>

የብሶት ፖለቲካ አዙሪት፤ በእኔ እና በእኛ ክቦች !!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የብሶት ፖለቲካ አዙሪት፤ በእኔ እና በእኛ ክቦች !!!

ያሬድ ሀይለማርያም
የዛሬ አመት ይችን ጽሑፍ ለአንባቢዎቼ አካፍዮ ነበር። እኛ እና በማንነት የተከለሉት ክቦቻችን ዛሬም ማዶና ማዶ አፋርጀውን በአብሮነት ውስጥ ልዩነቶቻችንን አጉልተው እያሳዩን ነው። ይሄን ሰሞን ደግሞ ከብሔር ክቦቻችን ይልቅ የኃይማኖት ክልሎቻችን ጎልተው እንዲወጡ እየተደረገ እና ወደ ግጭትም እንዲያመሩ ጥረት እየተደረገ ሳይ ይህ ጽሑፍ ትዝ አለኝ። ላላነበባችሁት እንድታነቡት፤ ላነበባችሁትም ዳግም እንድታሰላስሉት መልሼ ላካፍላችሁ ወደድኩ። 
 
በእኛነት የተካለሉት ክቦቻችን በጥንቃቄ ካልያዝናቸው የት ያደርሱን ይሆን? እርሶንስ የትኛው ክብ ይገልጽዎታል?
 
ሰዎች ብሶታቸውን ለመወጣት ወይም የጎደለ ጥቅማቸውን ለማሳካት ሊደራጁ እና ሊታገሉ ይችላለሉ። መብትም ነው። የመደራጀት መብት አንዱ እና ከጀርባው ያለው አመክንዮም ሰዎች በተናጠል ሊያሳኩት ያልቻሉትን ጉዳይ ወይም የጎደለባቸውን ጥቅም ወይም ሊያገኙ የሚመኙትን ወይም ያገኙትን ይዞ ለማቆየት ሲሉ ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር ህብር ይፈጥራሉ። ልጥ ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው ሁሉ በጋራ በመቆም ህልማቸውን ያሳካሉ፣ ጥማታቸውን ያረካሉ፣ የጎደለባቸውን ይሞላሉ፣ ካሰቡት ለመድረስም በተሻለ አቅም ይተጋሉ። መደራጀት ከዚህ ያለፈ ፋይዳ የለውም። ሰዎች በመደራጀት ሊያገኙት የሚችሉትን ዋና ጥቅም እና ግብ በግላቸው ሊያሳኩ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ እድር፣ እቁብ፣ ጽዋ ማህበር፣ የኃይማኖት ድርጅት፣ የፖለቲካ ድርጅት፣ የሙያ ማህበር፣ የበጎ አድራጎት ማህበር፣ ወዘተ የሚባሉ የማህበር ኮልኮሌዎች አይኖሩም ነበር።
የሰው ልጁ በተፈጥሮም ግለኛ ነው። ሁሉን ነገር ለራሱ እና በራዙ ዙሪያ ነው የሚያስበው። እኔ ብሉ ይጀምራል ከዛም እኛ ብሎ ይጨርሳል። በእኛ ውስጥም እኔ አለ። እራሱን የሁሉም ነገር ስበት ማዕከል አድርጎ ነው የሚያስበው። እኔ እና እኛ በሚለው ውስጥ እራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ልጆቹን፣ ካገባም የትዳር አጋሩን፣ ዘመድ አዝማዱን፣ የዘር ሃረግ፣ ጎሳ፣ የትውልድ አካባቢ፣ አገር እያለ እንደ ጭንቅላቱ ስፋት አለም አቀፍ የእኔ እና የእኛ መገለጫ ማዕከሎች ይፈጥራል። የአንድ ሰው የእኔ እና እኛ ክብ ስብስቦች እንደ ሰውየው የእውቀት እና የማገናዘብ ችሎታ ይጠባል፤ ይሰፋልም።
የአንዳንድ ሰው የእኔ እና የእኛ ማዕከል ከራሱ ወይም ከቤተሰቡ ወይም በዘር ሃረግ ወይም በቋንቋ ወይም በጎሳ ከሚመሳሰሉት ጋር ብቻ ይወሰናል። ይህ አይነቱ ሰው እርምጃው ሁሉ በእነዚህ የእኔነት ክቦች የታጠረ ነው። ሲደራጅ፣ ሲበላም፣ ሲሰራም፣ ጥቅሙን ሲፈልግም፣ ሲያሰላም የሚሰባሰበው በእነዚህ ክቦች ዙሪያ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ለእናት እና ለአባቱ አንድ ሆኖ ተፈጥሮም የሰው ዘር ሁሉ ወንድሙ፣ እህቱ፣ ዘመዱ፣ የዘር ሃረጉ ይሆንና ከማንም ሰው ጋር ጸኦታ፣ ቀለም፣ እድሜ፣ የትውልድ ስፍራ ወይም የሃብት ምንጭ ሳይወስነው ይዛመዳል፣ ይቧደናል፣ አብሮ ይኖራል፣ አብሮ ይሠራል፣ አብሮ ይበላል፣ አብሮ መከራን ይጋፈጣል፣ አብሮ ያቅዳል፣ የራሱ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሰዎች ጉዳይ ሁሉ ያሳስበዋል፣ የራሱም ጉዳይ የሌሎች ጉዳይ እንደሆነ ያህል ይሰማዋል።
ወደ ተነሳሁበት ዋና ርዕስ ልመለስና የብሶት ፖለቲካ ሁል ጊዜ በክቦች የታጠረ ነው። አንድ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ወይም አንድ የጋራ የሚያዛምድ የጥቅም ትስስር ያላቸው ሰዎች ጎደለብን ያሉትን ጉዳይ የፖለቲካ መዘውሩን በመያዝ ለመሙላት፣ የተነጠቁትን ለማስመለስ፣ የተመኙትን ለማሳካት በፖለቲካ ድርጅት ተቧድነው ወደ ትግል ሊገቡ ይችላሉ። ይህ አይነቱ መቧደን በራሱ ምንም ችግር የለበትም። በፖለቲካ የመቧደን ፋይዳውም ከዚህ የዘለለ ላይሆን ይችላል። ችግር የሚፈጠረው የተቧደንንበት የፖለቲካ ክብ ስፋት እና ጥበት፤ አቃፊነት እና አግላይነት ላይ ነው። እነ ማንን አቅፎ እነ ማንን ያገላል፣ ምን ያህል አሳታፊ ነው፣ ምን ያህል አግላይ ነው የሚሉት ነጥቦች የፖለቲካ ክቡን የፈጠሩት ሰዎችን ማንነት፣ ባህሪ፣ የዕውቀት ደረጃ እና ስነ ልቦናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
አቃፊ የሆነው የፖለቲካ ክብ በጠበበ ቁጥር የተሳታፊው መጠን ይጠባል። በውስጡ የሚሳተፉም ሆኑ የሚታቀፉ ሰዎች ቁጥር የዛኑ ያህሉ ውሱን ይሆናል። የአቃፊነቱ መለኪያው አንድ የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ወይም ርዮተ አለም ሲሆን እና ከማንነት መገለጫዎች ከሆኑት በአንዱ ላይ የተመሰረተ ሲሆን እንዲሁ አቃፊነቱም ሆነ አግላይነቱ የተለያየ ይሆናል። የሃሳብ ወይም የአመለካከት ማዕቀፍ ሲሆን በክቡ ውስጥ ለመታቀፍ መስፈርቱ ያንን ገዢ የሆነ ሃሳብ የራስ ማድረግ ብቻ ነው። ስለዚህ ያንን ሃሳብ የሚደግፍ ማንኛውም ሰው ሌሎች የሕግ መስፈርቶች እንደተጠቡቁ ሆነው በተዋቀረው የፖለቲካ ክብ ውስጥ ሊታቀፍ ይችላል።
በሃሳብ ላይ የተሰመሩ የፖለቲካ ማቀንቀኛ ክቦች ሰፊ እና አቃፊዎች ናቸው። መገለልም ሆን መታቀፍ ለእያንዳንዱ ሰው የተተዉ ምርጫዎች ናቸው። በፖለቲካ አደረጃጀት ደረጃ ትልቁ ክብም ይኼው በሃሳብ ላይ ወይም በአመለካከት ላይ የሚዋቀረው የፖለቲካ ማዕቀፍ ነው። በምሳሌ ለማስረዳት ዲሞክራት ወይም ሪፐብሊካን፣ ሶሻሊስት ወይም ሊብራል የሚሉት ማዕቀፎች የአመለካከት መሰረቶች ናቸው።
ከላይ ከተገለጹት ማዕቀፎች ጠበብ ሲል ደግሞ፤ የሠራተኖች ፓርቲ፣ የክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ፣ የአርሶ አደሮች፣ የሴቶች፣ የገጠር ነዋሪዎች፣ የከተማ እያለ ይቀጥላል። እነዚህ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ በባህሪያቸው አግላይ ቢሆኑም ሰፊ የሆነ የህብረተሰብ ክፍልን የሚያቅፉ ናቸው። በውስጣቸው በብዙ ነገሮች የተለያየ መገለጫ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ያቅፋሉ። ከዚህ ወረድ ሲል ያለው አደረጃጀት ደግሞ የመሬት አከላለልን ወይም አንድ በተወሰነ ቦታ ላይ የተማከለ አደረጃጀት ነው። እንዲህ እያለ ክቡ ወደ ታች በወረደ መጠን እየጠበበ ይሄዳል። ብሔርን፣ ቋንቋን፣ ዘርን፣ ጎሳን፣ ጎጥን፣ መንደርን እያማከለ ይሄዳል።
ብሔርን፣ ቋንቋን፣ ዘርን፣ ጎሳን፣ ጎጥን እያማከለ የሚወርደው የፖለቲካ አደረጃጀት ክብ የመደራጃ መሰረቱም ሆነ መስፈርቱ ሃሳብ ወይም የፖለቲካ እርዮተ አለም አይደለም። እነዚህን የማንነት መገለጫዎች ማሟላት ብቻ በቂ ነው። የአንድ ብሄር አባል መሆን በዛ ብሔር ስም በሚዋቀረው ክብ ውስጥ ለመታቀፍ በቂ ነው። የአንድ ጎሣ አባል መሆን በጎሣ ደረጃ ለሚዋቀረው ክብ በቂ መመዘና ነው። በዛኑ መጠን ክቡ የተዋቀረበት ብሄር ወይም ጎሣ ወይም ዘር አባል ያልሆነ ሰው በእነዚህ ክቦች ውስጥ ታቃፊ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ በጥበትም ይሁን በአግላይነት የመጨረሻውን ደረጃ የሚይዙት እነዚህ የማንነት መገለጫ በሆኑት መስፈርቶች ዙሪያ የሚዋቀሩ ክቦች ናቸው።
ክቦቹ በጠበቡ ቁጥር ከትልቁ የሃሳብ እና የፖለቲካ እርዮተ አለም ምልከታዎች እየራቅን እንሄዳለን። ሃሳብ እየመነመነ ማንነት እየጠበደለ ይሄዳል። ሃሳብ የሚመነምንበት ቦታ ላይ ብዙ መመራመር፣ ቡዙ ማወቅና መማር፣ ብዙ መፈላሰፍ፣ ብዙ ለእውቀት እና አዲስ የፖለቲካ አመለካከት ለማፍለቅም ሆነ ለመቀበል የሚሆን ቦታ የለም። እነኚህ የማንነት መገለጫዎች ጠባቡን ክብ ስለሚሞሉት የዛ ማንነት ባለበት መሆን ብቻውን የክቡ እድገት መገለጫ ነው። እንዲህ ያሉ በማንነት ላይ የተዋቀሩ የፖለቲካ ክቦች የጥንካሬያቸው መገለጫ የፖለቲካ ሃሳባቸው በሳይንሳዊ ምርምር መደገፍ ወይም የረቀቀ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማፍለቅ መቻል ወይም በአዳዲስ የፖለቲካ ሃሳቦች መምጠቅ አይደለም። ትልቁ ጥንካሬያቸው ከኋላ የሚያሰልፉት ሰልፈኛ እርዝመት ወይም ብዛት እና ማንነት ነው። ስንት አማራ፣ ስንት ኦሮሞ፣ ስንት ትግሬ፣ ስንት ጉራጌ፣ ስንት ወላይታ፣ ስንት ከንባታ፣ ስንት አፋር፣ ስንት ጋሙ፣ ስንት ሲዳማ፣ ወዘተ …። ለእነዚህ አይነት አደረጃጀቶች አጠገባቸው ካለው እና ተመሳሳይ ብሶት ካለበት የሌላ ብሔር ተወላጅ ይልቅ በእርቁ ያለው እና የእኔ ብሄር አባል የሚሉት ነገር ግን የማያውቁት ሰው ከፍ ያለ ዋጋ አለው።
እነዚህ ክቦች የተፈጠሩት በማንነት መገለጫ ልክ ስለሆነ አሻግረው በሌላ የማንነት ክብ ውስጥ ያሉትን አያዩም። ካዩም በፉክክር መንፈስ እንጂ ክቦቹን በማስፋት ወደ አንድ ክብ ለመጠቃለል አይሆንም። በማንነት መገለጫዎች የሚዋቀሩት የፖለቲካ ማዕቀፎች ከጥንስስ ሃሳባቸው አንስቶ የድርጅት ቅርጽ ይዘው አደባባይ የሚወጡት የብሶት ክምር ይዘው ውንጂ የፖለቲካ ማቀንቀኛ ንድፈ ሃሳብ ወይም የተለየ እርዮት አለም አይደለም። በብሶት ይጠነሰሳስሉ፣ በብሶቱ ያድጋሉ፣ በብሶት ጡዘት ይጎለምሳሉ፣ በብሶት ያረጃሉ፣ ከነብሶታቸ ግን አይከስሙም ሌላ ሆድ የባሰው ጨቅላ ተክተው ያልፋሉ። የብሶት ፖለቲካ ዋና ግቡ በክቡ ውስጥ ያሉትን ሰዎች መሰረታዊ የሆኑ ችግሮችን መፍታት እና ሆድ የባሰው ሌላ ትውልድ እንዳይፈጠር ምንጩን መድፈን ሲሆን ግባቸውን ካሳኩ በኋላ አንድም ይከስማሉ አለያም ክቡን አስፍተው ወደ ሃሳቦ ጎዳና ይመጡና በእርዮት አለም ላይ የሚያጠነጥ ፖለቲካ ያራምዳሉ።
የብሶት ድርጅቶች አላማቸው ሆድ በባሰው ሕዝም ስም መነገድ እና የሥልጣን ጥማታቸውን ማርካት ከሆነ ግን እራሳቸውም ብሶት አፍላቂ ይሆናሉ። ቦሶት እንዳይነጥፍ እና ህልውናቸውም አብሮ እንዳያከትም የቆየ ቁስል መጎድፈር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ቁስልም የመፍጠር አቅም እና ችሎታ ይዘው ይወጣሉ። ብሶት ከመታገያነት አልፎም የህልውና ማስጠበቂያ መሣሪያ ይሆናል።
የብሔር ድርጅቶች ሁሌም የሚያነሱት የመሟገቻ ሃሳባቸው እንታገልለታለን የሚሉት እና በክባቸው ውስጥ በሃሳብም ቢሆን የከተቱት የህብረተሰብ ክፍል ያጣቸው፣ ያልተከበሩለት እና የተነፈጉት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ሌሎች ጥቅሞች አሉ የሚል ነው። እነዚህን ጥቅሞች የፖለቲካ ሥልጣኑን በመያዝ እናስከብራለን ባዮች ናቸው። በእርግጥ የፖለቲካ ሥልጣን የፈለጉትን ጥቅም ለማስጠበቂያ የሚረዳ መሳሪያ ነው። ሰዎች በማንነታቸው የተነሳ የተነፈጉትን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በተለያዩ መልኩ ሊደራጁ እና ሊታገሉ ይችላሉ። ለሥልጣን መታገል ግን ሌላ ገጽታ አለው።
ሕውሃትን ጨምሮ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት ብዙዎቹ ድርጅቶች ለአሥርት አመታት የታገሉት በዚህ መነሻ ሃሳብ ነው። ስልጣን ሲይዙ ግን ታገልንለት የሚሉት ሕዝብ ትዝ አላላቸውም። የታገሉበትን አሥርት አመታት ትተን ሥልጣን ላይ በወጡ ከሃያ ሰባት አመታት ቆይታ በኋላም እንታገልለታለን ያሉት ህዝም በብሶት ላይ ብሶት ተደርቶበት መገኘቱ የብሶት ፖለቲካን ባህሪ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ብሶት የወለዳቸው የዛሬዎቹ ገዢዎች ሥልጣን ሲይዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶት ቢለካ ምናልባት ወገቡ ድረስ ውጦት ይሆናል። ከሃያ ሰባት አመት የብሶት ፖለቲካ ምሪት በኋላ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶት እንደተራራ ገዝፎ እና ተቆልሎ አንዱ ብሔር ሌላውን እንዳያይ ጋርዶታል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሶት ያልዋጠው የህብረተሰብ ክፍል የለም። ሁሉም ብሶተኛ ነው። ኢትዮጵያ በብዙ የብሶት ተራራዎች ተውጣለች። የኃይማኖት ብሶት፣ የብሔር ብሶት፣ የክልል ብሶት፣ የማንነት ብሶት፣ ብሶት በብሶት ሆነናል። ሁሉም በደጃፉ እና በተቧደነበት ክብ ውስጥ በተቆለለው ብሶት ተውጧል። ብሄረተኝነት እና ብሶት ሲገናኙ ደግሞ ቤንዚን እና እሳት እንደማለት ነው። በብሶት ቁልላቸው የሚፎካከሩት የብሄር ብሶት ፖለቲከኞች ጡዘቱን ሰለሚያከሩት አንዱ ብሶተኛ ሌላውን አያዳምጥም። ከባልሽ ባሌ አይነት፤ ከአንተ ብሶት የኔ ብሶት ይበልጣል እያለ ሁሉም ስለሚጮኽ አድማጭ አይኖርም። ብንደማመጥ ሁላችንም ተመሳሳይ ብሶት የዋጠን የመጥፎ ሥርዓቶች ሰለባዎች ነን።
የብሄር ብሶት አቀንቃኝ ድርጅቶች እድሜ ሊኖራቸው የሚችለው ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን መነሻ ስለሚያደርጉ ነው። አንደኛው በእርግጥ በዛ አገር ታሪክ ውስጥ በአንድ ዘር ላይ ወይም በአንድ ብሔር ላይ ብቻ ወይም በአንድ የተለየ የማንነት መገለጫ ባለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ብቻ ያነጣጠረ እና አግላይ የነበረ መንግስታዊ አስተዳደር ከነበረ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህ አይነቱ በአንድ የህብረተሰብ ክፍል ማንነት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ወይም በደል ዛሬም ቀጥሏል ወይ የሚለው ነው። ሦስተኛው ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ በማንነት መድልዎ የተነሳ የተፈጠሩትን ችግሮች፣ የምጣኔ ሃብት እና ሌሎች የጥቅም መበላለጦችን ያስከተሉት አሰራሮች እና ጥቃቶች ወደፊትም ይቀጥላሉ የሚል ስጋት ሲኖር ነው።
ከአርባ አመት በላይ በዚህ ፖለቲካ ያረጁ እና ያፈጁ ድርጅቶች ዛሬም በዛው አደርጃጀታቸው በቀጠሉበት እና አዳዲስ ግልገል ብሔረተኛ ድርጅቶች እየፈለቁ ባለበት አገር ከብሶት እና ከብሄር ተኮር ፖለቲካ ወደ ሃሳብ ፖለቲካ የሚደረገው ሽግግር እንዲህ ቀላል አይሆንም። አሁን የታየችውን የተስፋ ጭላንጭል ያዩ ብዙዎች የዘር ፖለቲካ በማግስቱ ተጠራርጎ ጠፍቶ ለማየት መመኘታቸው ትንሽ የዋህነት ይመስለኛል።
የብሔር ፖለቲካ ከኢትዮጵያ እንዲህ በአጭር ጊዜ እና በቀላሉ ይጠፋል የሚል እምነት የለኝም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ጠቅሼ ሃሳቤን ልቋጭ። አንደኛው የዘር ፖለቲካው የመሸገባቸው የብሶት ተራራዎች እንኳን ሊከስሙ ጭራሽ እየገዘፉ አገራዊ እይታችንንም እየጋረደን ነው። እንዲህ በቀላሉም የሚናዱ አይመስለኝም። ሊናዱ የሚችሉት ብሶቶቹን በአግባቡ ሊመልስ የሚችል እና ምንጫቸውንም የሚያነጥፍ ሥርዓተ መንግሥት በአግባቡ ሲዋቀር እና እነዚህ የሕዝብ ብሶቶች በአግባቡ ተጠንተው በጥንቃቄ በተቀረጹ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ምላሽ ሲያገኙ፤ በተጨማሪም ተቋማዊ ዋስትና ሲኖራቸው ነው። ሁለተኛው ግን የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞችም ሆነ የብሔር ስታቴጂስቶች ከታሪክ የሚቆፍሩት የብሶት ቁስል አልበቃ ሲላቸው አዳዲስ ብሶቶች እንዲፈበረኩ የሚያደርትን እኩይ እንቅስቃሴ ማቆም ሲችሉ ነው። ብሶት እና ሕዝብን በማንነቴ ተጠቅቻለው ብሎ እንዲያስብ የሚያደርጉት ነገሮች የእዝጌር ቁጣ ወይም ከሰማይ የሚወርዱ ነገሮች አይደሉም። አብዛኛዎች በፖለቲከኞች እኩይ እሳቤ እና ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ እና የሃሰት ትርክቶች የሚፈበረኩ ናቸው።
ሕዝብን በዘር ለማቧደን በመጀመሪያ በዘሬ ተበድያለሁ ብሎ እንዲያስብ ማድረግን ይጠይቃል። ይህን ደግሞ አንድም በትክክል የተፈጠሩ በደሎችን ደጋግሞ በመንገር ሕዝቡን የብሄር ብሶተኛ ማድረግ ይቻላል። ሁለተኛው ደግሞ በታሪክ የተፈጠሩትን በደሎች ሁሉ ችላ ብሎ ወይም በሁሉም ላይ የደረሰ ነው ብሎ አስቦ የብሄረተኝነት ከረጢት ውስጥ አልገባም ያለውን ሰው የጥቃት ሰለባ እንዲሆን ማድረግ ነው። ከመኖሪያ ቦታው ከሌሎች ነጥሎ ማፈናቀል፣ ከትምህርት ገበታው ማባረር፣ ማዋከብ እና ማሳደድ አንዱ ስልት ነው። በማንነቱ ላይ የተነጣጠሩ ጥቃቶች እንደ ክረምት ዝናብ ዛሬም ነገም እየመጣ መጠለያ ሲያሳጣው ያኔ የዘር ጥቃት ምን እንደሆነ ይገባዋል። ያኔ በዘሩ ይደራጃል። ያኔ እራሱን ከጥቃት የተከላከለ ይመስለውና ወደ መከላከል ይገባል። ያኔ በተፈበረከ ብሶት ተጠልፎ ወደ ብሔረተኝነት መንደር ይገባል። የሚፈለገውም ይሄው ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የብሔር ፖለቲካን ማሳካት የሚቻለው ሁሉንም ብሔረተኛ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው። አንድ ብሔር በብሔሩ ተደራጅቶ ሌሎች ህብረ ብሔራዊ ሆነው ቢቀጥሉ ለብሔረተኛው ድርጅት ኪሳራ ነው። አያተርፍም። እሱ ወደ ሌሎቹ መንደር ባይሔድም ህብረ ብሔር ድርጅቶቹ ግን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ ወደ እሱ መንደር ይመጣሉ። ያኔ ይዋጣል። ሁሉም ብሔረተኛ ከሆነ ግን ውድድሩ በየብሔሩ ስለሆነ አንዱ የሌላው ወዳጅ ባይሆንም ስጋት አይሆንም። የኦሮሞ ድርጅቶች ኦሮሚያ፤ የአማራ ድርጅቶች አማራ ክልል፤ የትግራዩ ትግራይን፤ የአፋሩ አፋርን ለማስተዳደር ስለሆነ ህልማቸው ሲሻቸው በፌደሬሽን አብረው ይኖራሉ። ሲሻቸው ሁሉም አገር ይሆናሉ። የመጣንበት የሃያ ሰባት አመት ጉዞ እውነታው ይሄው ነበር።
እነዚህን ጥያቄዎች ለእርሶ ልተውና ጽሁፌን ልቋጭ፤
በቀጣይ ወዴት እናመራ ይሆን?
እርሶስ እራስዎን በየትኛው ክብ ውስጥ ነው ያስቀመጡት?
በብሶት ወይስ በሃሳብ ፖለቲካ መቀጠል የሚፈልጉት?
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic