>

በአወዛጋቢ መረጃ የታጨቀው  የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ ያሳደረብኝ ቁጣ!!! (ዘሪሁን ተክሌ)

በአወዛጋቢ መረጃ የታጨቀው  የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ ያሳደረብኝ ቁጣ!!!

 


ዘሪሁን ተክሌ

 

የአንዳርጋቸው ጽጌን “ትውልድ አይደናገር፣ እኛም እንናገር” የተሰኘ የመጽሐፍ ምርቃት አስመልክቶ ብዙ ስልኮች ከብዙ አቅጣጫዎች ሰሞኑን ተደወሉልኝ። ‹‹አነበብከው ወይ?››፣ ‹‹ቃለ መጠይቁን ሰማኸው ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከወዳጅ ዘመዶቼ ተከታተሉ። መጽሐፉ በእጄ እስከሚገባ ድረስ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአርትስ ቲቪ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ በትዕግሥት አዳመጥኩ። መጽሐፉ እንደ ደረሰኝም ጊዜዬን ወስጄ በጥሞና አነበብኩት። ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› እንደሚባለው ሆኖብኝ ተወጣሁት ብል ይሻላል።

ከቃለ መጠይቁ ይዘት ጀምሮ የተሰማኝ ስሜት በጣም የተደበላለቀ ነው። የቁጣ፣ የንዴት፣ ከልብ የሚያሳዝንና የሚያስተዛዘብም ጽሑፍ ሆኖ ነው ያገኘሁት። አንድ ሰው ምን ሁኔታና ምን ዓይነት ሥነ ልቦና ቢኖረው ነው እንደዚህ ያለን የውሸት ጥርቃሞ የሚደረድረው? ራሱንና የእኔ የሚላችውን ሁሉ ከፍጥረቱ ጀምሮ እስከ ሽምግልና ዕድሜው የሌለ ታሪክ ጠፍጥፎ ያልሆኑትን ሆኑ ብሎ የሚተርከው? ሆን ብሎ የሌላውን ሰው ስም ለማጠልሸትስ ያን ያህል የሚጥረው? የእሳቤ መንገዱና የሚያገኘው ትርፍ ምን ቢሆን ነው?  የትስ ለመድረስ ነው? የተያያዘው የመመፃደቅ፣ የድፍረት፣ የንቀት፣ የውሸት፣ የውለታ ቢስነት፣ የእዘኑልኝ ተረት ተረት ማላዘን ምን ውጤት ለማግኘት ነው? ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ መጽሐፉን ለሚያነበውና ቃለ መጠይቁን ለሚሰማው ኅብረተሰብስ ያለው ግምትስ ምን ያህል ዝቅተኛ ቢሆን ነው?

እስካሁን ከሰማሁትና ካነበብኩት የምገነዘበው የትርክቶቹን ባዶነትና ጥራዝ ነጠቅነት ብቻ አይደለም፡፡ በዕወቁኝ፣ አድንቁኝ፣ አሞግሱኝ፣ አዙሪት ውስጥ ተነክሮ ዕድሜ ልኩን የሚዳክር ግለሰብ እንደሆነም ጭምር ነው። ከዚህ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት በየጊዜው በሚያደርገው ትንቅንቅ ስንት የሰው ጭዳ (ቪክቲም) ያስፈልገው ይሆን? እንደገለጸው ከሆነ፣ የመጽሐፉ ዓላማ ለተከታዩ ትውልድ  የአገሪቱ የታሪክ ጸሐፊ ምሁራን ያዛቡትን ለማቃናት፣ ታሪክን  በትክክል ለመተረክና እውነተኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ለማሳወቅ ታስቦ ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ  ለዚህ ዓላማው የአገሪቱን የታሪክ ምሁራን በመኮነን ይጀምራል። ቀጥሎም፣ የታወቁና የተከበሩ አዛውንት ምሁራን የሕይወት ታሪካቸውን ከአገሪቱ የታሪክ ሒደት ጋራ በማጣመር የጻፉትን ትረካ በመከለስና እንደፈለገው በመተርጎም በምንም መረጃ ላይ ያልተደገፈ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ ያቀርባል።

መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ የበረቱ የታሪክ ባለሙያዎች አስተያየታቸውንና ከዚህ መጽሐፍ የሚያገኙትን “ቁም ነገር” እንደሚያካፍሉን ፅኑ ተስፋ አለኝ። እስከ ዛሬ የወጡትን አንዳንድ ትችቶች/አስተያየቶች ሳነብ፣ ስለመጽሐፉ ያለኝን አሉታዊ አስተያየት የሚያጠነክሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።  የእኔ ፈንታ፣ ስሜን እየጠራና እኔን በቀጥታ በተመለከተ በተረካቸው ዋና ዋና አንኳር አንኳር ውሸቶች/የተዛቡ ትረካዎች ላይ አተኩሮ ዕውነቱን ማሳወቅ ነው።

1. የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበርን ጽሑፎችና መጽሔቶች ከአውሮፓ በየጊዜው ለወንድሞቼና ለእሱ በመላክ ንቃተ ህሊናውን ከፍ በማድረግ አስተዋጽኦ እንዳደረግሁለት ይጽፋል (ገጽ 303)። ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን ዓይን ያወጣ ውሸት ነው። በዚያን ጊዜ (እ.ኤ.አ. 1965/1966) እንኳን በፖስታ በሰውም በአገሪቱ የተከለከለ ጽሑፍ መላክ አደገኛ መሆኑን በሚገባ ስለማውቅ፣ ለወንድሞቼም ሆነ ለእርሱ መጽሐፍ ልኬ አላውቅም፣ የዚህ ዓይነቱ የጀብደኝነት ባህሪም የለኝም። እንኳን መጽሐፍ መላክ በደብዳቤ ከቤተሰብ ጋር ያለኝ ግንኙነት በጣም ውስን ነበር።  በዚህ ብቻ አላበቃም ውሸቱ፣ የአንድ ወዳጄን ስም በመጥቀስ በእርሱ በኩል “ማርክሲስታዊ” መጽሐፎች እንደላኩለት ይናገራል።

ይህ ወዳጄ ከእኔ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት አስቀድሞ ወደ አገር ተመልሶ በትልልቅ ኃላፊነት ቦታዎች አገሩን ያገለግል ነበር። አሁን በሕይወት የለም፣ ከኢሕአፓ  የመጀመርያ ሰለባዎች አንዱ ነበር። ስሙን ከእነ አያቱ ስምና ማዕረግ መጥቀስና የተገደለበትንም ሁኔታ መዘርዘር ያስፈለገው ለምንድነው? በገጽ 470ም ላይ እንደዚሁ ወደ ሌላው ወዳጄ ዘንድ ያውም “የፖለቲካ ትምህርት” እንዲሰጠው እንደላኩት ይጽፋል። ይኼ ሁሉ ፈጽሞ ውሸት ነው። በኢሕአፓ አመራር ውስጥ የነበሩትን ሁሉንም በሾፌርነት በማገልገሌ ከእነ አስተሳሰባቸው አውቃቸው ነበር ብሎ እንደሚተርከው ሁሉ፣ ሌሎቹንም ቢሆን በተለይ “አመራር” ቦታ ላይ የነበሩትን ሁሉ “አውቃለሁ” የሚል አባዜ ስለተጠናወተው ይሆን?   በመጽሐፉ ትረካ ላይ የሚንፀባረቀው ይኼው “ከእኔ በላይ ማን አውቆ” የማለት ግብዝነት ይመስለኛል።

2. አንዳርጋቸው ጽጌ በኢሕአፓ ውስጥ በወቅቱ የተከሰተውን መከፋፈል (የክሊክና የአንጃ) አሰቃቂ የመገዳደል ሁኔታ በመዘርዘር (የእዚያን ቀን አሱ የሚያውቀውን መኪና በመጠቀም ጓደኛውን ፊቱ ላይ ገድለው መሄዳቸውንና የሚቀጥለው ተረኛ ደግሞ እሱ እንደሆነ ነገረኝ) ሕይወቱ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደወደቀ፣ በድንጋጤና በፍርኃት ስሜት ሲገልጽልኝ ሕይወቱን ለማዳን ለአንዲት ሰኮንድ እንኳን አላመነታሁም ነበር። አብሮኝ የሚኖረውን ጓደኛዬን ወዲያውኑ አማክሬ፣ ለተወሰነ ጊዜ እቤታችን በመኖር ዘወር ማለት እንዲችል አደረግሁ። ወቅቱ ሁላችንም ከፍተኛ አደጋ ላይ የነበርንበትና ማን እንደገደለው እንኳን ሳይታወቅ ብዙ ሰው በየቀኑ፣ በየመንገዱ የሚገደልበት ጊዜ ነበር። እሱን በማስጠለል ሊደርስብን የሚችለውን አደጋ እኔና ጓደኛዬ በደንብ ብናውቅም፣ ዋናው ዓላማችን “አለብኝ” ካለው የሞት አደጋ  የእሱን ሕይወት ማትረፍ  ብቻ ነበር።

አንዳርጋቸው ጽጌ  ይህን ሰብዓዊ ድርጊት በመጽሐፉ ውስጥ (ገጽ 655/656) በሚያሳፍርና የሰብዕና ዝቅጠቱን በሚያመለክት ሁኔታ ገልጾታል። የተደረገለትን ሰብዓዊ ትብብር በእሱ ብልጥነትና በእኛ የዋህነት የተፈጸመ አድርጎ ከመውሰዱም በላይ፣ እኛ ሥራ በምንሄድበት ጊዜ በየክፍላችን እየዞረ መሳቢያችንን አንድ በአንድ እንደሚበረብር ያለ ኃፍረት ይተርካል። ወራዳ ድርጊቱን ለመደገፍ፣ “ወቅቱ እንዲህ ነበር” ብሎ ያልፈዋል። እንደዚህ ዓይነቱን አሳፋሪና ወራዳ ተግባር በድል አድራጊነት  ሲተርክ  ደግሞ፣ የመኢሶን ልሳን የነበረውን “የሰፊው ሕዝብ ድምፅ” ስቴንሲል እንዳገኘ ያትታል። ቀጥሎም እሱ ከስቴንስል ላይ አንብቦ የጨረሰውን ጽሑፍ፣ እኔ ከሁለት ቀን በኋላ የወረቀት ላይ ዕትሙን እንዲያነበው እንደምሰጠው ይናገራል።

በስቴንሲልም በወረቀትም ስላነበበው ጽሑፍ ይዘት፣ ጥቅምና ጉዳት ግን ትንፍሽ አይልም። ሊያሳውቅ የሚፈልገው ሊደርስብን የሚችለውን አደጋ ተቀብለን ያስጠለልነውን ሰዎች ቤት በመበርበር በፈጸመው ጀብድ የቱን ያህል ምጡቅ የህቡዕ ታጋይ እንደሆነ ነው። ከዚህ “ከፍታ” ለመድረስ በመቸኮሉም ነው ቀደም ሲል ንቃተ ህሊናው የዳበረው እኔ በምልክለት ጽሑፎችና መጽሐፍት ጭምር ነበር በማለት፣ የዋሸውን የረሳውና አሁን ደግሞ የቤቴ በርባሪ ሆኖ ያረፈው። ራሱ እንደሚለው እኔው በወረቀት ለመስጠት ያልደበቅኩትን ጋዜጣ፣ “የሰፊው ሕዝብ ድምፅ” አስቀድሜ ቤቱን በርብሬ አንብቤው ነበር ብሎ በጀግንነት የሚተርከው። ያስጠጋን ሰው ቤት መበርብር የሚያኮራ ድርጊት መሆኑ ነው? ሞት አደጋ ላይ እንደወደቀ አስተዛዝኖ የነገረኝ፣ ከቤቴ ገብቶ ሊበረብረኝ ኑሯል? ለትውልድ አስተላልፋለሁ የሚለው ቁም ነገር ምኑ ላይ ይሆን?

ከሁሉም የደነቀኝ ደረቅ ውሸት፣ እሱም ሆነ ሌላው ወንድሙ ከዓመታት በኋላ ፈረንሣይም ሆነ ኢትዮጵያ በተገናኘንባቸው ጊዜያት፣ አሁን በየሚዲያው እንደሚገልጸው ሁኔታዎችን አንስተን በቀጥታ የተነጋገርንበት ጊዜ የለም። ነገር  ግን ድርጅቱ “ባዘዘን መሠረት” በሚሉት “ተልዕኮዎቻቸው” ላይ የፈጸሙትን የወንጀል ድርጊቶችና ጅብዱዎች “ቴአትራዊ” በሆነ መልክ ይተረኩና ይሳለቁ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከጓደኞቻችንም ሰማን እያሉ እንደ “ጀብድ” የሚያወሩትንም የውንብድና ድርጊቶች ሳስታውስና አሁን ደግሞ በመጽሐፉ ላይ የሚያትታቸውን እውነትና ቅንነት የሚጎድላቸው ኑዛዜዎች ሳነብ፣ ታላቅ ሕመም ይሰማኛል።

3. በመጽሐፉ ገጽ 568/569 ላይ፣ የኢሕአፓ ገዳይ ስኳድ እኔን ሊገድል ሲል፣ ከእሱ ጋር በመታየቴ ሕይወቴ እንደተረፈ ያትትና ይህ በመሆኑ “ዛሬ ከፀፀት ድኛለሁ” ይላል።  በመቀጠልም በገጽ 656 ከኢሕአፓ ጋር የነበረውን ግንኙነት በመቋረጡ ነው እንጂ፣ እኔንና ጓደኞቼን በሙሉ ላስጨርሳቸው እችል ነበር ይላል። አንድ ጊዜ የገዳይ ስኳድ፣ በሌላ ጊዜ አዛዥ፣ ቆየት ብሎ ደግሞ ከበላይ ትዕዛዝ ውሳኔ ተቀባይና አስፈጻሚ፣ በአብዛኛው ደግሞ ደጋግሞ የድርጅቱ የበላይ አካላት ሾፌር እንደነበር በመግለጽ ይዋትታል።

አንዴ የቤታችን በርባሪ፣ በእኔና በአጋጣሚ አብረውኝ ባያቸው ወይም በእሱ አስተሳሰብ ሊያውቃቸው ይችላል ብሎ የገመታቸውን ሰዎች ላይ ሁሉ የሞት ፍርድ ፈራጅ! ይህንን ሁሉ ወንጀልና መሰሪነት ከአርባ ዓመታት በላይ አምቆ ኖሮ፣ ዛሬም እሱ ራሱ ከዚህ ሕይወትና ልምድ ትምህርት ያላገኘበት መሆኑን በግልጽ በሚታይበት ሁኔታ፣ “የትውልድ መምህር” ለመሆን የሚከጅልበት የእሳቤ መንገድ ምን ይሆን?

4. የከተማ ቀበሌና የገጠር ገበሬ ማኅበራት ለእኔ የመጀመርያዎቹ ሕዝባዊ የዴሞክራሲ ተሳትፎ መድረኮች ናቸው ብዬ አምናለሁ። ማኅበራቱ በወቅቱ ሕዝባዊ ድል የምንላቸውን አዋጆች በሥራ ለማዋል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በአዋጁ መሠረት እነዚህን መሠረታዊ ማኅበራት ማቋቋም፣ ማደራጀትና ማስተማር የማንም ዴሞክራትና ሕዝብ አፍቃሪ ዜጋ ሁሉ ኃላፊነት ነበር ብዬ እገምታለሁ። ለዚህም ነው በእዚያን ጊዜ ሌላ ሥራ ቢኖርብኝም፣ ይኼ አጋጣሚ ለማንም ዴሞክራት ኢትዮጵያዊ ከሕዝብ ጋር ለመሥራት ትልቅ ዕድል መሆኑም በማመን ባደግኩበትና የቤተሰቦቼ መኖሪያ ቤት በሚገኘው ቀበሌ ለመሳተፍ የወሰንኩት። በወቅቱ በለውጡ ሒደት የማይስማሙትንም ጨምሮ መወያየት፣ መማር፣ ማስተማር ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ። ይህን የሚቃወሙ ድርጅቶች ነበሩ። ሁኔታው አልጋ ባልጋ አልነበረም። በተመራጮች ላይ ጦርነት ከፈቱ። ከእኔ በፊትም የቀበሌው የመጀመርያ ተመራጭና ሊቀመንበር የነበረችው የሁለት ልጆች እናት ከቀበሌ ጽሕፈት ቤት ስትወጣ ተገድላ ነበር። ከፍተኛ 3 ቀበሌ 53 ተመራጭ ሊቀመንበር ሆኜ ከተመረጥኩ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ከምኖርበት ከእናቴ መኖርያ ቤት ስወጣ እንደዚሁ ተተኩሶብኝ ነበር። በዚህም ምክንያት የቤተሰቤን መኖሪያ ቤትና ቀበሌውንም ለቅቄ ወጣሁ። ስለተሞከረብኝ ግድያ ዛሬ በመጽሐፉ የሚተርከውን ካነበብኩ በኋላ በእጅጉ ጥርጣሬ ቢገባኝ ያስደንቃል?

5. በዚህ ወቅት በከተማው ውስጥ በተለይ የቀበሌ ተመራጮች፣ በመኢሶን አባላትነትና  ደጋፊነት በ“ሰፊው ሕዝብ ድምፅ” አንባቢነት ጭምር በሚጠረጠሩት የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች፣ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ግድያ  በሰፊው ይፈጸም የነበረበት አሳዛኝ ጊዜ ነበር። ይህን ተከትሎ በቀበሌዎች የተደረጉት ሁለት የመሣሪያ የማሰባሰብ ዘመቻዎች በየቀኑ፣ በየመንገዱ የሚደረገውን ግድያ መግታት አልቻሉም ነበር። ሦስተኛ ዘመቻ በተለየ መልኩ ለማካሄድ በመንግሥት ታቅዶ ለየቀበሌው የተደራጀና ሙሉ ትጥቅ የያዙ ወታደራዊ ቡድኖች የአሰሳው መሪዎች ሆነው ተመደቡ። ለቀበሌው ተመራጮችና ጥበቃ አባላት፣ ሠፈሩንና ነዋሪውን በቅርብ ስለሚያውቁና ወደፊትም አብረው አንደሚኖሩ በመገንዘብ፣ ፈቃድ ከሌለው መሣሪያ በስተቀር ሌላ እንዳይወረስ፣ ፍተሻው ሰውን በማክብርና በሥነ ሥርዓት እንዲካሄድ፣ ወደ ዝርፊያ የሚያመለክት ድርጊት እንዳይፈጸም ማብራሪያና ትምህርት ቀደም ብሎ ተሰጣቸው። በመንግሥት የሚፈለጉም ሰዎች ስምና ፎቶግራፎች በብዙኃን መገናኛዎች በሰፊው ተበተኑ። ኮፒ ለእያንዳንዱ ፈታሽ መሪዎች ታደለ። በዚህ መልክ የተቀናጀው አሳሽ፣ በቡድን ተከፋፍሎ አሰሳውን ሲያካሄድ ዋለ።

እኔ የነበርኩበት ቡድን የንግድ ባንክንና የመከላከያ ሚኒስቴርን አልፎ  ቢሮዎችን ለመፈተሽ ወደ ኪዳኔ በየነ ሕንፃ አመራ። ከሕንፃው ፊት ለፊት ሳንደርስና መንገዱን ገና ሁላችንም አቋርጠን ሳንጨርስ ከቀደሙት ከቡድኑ ወታደራዊ አባላት አንዱ የአውቶማቲክ መሣርያውን እሩምታ ለቀቀው። ወደ ተተኮሰበት አቅጣጫ ስመለከት ተመቶ የወደቀ ሰው አየሁ። በዚህ ጊዜ ሌላ የተኩስ መልስም ሊኖር እንደሚችል በመገንዘብ ዝቅ ብዬ ጥግ ያዝኩኝ። ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ የመጀመርያ ድርጊቴ የተኮሰውን ወታደር ለምን? እንዴት? ማን ላይ? እንደተኮሰ ስጠይቀው የሚፈለግ ሰው እንዳየ ነገረኝ። በእኔ ግምት “በመሰለኝ”፣ ሰላማዊ ሰው ላይ ተተኩሶ ይሆናል ብዬ ተበሰጫጨሁ። እነርሱ ግን በእርግጠኛነት መሯሯጣቸውን ቀጠሉ። የተመታው ሁለተኛው ሰው ወደ ፎቁ ወጥቶ ራሱን ወረወረ። ይህ ሰው በኋላ እንደተረጋገጠው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ነበር። የሆነው ይኼው ብቻ ነው። አንዳርጋቸው ጽጌና ወንድሙ በገጽ 566 ላይ የሚተርኩት የፈጠራ ወሬ ነው። የማንንም መኪና ሆነ የማውቀው ወይም የሚፈለግ ሰው አላየሁም።

7. ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን አውቀዋለሁ ወይ? በ1965/66 በፈረንሣይ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዓመታዊ ጉባዔ በሞንትፐሊዬ ከተማ በተሳተፈበት ጊዜ ከሌሎች ተሳታፊዎች ጋር አግኝቼው ነበር። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላም በምንም አጋጣሚ አልተገናኘንም። ትውውቃችን አንዳርጋችው ጽጌ  እንደሚተርከው ፈጽሞ አይደለም።  በዚያን ዘመን እርሱ ከሚለው ጓደኛዬ ጋርም ፓሪስ አልኖርኩም። ይህንን ሁሉ ፈጠራ መተረክ ምን ገፋፋው? ዓላማውስ ምንድነው? ጥያቄዎቹን ሊመልስ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው።

አንዳርጋቸው ጽጌ  የትረካውን እውነትነት ለማረጋገጥ፣ ወንድሙ እኔ እናት ቤት ምሳውን በልቶ አሰሳውን ይከታተል እንደነበርና የሆነውን ሁሉ እሱው እንደነገረው ያለ ማንገራገር፣ ያለ መጠራጠር፣ በእርግጠኝነት ይጽፋል/ይናገራል። ወንድሙ ለምን እኔንና አሰሳውን ተከትሎ እንደሚሄድ ሲያስረዳ፣ በገጽ 566 የገጽ ግርጌ ማስታወሻ “ከምሳ በኋላ ዘሪሁን ወደ ነበረበት አካባቢ ለምን እንደሄደ አልነገረኝም። የእዚን ጊዜ የትንንሾች ነገር አይታወቅም ብሎ እንደ ዋዛ ያልፈዋል። ይህ ነው የአንዳርጋቸውና የወንድሙ “የዓይን ዕማኝነት”። በሌላ ገጽ ይኼንኑ ወንድሙን፣ “በትልቅ ኃላፊነት”፣ በስፖርት ሜዳ ላይ የሰበሰባቸውን የጉለሌ ታዳጊ ወጣቶች የኢሕአፓን ማልያ በማስለበስ ለሜይ አንድ ቀን ሲቀረው እ.ኤ.አ. 1976  ሠልፍ ያዘጋጀና ያሠለፈ “ጀግና” በማለት በኩራት ያወድሰዋል። በእዚያ ቀውጢ ቀን ስንት ሕፃናት ቤታቸው እንደተመለሱ ቤት ይቁጠረው! በዚህ ዓይነቱ ምስክር ላይ በመመሥረት ነው፣ አንዳርጋቸው ጽጌ የውሸት መርዙን የሚረጨው። በእንደዚህ ዓይነት ማስረጃ ነው ታሪክ እየጻፍኩ፣ ትውልዱንም እያስተማርኩ ነው የሚለው። በዚህ አላለቀም። በአንዳርጋቸው ጽጌ ወሬ ላይ በመንተራስ አቶ ክፍሉ ታደሰም ይህንኑ ልብ ወለድ ትርክት አንዳርጋችው ጽጌ (የአክስቱ ልጅ) ስለነገረኝ ትክክል መሆን አለበት በሚል ግምት በመጸሐፉ ዘግቧል።

8. በመጨረሻ ገጾቹ ላይ ጸሐፊው (ገጽ 662) እኔ ከአገር የወጣሁት በእናቱ መላና የእሱ ቤተሰብ ባለው ግንኙነት እንደሆነ ጽፏል። ይህም ሌላው ልብ ወለድ ነው።  ለትረካው እሱ እንደሚለው ይበልጥ ሼክስፒሪያን ፍፃሜ ይሰጠዋል ብሎ ገምቶ ይሆን? ሁኔታውን የሚያውቁ ሰዎች በሕይወት አሉ። ይታዘቡኛል ብሎ እንኳን አለማሰቡ የሚያስደንቅ ነው። በታሪክም፣ በሁኔታዎችም፣ በገጠመኞችም፣ በዘመድም፣ በጓደኛም መዋሸቱን ሙያ አድርጎ ይዞታል? ሌላም፣ ሌላም አለ። ስለእኔ በዚሁ ላብቃ።

በዚህ አጋጣሚ ሳልገልጽው የማላልፈው ሌላ አጠቃላይ እውነት አለ። “የስልሳዎቹ ትውልድ” ከሚባለው ውስጥ  ለአገሪቱ ጭቁን ሕዝቦች በእውነት የወገኑ ወጣትና ምሁራን ነበሩ። ይህንን ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ በየአቅጣጫውና በየጎራው እየተደራጁ ብዙ ባትተዋል፣ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ስለዚህም ሊከበሩ ይገባል። ስለዚህ ትውልድ ድርሻ በአዎንታና በአሉታ መልኩ ገና ብዙ የሚጻፍና እስካሁንም ከተጻፉት የምንማረው ይኖራል። በአገራችን ታሪክ በተደጋጋሚ እንደታየውና ዛሬም በተመሳሳይ የአገሪቱን የፖለቲካ መድረክ እያጠለሸ ያለው፣ ሐሳብንና ግለሰብን ያለ መለየትና የሐሳብ ልዩነትን ያለ መቀበል አባዜ በሰፊው እያጠላለፈን ይታያል። ከዚህ አዙሪት ለመወጣት ከሁሉም አቅጣጫ ጥረትና የፖለቲካ ብስለት ያስፈልጋል። ካለፉት የፖለቲካ ታሪካችን የምንወስደው ትምህርት ስለአሁኑ የአገራችን ሁኔታ ግንዛቤ ብርሃን ሰጪና አስተማሪ መሆን አለበት እላለሁ።

በዚህ አቅጣጫ አንዳንድ ጸሐፊዎች በጽሑፍ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሌላውን ሰው ስም በማንሳት የፈለገውን ትርክት ያለ ምንም ልጓምና ያለቅንጣት ኃላፊነት፣ ትርክቱ በብዙ አቅጣጫ ሊያመጣ የሚችለውን ችግርና ቀውስ ከህሳቤ ባለማስገባት ሲባትቱ ይታያል። ይህ ብዙ ጊዜ የሚደረገው በጥራዝ ነጠቅነት፣ ያለ ምንም ጥናት፣ ያለ ምንም ማስረጃ፣ ከሚመለከተው ግለሰብ ጋር እውነቱን ለማግኘት ምንም ዓይነት ጥረት ሳይደረግ ነው። ይህ ሥነ ምግባር የጎደለው አሠራር እንደ አንድ የፖለቲካ ትግል ዘዴ ሆኖ በሰፊው አየተሠራጨ ነው። እያንዳንዱ ጸሐፊ፣ ጦማረኛ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስት፣ እንዲሁም ሚዲያዎች ለሚያሳልፉት መልዕክት ይዘት ተጠያቂነትና ኃላፊነት መውሰድ ይገባቸዋል። የሙያ ሥነ ምግባር የሚባልም የግል ልጓምም አለ። የሕግና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ይህን በተለይ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ማደግና በሰፊው መሠራጨት ጋር ተያይዞ የመጣ ስድ “ባህል”፣ ከልማቱ ጥፋቱ እንዳይበዛ ከወዲሁ መስተማር ይገባቸዋል።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከፈረንሣይ ሞንትፐሊዬ ዩኒቨርሲቲ በልማት ፕላንና በኢኪኖሚክ ትንተና በሰኔ 1966 (ጁን 1974) የማስተርስ ዲግሪ ካገኙ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ፋይናንስ ኢኮኖሚስትነት፣ ፕላን ቡድን መሪነት፣ የትምህርት አቅጣጫ ለውጥ ጥናት ለአራት ዓመታት አገልግለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች በፓሪስና በጄኔቫ ከ27 ዓመታት በላይ ሠርተዋል። ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለሕግ የበላይነት በማለት በጄነቫ የኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ) በኋላም ሰመጉ ድጋፍ ኮሚቴ ከሌሎች ጋር በማቋቋም ዕገዛ አድርጓል። አህሬ (AHRE- association for human rights in ethiopia) የሚባል የሰመጉ የድጋፍ ማኅበር ከሌሎች ጋር መሥርተው በቦርድ አባልነት  እያገለገሉ ነው። በአሁኑ ጊዜም የሚኖሩት ፈረንሣይ ውስጥ ነው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻው tecle.zerihoun@gmail.com ማግኘት ይቻላል

Filed in: Amharic