>
8:38 am - Saturday November 26, 2022

የናይል ተፋሰስ ተለዋዋጭ የውኃ ፖለቲካና ተቋማዊ ገፅታዎች (ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ)

የናይል ተፋሰስ ተለዋዋጭ የውኃ ፖለቲካና ተቋማዊ ገፅታዎች

 

ተስፋዬ ታፈሰ (ፕሮፌሰር)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም የጂኦፖሊቲክስና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፌሰር

 

ይህ አጭር ፅሑፍ በናይል ተፋሰስ ተቋማዊና የውኃ ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለመንደርደሪያ በሚሆን መግቢያ ይጀምርና ስለ ናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ (Nile Basin Cooperative Framework Agreement-CFA) ፍሬ ነገርና ያጋጠሙት ተግዳሮቶች እንዲሁም ስለ ውኃው ፖለቲካ ሁኔታ አትቶ በማጠቃለያ መልክ አንዳንድ መፍትሔ ሃሳቦችን ይጠቁማል፡፡ 

መግቢያ

 

የናይል ተፋሰስ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙት ችግሮችና ተግዳሮቶች በአምስት ተከፍለው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ አንደኛ፡- በላይኛው ተፋሰስ አገሮች በተለይም በኢትዮጵያ የሚታየው የአካባቢ መራቆት፣ የተፋሰስ እንክብካቤ አለመኖር፣ የአፈር መሸርሸር፣ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች በደለል መሞላትና የግድቦች እድሜ ማጠር፤ ሁለተኛ፡-የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድርቅና የውኃ እጥረት፤ ሦስተኛ፡- የውኃ ማኔጅመንትና የውኃ ቴክኖሎጂ በተፋሰሱ ደካማ መሆን የናይል ውኃ አጠቃቀምን እንዲዝረከረክ ማድረጉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የጠብታ መስኖ (drip irrigation) በተፋሰሱ ጥቅም ላይ አለመዋል 48% የሚሆነውን ለእርሻ የሚውል ውኃ እንዳይቆጠብ አድርጎታል፡፡ አራተኛ፡- በተፋሰሱ እየተመዘገበ ያለው የሕዝብ እድገት ካለው የተፈጥሮ ኃብት መጠን ጋር በተለይም የውኃ መጠን ጋር ያለመመጣጠን፡፡ ለመረጃ ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከ100 ሚሊዮን ካለፈ ሰንበትበት ቢልም የግብፅም ሕዝብ ብዛት እዚህ አሃዝ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ አምስተኛ፡- ምንም እንኳን እስከዛሬ ሦስት የናይል ተፋሰስ ተቋማት የተፈጠሩ ቢሆንም (ሃይድሮሜት ከአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1967-1992፣ ቴኮናይል ከ1992-1999 እና የናይል ተፋሰስ ጅማሮ ከ1999 ጀምሮ እስካሁን) ብዙዎቹ በግብፅ ፊትአውራሪነት የተመሰረቱ ስለነበር ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች የተስማሙበትና የተፈራረሙበት ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ እስከዛሬ ሊኖር አልቻለም፡፡

 

የናይል ትብብር ማዕቀፍ (Nile Cooperative Framework Agreement) 

 

ይህንን ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ (Legal and Institutional Framework) ለማዘጋጀትና ለውይይት ለማቅረብ ወደ 10 ዓመታት ፈጅቷል (እ.አ.አ 1997-2007)፡፡ ዋናው የዚህ ማዕቀፍ አላማ የናይል ወንዝ እንደሌሎች ድንበር ዘለል ወይንም አገር አቋራጭ ወንዞች (ለምሳሌ ሚኮንግ፣ ሴኔጋል፣ ኮሎራዶ፣ ራይን ወዘተ) የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ወይንም ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ኖሮት ቋሚ የሆነ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን (Nile River Basic Commission) ለማቋቋም ነው፡፡ ረቂቅ ሰነዱ የተዘጋጀው የተለያዩ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ልምድና እ.ኤ.አ. የ1997 የተባበሩት መንግሥታትን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን (UN Convention on the Law of the Non-Navigational Uses of International Water Courses) በመንተራስ ነው፡፡ ዋናው አላማው ፍትሐዊ ክፍፍልንና (equitable entitlement) በሌላ ተፋሰስ አገር ላይ ጉዳት አለማድረስ (no-harm rule) ጎን ለጎንና ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሰነዱ (ማለትም የCFAው) አንቀፅ 4.1. ስለፍትሐዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም ሲያትት አንቀፅ 5.1 ደግሞ ሌላ ተፋሰስ አገር ላይ ጉዳት አለማድረስን ይጠቅሳል፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ማዕቀፉ የናይል ውኃን እንክብካቤ፣ አጠቃቀም፣ ቁጠባና እድገትን ተግባራዊ ለማድረግ የተነደፈ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ብዙ ከተተቸበት በኋላ (ፀጉር ስንጠቃንም ጨምሮ) ተጠናቆ ወደ ፊርማና ብሎም ማፅደቅ (ratification) ሊደርስ ሲል የታችኛው ተፋሰስ አገሮች አንዱን ንዑስ አንቀፅ (14ለን) መዘው አውጥተው ይህ ካልተለወጠ ወይንም እኛ በፈለግነው መንገድ ካልተስተካከለ ሰነዱን ለመፈረም ዝግጁ አይደለንም ብለው በይፋ ገለፁ፡፡ በነሱ ሀሳብ መሰረት ሰነዱ ላይ የተቀመጠውን ንዑስ አንቀፅ 14ለ ‹‹not to cause significant harm to the water security of any other Nile basin countries›› (በማንኛውም የተፋስሱ አገሮች ላይ የውኃ ዋስትናን የሚፈታተን ጉዳት አለማድረስ) የሚለውን ‹‹not to adversely affect the water security of current users and the rights of any other Nile Basin countries›› (ባሁኑ ጊዜ የውኃው ተጠቃሚ የሆኑትን የተፋሰሱ አገሮችና ሌሎቹንም ጨምሮ የተጠቃሚ መብታቸውንና የውኃ ዋስትናቸው ላይ ጉዳት አለማድረስ) በሚል እንዲተካ ነው የጠየቁት፡፡ ይህንን በማድረግ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ማለትም ግብፅና ሱዳን ሁለት መሰረተ ሃሳቦችን ማለትም የውኃ ደህንነት መጠበቅና ቀደምት የናይል ስምምነቶች (እ.አ.አ. 1902፣ 1929፣ 1959) እንዲከበሩላቸው ነው የፈለጉት፡፡ ይህንን የሐረግ ለውጥ ሁሉም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በአንድ ድምፅ ተቃውመውታል፡፡  እንደዛም ሆኖ ማለት ልዩነቶቹ እንዳሉ ሆነው ሰነዱ ከእ.አ.አ. May 2010 ጀምሮ የአንድ ዓመት የፊርማ ጊዜ ተሰጥቶት እንቴቤ በሚገኘው የናይል ሴክሬታሪያት ተቀምጧል፡፡ እስካሁን ስድስት የላይኛው ተፋሰስ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ርዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ታንዛንያ) ፈርመውታል ከነዚህም ውስጥ የመጀመርያዎቹ ሦስቱ ለፓርላማዎቻቸው አቅርበው አፅድቀውታል፡፡ ምንም እንኳን በሕጉ መሰረት ሁለት ሦስተኛ አገሮች ከፈረሙት ሰነዱ የሚጸድቅ ቢሆንም የናይል ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት የሌሎቹን ተፋሰስ አገሮች መፈረም በትዕግስት እየተጠባበቀ የሚገኝ ይመስላል፡፡ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የቀሩት ሦስቱ የተፋሰሱ አገሮች ለፓርላማዎቻቸው አቅርበው ካፀደቁ ቁጥራቸው ወደ ስድስት ስለሚያድግ ሰነዱ (ማለት CFAው) በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን ይችላል፡፡

ግብፅ ይህንን ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ለመፈረም ያልፈለገችባቸውን ምክንያቶች በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛ ሰነዱ የማይነካ ድርሻዬን (acquired/natural/historical right) እንደገና እንዲታይ/እንዲከለስ ሊያደርግብኝ ይችላል ከሚል ስጋት የመነጨ፣ ሁለተኛ ምንም እኳን በሕግ የተደገፈ ባይሆንም ግብፅ ለብዙ ዘመናት በተፋሰሱ ስትተገብረው የቆየችውን የማገጃ ድምፅ ወይንም ቃልን በቃል የመሻር መብት (veto right) ይቀንስብኛል ከሚል ፍርሃት የተፈጠረ እንዲሁም ሦስተኛ ማንኛውም በናይል ወንዝ ላይ የሚደረግ የልማት ሥራና እንቅስቃሴ የቅድሚያ ማሳወቂያ (prior notification) ምልክት ሳይሰጠኝ እንዲሁም የጉዳት አለማድረስ (no harm rule) ሳይተገበር መከናወን የለበትም የሚል አቋም ስላላት ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡

ከታች ወረድ ብለን እንደምናየው የሱዳን ሰነዱን አልፈርምም ማለት ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከመስጠቷ ጋር ስለሚጣረስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሰነዱን ልትፈርም ትችላለች የሚለው እሳቤ ሚዛን የሚደፋ ይመስላል፡፡ በዚህ ፀሐፊ አስተያት በቅርቡ የመንግሥት ለውጥ የተካሄደባት ሱዳን በናይል የውኃ ፖለቲካ የሚኖራትን የወደፊት አቅዋም ከወዲሁ ለመገመት ያስቸግራል፡፡ ያለው ምርጫ ሁኔታዎችንና ሂደቶችን በጥሞና መከታተል ነው፡፡

 

የናይል ተፋሰስ ተለዋዋጭ የውኃ ፖለቲካ ሁኔታ

 

ለዘመናት የቆየው የናይል ተፋሰስ ነባራዊ ሁኔታ (status quo) በአጭር ጊዜያት ማለት ባለፉት አስር ዓመታት ያልተጠበቀ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ይህንን ለውጥ ካመጡት መካከል ዋና ዋና የሚባሉትን ስድስት ክስተቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሀ. የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን የውኃ ፖለቲካ አቅጣጫ በከፍተኛ ሁኔታ ማስለውጥ

ለ. የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበርና አንድ ዓይነት አቋም መያዝ

ሐ. የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የፖለቲካና ኢኮኖሚ አቅማቸውና ተሰሚነታቸው በአንፃራዊ መልክ መጎልበቱ

መ. የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የተለመዱትን/የታወቁትን ዓለምአቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶችን (ለምሳሌ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ወዘተ) ወደጎን በመተው ሌሎች አማራጮችን (ምሳሌ – ቻይናን፣ ብሪክስንና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን) መጠቀም መጀመራቸው

ሰ. የሱዳን ባልተጠበቀና ባልታሰበ ሁኔታ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ምንም እንኩን ለራስዋ ብላ ቢሆንም በማያወላውል ሁኔታ መደገፏ

ረ. የግብፅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጡንቻዎች መላላትና ላለፉት አስር ዓመታት በፖለቲካ ውጥረት ውስጥ መገኘት እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ያላት ተፅእኖ መቀነስ

 

ከላይ ከተጠቀሱት ስድስት ነጥቦች ውስጥ አንዱና ዋነኛ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው የሱዳን ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ የመደገፏን ምክንያቶች ማወቅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ሰባት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛ፡- ከሕዳሴው ግድብ በስተጀርባ የሚታቆረው ውኃ በፊት ከነበረው የናይል ፍሰት ተጨማሪ ውኃ ለሱዳንና ለግብፅ ማድረስ ስለሚችል፣ ሁለተኛ፡- የማይዋዥቅና የተመጣጠነ አስተማማኝ ውኃ (regulated water) ሱዳን ማግኘት ስለምትችል፣ ይህንን ለማስረዳት ከግድቡ ግንባታ በፊት የነበረውንና አሁን ከግንባታው በኋላ የሚኖረውን የውኃ ፍሰት በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከግድቡ ግንባታ በፊት የነበረውን 200 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በሰከንድ ፍሰት (ዝናብ በሌለ ወቅት) እና 6500 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በሰከንድ (በዝናብ ወቅት)  ወደ 3600-3800 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በሰከንድ በአማካይ በሁሉም ወቅቶች እንዲፈስ ያደርገዋል፡፡ ሦስተኛ፡- የህዳሴው ግድብ አፈሩንና ዝቃጭ ቅሪተ አካልን ግድቡ አካባቢ በማስቀረት የሱዳን ግድቦች ለምሳሌ ያህል ሮዜርስና ሴናር ግድቦችን ከጥቅም ውጭ እያደረጋቸው የነበረውን ደለል ያስቀርላቸዋል፡፡ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ሱዳን በየዓመቱ ከግድቦቿ ደለል ለማስጠረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች እንደምታወጣ መጥቀሱ በቂ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፣ አራተኛ፡- ካርቱምንና ሌሎችንም በናይል ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ ከተሞችንና የገጠር አካባቢዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃ የነበረው ጎርፍ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ወይንም ጨርሶ እንዳይኖር ያደርገዋል፡፡ አምስተኛ፡- ሱዳን ከሕዳሴው ግድብ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከራሷ ከሜሮዌ ግድብ ታገኝ ከነበረው 25% ዋጋ ብቻ በመክፈል ታገኛለች፡፡ ስድስተኛ፡- ሱዳን የሕዳሴውን ግድብ መገንባት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም እ.አ.አ. በ1929 እና በ1959 ከግብፅ ጋር የተደረገውን የናይል ውኃ አጠቃቀም ስምምነቶች ተጎጂ መሆኗን በማሳየት ሌላ ድርድርና ስምምነት እንዲኖር ፍላጎቷን ለማሳየት ትጠቀምበታለች፡፡

 

የሕዳሴው ግድብ መገንባት ግብፆች እንኳን በውናቸው በሕልማቸውም ያላሰቡት ጉዳይ ነው የሆነባቸው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አሰናካይ ምክንያቶችንና አፍራሽ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚዳዳቸው፡፡ ይህንንም ለማስረዳት አራት የሚሆኑ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛ – የጣሊያን ግንባታ ድርጅት የሆነውን ሳሊኒን የግድቡን ግንባታ እንዲያቋርጥ በጣሊያን መንግሥት በኩል ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሁለተኛ – የአውሮፓ ህብረትን፣ አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ሳውዲ አረቢያን፣ ጃፓንና ሌሎች አገሮችን በማነጋገር የግብፅን ፀረ-ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲደግፉላቸውና ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ አነጋግረዋቸዋል፡፡ ሦስተኛ የግድቡን ጉዳይ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Court of Justice) እና ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት (UN Security Council) ለማቅረብ ላይ ታች ሲሉ ነበር፡፡ በመጨረሻም ፕሬዚደንት ሞሐመድ ሞርሲ ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜና አሁንም በአዲሱ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ ኤልሲሲ ዘመን አልፎ አልፎ ጦር-አጫሪ የሆኑ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎችን በኢትየጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ሰንዝረዋል አሁንም በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡ 

 

ነገሮች ባሁኑ ጊዜ መካረር የጀመሩትና አሁን እየታየ ያለው የጋለ የውኃ ፖለቲካ ሊከሰት የቻለው የአባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ መፍሰሻውን ለግንባታ ሲባል ወደሰው ሰራሽ ቦይ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ እንዲዞር ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ የነበሩት አጨቃጫቂ ሁኔታዎች ባሁኑ ጊዜ የበለጠ የተካረሩት ከግድቡ ጀርባ የሚጠራቀመው ውኃ በምን ያህል ጊዜ ይሁን የሚለው ሰሌዳ ላይና ግድቡ ካለቀ በኋላ ምን ያህል ውኃ ይለቀቅ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ መስማማት ስላልተደረሰ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሕዳሴው ግድብ ወሳኝ ደረጃ ላይ ስለደረስ ነው ግብፆች ጉዳዩን በማጦዝ አሜሪካኖችን አማልዱን እስከማለት ደረጃ የደረሱት፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት እቅድ መሰረት የግድቡ ውኃ ማከማቻ (reservoir) ከ3 እስከ 4 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ማለቅ አለበት የሚል ሲሆን ግብፆች ደግሞ የውኃ አሞላሉ ቢያንስ ከ7 እስከ 10 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆን አለበት ነው የሚሉት፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ መንግሥት እቅድ መሰረት ውኃ ማከማቸቱ በመጪው ክረምት (2012 ዓ.ም) ተጀምሮ ከሦስት ወራት በኋላ በታህሣሥ ወር 2013 ዓ.ም ከአሥራሦስቱ የህዳሴው ግድብ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሁለቱ ኃይል ማምረት እንደሚጀምሩ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ሁለቱ አገሮች የማይስማሙበት ጉዳይ ግድቡ ከሞላ በኋላ ውኃ አለቃቀቅን በሚመለከት ነው፡፡ እንደ ግብፆች እሳቤ ኢትዮጵያ ከግድቡ ቢያንስ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በዓመት መልቀቅ አለባት እንዲሁም አስዋን ግድብ ላይ የውኃ መጠኑ ከባሕር ወለል በላይ ከ165 ሜትር ዝቅ ካለ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ውኃ በመልቀቅ መጠኑን ማስተካከል አለባት የሚል ነው፡፡ እነኚህ ቅድመ ሁኔታዎችን ኢትዮጵያ ላይ በመጫን አገሪትዋ ያልተሳተፈችባቸውንና ያልተቀበለቻቸውን የቅኝ ግዛት ዘመን የናይል ስምምነቶችንና (እ.አ.አ 1902 እና 1929) ከዛም በህዋላ የነበረውን የናይል ስምምነት (እ.አ.አ 1959) እጅ በመጠምዘዝ እንድትቀበል ለማድረግ ሙከራ እያደረጉ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ 

 

እነኚህ ከላይ የተጠቀሱት ቅድመሁኔታዎች አንድ ፀሐፊ እንዳለው “by so doing, the Egyptians like to make the Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD) hostage to the High Aswan Daam (HAD)” (ግብፆች ቅድመሁኔታዎቹን በማስቀመጥ የሕዳሴው ግድብ የታላቁ አስዋን ግድብ ታጋች እንዲሆን ይፈልጋሉ)፡፡ ከዚህም አልፎ ግብፆች ኡጋንዳ በሚገኘው ኦወን ፎልስ ግድብ (Owen Falls Dam) ላይ ሲያደረጉ የቆዩትን ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይም ለመድገም ይፈልጋሉ፡፡ ይኸውም የሕዳሴ ግድቡ አልቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር አንድ ግብፃዊ መሐንዲስ ግድቡ ያለበት ቦታ፣ ማለት ጉባ ላይ፣ ቢሮ ተሰጥቶት የግድቡን ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ እንዲቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ እንዲኖር ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ በግብፅ በኩል የተሰነዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች ባጠቃላይ በኢትዮጵያ በኩል ምንም አይነት ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ ተቀባይነት ሊያገኙ አይችሉም ብቻ ሳይሆን አይገባምም፡፡ እንደሚታወቀው ከ20 በላይ ስብሰባዎችን ያደረጉት የሦስቱም አገራት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እስከዛሬ ስምምነት ላይ መድረስ ስላልቻሉ በግብፅ ውትወታ አሜሪካኖች ጣልቃ በመግባት ጉዳዩ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አቅንቶ ባለፈው ጥቅምት 2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አሁን ደግሞ በቅርቡ በታህሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ የሦስቱም የተፋሰሱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የተወሰኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም ባንክና የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ተወካዮች ታዛቢ በሆኑበት ተገናኝተው እንዲወያዩ ተደርጓል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የተስማሙት እስከ መጪው ጃንዋሪ አጋማሽ ድረስ አንድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ይህ ካልተሳካ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ሸማጋዮች አማካይነት እንዲታይ ነው፡፡ 

 

የአሜሪካኖቹ ጣልቃ መግባት ብዙ ጥያቄዎችን ከመጫሩ በተጨማሪ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ የሴራ ፖለቲካዎችን (conspiracy theories) እንዲያጠነጥኑ አድርግዋቸዋል፡፡ የሴራ ፖለቲካዎቹን ለጊዜው ወደኃላ በመተው አንዳንድ የሚታዩ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡- (ሀ) አሜሪካኖቹና ግብፅ ጉዳዩን ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ሲወስዱት ምን አስበው ነው ምን ዓይነትስ ሤራ ጠንስሰዋል? (ለ) ኢትዮጵያ ለምን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ ነው የአሜሪካንን ጣልቃገብነት እና ስብሰባዎች በአሜሪካ እንዲካሄዱ የተስማማችው? (ሐ) በዚህ ጉዳይ የሚያገባው የአሜሪካኖቹ ስቴት ዴፓርትሜንት (በኛ አገር ውጭጉዳይ ሚኒስትሪ ማለት ነው) መሆን ሲገባው ለምን ትሬዠሪ ሴክሬታሪ (በኛ አገር የገንዘብ ሚኒስትሪ ማለት ነው) ሆነ? ይህ የሆነው ነገሩን በገንዘብ ለመሸንገል ታስቦ ይሆን? (መ) በአሜሪካኖች የሚዘወረው የዓለም ባንክ ተጋብዞ እንዴት ታዛቢ ሊሆን ቻለ? (ስ) ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምናልባት ሐ እና መ ን ብናቀናጅ ሌላ ጥያቄ ሊያጭር ይችላል፡- በትሬዠሪ ሴክሬታሪው በኩል ገንዘብ በዓለም ባንክ በኩል ደግሞ ዕርዳታና ብድር ለኢትዮጵያ በመስጠት የሕዳሴው ግድብ ውኃ አሞላል ግብፆች በሚፈልጉት የጊዜ መጠን እንዲዘገይ ታስቦ ቢሆንስ? ይህ ጭፍን መላምት ሳይሆን አንዳንድ ፀሐፊዎች ባደረጉት ጥቆማ አሜሪካኖቹ፣ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ቶሎ ግድቡን ባለመጨረስ ልታጣ የምትችለውን በዓመት ከ 1 እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለመካስ ተዘጋጅተው ቢሆንስ? ይህ ከተሳካላቸው ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን የውኃ ማከማቻ ለመሙላት ከ 10 ዓመታት በላይ እንድታዘገይላቸው ትስማማላቸው ይሆን? ይህንን ፕሮፖዛል ከ ጃንዋሪ 15፣ 2020 በፊት ያቀርቡታል የሚል ከፍተኛ ጭምጭምታ አለ፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማሳካት በሚመስል መልኩ ግብፆች በተለያዩ ስብሰባዎች የተለያዩ አቅዋሞችን በመያዝ፣ ባለፈው የተስማሙበትን በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ በመሰረዝ እንዲሁም ኢትዮጵያ በፍፁም ልትስማማባቸው የማትችላቸውን ጉዳዮች በማንሳት (ለምሳሌ የቀድሞ ስምምነቶችን ተቀበሉ፣ ይህን ያህል ውኃ ትለቃላችሁ ወዘተ) ጉዳዩን እንዲጉዋተትና ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ጥረት እያደረጉ ነው ብሎ መገመት የሚቻል ይመስላል፡፡ እነኚህና የመሳሰሉት ሁኔታዎች በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በእርግጠኝነት መተንበይ አስቸጋሪ ስለሚሆን ውጤቱን በትዕግስት ከመጠበቅ ሌላ ምንም አማራጭ ያለን አይመስልኝም፡፡ እንደዛም ሆኖ ከላይ እንደጠቆምኩት ጥልቅና አሳሳቢ የሆኑ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢና ወቅታዊ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

 

ማጠቃለያ

 

የናይል ትብብር ማቀፍ (CFA) አለመፅደቅ እንዲሁም የናይል ቤዚን ኮሚሽን (NRBC) አለመመስረት ተፋሰሱን በሕግና ስነስርዓት ለማስተዳደር እንቅፋት ሆኗል፡፡ ሰማንያ ስድስት በመቶ የናይል ውኃን እያበረከተች ሰባ በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያልሆነባት ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በመገንባት ወደ 6400 ሜጋዋት አቅም ያለው ኃይል ለማመንጨት ማሰብዋ ሲያንስባት እንጂ የሚበዛባት አይመስለኝም፡፡ በኔ ግምትና አስተያየት ባሁኑ ወቅት በተፋሰሱ ውስጥ የሚታዩት ችግሮችም ሆነ መፍትሔዎቹ እየተንከባለሉ ያሉት በግብፅ ሜዳ ላይ ነው፡፡ በሌላም በኩል ከቁመቱ ጋር (6825 ኪ.ሜ) ፍፁም የማይመጣጠን አነስተኛ ውኃ በሆዱ የያዘው የናይል ወንዝ (74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በዓመት በአማካይ) እንዲሁም አሥራአንድ የተፋሰሱ አገሮች በተለያየ ደረጃ ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት የናይል ውኃ ላይ ብቻ ከማተኮር የተለያዩ አማራጮችን ማየቱ ለግብፅም ሆነ ለሌሎቹ የናይል ተፋሰስ አገሮች ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ስለራስ ብቻ ከማሰብ ይልቅ የናይል ውኃ የጋራ ሃብት መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በፍትሐዊነት፣ ምክንያታዊነት እና ቀናዊነት መርሆ ላይ የተመሰረተ የውኃ አጠቃቅምን ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ቢያምኑበትና ስራ ላይ ቢያውሉት መፍትሄዎቹ እሩቅ አይሆኑም፤ ለምሳሌ፡- 

ሀ. ግብፅ አዳዲስ የውኃ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለእርሻ የምታውለውን ውኃ ልትቆጥብ ትችላለች፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ግብፅ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ (drip irrigation) በመጠቀም ለእርሻ የምታውለውን ውኃ በ48% ልትቀንስ ትችላለች፣

ለ. የዋጋው ውድነት እንዳለ ሆኖ ግብፅ ከቀይ ባሕርና ከሜዲቲራንያን ባሕር ውኃ በመጨለፍ ጨው አልባ ውኃ የማምረት (desalination) አቅሙም ሆነ ኃብቱ ከሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች በተሻለ ሁኔታ አላት፣

ሐ. ግብፆች በመጠኑ እየተጠቀሙበት ያለውን ውኃ አጣርቶ እንደገና መጠቀም (recycling) አጠናክረው በመቀጠል ተጨማሪ ውኃ ማግኘት እንደሌላ አማራጭ ሊይዙት ይችላሉ፣

መ. በግብፅና አካባቢው ባሉ አገሮች በስፋትና በብዛት የሚገኘውን የከርሰምድር ውኃ (aquifer) ጥቅም ላይ ማዋል ሌላው ተጨማሪ አማራጭ ነው፣ 

ሠ. አንድ ጥናት እንደጠቆመው ነጭ ናይልንና የኮንጎ ወንዝን በማገናኘት የኮንጎ ወንዝን ውኃ በቦይ ወደ ግብፅ እንዲፈስ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ከናይል ወንዝ ከሚገኘው ውኃ በተጨማሪ 95 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በዓመት ግብፅ እንድታገኝ ማድረግ ይቻላል፡፡ ጥናቱ እንደሚያትተው የኮንጎ ወንዝ በዓመት 1000 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚደርስ ውኃ ምንም ጥቅም ላይ ሳይውል ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ይፈሳል፡፡ ይህንን ውኃ 600 . ርዝመት ያለው ቦይ በመስራት የውኃውን አቅጣጫ አስቀይሮ 200 ሜትር ከፍታ ከነጭ ናይል ጋር በማገናኘት ወደ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ግብፅ እንዲፈስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ 2 ዓመታት ጊዜ፣ 4 ፓምፒንግ ጣቢያዎች ግንባታ፣ እና 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰኑ ተግዳሮቶችንም መቁዋቅውምን ይጠይቃል፡- ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከየትና እንዴት ነው የሚገኘው? ወደ 800 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ቦይ ሲቆፈር ደቡብ ሱዳን የሚገኘው ሱድ የተባለው ሰፊ ረግረግ (Sudd Swamp) ውስጥ የሚገኙት አዕዋፋት፣ ሕይወትና ከባቢ አየር እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? እንዲሁም የኮንጎ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች (ካሜሩን፣ ጊኒ እና መካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ) ፕሮጀክቱን ይደግፉታል ወይ? የሚሉት ከወዲሁ መታሰብ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፣

ረ. ግብፆች አሁን ለተፈጠረው የሪዘርቫየር ውኃ ሙሊት ጊዜና ግድቡ ካለቀ በሁዋላ ለሚኖረው የውኃ አለቃቀቅ መጠን አለመግባባት ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ቴክኒካል መፍትሔ ቢያዘነብሉ ለራሣቸውም ሆነ ለተፋሰሱ አገሮች የተሻለ አማራጭ ይሆናል

ሠ. ሌላው ለተፋሰሱ አገሮች በሙሉ ይበጃል ብዬ የማምነው ግብፅ አጨቃጫቂ የሆኑትን ቀደምት የናይል ተፋሰስ ስምምነቶችን (እ.አ.አ የ1902፣ 1927 እና 1959 ስምምነቶችን) በመሻር (abrogate በማድረግ) አዲስ የናይል ተፋሰስ ስምምነት እንዲፈረም ብታደርግ ይህ አሁን እያየነው ያለውን መፋጠጥና አጨቃጫቂ የውኃ ፖለቲካ ሁኔታ እስከወዲያኛው ሊቋጨው ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህንን ለማድረግ መፍትሄው ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፉን (legal and institutional framework ወይንም CFAውን) ከመፈረም ሌላ የተሻለ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡ CFAው ከፀደቀ ቀደምት የናይል ውኃ ስምምነቶችን ሙሉ በሙሉ ይተካቸዋል፡፡ ለነገሩ ባንድ በኩል የቀድሞ ስምምነቶች አይነኩም እያሉ በሌላ በኩል ስለሕዳሴው ግድብ አሞላልና አለቃቀቅ እንወያይ ማለት ሁለት የሚጣረሱ ሃሳቦች ናቸው፡፡

ሸ. የአረብ አገሮች ፓርላማ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅን ታሪካዊ የውኃ ድርሻ ሊያከብር ይገባል ብሎ መግለጫ ከማውጣት ይልቅ ትብብር ሊያጎለብቱ የሚችሉ ሃሳቦችን መስንዘር ይጠበቅበት ነበር፤ ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሱትን ቴክኒካዊ መፍትሄዎች ተግባራዊ ለማድረግ ግብፆችን በፋይናንስ መርዳት፡፡ 

ለማጠቃለል ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄና ሐገራዊ ሃላፊነት የሚጠይቁ የድርድር ሒደቶች እየተካሄዱ ባሉበት ሁኔታ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ሁሉ ሐሳቦቻቸውን በንቃት አገርን በሚጠቅም መልኩ ማንሸራሸር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ሕብረተሰቡ በድርድሩ ሂደቶችና ውጤቶች ላይ ግልፅ መረጃ እንዲያገኝ መደረግ ይኖርበታል፡፡

 

ለፀሐፊው አስተያየት ለመስጠት ወይንም ጥያቄ ለማቅረብ ይህንን ኢሜይል አድራሻ መጠቀም ይችላሉ፡ tesfayeidr@yahoo.com

Filed in: Amharic