>

የሰንሹ የጦርነት ጥበብ (ጦማር 1) [መስፍን አረጋ]

የሰንሹ የጦርነት ጥበብ (ጦማር 1)

 

 

መስፍን አረጋ

 

 

‹‹በጥበበኛ የጦር አበጋዝ የሚመራ የጦር ሠራዊት በወራጅ ወንዝ ይመሰላል፡፡  ወራጅ ወንዝ ከፍተኛ ቦታን እየለቀቀ፣ ወደ ዝቅተኛ ቦታ እያዘቀዘቀ በመፍሰስ ረባዳ ቦታን ያጥለቀልቃል፡፡  በጠቢብ የጦር አበጋዝ የሚመራ የጦር ሠራዊትም የጠላትን ጠንካራ ጎን እየራቀ፣ ደካማ ጎኑን እሰነጠቀ በመትመም፣ የጠላት ጦር ያልሰፈረበትን የጠላት ግዛት ሳይዋጋ በመቆጣጠር ይንቦራቀቅበታል፡፡  ወራጅ ወንዝ ወደ መዳረሻው የሚፈሰው አወራረዱን ከመሬቱ አቀማመጥ ጋር እያዛመደ ፍጥነቱን፣ ስፋቱንና ጥልቀቱን በመለዋወጥ እንደሆነ ሁሉ ሁሉ፣ በጠቢብ የጦር አበጋዝ የሚመራ ሠራዊትም ወደ ድል የሚያመራው የጠላቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ስልቱን እንዳስፈላጊነቱ በመለዋወጥ ነው፡፡››   ሰንሹ (Sun Tzu)

 

  1. መንደርደርያ
  2. ሰንሹ ማን  ነው?
  3. ሰንሹና ክሎዝቪዝ
  4. ሰንሹና ማኦ ዜዶንግ
  5. ሰንሹና ጃፓናውያን

 

መንደርደርያ

ይህ ጦማር ቻይናዊው ሰንሹ (Sun Tzu) በ 500 ዓ.ዓ. አካባቢ ጻፈው የሚባለውን  የጦርነት ጥበብ (Art of War) የተሰኘውን መጽሐፍ ዋና መሠረት አድርጌ፣ ከተለያዩ ቦታወች ያገኘኋቸውን ተመሣሣይ መረጃወች ጨማምሬ በመሰለኝ መንገድ እንደመሰለኝ አበጃጅቸና አቀነባብሬ የጻፍኩትና ወደ ሃያ በሚጠጉ ጦማሮች (ምዕራፎች) አከታትየ በየጊዜው የምለቀው ጽሑፍ የመጀመርያው ክፍል ነው፡፡  አብሔር ከፈቀደ ደግሞ ሁሉም ምዕራፎች ባነድ ላይ ተካትተው በመጽሐፍ መልክ ይታተማሉ፡፡  

የዚህን ጽሑፍ የመጀመርያ ረቂቅ ጽፌ የጨረስኩት ከሁለት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ባሁኑ ጊዜ ለማውጣት ምን አነሳሳህ ለሚለኝ ደግሞ ዐራቱን ዐበይት ምክኒያቶቸን እነሆ፡፡

  1. የሞት ሽረት ጦርነት አይቀሬነት፡፡  የሚፈልጉት ስለፈለጉት አይመጣም፣ የማይፈልጉትም ስላልፈለጉት አይቀርም፡፡  ለሁሌም የሚበጀው አይሆንምን ትቶ ይሆናልን በመያዝ መደረግ ያለበትን እያደረጉ ዝግጁ ሁኖ መኖር ነው፡፡  የሚታየውን ላለማየት፣ የሚሰማውን ላለመስማት ዓይናችንን ጨፍነን እዝናችንን ካልደፈንን በስተቀር፣ ተወደደም ተጠላም የጦቢያ ብሔርተኞች (በተለይም ደግሞ አማሮች) ጦቢያንና ጦቢያዊነትን ከህልፈት ለመታደግ የሞት ሽረት ትግል የሚያደርጉበት ጦርነት መጀመሩ አይቀሬ ነው፡፡  እንደውም ተጀምሯል፡፡ ፀረ ጦቢያወቹ ወያኔና ኦነግ በመተባበርና በመቀናበር ቃፊሮቻቸውን እያሰማሩ የትንኮሳ ጦርነት ከከፈቱብን ቆይተዋል፡፡ ዐብይና ደብረጽዮን ይዶልቱበን ከጀመሩ ሰንብተወል፡፡ ኦነግ የሚወጋን ደግሞ ስንቅና ትጥቅ ከሚያቀብለው፣ ቁስለኞቹን ከሚያነሳለት በለማ መገርሳ (ጦቢያ ሱሴ) ከሚታዘዘው ከብርሃኑ ጁላ ጦር ጋር በመቀናበር ነው፡፡  ከሁሉም በላይ ደግሞ ያምንነው ያንዳርጋቸው ጽጌ ፀራማራ ፈረስ በደንደሳችን ጥሎ በብአዴን ውስጥ በሰገሰጋቸው ምልምሎቹ አማካኝነት ጀግኖቻችንን ማስጨረሱን፣ አንድነታችንን ማዳከሙን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡  

አሁን ትናንትና ደግሞ የእንቅቡ ታየ ደንድኣ ከምጣዱ ይበልጥ በመንጣጣት ቁርጣችንን ነግሮናል፡፡  የቦረና ተስፋፊወችን አራዊታዊ ጭፍጨፋ ተከትሎ ይከናወን ለነበረው የሞጋሳና የጉዲፈቻ ክንውን (ማለትም ኦቦ ዐብይ አህመድ መደመር ለሚለው ክንውን) የማያሳስት ምልክት የሆነው ይህ ግለሰብ ‹‹ይለይልን›› ብሎናል፡፡  ወደድንም ጠላንም እንደሚለይልን ታየን ታይቶታል፡፡ ታየን ያልታየው ግን እንዲነሳ የቋመጠለት ጦርነት ከተነሳ፣ ጦርነቱ እውነተኛ ቦረኔ ነን ባዮች የሱን ቢጤ ገርባወች ፈንጅ ረጋጭ የሚያደርጉበት ጦርነት እንደሚሆን ነው፡፡  

  1. የዐብይ አህመድ የመከላከያ ድቅረጻ፡፡  ኦነጋዊው ኦቦ ዐብይ አህመድ የኦነግን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ከሠራቸው ዐበይት ሥራወች ውስጥ ቀዳሚው የመከላከያ ዳግም ቀረጻ  ወይም ባጭሩ ድቅረጻ (reformation) በሚል ሰበብ የወያኔ ጦር በኦነጋዊ ጦር (በተለይም ደግሞ አመራሩን) ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ የተካበት ሸፍጡ ነው፡፡  ጎጠኛው ወያኔ ጦቢያን ሲቆጣጠር፣ አገር ወዳድ ጦቢያውያንን ከመከላከያ አመራር ሙሉ በሙሉ አስወግዶ በጎጠኛ ወያኔወች ተካቸው፡፡  ዐብይ ከወያኔ ሲረከብ ደግሞ ኬኘኞችን ብቻ አጎረበት፡፡  

ስለዚህም ባሁኑ ጊዜ ወታደራዊ እውቀት (በተለይም ደግሞ የወታደራዊ አመራር ብስለት) ያላቸው ጎጠኞቹ ወያኔወችና ኦነጎች ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡  በተለይም ደግሞ አማራው ይህ ነው የሚባል ወታደሪዊ መሪ የለውም፡፡ አንድ አሳምነው ቢኖር ዐብይ (እንደኔ ግምት ከገንቦት ሰባት ጋር በመተባበርና በመቀናበር) ገድሎታል፣ የቀሩትን ጥቂቶች ደግሞ ስላሰራቸው ቢለቃቸውም የሚለቃቸው ምንም እንዳይተክሩ ከሞት አፋፍ ካደረሳቸው በኋላ ነው፡፡  ይህ ሁሉ ድርጊት ዐብይና ደብረጽዮን ለወሳኝ ጦርነት የሚያካሂዱት ወታደራዊ ቅድመ ዝግጅት የማያሳስት ምልክት ነው፡፡ 

 በፓለቲካው አንጻር ደግሞ የአንዳርጋቸው ጽጌ ግንቦት ሰባት/ኢዜማ አማራ የለም በሚል ትርክት አማራን የመከፋፈሉንና የማዳከሙን ዘመቻ አጧጡፎታል፡፡  ቀድሞውንም ቢሆን የወያኔወችና ኦነጋውያን የውሸት ትርክት ቁሞ ሊሄድ የቻለው፣ እነ ሙሐመድ ሐሰን፣ አሰፋ ጃለታ፣ ሕዝቅኤል ጋቢሳና የመሳሰሉት አልባሌወች ደግሞ አንቱ ሊባሉ የበቁት፣ የአንዳርጋቸው ጽጌ ገዳይ እስኳድ እነ የሺዋሉል መንግስቱን የመሳሰሉትን ምርጥ ጦቢያውያንን ሥራየ ብሎ እየመረጠ በመቅጠፉ ብቻና ብቻ ነው፡፡     

  1. የአማራውን የጦርነት ክሂሎት ማሳደግ፡፡  ጦቢያውያን በሚከፍሉት ግብር ዘመናዊ የጦርነት እውቀት የሚቀስሙት ፀረጦቢያወቹ ወያኔወችና ኦነጋውያን ብቻ እንዲሆኑ፣ በወያኔ ዘመን ለገሰ ዜናዊ፣ በኦነግ ዘመን ደግሞ ዐብይ አህመድ ያልተጻፈ ደንብ ደንበዋል፡፡  ስለዚህም አማራው ራሱን በመታደግ ጦቢያን ይታደግ ዘንድ፣ የጦርነት ክሂሎቱን ራሱ በራሱ ሊያሳድግ መጣር ግዱ ሁኗል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ደግሞ ለዚህ ጥረት ኢምንትም ቢሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፣ ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልምና፡፡ 

አማራው ካብናቶቹ (ማለትም ካባቶቹና ከእናቶቹ) በቀሰመው ባያሌ የጦር አውድማወች ላይ በተፈተነ፣ አያሌ አሸብራቂ ድሎችን ባጎናጸፈ ዘመን ጠገብ አራት ማዕዘናዊ የጦርነት ጥበብ (ፊታውራሪ፣ ጃዝማች፣ ግራዝማች፣ ደጀን) የተካነ ነፍጠኛ ነው፡፡  ይህን የጦርነት ጥበብ በሌሎች አገሮች (በተለይም ደግሞ በቻይናና በሩሲያ) የጦርነት ጥበቦች ካዳበረው ደግሞ አያስገመገመ ያለውን የሞት ሽረት ትግል ባሸናፊነት የመወጣት እድሉ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ 

አብዛኛው ታሪካችን የርስበርስ ጦርነት ታሪክ በመሆኑ ከፍተኛ የጦርነት ልምድ ሳለለን፣ የቦረኖችን መስፋፋት የዘገቡት የዓለማችን የመጀመርያው ደቦሰብሲነኛ (sociologist) የነበሩትን አባ በሕሬን የመሳሰሉት ሊቃውንቶቻችን ስለ ጦርነት ጥበብ የሚያወሱ፣ የሰንሹን የመሰሉ ጽሑፎች ጽፈው በግራኝ ዘመን ተቃጥለው ለዘላለሙ ጠፍተው ሊሆን ይችላል፡፡  የግራኝ ወረራ ቦረኔወችን በሁለት መንገዶች ረድቷቸዋል፡፡ 

  • በመጀመርያ ደረጃ ያለ ግራኝ ወረራ የቦረኔወች መስፋፋት ሊከሰት ቀርቶ አይታሰብም ነበር፣ ቦረኔወች አባገዳ በሚባሉ የመንጋ ግመሬወች የሚመሩ፣ መግደልም መሞተም ስሜታ የማይሰጣቸው ርህራሄቢስ አረመኔወች እንጅ፣ አንዳችም የጦርነት ጥበብ አልነበራቸውምና፡፡  
  • በሁለተኛ ደረጃ ከኋላ የመጡት ኦነጋውያን አይን በማውጣት ታሪክን እንዳሻቸው እያጣመሙ ራሳቸውን ቤተኛ ሌላውን መጤ እስከማለት የደረሱት ግራኝ ሙሐመድ ታሪካዊ መዛግብትን ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በማወደሙ ነው፡፡   

የመሣርያ ዓይነቶች እስካፍንጫቸው በታጠቁት በኦነግና በወያኔ ዙርያውን ተከቦ በግንቦት ሰባት ውስጥ ውስጡን የሚቦረቦረው መሣርያ አልባው አማራ ባጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን በራሱ ካላጠናከረ፣ በግራኝ ሙሐመድ ዘመን የተፈጸመው በዐብይ አህመድ ዘመን መደገሙ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  የሰንሹ ጽሑፍ በትክክል እንደሚያሳየው ደግሞ የጦርነትን ጥበብ የተካነ ትጥቁ እጅግም የሆነ ሠራዊት፣ እስካፍንጫው የታጠቀን ሠራዊት በቀላሉ ድል እንደሚመታ ነው፡፡ 

 

ሰንሹ ማን ነው?

ሰንሹ ወይም ሰንዙ (Sun Tzu) የሚባለው ግለሰብ (Wu) በሚባለው ያሁኒቷን ሻንግሃይን በሚያጠቃልለው በታላቁ በያንግዚ (Yangzi) ወንዝ አፍ ላይ በሚገኘው የቻይና ጥንታዊ ምሥራቃዊ ግዛት ውስጥ በ 550 ዓ.ዓ አካባቢ የተወለደና ‹‹የጦርነት ጥበብ›› (Art of War) የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፈ የጦር አዛዥ፣ ወታደራዊ ትልመኛ (military strategist) እና ፈላስፋ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡  የሰንሹ የውልደት ስሙ ሰንው (Sun Wu) ሲሆን፣ ሰንዙ (Sun Tzu) ደግሞ ትርጉሙ አለቃ ዙ (master Sun) ማለት የሆነ የክብርና የማዕረግ ስም ነው፣ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ አለቃ ደሰታ ተክለወልድ እንዲሉ፡፡  

ባፈታሪክ መሠረት ሰንሹ የጦርነት ጥበብ የተሰኘውን መጽሐፉን ከጻፈ በኋላ፣ የ ው (Wu) ግዛት ንጉስ የነበረው ሆሉ (Ho Lu) ወደ ቤተመንግስቱ ያስጠራውና ‹‹መጽሐፍህን አንብቤው ወደጀዋለሁ፡፡  የበለጠ ትኩረቴን የሳበው ደግሞ ወታደሮችን ትእዛዝ አካባሪ ስለማድረግ ያወሳህበት ክፍል ነው፡፡  በዚህ ክፍል ላይ የጠቀስካቸው ዘዴወች በርግጥም መሥራት አለመሥራታቸውን እዚህ እፊቴ ባጭር ምሳሌ በተግባር ልታሳየኝ ትችላለህ?›› በማለት ይጠይቀዋል፡፡

‹‹በሚገባ›› አለ ሰንሹ፣ ደረቱን ነፍቶ በመኩራራት፡፡

‹‹በሴቶች ላይ?›› አለ ንጉሱ፣ በመጠራጠር ቅላጼ፡፡

‹‹እንዴታ፣ ምን ችግር አለው?›› አለ ሰንሹ፣ የንጉሱን መጠራጠር ቸል በማለት፡፡

ንጉሱም በቤተመንግስቱ ውስጥ ከሚገኙት አያሌ ውብ ሴቶች ውስጥ ይበልጥ ውብ የሆኑት ሃያወቹ ተጠርተው ከሰንሹ ፊት እንዲቀርቡ አዘዘ፡፡  ሰንሹም ሃያወቹን ሴቶች አስር አስር ሴቶችን ባካተቱ ሁለት ቡድኖች ከፈላቸውና ቡድኖቹን ጭሬ (squad) አላቸው፡፡  ከንጉሱ ቁባቶች ውስጥ በንጉሱ ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑትን ሁለቱን ሴቶች ደግሞ ጭሬ አዛዥ (squad commanders) አደረጋቸው፡፡  

ቀጠለና ደግሞ ሁለቱን ጭሬ አዛዦች ከፊት ለፊት አድርጎ ሁለቱን ጭሬወች በሁለት ረድፍ ከረደፋቸው በኋላ ስለ ሶማያ አያያዝ ደጋግሞ አሳይቶ ‹‹ደረትና ጀርባ በየት በኩል እንደሆኑ ታውቃላችሁ?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡  ሴቶቹም ‹‹ምን ዓይነት ብሽቅ ጥያቄ ነው፣ ሕጻን አደረገን እንዴ›› በሚል እሳቤ ሳቃቸውን በግድ አፍነው ‹‹እናውቃለን›› አሉት፡፡  

‹‹ግራና ቀኝስ በየት በኩል እንደሆኑ ታውቃላችሁ?›› አለ ሰንሹ፣ የሴቶቹን ሁናቴ ከቁብ ሳይቆጥር፡፡

‹‹አወ›› አሉ ሴቶቹ፣ ሳቃቸው ይበልጥ እየተናነቃቸው፡፡

‹‹በጣም ጡሩ›› አለ ሰንሹ፣ በተረጋጋ መንፈስ ኮራ ብሎ፡፡  ‹አሁን እንግዲህ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ወለም ዘለም ሳትሉ ማክበር አለባችሁ፡፡  ደረት ስል ወደ ፊት፣ ጀርባ ስል ወደኋላ፣ ግራ ስል ወደ ግራ፣ ቀኝ ስል ደግሞ ወደ ቀኝ ዙሩ፡፡  ትዛዜ በትክክል ገብቷችኋል?››

‹‹አወ ገብቶናል››

‹‹ወታደሮቸ የታዘዙትን ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው›› አለ ሰንሹ፣ አልፍኝ ተቀምጦ ያስተውለው ወደነበረው ንጉስ ዙሮ እጅ ከነሳ በኋላ፡፡

‹‹አሳየና› አላ ንጉሱ፡፡

ሰንሹ ነጋሪቱን ሦስት ጊዜ ከጎሰመ በኋላ ‹‹ቀኝ› አለ፡፡

ሴቶቹ ግን እንደታዘዙት ወደ ቀኝ በመዞር ፋንታ ሳቃቸው ፈነዳና በቆሙበት ይንከተከቱ ጀመር፡፡

ሰንሹ ግን የሴቶቹ ሳቅና ስላቅ ግድ ሳይሰጠው ‹‹ወታደሮቹ ትዕዛዙን በትክክል ካልተረዱ፣ ጥፋቱ ያዛዡ ነው›› አለና፣ ትዛዙን እንደገና ሦስት ጊዜ ከደጋገመ በኋላ ‹‹ትዛዜ በትክክል እንደገባችሁ እርግጠኞች ናችሁ?››  ብሎ ጠየቀ፡፡

‹‹አወ እርግጠኞች ነን›› አሉ ሴቶቹ፡፡

‹‹እርግጠኞች ናችሁ?››  በማለት በድጋሚ ጠየቀ፡፡

‹‹አወ እርግጠኞች ነን›› አሉ ሴቶቹ፣ በተሰላቸ ስሜት ባንድነት በመናገር፡፡

‹‹በጣም ጡሩ›› አለና ነጋሪቱን ሦሰት ጊዜ ከጎሰመ በኋላ ‹‹ቀኝ› ብለ አዘዘ፡፡

ሴቶቹ ግን እንደታዘዙት ወደ ቀኝ በመዞር ፋንታ በሳቅ ፈነዱ፣ ሰልፋቸውም ፈርሶ ተመሰቃቀለ፡፡ 

ሰንሹም ቆጣ፣ ቆፍጠን ብሎ ‹‹ትእዛዞቸ ግልጽ ካልተደረጉ ያዛዡ ጥፋት ነው፡፡  ትእዛዞች ግልጽ ተደርገው በትክክል ካልተፈጸሙ ግን የመስመር መኮንኖች ጥፋት ነው›› አለና፣ ሁለቱ ጭሬ አዛዦች እንዲሰየፉ አዘዘ፡፡

ንጉሱም የሰንሹ ትዛዝ ሰቀጠጠውና ‹‹በቃ፣ በቃ፣ አቁም፡፡  ወታደሮችን ትዛዝ አክባሪ ማድረግ እንደምትችል አይቸልሃለሀ፡፡  እነዚህ ሁለት ሴቶች ግን ነፍሶቸ ስለሆኑ እንዲሞቱብኝ አልፈልግም›› አለ፡፡

ሰንሹ ግን ‹‹ንጉስ አዛዥ እንጅ ፈጻሚ አይደለም፡፡  ማናቸውም የጦር አዛዥ አንዴ ግዳጅ ከተሰጠው በኋላ አፈጻጸሙን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው እሱ ራሱ ብቻ ነው›› አለና፣  ለቀሩት ሴቶች መቀጣጫ እንዲሆኑ የሁለቱን ሴቶች አንገት ሰይፎ ከነሱ የሚቀጥሉትን ሁለቱን ሴቶች ጭሬ አዛዥ አደረጋቸው፡፡  

ከዚህ በኋላ ሴቶቹ ቀሉ፣ ሰሉ፣ ተገሩ፣ ሾሩ፡፡  ቀኝ ሲል ወደ ቀኝ፣ ግራ ሲል ወደ ግራ እየዞሩ የታዘዙትን ሁሉ ወለም ዘለም ሳይሉ በቅልጥፍናና በትክክል መፈጸም ጀመሩ፡፡  ሳቅና ስላቅ በሰጥ ለጥ ተተካ፡፡ ሰንሹ አዛዥ፣ ናዛዥ፣ ገዥ ሆነ፡፡ 

‹‹ወታደሮቸ የታዘዙትን ሁሉ በሙሉ ልብ ለመፈጸም ሙሉ ዝግጁ ናቸው›› አለ ሰንሹ፣ የሰንሹ ድርጊት ወደ ሰቀጠጠው ንጉስ ዙሮ እጅ ከነሳ በኋላ፡፡  ‹‹ከእልፍኝወ ይውረዱና ይዘዟቸው፡፡ ገደል ግቡ ቢሉ ቢሏቸው እንኳን ምንም ሳይፈሩና፣ ቅንጣት ሳያንገራግሩ ገደል ይገባሉ፡፡››

‹በል በቃህ፡፡   አሁን ወደ ቤትህ ሂድ፡፡  እንኳን የተረፉትን ገደል ግቡ ልላቸው፣ የሞቱትም ቆጭቶኛል›› አለ ንጉሱ፣  በመቀፈፍ ስሜት ፊቱን ከሰንሹ በማዞር፡፡

   ‹‹ታዲያ ሴቶቸን ታዛዥ አድርግ ብለህ ለምን አዘዘከኝ?›› አለ ሰንሹ፣ በቅሬታ ስሜት ንጉሱን አንተ በማለት፡፡  ‹‹ለማዘዘህ እንጅ ትዛዝህ ለመፈጽም አለመፈጸሙ ግድ ከሌለህ ንጉስነትህ ምኑ ላይ ነው?›› 

ንጉሱም የሰንሹን ወታደራዊ ብቃት በመረዳት በመስክ አበጋዝ (field marshall) ማዕረግ የጦሩ ዋና አዛዥ አደረገው፡፡  ሰንሹም ኃያላን የሚባሉትን የንጉሱን አጎራባች መንግስታት ተራ በተራ ድል በመንሳት የንጉሱን ግዛት አስፋፍቶ የተፈራና የተከበረ ታላቅ ግዛት እንዲሆን አደረገው፡፡      

ከንጉስ ሆሉ ተወዳጅ መዝናኛወች ውስጥ አንዱ ከታላላቅ መሳፍንትና መካንንት ጋር የፈረስ እሽቅድድም ቁማር መጫወት ነበር፡፡  ከዕለታት ባንዱ ቀን ንጉሱና አንድ ታላቅ መስፍን እያንዳንዳቸው ምርጥ የሚሏቸውን ሦስት ፈረሶች አቅርበው፣ ሁለት ሁለቱን በምርጥ ጋላቢወቻቸው እያስጋለቡ አሽቀዳድመው፣ ተሸናፊ ምርጥ ቁባቱን ለአሸናፊ አሳልፎ ለመስጠት ተስማሙ፡፡  ንጉሱም ሥርቁባቱን እጅግ ያፈቅራት ነበርና አሳልፎ እንዳይሰጣት በመሰጋት ውድድሩን የሚያሸንፍበትን ዘዴ እንዲጠቁመው ሰንሹን ጠየቀው፡፡ 

‹‹ሰንሹ፣ መጽሐፍህን እንዳነበብኩትና እንደገባኝ ከሆነ፣ በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ዘዴወች ለጦርነት ብቻ ሳይሆን በጦርነት ሊመሰሉ ለሚችሉ ማናቸውም ድርጊቶች (ንግድ፣ ስፓርት፣ ፖለቲካ ወዘተ.) የሚያገለግሉ ናቸው፡፡  ስለዚህም ያንተን ዘዴወች በመጠቀም ይህን ውድድር የማሸንፍበትን መንገድ ልትጠቁመኝ ትችላለህ?››    

‹‹በደስታ፡፡  ነገር ግን ዘዴውን ልጠቁምህ የምችለው የሁለታችሁንም ፈረሶች ጥንካሬወችና ድክመቶች በደንብ ከለየሁ በኋላ ነው፡፡››

‹‹የማሸነፊያውን ዘዴ ጠቁመኝ እንጅ፣ ያሻህን አድርግ›› አለ ንጉሱ፡፡

ሰንሹም በመጀመርያ ሦስቱን የንጉሱን ፈረሶች በእውቅ ጋላቢወች አስገምግሞ ጥንካሬወቻቸውንና ድክመቶቻቸውን አጣርቶ አወቀ፡፡  ቀጠለና ደግሞ ሦስት እርስ በርስ የማይተዋወቁ እውቅ ጋላቢወችን ሰላይነታቸውን ሳያውቁ ሰላይ አድርጎ በተለያዩ ጊዜወች ወደ መስፍኑ በመላክ፣ እያንዳንዱ ሰላይ ሦስቱንም የመስፍኑን ፈረሶች እንዲገመገም ካደረገ በኋላ፣ ግምገማወቻቸውን እያመሳከረ በማገናዘብ ስለ መስፍኑ ፈረሶች ጥንካሬወችና ድክመቶች በደንብ ተረዳ፡፡  በዚህም አንደኛው የንጉሱ ፈረስ፣ አንደኛ ከሚባለው የመስፍኑ ፈረስ ጋር፣ ሁለተኛው የንጉሰ ፈረስ፣ ሁለተኛ ከሚባለው የመስፍኑ ፈረስ ጋር፣ ሦስተኛው የንጉሱ ፈረስ ደግሞ ሦስተኛ ከሚባለው የመስፍኑ ፈረስ ጋር ከሞላ ጎደል እኩል እንደሆኑ ተገነዘበ፡፡     

‹‹እህሳ›› አለ ንጉሱ፣ ሰንሹ ጥናቱን ማጠናቀቁን ሲነግረው፡፡

‹‹አርግ የምልህን ካደረክ ያለ ምንም ጥርጥር ታሸንፋለህ›› አለ ሰንሹ፡፡

‹‹ለማሸነፍ ስል የማላረገው የለም፡፡››

‹‹ያንተን ሦስተኛ ደረጃ ፈረስ፣ ከመስፍኑ አንደኛ ደረጃ ፈረስ ጋር፣ ሁለተኛ ደረጃ ፈረስ ከመስፍኑ ሦስተኛ ደረጃ ፈረስ ጋር፣ አንደኛ ደረጃ ፈረስ ደግሞ ከመስፍኑ ሦስተኛ ደረጃ ፈረስ ጋር አጋጥማቸው፡፡›

ንጉሱም ሰንሹ እንደመከረው በማደረግ የመጀመርያውን ወድድር ተሸንፎ የሚቀጥሉትን ሁለቱን በማሸነፍ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ፡፡

‹‹አሳይቶ መንሳት ይሉሃል ይሄ ነው፡፡  ትልቁን ለማግኘት ትንሹን መጨደድ (ጭዳ ማድረግ)›› አለ ሰንሹ፡፡ 

 

ሰንሹና ክሎዝቪዝ

የሰንሹ ‹‹የጦርነት ጥበብ›› በዚህ ጉዳይ ላይ ከተጻፉት (በትክክል ለመናገር ደግሞ ተጽፈው ከተገኙት) ጽሑፎች ውስጥ ቀዳሚው ከመሆኑም በተጨማሪ በቅልብጭነቱ፣ በግልጽነቱ፣ በጥልቀቱና በምጥቀቱ ተወዳዳሪ የለውም፡፡  በጦርነት ላይ ከተጻፉት አያሌ ጽሑፎች ውስጥ ከሰንሹ ጽሑፍ ጋር በመጠኑም ቢሆን ለንጽጽር የሚቀርበው ፕሩሲያዊው ካል ፎን ክሎዝቪዝ (Carl Von Clausewitz) ‹በእንተ ጦርነት›› (On War) በሚል ርዕስ በ 1830 ዓ.ም (ማለትም የሰንሹ ጽሑፍ ከተጻፈ ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ በኋላ) የጻፈው ነው፡፡  የክሎዝቪዝ ጽሑፍ የሰንሹን ጽሑፍ ያህል ምሉዕና ምጡቅ ካለመሆኑም በላይ፣ በብዙ መንገዶች ሊተረጎሙ በሚችሉ ግልጽነት በጎደላቸው አሻሚ ሐሳቦች የተሞላ ነው፡፡

በተጨማሪ ደግሞ የክሎዝቪዝ ዋና ሐሳብ ከሰንሹ ዋና ሐሳብ ጋር ፍጹም ይቃረናል፡፡  በሰንሹ እሳቤ መሠረት ‹‹ከጦርነት፣ በተለይም ደግሞ ከረዥም ጦርነት የተጠቀመም ሆነ የሚጠቀም ሕዝብም ሆነ ሐገር የለም፡፡  እውነተኛ ድል ማለት ያለ ምንም ደም የሚገኝ ድል ነው፡፡ ደም አፍስሶ፣ አጥንት ከስክሶ፣ ንብረት አውድሞ የሚገኝ ድል፣ የደም ካሳ እንጅ ድል አይባልም፡፡  ትልቁ የጦርነት ጥበብ ሳይዋጉና ደም ሳያፈሱ ጠላትን ድል መምታት ነው፡፡ ጥበበኛ የጦር መሪ የሚዘምተው ከውጊያ በፊት አስቀድሞ የረታውን የጠላት ሠራዊት ለመማረክ ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም ይበልጥ ማትኮር የሚያስፈልገው ጠላት ከመደራጀቱ በፊት እንዳይደራጅ፣ ከመታጠቁ በፊት እንዳይታጠቅ፣ ከመዝመቱ በፊት እንዳይዘምት በማሰናከል ላይ ነው፡፡››   

በክሎዝቢዥ እሳቤ መሠረት ግን ‹‹ጦርነት ሲባል፣ የአመጻወች አመጻ፣ የአውሬነት መጨረሻ፣ የኢሰብአዊነት ዲካ በመሆኑ፣ ጠላትን ለማንበርከክ ሲባል፣ ማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ያለ ምንም ገደብና ርህራሄ በሙሉ ጭካኔ ማድረግ እንጅ በወጉ፣ በልኩ፣ በገደቡ የሚባል ነገር በጦርነት ላይ አይሠራም፡፡››  ይህን የክሎዥቪልን ጭራቃዊ እሳቤ ሂትለር በሩሲያውያን ላይ ሙሶሊኒ ደግሞ ባማሮች ላይ በሰፊው ተጠቅመውበታል፡፡ የቦረና ተስፋፊወችም ከሃያ በላይ የጦቢያ ነገዶችን ድምጥማጣቸውን ያጠፉት በዚሁ ጭራቃዊ መንገድ ነበር፡፡ የጌድኦ፣ የደቡብ ማላ (የደቡብ ወሎ) እና የሰሜን ሺዋ ምግባራቸው በግልጽ የሚያመለክተው ደግሞ፣ አሁንም ሊወጉን የሚዘጋጁት በዚሁ ጭራቃዊ መንገድ የቀሩትን የጦቢያ ነገዶች ቴሳቸውን ለማጥፋት ነው፡፡  ስለዚህም ኦነጋውያንን በማያዳግም ሁኔታ መምታት ላማራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አልኦሮሞ ጦቢያውያን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፡፡   

 

ሰንሹና ማኦ ዜዶንግ

የሰንሹ ጽሑፍ ባያሌ ቻይናዊ፣ ጃፓናዊና፣ ሩሲያዊ ታላላቅ የጦር ሰወች በተለይም ደግሞ የጦር ተላሚወች (strategists) እና ስልተኞች (tacticians) ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ ሲሆን፣ ከነዚህም ታላላቅ የጦር ሰወች ውስጥ አንዱና ዋናው የቻይናን ሕዝባዊ ኡምቴካ (Peoples Republic of China) የመሠረቱት፣ የቻይና ወልፈናኝ ድርጅማ (Communist Party of China) መንባሪ (chairman) የነበሩት መንባሪ ማኦ ዜዶንግ (chairman Mao Zedong) ነበሩ፡፡  በተለይም ደግሞ ማኦ ዜዶነግ በእንተ ሽምቅ ውጊያ (On Guerrilla Warfare)፣ በእንተ ረዥም ጦርነት (On Protracted War)፣ የቻይና አብዮታዊ ጦርነት ትልማዊ ችግሮች (Strategic Problems of China’s Revolutionary War)  በሚሉ ርዕሶች የጻፏቸው ተጽእኖ ፈጣሪ ጽሑፎች በሰንሹ መሠረታዊ  ሐሳቦች ላይ የተመረኮዙ ጽሑፎች ናቸው፡፡  

የቻይና ቀይ ጦር (Red Army) ይመራባቸው የነበሩትን ሦስቱን ስልታዊ ትእዛዞች (The Three Tactical Commandments) እና አሥሩን ጀገባዊ (ስነስርዓታዊ) ትዕዛዞች (The Four Disciplinary Commandments) የቻይና አርነት ሠራዊት (People’s Liberation Army) መሥራች ከነበሩት ከ ዙዴ (Zhu De) ጋር በመተባበር ያረቀቁት ማኦ ዜዶንግ ነበሩ፡፡   ሦስቱ ስልታዊ ትእዛዞች የሚባሉት

  1. ጠላት ሲበረታ አፈግፍግ
  2. ጠላት ሲዳከም አጥቃ
  3. ጠላት ሲያርፍ አውክ

የሚሉት ሲሆኑ፣ አሥሩ ጀገባዊ (ስነስርዓታዊ) ትዕዛዞች የሚባሉት ደግሞ

  1. ያለቃህን ትእዛዝ ቅንጣት ሳትጠራጠርና ላፍታ ሳታንገራግር ፈጽም፡፡
  2. የሕዝብ የሆነን አትውሰድ፣ መርፌም ብትሆን፡፡
  3. ከሕዝብ ስጦታ አትቀበል፣ ክርም ብትሆን፡፡
  4. ከሕዝብ ምንም ነገር አተዋስ፣ የግድ መዋስ ካለብህ ደግሞ የተዋስከውን ወዲያውኑ ተጠቅመህ በተዋስክበት ሁኔታ መልስ፣ ካበላሸህም ትክክለኛ ዋጋውን ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  5. ከገበያም ሆነ ከየትም ቦታ ለምትገዛቸው ወይም ለምትሸምታቸው ነገሮች ሁሉ ተገቢ ዋጋቸውን ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  6. በውጊያ ወቅት ላወደምከው ወይም ላጠፋኻው ወይም ለጎዳኻው የሕዝብ ሐብት፣ ንብረትና ሂወት ተገቢውን ካሳ ሙሉ በሙሉ ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  7. የውጊያ ግርግር ለዘራፊ ያመቻልና፣ በግርገሩ የተዘረፈን፣ የተበዘበዘን ወይም የተመዘበረን የሕዝብ ሐብትና ንብረት አስመልስ፣ ማስመለስ ካልቻልክ ደግሞ ተገቢውን ካሳ እራስህ ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  8. ሴት፣ ወንድ፣ ሕጻን፣ አረጋዊ ሳትል ማናቸውንም ሰው ስታናግር ሁልጊዜም በትሕትና አናግር፣ በተቻለህ መጠን ደግሞ እርዳ፡፡
  9. ልጃገረድ፣ ኮረዳ፣ ባለትዳር፣ ፈት፣ ጋለሞታ፣ ሴተኛ አዳሪ ሳትል ሴትን ሁሉ ከልብህ አክብር እንጅ በጭራሽ እንዳትደፍር፡፡  ግዳጅ ላይ ሳለህ ከሩካቤ ሥጋ ፈጽሞ ታቀብ፡፡
  10. ምርኮኛም ሆነ እስረኛ አታጎሳቁል፣ በተቻለህ መጠን ተንከባከብ፡፡

የሚሉት ናቸው፡፡  ከሦስቱ ስልታዊ ትእዛዞችና ካሥሩ ጀገባዊ ትእዛዞች በተጨማሪ ደግሞ፣ ማኦ ዜዶንግ በሰንሹ ሐሳብ ላይ የተመረኮዙትን የሚከተሉን የመሳሰሉ የተለያዩ መመርያወችን በተለያዩ ጊዜወች አርቅቀው ነበር፡፡  

  1. በሰላዮችና በውስጥ አርበኞች (አምስተኛ ረድፎች) አማካኝነት የጠላትን ደካማና ጠንካራ ክፍሎች አጣርቶ በማወቅ፣ ከጠንካራ ክፍሎቹ ርቆ፣ ጠላትን አደናግሮና አደናብሮ የመጨረሻውን ደካማ ክፍል በድንገት ማጥቃት፡፡
  2. አንዳንድ ሰወች የራሳቸውን ማንነትና ምንነት አብጠርጥረው ሲያውቁ፣ ስለባላንጣቸው ማንነትና ምንነት ግን ፍንጭ እንኳን የላቸውም፡፡  አንዳንዶቹ ደግሞ የነዚህ ዓይነት ሰወች ተቃራኒወች ናቸው፡፡ ሁለቱም ዓይነት ሰወች ለጦር አመራር ብቁ አይደሉም፡፡
  3. የውጊያ እቅድ ከውጊያ በፊት አስቀድሞ ቢዘጋጅም፣ ውጊያው በሚካሄድበት ወቅት ከሁኔታወች ጋር እየተገናዘበ መሻሻል የሚችል፣ ካስፈለገ ደግሞ ሙሉ በሙሉ መለወጥ የሚችል ሑሲናዊ (dynamic) (ማለትም ተቀያያሪ) እቅድ መሆን አለበት፡፡  የውጊያ እቅድን ድንጋይ ላይ እንደተጻፈ ኖምሲናዊ (static) (ማለትም ቋሚ) መመርያ ሙጥኝ ማለት ትርፉ የሽንፈት ጽዋን መጎንጨት ብቻ ነው፡፡  የውጊያ ሂደት የውሃ ላይ ኩበት ስለሆነ፣ ሁኔታወች እተገናዘቡ ማጥቃት ወደ መከላከለ፣ መከላከል ወደ ማጥቃት፣ መግፋት ወደ ማፈግፈግ፣ ማፈግፈግ ወደ መግፋት መለዋወጥ አለባቸው፡፡
  4. አየለን ለመታደግ ሲባል ታከለን ሥራየ ብሎ መጨደድ (ጭዳ ማድረግ) ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡  ይህን ዓይነት ጭደዳ አዋጭ ጉዳት ሲባል፣ ከእንዝህላልነት የሚመነጭ የአክሳሪ ጉዳት ተቃራኒ ነው፡፡  በተጨማሪ ደግሞ ከባድ አደጋን ለመከላከል ሲባል ለቀላል አደጋ ራስን ሥራየ ብሎ ማጋለጥ የግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡  ይህን ዓይነት አደጋ አዋጭ አደጋ (calculated risk) ሲባል፣ ምንም የማይፈይድ ከባዶ ዠብደኝነት የሚመነጭ አደጋ ደግሞ አክሳሪ አደጋ ይባላል፡፡   
  5. ታላቁ የጦር መሪ ቀዳማዊ ናፖሊዮን እንዳለው ‹‹ባለም ላይ ያሉት ሁለት ኃይሎች ብቻ ሲሆኑ እነሱም ሰይፈና መንፈስ ናቸው፣ የመጨረሻው ድል ደግሞ ሁልጊዜም የመንፈስ ነው፡፡›› (There are only two forces in the world, the sword and the spirit. In the long run the sword will always be conquered by the spirit.)  በጦርነት ላይ ጦሳር (weapon) (ማለትም የጦር መሳርያ) ከፍተኛ ሚና ቢጫወትም፣ ወሳኙን  ሚና የሚጫወተው ግን ጦሳር ሳይሆን ወኔ ነው፡፡ ስለዚህም ይበልጥ ማትኮር የሚያስፈልገው በጦሳር ጋጋታ ላይ ሳይሆን፣ የራስን ሠራዊት ወኔ እየገነቡ፣ የጠላትን ሠራዊት ወኔ በመስለብ ላይ ነው፡፡
  6. ያለ ምንም ደም ጠላትን ድል ለማድረግ የመጀመርያው አማራጭ የጦርነት እቅዱን ከጅምሩ ማጨናገፍ ሲሆን፣ ይህ ካልተቻለ ደግሞ የጦርነት ወኔው መስለብ ነው፡፡  ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት የችግሮችን ምንጭ የሚያደርቅ፣ ጠላት ለጦርነት ከመሰለፉ በፊት እቅዱን ከጅምሩ የሚያመክን እሱ ታላቅ የጦር መሪ ይባላል፡፡
  7. ጥበበኛ የጦር መሪ አንዱ ትጥቁ ትህትናው ስለሆነ፣ ጠላቱ በትዕቢት ተወጣጥሮ እንዲፈነዳ ያደፋፍረዋል፣ የውድቀት መጀመርያው ትዕቢት ነውና፡፡

 

ሰንሹና ጃፓናውያን

የቻይናዊው የሰንሹ ጽሑፍ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረው በራሳቸው በቻይናውያን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በቻይናውያን ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ ጥልቅ እውቀት ባላቸው በጃፓናውያን ምሁሮችና የጦር መሪወችም ጭምር ነበር፡፡  ቁጥራቸው ከመቶ ያላነሰ ጃፓናዊ ምሁሮችና የጦር መሪወች የሰንሹን ጽሑፍ በመሰላቸው መንገድ እያብራሩ ለሚፈልጉት ጉዳይ በሚጠቅም መልኩ ተርጉመውታል፡፡ ከነዚህም ትርጉሞች ውስጥ የሰንሹ ጽሑፍ በንግዱ ዘርፍ ዓለምን ለመቆጣጠር ያለውን ጠቀሜታ በስፋት የሚተነትኑ ትርጉሞች ይገኙበታል፣ ንግድ ማለት ደም የማይፋሰሱበት ጦርነት ማለት ነውና፡፡  ፖለቲካና እስፖርትም እንደዚሁ፡፡ 

የሰንሹ ጽሑፍ ያማረኛ ትርጉም ደግሞ ጦቢያን ከነጭ ፀረጦቢያወችና ካሽከሮቻቸው ወያኔና ኦነግ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ኢኮኖሚዋንም በማሳደጉ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ የተርጓሚው የመስፍን አረጋ ታላቅ ምኞትና ተስፋ ነው፡፡  የሚቀጥለው ጦማር (ምዕራፍ) የሚያተኩረው የጦርነትን አማራጭ የግድ ለመምረጥ በሚያስገድዱ ሁኔታወች ላይ ነው፡፡ 

     

የሚሉት ካለ:- መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic