ዶ/ር ኤልያስ ገብሩ
…አንዳንዴ በዙሪያህ ያለው ሰው ቢቃወምህም እውነትን መመስከር አለብህ። የሚቀየመኝም ካለ መቀየም ይችላል። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ግን የአንድ ድርጅት፣ የአንድ ብሔር ወይም የአንድ ሐይማኖት መለያ ብቻ የሆነ መለያችን አይደለም። የባንዲራውን ቀለሞች እየተጠቀሙ “የኛ ብቻ ነው” ማለት ይቻላል፤ እውነታው ግን ሌላ ነው። ወደድንም ጠላንም እውነት ግን እውነት ናትና!
… ከጅምሩ እነዚህ ሦስት ደማቅ ቀለሞች ምንጫቸው ከላይ ከሳብዓይ ሰማይ ነው። ሰማያዊ ክቡር ማዕድናት ኢያስጴድ (አረንጓዴ እንቁ)፣ ዮጵ(ቢጫ እንቁ) ና ሰርዲኖን(ቀይ እንቁ) የተንጸባረቀ ታላቅ ምልክት (Revelation) ነው። እነዚህ ቀለማት በቅድሚያ ለኖህ የተገለጹ ናቸው። በኖህ ጊዜ ህዝበ-አዳም ሀጥያቱና ማፈንገጡ በዝቶ ስለነበር ኤሎሄም ዓለምን ሙሉ በሙሉ በውሀ አጥለቅልቆ የምድር ገፅ ላይ የነበሩትን ሰዎች በሙሉ አጠፋ፤ ኖህና ቤተሰቦቹ ሲቀሩ።
ኋላም መሬት ውሀዋን መጣ፣ ደርቃ የኖህ መርከብም ከኢትዮጵያ ግዙፍ የአራራት ተራሮች ደርሳ፣ ከየብስ ስትነካካ ለኖህ ቃልኪዳን ተገባለት። አምላክ ድጋሚ ዓለምን በውሀ ሙሉ ለሙሉ እንደማያጠፋ ቃል የገባውም ሰማይ ላይ ቀስተ-ደመናን ከጥግ እስከጥግ በመዘርጋት ነበር። ጎልተው የወጡት ህብረ-ቀለማትም …
፩, አረንጓዴ-(ልምላሜ፣ ተፈጥሮ፣ ፀጋ፣ ሰላም፣ እርጋታ፣ ተመስጦ…)
፪, ቢጫ-(እምነት፣ ተስፋ፣ ራእይ፣ መንፈሳዊነት ጥበብ፣ ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ምህረት…)
፫, ቀይ – (ደም፣ መሰዋእት፣ ነፃነት፣ በደም መተሳሰር፣ ሉዓላዊነት፣ አንድነት…) ነበሩ።
.
የኖህ፣ ከዚያም (በተለይ) የኩሽ ልጆች ይህንን የቃልኪዳናቸውን ምልክት ላይረሱ አከበሩት። የልጅ ልጆች እነ ኢትኤልም ይህንን ምልክት ከልባቸው አውታር አትመውት ዘለቁ።
ኋላ ግን ዲበ-ሰው እስያኤል(ራምሃይ፣ ዙልቀርኒን) እነዚህን ቀለማት በግዛቱ እያውለበለበ፣ ለዓለማት ከ2800 ዓመታት በፊት የባንዲራን ኮንሰፕት አስተዋውቋል። ጦርነቶች ሊዋጋ ሲሄድም ይሄን ባንዲራ እንዲያውለበልቡ ወታደሮቹን አዟል። በኋላም ሰንደቅ ኣላማ በሚል ስሙ የነገሰ ንጉሳችን ሰንደቅ ኣላማ ሲል ሰይሞ የሐገር ዳር ድንበር ሉዓላዊነት መለያ መሆኑን አውጇል። እናም ጥንታዊ ነገስታቶቻችን ከጅምሩም የቀስተ ደመና ቀለማትን ከፍ አድርገው አንፀባርቀዋል።
“በሰማዩ ላይ ቢታይ ቀለም
የሷ ነው እንጂ ሌላ አይደለም!” እንዲል ብላቴናው፤
ባንዲራ…አርማ…መለያ…መኩሪያና መታያ ነው። ቀስተ-ደመና በወጣ ቁጥር የቃልኪዳናችንን ህያውነት ያበስረናል።
ይህንን ዋጋውን ያወቁ እልፎች ባንዲራው ዝቅ እንዳይል ተዋድቀውለታል። ወታደሮች ደም አጥንት ከስክሰው አስከብረውታል። በዓድዋ ላይ የነፃነት ፋና ወጊ በመሆኑ ለእልፎች የተስፋ ስንቅ ሆኗል። በዚህ እልህ ተነሳስተው ነፃነታቸውን የተቀዳጁ የአፍሪካ ሃገራትም በድላቸው አጥቢያ ይህንን ባንዲራ ኮፒ በማድረግ የሃገራቸውን ሰንደቅ ቀርፀዋል።
ባንዲራው ከኛ አልፎ ወደ ሃያ ለሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መለያም ሆኗል!
እንግዲህ …
“እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ፥
ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ?”
እንዳለው ለዚህች ሰንደቅ ብዙዎች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። አማራ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ትግራዋይ፣ ጉራጌ ወዘተ… ሙስሊም፣ ኦርቶዶክስ ፣ ዋቄ ፈና፣ ፕሮቴስታን ወይ ካቶሊክ ሳይለይ ልጆቿ ለነዚህ ቀለማት ተዋድቀዋል። አትሌቶች ላባቸውን ጠብ አድርገው ሰንደቋን ከፍ አድርገውታል። ምንም ቢደረግ ምንም ግን ጸጋው እልፍ ለሆነው ሰንደቅ አላማችን ቢያንስ እንጂ አይበዛበትም።(ለሁላችሁም መልካም የባንዲራ ቀን)