>
5:16 pm - Wednesday May 23, 7973

ኦ.ዴ.ፓ በኦሮምያ ምድር በአክራሪዎቹ እንደሚሸነፍ ማወቁ ለብልጽግና ፓርቲ ገፊ ሀይል ሆኖ እንዲቀርብ አስገድዶታል!!! (ዶ/ር አሰማህኝ ጋሹ)

ኦ.ዴ.ፓ በኦሮምያ ምድር በአክራሪዎቹ እንደሚሸነፍ ማወቁ ለብልጽግና ፓርቲ ገፊ ሀይል ሆኖ እንዲቀርብ አስገድዶታል!!!
ዶ/ር አሰማህኝ ጋሹ
የኦዴፓ ሰዎች በምርጫዉ በክልላቸዉ ተሸንፈዉም ቢሆን የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥረዉ ይቀጥላሉ ማለት ነው። ይህ ሁኔታ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ወደ ፓርላማ በስፋት መግባት ጋር ተዳምሮ ህገ መንግስቱን የማሻሻሉን እድል ያጨልመዋል!!!
ሊመሰረት የታሰበዉ የብልፅግና ፓርቲ ውህድ ስለሆነ ብቻ የአማራዉን ህዝብ ጥያቄ ወይም የኢትዮጵያን አንድነት ያረጋግጣል ማለት አይደለም። የአገሪቱ መሰረታዊ ችግር ይህ አማራዉን እንደ ጨቋኝ በመቁጠር አገሪቱን በጎሳ የከፋፈለዉ ህገ መንግስት ነዉ። ይህ ሳይለወጥ የፓርቲ ዉህደት ብቻዉን ሁኔታዉን አይቀይረውም። በተለይ አዴፓ ዉህደት ለማድረግ ከመሮጡ በፊት ሊያስባቸዉ የሚገቡ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ።
..
በተለይ በአዲሱ የብልፅግና ፓርቲ የም/ቤትና ስራ አስፈፃሚ ዉክልና እንደ ኢህአዴግ እኩል ፓርቲዎች የሚወከሉበት ሳይሆን ዉክልናዉ ክልሎች ባላቸው ህዝብ ብዛት መሰረት በሚደረግ ድልድል ነዉ የሚለዉ በርካታ ችግሮች ይኖሩታል። በፓርቲዉ አወቃቀር ክልሎች እንደ ህዝብ ብዛታቸዉ ተመጣጣኝ ውክልና ይሰጣቸዋል ማለት ነዉ። ኦሮምያ ቀዳሚዉን የስራ አስፈፃሚና ም/ቤት አባላት ዉክልና ሲኖረዉ አማራና ደቡብ በሁለተኛ ሶስተኛ ደረጃ ዉክልና ይኖራቸዋል ማለት ነዉ። ‘ታዳጊ ክልሎችም’ እንደ ህዝብ ብዛታቸዉ ዉክልና ይኖራቸዋል። በዚህም መሰረት በሚፈጠረዉ ፓርቲ  ዉሳኔ አሰጣጥ ላይ ኦዴፓና ሌሎች ህገ መንግስቱ እንዲቀየር የማይፈልጉ ሃይሎች በድምሩ በድምፅ የበላይነት ይኖራቸዋል ማለት ነዉ።
አዴፓ የሚያቀርባቸዉን የህገ መንግስት ማሻሻያም ሆነ አማራን በአገሩ እንደ ባይተዋር እንዲኖር  ያደረገዉን ይህን የጎሳ ፌዴራል አደረጃጀት እንዲቀየር የሚያቀርበዉ ጥያቄ በቀላሉ በኦዴፓና ሌሎች ክልሎች ተወካዮች ዉድቅ ሊደረግበት ይችላል።  አዴፓ ዉህድ ፓርቲ መኖሩ አገሩን አንድ ያደርጋል ከሚል ቀና አመለካከት የተንሳ ቢሆን እንኳን እንዲህ አይነት አጣብቂኝ ዉስጥ እንደሚገባና የአማራዉን ህዝብ ችግር የበለጠ ሊያወሳስበው እንደሚችል ማሰብ ይገባዋል።
በስልጣንም አኳያ የብልፅግናዉ ፓርቲ ኦዴፓን የሚጠቅምበት እድል ይኖራል። ውህድ ፓርቲዉ ወደ ምርጫ ቢገባ በኦሮምያ የሚኖረዉ ተወዳዳሪነት ዝቅተኛ ስለሚሆን በአክራሪ ብሄርተኞች መሸነፉ አይቀርም። ነገር ግን የብልፅግና ፓርቲው በኦሮምያ ቢሸነፍና አማራን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ቢያሸንፍና ስልጣን ቢይዝ ኦዴፓ በፓርቲዉ ስራ አስፈፃሚና ም/ቤት ባለዉ የበላይነት የመንግስትን ስልጣን በበላይነት ይዞ የመቀጠል እድል ይፈጥርለታል። የኦዴፓ ሰዎች በምርጫዉ በክልላቸዉ ተሸንፈዉም ቢሆን የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥረዉ ይቀጥላሉ ማለት ነው። ይህ ሁኔታ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ወደ ፓርላማ በስፋት መግባት ጋር ተዳምሮ ህገ መንግስቱን የማሻሻሉን እድል ያጨልመዋል። አዴፓ ዉህድ ፓርቲ መመስረት በራሱ መጥፎ ነገር ባይሆንም እንዲህ አይነት አጣብቂኝ ሁኔታዎች እንደሚጠብቁት አስቦ ነገሩን በርጋታ ቢያየው የተሻለ ይሆናል። የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም ። ለአዴፓ የተሻለዉና ዉጤታማ የሚሆነው በዚህ ዉህድ ፓርቲ ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምነውን ህዝብና የፖለቲካ ሃይሎች በማስተባበር  አበክሮ ህገ መንግስታዊ ለዉጥ እንዲደረግ መስራት ነዉ።
Filed in: Amharic