>
5:13 pm - Saturday April 18, 7778

ጣይቱ የባሕልና የትምህርት ማዕከል 19 ነኛ ዓመት አብራችሁት እንድታከብሩ ይጋብዛል

ጣይቱ የባሕልና የትምህርት ማዕከል ባለፉት 19 ዓመታት በስደት ዓለም ሊከናወኑ ሳይሆን ሊታሰቡ የሚከብዱ በርካታ የጥበብ ሥራዎችን በሚያኮራ ውጤት አከናውኖአል:: በጥቂት ቀና ሰዎች ድጋፍ ባለማቋረጥ ጥበብን በጥራት በመላው ሰሜን አሜሪካ በካናዳና በአውሮፖ እየተዘዋወረ ከሃገሩ ውጭ የሚገኘውን ኢትዮዽያዊ ሲያዝናና ሲያስተምር ቆይቷል:: የኢትዮዽያን ታሪክና ባሕልና ጥበብ ሲያቀርብ እነሆ 19 ዓመታትን አስቆጠረ:: ያልተቋረጠ 230 የግጥም ምሽቶችን አስተናግዷል:: ከአንጋፋዎቹና ዕውቆቹ ፀሐፊያን ከነሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን- ከሰለሞን ደሬሣ – ከሰይፉ መታፈሪያ- ከማሞ ውድነህ- ከተስፋዬ ገሠሠ- ከዶር ፈቃደ አዘዘ – ከፕሮ አዱኛው ወርቁ . . . ጀምሮ በሕይወት እያቀረበ ሥራቸውን ዘክሮአል::

ወጣት ፀሐፊያንን በማበረታታት ፅሑፋቸው ለሕትመት እንዲበቃ በማድረግ አስመርቋል:: በአጠቃላይ 3555 የግጥም አንባብያንን አስደምጧል:: ከ50 በላይ ዕውቅ ተዋንያን በድርጅቱ ምርጥ ተውኔቶች የተሳተፉ ሲሆን በሄደበት አካባቢ ሁሉ ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት 103 አማተር ተዋንያንን በመድረክ አሳትፏል:: 271 የቴአትር ጉዞዎችን ያደረገ ሲሆን 378 ትርኢቶችን ለተመልካች አቅርቧል:: በየዓመቱ ህዳር ወር ነፃ የሙያ ሥልጠና በትወና – በፅሑፍ -በዝግጅት- በሲንማ ጥበብ በጋዜጠኝነት ወዘተ ከመስጠቱም ባሻገር በዕውቅ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ዘውትር አርብና ቅዳሜ ነፃ Tutering በመስጠት ወጣቶችን ይረዳል :: የመጀመሪያውን የአማርኛ ቤተመፃህፍ ከፍቶ የአማርኛ መፃሕፍትን ለሚፈልጉ አገልግሎትይሰጣል:: በአሁኑ ጊዜ ጣይቱ ማዕከል ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያና ኩራት ነው::

እጅግ የሚያኮራና የሚያስደንቅ ክንውኖችን ያስመዘገበው ድርጅት 19 ነኛ ዓመቱን September 22nd, 6:30 at Civic Building, Silver Spring MD አብራችሁት እንድታከብሩ ይጋብዛል::

Filed in: Amharic