>
5:13 pm - Thursday April 19, 6040

የአሕመዲን ጀበል ማምታቻ! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአሕመዲን ጀበል ማምታቻ!

 

አቻምየለህ ታምሩ
የኦነግ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ ደራቹ አሕመዲን ጀበል  በLTV ላይ ቀርቦ “የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ለምሳሌ የኃይለ ሥላሴን የ1923ቱን ስናይ በግልጽ ሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያ በታሪኳ በአረመኔዎችና በእስላሞች ተከባ ስትጨነቅ እንደኖረች እያለ ነው መንደርደሪያው የሚነሳው፤ ሕገ መንግሥት ተብሎ የቀረበው ሙስሊዎችን በአሉታዊ መልኩ የሚያይ ነው።” ሲል ለደሰኮረው ፈጠራ የጠቀሰውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ሙሉውን እዚህ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በማተም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ  እሱ ተጽፏል ብሎ ያቀረበው አይነት ነገር እንደማይገኝ አሳይተን ነበር። የቀጠፈው ነገር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንደሌላ ሲጋለጥ ዛሬ ደግሞ ከአስር ዓመት በፊት በማስታወሻ ደብተሬ የጻፍሁት ነው የሚልን  ማምታቻ ይዞ  መልስ ሰጠ ለመባል ብቅ ብሏል።
ሕገ መንግሥት  የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕገ የሆነ ራሱን የቻለ ሰነድ ነው። አንድ ሕገ መንግሥት የሽፋን ገጽ፣ ማውጫ፣ መቅድም(መግቢያ) ና በውስጥ የሚካተቱ አንቀጾችንና ምዕራፎችን ይይዛል። ከነዚህ ውጭ አንድ  ሕገ መንግሥት ሌላ ክፍል የለውም። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትም  የሽፋን ገጽ፣ ማውጫ፣ መቅድምና በውስጡ የተካተቱ  አንቀጾችና ምዕራፎች አሉት።
ዛሬም በድጋሜ ከታች  ካተምሁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ማየት እንደሚቻለው  የሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያ ገጽ የሽፋን ገጹ ነው። ከዚያ ማውጫው ይገኛል። ከዚያ መቅድም(መግቢያ) እና በውስጥ የሚካተቱ አንቀጾችንና ምዕራፎችን የያዘው ክፍል ነው። ከዚህ ሕገ መንግሥት የሽፋን ገጽ  እስከ መጨረሻው  ክፍል፣ አንቀጽና ገጽ ስታገላብጡ ብትውሉ አሕመዲን ጀበል በLTV  ቀርቦ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ይገኛል ብሎ ያስተጋባውን ቅጥፈት አታገኙም።
እስቲ አሕመዲን ጀበልን የምታውቁ እነዚህ ጥያቄዎች ጠይቁት፤
1ኛ. 16 ገጾች፣ ሰባት ምዕራፎችና  55 አንቀጾች  ባሉት የ1923ቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያ ሕገ መንግሥት ውስጥ በየትኛው የሕገ መንግሥቱ ገጽና ክፍል ላይ ነው ኢትዮጵያ በታሪኳ በአረመኔዎችና በእስላሞች ተከባ ስትጨነቅ እንደኖረች የሚያወሳው በሉት?
2ኛ. 16 ገጾች፣ ሰባት ምዕራፎችና  55 አንቀጾች  ካሉት ከታች ከተለጠፈው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1923ቱ ሕገ መንግሥት ውጭ አንተ የምታውቀው የሽፋን ገጽ፣ ማውጫ፣ መቅድም(መግቢያ) ና በውስጥ የተካተቱ አንቀጾችንና ምዕራፎችን የያዘ እንደ ወያኔና ደርግ ሕገ መንግንሥቶች ራሱን የቻለ ሰነድ አለ ወይ በሉት?
3ኛ. የ«ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል» ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  አቶ አብዲላሂ ሶጃር ትናንትና  ወደ ነቀምት ለስራ እየሄዱ እያሉ በኦነግ ሸኔ መገደላቸውን መቼም ሳትሰማ አልቀረህም። እንደሚታወቀው አንተ ጎንደርና ጎጃም፤ ወሎና ሸዋ አንድ ነገር ኮሽ ባለች ቁጥር በሙስሊሞች ላይ ጥቃት ደረሰ የሚል ሰበብ እየፈጠርህ አማራን ለመከፋፈልና  በራሱ  ለማጣራትና  ለማሰብ ፈቃደኛ ያልሆነው መንጋ በአማራው ላይ ለማሳመጽ የሚቀድምህ የለም። ወለጋ ውስጥ በኦነግ ለተገደለም የ«ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል» ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  አቶ አብዲላሂ ሶጃርን ግን እስካሁን አንዲት ነገር አልተነፈስህም? ኦነግ በሙስሊም ላይ  የሚያደርሰው ጥቃት ከጥቃት አይቆጠርም? ነው የአቶ አብዲላሂ ሶጃር ነፍስ ከሌላው ሙስሊም ነፍስ ያነሰች ናት? እስቲ ወለጋ ውስጥ  ኦነግ በግፍ ለገደለውና   ትናንትና ሞጣ ደረሰ ብለህ ስታራግበው ከነበረው ጥቃት በላይ ጥቃት ለደረሰበት ለሙስሊሙ ለአቶ አብዲላሂ ሶጃርም ሰልፍ እንዲካሄድና  ከሌሎች ተለይቶ በአሰቃቂ ሁኔታ  የተገደለበት ጭካኔ  በሙስሊም ላይ የደረሰ ጥቃት ነው ተብሎ እንዲወገዝ ዘመቻ ጀምር?
አንባቢ በራሱ መንገድ የአሕመዲን ጀበልን ማምታቻ  ያጣራ ዘንድ በላይበራሪያችን የሚገኘውን  16 ገጾች፣ ሰባት ምዕራፎችና  55 አንቀጾች  ያሉትን  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1923ቱን ሕገ መንግሥት ዋናውን  የአማርኛ ቅጂና  በወቅቱ አብሮ ከታተመው የፈረንሳይኛ ትርጉም ጋር   አትሜዋለሁ ። በማህበራዊ ሚድያ ገጼ ላይ ታገኙታላችሁ።
አበቃሁ
★★★★★★★★★★★★★★★★★★

የአህመዲን ጀበል ምላሽ

‹‹በእስላምና በዐረመኔ የተከበበችዋ ኢትዮጵያ››
 
ውዥንብሮችን ለማጥራት መረጃን ከምንጩ!
ትናንት ምሽት ከኤል ቲቪ ጋር የነበረኝን ቃለ-መጠይቅ አስመልክቶ በርካቶች የተሰማቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ከእነዚህ ዉስጥ በጥያቄ መልክ በፈስቡክ ከቀረቡልኝ ጥቄዎች መካከል አንድ  የሰሜን ብሔርተኛ ነኝ የሚል ጸሐፊ ከቃለ-መጠይቁ ዉስጥ ቃላት በመምዘዝ ለማጠልሸት ሲዳክር ቆየቶ በመጨረሻ አንድ ወሳኝ ነጥብ እንዳገኘ ተሰማው። ጸሐፊው ማህበራዊ ሚድያ  ተከታዮቹንና ወገኖቹን ከተጽዕኖ ለመጠበቅ ሲል ወዲያዉኑ ‹‹የአሕመዲን ጀበል የፈጠራ ታሪክ›› በሚል ርእስ ጽሑፍ ለጠፈ፡፡ ይህን ያነበቡ ጥቂት ወንድምና እኅቶች ጽሑፉን ልከዉልኝ ማብራሪያ ጠይቀውኛል።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፡- በቃለ መጠይቁ ላይ ‹‹የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት ለምሳሌ የኃይለ ሥላሴን የ1923ቱን ስናይ በግልጽ ሕገ-መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያ በታሪኳ በአረመኔዎችና በእስላሞች ተከባ ስትጨነቅ እንደኖረች እያለ ነው መንደርደሪያው የሚነሳው፤ ሕገ መንግሥት ተብሎ የቀረበው ሙስሊሞችን በአሉታዊ መልኩ የሚያይ ነው።›› በሚል ያነሳኹት ሐሳብ ነበር፡፡
በዚህ ጥሬ ሐቅ ያልተስማማው ጸሐፊው ‹‹አሕመዲን ጀበል ይህን ያደረገው የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትን ለማጠልሸት ሆነ ብሎ ኦነጋዊ ታሪክን የመበረዝ አጀንዳውን በታሪክ አመካኝቶ በሕዝቡ ዉስጥ እያሰራጨ ነው ሲል ውንጀላ አቀረበ። የኼ ጸሐፊና እሱን የመሳሰሉ ሰዎች ከጅምሩ በእኔና እኔን በመሳሰሉ ግለሰቦች ላይ አንዳንዴ የሚነዛውን ተራ ፕሮፓጋንዳ ያለማመዛዘን ለማቀበል የተዘጋጀውን ከፊል አንባቢያቸውን ተማምነው በስፋት የሚያሰራጩትን አሉባልታ ከዚህ ቀደም ተመልክቼያለሁ፡፡
የእስከዛሬዎቹ አሉባልታዎች ተራ ትችትና የማጠልሸት ጥረት ያለሙ መኾናቸውን እንዲሁም የተጽእኖ አድማሳቸው አናሳ በመኾኑ በዝምታ አልፌያቸዋለሁ። በእርግጥ አንዳንዴ የእነኝህ ወገኖች የዋህ ተከታዮች ግለሰቦቹ የሚጽፉት ነገር እውነት መስሏቸው ሳያመዛዝኑና ሳያጣሩም ለሌላ ወገን እንደሚያሰራጩም  የምንረዳው ጉዳይ ነው። ለማንኛዉም በዚህ በኤል ቲቪ ቃለ-መጠይቅ ላይ የሌለ ነገር ፈጥሬ ሳይኾን ጥሬ ሐቅ ወይንም ፋክት ብቻ ማስቀመጤን እዚህ ጋር ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ጥውን ሐቅ በነጥብ በነጥብ አድርጌ ከታች አስቀምጣለሁ፡፡
የ1923ቱን ሕገ-መንግሥትን ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በሐምሌ 9 ቀን 1923 ረቂቁን በፊርሚያቸው ሲያጸድቁ የተናገሩት ንግግር ለሕገ-መንግሥቱ መግቢያ (መቅድም) ኾኖ አብሮ በታተመው በአጼ ኃይለ-ሥላሴ ንግግር ዉስጥ ከአንድም ሦስት ጊዜ ተመሳሳይ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ይህንን ለመረዳት ለምሳሌ እኔ ያጣቀስኩበትን እና በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ የታተመውንና ከ1923-1983 የነበሩትን ሕገመንግስቶችን  በአንድነት የያዘው ‹‹የኢትዮጵያ ሕገ- መንግሥት ከ1923-1983 ልዩ ዕትም (ቁጥር 1)›› የሚለው መጽሐፍ ላይ ‹‹በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቆመ ሕገ-መንግስት ሐምሌ 9 ቀን 1923›› በሚል ርዕስ በሚጀምረው የንጉሡ መግቢያ (መቅድም) ላይ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡
በመጀመሪያው የመግቢያ ክፍል ገጽ አንድ ብቻ ሦስት ጊዜ ያክል  ጊዜ እኔ በቃለ-ምልልሱ ላይ ‹‹የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት ለምሳሌ የኃይለ ሥላሴን የ1923ቱን ስናይ በግልጽ ሕገ-መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያ በታሪኳ በአረመኔዎችና በእስላሞች ተከባ ስትጨነቅ እንደኖረች እያለ ነው መንደርደሪያው የሚነሳው፤ ሕገ መንግሥት ተብሎ የቀረበው ሙስሊሞችን በአሉታዊ መልኩ የሚያይ ነው።›› በሚል የተናገርኩትን ሐሳብ የሚገልጹ የሚከተሉትን በቀጥታ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ካሰፈርኩት ማስታወሻ ልጥቀስ።
1ኛ) ‹‹ከክርስቶስ ልደት በኃላ እስከ አጼ ቴዎድሮስ ዘመን ድረስ አረመኔ፣ እስላምና ፈላሻም ዙሪያዋን ስለከበባት ወደ ሃይማኖት ትግል ተመልሳ ይህ የሃይማኖት ትግል በግዛቷ ዉስጥ እየባሰና እየከፋ በመሄዱ በኋይልና በጉልበት የቀድሞውን ግዛቷን ለማስፋት ሳይመቻት ቀረች፡፡›› (ገጽ 1፣ የመጀመሪያ ክፍል፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ከ1923-1983 ልዩ-ዕትም (ቁጥር 1)፣ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡)
 2ኛ) ‹‹ይልቁንም አረመኔና እስላም ዙሪያዋን ስለከበባትና ሃይማኖቷን ለማስካድ ስላስጨነቃት እርሷም ለክርስትና ሃይማኖቷ ቀናተኛ ስለሆነች የባሕር ጠረፎቿን እየለቀቀች ወደ ተራሮቿ ለመጠባበቅ ግዴታ ሆነባት፡፡›› ( ገጽ 1፣ የመጀመሪያ ክፍል፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ከ1923-1983 ልዩ-ዕትም (ቁጥር 1)፣ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡)
3ኛ) ‹‹በዚህም ምክንያት ከዉጭ አገር መንግሥታቶች ጋር መገናኛዋ ተቆረጠና ከዉጭ ይመጣላት የነበረው የእዉቀትና የንግድ ጥቅም እርዳታ ሁሉ ቀረባት፣ ይህንንም በመሰል ችግር ተጨንቃ ካረመኔና ከእስላም ጎርፍ ስትከላከል ብዙ ዘመን ቆየች፡፡›› (ገጽ 1፣የመጀመሪያ ክፍል፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ከ1923-1983 ልዩ-ዕትም (ቁጥር 1)፣ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡)
እኔ ከላይ የተጠቀሰውን ያጣቀስኩትና በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያሰፈርኩት የዛሬ 10 ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ዉስጥ ካለው ቤተመጽሐፍ ነበር። አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት መጽሐፉን ሲመቸኝ ከላይብረሪው ፎቶ አንስቼ እለጥፈዋሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከላይ የተጠቀሰውን ነጥብ በቃለ ምልልሱ ማንሳቴ ለደነቃቸው ወገኖች አስፈላጊነቱ ከታየኝ በሌላ ጊዜ   በተከታታይ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት እና ሌሎች አጼዎች ለሙስሊሞች የነበራቸውን ፖሊሲ በማስረጃ እያስደገፍኩ በተከታታይ ላቀርብ እችላለሁ። ቸር እንሰንብት። ለአሁኑ አበቃሁ።
Filed in: Amharic