>
5:18 pm - Friday June 15, 0908

ቤተእምነቶች ለምን ኢላማ ሆኑ!!! (በፍቃዱ ኃይሉ)

ቤተእምነቶች ለምን ኢላማ ሆኑ!!!

በፍቃዱ ኃይሉ
ሃይማኖታዊ ማንነቶች ብሔራዊ ማንነት መሥለው መቅረባቸው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው። “The Oxford Handbook of the History of Nationalism” የተባለ መጽሐፍ «በዚህ ዘመን ሃይማኖት ወደ ብሔር ተቀይሯል» ይላል። «ሃይማኖቶች የብሔራዊ ማንነት አካል እንዲሆኑ ሲደረጉ ሃይማኖታዊ ግጭቶች ደግሞ የብሔራዊ አንድነት ትርክቶችን እንዲስማሙ ተደርገው ተቀይረዋል» ይላል። በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። ሃይማኖታዊ ትርክቶች ወደ ብሔራዊ ትርክትነት ተቀይረዋል። ነገር ግን ትርክቶቹ ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ባለመሆኑ ምክንያት ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነቶች ተፈጥረዋል፤ ምናልባትም ሃይማኖታዊ ገጽታቸው ከብሔርተኛ ገጽታቸው ጎልቶ ሊወጣ ይችላል።
ያሳለፍነው ሳምንት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ያሰሙበት ሳምንት ነበር። መነሻው በሞጣ ከተማ የመስጂድ መቃጠል እና የሙስሊሞች ንብረት መውደም ቢሆንም ቅሉ፥ ያገረሸው ቁጣ ግን የተዳፈነ እና የተከማቸ እንደነበር ግልጽ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተ ክርስቲያናት እና መስጂዶች የፖለቲካዊ ጥቃት ዒላማ ሲሆኑ ባልተለመደ ሁኔታ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ነው። ከዚህ ቀደም፣ ብዙ የእምነት ነጻነት አፈናዎችን ብንሰማም ቤተ እምነቶችን ማጥቃት ግን እምብዛም የተለመደ አልነበረም። አሁን ምን ተከሰተ?
ታሪካዊ ቅራኔ
ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሠረት የጣለው ዘውዳዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ቅቡልነት ምንጭ ክርስትና ነበር። ለነገሥታቱ ክርስትናን ማስፋፋት ግዛታቸውን ከማስፋፋት እኩል ተልዕኳቸው ነበር ማለት ይቻላል። በ1966 ንጉሣዊ ስርዓቱ በሕዝባዊ አብዮት ከመገርሰሱ አስቀድሞ ኢትዮጵያን ይገዙ የነበሩ መሪዎች ራሳቸውን «ሥዩመ እግዚአብሔር» እያሉ ይጠሩ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ሊቃውንቷ በንጉሣዊ ሥርዓቶቹ በብዙ ረገድ ተጠቃሚ ነበሩ። የነገሥታቱ ድርሳናት ጸሐፊዎች የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት እንደመሆናቸው አድሏዊ ትርክት ይበዛባቸዋል። ይህ በተለይ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚበዙት ኢትዮጵያውያን እና ለአገር በቀል እምነት ተከታይ ለነበሩት ሌሎች ብሔረሰቦች የታሪካዊ ቁርሾ መንሥኤ ሆኗል፤ በታሪካዊ ትርክቶች ረገድ ያለው ጭቅጭም ምንጩ ከዚህ ነው የሚጀምረው።
ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃርኖ ምንም እንኳን በብሔርተኝነት የተቃኘ ቢመስልም በውስጠ ታዋቂነት የሃይማኖት ተቃርኖ ያለበት መሆኑን መካድ አይቻልም። የኦሮሞ ብሔርተኞች የክርስትና ወይም የእስልምና እምነት ተከታዮች ቢሆኑም ቅሉ፥ አብዛኛዎቹ የዋቄፈና እምነት ዓመታዊ በዓል የሆነውን የኢሬቻ በዓል ከማክበር አይቆጠቡም። እነዚሁ ብሔርተኞች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ጋር እሰጥ አገባ የሚገቡበት ምክንያትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት (በእነርሱ አባባል አሐዳዊ ኢትዮጵያዊነት) ማጠናከሪያ መሣሪያ ናት ብለው ስለሚያስቡ ነው።
ነገር ግን ከፖለቲካዊ ቅራኔዎቹ በስተጀርባ ሃይማኖታዊ አንድምታ መኖሩን የሚያሳየን በተለይ ከኦሮሞ ብሔርተኞች እና ከኢትዮጵያ ብሔርተኞች በስተጀርባ ያለው መከፋፈል ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥም ጭምር ያለውን ተፅዕኖ መመልከት ስንችል ነው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከገጠሙት የመከፋፈል ፈተናዎች መካከል በሃይማኖት መከፋፈል ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው። ከዚያም ውጪ ሙስሊሞች በሚበዙባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ኦሮሞዎችን ዛሬም ድረስ አማራ ብለው ይጠሯቸዋል።
ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት
ሃይማኖታዊ ማንነቶች ብሔራዊ ማንነት መሥለው መቅረባቸው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው። “The Oxford Handbook of the History of Nationalism” የተባለ መጽሐፍ «በዚህ ዘመን ሃይማኖት ወደ ብሔር ተቀይሯል» ይላል። «ሃይማኖቶች የብሔራዊ ማንነት አካል እንዲሆኑ ሲደረጉ ሃይማኖታዊ ግጭቶች ደግሞ የብሔራዊ አንድነት ትርክቶችን እንዲስማሙ ተደርገው ተቀይረዋል» ይላል። በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። ሃይማኖታዊ ትርክቶች ወደ ብሔራዊ ትርክትነት ተቀይረዋል። ነገር ግን ትርክቶቹ ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ባለመሆኑ ምክንያት ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነቶች ተፈጥረዋል፤ ምናልባትም ሃይማኖታዊ ገጽታቸው ከብሔርተኛ ገጽታቸው ጎልቶ ሊወጣ ይችላል።
ከላይ የተመለከትነው ታሪካዊ የሃይማኖት ተቃርኖ በብሔር ማዕቀፍ ውስጥ እንደመጣ ግልጽ የሚሆንልን፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖለቲካዊ የብሔር ግጭቶች ቤተ እምነቶችን ወደ ማጥቃት እየተሸጋገሩ መምጣታቸውን ስንመለከት ነው። የቀድሞው የሶማሊ ክልል ፕሬዚደንት ከመነሳታቸው በፊት ደጋፊዎቻቸው በጅግጅጋ ነዋሪዎች ላይ ያደረሱት ጥቃት ቤተ ክርስትያናትን እስከማቃጠልም ደርሷል። በሲዳማ ክልልነት ጥያቄ የተቀሰቀሰው አመፅም ቤተ ክርስትያናትን ወደ ማቃጠል ተዛምቶ ነበር። በተመሳሳይ፣ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ በመንግሥት የተመደቡለት ጥበቃዎች ሊነሱ ነው በሚል የተቀሰቀሰው አመፅ የሁለቱም ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ምክንያት ሆኗል። ይኸው አክቲቪስት ከተናገራቸው የአፍ ወለምታዎቹ በሙሉ ብዙዎች ቂም የቋጠሩበት ሙስሊሞች በሚበዙበት የትውልድ ሥፍራው ክርስቲያኖች ቀና ብለው ቢሔዱ አንገታቸውን በሜንጫ ነው የምንለው ማለቱ መሆኑ ያለ ምክንያት አይደለም። በመጨረሻም፣ መረዳት የምንችለው የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚንጠው ብሔርተኝነት ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት እንደተጫጫነው ይሆናል።
ለምን አሁን?
ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ተከታዮች ቁጥር በመቶኛ ሲታይ እየቀነሰ መሔዱን አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በተለይም በኦሮሚያ ክልል የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ቁጥር ሲቀንስ፣ የፕሮቴስታንቶች ቁጥር ደግሞ እየጨመረ ነው። ከኦርቶዶክስ እምነት ቀሳውስት መካከል የተወሰኑት የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክሕነት ለመመሥረት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ያስቀመጡት ምክንያት የምዕመናኑን ቁጥር መቀነስ ቢሆንም ቅሉ ንቅናቄው ብሔርተኛ መሠረት እንዳለው ሳይነጋገሩበት የተግባቡት ብዙኀን ናቸው።
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኝነቶች ከዕለት ዕለተ የባሰ እየጦዙ ነው። ብሔርተኝነቶች እየጦዙ በመጡ ቁጥር ደግሞ በውስጣቸው ያመቁት ሃይማኖታዊ ተቃርኖ ራሳቸውንም ይሰነጥቃቸዋል፣ ከሌሎችም ጋር ግጭቶች ውስጥ ይከታቸዋል። አልፎ ተርፎም በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሥልጣን ሽኩቻ እና ትዕይንተ ኃይል (እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ) ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ እየገፋው ነው። በሽግግር ሥም ሕጋዊ ርምጃዎች መላላታቸውም ፈሪሐ ሕግ እንዳይኖር አድርጓል።
ዑስታዝ በድሩ ሑሴን የተባሉ የእስልምና መምህር ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሞጣው ክስተት ብቻውን እንዳልቆመ ሲያስረዱ እስቴ የተባለ አካባቢ የተከሰተ የመስጊድ መቃጠል እና የሙስሊሞች ንብረት መዘረፍን ነው በምሣሌነት ያነሱት። ይህ ጉዳት ሲደርስ የተጠየቀ አካል ባለመኖሩ ነው የሞጣው የተከሰተው በማለት የሕጋዊ እርምጃዎች አለመኖር ከዚህም በላይ ሊያመጣ ይችላል በማለት ስጋታቸውን ተናግረዋል።
ታሪካዊ የሃይማኖት ቅራኔው ላይ በውስጠ ታዋቂነት ሃይማኖትን ያነገቡ ብሔርተኝነቶች መግነን ተጨምሮበታል። በዚህ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሲታከሉበት አሁን የምናየውን ዓይነት ለማመን የሚያስቸግር የርስ በርስ መጠፋፋት አዝማሚያ አስከትሏል። ይህንን የመጠፋፋት ሰደድ እሳት ለመግታት ዋናው ኃላፊነት የመንግሥት ነው። ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ያሉ ክርስቲያኖች እና ቤተ ክርስቲያኖች እንዲሁም ክርስቲያኖች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ያሉ ሙስሊሞች እና መስኪዶች የተለየ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። አለበለዚያ በነባሩ የታሪክ ቁርሾ ላይ አዲስ እየተጨመረበት ይቀጥላል።
Filed in: Amharic