>

በተቃርኖ የተሞላው "መደመር"ን አንብቤ ጨረስሁት-!! (ያየሰው ሽመልስ)

በተቃርኖ የተሞላው” መደመር”ን አንብቤ ጨረስሁት!!
ያየሰው ሽመልስ
መጽሐፍ እንኳን መሪ ጽፎት ማንም ቢጽፈው መነበብ አለበት፡፡መሪ ሲጽፍ ደግሞ ለየት ይላል-እያሰበብንም፤እያሰበልንም መሆኑን ለማረጋገጥ ይበጃል፡፡
ድሮድሮ መሪዎች መጽሐፍ የሚያጽፉት ሙዋዕለ-ዘጋቢያቸውን ነበር፡፡ለምሳሌ የአጼ ቴዎድሮስን መጽሐፍ የፃፈው ደብተራ ዘነብ ነው፡፡የአሁኑ መሪያችን እራሳቸው እንደፃፉት ነግረውናል፡፡የዘንድሮዎቹ ደብተራ ዘነቦች መጽሐፉን በሚገባ አርትዖት እንደሰሩለት ግን ከቋንቋና ፊደላቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡ድንቅ አርትኦት ነው፡፡
መጽሐፉ ቆንጆ ነው-በሕትመት፡፡የደላው የአረብ ሕፃን ይመስላል፡፡ሀብታም ሲሆን አሳትመዋለሁ ያልኩትን መጽሐፍ የሚያህል ጥራት አለው፡፡ሎል!
ሲነበብ ግን ትዕግስትን ይፈትናል፡፡እርስበርሱ የሚጣረስ፣አንዱ አንዱን የሚነክስ መከራከሪያ እያመጣ የአንዲት አገር መሪ ድርሰት መሆኑ ይቅርና መጽሐፍነቱንም ለጥርጣሬ የሚዳርግ ነው፡፡
ደፈር ብለን እንናገረው ካልን፤ደራሲው የፖለቲካል ኢኮኖሚ እውቀት እንደሌላቸው በአደባባይ ያመኑበት መጽሐፍ ነው፡፡በተለይ Government, State, nation state, state formation, nation building, nationalism ወዘተ ስለሚባሉ ጽንሰሐሣቦች ግማሽ ገጽ እንኳን አንብበው እንደማያውቁ ያሳብቃል፡፡ለምሳሌ በGovernment ትርጓሜ ስለ State ደጋግመው ይጽፋሉ፡፡ስለ nation building እያወሩ የ nation stateን ትንታኔ አምጥተው ይቀረቅሩበታል፡፡ከሁሉም ደግሞIdeological ትንተና ባይሰጡ መልካም ነበር፡፡ፖለቲካዊ ሊብራሊዝምንና ሶሸሊዝምን፣ ከግለሰብና ከገበያ ጋር እያምታቱ፣ በሪያሊዝም ቦታ ሊብራሊዝምን እየፃፉ የተረኩት ነገር ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው፡፡
የኢኮኖሚ ‹ትንታኔያቸው› ደግሞ የበለጠ አስተዛዛቢ ነው፡፡‹‹ዋነኛ የኢኮኖሚ ችግራችን የሥርዓት ጉድለት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል›› የሚል ዐረፍተነገር ደጋግሞ ተጽፎ፤ደጋግሜ አንብቤውም አልገባህ ብሎኛል፡፡ወደማውቃቸው ኢኮኖሚስቶች ብደውልም፣ አሳስቀው መለሱኝ፡፡
ጠሚሩ 29 ሚሊዮን ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ሕዝብ፣80 ሚሊዮን ገበሬ፣ኑሮ የመረረው ከተሜ የሚመሩ መሆናቸውን ትተው፣የአንድ የደላው ንጉስ ባለሟል ሆነው የፃፉት ነው፡፡በመጽሐፉ ውስጥ የጤና ፖሊሲ የለም፡፡የኢንዱስትሪ ማሻሻያ አማራጭ አልቀረበም፡፡የአገሪቱን የፖለቲካ ተቃርኖዎች  (ብሄርና ዜግነት) ማስታረቂያ መስመር አልተጠቆመም፡፡ቢያንስ በመንግሥታዊ ሥልጣናቸው የሚያገኙዋቸውን አሀዛዊ መረጃዎች በመጠቀም  ይተነትናሉ ብሎ የጠበቀ አንባቢ፣ሆድ ይብሰዋል፡፡በአጠቃላይ ለቅዳሜ ህትመት አርብ ከሰዓት ተሯሩጦ አምድ እንደሚሞላ ሰነፍ ጋዜጠኛ ሆና የተዘጋጀች መጽሐፍ ነች፡፡ደፋር ድምዳሜዎችም ሞልተውታል፡፡
እርስ በርሷ ያላት መቃረን ደግሞ አስገራሚ ነው፡፡ተቃርኖው ከነባራዊው የጠሚሩ አቋምና እዛው መጽሐፉ ላይ ካሉ ሐሳቦች ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ጥቂት እንመልከት፤
ተቃርኖ 1-‹‹ኢትዮጵያዊያን…ማንነታቸው እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ እንዳይለያይ ሆኖ የተዋደደ ነው›› ገጽ iv
          ‹‹ኢትዮጵያዊያን ባለመዋደዳችን አገራችንን…ለትርምስ ዳርገናታል›› ገጽ iv
           ‹‹ዴሞክራሲን ማስፈን ያልቻልነው የወንድማማችነት እሴት ደካማ በመሆኑ ነው››
ተቃርኖ 2-  ‹‹የመደመር ዋነኛ  ዓላማ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን ድሎች ጠብቆ ማስፋት ነው››ገጽ          54
             ‹‹በትናንት ላይ ማተኮር የመደመር እንቅፋት ነው›› ገጽ 36
ተቃርኖ3- ‹‹መደመር በሌሎች እና ታሪክ ላይ ማላከክን አይወድም›› ገጽ 59
       ‹‹እዚህ ለደረስንበት ሁሉ ተጠያቂው የቀደመው መንግሥታትና ልሂቃን ናቸው›› ከገጽ13-238
ተቃርኖ 4- ‹‹መሪዎች አዲስ ሕልም ይዘው ሲመጡ በሞገደኛ ሕዝባቸው ይጨናገፋል፤አጼ ቴዎድሮስ እንደምሳሌ››
                   ‹‹የመሪነት ብቃት የሚወሰነው ሕልምን ወደ ሕዝብ ማድረስ በመቻል ነው››
ተቃርኖ 5- ‹‹መደመር አገር በቀል እሳቤ ነው›› ገጽ ii
           ‹‹መደመር ካለፉት ዓመታት ስኬት [ከአብዮታዊ ዴሞክራሲና ሶሻሊዝም] እና ውድቀት የሚማር ነው›› ገጽ 107
ተቃርኖ 6- ‹‹የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥትነት  የቀጠለው በተቋማት ብርታት ነው›› ገጽ 110
‹‹የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት  ሙያዊ ብቃታቸው ዝቅተኛ በሆነ፣ነጻና ገለልተኛ ባልሆኑ ተቋማት የተደራጀ ነው›› ገጽ 128
ተቃርኖ 7- የቀደሙ  መንግሥታትን ማውገዝ እንደማይጠቅም (ገጽ123) ይገልጽና እዚያው ገጽ ላይ  የቀደሙት መሪዎች ሕዝባዊ ቅቡልነት ለማግኘት የቀደመውን ሐጢአት ይዘረዝራሉ ይልና እራሱ ያወግዛቸዋል፡፡
ተቃርኖ8-  አሽሙረኛነት፣ ለበጣና ሽርደዳ የጠበኝነት ባሕላችን በመሆናቸው እንጋፈጣቸዋለን (153) የሚለውን ስናነብ. ‹‹ጸጉረ ልውጥ፣የቀን ጅብ፣ውስኪ ጠጪ፣መንጋ፣ጀዝባ›› የሚሉ ንግግሮችን የተናረ አሽሙረኛ ደራሲ እንደፃፈው መርሳት አለብን፡፡
ተቃርኖ 9 -‹‹ፌደራላዊ ሥርዓታችን የብሔረሰቦችን መብት አስከብሯል›› ገጽ 116 የሚለውን ስናነብም፣‹‹ ባለፉት 27 ዓመታት እውነተኛ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ አልነበረም›› ሲሉ የተናገሩት ደራሲው መሆናቸውን አናስታውስ፡፡
ተቃርኖ 10-በምዕራፍ አስራ አንድ ላይ የተዘረዘሩት የኢትዮጵያ የ27 ዓመታት (እርሳቸው 28 ነው ያሉት) የኢኮኖሚ ስኬቶች፣‹‹የጨለማማውንና ቆሻሻውን ዘመን የት ጣሉት ያስብላል፡፡
ይብቃኝ!!
ከላይ የተዘረዘሩት ተቃርኖዎች አውዳዊ ንባብ ይጠይቃሉ፡፡እንዲሁ ሲቀመጡ የሚዛመዱ ይመስላሉ፡፡ማንበብ ያስፈልጋል፡፡
በተለይ ስለ ርዕዮትዓለምና ስለ ውጭ ጉዳይ የፃፉትን ነገር በተመለከተ ግን ከአንድ ሳምንት በኋላ በፍትሕ መጽሔት ላይ በዝርዝር እጽፈዋለሁ፡፡እንድታነቡ ከወዲሁ እጋብዛለሁ፡፡
ከገጽ 139 ላይ በወሰድኳት አባባል ጽሁፉን ልቋጨው፡፡
‹‹አንድ መሪ የተከታዮቹን (የህዝቡን) ስሜት ካልተረዳና የሚያስከትለውን ውጤት ካልመረመረ የስሜት ልቀቱ ላሽቋል፣ወይም የስሜት ድቀት ውስጥ ገብቷል ማለት እንችላለን››
Filed in: Amharic