>

በኢሬቻው ማን ተጠቀመ? ማንስ ተጎዳ? (አሊጋዝ ይመር)

በኢሬቻው ማን ተጠቀመ? ማንስ ተጎዳ?

አሊጋዝ ይመር

 

አንድን ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ ወይም ሕዝባዊ በዓል ማክበር በተለይ ለባለቤቱ ትልቅ ደስታንና ሃሤትን ያጎናጽፋል፡፡ በዓላት የሚከበሩት ቢያንስ በዓመት አንዴ እንደመሆኑ ብዙዎቹ በጉጉት ይጠበቃሉ፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንዶቹ የሀገራችን የበዓላት አከባበሮች ከሥርዓት እየወጡ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው በማመዘን ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የሚያሣየው እንደካሮት ቁልቁል እንጂ እንደሸምበቆ ሽቅብ ማደግ አለመቻላችንን ነው፡፡ እንነጋገርበትና ይህን እየተበላሸ የመጣ አካሄድ እናስተካክል፡፡

በቤታችን ውስጥ ካለው ሸፋፋ የበዓል አከባበር ብንጀምር ብዙ እንታዘባለን፡፡ ለስሙ በብሂላችን “ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” ብንልም ብዙዎቻችን ማሰብ ያቆምን ይመስል “የልጄ / (የራሴ) ሠርግ ከእገሌ ሠርግ ካልበለጠ፤ የልጄ ምርቃት ከጎረቤቴ ልጅ ምርቃት ዕጥፍ ድርብ ካልደመቀ፣ የልጄ ልደት ከእገሌ ልጅ ልደት ካልበለጠ፤ የእማዬ ወይ የአባዬ ዐርባና ተዝካር እንዲሁም ሙታመት ከእነገሌ ካልበለጠ፤ የቡጡ ክርስትና የነእንትናን ቤቢ ክርስትና ካላስከነዳ…. ምን ሰው ሆንኩት! ክንዴን ሳልንተራስ! እኔ ወንዱ!” በሚል አጉል ጀብደኝነት እየተነሳን ብዙ ወጪ እንከሰክሳለን – ሩቅ ሳንሄድ በጎረቤታችን የሚገኙ ምንዱባን (ድሆች) ግን የሚቀምሱት ቆሎ አጥተው አፈር ይግጣሉ፤ ቁርና ፀሐይም እየተፈራረቁባቸው ፍዳቸውን ያስቆጥሯቸዋል፡፡ ይህም እንደመጽሐፉ ቃል ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ለሙስና መንሰራፋት ይሄው የከማን አንሼ የፉክክር ጠባያችን ዓይነተኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም መገመት አይከብድም፡፡ ከዚህ አንጻር እንኳን ያለውን አጉል ጠባያችንን ብናስተውል እጅግ የተወሳሰበና በቀላሉ ሊፈታ የማይችል ማኅበራዊ ነቀርሣ ነው፡፡

ወደሌሎች ስንመጣም የሚታየው ስንክሳር ሁሉ የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ አንድ ሃይማኖታዊ በዓል ሲከበር ያስተዋልን እንደሆነ ፈጣሪን ለማመስገንና የዕለቱን ክብረ በዓል በሚመለከት ብቻ ድምቀት ለመስጠት ሳይሆን በሕዝብ ብዛትም ሆነ ለፈጣሪ በመቅረብ ከሌሎች ተሽሎ መገኘትን ማዕከል ያደረገ የታይታ የበዓል አከባበር ፍላጎት በየጊዜው ይንጸባረቃል፡፡ ይህን ማለት የሚያስቸሉን አስረጂዎች በዓላቱ ሊከበሩባቸው ከሚገቧቸው መቼቶች ባፈነገጠ መንገድ ብዙ የቦታ ስፋቶችን ማካለላቸው፣ የሌሎች እምነት ተቋማት አካባቢዎች ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥር ሁኔታ ለማክበር ዳርዳርታዎች መታየታቸውና አንዳንድ ካንጀት ሳይሆን ካንገት የሚመስሉ የይስሙላ አከባበሮች የሚያሳብቁት ከእምነቱ ይልቅ ወደ ባህሉ፣ ከማተቡ ይልቅ ወደ ሆዱ፣ ከነፍስ ይልቅ ወደ ሥጋ እያዘነበልን መምጣታችንን ነው፡፡ ይህንንም እናርምና እንስተካከል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሞኑ ነገራችን ደግሞ ከምንጊዜውም ለዬት ያለና ጠብ ጫሪነቱ ከፈሪ በቀር የሚያገዳድል ነበር፡፡ ፍርሀት ጥሩ ነው በመሠረቱ፡፡ ለምን ብትል መግደል ያማረው ጀግና ሟች ሳይቀርብለት ሲቀር በራሱ ጊዜ ፎክሮ ፎክሮ ይበርድለታልና፡፡ ከዚህ አኳያ የበቀደሙ እሬቻ ሳይቸግር ጤፍ ብድር ዓይነትና የከሸፈ ሥውር ተልእኮ ያነገበ መሆኑ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላውም ዓለም ሳይነገረው የሚገባው እንደነበር መረዳት አይከብድም፡፡ በመሠረቱ ግጭት ፍለጋ ያን ሁሉ የጠብ ድግስ መደገስ ብልግናም ማይምነትም ነው፡፡ የነዚህ የአእምሮ ድኩማን ‹ሰዎች› ድርጊት የሚጠቁመው ብቸኛ ነገር ዓለም ወደፊት ስትበር እነሱ ግን በብርሃን ፍጥነት የኋሊዮሽ መክነፋቸውን ነው፡፡ ከነዚህ ጋር መኖር በውነቱ ይቆጫል፡፡ እውነቴን ነው እኔም እነሱም መሄጃ አጥተን እንጂ ቢኖረን በየፊናችን በሄድንና አንዳችን አንዳችንን በተገላገልን – ችግሩ አንችልም፡፡ ኒኩለር ያሳዩን መሰላቸው ይሆን? አትታዘቡኝና የኒኩለር ቦምብ ቢኖራቸው ምን ያደርጉን ይሆን? አንዲትም ሌሊት አዲስ አበባ ላይ አያሳድሩንም፡፡ አሁንም በዚህ ከቀጠሉ በስድስት ወራት ውስጥ ብዙ ተዓምር ያሳዩናል፡፡ እሱ ይጠብቀን እንጂ፡፡

አንድ በዓል ሲከበር ደስ የሚለው በቦታው ነው – ለዚያውም ሳይደጋገም በብርቅነቱ አንድ ጊዜ ብቻ፡፡ ሁሉም ነገር ደስ የሚለው በግጥም በግጥሙ ነው – አለግጥሙ ሲሆን ይንሻፈፍና ያስጠላል፡፡ ግሸንን ተመቸኝ ብለህ ባህር ዳር ላይ አታከብርም፡፡ ቁልቢን ቦታው ሰፋኝ ብለህ ቦሩ ሜዳ ላይ አታከብርም፡፡ አክሱም ጽዮንን ጎንደር ላይ ወይም እዚያው አጠገብ ዐድዋ ላይ አታከብርም – ጣም የለሽ ይሆናል፡፡

አንድ ሰካራም እሪ በክንቱ ላይ ስሙኒ ትጠፋዋለች፡፡ ቸርችል ሄዶ ፍለጋውን ይያያዘዋል፡፡ ሰው ሊያግዘው “የት ነው የጠፋብህ?” ቢለው እሪ በከንቱ እንደሆነ ይነግረዋል፡፡ “ታዲያ እዚህ ለምን ትፈልገዋለህ?” ቢለው “እዚህ መብራት አለ፤ እዚያ ግን ይጨልማል” ብሎት ዕርፍ፡፡ ያልተገናኝቶ ነው፡፡ የበዓል ቦታ ደብረ ዘይት የቆሪጥ ግቢ – አሁን ማክበር የተፈለገው አዲስ አበባ፡፡ ቆሪጥስ አይቀየማቸውምን? ንቀት ነው!

ሌላ ምሣሌ ልስጥህ፡፡ አንድ ጋዜጠኛ አንድን ሣይንቲስት “ለመሆኑ ወንድን ወደሴት ለውጦ እንዲያረግዝና እንዲወልድ ማድረግ ይቻላል?”ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ሣይንቲስቱም “እሱን ማድረግ ሣይንስ አያቅተውም፤ ይቻላል፡፡ ግን ለምን? ያ ለምን አስለፈገን? ሴቶቻችን እምቢ አሉ?” ብሎ እንደመለሰለት በአንድ ቀደም ያለ ኒውስዊክ ይሁን ታይም መጽሔት ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡

እሬቻን አዲስ አበባ ላይ ማክበር ይቻላል? አዎ፣ በደምብ ይቻላል፡፡ ግን ለምን? ለምን ባልተለመደ ቦታ ማክበር አስፈለገ? ብሎ መጠየቅ የአስተዋይ ሰው ተግባር ነው፡፡ አንዱ ሲወጣ ሌላውም ግር ብሎ እንደሚወጣ የጎረኖ በግ ከደብረ ዘይት ብቻ ሳይሆን ከሞላው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢ ተነቅሎ በመምጣት አዲስ አበባን ለሦስት ቀናት ሥራ ማስፈታትና ምሥኪን ዜጎችንም ለርሀብ፣ ለብርድና ለበሽታ ማጋለጥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይቅርና በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመንም አይጠበቅም፡፡ አንዳንዴ የራስን አንጎል መጠቀምም ካልተጠበቀ ጉዳት ይታደጋልና ለወደፊቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሳይቀር ትዝብት ውስጥ ሳይገቡ አቅምንና ችሎታን ማሳየት እንደሚቻል ጥቂት ቆም ወይም ቁጭ ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ በስሜት መነዳት መከራን እንደሚጋብዝ አለመረዳት ከአበራሽ ጠባሳ ባለመማር በእሳት እንደመጫወት ይቆጠራልና ጃዋርና ገ. መገርሣ፣ ሕዝቅኤልና በቀለ ገርባ በሚቆፍሩት ጉድጓድ ዘው ብሎ ላለመግባት ከወዲሁ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የዱባን ጥጋብ ለመቆጣጠር የዱባን ሥነ ሕይወታዊ ተፈጥሮ ከመረዳት ይጀምራል፤ ነገንም ለመተንበይ ትናንትን ከዛሬ ማነጻጸር አግባብ ነው፡፡ የሁልጊዜ ትናንት እንደሌለ ሁሉ የሁልጊዜ ዛሬም የለም፡፡ ዛሬ ላይ የቆመ ትናንትንና ነገን አያውቅም፡፡ ሦስቱም ይለያያሉ፡፡ አንዳንድ ጅል ሰው ግን እንደዚያች በፋሲካ እንደተቀጠረችዋ ገረድ ይሆንና ትንንሽ ጊዜያዊ ድሎች ናላውን እያዞሩት በስካር በሚናገረው የዕብድ ዲስኩር ለራሱም ለሌላውም ጠንቅ ይሆናል፡፡

አማራውም ሆነ ጉራጌው ወይም ትግሬው አንድን በዓል አስታኮ ኃይሉንና መላ አቅሙን ማሳየት ቢፈልግ ቀላል ነው፡፡ (በዓላትን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም በውነቱ ነውር ነው – ከመነሻው) የመንግሥትን ባዶ ካዝና ለትርኪ ምርኪ ዓላማ እያሟጠጡ አንድ ሳንቲም ለማይገኝበት የፖለቲካ ቅስቀሳ ማዋል ዛሬ ባይሆን ነገ ያስጠይቃል፡፡ በበዓሉ ላይ ማን ምን ተናገረ ያ ሌላ ጉዳይ ሆኖ ያን የመሰለ ግርግርና ሁከት በሰላማዊ ከተማ ውስጥ መፍጠር ለበርካታ ዓመታት ለእስር የሚዳርግ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በዚያ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተው በነበረበት ወቅት እሳት ቢነሳ፣ ምጥ ቢመጣ፣ ሰው ቢታመም፣ ሽፍታ ቢገባና ግድያና ዝርፊያ ቢጀምር (ያልተጠበቀና ያልታወቀ ሌላ ሽፍታ ማለቴ ነው) እንዴት ይኮናል? አገር መግዛት እንደዚህ ነው ወይ? አገርን ማስተዳደር እንዲህ ተሁኖ ነው ወይ? በዚያ ላይ ራሳቸው በባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ በጠባቂ ታጅበው እየተንፈላሰሱ ፊንፊኔም ይበሏት አዲስ አበባ አይቷት ቀርቶ ስሟን እንኳን ሰምቶ የማያውቅን ገበሬና እረኛ በሰላም ከየሚኖርበት ሰብስቦ በማምጣት በርሀብና በርዛት እየቀጡ ስሚንቶ ላይ ማሳደር ህግ አውጭዎቹ፣ ተርጓሚዎቹና አስፈጻሚዎቹ እነሱ ራሳቸው ሆነው ባሉበት ሁኔታ በወንጀል ባያስቀጣ ኃጢኣትነቱ ግን አያጠያይቅም – እናም በዚህ ግፈኛ አሠራራቸው እነሱ ዋጋቸውን ያገኙበታል፡፡ ያኔ ከግብጽ በገፍ የሚሰጣቸው የሀገር ሽያጭ ይሁዳዊ ገንዘብ ገመድ ገዝተው ይሰቀሉበት እንደሆነ እንጂ አይጠቅማቸውም፡፡
በተረፈ በአክራሪዎች የተነዳ ጥቂት ኦሮሞ አዲስ አበባን ስላስጨነቀ ኢትዮጵያ አትፈርስም፡፡ በጩኸት የፈረሰች አንዲት ከተማ ብቻ ናት – ኢያሪኮ፡፡ ያም የሆነው በዘመናዊው ዓለም ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የኦሪት ዘመን ይመስለኛል፡፡ ከዘመን በኋላ ተሰልፋችሁ የዚህችን ፈጣን ዓለም ጉዞ በሩቅ የምትመለከቱ ወገኖቻችን በቶሎ ከእንቅልፋችሁ ንቁ፤ የማንም ብልጣብልጥ መጫወቻም አትሁኑ፡፡ በከርሞ በሬ እንዳረሳችሁ አትኑሩ፡፡ አንድ መቶ ሰው በዓልን ያከበረበት የዘመን ድባብና ሁኔታ በሌለበት በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በሰላም እንዲያከብር መጠበቅ ከየዋህነትም ያለፈ ከፍተኛው ሞኝነት ነው፡፡ በዓልን በቅርብ ያለ ያክብረው፡፡ እጅግ ብዙ ምንጭና ወንዝን ረግጦ ወደ ደረቅ ጣቢያ አዲስ አበባ በመግባት በሣፋ ውኃ እሬቻን ማክበር መሣቂያ መሆን ነውና አስቡበት፡፡ ሁከትን በመፍጠር ሰላምን ማወክ ፈጣሪ አይወደውምና ለሁላችንም ልብ ይስጠን፡፡

Filed in: Amharic