>

እንቁጣጣሽ! አዲሱ አመት . . . ? ወይስ . . . ?   (ዶር በድሉ ዋቅጅራ)

እንቁጣጣሽ! አዲሱ አመት . . . ? ወይስ . . . ?
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
.
እኛ፣
የተስፋና ስጋት ድቅል፤
ድምጽ ብቻ፣ ድፍን ቅል፡፡
አትለቅ! አምና ጥለኸን፤
ያላንተ ማንም አያውቀን፡፡
.
የለመድንህ የለመድከን፤
ያባከንህ ያባከንከን፤
እባክህ አምና – አትለቅ! 
ባንወልድ – አብረን እንገልሙት፤
ባንኖር – አብረን እንሙት፡፡
.
ከላይ ያለውን ግጥም ከረዥም ጊዜ በፊት ያነበብኩትን የአልፈርድ ኤል. ቴናሲይ “The Death of the Old Year”   በሚል ግጥም  መንፈስ የጻፍኩት ነው፤ አስታውሼው ይሁን የገዛ መንፈሴን አውርሼው በውል አላውቅም፡፡
.
አዲስ አመት የሚናፈቀው በልብ ተስፋ ሲሰነቅ፣ ላለሰለስነው ማሳ ዘር፣ ለለቀለቅነው ጎተራ መኸር ሲኖረው ነው – ቢያንስ ይኖራል ብለን ስናስብ፡፡  አመሻሽ አድማስ ላይ የምትሞት ጀምበር ነገ ማለዳ ላይ ውብ ሆና – ደምቃ እንደምትወጣ የምናውቀውን ያህል ጵጉሜ 5/6 የሚያልቀው አመት፣ መስከረም 1 ተውቦ/ደምቆ ይጀምራል ወይ? የአዲስ አመት ናፍቆትና መሻት ከዚህ ጥያቄ መልስ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ይመስለኛል፡፡ ‹‹እንቁጣጣሽ!›› ብለን የምንቀበለው ቀን ውስጥ፣ ከአምና የተሻለ ተስፋ አለ ወይ?
.
የተቀበልነው ዘንድሮ አምና መዳኒት ላላገኘንለት ደዌ ፈውስ አለው? ላልሻረው ጥላቻችን ፍቅር፣ በየልባችን ያስቀመጥነውን የቂም በረዶ የሚያሟሟ የይቅርታ ሙቀትስ? ከሌለው፣ አምና ለምን ይሞታል?! ዘንድሮንስ ለምን እንናፍቃለን?! ተስፋና መልካምነት በልባችን ከሌለ፣ ስለምንስ ‹‹እንቁጣጣሽ›› ብለን፣ መልካም ምኞት እንለዋወጣለን!?
.
እስቲ ተመልከቱ! የክረምቱ ማጥ ከምድር፣ ዳመናው ከሰማይ፣ ጭጋጉ ከየተራራውና ኮረብታው እየገፈፈ ነው፡፡ ዝናቡ ጠገግ ብሏል፡፡  ሜዳውና ተራራው በአደይ አበባ መዋብ ጀምሯል፡፡ የመስቀል ወፍ በትፍስህት ለተፈጥሮ በረከት ታረግዳለች፤ . . . .   ስለምን ከተፈጥሮ እንጎድላለን?  የተፈጥሮ አካል አይደለንምን? እኛስ? አምና አብሮን የከረመው የቂም፣ ጭጋግ ከልባችን ተገፏል? አላጠጋጋ ያለን የጥላቻ ማጥ መጥገግ ጀምሯል? አፈናቃይና ተፈናቃይ፣ ሟችና ገዳይ ያደረገንን ቂም የሚሽር ፍቅር በልባችን አለ? ልቦናችንን ከህሊናችን የለያየው፣ አስተውሎታችን የጋረደው በጎሰኝነት ከንች ላይ የተገደገደው ከፋፋይ የብሄር ግርግዳ ፈርሷል? . . . . . . .ይህን ካልሰነቅን እንዴት እንቁጣጣሽ የአዲስ አመት መጀመሪያ፣ አዲስ ቀን ይሆናል?
.
ፍቅርና መተሳሰብን፣ ይቅርታንና መቻቻልን የነፈገንን የብሄረተኝነት ግድግዳ አፍርሰን ከከረመ ደዌያችን ለመፈወስ ስንዳክር አምናን ሸኝተን፣ አዲስ ሀይማኖታዊ ከፋፋይ ግድግዳ ለማቆም ከንች ጠርበን ወደ አዲሱ አመት እየገባን፣ ስለምን ‹‹እንቁጣጣሽ!›› እንባባላለን? የብሄርን ከፋፋይ አጥር፣ በብሄር የፍቅር ሰንሰለት ለመተካት የዳከርንበትን አምና ፍሬ በማየት ተስፋ ሳይሆን፣ በአዲስ የሀይማኖት ከፋፋይ ግንብ ስጋት ከተቀበልነው፣ አዲስ አመት አለ!? ‹‹እንቁጣጣሽ›› መባባል አግባብ ነው!? ከልጃገረዶች ‹‹አበባ አየሽ ወይ – ለምለም›› ቄጠማ፣  ከኮበሌዎች በቀለማት ያሸበረቀ አበባስ ስለምን እንቀበላለን? ሁሉስ ስለአዲስ ተስፋ፣ በልባችን ስለሰነቅነው ብሩህ ቀን ተምሳሌት አይደለምን? ከሜዳው፣ ከሸንተረሩ፣ ከዥረቱ፣ ከአደዩና ከመስቀል ወፉ – ከተፈጥሮስ ይሁን እንጉደል፣ እንዴት ከልጆቻችን ተስፋና ምኞት እንጎድላለን?
.
አዲስ አመትን ለማድመቅ፣ አደይ የፈነዳችው ሜዳና ኮረብታውን ያጌጠችው ለይምሰል ነውን? የመስቀል ወፍስ ብትሆን፣ ከተደበቀችበት የትም ወደ ሜዳው ወጥታ የምትሽከረከረው፣ ስለእንቁጣጣሽ ተፈጥሯዊ ትሩፋት ልባዊ ደስታና ተስፋዋን ለመግለጽ አይደለምን? እኛ ስለምን የልጃገድና የኮበሌ ልጆቻችንን የእንቁጣጣሽ መልካም ምኞት፣ የአምናን ቂምና ጥላቻ በቋጠረ ልብ እንቀበላለን?  በገዛ ልጆቹ ላይ የሚያስመስል ወላጅስ ሰው ለመሆኑ መረጋገጫው ምንድነው? ልጆቻችን ከዚህ የሚማሩት መንታ ጥፋት – አንድም ቂምና ጥላቻ፣ አንድም ማስመሰልን አይደለምን?
.
በአዲስ አመት መጀመሪያ የምንሰናበተውን አምና ዞር ብሎ መቃኘት የተለመደ ነው፤ ዞሮ መመልከቱ – ቅኝቱ፣ አንድም በጸጋው ለመደሰት፣ አንድም በህጸጹ ለመቆጨትና ለመጸጸት ነው፡፡ ዛሬ ለምንጀምረው አዲስ አመት ደግሞ ከአምናው አዝመራ ካመረትነው ደስታና ትፍስህት የበለጠ፣ የቃረምነው ቁጭትና ጸጸት የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ በመጀመሪያ፣ ቁጭትና ጸጸት የሚመነጨው መጥፎ ስራን ለይቶ ከማወቅ ነው፡፡ ቀጥሎ፣ ቁጭትና ጸጸት የለየነውን ክፉ አረም ማጥፊያ መርዝ/መዳህኒት ነው፡፡ በፈንጠዝያ ከጀመርነው አዲስ አመት ይልቅ፣ በቁጭትና በጸጸት በጀመርነው አዲስ አመት ብዙ በጎ ለውጥ እናደርጋለን፡፡ ጸጸት የነፍስን የክፋት ሽንቁር ከመለየት፣ ቁጭት ሽንቁሩን ሳይደፍኑ ከመቅረት የሚመጡ ህመሞች ናቸውና፣ የአዲስ አመት የመጀመሪያ ተግባር ይህን የክፋት ሽንቁር ደፍኖ (ባይቻል አጥብቦ) ከጸጸትና ቁጭት ደዌ ነፍስን መፈወስ ነው፡፡
.
እስቲ ከዚህ የሚወርደውን ጽሁፍ አይናችንን ጨፍነን በልቦናችን ብርሀን አምናን እንመርምር፤ የመጪውን አዲስ አመት ተስፋ እንቃኝ፡፡  አምና በደስታ ነው በቁጭትና በጸጸት የምንሸኘው? ስንቱን ይቅር ብለናል? ለስንቱ ቡጢ ሰንዝረናል? ለስንቱ አቅም አንሶን ቂም ቋጥረናል? ስንቱን ስለበጎ ስራው አመስግነን፣ ስንቱን ክፋት ረግመናል?  . . . . አምና ገድለናል? አስገድለናል? ወይስ ሞተናል? የስስትና የብሄር አጥር ስናጠብቅ፣ አብረውን የኖሩ ጎረቤቶቻችንን አፈናቅለናል? ወይስ አጥራችንን አፍርሰን (ቢያንስ በሩን ከፍተን) የተፈናቀሉትን አስጠግተናል? በተራቡ ላይ በራችንን ከርችመን፣ በመሶባችን የበሰለ ምግብ አሻግተናል? ወይስ በራችንን ከፍተን አብልተናል? ካልዋልንበት የአባቶቻችንና የአባቶቻቸው የህይወት እርሻ በቃረምነው ቂም ተመርዘን – ታመናል? ወይስ በበጎው ተፈውሰናል? ጥሪታችን ላይ ጨምረናል? ወይስ ጥሪት ያልነው አፍርሶናል? . . . .
.
በተቀበልነው አዲስ አመት አምና የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ጥሪታቸው ይመለሳሉ? ወይ ጎጆ ይቀልሳሉ? መቀሌ የከተሙት ህውሀቶች በፍትህ ይዳኛሉ? ወይ በይቅርታ ሰላም ያገኛሉ? ወይስ ህገመንግስቱን ‹‹ያድናሉ››? ምርጫው ለዲሞክራሲ ያበቃናል? ወይስ ከፋፍሎ ያጫርሰናል? አዝመራው አመት ይመግበናል? ወይስ ለልመና አደባባይ ያቆመናል? ታሪክ ያስተምረናል? ወይስ ያጫርሰናል? አጥሩ ይከልለናል? ወይስ ይጠብቀናል? . . . .እንቁጣጣሽ !
Filed in: Amharic