>

ጥልቅ ስሜቶቻችና ሟቾች!!!     (እንዳለጌታ ከበደ)

ጥልቅ ስሜቶቻችና ሟቾች!!!
    እንዳለጌታ ከበደ
ፈረንጆች ዩሎጂ (EULOGY) የሚሉት ቃል አላቸው፡፡ ኢዩሎጂ በአጭር ቃል እንግለጸው ከተባለ ቀብር ላይ የሚነበብ፣ ለሚወዱት ሰው ሲባል በድምጽ የሚገለጽ የሀዘን እንጉርጉሮ ማለት ነው፡፡ አንድ የምንወደው ሰው ከአጠገባችን ሲለይ የምናስደምጠው፣ ከፍ ባለ ስሜት የሚገለጽ በንባብ ወይም በንግግር የሚገለጽ ጥበብም ነው፡፡ ያ ሰው ይህችን ዓለም ተሰናብቶ ሲሄድ ስለፈጠረብን ድንጋጤ፣ ተለይቶን ሲሄድ ስለተዘራብን መንፈስና የሟቹ አለመኖር ስለሚያጎድለው ክፍተት የሚነገርበት ይህ ጥበብ፣ ብዙውን ጊዜ በግጥም ይገለጻል፡፡ አልፎ አልፎም ዜማ ይለብሳል፡፡ ግጥሙም በሟቹ የቀብር ዕለትና ስፍራ፣ ወይም በአርባ ቀን፣ በሙት ዓመት መታሰቢያ ተብሎ በሚዘጋጅ ካርድ ላይ፣ ወይም ሟችን ለመዘከር በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ ይነበባል፤ አንዳንዴም በመጻሕፍት ይታተማል፡፡
…..
ግጥምና  ሀዘን
….
ግጥም እንደ ማንኛውም የጥበባት ዘርፍ ጥልቅ ስሜት የሚወልደው ጥበብ ነው፡፡ የመነካት ውጤት ነው፡፡ በመበሰልሰልና ስለጉዳዩ ከመቆዘም ብዛት የሚወለድ ስሜት ነው፡፡ እጥር ምጥን ባለ መንገድ የሚገለጽ፣ ለራስ የሚበረከት ጸጋ፣ መተንፈሻ፣ መጽናኛና ማጽናኛ እንዲሁም በወጉ ከተከየነ ዘመን የሚሻገር፣ ሥፍራ የማይወስነውና በበዙዎች ልብ በቀላሉ ተንፈላሶ የሚቀመጥ ‹ከራሚ እንግዳ› ነው፡፡ከራሚ እንግዳው ደግሞ ውበት የለበሰ የልቅሶና የሳቅ ባለጸጋ ነው፡፡ ሆኖም፣ ሆን ተብሎ ለመዝናናትና ሣቅ ለማጫር ተብለው የሚደረሱትን ግን አይጨምርም፡፡ ቤት የመታ ሁሉም ግጥም አይደለም፡፡
ሰው በሕይወት ሳለ ከሚያስተናግዳቸው ከባድና መራር ስሜቶች መሃል አንዱ የሚወደው ሰው ከጎኑ በሞት ሲለየው፣ ለዓመታት የደከመበት ከንቱ ሲሆን፣ የሰበሰበው ሲበተን፣ ባመነው ሰው ሲከዳ፣  ውርደት ሲደርስበት፣ ፈተናውን ማለፍ ሲያቅተው…የሚሰማው ስሜት ነው፡፡ በአጠቃላይ ክስረትና ጉድለት ሲሰማው ነው፡፡ ያን የመረረ ስሜቱን፣ ሽንቁሩን ለመድፈን ጸጸትና ሀዘኑን የሚገልጸው በዕንባና በልቅሶ ነው፡፡ ዕንባና ልቅሶውን በተሻለ መንገድ ወይም ከፍ ባለ ደረጃ ለመወጣት፣ ከስሜቱ ጋር የተያያዘ ግጥም ያመነጫል፤ ወይም ሌሎች አመንጭተው ያቆዩለትን ግጥም መጽናኛ ያደርገውና ራሱን ያድስበታል፡፡
…..
ኢትዮጵያና የሀዘን እንጉርጉሮ
…..
እንደሚታወቀው እኛ አገር፣ ከተቀረው ዓለም በተለየ መልኩ፣  ንባብ የማያውቁ  አንዳንድ ሰዎች እንኳን፣ በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ  ‹ነጠላ ግጥም› አላቸው፡፡ አንድ የገጠር ሰው – በተለይ አማራ ክልል ያሉ ገበሬዎችን ብናይ – ከሌላው ያልተዋሰው፣ ለምን ጻፍከው ቢባል ማብራርያ የሚሰጥበት፣ ቤት አመታቱ፣ ሃሳብ አመጣጠኑና ዜማ አወራረዱ ይበል የሚያሰኝ ግጥም ሞልቶታል፡፡
ይህ ግለሰብ ግጥሙን በወረቀት አስፍሮ፣ ሰርዞና ደልዞ ሳይሆን፣ ግጥሙ እንደወረደ አጠገቡ ላለው አዝማሪ ወይም አልቃሽ ይልለታል፡፡ አዝማሪው ወይም አልቃሹ የሃሳቡ መልዕክተኛ ይሆናል፡፡ በነበረው እየቀነሰ ወይም እየጨመረ፡፡ የግጥሙ ባለቤት ንባብና ጽሕፈት አይችል ይሆናል፤ እሱ ግጥሙን ሲለውም በወቅቱ ለተሰማው ስሜት መግለጫ እንዲሆነው  እንጂ የባለቤትነት ፍቃድ ሊጠይቅበት አይደለም፡፡ ጠርቀም ሲልለት በመድበል ሊሳትመውም አይደለም፡፡ ባለማሲንቆው ቢያንጎራጉርበት፣ አልቃሹ ደረት ቢያስደቃበት፣ ዘፋኙ ቢያንጎራጉርበት፣ ሰርገኛ ቢሞሽርበት ግድ የለውም፡፡
በነገራችን ላይ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት በገና ይደረድሩ፣ ግጥም ይደርሱ፣ ቅኔ ለማዳመጥ ቦታና ጊዜ ይመድቡ ነበር፡፡ ይህ ጥበብን የመከየን ነገር እየተቀዛቀዘና መልኩን እየቀየረ የመጣው ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኋላ ይመስለኛል፡፡ በእስካሁኑ ንባቤ እሳቸው ገጥመውታል የተባለ ግጥም አልገጠመኝም፡፡ ጥበበኛው በዘመናዊ ትምሕርት የሚጎለምስበት፣ መከወኛ ጊዜና ቦታ የሚያገኝበት መድረክ በመዘርጋት ግን እንደእሳቸው ቀደም ብሎም አልነበረ፤ ከዚያም በኋላ አልተገኘ፡፡ ኪነጥበብን ራሱን የቻለ ተውሎ የሚገባበት ሙያና ሕዝቡን የሚያገናኝ ድልድይ አድርገውታል፡፡
በኋለኛው ዘመን የነበሩ ሁሉም ነገሥታት መሳፍንት መኳንንት ማለት ያቻላል የሚጠቀሱላቸው ግጥሞች አሏቸው፡፡ በተለይ ተፎካካሪዎቻቸውን የሚተርቡበትና ሃይለኝነታቸውን የሚሰብኩበት፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ አጠገባቸው አንድ የሚወዱት ሰው ሞት ይዞባቸው ሲሄድ ይገጥማሉ፡፡ ምሳሌ ይሆነኝ ዘንድ ሁለት የሀዘን እንጉርጉሮዎችን ለስከትል፡፡ አንዱ  ግጥም የንግሥት የዘውዲቱ ነው፡፡  ዳግማዊ ምኒልክ  በ1906 ዓ.ም ሲሞቱ ዘውዲቲ  ካሰሙት ልቅሶ መሃል በሚከተሉት ስንኞች ላይ ቆዙምባቸው፡፡
          ‹ቀድሞ የምናውቀው የለመድነው ቀርቶ
              እንግዳ ሞት አየሁ ካባቴ ቤት ገብቶ
                   እጅግ ያስገርማል ያስደንቃል ከቶ
      ከሁለታችን በቀር እሚያውቀው ሰው አጥቶ
ብላታ ኋላ እሸት፣ በተደላደለ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲመሩ፣ ትዳራቸውንም ሲያስተዳድሩ ቆዩና ልጆቻቸው በጠና እየታመሙባቸው፣ በወረርሽኝም እየተጠቁባቸው ቀስ በቀስ አለቁ፤ ቤታቸው የልጅ ድምጽ የማይሰማበት ሆነ፡፡ ‹ገና ልጆች ናችሁ፤ ትወልዳላችሁ› የሚል አጽናኝ በዛና፣ በእናቲቱም ማኅጸን አዲስ የሚመጣ ሕጻን ነበራቸውና፣ ይህን ተስፋ ሲጠባበቁ ሚስት በወሊድ ምክንያት የሕይወቷ ፍጻሜ ሆነ፡፡ ብላታም፣ ‹የልጆቼን ሀዘን በሚስቴ አጽናኝነት ችየው ነበረ፤ አሁን እሷ የለች፤ በምን እጽናናለሁ? ሀዘኑንንስ በምን እቋቋመዋለሁ? አሉና፣ ለመመነን ቆርጠው ተነሱ፡፡(ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ከጻፉት ‹የልቅሶ ዜማ› መጽሐፍ ላይ እንዳገኘነው)  ገዳማዊ ሕይወትን ለመሞከር ቆርጠው ተነሱና በራቸው ላይ ወረቀት ለጥፈው መንገዳቸውን በሌሊት ቀጠሉ፡፡ ለቀስተኛ ጠዋት እያለቀሰ ቤታቸውን ቢያንኳኳ መልስ የለም፡፡ ይልቁንስ ሰውየው ትተውት የሄዱትን የሀዘን እንጉርጉሮ አገኙ፡፡
                   እኔ እዘጋዋለሁ ቤቴን እንዳመሉ
                  ቢጢይቋችሁም ከፍቶት ሔደ በሉ፡፡
…..
 የሀዘን እንጉርጉሮ ግጥሞች፣ ገጣሚዎና አጥኚዎች
….
ምዕራባውያን ዩሎጂን ለብቻ ነጥለው ያጠኑታል፡፡ እንዴት እንደሚጻፍም ያስተምሩታል፡፡ ማርጋሬት ታቸር ለሮናልድ ሬገን፣ ኦፕራ ዊንፍሬይ ለሮዛ ፓርክ ሌሎችም ለሌሎች የሰማዋቸው እንጉርጉሮዎች ተጠንተዋል፡፡ በዘመንም፣ በቅርጽም፣ በይዘትም እየከፋፈሉ፡፡ እኛ አገር ግን ሥራዬ ተብሎ የተመረመረ አይመስለኝም፡፡ ስለሀዘን እንጉርጉሮ ማጥናት ማለት ገጣሚያኑ ሞትን የሚመለከቱበትን መነጽር ማየት እንደሆነ የተገነዘብን አይመስልም፡፡
እኛ አገር በነባሩም ሆነ በአዲሶቹ ገጣምያን ዘንድ የሚወዱት ሰው – የቤተሰብ አባል፣ ወዳጅ፣ የሚያደንቁት ሰው – ሲሞት ሀዘናቸውን ለመግለጽ፣ ወዳጅነታቸውን ለማሳየትና የስንብት ቃላቸውን ለማስደመጥ ግጥም መጻፍ በፊትም አሁንም አለ፡፡ የነቢይ መኮንንን ያህል ግን በሥፋትም በጥራትም የሠራ አልገጠመኝም፡፡ ለአንዱ የተጠቀመበትን ቃልና ሃሳብ ለሌላው ሳይጠቀም ስንት አስርት ኣመታትን አሳልፏል? ማዕከላዊ አብሮት ታስሮት ለነበረውም፣ ለአርቲስቱም፣ ለአትሌቱም ይጻፍ በግጥሙ ውስጥ ጎልታ ምሰሶ ሆና የምትታየው ግን ሁሌም ኢትዮጵያ ነች፡፡
ነቢይ ሕዝብ በጋራ ባስተናገዳቸው ጉዳዮች ላይ አዘውትሮ ይጽፋል፤ በተለይ ድንኳን ውስጥ ያለ፣ ወይም በአበባ የተገለጸ ስሜት ግድ የሚሰጠው ይመስላል፡፡ ድንኳን ውስጥ ሀዘንም ደስታም አለ፡፡ ሀዘኑም ደስታውም ግን አደባባይ ላይ የተሰጣ ነው፡፡ ነቢይ አትሌቶች ሮጠው የድል አክሊል ሲቀዳጁ፣ አገር በእልልታ ስትሞላ፣ ብዕሩን እንደሰንደቅ ተክሎ ቃላቱን እንደ ባንዲራ ማውለብለብ ይጀምራል፡፡ እንበል ነቢይ የሀዘን እንጉርጉሮ የሚጽፍላቸው ሰዎችን በምን ይመስላቸዋል፤ ሞትንስ እንዴት ነው የሚያየው? በግጥሞቹ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀምበት ገለጻስ ምንድነው? ከሟቾቹ ጋር የነበረው ቅርበት ምን የመሰለ ነበር? የግጥሞቹ ድምጸትስ እንዴት ያለ ነው? ሁሉም ግጥሞቹ፣ ወይም አብዛኞቹ ምን የሚያስተሳስር ፍልስፍና አላቸው? እሱም ሆነ የሌሎች ገጣምያንና ነገሥታት የሀዘን እንጉርጉሮ ቢጠና የምናገኘው ነገር ይበዛል፡፡
ነቢይ ለተወዳጁ ድምጻዊ ለጥላሁን ገሠሠ ‹አገር ለአገር ያልቅስ› (ስውር ስፌት፣ ቁጥር 2፣ 2006 ዓ.ም) በሚል ርዕስ ግጥም እንደጻፈለት ይታወቃል፡፡ የሚከተሉትን ስንኞች እዩዋቸውና መሰናበቻ ላድርገው፡፡
           ‹ዝሆን ሞቱ ሲቀርብ፣ ከወገኑ ርቆ
            ይሄዳል ይላሉ፣ የእልፈቱን ቀን አውቆ፡፡
           አንተ ያገር ዝሆን፣
       ግን እንዲያ አላረክም፣ መጥተሃል ወደኛ፡፡
           ለአገር ፍቅር ጥሪህ፣ ለእትብትህ መገኛ
           እኛው ማህል አርፈህ፣ ጸንተህ እንድንተኛ ትንሳኤን አልመህ፣ መጥተሃል ወደኛ 
 አንተን ብቻ አየሁኝ፣ በገዛ ዘፈኑ ቀብሩን የሚያስከብር
   አገር ወገን መንግስት ሕዝብ የሚያስተበባብር
                   በገዛ ዘፈኑ ለቅሶውን የሚነገር….› 
Filed in: Amharic