጅቶ፣ የሰው ኃይሉን አሰባስቦ፣ ገንዘብ በሚገባ መድቦ መሥራት ነበረበት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አልፎ አልፎ እንደ አቡነ ቄርሎስ ያሉ አባቶች ሲነሡ ለስብከተ ወንጌልና ለሐዋርያዊ አገልግሎት ትኩረት ይሰጣሉ እንጂ፣ መላው ቤተ ክህነቱ አንድ ሆኖ አልተነሣም፡፡ ከዮዲት ዘመን በኋላ የተፈጠረውን መንፈሳዊ ችግር ለመፍታት መላው አባቶች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አንደ ሆነው ነበር የተነሡት፡፡ ለዚህም ነበር ያ ዘመን ወርቃማው የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘመን የተባለው፡፡ የቤተ ክህነቱ አጠቃላይ ድክመት ያስከተለው ሀገራዊ ድክመት ነው፡፡ ድካሙም እንደ ሌሎች ችግሮች ሁሉ ተጽዕኖው በሁሉም ላይ እንጂ በኦሮምያ ላይ ብቻ አይደለም፡፡
2. ችግሩን የሚያባብሱ ምክንያቶችም መብዛት፡፡ ከተለያ አቅጣጫ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች (በተለይ ደግሞ በኦሮምኛ) ቋንቋ ስብከተ ወንጌል እንዲጠናከርና የክህነት አገልግሎቱ እንዲበረታ የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ጥረቶቹን ከማገዝ ይልቅ አንዴ ፖለቲካዊ፣ ሌላ ጊዜ የብሔር ስም እየሰጡ የሚያዳክሙ አካላት ነበሩ፡፡ የአገልጋዮቹንና የምእመናኑን መብት በፖለቲካዊ ሥልጣናቸው ተገን ሲጫኑ የኖሩ አካላት ነበሩ፡፡ ይህም የጥረቱን ፍሬ አሳንሶታል፡፡
ታድያ ችግሩ እንዴት ይፈታ?
ዘላቂው መፍትሔ
ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታው የጠቅላላው ቤተ ክህነት ችግሩን ሲፈታ ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ ለኦሮምያ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አካባቢዎች የሚሆን ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ፣ ተቋማትን አዘጋጅቶ፣ የሰው ኃይልን መድቦ ሲሠራ ነው ችግሩ በመሠረታዊነት የሚፈታው፡፡ ችግሩ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ በውጭ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትም የአስተዳደር ችግር አለባቸው፡፡ ቤተ ክህነቱ ለ21ኛው መክዘ የሚመጥን ሆኖ እስካልተደራጀ ድረስ ችግሩ አይፈታም፡፡
በቅርብ የተቋቋሙ አህጉረ ስብከት የቀደምቶቹን ችግር ወረሱ እንጂ አዲስ መንገድ መጓዝ አልቻሉም፡፡ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ቢቋቋምም ችግር ወራሽ ይሆናል እንጂ አዲስ ተአምር አይፈጥርም፡፡ ችግሩ ክልላዊ ሳይሆን ሀገራዊ ነውና፡፡ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጉዳዩን ከሀገራዊነት ወደ ክልላዊነት ነው የሚያወርደው፤ በአማራ ክልል የአሮሞ ብሔረሰብ ዞንን፣ በየክልሉ ባሉ ኮሌጆች የሚማሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን፣ በሌላ ክልል የሚኖሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የኦሮምኛ ተናጋሪዎችን ጉዳይ ሊመለከት አይችልም፡፡ ክልላዊ ነውና፡፡ ችግሩ ሀገራዊ ስለሆነ መፍትሔውም ሀገራዊ መሆን አለበት፡፡
መሥራት ያለብን አንድ የኦሮሞ ዲያቆን ኦሮምኛ፣ ግእዝና ሌሎች ቋንቋዎችን ችሎ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ነባር ትምህርት በሚገባ ተምሮ የአኩስም ንቡረ እድ፣ የላሊበላ አስተዳዳሪ፣ የደብረ ሊባኖስ እጨጌ፣ የጣና ገዳማት አበ ምኔት፣ የኢየሩሳሌም ገዳማት ራኢስ፣ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ለመሆን የሚያግደው ነገር እንዳይኖር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ክልላዊ ሳይሆን ሀገራዊ ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታት መነሣት ያለባቸውም መላው ኦርቶዶክሳውያን እንጂ የአካባቢ ተወላጆች ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቅ ዐቅማችንን አስተባብረን ቤተ ክህነቱን ለቤተ ክርስቲያን የተመቸ እንዲሆን እናድርገው፡፡ ያን ጊዜ የኦሮምያን ምእመናን ችግር ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም ችግር ይፈታል፡፡ ቤተ ክህነቱን ለቤተ ክርስቲያን እንዲሆን አድርገን ካላመቻቸነው ግን የኦሮምያ ቤተ ክህነት የኦሮምያን ችግር ሌላ ስም ይሰጠዋል እንጂ አይፈታውም፡፡ የምእመናኑ ችግር በክልል ደረጃ ካለመዋቀር የመጣ አይደለምና፡፡
ቤተ ክህነቱ ክልላዊ መዋቅር ያስፈልገዋል ከተባለም ለሁሉም ክልል የሚሆን መዋቅር ተጠንቶ፣ ከቃለ ዐዋዲው ጋርም ተያይቶ ተግባራዊ ይሁን፡፡ የአንድን አካባቢ ቤተ ክህነት ራሱ ዋናው ቤተ ክህነት በቅርንጫፍነት ይመሠርተዋል እንጂ ሌላ አካል ቀን ቆርጦና በምሥጢር ይዞ አይመሠርትለትም፡፡ ቅርንጫፉን፣ ያክለኛል ይመስለኛል ብሎ መፍቀድ የሚችለው ዋናው አካል ብቻ ነው፡፡ ይህም ማንም የማይገሠው ሕጋዊ መብት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዚህ የሚመጣባትን ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ በሕግ መመከት አለባት፡፡
በሌላም በኩል ለሕዝቡ በመቅረብ ረገድ አጥቢያ፣ ወረዳና ዞን ይበልጥ ይቀርባሉ፡፡ የሕዝቡን ችግር ለመረዳትና ለመፍታት ከእነዚህ ሦስቱ ቀረበ መዋቅር የለም፡፡ ታድያ ለሕዝብ በሚቀርበው መዋቅር ያልተፈታ ችግር ለሕዝብ በሚርቀው የክልል መዋቅር ይፈታል ብሎ ማሰብ ሕልም ነው፡፡
የመቆያ መፍትሔ
የጠቅላላው ችግር እስኪፈታ ድረስ ግን በኦሮምያ የሚገኙ ምእመናን ያነሡት ትክክለኛ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሊያገኝ ይገባል፡፡
1. ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በፊት ጥያቄውን ተመልክቶት ነበር፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቀርበው ምእመናኑ አስረድተዋል፡፡ ያኔ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ዕቅድ ጋር በጋራ ይታያል የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የመሪ ዕቅዱ ጉዳይ ሊዘገይ ስለሚችል የምእመናኑን ጥያቄ ቅዱስ ሲኖዶስ ኮሚቴ አቋቁሞ በሚገባ ማየት አለበት፤ የፖለቲከኞችን ጥያቄም ከሃይማኖተኞቹ ጥያቄ መለየት አለበት፡፡ የምእመናኑ ጥያቄ ተገቢነት ያለው ጥያቄ ስለሆነ፡፡
2. በኦሮምያ ክልል የሚገኙ አብያተ ክርስቲናትን ሁኔታ፣ የአገልጋዮችን ሁኔታ፣ የአገልግሎቱን ሁኔታ የሚያጠና ኮሚሽን አቋቁሞ ችግሩን በጥናት መለየት ይገባል፤
3. በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ፣ በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ኮሌጅና በሌሎችም ማሠልጠኛዎች በኦሮምኛ ቋንቋና በሌሎችም ቋንቋዎች ዲፓርትመንቶችን ከፍቶ አገልጋዮችን በየደረጃው ማሠልጠን፤
4. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ተቋም አደራጅቶ ቅዱሳት መጻሕፍት የትርጉም ሥራ መጀመር
5. በኦሮምያ አካባቢዎች የስብከተ ወንጌልና የክህነት አገልግሎትን የሚያጠናክር ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ ምክር ቤት ማቋቋም፤ በኦሮምያ ክልል የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት የምክር ቤቱ አባላት እንዲሆኑ ማድረግ፤ ሊቃውንትንና ምእመናንን ማካተት፡፡ ምክር ቤቱ በየኮሌጆቹ ለሚሠለጥኑ አገልጋዮች፣ መተርጎም ላለባቸው መጻሕፍት፣ መጠናከር ላለባቸው አብያተ ክርስቲናት፣ ወዘተ. ዓመታዊ እቅድ እንዲያወጣ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያቀርብና እንዲያስወስን ማድረግ፤ ተግባራዊነቱንም እንዲከታተል ሥልጣን መስጠት፤ የሚያጋጥሙ አስተዳደራዊ ችግሮችን በየደረጃው እንዲፈታ ማስቻል፤
6. በየቦታው የተጀመሩትን አገልግሎቶች በምክር ቤቱ በኩል ማስተባበር
7. በኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚገኙ የካህናት ማሠልጠኛዎችን በመጠቀም በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ካህናትን ማፍራት፤ ለነባሮቹም ተከታታይ ሥልጠና መስጠት፤ ከዚህ በፊት የተጀመሩትንም ማጠናከር፤
8. በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠትን በተመለከተ ፖሊሲና ዝርዝር መመሪያ አዘጋጅቶ፤ አንድነትን ከኅብረ ብሔራዊነት፤ ኦርቶዶክሳዊነትን ከአካባቢያዊነት፤ በማያጣርስ መንገድ ወጥ ሥራ መሥራት፤
የአካባቢውን ችግር መፍታት የሚቻለው በክርስቲያናዊ መንገድ ብቻ ነው፤ መንገዱ ክርስቲያናዊ ከሆነ ማስተባበር ያለበት መላ የኦርቶዶክስ ልጆችን ነው፡፡ ጉዳዩ የብሔር ጥያቄ ሳይሆን የድኅነት ጥያቄ ነውና፡፡ የምእመናኑ ጥያቄ ትክክል ነው፡ ጥያቄያቸውም የመዳን ጥያቄ ነው፡፡ የፖለቲከኞች ጥያቄ ደግሞ ዓላማው ሌላ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ያለባት የምእመናኑን ጥያቄ ነው፡፡ የቄሣር ጥያቄ ለቄሣር ይቅረብ፣ የእግዚአብሔርም ለእግዚአብሔር፡፡እርሱ ይርዳን፡፡
Filed in: Amharic