>

ኮሎኔል ማሞ ተምትሜና የናቅፋ ከበባ 1974 (መንግስቱ ሳሙኤል)

ኮሎኔል ማሞ ተምትሜና የናቅፋ ከበባ 1974

መንግስቱ ሳሙኤል
የቀይኮከብ ትዝታዎች ሊባል በሚችል መልኩ በ1974 በናቅፋ (ሰሜናዊ ኤርትራ) ከበባ ስር ስድስት ወራት የተዋጋው ኢትዮጵያዊው የጦር ጀግና ኮሎኔል ማሞ ተምትሜ የጦር ሜዳ ገድል  መድበል ላይ ስለ ናቅፋ መያዝ የተተረከውን  The Siege of Nakfa በሚል ርእስ ተተርጉሟል። 
—-
በኤርትራ የተሰሩ አንዳንድ የቀድሞ የጦርነት ፊልሞችን ስመለከት የደርግ ወታደሮችን እንደ ፈሪ ያቀርባሉ። ይህ መቸም እውነት እንዳልሆነ የሻእቢያ ሰዎች አሳምረው ያውቁታል። ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ መሆኑ የታወቀ ነው። በመሰረቱ የደርግ ወታደሮች ፈሪ ቢሆኑ ኖሮ ሻእቢያ ጦርነቱን ለማሸነፍ 30 አመታት አይወስድበትም ነበር። የደርግ ወታደር ፈርጣጭ ቢሆን ኖሮ የሙሴቪኒ ጦር እንደ ፓሎኒ ኩዋስ እየነጠረ ካምፓላን እንደተቆጣጠረው ሁሉ ሻእቢያም አስመራን በ1970 አጋማሽ ያለችግር ይቆጣጠራት ነበር።
ጄኔራል ስብሃት ኤፍሬም ሲናገር እንደሰማሁት የደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ወታደሮች ተዋጊዎች ነበሩ። እንደ ጄኔራል ረጋሳ ጅማ ያሉ በወታደራዊ ሳይንሱም ሆነ በዲሲፕሊንና በአካላዊ ብቃታቸው የተመሰገኑ የጦር አዛዦችም ነበሩዋቸው። ለነገሩ ትጥቅ እና ስንቅ በገፍ ነበራቸው። በአንጻሩ ሻእቢያ የትጥቅም ሆነ የስንቅ ችግር ነበረበት። እየማረከ ታጥቆ፣ እየማረከ በልቶ የሚዋጋ የነቃ፣ አላማ ያለው ሰራዊት እና የተማረ አመራር እንደነበረው ግን ይታወቃል። የታጋዮቹ የጥንካሬ ዋና ምንጭ የጥያቄያቸው እውነት መሆን እና ጽናት ነበር። ያምሆኖ “ያለመሸነፍ እልህ” የተባለውን የኤርትራ ህብረተሰብ ነባር ባህል ችላ ማለቴ አይደለም።
“ኢትዮጵያዊነት ድሮ ቀረ” እንዲሉ በዚያን ዘመን እነዚያ አረንጉዋዴ ካኪ ለባሾች አቅማቸው በፈቀደው መጠን ለኢትዮጵያዊነት ታግለዋል። 300 ሺህ (+/-) ሰው ኤርትራ ላይ ገብረው ሲያበቁ ተሸንፈው ኤርትራን ለቀው ሄደዋል። ወያኔም በተመሳሳይ አስመራን ለመያዝ ተንደርድራ ስታበቃ 75 ሺህ (+/-) የሰው ህይወት ገብራ ቀንድዋ ተመትቶ ተመልሳለች።
(ወያኔ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በህግ ፊትም ተሸንፋለች። በፍጻሜው አልቀናትም። እንደ ኢዲዩ ትንቢት “በድንጋይ ማረኩህ” እያለች ቡፋዋን በዘፈን የረጨችበት ህዝብ በድንጋይ አባርሮ መቐለ ከተታት።)
በርግጥ ኤርትራም ብትሆን የከፈለችው ዋጋ ከባድ ነው። በሶስቱም ስርአት ወረራዎች (ጃንሆይ – ደርግ – ወያኔ) ሲቪሉን ጨምሮ 110 ሺህ (+/-) ህይወት ለጦርነቱ ገብራለች። ከነጻነት በሁዋላ ለማግኘት ያለመችውንም ለማሳካት፣ ከአለማቀፍ ሸር እና አሻጥር ጋር እየታገለች 2020 ላይ ደርሳለች። የኤርትራ ጉዳይ ሲነሳ የሚደንቀው ከነጻነት በሁዋላ ህልምዋ ላይ ገና አለመድረስዋ ሳይሆን፣ እንደተፈጸመባት የሴራ መጠን እስካሁን እንደ አገር መቀጠል መቻልዋ ነው። ጉዳዩ መራር እና አከራካሪ ቢሆንም ይህ የዘመናችን እውነት ነው።
እንግዲህ ምን ቀረን?
“የሰላም ዘመን መጥቶአል” ስለተባለ ያለፈውን እየተረክን እንማርበታለን። ዛሬ ዶክተር አብይ አህመድ በስልጣን ላይ አለ። ይችን እስክጽፍ ስለሰላም የሚናገረውን አምኜዋለሁ። እንደሚቀጥልበት ግን ምንም ዋስትና የለም። ፖለቲካ ሸርሙጣ ናት። ከመጪው ግንቦት ወር ጀምሮ ማን ወደ ኢትዮጵያ ስልጣን እንደሚመጣ አይታወቅም። አንድ ወፈፌ ሊመጣ ይችላል። አንድ ክቡር ሰው ሊመጣ ይችላል። አንድ ጭምት ሊመጣ ይችላል። የእነ እንትና ቅጥረኛ ሊመጣ ይችላል። ምርጫ ሁሉ ቅዱስ እንዳልሆነ አዶልፍ ሂትለርን ካነገሰው የጀርመን ምርጫ መረዳት ይቻላል።
ዞረም ቀረ ወጋችን ናቅፋ ነው።
በ1974 በናቅፋ ከበባ ስር ስድስት ወራት የተዋጋው ኢትዮጵያዊው የጦር ሰው ኮሎኔል ማሞ ተምትሜ ታሪኩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብዙም አይታወቅም። ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው የሞቱላት ልጆችዋን የማታከብር ከሃዲ አገር ስለሆነች እንጂ ኮሎኔል ማሞ ተምትሜ ሃውልት ቢቀርበት እንኩዋ የከበባ እና የሽንፈት ታሪኩ በወጉ መጻፍ ነበረበት። ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማሪያም የራሱን ታሪክ ሲጽፍ በእግረመንገድ ስሙን ከመጥቀሱ በቀር ኮሎኔል ማሞ ጨርሶ አይታወቅም።
የኮሎኔል ማሞን የአዋጊነት ብቃት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዝርዝር ጽፎ ያሳተመው  ደግሞ ንብረትነቱ የሻእቢያ የሆነው Hidri Publishers መሆኑ ነገሩን አስቂኝ ያደርገዋል። ርግጥ ነው ሻእቢያ (ከነሙሉ ችግሮቹ) ታሪክን የመካድ ልማድ የለውም። ማለቴ ሻእቢያ ታሪክ ላይ ሲናገር አያጋንንም። ይህን የምለው ካነበብኩዋቸው መጻህፍቱ በመነሳት ነው።
ኮሎኔል ማሞ ተምትሜ ሆይ! 
ወገኖችህ ቢረሱህም ለወረራ ሄደህ የተዋጋኻቸውና ያሸነፉህ “ወንበዴዎች” ታሪክህን ሳይቀንሱ እና ሳይጨምሩ ጽፈውልሃል። በናቅፋ ተራራ ላይ ለዘልአሙ ያረፈ አጽምህም እርፍት ያገኛል። እንኩዋን ደስ ያለህ!!
Filed in: Amharic