>

የጎንደር ምሕላ...!!! (ዲ/ን ብርሀኑ አድማሴ)

የጎንደር ምሕላ…!!!
ዲ/ን ብርሀኑ አድማሴ
ፍጹም ባላሰብኩበትና ባላቀድኩበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ፈቃድ በዚህ ሰሞን ጎንደር ነው ያለሁት፡፡ ለካ ጎንደር ከመጣሁ እንደዋዛ ዐራት ዐመት ተኩል ሆኖኝ ኖሯል፡፡ ትላንት የጥቅምት መድኃኔዓምንና የጻድቁ የአባ መብዐ ጽዮንን በዓል ከታቦተ መስቀል ጋር በዐመት አንድ ጊዜ ብቻ ወጥተው በሚከበሩበት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በሚያስተዳድሩት በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም ደብር በልዩ ሁኔታ አከበርን፡፡ በጽጌ ምክንያት በታዘዘው ጾምም ምክንያት ቅዳሴው ውሎ ስለሆነ ረቡዕ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በመኅሌት የተጀመረው ክብረ በዓል የተጠናቀቀው ሃያ ዐራት ሰዓት ሊሞላው ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት ነበር፡፡ ከቅዳሴ ውጭ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ከመምህራቸው ከክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን የወረሱትን ዝክር አሁንም  በመምህራቸው ስም ለሕዝቡ ሁሉ ይዘከራሉ፡፡ በዐውደ ምሕረት ሁሉም ሰው ከተጠራ በኋላ ቅዳሴ ውጭ ለሕዝቡ በግንባታ ላይ ከሚገኘው የጉባኤ ቤቱ ሕንፃ ለሊቃውንቱና ለካህናቱም እንዲሁ በተዘጋጀ ቦታ ይደረጋል፡፡ እነየንታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትውፊት ስለሚጠብቁ መጋቢት መድኃኔ ዓለም  በዐቢይ ጾም ስለሚውል ታቦት አውጥው አያነግሡም፤ ዝክሩም በዚህ ወቅት የሚውልበት ምክንያትም ለዚሁ ይመስላል፡፡  የኔታም በደቀ መዛሙርቱ እና በተአዛዚ ምእመናን ወምእመናት በኩል መስተንግዶውን አዳርሱ ይላሉ፡፡ እኔም በዚያው በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ስለነበርኩ ከየኔታ ዝክር ታድሜ በረከቱን ተሳትፌያለሁ፡፡
ያለፈው አልፎ በእግዚአብሔር ፈቃድ በምሕላው ጸሎት ላይ ዛሬ ጧት ተገኘሁ፡፡ በእውነት ያስቀናል፤ ደስ ያሰኛል፤ መንፈስንም ነፍስንም ያድሳል፡፡ አእምሮንም ያቀናል፡፡ ከሲኖዶስ ስብሰባ ረቡዕ ዕለት የተመለሱት የክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፤ የሀገረ ስብከቱ ሠራኞች፣ የጎንደር ታላላቅ ሊቃውንት ከነደቀመዛሙርቶቻቸው ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር አደባባይ ኢየሱስ ፊት ለፊት ላይ ባለችውና ከፋሲል ግንብ 12 በሮች አንዷ በሆነችውና ስንቆም ተብላ በምትጠራው በር ላይ ጊዜያዊ ዐውደ ምሕረት በማድረግ የጸሎት መሪዎቹ ካሕናቱና ሊቃውንቱ ይቆማሉ፡፡ከዚያ ከአደባባ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ምዕራብ በር ፊት ለፊት የሚገኘውን የጃን ተከል ዋርካ ከመሐል አድርገው በፋሲል ግንብ ታክኮ በሚሔደው ዋናው አስፋልት ወንዶቹ በተቃራኒው በኩል ደግሞ ሴቶቹ ይሆኑና ጸሎቱ ይከናወናል፡፡
ጎንደር በዚህ ሳምንት
የጎንደሩ ምሕላ ከተጀመረ ብዙ ቀናት ቢሆንም በዚህ ሳምንት (ከጥቅምት 24 – 30) ግን በኢትዮጵያ ካሉት እጅግ ታላላቅ ገዳማት አንዱ የሆነው የማኅበረ ሥላሴ ገዳም አባቶች ምሕላና ጸሎት ከጾም ጋር ባዘዙት መሠረት በዚህ ሳምንት በጎንደር ሥጋ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዝግ ናቸው፡፡ ከዚህም አልፎ ብዙ የጎንደር ባሕላዊ ምሽት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ የታዋቂዋ የጎንደር የባሕል ውዝዋዜ ንግሥት የምትባለው የአርቲስት እነዬ የባሕል ምሽት ሳይቀር “ይቅርታ ከሃይማኖት የሚበልጥ ነገር ስለሌላ ለዚህ ሳምንት ዝግ ነው” የሚል ማስታወቂያ በመለጠፍ እነደተዘጋ ያየ ሰው ነግሮኛል፡፡ በመሆኑም እንዳለ ከተማዋ በሱባኤ መንፈስ ውስጥ ናት፡፡ እንደ እኔ ሔዶ ላየው ካልሆነ ሙሉ ስሜቱን በጽሑፍ መንገር የሚቻል እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፡፡
የጎንደር ምሕላ ታሪካዊ ዳራ
የጎንደር ምሕላ ራሱን የቻለ ታሪካዊ ዳራ ስላለው በዚህ አጋጣሚ ብናውቀው መልካም መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ የጎንደር ዐረጋውያን ሊቃውንት እንደሚሉት ፤ ለእኔ ደግሞ የደብረ ጽባህ እልፍኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪና ከጎንደር አረጋውያን ሊቃውንት አንዱ የሆኑት ክቡር መልአከ ሕይወት ብርሃኑ አሰፋ እንደ ነገሩኝ የምሕላው ታሪክ የሚጀምረው ከራሱ ከዐፄ ፋሲል ነው፡፡
ዐፄ ፋሲል እንደ ነገሡ ለአምስት ዐመታት ያህል ደንቀዝ ላይ ቤተ መንግሥታቸውን አድርገው ከቆዩ በኋላ በተለያዩ ባሕታውያን ንግርት መሠረት ወደ አሁኗ የጎንደር ከተማ ሲመጡ በዘመኑ የነበረው ጫካው አጅግ ብዙ አራዊት የነበሩበት ስለሆነ ልክ ቤተ መንግሥታቸውን የሠሩበት አካባቢ ሲደርሱ ጎሽ ያገኙና አንድ ጎሽ ይገድላሉ፡፡ በዚያው ቅጽበት አንድ ሥውር ባሕታዊ ይወጣና የቤተ መንግሥታቸው ቦታ ያ ባሕታዊው ሲጸልይ  የኖረበት ቦታ መሆኑን ይነግራቸዋል፡፡ ባሕታዊው ለዐፄ ፋሲል መጀመሪያ አድባራቱን እንዲያስተክል፣ ከዚያም አሁን ቤተ መንግሥቱን የሚዞረውን  አጥር እንዲያሳጥርና ቤተ መንግሥቱን በመካከሉ እንዲያሠራ ከዚያም እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ መታሰቢያቸው ሆኖ እንደሚኖር ይነግራቸዋል፡፡ ባሕታዊው ይህንና የመሳሰሉትን ከነገረ በኋላ ራሱ ወደ ሌላ ቦታ ይሔዳል፡፡ ዐፄውም በታዘዙት መሠረት ሁሉን ያከናውናሉ፡፡
ከዚያ ከተወሰኑ ዐመታት በኋላ ይህ ባሕታዊ እንደገና ይመለስና የእርሱ የማረፊያ ጊዜ መድረሱን ገልጾ ሦስት ነገሮችን እንዲፈጽሙ ያዝዛቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ወር በገባ የመጀመሪያው ሳምንት ምሕል እንዲደረግ ነው፡፡ በምሕላውም ሁልጊዜም  ቅድም በገለጽኳት በአደባባይ ኢየሱስ በኩል ባለችውና አሁን ስሟ “ስንቆም” በምትባለው በር ንጉሡ ከነሠራዊቱ ከቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ልክ አሁን ምሕላውን የሚመሩት አባቶች በሚቆሙበት ቦታ ላይ ከነሠራዊቱ እንዲቆምና የኩርዓተ ርእሱ እና የእመቤታችን ሥዕል እንዲሁም የለበሱ ካህናት ከመስቀል ጋር ወጥተው ሕዝቡም ተሰብስቦ ሁል ጊዜም ለሰባት ቀን ምሕላ እንዲደረግ ያዝዛቸዋል፡፡ ሁለተኛም ራሱ ባሕታዊው ሲሞት አሁንም በቤተ ክርስቲያኑና በጃንተከል ዋርካ መካከል መስቀልኛው ቦታ ላይ እጁን እንደዘረጋ በመስቀልኛ ቅርጽ እንዲቀብሩት አዘዘ፡፡ ሦስተኛም  በሀገር መከራ፣ ችግር፣ ረሀብ ቸነፈር በሆነ ጊዜ ሁሉ ምሕላ እዚህ ባሕታዊው የተቀበረበት ቦታ ላይ  እንዲደረግ ያዝዛቸዋል፡፡  ወዲያው ባሕታዊው ያርፋል፤ ዐፄ ፋሲልም ከመጠን በላይ ያዝናሉ፤ ነገር ግን እንደታዘዙት አድርገው ባሕታዊውን በዚያ ቦታ ላይ አስቀበሩ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወር በገባ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ቀናት በርእሰ አድባራት አደባባይ ኢየሱስ እየቆየም በሁሉም አድባራት የምሕላ ጸሎት ይደረግ ጀመረ፡፡ ከዚህም ሁሉ በላይ ልክ ዘንድሮ እንደሚደረገው እዚሁ ቦታ ላይ በሀገርና በሕዝብ ላይ ትልቅ አደጋና ችግር በተፈጠረ ቁጥር ሁሉ ለተለያዩ ቀናት (ለአንድ ሱባኤ፤ ለሦስት ሱባኤ ወይም እንደዘንድሮ ለ40 ቀናት) ምሕላ ይደረጋል፡፡ በዚህም ብዙ ተአምራትና ቸርነትም ሲደረግ ኖሯል፡፡
በዚህ በየወሩ በመጀመሪያ በሚደረገው ጸሎት በቅርቡ  ከተደረጉ ተአምራቶች አንዱን ብቻ ልንገራችሁ፡፡  አንድ ሰው ልጁ እጅ እግሯ ሽባ ሆኖበት በብዙ መንገድ ቢሞክር አልሳካት ስላለ አዲስ አበባ ወስዶ ሕክምና ለመሞከር ያስባል፡፡ ከዚያም መንገዱን በእግዚአብሔር ፈቃድ ምሕላው ባለበት ሳምንት ይወስናል፡፡ ከዚያም ልጁን ይዞ ወጥቶ አውቶብስ የሚቆምበት ድረስ እርሷን ከመውሰድ  ብሎ  (አውቶብሱ በዚህ ሲያልፍ ልጅቱን እዚህ ላይ ለማሳፈር አስቦ)  ምሕላው የሚደረግበት ቦታ መንገድ ዳር አስቀምጧት ወደ አውቶብሱ ይሔዳል፡፡ ሲመጣ ተቻኩሎ አሳፍሯት ይሔዳል፡፡ አዲስ አበባ ሲደርስ ግን ልጅቱ ድና በእግሯ መራመድ ጀመረች፤ ሙሉ በሙሉ ዳነችም፡፡ ተመልሶም ምስክርነቱን ሰጠ፡፡
 የዘንድሮው ጸሎተ ምሕላ
የጎንደር ምሕላ በታሪክ ከተጀመረበት አንሥቶ በየወሩ በአደባባይ ኢየሱስና በተወሰኑት አድባራት እንዲህ በሀገር መከራን ችግር ሲያጋጥም ደግሞ ለተወሰኑ የሱባኤ ቀናት አሁን በሚደረግበት ቦታ ላይ ለተወሰኑ የሱባኤ ቀናት ይደረጋል፡፡ ከዛሬው በፊት በአደጋ ምክንያት በቅርቡ የተደረገው ደርግ ሊወጣና ኢሕአዴግ ሊገባ ሲል እንደነበር አባቶች ይናገራሉ፡፡ እንደሚናገሩትም ጎንደር ዙሪያ የነበረው የደረግ ጦር በሰላም  ሔደ፤  ኢሕአዴግም በሰላም ገባ፤ ከተማዋና ሕዝቡም ከጥፋትና ከመቃጠል ተረፉ፡፡ ከዚያ ጊዜ ከ1983ዓ.ም. በኋላ እንዲህ ያለ ሱባኤ የተደረገው ዘንድሮ ነው፡፡
ዘንድሮ ድግሞ ከጥንቶቹ የጎንደር ሊቃነ ጳጳሳት ከእነ አቡነ ጴጥሮስ እስከ አቡነ ኤልሣዕ ድረስ ለረጂም ዐመታት አቡነ ቀሲስ በመሆንና በተለያየ ዘርፍ እጅግ በርካታ አግግሎት ሲሰጡ በኖሩት በአረጋዊው አባት በአባ ሙሉ እና በሌሎች አረጋውያን አባቶች ምክርና በጎንደር ወጣቶች አስተባባሪነት ከተማዋ በዚህ ልዩ ሱባኤና ምሕላ ላይ ትገኛለች፡፡ ምሕላው በታሪክም በመልሱም ስለሚታወቅ የጎንደር አረጋዉያን ሊቃውንትም ሆኑ ጎልማሳ ሊቃውንት ለምሕላው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡታል፤ በፍጹም መታመንም ጸሎቱን በጥንቃቄ ያደርሳሉ፡፡ እጅግ ብዙ ዳዊት ይደገማል፤ የቁጥር ጸሎቶች( በተገቢ ቦታቸው እየታደሉ) ይደረሳሉ፡፡ ከዚያም ዐራት መቶ እግዚኦታ ይደረሳል፡፡  ዐራት መቶ እግዚኦታው  መጀመሪያ ሁሉም ሕዝብ ፊቱን ወደ ምሥራቅ አዙሮ አንድ መቶ እግዚኦታ ይደረሳል፤ እንደገና አንድ መቶ ወደ ምዕራብ ይደረሳል፤ ከዚያም መቶው ወደሰሜን፣ መቶውም ወደ ደቡብ በመዞር በዐራቱም ማዕዘን ለሚመለከው አምላክ በዐራቱም ማዕዘን ለኢትዮጵያና ለዐለም ለሚኖሩ ሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብሎ ሰላምን  እንዲሰጥ ይለመናል፡፡ እግዚኦታው ሲደረስም የቁጥር መዛባት ግራ መጋባት የሚባል ነገር የለም፡፡ በጸሎቱ መካከል ምንም ድምጽ የለም፤ ቁጥሮ ደርሶ ፊቱን ወደ ሚቀጥለው አቅጣጫ ሲያዞር በኮምፒዩተር የሚታዘዝ ይመስላል፡፡ እግዚኦታው ዋናው ስለሆነ እንጂ ሌሎች ጸሎቶች ( አድኅነነ ሕዝበከ፤ ሊጦንና መስተብቁዕን የመሰሉት በሥርዓቱ መሠረት) ይደረሳሉ፤ ተአምረ ማርያምም ይነበባል፤ በመጨረሻም አጭር ስብከት ለዐሥር ወይም ለአሥራ አምስት ደቂቃ ተሰጥቶ ብፁዕ ሊቀጳጳሱ ምዕዳን  ሰጥተው ምዕራገ ጸሎት ይደረግና ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡
በዚሁ መሠረት ምሕላው ዐርባው ቀናት እስኪፈጸም ይቀጥላል፤ የማኅበረ ሥላሴው የጾም አዋጅ ግን በአሁኑ ቅዳሜና እሑድ እዚያው አደባባይ ኢየሱስ የከሰዓት ልዩ ጉባኤ በማድረግ ይጠናቀቃል፡፡ እኔም እንደ ፈቃዱ እስከ ሰኞ ጎንደር ስለምቆይ ከምሕላው መሳተፌን እቀጥላለሁ፡፡ ደስ ያለው ሰው በተመቼው ጊዜ መጥቶ ተሳትፎ ጎብኝቶም መመለስ ይችላል፡፡ በርግጥም እንዲህ ያለውንና አክሱም በየወሩ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ቀናት የሚካሔዱትን ዐይነት ምሕላዎች የቻለ ሰው ሥራዬ ብሎ እየሄደ ቢሳተፍባቸው ያተርፋል እንጂ አይጎዳምና የቻልን ብንሳተፍባቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ ካልሆነም ዋናው ጸሎቱ ነውና በያለንበት ለሀገራችንና ለሕዝቡ ደኅንነትና ሰላም በእውነት እንጸልይ፡፡
እንደ ስምዖን ጫማ ሰፊው በሕዝቡ መሐል ተደብቀው አብረው የሚጸልዩትን ቅዱሳንና የሕዝቡንም ንስሐና ልመና ተመልክቶ አምላካችን መዓቱን በምህርት፤ ቁጣውን በትዕግሥት መልሶ መቅሰፍቱን አርቆ ሣሕለ ምሕረት ያውርድልን፤ በጭንቀት፣ በስደትና በመከራ ላሉት ወገኖቻችን እንዲሁም ለመላው የሀገራችን ሕዝብ አምላካችን ሰላሙንና ፍቅሩን ያድልልን፤ አሜን ፡፡
Filed in: Amharic