>

ህገ መንግስቱ አግላይ ነው የሚባለው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ?  (ግርማ ካሳ)

ህገ መንግስቱ አግላይ ነው የሚባለው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ?  

 

ግርማ ካሳ
 

• አብይ አህመድ ህገ-መንግስቱን መቀየር የማይፈልገው ለምንድነው?

በኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎች አሉ። ከትግራይ ክልል በስተቀር የሌሎች ክልሎች ሕግ መንግስታትን ለመመልከት እድል አግኝቻለሁ። #የክልል ሕግ መንግስታቱ በጣም ተመሳሳይነት አላቸው።
እንዲሁም  የፌዴራል መንግስቱን ሕገ መንግስት በቀጥታ የሚቃረኑ አንቀጾችም አሏቸው።
ለምሳሌ የክልሎችን ባላቤትነትን ( Sovereignity of the regions) ጉዳይ  የፌደራል መንግስቱ ሕገ መንግስት የሚለውን እንመልከት።
– አንቀጽ 38 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄር በብሄረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝቡ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ፣ የመምረጥ፣ በማናቸዉም የመንግስት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው ይላል።
• አንቀጽ 32 ደግሞ ማንኛውም  ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት መብት አለው ይላል።
ይሄ ማለት አንድ ኦሮሞ ትግራይ ሄዶ እዚያ ካለው ትግሬ እኩል የመኖር፣ የመመረጥና የመምረጥ መብት አለው።  አንድ ጉራጌ አፋር ክልል ሄዶ የመኖር፣ የመምረጥና የመመረጥ አለው ወይንም “አማራ ነኝ” የሚለው “ኦሮሞ ነኝ” ከሚለው የተለየ መብት በአማራ ክልል አይኖረዉም ማለት ነው። ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በመንግስት ስልጣን የመሳተፍ መብት አለው።
ሆኖም የክልል ህግ መንግስታት በቀጥታ የፌደራል ሕግ መንግስቱን ይቃረናሉ።
ምሳሌዎች እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
1.  በሃረሪ ክልል ራሳቸውን “ሃረሪ” ብለው የሚጠሩት ዜጎች የክልሉ 8% ብቻ ናቸው። ወደ 50% የሚሆኑት “ኦሮሞ ነን” ፣ 26% ፣ “አማራ ነን” የሚሉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወጣጡ ናቸው።
ሆኖም የሃረሬ ክልል ባለቤት የክልሉ 8% ነዋሪ የሆኑት ሃረሬዎች(አደሬዎች) ናቸው። የክልሉ ሕግ መንግስት አንቀጽ 8 ፣ “የሃረሬ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ስልጣን ባለቤት ሲሆን..” ብሎ ነው የሚጀምረው።
ይህ ማለት 92% የሚሆነው የክልሉ ነዋሪ የወሰነዉን 8% ካልተስማሙ አይጸድቅም፣ የሌላ ብሔር አባላትም የመንግስት ስልጣን በክልሉ አያገኙም ማለት ነው።  ሌሎች ብሔሮችን ያገላል።  ይህ በቀጥታ የፌደራል ህገ መንግስቱን ይፃረራል።
2. በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ52% በመቶ በላይ ነዋሪዎች ራሳቸውን ኦሮሞና አማራ ብለው የሚጠሩ ናቸው። ሆኖም የክልሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 2 መሰረት፣ በክልሉ እንደ “እንግዳ” ናቸው።
“በክልሉ ዉስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም፣ የክልሉ ባለቤት ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሸናሽ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው” ይላል የክልሉ ሕገ መንግስት።
3. በኦሮሞ ክልል ትላልቅ ከተሞች በብዛት የሚኖሩት ኦሮሞ ያልሆኑ ወይንም ከኦሮሞና ከሌላው ብሄረሰብ የተደባለቁ ሕብረብሄራዊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ለምሳሌ ከኦሮሞ ክልል ከአንድ እስከ 4 ያሉትን ትላልቅ ከተሞች (ናዝሬት፣ ጂማ፣ ሻሸመኔና ደብረዘይት) ብንወስድ አብዛኛው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ነው። በአዲስ ዙሪያ ባሉት የአራቱም የኦሮሞ የሸዋ ዞኖች የሚኖረዉን ሕዝብ ብንመለከት ወደ 44% የሚሆነው አማርኛ ተናጋሪ ነው።
ሆኖም የኦሮሞ ክልል ሕገ መንግስት በአንቀጽ 8 ላይ “የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ #የበላይ ስልጣን ባለቤት ሲሆን…” ብሎ ይጀምራል።  ይህ ማለት ሌላ ብሔር ያላቸው ዜጎች በኦሮሞ ክልል መንግስታዊ ስልጣንም ሆነ ስራ አይሰጣቸውም ማለት ነው።
በአንቀጽ 38 ማንኛውም ዜጋ የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው ቢልም “በዚህ ሕግ መንግስት አንቀጽ 33 የተጻፈው እንደተጠበቀ ሆኖ” በሚለው አባባል የዜጎችን የመመረጥ መብት #ይደፈጥጣል።
አንቀጽ 33፣ የክልሉን የሥራ ቋንቋ የማያውቅ በማንኛውም የክልሉ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ሥራ ተመርጦ ወይንም ተቀጥሮ የመስራት መብት እንደሌለው ያስቀምጣል።
ስለዚህ በኦሮሞ ክልል ትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ ኦሮምኛ የማያውቁ በኦሮሞ ክልል የመንግስት አካል መሆን አይችሉም።
4. የአፋርና የሶማሌም ክልሎች ባለቤት የሆኑት የአፋርና የሶማሌ ብሄረሰቦች ናቸው። በነዚህ ክልሎች ነዋሪው በአብዛኛው ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ አፋር፣ ወይንም ሶማሌ በመሆኑ ችግሩ ጎልቶ ባይታየም፣ ተመሳሳይ የመብት ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።
5. በአንፃሩ የአማራ ክልል ህገመንግስት ከፌዴራል ሕግ መንግስት ጋር የሚቀራርረብ ሲሆን ከኦሮሞ፣ ከሀረሪ እና ከቤኒሻንጉል #የሚቃረን ነው።
ክልሉ የአንድ ዘር ወይንም ብሄረሰብ አይደም።
የአማራ ክልል ህገ መንግስት ‘“አማራ” የሚሉት የአማራው ክልል ባለቤት #አይደለም ፤ በክልሉ የሚኖሩ ብሄረሰቦች በሙሉ የክልሉ ባለቤት ናቸው ይላል።
“የአማራው ክልል ሕግ መንግስት አንቀጽ 8 “የአማራ ክልል ሕዝቦች የብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የበላይ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ናቸው ይላል።
6.  በተመሳሳይ የጋምቤላና የደቡብ ክልል ሕገ መንግስታት ከፌደራል ህገ መንግስቱ ጋር ይቀራረባል።
የጋምቤላ ሕግ መንግስት አንቀጽ 9.1 “ የጋምቤላ ሕዝቦች ብሄራዊ ክልል ሕዝብ የክልሉ ብሄራዊ መንግስት የበላይነት ስልጣን ባለቤት ናቸው” ሲል የደቡብ ክልል ሕግ መንግስት ደግሞ በአንቀጽ 8 “የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የክልሉ መንግስት የበላይ ስልጣን ባላቤቶች ናቸው” ሲል ክልሉ የአንድ ዘር ሳይሆን በክልሉ የሚኖሩ የሁሉም እንደሆነ ያስቀምጣል።
ሆኖም በደቡብ ክልል የዘር ክፍፍሉ ወደ ዞን ይወርዳል፡ ለምሳሌ የሲዳማ ዞን የሲዳማዎች እንደሆነ ነው ተደረጎ የሚቆጠረው።
7. የትግራይን ክልል ሕገ መንግስት ለማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ አስተያየት ብዙ አልሰጠሁበትም። ግን በትግራይ የሥራ ቋንቋ ትግርኛ መሆኑና እንደ ኦሮሞ ክልል ትግርኛ የማይናገር በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ የመስራት መብት እንደለለው ግን የሚታወቅ ነው።
ለምሳሌ ትግራይ የሚኖር ኦሮሞ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ መስራት አይችልም።
በተለይም ራሳቸው “ትግሬ  አይደለንም” የሚሉ ከጎንደርና ከወሎ ተቆርሰው ወደ ትግራይ በተጠቃለሉ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች መብታቸው የሚጨፈለቅበት ሁኔታ በስፋት ሊኖር እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
Filed in: Amharic