>
12:21 am - Thursday December 1, 2022

"ተወው ባክህ የደብተራ ተረት ነው!" (ሙክታሮቪች) 

“ተወው ባክህ የደብተራ ተረት ነው!”

ሙክታሮቪች
ስለኢትዮጵያ ታሪክ አንስተህ በጥንት ጊዜ እንዲህ ነበር፣ ይህ ተፈፅሞ ነበር፣ ይህ በዚያ የዘመን መንፈስ እንዲህ ነበር የሚታየው፣ ያን ዘመን በዚህ ዘመን መነፅር መመልከት አግባብ አይደለም….. እያልክ ስትከራከር አንዳንድ ከእውቀት የፀዱ፣ ምንጫቸው ፅንፈኞች፣ ለፅንፈኞች ሀሳብ ያቃበሉ መሰሪ ሚሲዮናውያን፣ በዚህ ዘመን ደግሞ ዊከፒድያን የመሰሉ ማንም እየገባ ከሚፀዳዳበት ድረገፅ ያገኙትን ትርክት እንደ እውቀት የሚወስዱ ሰዎች ከላይ እንደመግቢያ ስላነሳሁት ሀሳብ አንድ አይነት መልስ አላቸው። እሱም:—
የደብተራ ተረት?!”
አብዛኞቹን ደብተራ ማለት ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድነው? ብሎ ለጠየቀ ትክክለኛ መልስ አልሰጡም። ስህተቱ ከእውቀት ማነስ ጋር ይያያዛል። ምንጩ ደብተራ ማለት ምን ማለት ነው? ማነው ደብተራ? ለሚለው ጥያቄ የተብራራ መልስ ካለማግኘት ጋር ይገናኛል። እስቲ ዛሬ የሚሰሙኝ ከሆነ ስለደብተራ የሚከተለውን ፅሁፍ ላጋራ።
ለመሆኑ ደብተራ ማለት ምን ማለት ነው?
‹ደብተራ› የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉሙ ‹ድንኳን› ማለት ነው፡፡ እንዲሁ መደበኛው አይነት ድንኳን ሳይሆን ከጥንት ዘመን ጀምሮ ነገስታቱ ከሀገር ሀገር ለማስተዳደርና አቤቱታ ለመስማት፣ ያመፀን ለማስገበር ይዟዟሩ ስለነበረ፣ አብራቸው የምትጓዝ የጸሎት ታቦት አብራቸው ትጓዝ ነበር፡፡ ለዚህች ታቦት የምትሆን ጥብቅ የተለየች ድንኳን ይዘጋጅ ነበር፡፡ ታቦቷ በቤተ መንግሥት ግቢ ተተክላ ትቀመጥና ንጉሡ ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀስ ተነቅላ ትንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህች ድንኳን ውስጥ ማንም ዘው ብሎ አይገባም። የተለዩ ጠቢብ ካህናት ናቸው የሚገቡት። በድንኳን መቅደስ ውስጥ ለአገልግሎት የሚመረጡት በዕውቀታቸውና በንጽሕናቸው፣ በስነምግባራቸው፣ በአስተሳሰብና እውቀታቸው የተመሰገኑ ካህናት ናቸው። ባጠቃላይ ከእኩዮቻቸው በእኛ የዘመኑ አነጋገር “የሰቀሉ” ጠቢባን ብቻ ናቸው ፡፡
በዚህች ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት ካህናት አንዱ ሥራቸው ንጉሣውያን ቤተሰቦችን ማስተማር ስለነበር የችሎታቸው አስፈላጊነት ለድርድር አይቀርብም ነበር።
ደብተራ የድንኳኑ መጠሪያ ከሆነ አሁን ለምን ውስጡ ላሉ ጠቢባን ተንሻፎና ተንጋዶ አሉታዊ እንድምታን እንዲይዝ ሆነ?
ነገሩ ወዲህ ነው። 
በነዚህ የቤተ መንግሥት መቅደስ ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ‹በማደሪያው አዳሪው፣ በአዳሪውም ማደሪያው ይጠራል› በሚባለው መሠረት በደንኳኗ (በደብተራ) እነርሱም ‹ካህናተ ደብተራ› እየተባሉ መጠራት ስለጀመሩ፣ ቋንቋ እየተሸረፈ፣ እያጠረ መምጣቱ ሀቅ ነውና ቆይቶ ቆይቶ ‹ካህናት› የሚለው ስም ተገርዞ ‹ደብተራ› ብቻ ቀረና “ካህናተ ደብተራ” ወደ “ደብተራ” አጥሮ መጠሪያቸው ሆኖ ቀረ፡፡ ከመነሻው ታሪኩን በወጉ ለተከተለ “ደብተራ” ማለት በዕውቀትና በሕይወት ተመርጦ የቤተ መንግሥቱን የደብተራ ቤተ መቅደስ ድንኳን ለማገልገል የተሰየመ ሊቅ ካህን ማለት ነው ትክክለኛ ትርጉሙ፡፡
አሉታዊው ትርጉም እንዴት መሰረቱን ጣለ?
ደብተራዎች ከንጉሡ ጋር የተሻለ ቀረቤታ በማግኘታቸው በኋላ ዘመን የርስትና የሹመት ተካፋዮች ሆኑ፡፡ ይህ የሚያጓጓ ጥቅም እያባባ መጣ። ይህን ላለማጣት ሲሉም አንዳንዶቹ ቀኖናው ከሚያዛቸው ይልቅ ንጉሡ የሚያዛቸውን መቀበል ጀመሩ፡፡ ከስርዓት እያፈገፈጉ ሞያቸው በስልጣንና ጥቅም እየተሸረሸረ መጣ። በዚህ የተነሣም “ካህናተ ደብተራ” ለንጉሡ የሚያደሉና ለእውነት የማይቆሙ እየሆኑ መጡ። ይህም ክብራቸውን እያወረደው መጣ።
በሌላ በኩል ደግሞ ከንጉሱ ያች ድንኳን ያልገቡ፣ ማለት “ሰቃይ” ያልነበሩ ጠቢባን ደብተራዎች ወደ ታሪክ፣ ወደ የህክምና ጥበብ፣ ወደ የክዋክብት ጥናት፣ ወደ ፍልስፍና፣ ወደ ቲዎሎጂ ገብተው በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል። የነዚህም ጠቢባን ክብርና መልካም ስራ በሌሎች እየተጋረደ መምጣቱ አልቀረም።
ምክንያቱ ደግሞ፣ 
በኋላ ዘመን አንዳንዶቹ ከማኅበረሰቡ በተሻለ የተማሩ መሆናቸውን በመጠቅም ጥንቆላና አስማት እንችላለን በማለታቸው በድብትርና ከለላነት ሀይማኖቱ የማይፈቅደውን ተግባር ላይ ተሰማሩ። በዚህም ‹ደብተራ› የሚለው ስም የምሁርነትና የጠቢባን ስም መሆኑ ቀርቶ ከጥንቆላና መተት ጋር የተያያዘ ስም እየሆነ መጣ፡፡ እንደማንኛውም ሞያ፣ ድብትርናም የተከበረ ሞያ መሆኑ ቀርቶ ‘ኮራፕት‘ ሆኖ ቀረ።
ደብተራ› የሚለው ስም አጠፋፍ ›ሐኪም› ከሚለው ስም አጠፋፍ ጋር ይመሳሰላል ይላሉ አንዳንድ ሰዎች፡፡ ‹ሐኪም› የሚለው ስም ትርጉሙ ‹ብልህ፣ ጠቢብ› ማለት ነው፡፡ ሐኪም አሁን የጤና ባለሞያ ነው። ጥንት ግን ሐኪም ሙያን ሳይሆን ጥበብን የሚመለከት ነበር፡፡ ‹ወስመ መምህሩ ዘመሀሮ ጥበበ አርስጣጣሊስ ሐኪም› ሲባል፣ ‹ጥበብን ያስተማረው መምህሩ ጠቢቡ አሪስጣጣሊስ ነው› ለማለት ነው፡፡
በዐረብኛም ሆነ በእብራይስጥ ትርጉሙ ይሄው ነው፡፡ የእስልምና ወርቃማው ዘመን በሚባለው ጊዜ ‹ሐኪም› ማለት በእስልምና ሃይማኖት፣ በሳይንስ፣ በመድኃኒትና በፍልስፍና፣ በሂሳብ፣ በክዋከብት ባጠቃላይ ሁለገብ ዕውቀት ያለው ጠቢብ ሰው ስያሜ ነበር፡፡ በዕብራይስጥ ቋንቋም ሁለገብ ዕውቀት ላለው የሃይማኖት መሪ የሚሰጥ ስም ነው – ሐኪም፡፡
በሀገራችን ‹ሐኪም› የሚለው ስም ለጠቢብ የሚሰጥ ስም ነበረ፡፡ በኋላ ግን ባሕላዊ መድኃኒት ለሚያውቅ ባለሞያ ሁሉ መሰጠት ተጀመረ፡፡ በየጋዜጣው ዛሬ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ‹ሐኪም እገሌ› እያሉ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት ለዚህ ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ሲጀመርም በሞያው የተሰማሩት በዚህ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህን ማስታወስ ለዚህ ይረዳል፡፡ አሁን አሁን ብዙዎቹ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ይህንን ስም ስለሚጠቀሙት ስሙ እንደ “ደብተራ” ሁሉ ከጥበብና ሞያ ይልቅ ከጥንቆላ ጋር የመያያዝ ዕጣ እየገጠመው እንዳለ እሙን ነው፡።
የደብተራም ዕጣው እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ‹ዐዋቂ፣ ጠቢብ፣ የተመረጠ› ነበር ትርጉሙ፡፡ በኋላ ያንዳንዶች ግብር ስምን ያጠፋልና የአንዳንድ ‹ደብተሮች› ሥራ ደብተራነትን ሞያዊ ልዕልና ና ክብሩን አጠፋው፡፡ ወያኔና ፅንፈኞችም የአንዳንድ ደብተሮችን ስህተት እያሳዩ ሁሉን ደብተራ ፈረጁት።
ለዚያም ነው “ባክህ ተወው የደብተራ ተረት ነው” የሚሉት።
“አክቲቪስት” ለምሳሌ ማህበሰብ አንቂ ማለት ነው። የዛሬ መቶ አመት “ቀጣፊ፣ አጋጭ፣ ጥላቻ ነዢ፣ መሰሪ” ሆኖ ትርጉሙ ሊዛባ ይችላል።
እንጂማ፣
ደብተሮች ታሪክ ሰንደው ቋንቋ አበልፅገው፣ ህክምናን አስተምረው፣ የክዋክብት ጥናትን አስተምረዋል። ስለማህበረሰብ፣ ስለሀገር፣ ስለነፃነት ስለፍልስፍና ፅፈዋል። በየትኛውም አለም ፊደልን ከብራና እያዋሐዱ የራስን የዘመን መንፈስ ከትቦ ለትውልድ ማስተላለፍ የሰለጠነ ማህበረሰብ መሆን ነው።
በዚህ በኩል በርካታ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን ከተለያዩ ሀገራት ማንሳት ይችላል። በእስልምናው ወርቃማ ዘመናት ሀዲስን የሰነዱ፣ ቁርኣንን ከሀፊዞች በፅሁፍ ወደ ኪታብነት የመለሱት ደብተራዎች ናቸው። እነ ቡካሪ እነ ሙስሊም፣ እነ የመዝሃብ ባለቤቶች እነ ሀኒፋ ፣ ማሊኪ እነ ሻፊኢ ደብተራዎች ናቸው። በቻይናም ሆነ በህንድ ፊደል ቀርፀው ታሪክና ትውፊትን የሚሰንዱት በእኛው ሀገር ስያሜ “ደብተራዎች” ናቸው።
አፄ ቴድሮስ መቅደላ ላይ በመሰረተው ቤተ መፅሃፍት የነዚህን ደብተሮች ስራ አጠራቅሞ እንግሊዝ በብዙ ዝሆኖች ዘርፈው ሄደዋል። እንግሊዞች የደብተራዎችን ጥበብ ለመፈተሽና ለመሰልጠን ብለው ውዱን እና የተለፋበትን እውቀት የዘረፉት። እነ ጀምስ ብሩስና አልቫሬስ ኢትዮጵያን ሲያስሱ ዋነኛው ታርጌታቸው የደብተራዎችን ስራ ነበረ።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል መፍትሄን የምታገኝበት ሁነኛ የእውቀት ምንጯን ባለመጠቀሟ ተጎድታለች።
ኢትዮጵያ በጣም የተጎዳችው በተለይ በጣም በጣም የተጎዳችው የስልሳዎች ትውልድ የሀገሩን ታሪክ ሳያውቅ ሀገር ለማነፅ የሄደበት መንገድ የተውሶ እውቀት ላይ መመስረቱ እና ይህም የሀሰት ትርክት ለሀገራችን አንድነት በሚያሰጋ መልኩ የስርአት ችግርን እንደ ብሄር ተቃርኖ ጉዳዩን የህዝብ ለህዝብ ቅራኔ ማድረጋቸው፣ ለዚህም የኢትዮጵያን ታሪክ አንስቶ ለመሞገት “የደብተራ ተረት” በሚል የድንቁርና ጭንብል ትውልዱን መጋረዳቸው ከጉዳቶች ሁሉ የከፋ ጉዳት ሊሆን በቅቷል።
ስለዚህ እንዲሁ በደፈናው የደብተራ ተረት ነው የሚሉ ሰዎች የጥንቱን እውቀት መጣላቸው ብቻም ሳይሆን የሀገራቸውን ታሪክ አብረው ይጥላሉ። ከመጥፎው ለመማር፣ ከበጎው ለማስቀጠል እድሉ ይጠፋል። በፈረንጅ አፍ ብቻ የተፃፈን እንደ እውነት መቀበል እና የራስን ማናናቅ የአዕመሮ ባርነትን ያመጣል።
እውቀት ልፋትን ይፈልጋል። ወርቅ ከብዙ አፈርና ድንጋይ ተጣርቶ እንደሚወጣ ሁሉ፣ የማይዛነፍ እውቀት በርካታ መፅሃፍትን ማንበብና ማመሳከር ያስፈልጋል። አንድ መፅሃፍ ብቻ ካነበበ አደገኛ ሰው ራቅ የሚባለው ለዚህ ነው። “ተወው ባክህ የደብተራ ተረት ነው!” ከማለት እያነበቡ፣ እያመሳከሩ እውቀትን መፈለግ፣ አዕምሮን ማበልፀግ ያስፈልጋል።
Filed in: Amharic