>

የሰንሹ የጦርነት ጥበብ (ጦማር 3) የማጥቃት ትልም [መስፍን አረጋ]

የሰንሹ የጦርነት ጥበብ (ጦማር 3)

የማጥቃት ትልም

 

    መስፍን አረጋ

 

 

     አጉል ጀብደኛ ለመሆን ቸኳይ

     የእሳት ራት፣ ያሞራ ሲሳይ፡፡

 

  1. የጠላትን ቀጠና ለማውደም ሳይሆን፣ ብትችል ያለ ምንም ጉዳት ባትችል ደግሞ በመጠነኛ ጉዳት ለመቆጣጠር ሞክር፡፡  ባድማን ብትቆጣጠረው ምን ይተርክልሃል?  
  2. ጠላትን ለመግደል ሳይሆን፣ ብትችል ያለ ምንም ጉዳት ባትችል ደግሞ በመጠነኛ ጉዳት ለመማረክ ሞክር፡፡  ምርኮኛን መንከባከብ የጠላትን የመዋጋት ወኔ ሲቀንስ፣ ማጎሳቆል ግን ሀሞቱን ያመረዋል፡፡  
  3. አስር ጊዜ ተዋግቶ አስሩንም ድል ማድረግ ትልቅ ገድል ቢሆንም፣ የሚበልጠው ገድል ግን እንበለ ውጊያ ድል ማድረግ ነው፡፡ 
  4. ጠላትን እንበለ ውጊያ ለማንበርከክ፣ እቅዱን ከጅምሩ ማኮላሸት፡፡  ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ምንጮቻቸውን አድርቅ፡፡
  5. የጠላትን የጦርነት ፅንስ ማጨንገፍ ካልቻልክ፣ እንደተወለደ በወሳኝ ኃይል አጥቃው፡፡
  6. ጠላት ከመሠማራቱ በፊት መሠማርያውን ልትዘጋበት ካልቻልክ፣ እየተሠማራ ሳለ በታትነው፡:
  7. ሥምሪቱን አጠናቆ፣ ቦታ ቦታውን ይዞ፣ ለውጊያ ተዘጋጅቶ፣ በተጠንቀቅ ከሚጠባበቅ ጠላት ጋር ለመፋለም የሚዘምት ጦር ለቅርጫ የተዘጋጀ የፋሲካ በሬ ነው፡፡ 
  8. ስለዚህ ጠቢብ የጦር አዛዥ ጠላትን ድል የሚነሳው፣ ከተማውን የሚቆጣጠረው፣ መንግስቱንም የሚገለብጠው ከቻለ ያለ ምንም ውጊያና መስዋዕትነት፣ ካልቻለ ደግሞ ባጭር ውጊያና ባነስተኛ መስዋዕትነት ነው፡፡ 
  9. ምሳሌ፡  በቻይና ዘመነ መሳፍንት የሃን መስፍን የጦር አዛዥ የነበረው ኩንግ በመስፍኑ ላይ ያመጹትን ወንበዴወች ተራራማ ምሽጋቸውን ዙርያውን ከቦ መፈናፈኛ በማሳጣት ቀን ከሌት እያጠቃ አንድ ወር ሙሉ ቢያስጨንቃቸውም ምሽጋቸውን ግን ሊሰብር አልቻለም ነበር፡፡  መስፍኑም ኩንግን ጠርቶ ‹‹እነዚህን ወንበዴወች ዙርያቸውን ከበህ መፈናፈኛ በማሳጣት በሁሉም አቅጣጫ ስለምትደበድባቸው፣ ያላቸው አንድ ምርጫ እስከሞት ድረስ በቆራጥነት መዋጋት ነው፡፡ ጀግኖች ያልሆኑትን ጀግኖች አድርገኻቸዋል፡፡ የሰጠኻቸውን ጀግንነት እንድትወስድባቸው የወንድ በር እንድተከፈተላቸውና በሩ በየት በኩል እንደሆነ በተዛዋሪ አሳውቃቸው›› ብሎ መከረው፡፡  ኩንግም የመስፍኑን ምክር ሲገበርተው (ሲተገብረው፣ በተግባር ሲያውለው፣ apply) አንድ ወር ሙሉ ተዋግቶ፣ አያሌ ወታደሮቹን ሰውቶ ሊሰብረው ያልቻለውን ምሽግ በግማሽ ቀን ውጊያና ባነስተኛ መስዋዕትነት በረጋገደው፡፡  ያገራችንን የጦቢያን ዳር ድንበር ለማስከበር በተደረገው ጦርነት (በተለይም ደግሞ በናቅፋው ግንባር) ከተፈጸሙት አያሌ ስሕተቶች ውስጥ አንዱና ዋናይ ይህ ይመስለኛል፡፡  የናቅፋን ቀበሮ አንበሳ ያደረግነው እኛው ራሳችን ነበርን፡፡
  10. በተራ ቁጥር ሦስት ላይ እንደተገለጸው በትክክል ለመናገር ድል ማለት ያለ ምንም ውጊያ የሚገኝ ድል ነው፡፡  ነቅቶ፣ ተደራጅቶ፣ ታጥቆና፣ ተዘጋጅቶ በንቃት ከሚጠባበቅ ጠላት ጋር በመፋለም ደም አፍስሶ፣ አጥንት ከስክሶ የሚገኝ ረችነት፣ የደም ካሳ እንጅ ድል አይባልም፡፡  ጠላትን እንበለ ደም ማውደም የሚቻለም ደግሞ ዓላማው ተመክሮበትና ተዘክሮበት፣ ትልም (stragegy) ተተልሞበት፣ ስልት (tactic) ተሰልትሞበት ወደ ግብረት (ተግባር) ከመሸጋገሩ በፊት ገና ከጅምሩ እንዳያልም በማድረግ ነው፡፡  ይህን ማድረግ ሳይቻል ቀርቶ ጠላትን የግድ መዋጋት ካስፈለገ ደግሞ ውጊያው መካሄድ ያለበት በሚከተሉት ሁኔታወች መሠረት ነው፡፡ 
    • ጠላትን በሁሉም ዘርፎች (በተለይም ደግሞ በወታደርና በመሣርያ) አስር እጥፍ የምትበልጠው ከሆነ፣ የወንድ በር ብቻ ከፍተህ ክበበውና በሁሉም አቅጣጫወች እያበራየህ ውቃው፡፡
    • ጠላትን በሁሉም ዘርፎች (በተለይም ደግሞ በወታደርና በመሣርያ) አምስት እጥፍ የምትበልጠው ከሆነ፣ በሁሉም አቅጣጫወች እያዋከብክ ግራ አጋባውና በሁለት አቅጣጫወች ሽታ ሽቶ ውቀጠው፡፡
    • ጠላትን በሁሉም ዘርፎች (በተለይም ደግሞ በሠራዊትና በጦሳር ብዛትና ጥራት) ሁለት እጥፍ የምትበልጠው ከሆነ፣ ባንድ አቅጣጫ የምታጠቃው አስመስለህ አብዛኛውን ኃይሉን ወደዚያ ሲያዞር በተቃራኒ አቅጣጫ ውገረው፡፡
    • ከጠላት ጋር በሁሉም ዘርፎች አቻ ከሆንክ፣ በደካማ አቅጣጫው በሙሉ ኃይልህ ነርተው፡፡  ይህን አድርገህም ጠላትን ልትረታ የምትችለው ግን አያሌ ሁኔታወች ሰምረውልህ በለስ ከቀናህ ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም በኃይል የሚመጣጠንህን ጠላት ለማጥቃት ከመወሰንህ በፊት በጥልቅ ልታስብበት፣ በስፋት ልትመክርበትና፣ በምጥቀት ልትዘይድበት ይገባል፡፡ 
  11. በሁሉም ዘርፎች (በተለይም ደግሞ በሠራዊትና በጦሳር ብዛትና ጥራት) እጅግ የሚበልጥን ጠላት ፊት ለፊት መግጠም አጉል ጀብደኝነት ሲሆን፣ ከፊቱ ዘወር ብሎ መሸመቅ ግን ጀግንነት ነው፡፡  አጉል ጀብደኛ ለመሆን ቸኳይ፣ የእሳት ራት፣ ያሞራ ሲሳይ፡፡   
  12. የጠላት ሠራዊት ወታደር ሳይሆን ሆዳደር፣ መኮንኖቹ ደግሞ አገር ወዳጆች ሳይሆኑ ጥቅም አሳዳጆች ከሆኑ ግን ፣ በሠራዊትና በጦሳር እጅግ ቢበልጥም እንኳን ራሱን እራሱ እንዲበላ ማድረግ ይቻላል፡፡ 
  13. ወታደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ማናቸውም ያገር መሪ ወይም ንጉስ አገሩን ለሽንፈት ብሎም ለውርደት ከሚያጋልጥባቸው ድርጊቶች ውስጥ ዐብዮቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
    • በቅናት መንፈስ፣ በፍራቻ ወይም በሌሎች የራስ ወዳድነት ምክኒያቶች የሠራዊቱ አዛዦች ሊሆኑ የሚገባቸውን ግለሰቦች ከሠራዊቱ ማራቅ፡፡
    • በሁሉን አውቃለሁ ባይነት መንፈስ ሙያን ለባለሙያው አለመተው (ያለ ባለቤቱ አይነድም እሳቱ)፡፡  በተለይም ደግሞ የሠራዊቱን አመራር ለሠራዊቱ መሪወች እንደመተው ጣልቃ እየገባ መፈትፈት፡፡ ያገር መሪ መወሰን ያለበት ወደ ጦርነት መግባት አለመግባትን ብቻ ነው፡፡  ከተገባ በኋላ ግን ጦርነቱን በተመለከተ በማናቸውም ጉዳይ ላይ (እቅድ፣ ስምሪት፣ ትልም፣ ስልት፣ ወዘተ.) እጁን ማስገባት የለበትም፡፡ የጦርነት አመራር ሰንሰለታዊ ስለሆነ፣ እያንዳንዷ ሰለበት (የሰንሰለት ቀለበት) ወሳኝ ሚና አላት፡፡  በተጨማሪ ደግሞ ወታደሮች ባዛዣቸው ላይ ሙሉ እምነት የሚኖራቸው፣ አዛዡ (በተሰጠው የግዳጅ አውድ ውስጥ) ያመነበትን ሁሉ ማድረግ የሚያስችል ሙሉ ስልጣን እንዳለው ሲያውቁ ብቻና ብቻ ነው፡፡  የሽንፈት መጀመርያው ጥርጣሬ ነው፡፡  
  14. አምስቱ የድል መንገዶች
    • የራስንም የጠላትንም ጥንካሬወችና ድክመቶች በደንብ ማወቅ፡፡  ራሱን በደንብ አውቆ ጠላቱን በደንብ የማያውቅ ድለኛ (ድል አድራጊ) የመሆን ዕድሉ አምሳ በመቶ ብቻ ነው፡፡  ራሱንም ጠላቱንም የማያውቅ ግን ሁልጊዜም ተሸናፊ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ አጉል ጀብደኛ ከእብድ ሽፍታ ይቆጠራል፡፡  እብድ ቢሸፍት ምን ይተክራል? ፊሪ ቢሸፍት ጓሮ ለጓሮ፣ እብድ ቢሸፍት አምባጓሮ፡፡     
    • ለማጥቃት ምቹ የሆነውን አጋጣሚ ነቅቶና ተግቶ በትእግስት መጠባበቅ፡፡  የድል ቁልፎች ጊዜና ትግስት ናቸው፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል ዲንጋ ይሰብራል፡፡ 
    • በመረጡት መቸት (መቸና የት) መዋጋት፡፡
    • በሚስማሙ፣ በሚተማመኑ፣ በሚከባበሩና፣ በሚተባበሩ መኮንኖች መታዘዝ፡፡  ድለኛ (ድል አድራጊ) ለመሆን ከወቅቱ አመችነት፣ የቦታው አመችነት፣ ከቦታው አመችነት ደግሞ የአዛዦቹ መናበብ የበለጠ ወሳኝ ነው፡፡
    • የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመፈጸም ሙሉ ስልጣን ያላቸው ብቁ መኮንኖች፡፡  የውጊያ ሂደት የውሃ ላይ ኩበት ስለሆነ፣ ሁኔታወች እየተገናዘቡ ማጥቃት ወደ መከላከለ፣ መከላከል ወደ ማጥቃት፣ መግፋት ወደ ማፈግፈግ፣ ማፈግፈግ ወደ መግፋት ባስፈላጊው ፍጥነት መለወጥ መቻል አለበት፡፡  ይከላከል የነበረ ጦር ሊያጠቃ የሚችልበት ቀዳዳ ላጭር ጊዜ ሊከፈትለት ይችላል፡፡ ያጠቃ የነበረ ጦር ደግሞ ወደ መከላከል እንዲዞር ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊገደድ ይችላል፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማከናወን የበላይ ፍቃድ መጠየቅና እስኪፈቀድ መጠባበቅ ማለት፣ የማጀትን እሳት ለማጥፋት ጎረቤትን ለመጥራት መውጣት ማለት ነው፡፡  እሳቱን ለማጥፋት ቢያንስ የመጀመርያውን እርምጃ ለመውሰድ፣ እንኳን ጎረቤትን ቤተኛን በመጥራት ወሳኝ ጊዜ መባከን የለበትም፡፡   

    

የሚሉት ካለ :– መስፍን አረጋ 

 mesfin.arega@gmail.com

 

ያለፈውን ካላነበቡ:- 

የሰንሹ የጦርነት ጥበብ (ጦማር 1) [መስፍን አረጋ]

Filed in: Amharic