>

ጃንሆይ በቅርብ ዘመድ ዓይን (ባየህ ኃይሉ ተሠማ)


ጃንሆይ በቅርብ ዘመድ ዓይን

ከባየህ ኃይሉ ተሠማ 
“–ጃንሆይ ራስ አሥራተ ከእግራቸው ላይ እንዲነሱ ካደረጉ በኋላ፣ የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ፤ ‹‹እስኪ ንገረን እባክህ? ንጉሥ ዳዊት ሥልጣኑን በፈቃዱ ለቅቋል? ወይስ ሥልጣኑን በፈቃዱ የለቀቀ የኢትዮጵያ ንጉሥ በታሪክ ውስጥ ነበር? እግዚአብሔር እስከፈቀደልን ጊዜ ድረስ እንገዛለን፡፡ እኛ ከሄድን በኋላ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማትን እርሱ ያውቃል!!!››”
        —-
ዶ/ር አስፋ ወሰን አሥራተ፣ የታዋቂው መሥፍን፣ የልዑል ራስ ካሣ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አያታቸው ራስ ካሣ፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመድና የቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡ አባታቸው ልዑል ራስ አሥራተ ካሣ፣ በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች በአገረ ገዢነት፣ በኤርትራ የንጉሠ ነገሥቱ እንደራሴ፣ በመጨረሻም የዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን፣ በደርግ ተይዘው እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም የተወለዱት ዶ/ር አስፋ ወሰን፤ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ትምህርት ቤት እንዲሁም በቱቢንገን ዩኒቨርሲቲ፣ ካምብሪጅ ዩነቨርሲቲ በሚገኘው የማግደሊን ኮሌጅና በታሪክ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በተቀበሉበት በፍራንክፈርት ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡
ዶ/ር አስፋ ወሠን በጀርመንኛ ቋንቋ ባቀረቧቸው መጻሕፍት፣ ከፍተኛ ተነባቢነት በማግኘታቸው፣ ሁለት የተከበሩ የጀርመን የሥነ ጽሑፍ ሽልማቶችን ለመቀበል በቅተዋል:: ከዚህም ሌላ እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም ‹‹King of Kings›› በሚል ርዕስ ስለ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪካዊ አነሳስና አሳዛኝ አወዳደቅ በጀርመንኛ ቋንቋ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ መጽሐፉ ከታተመ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ፣ ለመላው ዓለም አንባቢያን ቀርቧል፡፡ መጽሐፉ ስለ ጃንሆይ እስካሁን የማናውቃቸውን አዳዲስ ጉዳዮች ይዟል፡፡ ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
***
ጃንሆይ ወደ ጠቅላይ ግዛት ወይም ወደ ውጪ አገር ካልሄዱ፣ ከቀትር በኋላ በመናገሻ ከተማቸው በመኪና የመዘዋወር ልማድ ነበራቸው፡፡ በዚህ ጉዞ የንጉሣዊ ቤተሰቡ ልጆች፣ ጃንሆይን አጅበው እንዲሄዱ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ ጃንሆይ ብዙ ጊዜ መጓዝ የሚወዱት ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ባበረከቱላቸው ሽንጣምና ባለ ሶስት ረድፍ ወንበር ባላት ካዲላክ ሊሞዚን ነበር፡፡ በሹፌሩና ከኋላ ባለው መቀመጫ መካከል ዙሪያውን በሮዝውድ የተጌጠ የመስተዋት መከለያ አለ:: ከመስተዋቱ ዝቅ ብሎ ባለው ሠሌዳ ላይ H.I.M (His Imperial Majesty) የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል፡፡ ከሹፌሩ ጀርባ የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ረዳት የሚቀመጥ ሲሆን ከዚሀ ጀርባ ያለው መሐል ወንበር ላይ ልጆች ተደርድረው፣ ጃንሆይ ደግሞ ከመጨረሻው ወንበር ላይ ይሰየማሉ:: ንጉሡ እንደ ጥንት ሮማውያን ገዢዎች፣ በከተማ ውስጥ እየተዘዋወሩ፣ ምጽዋት መስጠት ያስደስታቸዋል:: አንዳንድ ጊዜ እኛም እንድንመጸውት ረብጣ የብር ኖቶች ይሰጡናል:: ምጽዋቱን መስጠት ገና ከመጀመራችን፣ በመጠኑ ዝቅ ባለው የመኪናው መስኮት በኩል፣ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩ እጆች፣ ብሮቹን ከመቅጽበት ይናጠቋቸዋል፡፡
***
ጃንሆይን ያለ ንጉሣዊ ፕሮቶኮል እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ሲንቀሳቀሱ መመልከት የተለመደ ነገር አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት በአስመራ የእንደራሴው መኖሪያ ቤተ መንግሥት ውስጥ ጃንሆይ ከራስ እምሩና ከአባቴ ከራስ አሥራተ ጋር ፑል ሲጫወቱ ለማየት ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ጃንሆይ የፑል ማጫወቻውን እንደተመለከቱ ወደ ራስ እምሩ ዘወር ብለው፤ ‹‹ልጅ እያሱ ቤት ልጆች ሆነን ፑል እንጫወት እንደነበር ታስታውሳለህ? እስኪ ጨዋታው አልጠፋህ እንደሆነ እናያለን›› አሉና ኮታቸውን አውልቀው ለአባቴ ሰጡት፡፡ ሁለቱ ትልልቅ ሰዎች ጥቂት ከተጫወቱ በኋላ ራስ እምሩ፣ አባቴን ወደ ጨዋታው እንዲገባ ሲጠይቁት፣ የጃንሆይን ኮት ለኔ ሰጠኝና ወደ ጨዋታው ገባ፡፡ እንደተመለከትኩት በጨዋታው ጃንሆይ ከአባቴም ሆነ ከራስ እምሩ የተሻለ ችሎታ አላቸው፡፡ ይህ ቀን ንጉሠ ነገሥቱ ያለ ኮት ወይም ያለ ካባ፣ በሸሚዝ ብቻ ሆነው የተመለከትኩበት የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አጋጣሚ መሆኑን መናገር አለብኝ፡፡ ንጉሡን የከበባቸው ያ ሁሉ አስፈሪና የሚያርድ ግርማ ሞገስ፣ በድንገት ከራሳቸው ላይ ወልቆ ራሱን በጨዋታ የሚያዝናና ተራ ሰው ሆኑ፡፡ በቆምኩበት ቦታ ደርቄ፣ የጃንሆይን ኮት በተዘረጋው እጄ ላይ እንደያዝኩ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ድንጋዮቹን እያጋጩ፣ ተራ በተራ በጉድጓዱ ውስጥ ሲያስገቡ ፍዝዝ ብዬ እመለከት ነበር፡፡ በመጨረሻ ጨዋታው በጃንሆይ ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ፣ ኮታቸውን አቀበልኳቸው፡፡ ጃንሆይ ኮታቸውን አስተካክለው ለብሰው ሲጨርሱና እንደገና ወደ ‹‹ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትነት›› ሲለወጡ ተመለከትኩ፡፡
***
በ1957 ዓ.ም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ሄንሪክ ሉብክ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ፣ በአሥመራ ቤተ መንግሥት የቁርስ ግብዣ ተደርጎላቸው ነበር፡፡ ከቀረበላቸው ቁርስ ውስጥ ገንፎውን እንግዶቹ በጣም ወደውት ነበርና የፕሬዚዳንቱ ባለቤት የገንፎውን መጣፈጥ ምሥጢር ለማወቅ ኦስትሪያዊቷን የቤተ መንግሥቱን ዋና ሼፍ አስጠርተው አነጋግረው ነበር፡፡ የምግቡ መጣፈጥ አንዱ ምሥጢር በተለይ የተሰራው ማብሰያ ድስት መሆኑ ተገለጸላቸውና፣ አንዱ ድስት ተጠቅልሎና በካርቶን ታሽጎ፣ ለፕሬዚዳንቱ ባለቤት በስጦታ ተበረከተላቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ያገለገለ ድስት ለጀርመኑ ፕሬዚዳንት ባለቤት በስጦታ መሰጡትን ያወቁት እንግዶቹ ከሄዱ በኋላ ስለነበር፤ ተመሳሳይ አዳዲስ ድስቶች ተገዝተው፣ ጀርመን ወደሚገኘው የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት እንዲላክ አስደርገዋል፡፡
***
በከሸፈው የታህሳስ 1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ማግሥት፣ ጃንሆይ የብራዚል ጉብኝታቸውን አቋርጠው በአስመራ በኩል ወደ አዲስ አበባ አመሩ፡፡ የንጉሳዊው ቤተሰብ፣ ከፍተኛ ባለስልጣኖችና ሌሎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አየር ማረፊያውን ከበው፣ የጃንሆይን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር:: ንጉሠ ነገሥቱን የያዘቸው ዲሲ 6 አውሮፕላን እንዳረፈች፣ የመውረጃው ደረጃው ቀርቦ ቀይ ምንጣፍ አውሮፕላኑ ድረስ ተዘረጋ፡፡ ከአውሮፕላኑ ቀድመው የወረዱት የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ረዳት ጀነራል ደበበ ኃይለ ማርያም ነበሩ፡፡ ጃንሆይ ወታደራዊ ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ፣ ገና ከአውሮፕላኑ ብቅ እንዳሉ፣ ዙሪያውን ከቦ የነበረው ሕዝብ፣ እልልታና ጭብጨባ አሰማ፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ እግር መሬት እንደረገጠ፣ አልጋ ወራሹ ልዑል አስፋ ወሠን፣ የጃንሆይ እግር ሥር ተደፉ፡፡ ከመፈንቅለ መንግሥቱ አድራጊዎች ጋር በመተባበራቸው ይቅርታ መጠየቃቸው ነው፡፡ ጃንሆይ እግራቸው ሥር የተደፋውን ልጃቸውን ለማንሳት ምንም ሙከራ ሳያደርጉ በቁጣ፤ ‹‹ለእኛ ክብር የሚሆነው፣ አንተ ሞተህ ለቀብርህ ብንገኝ ነበር! ተነስ!›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
***
ስለ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሚደረጉ ጥናቶች ሁሉ፣ ስለ እቴጌ መነን የሚጽፉት ከግርጌ ማስታወሻ ያልዘለለ መሆኑ፣ እቴጌይቱ በንጉሣዊው ቤተሰብ ላይ የነበራቸውን ሚና አኮስሶ የሚያሳይ እንደሆነ ዶ/ር አስፋ ወሰን ጽፈዋል፡፡ እቴጌ መነን ምንም እንኳ እንደ እቴጌ ጣይቱ በመንግሥት የእለት ተእለት ፖለቲካዊ ውሣኔ ተሳታፊ ባይሆኑም፣ ለንጉሠ ነገሥቱ የቤተሰብ ሕይወት አለኝታነታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያን ለሚጎበኙ የውጪ እንግዶች የሚሰናዱ መስተንግዶዎችና ግብዣዎች የሚከናወኑት በእቴጌ መነን ብርቱ ቁጥጥር ነበር፡፡ በስደቱ ዘመን የእንግሊዝ አገር ብርድና ቅዝቃዜ፣ ጤናቸውን ጎድቶት ስለነበር በውጪ አገር ጉብኝቶች ጃንሆይን ተከትለው ለመሄድ ፍላጎት አላሳዩም፡፡ እቴጌ መነን መንፈሳዊ እመቤት እንደመሆናቸው፣ የሞት ፍርድን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር፡፡ ‹‹የሰውን ሕይወት መልሶ ለመውሰድ ሥልጣን ያለው የፈጠረው እግዚአብሔር ብቻ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ በአገር ክዳት ወንጀል ተከሰው ሞት የተፈረደባቸው አንዳንድ ሰዎች፣ ቅጣቱ ሳይፈጸምባቸው የቀረው በእቴጌ መነን አማላጅነት የተነሳ ነበር፡፡
***
ራስ ተፈሪ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዘውድ ለመድፋት ሲዘጋጁ፣ እቴጌ መነንን ለመፍታትና በውበታቸው የታወቁት ወ/ሮ አስቴር መንገሻን (የራስ ስዩም መንገሻ እህት) ለማግባት ያውጠነጥኑ እንደነበር ታውቋል፡፡ ንጉሡ ይህንን ሀሳባቸውን እንዲተዉ ያግባቡት ራስ ካሣ ነበሩ፡፡ ‹‹ወ/ሮ መነን በክፉም በደግም ከጎንዎ አልተለዩም፡፡ ከእንግዲህ ውለታቸውን መክፈል ደግሞ የእርስዎ ተራ ይሆናል›› በማለት ራስ ካሣ ሀሳባቸውን ማስቀየራቸው ተጠቅሷል:: እቴጌ መነን ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ከዶክተር አስፋ ወሰን እናት ጋር ሲጫወቱ፤ ‹‹ጃንሆይ እኔን ትተው ሌላ ቢያገቡ ኖሮ፣ እኔም ቤቱን ትቼላቸው ወጥቼ፣ ራስ ኃይሉን አገባ ነበር›› ብለዋል፡፡ የጎጃሙ መሥፍን ራስ ኃይሉ፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ብርቱ ተቃዋሚ የነበሩ ሲሆን ለወ/ሮ መነን ያላቸውን ፍቅር ሳይደብቁ ይናገሩ ነበር ይባላል፡፡
***
በሐምሌ ወር 1964 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ፣ 80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከብሩ ስለነበር፣ ክረምቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ደምቆ ነበር፡፡ የልደታቸው ዕለት ጠዋት ራስ አሥራተና ባለቤታቸው፣ ጃንሆይን “እንኳን አደረሰዎ” ለማለት ወደ ቤተ መንግሥት አመሩ:: ጃንሆይ የተቀበሏቸው ከመኝታ ክፍላቸው ጋር በተያያዘው የእንግዳ መቀበያ ክፍል ነበር፡፡ ራስ አስራተ በተለይ ያዘጋጁትን ስጦታ ካበረከቱ በኋላ ጃንሆይ አልጋ ወራሻቸውን አሳውቀው፣ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደሌለና “ይህንን ከፈጸሙ በታሪክ ውስጥ ስምዎ ለዘላለም ሲነሳ ይኖራል” ሲሉ በጃንሆይ እግር ስር በመውደቅ ተማጸኑ፡፡ ጃንሆይ ራስ አሥራተ ከእግራቸው ላይ እንዲነሱ ካደረጉ በኋላ፣ የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ፤ ‹‹እስኪ ንገረን እባክህ? ንጉሥ ዳዊት ሥልጣኑን በፈቃዱ ለቅቋል? ወይስ ሥልጣኑን በፈቃዱ የለቀቀ የኢትዮጵያ ንጉሥ በታሪክ ውስጥ ነበር? እግዚአብሔር እስከፈቀደልን ጊዜ ድረስ እንገዛለን፡፡ እኛ ከሄድን በኋላ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማትን እርሱ ያውቃል›› ብለው ነበር፡፡
***
በመስከረም ወር 1965 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻቸው የሆነውን የአውሮፓ ጉብኝት በምዕራብ ጀርመን አደረጉ፡፡ ጃንሆይ ያረፉበት ሆቴል ድረስ እንድመጣ ተጠራሁ፡፡ የአንድ መቶ ዶላር ኖት ሰጡኝና በጀርመን የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች መገበያያ ወደ ሆነው PX Supermarket ሄጄ ‹‹ቪታሊስ›› የተሰኘ ግማሽ ደርዘን የጠጉር ቶኒክ ገዝቼ እንድመጣ አዘዙኝ:: የዚያን ቀን ምሽት የጠጉር ቶኒኩንና በመልስ የተቀበልኩትን ገንዘብ ሰጠኋቸው፡፡ ጃንሆይ መልሱን ቆጠሩና ‹‹ምን! ዋጋው ሰላሳ ዶላር ነው?›› አሉና ጠየቁኝ፡፡ ‹‹ግርማዊነትዎ! አዎ!›› አልኩና ደረሰኙን አሳየኋቸው፡፡ ‹‹የማይታመን ነው! ይኼ ነገር እንዴት ተወዷል?›› አሉና አጉተመተሙ፡፡ የመልሱን ገንዘብ እንድወስደው እየሰጡኝ ‹‹ፍራንክፈርት ስትመለስ የኪስ ገንዘብ ይሰጥሃል›› አሉኝ፡፡ የታዘብኩት ነገር፣ ለእቃዎች ዋጋ ጃንሆይ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጡ ነው፡፡ የግል ኑሯቸውን በተመለከተ ጃንሆይ በጣም ቁጥብ ናቸው፤ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ደግሞ ጃንሆይ ለጋስ እንደሆኑ የታዘብኩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡ በዚያን ጊዜ ግን በአገሪቱ በጣም ውስን የሆነ የውጪ ምንዛሪ ነበር – ለንጉሠ ነገሥቱም ጭምር!
***
በሚያዝያ ወር 1966 ዓ.ም አንድ ምሽት የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የነበሩት ጀነራል አበበ ገመዳ፣ ራስ አስራተ ካሳ ቤት ተገኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ተሰናብተው ይሄዳሉ፡፡ ይህንን አስመልክተው ዶ/ር አስፋ ወሠን ሲጽፉ ‹‹ከምሳ በኋላ በአትክልቱ ስፍራ ስንዘዋወር አባቴ ያስጨነቀውን ጉዳይ ያካፍለኝ ጀመር፡፡ ለካስ ባለፈው ምሽት ጀነራል አበበ ከቤታችን የመጡት አማጺ ወታደራዊ መኮንኖች ችግር ከመፍጠራቸው በፊት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጃንሆይ እንዲፈቅዱ ለመምከር ኖሯል… የዚያን እለት ጠዋት አባቴና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል አቢይ አበበ ያቀረቡት ሃሳብ በጃንሆይ እምቢተኛነት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ በአትክልቱ ውሥጥ የምናደርገው ሽርሽር ሊያበቃ ሲል፣ አባቴ ፍርሃቱን ፍርጥርጥ አድርጎ ሲገልጽልኝ ‹መጨረሻችን ተቃርቧል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ አማጺ ወታደሮች ለጃንሆይ ታማኝ እንደሆኑና የሚቃወሙትም ባለሥልጣኖቻቸውን ብቻ እንደሆነ አድርገው፣ ሀሰተኛ ተስፋ ለምስኪኑ ንጉሠ ነገሥት የሚመግቡ ኃይሎች፣ በቤተ መንግሥቱ ውሥጥ አሉ፡፡ ነገር ግን የአማጺዎቹ ዋንኛ ዒላማ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ እንደሆኑ ጃንሆይ አሁን በቅርቡ ይረዱታል፡፡ በዝግታ ከምትሰምጠዋ መርከብ ላይ ምንም ሳያደርጉ ተቀምጦ ከማለቅ በስተቀር ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም››› ብሎኝ ነበር፡፡ አባቴ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሁናቴ እንደዚህ ተስፋ ቆርጦ አይቼው አላውቅም፡፡
***
በሚያዝያ መጨረሻ 1966 ዓ.ም የአባቴን 52ኛ ዓመት የልደት በዓል በመጠነኛ ዝግጅት ካከበርን በኋላ፣ በጥናት ከፍሉ ውስጥ እኔና አባቴ ብቻ ቀረን፡፡ የጃንሆይ መንግሥት ሊወድቅ በቋፍ ላይ እንዳለ አጫወተኝ:: በአባቴ አስተያየት፣ በዘውድ ሥርዓቱ ላይ የተጋረጠው ተጨባጭ አደጋ የተማሪዎች ወይም በየጊዜው የሚሰለፉ ተቃዋሚዎች ሳይሆን የጦር ሠራዊቱ ንቅናቄ ነው፡፡ ከ1953 ዓ.ም የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ በኋላ ሌላ የከፋ አደጋ በመንግሥት ላይ ሊደርስ ይችላል ብሎ አባቴ ለረጅም ጊዜ ሲጨነቅበት ቆይቷል:: ከአንድ ኤንቨሎፕ ውስጥ የተጣጠፈችና በደም የተበከለች ወረቀት አውጥቶ ሰጠኝ፡፡ ከታህሳስ 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሪዎች አንዱ ከነበሩትና በኋላ ከተገደሉት የፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ ከጀነራል ጽጌ ዲቡ ኪስ የተገኘች መሆንዋን ነገረኝ፡፡ ወረቀቷ የልዑላን፣ የመሳፍንትና የባለሥልጣናት ስም ዝርዝር የያዘች ሲሆን በስማቸው ትይዩ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥቱ ከተሳካ በኋላ ቤታቸውን የሚወርሱት የአመጹ ዋና ዋና ተዋንያን ስም ተጽፏል፡፡ የቤተሰባችን ስም ከሰፈረበት ትይዩ፣ ቤታችንን የሚወርሰውን ግለሰብ ስም አየሁ – ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ!
***
ሰኔ 24 ቀን 1966 ዓ.ም ልዑል ራስ አሥራተ ካሣ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው በወታደሮች ተያዙ:: ከመያዛቸው በፊት አስቀድመው ያዘጋጁትን አንድ ኤንቨሎፕ ለጃንሆይ በእጃቸው እንዲሰጥላቸው ለልጃቸው ለሙሉጌታ አሥራተ አደራ ሰጥተው ነበር፡፡ ሙሉጌታ በአደራ የተቀበለውን ኤንቨሎፕ ለማድረስ ወደ ቤተ መንግሥት ውሥጥ ሲገባ፣ ጃንሆይን ያገኛቸው በመኝታ ክፍላቸው ውሥጥ  ነበር፡፡ ራስ አሥራተ በደርግ መታሰራቸውን ጃንሆይ ሰምተዋል፡፡ ‹‹የቀኝ እጃችንን ዛሬ ቆረጡት! ግልገሎቿን የተነጠቀች ድመት ምን ለማድረግ ትችላለች? መጮህ ብቻ! እኛም ከመጮህ በስተቀር ለማድረግ የምንችለው ምንም የለም!›› አሉ፡፡ ከራስ አሥራተ የተላከላቸውን ኤንቨሎፕ ሲመለከቱም ሙሉጌታን እንዲከፍተው አዘዙት:: ኤንቨሎፑ የያዘው ቀደም ባሉ ሳምንቶች፣ ንጉሠ ነገሥቱ ከኢትዮጵያ የሚወጡበትንና ጥገኝነት የሚያገኙበትን ሁኔታ አስመልክቶ፣ ራስ አሥራተ ካሣ፣ ከአሜሪካና ከብሪታንያ ኤምባሲዎች ጋር ያደረጉትን የደብዳቤ ልውውጥ  ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግሥት፣ ለንጉሠ ነገሥቱ፣ ጥገኝነት ለመስጠትና ከኢትዮጵያ ክልል ከሚወጡበት ጊዜ ጀምሮም፣ ለደህንነታቸው ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ዋስትና ሰጥቶ ነበር፡፡
Filed in: Amharic