>
4:53 pm - Friday May 25, 0457

ዲሞክራሲያ . . . ኢትዮጵያዊቷ ‹‹ፍንጥቅጥቅታ!›› ! ! ! (አሰፋ ሃይሉ)

ዲሞክራሲያ . . . ኢትዮጵያዊቷ ‹‹ፍንጥቅጥቅታ!›› ! ! !

 

አሰፋ ሃይሉ
ዲሞክራሲያ በ1966ቱ የኢትዮጵያ የአብዮት ግርግር ወቅት ‹‹ዳምጠው›› በሚባል ቤት-ውስጥ-ሠራሽ ቀለም መደፍጠጫ በድብቅ እየታተመች (እና ከታተመችውም ላይ በወጣቱ በብዕር እየተገለበጠች) ለሕዝቡ ትሰራጭ የነበረች የኢህአፓ ህቡዕ ልሣን (ወይም የፓርቲው ወቅታዊ የአቋም መግለጫና ማታገያ ጋዜጣ) ነበረች፡፡
ልክ እንደዚህችው ዓይነት ጋዜጦች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመጻፍ፣ የመናገር፣ የሚያስቡትን በሕትመትም ሆነ በሌሎች መንገዶች ለሌሎች የማካፈል፣ ወዘተ… መሠረታዊ የሰው ልጅ ነፃነቶች በተነፈጉባቸው ሃገራት ሁሉ ውስጥ እናገኛለን፡፡ ለምን??
ምክንያቱም በግልጽ ከተከለከልክ ሰው ነሃ! ታፍነህ አትሞት?! እና በግልጽ የታፈነውን በድብቅ እየተቀባበልክ ነፃነት የተራበ መንፈስህን እፎይ ታሰኛለሃ!!! እንደ ‹‹መታፈን›› ያለ አያድርስ ነገር የለም እኮ!! ልክ ስትታፈንና አየር ሲያጥርህ ከታፈንክበት ነፃ ለመውጣትና ኦክስጂን ለመሳብ በደመነብስ ትጣጣራለህ አይደል? በቃ ሕትመቶችም በታፈኑበት ሃገር ጸሐፊዎችና አንባቢዎች የሚያደርጉት ያንኑ ነዋ!!!
ለምሣሌ የሩሲያን ታሪክ ስንቃኝ… በታህሣሥ ወር 1900 እ.ኤ.አ. ሌኒን ያስጀመራትን የቦልሼቪኮች ደብቅ ልሣን ‹‹ኢስክራ››ን እናገኛለን፡፡ ‹‹ኢስክራ!›› በሩስኪ ቋንቋ ‹‹ፍንጥቅጥቅታዋ!›› ወይም ‹‹ብልጭታዋ›› (‹‹ዘ ስፓርክሊንግ!) ማለት መሆኑን ያገኘናቸው መዝገበ-ቃላት ይናገራሉ፡፡
ታዲያ ይህች የሌኒኗ ‹‹ኢስክራ›› የተሰኘች ደብቅ የቦልሼቪክ አብዮተኞች ‹ቡለቲን› — በራሱ በሌኒን እና ሌሎች 6 በማይሞሉ ሰዎች የምትጻፍ ነበረች፡፡ ግን ዝናዋ ከሩሲያኖችና ከሩሲያ ድንበርተኞች አልፎ . . . ዓለምን ሁሉ ያዳረሰ ታሪካዊ የአብዮተኞች ሁሉ ልብ-መግዣ ልሣን ነበረች፡፡
እንግዲህ ይህች ‹‹ኢስክራ›› ከተቀየሰችበት ከሃገረ መስኮብ በጀርመን፣ በፈረንሣይ፣ …  አሰባብራ — ወደ እኛ ሃገር በምልሰት-ጉዞ መንገዷን ስታቀና ይመስለኛል እንግዲህ . . . የሩሲያዋ ‹‹ብልጭታ›› እኛ ጋር ደግሞ ‹‹ዲሞክራሲያ›› ተሰኝታ የተዳፈነውን አብዮት ብርሃኗን ልትፈነጣጥቅበት…. በድብቅ ጉያችን የገባቸውች፡፡
እናም. . . የኛይቱ የ‹‹ዲሞክራሲያ›› የብዕር ጠብታ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1966 ዓ.ም. ነው የብራና መስክ በሆነችው … በዚህች ያላለፈላት ሃገራችን ከነአብዮተኛ አጀንዳዋና መፈክሮቿ … በትልቁ ጠብ ጠብ ስትል የተሰማችው፡፡
ዲሞክራሲያ ‹‹ሀ›› ብላ ስትጀመር — ፀሐፊዎቿ ማን እንደሆኑ በሕዝቡ ዘንድ በይፋ አይታወቁም ነበር፡፡ ድብቅ ናቸው፡፡ ጥብቅ ምስጢሮች፡፡ እና ምስጢረኞች፡፡ በወቅቱ ስለማንነታቸው ማንም በግላጭ የማያውቃቸው ህቡዕ የኢህአፓ ብዕርተኞች . . . ማንነት የምንረዳው ኋላ ላይ በደርግ-የደህንነት ሰዎችና በሌሎች ስለ ወቅቱ ታሪክ በሚያትቱ ድርሳናት ላይ ሠፍሮ ስናገኘው ነው፡፡
ለምሳሌ ዲሞክራሲያ ላይ የተባ ብዕራቸውን ከሚያፈሱት መሐል የኢህአፓ መሪዎቹን የእነ ተስፋዬ ደበሳይን፣ የእነ ጌታቸው አሰፋንና አሁንም በህይወት ያለውን የክፍሉ ታደሰን ስም ማግኘቱ ብዙም ላይገርመን ይችላል፡፡
ግን እነ ፀጋዬ ገ/መድህንና እነ ዮናስ አድማሱን የመሣሠሉ የወቅቱ ፊደል የቆጠሩ የታወቁ ጸሐፍት ኢትዮጵያውያንን… በዚያች የአብዮተኞች ህቡዕ አምድ ላይ ታዳሚዎ እንደነበሩ መስማት ግን… ምናልባት በጣ….ም ግርርርም ሳያሰኝ አይቀርም!!!
እንግዲህ በኛ በኩል ይህን ያህል ካወራን . .. ስለዚህችው — ያኔ በዘመነ-አብዮት ይዘሃት ብትገኝብህ — ሌላ ቀርቶ አኝከህ ብትውጣት እንኳ (ያደረጉም ነበሩ!) — አንድም ለ ‹‹ወፌ ላላ!›› የግልብጥ ግርፍ — አሊያም ለአብዮት ጠባቂ ወንጭፍ — አሊያም ከሄድክ ወደማትመለስበት ህልፈተ-ዓለም ትዳርግህ ስለነበረችው — ስለዚህችው የዘመኑ ኢህአፓዎች ልሳን በወቅቱ በዚህችው የምስጢር-ጋዜጣ ላይ ሲፅፉባት ከነበሩ የታሪክ ተዋናይ አፍ — በመጽሐፋቸው ከጻፉት ላይ ቀንጭበን — የዲሞክራሲያን ገድል ብንሰማ፣ መልካም ሳይሆን አይቀርም፡- ‹‹ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የነበረ›› እንዲሉ አበው፡፡
እናም . . . እነሆ በ2008 ዓ.ም. ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ… — አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ – ከመስከረም 2 1967 ዓ.ም አዋጅ በኋላ›› በሚል ርዕስ — በወቅቱ የኢህአፓ መሪዎች ከነበሩት አንዱ በሆነው (እንደሆነ በሚነገርለት) በ‹‹ያ ትውልድ›› በሚታወቀው — የወቅቱ ዋነና ተዋናይ… — በደራሲ ክፍሉ ታደሰ — ከተጻፈው መጽሐፍ ላይ ቀንጨብ አድርገን አንባቢ ስለዚህችው ህቡዕ ልሳን ከራሱ ከባለታሪኩ ግላጭ ልሳን ሰምቶ አንባቢው የራሱን ግንዛቤ እንዲወስድ በማሰብ ፍላጎቱ ላለው — ከከበረ ምስጋና ለደራሲው እያቀረብኩ — ከዚህ በታች የተመለከተውን የፀሐፊውን የታሪክ እማኝነት — ‖ከአንዳንድ መጠነኛ ግድፈቶች ጋር‖ — እንዲያነብ ለፈለገ ሁሉ ጋብዤ፣ አንባቢውንም ጭምር አመስግኜ — የራሴን ጨርሻለሁና፤ የባለታሪኩ ትርክት ደግሞ እንዲቀፅል — በትህትና — ‹‹ወራጅ አለ!!!!›› ብዬ ወረድኩ እዚህ ጋር፡፡
‹ኢትዮጵያ ሆይ . . . ››
ተጀመረ እንግዲህ. . . ከገጽ ፻፲፯—፻፴. . . በደራሲው ክፍሉ ታደሰ ብዕር. . . እንዲህ እየወረደ፡-
‹‹… የመጀመሪያዋ የዲሞክራሲያ እትም ሰኔ ወር 1966 ዓም ላይ ወጣች፡፡ ከ1966 ዓም መገባደጃ እስከ 1970 ዓም ድረስ በነበረው ጊዜ [. . .] ብዕር ስለኢትዮጵያ ጎስቋላና ደሀ ህዝቦች ዋይታና ለቅሶ በመጻፍ የብዙዎቹን ልብ ነካ፡፡ ድህነቱን የሚጋሩ ዜጎች አነቡ፡፡ [. . .] ብዕር ሥልጣን የሕዝብ ነው አለ፡፡ ለሕዝባዊ ስርዓት መታገል የተቀደሰ ተግባር መሆኑንም ሰበከ፡፡
‹‹ብዙ ወገኖች ጥሪውን ተቀበሉ፡፡ ዲሞክራሲና ሰብዐዊ መብቶች የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተጎናጸፋቸው መብቶቹ ናቸው ሲል ብዕር ጻፈ፤ አስተማረ፡፡ እነዚያን መብቶች የተገፈፉ ወገኖች ጆሮአቸውን ሰጥተው አዳመጡ፡፡ ለመብት መታገል ይገባል ሲሉም [. . .] ተሰለፉ፡፡
‹‹ብዕር ስለአንድነትና የህዝቦች እኩልነት ጻፈ፡፡ የህዝቦች እኩልነት መብት ሊከበር ይገባል፣ የማይታለፍ ሀገራዊ ጥያቄ ነው ሲል አስተማረ፡፡ የእኩልነት መብት ተነፍገው የቆዩ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ስሜት ኮረኮረ፡፡ ለመብት መነሳት የተቀደሰ ዓላማ ነውም አሉ፡፡ [. . .] ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ በሀገሪቱ ያሉ ብሄረሰቦች የሚሳተፉበት ድርጅት ተፈጠረ፡፡ [. . .] አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡
‹‹ብዕር በለውጡ ሂደት ላይ አሻራውን አሳረፈ፡፡ መልህቁ እንደጠፋው በውቅያኖስ ውስጥ እንደሚዋዥቅ መርከብ ግራ የተጋባው ደርግን ጭምር ብዕር አቅጣጫ አሳየ፣ አመላከተ፡፡
‹‹… የያ ትውልድ ብዕር መሰረታዊ ከሆነው የሰው ልጆች መብት፣ ማለትም፣ የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ብሎም የማሰብ መብት ከሚለው እሳቤ ይነሳል፡፡ የሰው ልጅ የተፈጥሮአዊ መብቱ በተረገጠበት አገር [. . .] ብዕር ህጋዊ አልነበረም፡፡ እንዲያውም በ1967 ዓም በወጣው አዋጅ መሰረት መጻፍ ራሱ በህግ ተከልክሏል፡፡ መንግስት ያልፈቀደው ጽሁፍ አባዝቶ ማሰራጨት ለእስር፣ ኋላ ላይም ለሞት የሚዳርግ ሆኗል፡፡
‹‹[. . .] ዲሞክራሲያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን መልዕክት ማስተላለፏን ቀጠለች፡፡ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የማተም ዘዴ ጭምር እየተባዛች ተሰራጨች፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ግን፣ ማንም ሳያዛቸውና ሳይነግራቸው ወጣቶች በሺህና በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ቅጅዎች በእጅ እየተገለበጡ አሰራጩ፡፡ ብዕር የለውጥ ከፍተኛ መሳሪያ ሆነ፡፡ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገወዲያም እንደሚሰራ ተረጋገጠ፡፡
‹‹… በዚያ ወቅት፣ ዲሞክራሲያን ያነብ የነበረው ሰው እነማ እንደሚጽፉት ግምትም አልነበረውም፡፡ [. . .] ሰውን አይቶ [viz. ትግሉን] የተቀላቀለ የለም፡፡ ዲሞክራሲያ የምታቀርባቸው ሃሳቦች፣ ትንታኔዎች፣ ዜናዎችና መረጃዎች ማርከዋቸው እንጅ! በአማርኛ መታተም የጀመረችው ዲሞክራሲያ፣ በኦሮምኛ፣ ደራስኛ፣ ወላይታ፣ ትግርኛ፣ እንግሊዝኛና ሌሎች ቋንቋዎች ትታተም ጀመረ፡፡
‹‹በብዕር አማካይነት ድርጅት አድጎ ጎለበተ፡፡ በርካታ አባላትም አሰባሰበ፡፡ በብዕር አማካይነት ድምጽን ማሰማት ተቻለ፡፡ [. . .] የተቃውሞ ድምጽ መገልገያ መሳሪያ ሆኖ፣ ድምጽ እንዳይኖራቸው የተከለከሉ ወገኖች ልሳን በመሆን ብዕር ድምጻቸውን ከፍ አድርጎ አሰማ፡፡ አዲስ አቅጣጫና አተያይ እንዳለና ሊኖር እንደሚችል አሳየ፡፡ ብዕር የፖለቲካ ፓርቲን መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብትና እንዲስፋፋ ረዳ [viz. የተሰመረበት]፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ የዲሞክራሲያ [. . .] ሚና ከፍተኛ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት ማድረግ ሲሆን፣ ብዕር ሃይለኛና ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ በተጨማሪ፣ ዲሞክራሲያ ያ ትውልድን ፈጠረች፣ አጎለበተች [viz. የተሰመረበት]፡፡
‹‹[. . .] በሀገሪቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ ዲሞክራሲያ በተከታታይ ጻፈች!!!
 [. . .] በ1966 ዓም አደባባይ ከወጣ ጀምሮ ሕዝቡን የሚያሳትፍ የሕዝባዊ መንግስትና የዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ጉዳይ ዐበይት ከሚባሉ ጥያቄዎች መሀል ሆኑ፡፡ ያ ጥያቄ ዛሬም ቢሆን ምላሽ አላገኘም፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ ምህዳርም ገና አልሰፋም፡፡ ምናልባትም፣ ያ ሥርዓት በእኛ ዕድሜ ሳይሆን የሌላ ትውልድ ጥረትን ሊጠይቅ ይችል ይሆናል፡፡››
ደራሲውንና አንባቢውን እነሆ በድጋሚ አመሰገንን፡፡ ከጽሑፉ ጋር የወጣውን ምስል — ማለትም የ1970 ዓመተ ምህረት የዲሞክራሲያን ኦሪጂናል እትም — በቸርነት ፎቶውን በድረገጻቸው ላካፈሉን ባለቤቶችም ጭምር ልባዊ ምስጋናችንንም አቀረብን፡፡ ‹‹አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለምት ትኑር!››፡፡ ቻው፡፡ መልካም ንባብ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡ መልካም እንቅልፍ፡፡ መልካም ዘመን ለሁላችን ይሁንልን፡፡ ቻው፡፡
የምስሉ ምንጭ (የእስክሪብቶውን ጭማሪ አይመለከትም!)፡-
Democracia, vol. 5, 1970 Ethiopian Calendar (1978 CE)፡
‹‹Democracia  kist 5  kutir  1-1_cover››
Filed in: Amharic