>

ይድረስ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች!(“ከገዳም የተላከ አስቸኳይ መልእክት!”) ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ይድረስ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች!(“ከገዳም የተላከ አስቸኳይ መልእክት!”)

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

በሀገራችን በተለይ በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ብዙ ነገሮች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ብዙዎቹ የሚዘገንኑ ናቸው፡፡ ደግ ወሬ መስማት ብርቃችን ከሆነ ሰነበተ፡፡ የሚሰሙ አሳዛኝ ክስተቶችንና ወሬዎችን ሁሉንም ወይም ስለሁሉም መጻፍ አይቻልም፡፡ ሙሉ ጊዜያችንን ለዚህ ጉዳይ ብናውለው እንኳን አንሸፍናቸውም፡፡ ግን አንዳንድ ጠንከር ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ጠቃሚ ነውና ለዛሬ የሚከተለውን ሃሳብ መሰንዘር ወደድኩ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በጣሊያን ሀገር ነው፡፡ እጅግ ቀደም ባለ አንድ ወቅት ሮም አካባቢ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ አንድ ሕጻን ሜዳ ላይ እየቦረቀ ሳለ ድንገት ይሠወራል፡፡ ቤተሰብና ጎረቤት ለፍለጋ ሲወጡ አቅጣጫው ካልታወቀ ሥፍራ የሕጻን ልቅሶ ይሰማሉ፡፡ ሲያጣሩ ያ የጠፋው ሕጻን በአንድ 36 ሜትር በሚርቅ የደረቀ ግን ያልተሸፈነ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ገብቷል፡፡ የፈጣሪ ተዓምር በሚመስል ሁኔታ ልጁ ወደጉድጓዱ በሚገባበት ጊዜ በመሬት ስበት ኃይል ተወርውሮ እጉድጓዱ ግርጌ ሲደርስ አልሞተም፡፡ ሕዝቡ የሚያደርገውን አጥቶ በጭንቀት ይዋልላል፡፡ ልቅሶውና ዋይታው በዐዋቂ በሕጻኑ ዘንድ ይቀልጥ ይዟል፡፡ ጉድጓዱ እጅግ ጠባብ ከመሆኑ የተነሣ ልጁን እንዴት ማውጣት እንደሚቻል አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይቻል ጭምርም ማድረጉ ይበልጥ ያስጨንቃል፡፡

ያ የሕዝብ ጭንቀት የሀገሪቱ መሪ ጆሮ ገባ – ‹አንዱ የሁሉም፣ ሁሉም የአንዱ› መሆኑን እዚህ ላይ ያጤኗል፡፡ መሪው ወዲያውኑ መጣ፡፡ ከሕዝቡም ጋር  በጭንቀት ነጭ ላብ እያላበው ልጁ እንዴት መውጣት እንደሚችል ይወያይና አመራር ይሰጥ ገባ፡፡ ከሀገር መሪነት የአንድ ሕጻንን ሕይወት ወደ ማትረፍ መሪነት ተዛወረ – ለጊዜው፡፡ ድንቅ ዝውውር!

መሪ ማለት እንደዚህ ነው፡፡ ሥልጣን ማለት መኩራሪያና መኮፈሻ ሳይሆን ዝቅ ብሎ ለሕዝብ አሽከርና ገረድ መሆን ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን አመራር ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው በተግባር ያሳየው፡፡ ክርስቶስ ታጥበውና ጸድተው የቀረቡ እግሮችን ለይስሙላ ሳይሆን ቆሽሸው የነበሩ እግሮችን በእውነት ስለእውነት አጥቧል፤ ከድውያንና መፃጉኣን ጋር ውሎ ከሥጋዊና መንፈሣዊ ህመማቸው ፈውሷቸዋል፤ ጓደኞቹ ያጡና የነጡ እንጂ ከበርቴዎችና ባለፀጎች አልነበሩም፡፡ ለታመሙ እንጂ ለጤነኞች አልመጣም፡፡ የሀብት ውድድር ውስጥ ገብተው አስበልጠው ብድራትን ለሚከፍሉ ተጋባዦች ሳይሆን ለድሆች እንድናበላና እንድናጠጣም መክሯል፡፡ በ33 ዓመት ምድራዊ ዕድሜው ያላደረገው መልካም ነገርና ያላበረከተው በጎ የአመራር ጥበብ የለም፡፡ ከርሱ ብዙ ነገር መማር ሲገባ የዘመናችን መሪዎች በተገላቢጦሽ ራሳቸውን መቆለልና ከሕዝብ መነጠልን መመለክንም መርጠዋል፡፡ ግን አላወቁም እንጂ ሲወድቁ ከማንምና ከምንም በታች ናቸው፡፡ ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን፡፡ የሰውን ልክ የማያውቁና ከሰው በታች በሆነ የስብዕና ምስቅልቅሎሽ የሚሰቃዩ መሆናቸውን ከአኗኗር ዘይቤያቸው መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ሥልጣንና ልብስ ደግሞ ገመናን አይሸፍኑም፡፡ ለማያቃቸው ይታጠኑ፡፡ የአሁን መኮፈስ ለነገ መሽቆጥቆጥ ነው፡፡ ሰውነትን ሳይሆን አንጎልን እናሳድግ ይልቅ፡፡

ይህን የምለው የሀገራችን ባለሥልጣናት ነገረ ሥራቸው ሁሉ እርር ብግን ስለሚያደርግ ነው፡፡ በመሠረቱ አንድ ሰው ለአመራርነት መታጨትና መብቃትም ያለበት ከፍ ያለ የአስተሳሰብና የአመለካከት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ለዚህም ነበር በደጉ ዘመን “ከሰው መርጦ ለሹመት፤ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” ይባል የነበረው፡፡ ዛሬ ግን ሁሉ ነገር የተገላቢጦሽ ነው – “አህያ ወደ ሊጥ ውሻ ወደ ግጦሽ…” እንዳለው ያ ለሀገሩ አፈር እንኳን ያልበቃ ገጣሚ ገሞራው፡፡ (ዐፅሙ ወዳገር መጥቶ ይሆን?)

እዚህ ላይ ፈረንጆቹ “Give the devil its due” እንደሚሉት ለዶክተር አቢይ የምሰጠው የተወሰነ መልካም ሥፍራ አለ፡፡ ብዙ ተቺዎች በአስመሳይነትና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እንዲሁም ተቀባይነትን ለማስገኛነት እንደሚያውለው ቢያሙትም አንዳንዴ የሚያደርጋቸው ሰብኣዊ ተግባራቱ ሊመሰገኑለት ይገባል፡፡ ይህን ብላቴና በተመለከተ ችግሬ የሚናገረውና የሚያደርገው ብዙውን ጊዜ እየተለያየብኝ መሄዱ ነው፤ ለሥልጣኑ ስስ ከመሆኑ የተነሣ በርካታ እውነታዎች ይፋለሱበታል፤ ይጋጩበታልም፡፡ እንጂ ከሚያደርጋቸው የበጎ አድራጎት ድርጊቶቹ ተነስቼ ብመሰክርለት ልጁ በርግጥም ሆደ ብቡና ለሰው አዛኝ ይመስላል፡፡ ወደ ፖለቲካው ስንገባ ግን ፖለቲካ በተፈጥሮው መሠሪነትንና የሸር አካሄድን ስለሚጠይቅ በእጅ አዙር የመግደልንና የማስገደልን “ጥበብ” መሪዎቻችን አይከተሉም ብሎ መገመት መሞኘት ነው፡፡ ቦታው ራሱ የቆቅንና የእባብን ባሕርያት አዛንቀው ካልያዙ አንድም ቀን አያሳድርምና ሥልጣንን አውሎ ለማሳደር በሚደረግ ትግል ብዙ ጥፋት መኖሩ አይካድም – ሥልጣንን በሚመለከት ይሉኝታና ሀፍረት ደግሞ የለም፡፡ ለሥልጣን ሲባል ምሕረት የሚደረግላት አንዲትም ዐይጥ የለችም፡፡ በሀገራችን የምናየውም ይህንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ባቢሎን የሆነችው በሥልጣን፣ በዝናና በገንዘብ አፍቃሪዎች መሆኑ ግልጽ ከሆነ ዋል አደር አለ፡፡

እናም እባካችሁ ባለሥልጣኖቻችን ሆይ!

ነገ ጥርኝ አፈር ለምትሆኑት ነገር፣ ነገ አርጅታችሁ የዝምብ መጫወቻ ለምትሆኑት ነገር ( ለዚያም ከበቃችሁ እሰዬው ነው!)፣ ነገ ከሥልጣን ስትባረሩ መግቢያ ቀዳዳ ለሚጠፋችሁ ነገር፣ … እባካችሁን የወስፋታችሁ መሸንገያ በሆነው፣ የጌጣችሁ መሠረት በሆነው፣ የእህል ውኃችሁ ገመድ በሆነው ወርቁ ሕዝባችሁ ላይ አትኩሩ፤ አትንጠባረሩ፡፡ በስንት ልመናና ደጅ ጥናት እንዲሁም በስንት ትውውቅና አማላጅ በቅጡ ሳትማሩና ብቃትና ችሎታ ሳይኖራችሁ ባገኛችሁት ሹመት (ሽህ-ሞት) ዕድሜ ልክ የምትቆዩበት ይመስል አጓጉል ጠባይ አታሳዩበት፤ ተከበሩበት እንጂ አፈሩበት፡፡ ከመፈራት መከበር እጅግ የበለጠ ዋጋ አለውና፡፡ በቅርብ በአንድ ሚዲያ አንድ የተከበሩ ታላቅ ዲያስፓራ በመጽሐፋቸው ያሠፈሩትን ደረጀ ኃይሌ በቲቪ ፕሮግራሙ ላይ ሲናገር እንደሰማሁት በሚኒስትርነት ቦታ ላይ ያለ አንድ ሞልቃቃ ከውጭ ሀገር ጠርቶ እንዲመጡ እንዳላደረጋቸው በሰጣቸው የስልክ አድራሻ ሀገር ውስጥ ሆነው ቢደውሉለት፤ “ከውጭ ስለመጣህ ከሰማይ የመጣህ መሰለህ እንዴ? እንዲያውም ዳግመኛ እንዳትደውል!” በማለት አዋርዶ መልሷቸዋል፤ ያን ታሪክ ስሰማ በኢትዮጵያዊነቴ በሀፍረት ተሸማቀቅሁ፡፡ ዶ/ር አቢይ ያን ታሪክ እንደኔው ሰምቶ ከሆነና ካስቻለው አቢይ ራሱ የተለያዩ ስብዕናዎች ባለቤት መሆን አለበት፤ የዚያ ሚኒስትር ጸያፍ ተግባር ከማሳሰርም በላይ ነው፡፡ እኔ ብሆን ይህን ሰው ከሥራ አባርሬ በሚቀልድበት ሕዝብ መሀል የቀን ሠራተኛ ሆኖ እንዲኖር አደርግ ነበር – ተራ ዜጋ መሆንን እንዲቀምሰው፡፡ “በማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ” ይባላል፡፡ በማን ላይ እንደቆማችሁና በማን ምክንያት በቪ8 እንደምትዘባነኑ ተረዱ፡፡ የየትኛው ሀገር፣ የየትኛው ሕዝብ … መሪዎች መሆናችን ተገንዘቡ፤ የቆማችሁበትን ሰገነት በእግራችሁ አትናዱ፣ የገዛ ቤታችሁን በክብሪት አታቃጥሉ፡፡ 

እኔ የወር ደሞዜ ለወር ቀርቶ ለሣምንት አልበቃ እያለ በችግር ስኖር ከኔ ደሞዝ ተቆርጦ የሚሄደው ብዙ ገንዘብ ግን ለነዚህ ዓይነት ሞልፋጣ ደናቁርት ባለሥልጣናት መጫወቻ ሲሆን ያናድደኛል፡፡ ጥሩ በመኖራቸው አልቀናም፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ በምዝበራና በሙስና፣ በስርቆትና በማጭበርበር የሀገር ሀብት ማግበስበሳቸውና ማባከናቸው ሳያንስ ማለቂበሌለው የይስሙላና አልፎ አልፎም የውሸት ስብሰባ ምክንያት በቢሮ እንደለሌሉ በጸሐፊዎቻቸው ዘወትር እያስነገሩ ሥራቸውን የሚበድሉና በዜጎች ስቃይ የሚደሰቱ ባለሥልጣናትን ሳይ ግን በውነቱ ያመኛል፡፡ በቅርቡ አንድ የኦሮምያ ፖሊስ ባለሥልጣን – ማን እንደሆነ ብቻ እንጃ – ወደሀገራችን በገባው አዲሱ ባህል ምክንያት ወለጋ ውስጥ ስለተጠለፉት ወጣቶች ሲጠየቅ እየተንቀባረረ የመለሰው መልስ በእጅጉ ያበሳጫል፡፡ ባለሥልጣኖቻችን ቅልና ዱባ ወይም እንጨትና ድንጋይ እንጂ ሰው የሚያስተዳድሩ አይመስሉም – ቅልና ዱባም እኮ አላግባብ ሲሰቃዩ ሊያሳዝኑን ይገባል፡፡ የኛ ባለሥልጣናት ግን አንጎላቸው ወደ ድንጋይነት ሳይለወጥ አልቀረም፡፡ ለምሣሌ ባለፈው ሰሞን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሆዱን በቅጡ ላልሸፈነ ድሃ ገበሬ – ቁጥሩ ሲጠራ እንኳን ሰምቶት የማያውቀው 120 ሽህ ብር በልጅ እንዲከፍል ተጠይቆ ባለመከፈሉ “ምክንያት” እነዚያ ስድስት ሕጻናት ሲታረዱ በሌላ ሀገር ቢሆን ባንዲራ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል፤ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ይታወጃል፤ መሪው ካንገት ሳይሆን ካንጀት በሀዘን ድባብ ተውጦ የሀዘን መግለጫ ይሰጣል፣ በጥቅሉ ሀገር ማቅ ትለብሳለች … በኛ ሀገር ግን ድመትም የሞተብን አንመስልም- ነግ በኔንም እርግፍ አድርገን ትተናል፡፡ እናስገርማለን፤ መሪዎቹም ሕዝቡም ወደምን የዘቀጠ ደረጃ እየወረድን እንደሆነ ለመረዳት ይቸግራል፡፡ … ሰው ለሰው ማዘን ሲኖርበት በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ደግሞ በማስመሰል ሳይሆን በምር ማዘንና መቆጨት ሲጠበቅበት በተለይ ሕዝን እራለሁ የሚለው አካል እንዲህ በዜጎች ላይ መዘባነኑ ያሳፍራል፡፡ መንግሥት አለን ለማለትም እንዲሁ ያሳፍራል፡፡ አቢይ በዚህ መሀል ምን እየሠራ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው አንድ ሰው በመሆኑና ሥራውም ውስብስብ በመሆኑ ሊቸገር እንደሚችል እረዳለሁ፡፡ የነሱ ተባባሪ ባለመሆን ሀገሩን እንዲያግዝ ግን እመክራለሁ – ለምን ቢባል የወንበዴዎች መሪ መሆን ከወንበዴነት ተለይቶ አይታይምና፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ተግባር በነፃ ለመተባበር ዝግጁነቴን በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ሕዝብን የማያከብር ባለሥልጣን የጠላት መሣሪያ ከመሆኑም በተጨማሪ ሰው ስለመሆኑ ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ መረገም ነው ወንድሞቼ፤ አለመታደል ነው እህቶቼ፡፡ እኔ ma74085@gmail.com ነኝ፡፡ ልፋ ብሎኝ እንጂ ዘመኑ የክህደትና የሆድ በመሆኑ ማንም ምክሬን እንደማይሰማ ይገባኛል፡፡ ቢሆንም ነገ  ላይ “ትናንት እንዲህ ብዬ ነበር” ለማለትም የምችል ከሆነ ለኔ አንድ እፎይታ ነው – ነገ ደግሞ አይቀርም – ይመጣል! (በነገራችን ላይ በርዕሴ የጠቀስኩት የቅንፍ ሃሳብ ለቀልብ መሳቢያነት ለቀልድ ያህል እንጂ ካንዠት እንዳይመስልብኝ፤ አደራ)

Filed in: Amharic