>
5:13 pm - Friday April 19, 1776

የዚያን ዘመን ሽኩቻ ለዚህኛው ዘመን የጎጥ ፖለቲከኞች ጥፋት ማቻቻያ ማድረግ በህሊና መሸቀጥ ነው!!! (ሳምሶም ዮሴፍ)

የዚያን ዘመን ሽኩቻ ለዚህኛው ዘመን የጎጥ ፖለቲከኞች ጥፋት ማቻቻያ ማድረግ በህሊና መሸቀጥ ነው!!!
ሳምሶም ዮሴፍ
 
እንደኮራ ሄደ እንደተጀነነ
ጠጅ ጠጣ ቢሉት ውሀ እየለመነ
የጎንደር ባላባት ሊጋባ በየነ!
—-
አንድ የዶ/ር አብይ አክራሪ ደጋፊ የሆኑ ምሁር በየትኛው መድረክ ላይ እንደሆነ ባላውቅም ስለሰሞንኛው የሀገራችን ሁኔታ አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር አስተላልፈው በዚህ መከረኛ ዩቲዩብ ተመለከትኩ(አዳመጥኩ) ምክሩም ሆነ ሀሳቡ ጥሩ ነው በአሁኑ ሰዓት በሀገር ቤት ስሙን መጥራት አይደፈሬ የሆነው ጁሀር ላይ እና ግብረአበሮቹ ላይ እርምጃ ውሰዱ ነው፤ ግን የአሸባሪውን ስም መጥራት ያልደፈሩት ምሁር ከእርሱ ጋር አወዳድረው የጀግናውን አርበኛ ሊጋባ በየናን ስም ሲጠሩ ያስገርማልም፤ ያስደነግጣልም፤ ምሁሩ ለምን ሊጋባ በየነን እንደ ምሳሌ መጠቀም እንደፈለጉ ባይገባኝም፤ ሊጋባ በየነ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱን ይናገሩና ከዚያ በኋላ አልጋ ወራሽ ተፈሪ እንደገረፏቸውና ከዚያም በኋላ ሸዋ አልጋ ወራሽ ተፈሪን  እጅ ነሳቸው ይላሉ፤ አልጋ ወራሹ ጥሩ የማኬቬሌ ተማሪ እንደሆኑ ለመግለፅ ብለው መሰለኝ ጀግናውን ሊጋባ በየነን ሰለባ ያደረጓቸው፤ የተሰበሰበውም ሕዝብ ቤቱን በጭብጨባ አናጋው።
ሲጀመር ሸዋ ለኃይለሥላሴ ታዛዥ እና እጅ ነሺ ነበር አልጋ ወራሹን ተፈሪ መኮንን እና ንግስት ዘውዲቱን ያነገሰው ሸዋ ነው፤ ለአልጋ ወራሹ አንገዛም ብለው ሲያስቸግሩ የነበሩት ጎንደር፣ ወሎ፣ ትግሬ፣ እና ጎጃም ነበሩ፤ ..
እነ ራስ ጉግሣ ወሌ፣ ራስ ኃይሉ፣ ንጉሥ ሚካኤል፣ ነበሩ እንጂ ሸዋማ ነገር ዶልቶ ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ያወረደ ነው። ምሁሩ በምን ግንዛቤ ሸዋን እዚህ ውስጥ እንዳስገቡት አልገባኝም፤ ሊጋባ በየነ እንደማንኛውም
የአፄ ምኒልክ ሹማምንት ልጅ ኢያሱ ሰልሟል ኢትዮጵያን የሙስሊም ሀገር ሊያደርግ ነው በሚለው ወሬ ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን እንዲወርዱ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል…
“የሸዋ መኳንንትን ምክር ወደ ተግባር ለመቀየር ቁርጥ ቀን የተያዘው ለመስከረም 17 የመስቀል በዓል ዕለት 1909 ዓ.ም ነበር፤ የልጅ ኢያሱ መንግሥት ወደ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲዞር ቀድሞ ተቆርጧል።
በዙሁ ዕለት ሊጋባ በየነም በአንድ በኩል በሊጋባነታቸው ሚኒስትሮችን፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ መሣፍንት እና መኳንንቶችን ከነ ሠራዊታቸው ወደ ቤተመንግሥት ያስገባሉ፤
እንደውም አቡነ ማቲዎስን እና እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስን ጠርተው  እየመሩ ያመጡት ራሳቸው ነበሩ። በዚሁ ዕለት ጥሪ የተደረገላቸው በግቢው ውስጥ በተተከለው ድንኳን እንደየማዕረጋቸው ተቀመጡ፤ ከዚያ ከንቲባ ወልደጻዲቅ ጎሹ ልጅ ኢያሱን ለመሻር እና ሕዝቡን ለማሳመን በመካሪዎቹ የተዘጋጀውን ጽሁፍ አነበቡ።
ጽሑፉ ተነቦ እንዳለቀ አቡነ ማቲዎስ “ትንሽ ጊዜ ስጡኝና እኔ ራሴ ሐረር ሄጄ ልምከረው ላናግረውና ላስታርቃችሁ” ይላሉ፤
የአቡኑን ሐሳብ እጬጌው ተቃወሙ፤ እጬጌው አክለውም
“የእስላሞቹን የአባ ጅፋርን፣ የነጋድራስ አቡበክርን ልጅ ማግባቱን አልሰሙ ሆነው ነው፤ አሁን ልምከረው የሚሉት?” በማለት በቁጣ ተናገሩ፤ ከዚያም አቡኑ ልጅ ኢያሱን የተከተለና የተቀበለ ውግዝ ይሁን የሚል ቃል አወጡ።
የአቡነ ማቲዎስን ንግግር ተከትሎ ቀኛዝማች ተሰማ ከተማ “ጳጳሱ ልምከር ማለታቸው ስለምን ተጠላ?”በማለት ንግግር  እንደጀመሩ ሊጋባ በየነ አቋርጠዋቸው ጎራዴያቸውን በመምዘዝ ” የእስላም ወገን የሆንክ እንግዲህ ተለይ ” በማለት በፉከራ ይናገራሉ።
የሊጋባ በየነን ፉከራ ተከትሎ ቀኛዝማች ተሰማ አንድ ጥይት ወደ ሰማይ ከተኮሱ በኋላ መሰሎቻቸው ጋር መሸሽ ቢጀምሩም የተለያዩ ሰዎች ጥይት መተኮሳቸውን ይቀጥላሉ። በተፈጠረው ክስተት ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አምስት ሰዎች ይቆስላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱ ቀውጢና አስፈሪ  ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ ሊጋባ በየነ ወደ አዋጅ መንገሪያው  በመሄድ “አሁን የተተኮሰው የደስታ ነው የክፋት አይደለም ባለህበት እርጋ” አሉ። ሁሉንም አረጋግተው እንደውም ጳጳሱ፣ ደጃች ተፈሪ እና ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አድርገው ሁኔታውን አረጋጉ።
ሊጋባ በየነ ለማንም የማይወግኑ ሀገራቸውን የሚወዱ ሰው ለአመኑበት አላማ የሚቆሙ ሰው ነበሩ በ1903 ዓ.ም የልጅ ኢያሱ ሞግዚት የነበሩት ራስ ተሰማ ናደው በሞቱ ጊዜ ልጅ ኢያሱ ሞግዚት አያስፈልግኝም ሲሉ ሊቀ መኳስ አባተ
ቧ ያለው ልጅ ነው ሞግዚት ያስፈልገዋል ብለው በተነሱ ጊዜ ሊጋባ በየነ ከልጅ ኢያሱ ጎን ነበር የየቆሙት።
በ1905 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከጊሚራ ዘመቻ ሲመለሱ
አጼ ምኒልክ በጠና ታመው ስለነበር በቤተመንግሥቱ ውስጥ አንድ ወሬ ይነዛል ይኸውም “ልጅ ኢያሱ ጃንሆይን ከትልቁ ቤተመንግሥት አስወጥተው በቃሬዛ ወደ አንኮበር ሊወስዷቸውና ራሳቸው ከቤተመንግሥቱ ገብተው እንዲነግሡ ምክር ተቆርጧል” የሀሰት ወሬ ነው ይሄንን ወሬ በመስማት የእልፍኝ ዘበኛ ጦር አለቆች ፊታውራሪ ገብረማርያምና ባሻ ደቻሳ ሌሎች ሻምበሎችም ጭምር ልጅ ኢያሱ ከጊሚራ ጦርነት ሲመለሱ አናስገባም ይላሉ፤ በዚህ ጊዜ ሊጋባ በየነ እና በጅሮንድ አሸናፊ በድርጊቱ በጣም ተናደዱ በጅሮንድ አሸናፊ በግምጃ ቤት በኩል፣ ሊጋባ በየነ ደግሞ በፊት ለፊት ቤተመንግሥቱን ማስጠበቅ ይቀጥላሉ።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ጥቂት ቀን እንደቆዩ የካቲት 22 ቀን ግጭት ተፈጠረ፤ የግጭቱ መነሻም የሊጋባ በየነ ጭፍሮች ላይ አስቀድሞ ስለተተኮሰባቸው እንደሆነ ይነገራል።
የልጅ ኢያሱ ወገኖች ከውጭ የእነ ፊታውራሪ ገብረማርያም ወገኖች ከውስጥ ሆነው ተኩሱ ቀጠለ በዚህ ጊዜ ሊጋባ በየነ ከልጅ ኢያሱ ጎን ነበሩ፤ መጨረሻም የልጅ ኢያሱ ወገኖች አሸነፉ።
 የልጅ ኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል ሸዋ ከደጃዝማች ተፈሪ ጋር ተማክሮ ልጄን ከሥልጣን አወረደብኝ ብለው ጦር በሰበቁ ጊዜ በሰገሌው ጦርነት ሊጋባ በየነ ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ጋር በመሆን ከአልጋ ወራሹ ጎን በመቆም ዘምተዋል። የሰገሌው ጦርነት አልቆ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የንግሥና በዓል ላይ ከሰልፈኞቹ መሪ አንዱ ሊጋባ በየነ ነበሩ፤ ለንግሥናው በቤተመንግሥት በተደረገው ግብዣ ላይ ሊጋባ በየነ በቅሎ ላይ ተቀምጠው ነበር ሲያጋፍሩ የነበሩት።
ሊጋባ በየነ በደጃዝማችነት ማዕረግ በባሌ፣ በወላይታ ተሹመው አገልግለዋል፤ ወደ ኋላ አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሥልጣን ጣልቃ አይግቡ ከሚሉት ወገን ነበሩ፤ ግን እሳቸው ጓዳጓዳውን ሳይሆን ፊት ለፊት ይጋፈጡ ነበር፤ እርሱ የአልጋ ወራሽነቱን ሥራ ይሥራ እንጂ በእሳቸው ሥልጣን ለምን ይገባል ባይ ናቸው፤ ወላይታ እያሉ ህዝብ ላይ በደል አድርሰሃል በሚል እና ወደ አዲስ አበባ ወደ ራስ ተፈሪ መልዕክት የሚያመላልስላቸው አሽከራቸው ስለኔ የሚያውቀውን በሚስጥር ያወራል ብለው ተፈርዶበት እንዲታሠር ይደረጋል፤ የእስረኛውን ጠባቂዎችና ቁራኛውን በመጠጥ አስክሮ ያመልጣል። እነዚህ ጠባቂዎችና ቁራኛው ተከሰው ግርፋት ይፈርድባቸዋል፤ ገራፊው ጅራፉ ሲበጠስበት በእጀታው (በጉንድሹ) ስለደበደበው አንደኛው ይሞታል፤ በዚህ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል እና የወላይታን ሕዝብ በድለሃል በሚል ሊጋባ በየነ ተከሰው ተፈርዶባቸው በግዞት ይቀመጣሉ።
በኋላም ምህረት ተደርጎላቸው በወሊሶ በእርስታቸው እንዲቀመጡ ተፈቀደላቸው፤ በወሊሶ እያሉ ለሀብተ ጊዮርጊስ ደብዳቤ ይጽፋሉ ንግሥቲቱ በሕይወት እያሉ ተፈሪ በሥልጣናቸው ጣልቃ ሊገቡ አይገባም፤ በአልጋ ወራሽነታቸው ብቻ ከመጠበቅና ፈንታቸውን ከመወጣት ሌላ በመንግሥቱ ሥራ ጣልቃ አይግቡ፣ የውጭ ትምህርትም እያመጡብን ነው ይሄም ልክ አይደለም እያሉ ከዚህ ነገር እንዲታቀቡ ቢያደርጓቸው እርሳቸውም ጭምር እንደሚረዷቸው ለአባ መላ ይጽፋሉ።
ይህ ነገር በአልጋ ወራሹ ተሰምቶ ደጃች በየነ ሚያዝያ7 ቀን 1917 ዓ.ም ተከሰው በንጉሡ ችሎት ይቀርባሉ፤ የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ከማመን አልፈው ሌላም ትርፍ ቃል ስለተናገሩ እንዲገረፉ ይወሰንባቸዋል፤ 29 ጅራፍ እንደተገረፉ የምኒልክን ስም ስለጠሩና በራስ ስዩምና በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ አማላጅነት ግርፊያው ቆሞ በደጃዝማች አባ ሻውል እጅ እንዲታሰሩ ወደ ሐረር ተላኩ።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ አልጋ ወራሽ ተፈሪ የንግሥና በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ምህረት ስላደረጉ ደጃዝማች በየነም ተለቀቁ።  ከዚያ ቀጥለው ንጉሥ ተፈሪ የጎንደር ገዥ አድርገው ይሾሟቸዋል፤በዚህ ጊዜ ደጃች በየነ “ሀገሬን እንጂ ያሰረኝን መንግሥት አላገለግልም” ብለው ሹመቱን እምቢ አሉ። በዚህ ጊዜ ነው እሄ ግጥም የተገጠመላቸው…
እንደኮራ ሄደ እንደ ተጀነነ
ጠጅ ጠጣ ሲሉት ውሀ እየለመነ
የጎንደር ባላባት ሊጋባ በየነ።
ከሁለት ዓመት በኋላ በ1923 ዓ.ም ደጃች በየነ የኮንታ ገዥ ሆነው ተሾሙ ጣልያን ሀገራችንን በወረረ ጊዜ በራስ ካሣ በሚመራው  ጦር ሥር ዘምተው ለእናት ሀገራቸው ወደቁ።
አፄ ኃይለሥላሴንም በዘንጋቸው እያመለከቱ
“አንተ ጀርባህን፤ እኔ ደረቴን ለሀገር እንሰጣለን” ይሉ እንደነበር ይነገራል።
እኚን የመሰሉ ጀግና ላመኑበት ደረታቸውን ለጥይት የሚሰጡ ከዚህ ዘመን ውርጋጥ ጋር አወዳድሮ ምሳሌ መስጠት ያስገርማል፤ ለአፄ ኃይለሥላሴ አንገዛም ብለው ጦር ሰብቀው የመጡ እያሉ በንግሥቲቷ ሥራ ጣልቃ አይግቡ ባሉ በአልጋወራሹ ጥርስ ተነክሶባቸው የነበሩ እንጂ ሀገርን እንደ ሀገር እንድትቆምም ሆነ ለአልጋ ወራሹ ሥልጣን የበኩላቸውን ተወጥተዋል፤ ታሪካቸውን እንዳየነው ላመኑበት የሚሞቱ እንጂ አድር ባይ አልነበሩም።
የዚያን ዘመን ሽኩቻ አምጥቶ በዚህ ዘመን ምሳሌ ማድረግ ከአንድ ምሁር አይጠበቅም ያውም በተሳሳተ መልኩ።
ክብር ለጀግኖቻችን!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በክብር ትኑር!!!
Filed in: Amharic