>
5:31 pm - Thursday November 12, 2263

የጥበቡ ቀዲል ወጋየሁ ንጋቱ (መሰለ ምትኩ)

የጥበቡ ቀዲል ወጋየሁ ንጋቱ

መሰለ ምትኩ
ወጋየሁ ንጋቱ በኢትዮጵያ እጅግ አድርጐ ስማቸው ከሚጠራ የመድረክ ተዋንያን አንዱ ነው።
ወጋየሁ ከአባቱ ከአቶ ንጋቱ ብዙነህና ከእናቱ ከወ/ሮ አምሳለ በየነ በግንቦት ወር 1936 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀበና እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተወለደ:: ወጋየሁ በ1942 ዓ.ም. አካባቢ አቃቂ በሚገኘው የስዊድን ወንጌላዊት ሚሲዮን ት/ቤት ትምህርቱን ጀመረ::
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በዳግማዊ ምኒልክ እና በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤቶች ተከታተለ:: ወጋየሁ በት/ቤት ቆይታው በአንዳንድ የተለዩ አጋጣሚዎች የተሰጥኦ ትርዒት ያቀርብ ነበር:: ከተሰጥኦ ትርዒቶቹ ዋናው የልዩ ልዩ እንስሳትን ድምፅ አስመስሎ ያወጣው የነበረው ይጠቀሳል::
በ1955 ዓ.ም. የሁለቱኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አቋቁሞት በነበረው “ኪነ ጥበብ ወትያትር” ይባል ወደነበረው የአሁኑ “የባህል ማዕከል” በመግባት ክጓደኞቹ ከአባተ መኩሪያ እና ደበበ እሸቱ ጋር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ::
በወቅቱ የማዕከሉ ኃላፊ በነበሩት ፍሊፕ ካፕላን አማካኝነትም የትወናን፣ የዝግጅትንና የፅህፈተ-ተውኔትን መሠረታዊ እውቀት ተማረ:: ከዚያም የተማረውን በተግባር በማዋልም በተከታዮቹ ዓመታት ቀጥሎ የተዘረዘሩት ተውኔቶ ች በዝግጅትና በትወና የላቀ ተሳትፎ አደረገ ::
– ሮሜውና ጁሌት
– ጠልፎ በኪሴ
– የከርሞ ሰው
– መድሃኒት ቀምሰዋል
– ዳንዴው ጨቡዴ
– የዋርካው ሥር ምኞት
– ላቀችና ድስቷ በተባሉ ትርጉምና ወጥ ተውኔቶች አብይ ሚናዎችን ይዞ በመጫወቱ ተደናቂ ሆነ::
የቲያትር ሙያ እውቀቱን ለማጐልበትም ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር:: በ1959 ዓ.ም. ከደበበ እሸቱ ጋር ወደሀንጋሪ ቡዳፔስት ተልኮ የሥነ-ተውኔት ሙያን ለሁለት ዓመታት አጥንቶ ተመለሰ:: ከሀንጋሪ እንደተመለሰ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አጫጭር ተውኔቶችን ማቅረብ ቀጠለ::
በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች እንግዳ የሆኑ “አስማተኛው፣ ቁንጫ፣ ባሉን፣ ቀለም ቀቢው፣ የተዘጋ በር” እና የመሳሰሉ ድምፅ አልባ (ማይም) ተውኔቶችን ማቅረብ በመጀመሩ ተደናቂነትን እያተፈ መጣ።
በ1962 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተቀጠረ:: የቲያትር ክፍሉ ኃላፊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይና እንዲሁም በሙያው ለመስራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በማስተማር ሁለጉብ አገልግሎት ሰጠ:: ከዚህ በኋላ ወደኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዛወረና በመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት ሲሰራ ቆየ::
በዚህ ሥራ ለአራት ዓመታት አገልግሎ በብሄራዊ ቴያትር ቤት ተቀጠረ:: በብሄራዊ ቲያትር ቤት ከተቀጠረበት ጊዜ ኣንስቶም ቀጥሎ በተዘረዘሩት ተውኔቶች አብይ ሚናዎች እየወከለ ተጫውቷል::
– የበጋ ሌሊት ራዕይ ፣   – ትግላችን፣
– ደመ መራራ ፣   – ደማችን፣
– ሀሁ በስድስት ወር፣  – ሞረሽ፣
– አፅም በየገፁ ፣   – ፀረ-ኰሎኒያሊስት፣
– እናት ዓለም ጠኑ ፣   – የአዛውንቶች ክበብ፣
– ዋናው ተቆጣጣሪ፣   – ፍርዱን ለእናንተ ፣
– ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት፣   – ክራር ሲከር፣
– ሀምሌት ፣   – ሊየር ነጋሲ ፣
– የድል አጥቢያ አርበኛ፣   – ዘርዓይ ደረስ፣
– ገሞራው ፣   – አሉላ አባነጋና እና እናት ነሽ ናቸው::
ከነዚህ ተውኔቶች በአንዳንዶቹ በዋና አዘጋጅነትና በተዋናይነትም ሰርቷል:: ወጋየሁ ንጋቱ ከሚታወቅባቸው ተግባራቱ አንደኛው በሬዲዮ ያቀርብ የነበረው የመፅሃፍት ትረካ ነው:: በመፅሃፍት ዓለም ፕሮግራም በሬዲዮ ከተረካቸውና አድናቆትን ካተረፉለት መፅሃፍት መካከል የሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ሶስት መፅሃት ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ እና ማዕበል የአብዮት ማግስት የተባሉትና የገበየሁ አየለ ጣምራ ጦር ከተደራሲያን አዕምሮ የማይጠፉ ናቸው::
ሀዲስ አለማየሁ መፅሃፋቸው ተተርኮ እንዳለቀ ለወጋየሁ “እኔ ከፃፍኩት ይልቅ አንተ በህዝቡ አዕምሮ የሳልከው ይበልጣል ̈ የሚል የአድናቆት አስተያየት ሰጥተውታል::
በ1966 ዓ.ም. ፀጋዬ ገ/መድህን ከብሄራዊ ቲያትር እንዲነሱ ብዙ የቲያትር ቤቱ ሠራተኞች በተሳተፉበት ሠልፍ ውስጥ ሌላ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው በመደባለቃቸው እንደፀረ-አብዮተኛ ተቆጥሮ ለተወሰኑ ወራት ታስሮ ተፈቷል::
ወጋየሁ በ1977 ዓ.ም. ከባህል ሚኒስቴር ሠራተኞች መካከል ምሥጉን ሠራተኛ ተሰኝቶ ተሸልሟል:: ወጋየሁ ወደመጨረሻው የህይወት ዘመኑ በግልፅ አውጥቶ በማይናገራቸው ጉዳዮች ይበሳጭ እንደነበርና አብዝቶ የመጠጣት ችግርም አጋጥሞት እንደነበር ታውቋል።
ህዳር 6 ቀን 1982 ዓ.ም. ባደረበት ህመም ሳቢያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል::
Filed in: Amharic